የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

የትንቢት ስጦታ



4ኛ ሩብ ዓመት 2026


ጥቅምት 21 - 27

6ኛ ትምህርት

Oct 31 - Nov 6




ትንቢታዊ ጽሑፎች



ሰንበት ከሰዓት በኋላ

ለዚህ ሳምንት ጥናት እነዚህን ጥቅሶች ያንብቡ፦ዘፀ 17:14፣ ኢሳ 13:1፣ ኤር 36:17ና 18፣ ሮሜ 16:22፣ ሉቃ 1:1-4፣ ይሁዳ 14ና 15፣ 2ኛ ቆሮ 4:7።


የመታሰቢያ ጥቅስ፡“በመጽናናትና መጻሕፍት በሚሰጡት መጽናናት ተስፋ ይሆንልን ዘንድ አስቀድሞ የተጻፈው ሁሉ ለትምህርታችን ተጽፏልና” (ሮሜ 15:4)።

እግዚአብሔር ራሱ የደረሰውን መዝሙር መዘመርን መማር የሚፈልጉት እንዴት ነው? በዘዳግም 32 ላይ የሚገኘው ግጥም በእግዚአብሔር ምሪት በሙሴ የተጻፈ ነው (ዘዳ 31:19-32።) ስለ ትንቢታዊ መጻሕፍት ስናስብ መዝሙሮች ወደ አይምሮአችን አይመጡም። ጝጥሞቹ ቀጥታ ቃል በቃል በእግዚአብሔር የተነገሩ ባይሆኑም መዝሙረ ዳዊት በአብዛኛው በመንፈስ ቅዱስ ምሪት የተጻፈ መዝሙር ነው።

ነቢያት የእግዚአብሔርን መልዕክት የሚያስተላልፉባቸውን 3 መንገዶች መጽሐፍ ቅዱስ ዘግቧል፦ (1) በቃል (2) በጽሑፍ (3) በምልክት ወይም በትይንት። በዚህ ሳምንት በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ በሚገኙት ጽሑፎች ላይ እናተኩራለን። መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔርን ቃል፣ በመልእክተኞቹ በተገለጹ ቃላት አማካይነት፣ የነቢያቱን ስብከቶችና ንግግሮች በማካተት መዝግቦታል።

በትንቢታዊ ጽሑፎች ውስጥ ስላሉ የተለያዩ የአጻጻፍ ዘይቤዎች ዓይነቶች አስቡ፦ ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያክል ትረካ፣ ታሪክ፣ ግጥም (ቅኔ)፣ ሰቆቃና ደብዳቤዎች ይገኙበታል። የተመረጡ ወንዶችና ሴቶች ሰዎች በመንፈስ ቅዱስ ተመርተው የተቀበሏቸውን መልዕክቶች በራሳቸው ቋንቋ ዘገቧቸው። በዚህ ሳምንት ጽሑፎቻቸውን ስንመለከት በረዳት ፀሐፊዎች መገልገላቸውንና አንዳንድ ለማስተዋል ቀላል ያልሆኑ ጽሑፎች ሲገጥሙን ማሰብ ሰላለብን ነገሮች እንመለከታለን።

*የዚህን ሳምንት ትምህርት ለጥቅምት 28 ሰንበት ለመዘጋጀት ያጥኑ።

ጥቅምት 22
Nov 1

ለመፃፍ መጠራት


እግዚአብሔር መልእክቱን ለሰዎች ለማስተላለፍ የተጠቀመበት ቀደምት ዘዴ እንደሚሰማ ድምጽ ወይም ሕልም፣ ወይም መላእክት ያለ ቀጥተኛ ንግግርን በመጠቀም ነበር። ቃሉ በጽሑፍ መዘገብ የተጀመረው ለመጀመሪያ ጊዜ በሙሴ ዘመን ነበር። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ ስለ ጽሑፍ የተወሳው መቼ ነበር? ዘፀ 17:14ን ያንብቡ።



ቃሉን ዘግበው ለህዝቡ እንዲያስቀምጡ እግዚአብሔር መልእክተኞቹን እንዳዘዛቸው በብሉይ ኪዳን ውስጥ በብዙ ቦታዎች እናገኛለን። ለሙሴ እንደተነገረው ለኤርምያስም ተነግሮት ነበር። “አንድ የመጽሐፍ ክርታስ ውሰድ፥ ለአንተም ከተናገርሁበት ቀን ከኢዮስያስ ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በእስራኤልና በይሁዳ ላይ በአሕዛብም ሁሉ ላይ የተናገርሁህን ቃል ሁሉ ጻፍበት” (ኤርምያስ 36:2)።

ትንቢቶቹን ለምን መጻፍ እንዳለበትም ተነግሮት ነበር። “ምናልባት የይሁዳ ቤት፦ እኔ አደርግባቸዋለሁ ያልሁትንና ያሰብሁትን ክፉ ነገር ሁሉ ይሰሙ ይሆናል፥ ከክፋ መንገዳቸው ይመለሱ ዘንድ እኔም በደላቸውንና ኃጢአታቸውን ይቅር እል ዘንድ” (ኤርምያስ 36:3)። ትንቢቶቹ የተሰጡት የሰዎችን የወደፊቱን ለማወቅ ያላቸውን ጉጉት ለማርካት ሳይሆን ለመዳናቸው ነበር።

የእግዚአብሔር መልክተኞች የፃፉት በተለያዩ ሁኔታዎች እያሉ ነበር። ሙሴ የመጀመሪያዎቹን አምስቱን የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት የጻፈው በምድረ በዳ ሳለ ነው። ዳዊት ብዙዎቹን መዝሙሮቹን የፃፈው ሳኦል እያሳደደው ሳለ ነው (መዝ 52፣54፣57፣59ን ይመልከቱ)። ዳንኤል ራዕዮቹን የፃፈው በባቢሎን እና በሜዶ-ፋርስ ቤተ መንግስታት በሚያገለግልበት ጊዜ ነበር። በአንጻሩ ደግሞ ጳውሎስ የኤፌሶንን፣ የፊሊጵስዩስን፣ የቆላስያስንና የፊሊሞናን ደብዳቤዎች የፃፈው እስር ቤት ውስጥ ሆኖ ነበር። ዮሐንስ ደግሞ ራእዩን የጻፈው በጳጥሞስ ደሴት ተግዞ ሳለ ነበር።

የእግዚአብሔር መልክተኞች መልዕክቱን ለመጻፍ በመንፈስ ቅዱስ ከተመሩ ያሉበት ሁኔታ ልዩነት አያመጣም። የሚያስገርመው ነገር ደግሞ ኢየሱስ ያስተማራቸው እነዚያ የከበሩ እውነቶች ሁሉ የተጻፉት እግዚአብሔር በተማመነባቸው እና በመረጣቸው ሰዎች ነበር። ይህ የሚያሳየን እነዚህ መለኮታዊ መልዕክቶች በጥንቃቄ መዘገባቸው ምን ያህል አስተማማኝ መሆኑን ነው። አንድ ሰው የመጀመሪያዎቹ (original) ጽሑፎች ሰለሌሉን መጽሐፍ ቅዱስን ማመን አንችልም ቢል ምን ይመልሱለታል? በነገራችን ላይ ይህ አይነት ጥያቄ ደካማ ጥያቄ የሆነው ለምንድር ነው?

ጥቅምት 23
Nov 2

የስነ-ጽሑፍ አይነቶችና የአፃፃፍ ስልቶች


መጽሐፍ ቅዱስ በመንፈስ ቅዱስ የተነሳሱ የእግዚአብሔር መልክተኞች የተጠቀሙአቸውን የተለያዩ የኣአጻጻፍ ስልቶችን ይይዛል። አንዳንዶቹ ማስታወሻ ይመስላሉ (ዘሁ 33:1-49ን ይመልከቱ)። በሌላ በኩል ደግሞ የዳንኤል፣ የዘካሪያስ እና የዮሐንስ መጻሕፍት ደግሞ ትንቢታዊ ጽሑፎችን፣ ታላላቅ ምስሎችን፣ ዓለም አቀፋዊ ሃሳቦችን እና የሰማይ ፍጡራንን መግለጫዎችን ይይዛሉ። ኢሳያስ 13:1ን ያንብቡ። ኢሳያስ ያስተላለፈውን መልእክት መጽሐፍ ቅዱስ ከዚህ ላይ እንዴት ያቀርበዋል?



ነቢያት የሚያዩአቸው ራእዮች አንዳንድ ጊዜ “ቃል ኪዳን” ይባላሉ። ይህም ማለት ከእግዚአብሔር የመጣ መልዕክት ማለት ነው። አዲስ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች በተደጋጋሚ የተጻፉ ቅኔዎች አድርገው ያቀርቧቸዋል። ለምሳሌ: “በዚያ ቀን ሰው ወደ ፈጣሪው ይመለከታል፣ አይኖቹም ወደ እስራኤል ቅዱስ ያያሉ” (ኢሳ 17:7)። ከዚህ ላይ “ፈጣሪ” እና “ቅዱስ” ተመሳሳይ ናቸው። አንዱ ሌላውን ያብራራል።

በተጨማሪም ነቢያት እንደ ምሳሌ (ምስል) እና ቃለ አጋኖ (ማጋነን) የመሳሰሉ የተለመዱ የአጻጻፍ ስልቶችን ስልቶችን ተጠቅመዋል። መልእክቶቹን አስተውለን ከስራ ላይ ማዋል እንድንችል እነዚህን የመሳሰሉትን ያፃፃፍ ስልቶችን ማዋቅ ይጠቅመናል።

ሌላ በብዛት ከስራ ላይ ውሎ የምናየው የአፃፃፍ ስልት ደግሞ “የክስ ቃል ኪዳን” የተባለውን የአፃፃፍ ስልት ነው። ለምሳሌ በኤርምያስ 2:4-9 ላይ ኤርምያስ ሕዝቡ የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ስለጣሱ ህጋዊ ክስ ያቀርብባቸዋል። የፍርድ ቤት ምስል በመጠቀም እግዚአብሔር እንደ አቃቤ ህግ ሆኖ ሕዝቡን ለምን እንደቀጣቸው ምክንያቶቹን በግልጽ ዝርዝሮ ያቀርባል።

በተጨማሪ መጽሐፍ ቅዱስ ትንቢታዊ መጻሕፍትን፣ ታሪክን፣ መዝሙሮችንና ምሳሌዎችን ያካትታል። ኤርምያስ መልዕክቱንበመጽሐፍ መልክ እንዲያቀርብ ሲጠየቅ (ኤር 36:2) በአንጻሩ ደግሞ አብዛኛው የአዲስ ኪዳን ክፍል ለግለሰቦችና ለህብረተሰቦች የተፃፉን ደብዳቤዎች ያካትታል። ቢሆንም አንድ አይነት የአፃፃፍ ስልት ከሌላው አያንስም ወይም አይበልጥም። በመንፈስ ቅዱስ ተነሳስቶ መጻፉን በግልጽ ስለሚናገሩ የጳውሎስ ደብዳቤዎች የጥንት ነቢያት ከጻፏቸው መጻሕፍት ጋር እኩል ክብደት አላቸው (1ኛ ቆሮ 7:10፣12:40)። አንዳንድ ምሁራን የመጽሐፍ ቅዱስን መለኮታዊ ክፍል በሚበድል አይነት የሰብአዊውን ክፍል አጉልተው ይናገራሉ። ይህ አቀራረብ መንፈሳዊ ጉዳት የሚያደርሰው እንዴት ነው? (ለምንድነው?)

ጥቅምት 24
Nov 3

የፅሁፍ ረዳቶች


ኤርምያስ 36:17ና 18 እና ሮሜ 16:22ን ያንብቡ። የመጽሐፍ ቅዱስ ፀሐፊዎች የፅሁፍ ረዳቶች ስለ መጠቀማቸው እነዚህ ጥቅሶች ምን ይነግሩናል?



ምናልባት ኤርምያስ መልዕክቱን ራሱ ሊጽፈው ይችል ነበር። ነገር ግን ትንቢቶቹን በጥንቃቄ ጽፎ ለህዝቡ መሪዎች እንዲያቀርብ የሚተማመንበትን ፀሐፊውን ተጠቀመ። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መለኮታዊ መልዕክቱን ለሌሎች ለማስተላለፍ የጽሑፍ ረዳትን አገልግሎቶች የተጠቀሙ ነቢያት ምሳሌ ኤርምያስ ብቻ አልነበረም።

በአዲስ ኪዳን ውስጥ ደግሞ ምንም እንኳን ጤርጥዮስ “ይህን መልዕክት ጻፍሁት” (ሮሜ 16:22) ቢልም ከሮሜ መጽሐፍ ጅምር ጀምሮ ጳውሎስ የተናገረውን መጻፉ ግልጽ ነው። ጤርጥዮስ የጳውሎስ ፀሐፊ ነበር። ጳውሎስ የተናገረውን በጽሑፍ አሰፈረ።

ይህ ለጳውሎስ ያልተለመደ ነገር አልነበረም። ደብዳቤው በሙሉ እውነተኛ መሆኑን ለማረጋገጥ በቆላስያስና በተሰሎንቄ ደብዳቤዎች መደምደሚያ ላይ “በገዛ እጄ” ሲል ደብዳቤዎቹን ይደመደማል (ቆላ 4:18፣ 2ኛ ተሰ 3:17)። ይህ የሚያመለክተው ደብዳቤዎቹን በጽሑፍ የሚያሰፍርለት ሌላ ሰው እንደነበር ነው። ደብዳቤው በትክክል እርሱን ስለመወከሉ ወይም በፍጹም ከእርሱ ላለመሆኑ ይህ እውነታ ጥርጣሬ ሊያነሳ ስለሚችል ስለ መልእክቱ ትክክለኛነት ምንም ጥርጣሬ እንዳይኖር ጳውሎስ በመጨረሻ ላይ የራሱን የእጅ ጽሑፍ አስቀመጠ።

ብዙ ምሁራን የጳውሎስ ደብዳቤዎች የተለያየ አጻጻፍ ስልት ያላቸው፣ የተለያዩ ረዳቶች እንዲፅፉለት ስላደረገ ነው ይላሉ። ስለ ጴጥሮስ 2 ደብዳቤዎችም የዚሁ ዓይነት ጥርጣሬ አለ። “የ1ኛ ጴጥሮስና የ2ኛ ጴጥሮስ የአጻጻፍ ስልት የተለያየ ቢሆንም በግሪክ ቋንቋ ለጻፈው መልዕክቱ ረዳት ተጠቅሞ ይሆናል። የግሪክን ቋንቋ በሚገባ የሚያውቅ ጳውሎስ ጸሐፊዎችን ከተጠቀመ የአረማይክ ቋንቋ ተናጋሪ የነበረው ጴጥሮስ ጸሐፊዎችን መጠቀሙ አመክንዮአዊ ሲሆን ፀሐፊዎቹ በግሪክ በተጻፉ ደብዳቤዎቹ የቃላት አጠቃቀም ላይ ተጽዕኖ አሳድረው ሊኖራቸው ይችላል (SDA Bible commentary ጥራዝ 5 ገፅ 186)።

ይህ የሚያመለክተው የእግዚአብሔር መልክተኞች ለማስተላለፍ ለሚፈልጉት ሀሳብና ትርጉም ታማኝ ሆነው ሳለ በቃላት አመራረጥና በአረፍተ ነገር አሰካክ ላይ የረዳቶቹ አፃፃፍ ስልቶች ተጽዕኖ አላቸው ማለት ነው። የእግዚአብሔር መንፈስ የመራው ሀሳቦቹን እንጂ በመንፈስ ምሪት የተሰጡ ሀሳቦችን ለመግለጽ ስራ ላይ የዋሉትን ቃላት አይደለም።

ጥቅምት 25
Nov 4

የስነ-ጽሑፍ ምንጮች


“ሰባኪውም ጠቢብ ስለ ሆነ ለሕዝቡ እውቀትን አስተማረ፤ እርሱም ብዙ ምሳሌዎችን መረመረና ፈላለገ አስማማም። ሰባኪው ያማረውን በቅንም የተጻፈውን እውነተኛውን ቃል መርምሮ ለማግኘት ፈለገ” (መክ 12:9፣10)።

ይህ ምንባብ የሚያሳየው ሰለሞን የዘገባቸውን ምሳሌዎች ሁሉንም እራሱ እንዳላመነጨ ነው። በእግዚአብሔር ምሪት ብዙ አባባሎችን “ፈለገ” እና “ያማሩ ቃላትን”ፈለገ። እንዲያውም በምሳሌ 31 ላይ የምትገኘውና ብዙ ጊዜ የምትጠቀሰው የመልካሟ ሴት ታሪክ የሰለሞን ሳይሆን የአንድ የማይታወቅ ንጉስ እናት ንግግር ነው (ምሳሌ 31:1)። በምሳሌ መጽሐፍ ላይ የግብጻዊያን ስነጽሑፍ ተጽዕኖ እንዳለበት መረጃ ያመለክታል።

በተመሳሳይ ሁኔታም በመንፈስ ቅዱስ ተነስተው የፃፉ የብሉይ ኪዳን ታሪክ ዘጋቢዎች የእግዚአብሔርን ህዝብ ታሪክ በታማኝነት ለመተረክ የታሪክ ቅርሶችንና ሌሎች ምንጮችን እንደ ማጣቀሻ መጠቀማቸውን ነግረወናል። 1ኛ ነገ 11:41፣ ሉቃ 1:1-4 እና ይሁዳ 14፣15ን ያንብቡ።። በመንፈስ ቅዱስ የተነሳሱ ፀሐፊዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጭ የሆኑ ምንጮችን መጠቀማቸውን እነዚህ ጥቅሶች እንዴት ያሳዩናል?



መጽሐፋቸውን ለመፃፍ ታሪካዊ ዘገባዎችን ከተጠቀሙት የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች መካከል ዕዝራና ነህምያ ይገኛሉ። ዕዝራ እየሩሳሌምንና ፋርስን በሚመለከት ንጉሳዊ ደብዳቤዎችንና አዋጆችን ይጠቀማል (ዕዝራ 4:7ን ይመልከቱ)። ነህምያ ደግሞ ያገኛቸውን የትውልድ መዝገቦች በታሪክ ውስጥ ያካትታል (ነህ 7:5- 72ን ይመልከቱ)።

የዚህ ዓይነት አሰራር በአዲስ ኪዳንም ይገኛል። “የሉቃስ ልምምድ የሚያሳየው የመንፈስ ቅዱስ አነሳሽነት ከአእምሮ አስተሳሰብ ጋር ተባብሮ እንደሚሰራ ነው። በዚሀ ቦታ በመንፈስ ቅዱስ የተነሳሳ ፀሐፊ በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶ ስለ ክርስቶስ ሕይወት በቃልና በጽሑፍ አስቀድሞ ያለውን ታሪክ አቀነባብሮ በጽሑፍ ለማቅረብ ተግቶ አጠና።” (Bible commentary vol.5 page 669)።

ይሁዳ ከመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያልተካተተውን የአይሁዶች ስራ የሆነውን አንደኛ የሄኖክ መጽሐፍ 1:9ን ይጠቅሳል። ጳውሎስ ስማቸውን ሳይጠቅስ ከግሪክ ፈላስፋዎችም ተውሷል (የሐዋ 17:28 ና ቲቶ 1:12ን ይመለከቱ) የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች አብዛኛውን ጊዜ መልዕክታቸውን በሕልምና በራዕይ ቢቀበሉም መንፈስ ቅዱስ ከሌላ ምንጮች መረጃ እንዲመርጡ አነሳስቷቸዋል። ይህን መገንዘባችን ለእኛ እንዴት ይጠቅመናል?

ጥቅምት 26
Nov 5

መለኮታዊ መልዕክትና ሰብአዊ ጉድለቶች


ጳውሎስ ስለ እግዚአብሔር መዝገብ በ2ኛ ቆሮንቶስ 4:7 ላይ ምን ይላል?



ጳውሎስ የእግዚአብሔር ኃይል ከሰብአዊ ድክመት ጋር ያለውን ንጽጽር ለማሳየት የእግዚአብሔር መዝገብ “በሸክላ ዕቃ ውስጥ” እንድተቀመጠ በመጥቀስ ይጽፋል። የእግዚአብሔር መልእክተኞች በግል ህይወታቸው እንዳይሳሳቱ ከተፈጥሮ ውጭ በሆነ ሀይል እንዳልተጠበቁ ሁሉ (ለምሳሌ ሙሴ፣ ኤልያስ፣ ዮናስና ጴጥሮስ) ጽሑፎቻችውም ከሰብአዊ መረዳትና ግንኙት ጉድለቶች የጸዱ አልነበሩም።

“በክርስቶስ የታየው መለኮታዊና ሰብአዊ ህብረት በመጽሐፍ ቅዱስም አለ። የተገለጡት እውነቶች ሁሉ “በእግዚአብሔር አነሳሽነት” የተሰጡ ናቸው። ነገር ግን የሰዎችን ፍላጎት ለማሟላት በሰዎች ቃላት የቀረቡ ናቸው።”(Testimonies to the church vol. 5 p. 747)

ጳውሎስ በ2ኛ ቆሮንቶስ 4:7 እንደጻፈው የእግዚአብሔር መልክተኞች እውነቱን እንዲያስተላልፉ ሲጠሩ ሰብአዊነታቸው አልተሰረዘም። በተጨማሪም ዛሬ ለእኛ ለማስተዋል የሚያስቸግሩ አነጋገሮችና አጻጻፎች እንዳይነገሩና እንዳይፃፉ አልከለከላቸውም። ቢሆንም በእነዚህ ለማስተዋል አስቸጋሪ በሚመስሉ በመጽሀፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኙ ሃሳቦች የምንሰናከልባቸው በጠባብ አስተሳሰብ ስናያቸው ብቻ ነው። አማኞች ክርስቲያኖች እንደመሆናችን በተገለጠልን ብርሃን እየተመራን ያልተገለጠልንን ደግሞ ለእግዚአብሔር መተው አለብን።

አንዳንድ ልዩነቶች ሰዎች በኋላ ሲገለብጡ የፈጸሟቸው ቀላል ስህተቶች ሊሆኑ ወይም በመንፈስ ቅዱስ ምሪት የጻፉ ጸሐፊዎች ከተደገፉአቸው ምንጮች የተነሳ የመጡ ሊሆኑ ይችላሉ። እንዲህ አይነት አስቸጋሪ ክፍሎች ሲያጋጥሙን የፀሐፊዎችን ሀሳብ በተሳሳተ መንገድ ወስደን እንዳይሆን

ተጨማሪ ሀሳብ


ማድረግ ያስፈልገን እንደሆነ ራሳችንን መጠየቅ አለብን።

ስህተት ለሚመስሉ ሃሳቦች ወይም ልዩነቶች ሁሉ መፍትሄ ባናገኝላቸውም እየተሰጠ ካለው ዋና መልዕክት በፍጹም የማይጣጣሙ አይደሉም። የእግዚአብሔር መልክተኞች ጉድለት ቢኖርባቸውም በተገለጡላቸው መለኮታዊ እውነቶች ሙሉ በሙሉ ልንተማመን እንችላለን። መልክቱን ለማቀበል ኃጢአት ያልሰሩን መላዕክት በመምረጥ ፋንታ ጉድለት ያላቸውን ሰብአዊ ፍጡራን የመረጠው ለምን ይመስልዎታል?

ጥቅምት 27
Nov 6

የኤለን ጂ ዋይት ጽሑፎች


የኤለን ጂ ዋይት የኑሮ ተሞክሮና ጽሑፎች በዚህ ሳምንት ካጠናናቸው የመጽሐፍ ቅዱስ መልዕክተኞች የኑሮ ተሞክሮና ጽሑፍ ይመሳሰላል። እርስዋም የተገለጠላትን እንድትጽፍ መለኮታዊ ተልዕኮ ተቀብላለች።

ኤለን ጂ ዋይት በ 1909 ዓም እንዲህ ስትል ፃፍች፦ “ለሕይወቴ ያሰጋ ከባድ አደጋ ደርሶብኝ ስለነበረ የጤና ችግር ስለነበረብኝ ልጽፍ አልቻልኩም ነበር። ነገር ግን አንድ ሌሊት የእግዚአብሔር መልአክ አልጋዬ አጠገብ ሆኖ እንዲህ አለኝ፦ ´የሰጠሁሽን ነገሮች መጻፍ አለብሽ።´ እኔም መጻፍ አልችልም አልኩት። ነገር ግን እንደገና ´የሰጠሁሽን መጻፍ አለብሽ አለኝ´። መሞከር አለብኝ ብዬ መጻፍ ጀመርኩ። ከዚያም ቃላቱን ለመጻፍ እንደማይቸግረኝ ተገነዘብኩ።” (The General confer- ence Bulletin, may 31, 1909)።

እንደ መጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ሁሉ ኤለን ጂ ዋይትም ረዳት ፀሐፊዎችን ተጠቅማለች። ፀሐፊዎቿ አርታኢዎች እንዲሰሩ የሚጠበቅባቸውን ነገር--የራሳቸውን ሀሳብ ሳይጨምሩ መልእክተኞቹ ሀሳባቸውን በግልጽ እንዲገልጹ በማገዝ አልሰሩም። ድብቅ ደራሲዎች (ghost writers) ወይም ተባባሪ ደራሲዎች አልነበሩም። ስራቸው በቃልም ሆነ በጽሑፍ ኤለን ጂ ዋይት የሰጠቻቸውን መጻፍ ነበር።

ኤለን ጂ ዋይት መልእክቷን ለማስተላለፍ በበለጠ እንዲረዳት ክሌሎች የሰነ- ጽሑፍ ምንጮች አንዳንድ ነገሮችን ጠቅሳለች ወስዳለችም። እሷ የተጠቀመቻቸውን መጻሕፍት አንባቢዎች እንዲያነቡ ማደፋፈሯ ለማታለል ላለመሞከሯ ማስረጃ ይሆናል። ነገር ግን በእነዚያ ደራሲያን ቋንቋ መልዕክቱን በግልጽ ለማስተላለፍ ጠቃሚ ነገሮችን አገኘች።

ስለ መሳሳትና ስለ መቃረንስ? “መሳሳትን በተመለከተ አልሳሳትም አላልኩም። የማይሳሳት እግዚአብሔር ብቻ ነው” ብላለች። (ምርጥ መልክቶች 1ኛ መጽሃፍ ገፅ 37)

አንዳንዴ በጽሑፎቿ ውስጥ ለማስተዋል የሚያስቸግሩና ከሌሎች ጋር ለማጣጣም የሚያስቸግሩ አባባሎች ሊገኙ ይችላሉ። የኤለን ጂ ዋይት ሰብአዊነት በመለኮታዊ ጥሪዋ አልተሰረዘም። ኤለን ጂ ዋይት እንደ ሁላችንም ታድጋለች ብስለትንም ታገኛለች። ዕድገቷና ብስለቷ በጽሑፎቿ ተንፀባርቋል።

አስቀድሞ እንደተገለጸው፣ ግን ቢደገም የተገባ ስለሆን፣ እሷ የጻፈችው ቃል ሁሉ ከእግዚአብሔር የመጣ ነው ብለው የሚያምኑትን አርማለች። “አንዳንድ ጊዜ ተራ ነገሮች መነገር ያለባቸው ጊዜያቶች አሉ፣ ተራ ሀሳቦች አእምሮን መያዝ ያለባቸው ጊዜያቶች አሉ፣ ተራ ደብዳቤዎች መፃፍ ያለባቸው ጊዜያቶች አሉ፣ ከአንዱ ሰራተኛ ወደ ሌሎች ሰራተኞች መተላለፍ ያለበት ተራ መረጃ መሰጠት አለበት። እነዚህን የመሰሉት ቃላትና መረጃዎች በእግዚአብሔር መንፈስ አነሳሽነት የተሰጡ አይደሉም።” (ምርጥ መልእክቶች 3ኛ መፃፍ ገፅ 58)




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA Union SSL