የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ለዚህ ሳምንት ጥናት እነዚህን ጥቅሶች ያንብቡ። ዕብ 1:1-2፣ 2ኛ ጢሞ 3:15-17፣ 2ኛ ጴጥ 1:18-21፣ዘፀ 17:14፣ ራዕ 1:19፣ ሕዝ 4:1-8
የመታሰቢያ ጥቅስ፡“ቶሎ ይሆን ዘንድ የሚገባውን ነገር ለባሪያዎቹ ያሳይ
ዘንድ እግዚአብሔር ለኢየሱስ ክርስቶስ የሰጠው በእርሱም የተገለጠው ይህ
ነው፥ ኢየሱስም በመልአኩ ልኮ ለባሪያው ለዮሐንስ አመለከተ፥ እርሱም
ለእግዚአብሔር ቃልና ለኢየሱስ ክርስቶስ ምስክር ላየውም ሁሉ መሰከረ”
(ራዕይ 1:1፣ 2)።
ሐዋርያው ዮሐንስ ከኢየሱስ ደቀ መዛሙርት መካከል ለኢየሱስ ቅርብ
ከሆኑት አንዱ ነበር (ሉቃ 8:15፣ማቴ 17:1፣ማቴ 26:36፣37)። ከክርስቶስ
እርጋት በኋላ ዮሐንስ አገልግሎቱን በኢየሩሳሌም ቀጠለ። ከእየሩሳሌም
ውድቀት በኋላ ግን (70 ዓም) ትንሹ እስያ በመባል በሚታወቀው የሮማ ክፍለ
ግዛት ያሉትን አብያተ ክርስቲያናት ለማስተዳደር ወደ ኤፌሶን ሄደ። በሮማ ንጉስ
በድምጥሬስ ዘመነ መንግስት የክርስቲያኖች ስደት ጊዜ ዮሐንስ በአግኒያስ ባህር ወደ
ምትገኘው ወደ ጳጥሞስ ደሴት ተጋዘ።
በጳጥሞስ ደሴት ሳለ በዘመኑ ለነበሩ በትንሿ እስያ ለሚገኙት ሰባት አብያተ
ክርስቲያናት ብቻ ሳይሆን ለዘመናት ሁሉ ለሚኖሩት ክርስቲያኖች የሚጠቅም
የተለየ ትንቢታዊ መልዕክት ተቀበለ (ራዕ 1:2-3፣9-11)። ዮሐንስ የመልእክቱ አካል
የሆነበት የትንቢታዊ መልእክቱ ሰንሰለት ይህን ይመስላል፦ ከእግዚአብሔር አብ ወደ
ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ከዚያ ለመልአኩ፣ ከዚያ ለሐዋርያው ዮሐንስ፣ እና በመጨረሻም
ለአንባቢያንና ለአድማጮች። እግዚአብሔር ለሰው ዘር ሁሉ መልዕክቱን ለማድረስ
በራዕይና በመገፋፋት ነቢያትን የሚጠቀምበት ታዋቂ መንገዱ ይሄው ነው።
የዚህ ሳምንት ትምህርት የራዕይና በመንፈስ ቅዱስ የመገፋፋትን ሂደት፣ እንዲሁም
መልእክቱ በተለያዩ መንገዶች እንዴት ለሰው ዘር ሁሉ እንደሚደርስ እንመለከታለን።
ይህን የምናደርገው በተለየ መንገድ በጽሑፍ፣ በቃልና ትይንታዊ በሆኑ መንገዶች
መለኮታዊ መልእክት ለሰዎች በተላለፈበት መንገድ ላይ ትኩረት በማድረግ ነው።
*የዚህን ሳምንት ትምህርት ለጥቅምት 21 ሰንበት ለመዘጋጀት ያጥኑ።
ዕብ 1፣1ና 2ን ያንብቡ። እግዚአብሔር ይህን ያህል ሊናገረን የፈለገው ለምንድነው? በኢየሱስ እና በነብያቱ በኩል ሊነግረን የፈለገው ነገር ምንድነው?
አለማትን ሁሉ የፈጠረው ፈጣሪ ምን ይለናል? ከእኛ ጋር ለመነጋገር የሚፈልገው
ለምንድን ነው? ምክንያቱም በኀጢአት በተሞላ ዓለም የምንኖር የወደቅን ሰብአዊያን
ስለሆንን እና ለመከራ፣ ለስቃየና ለሞት የተዳረግን ስለሆንን ነው። ከዚህ ለምን
እንደተገኘን፣ ነገሮች በጣም የከፉ እንደሆኑ፣ ያ ሁሉ ሆኖም ለእኛ ባለው ፍቅር ተስፋ
እንዳለን እንድናውቅ ይፈልጋል።
በተፈጥሮ ሁሉ የሚታየው የእግዚአብሔር ጠቅላላ ራዕይ ወሰን የሌለውን
ኃይሉንና ጥንቃቄውን በግልጽ ይናገራል። “ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር
ይናገራሉ የሰማይ ጠፈር የእጁን ስራ ያወራሉ” (መዝ 19:1)። ሐዋርያው
ጳውሎስም እንዲህ ይላል፦”የማይታየው ባሕርይ እርሱም የዘላለም ኃይሉ
ደግሞም አምላክነቱ ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ ከተሠሩት ታውቆ ግልጥ ሆኖ
ይታያልና፤ ስለዚህም እግዚአብሔርን እያወቁ እንደ እግዚአብሔርነቱ መጠን
ስላላከበሩትና ስላላመሰገኑት የሚያመካኙት አጡ፤ ነገር ግን በአሳባቸው ከንቱ ሆኑ
የማያስተውለውም ልባቸው ጨለመ” (ሮሜ 1:20-21)።
በአለማችን የሚታየውን ምስጢራዊ የመፈወስ ሂደት ስናይ የእግዚአብሔር
ግሩም የአዳሽነት ኃይሉ ላይ ማጤን (ማሰላሰል) ያስፈልጋል። እውነቱን ለመናገር
“የእግዚአብሔር የመፈወስ ኃይል በተፈጥሮ ሁሉ ላይ ይታያል። ዛፍ ሲቆረጥ፣ ሰው
ሲቆስል ወይም አጥንቱ ሲሰበር ተፈጥሮ በተጎዳው ላይ እደሳዋን ትጀምራለች።
ጉዳቱ ከመድረሱ በፊት የፈውስ ወኪሎች በተጠንቀቅ ቆመዋል። ጉዳቱ ወዲያው
ሲደርስ የፈውሱ ወኪሎች ስራቸውን ወዲያውኑ ይጀምራሉ።” (ኤለን ጂ ዋይት
ኤዱኬሽን ገጽ 113)።
ተፈጥሮኣዊ ዓለም ውብና ትምህርት አዘል ቢሆንም የእግዚአብሔርን ኃይል እና
ፍቅር ከመግለጹ አንጻር የክፋትን መኖር ያመለክታል (ዘፍ 3:14-19፣ማቴ 13:24-30)።
ይህ የተዘበራረቀ መልዕክት ግልጽ ሊሆን የሚችለው በእግዚአብሔር ልዩ መገለጥ
ብርሃን--ስጋ በለበሰው በኢየሱስ ክርስቶስ እና ለእርሱ በሚመሰክረው በተጻፈው
በእግዚአብሔር ቃል፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ብርሃን ብቻ ነው (ዮሐንስ 5:39)።
ቃሉ በዘመናት ሁሉ ለሚገኘው የሰው ዘር ሁሉ በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት
የተሰጠ የእግዚአብሔር መልዕክት ነው። ስለ ዓለም አፈጣጠርና ስለሚያሳዝን
ውድቀቱ፣ ስለ እግዚአብሔር አስገራሚ የማዳን ዕቅድ እና ስለ ምድር በመጨረሻ
መታደስ የምስራች ይነግረናል። መጽሃፍ ቅዱሳዊ መረጃዎች አንዳንዴ አጭርና
ምርጥ ቢሆኑም ከእግዚአብሔር ስለመነጩ ምን ጊዜም የታመኑ ናቸው (2ኛ ጢሞ
3:16፣2ኛ ጴጥ 1:19-21)።
ተፈጥሮ የፈጣሪን ኃይልና ፍቅር በግልጽ ቢያሳይም፣ አሁንም የተጻፈው
ቃሉ በጥብቅ የሚያስፈልገን ለምንድን ነው? ተፈጥሮ ብቻውን ሊነግረን
የማይችለው ግን ቃሉ የሚነግረን ነገር ምንድር ነው?
በዘመናት ሁሉ መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ሳይሆን ሌላም ጽሑፎችና መጻሕፍትም ተጽፈዋል። ቢሆንም መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል መሆኑን እንቀበላለን። ከሌላ መጽሃፍት በምን ይለያል? 2ኛ ጢሞ 3:15-17ን እና ያዕ 1:17ን ያንብቡ። እነዚህን ጥቅሶች ስናነብ የምናገኘው ዋና መልዕክት ምንድነው?
የ2ኛ ጢሞቴዎስ 3፡16ን ትርጉም በተመለከተ አንዳንድ ውይይቶች አሉ፣ ነገር
ግን አብዛኛዎቹ ትርጉሞች መጽሀፍ ቅዱስ በሙሉ ምንጩ መለኮታዊ በመሆኑ ላይ
አጽንዖት ስለሚሰጡ የሚሰጡት መልዕክት ተመሳሳይ ነው (2ኛ ጴጥ 1:20-21)።
አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ አብራሪ(ተንታኝ) እንዲህ የሚል መግለጫ
አበርክቷል(ሰጥቷል)፦”ጳውሎስ መጽሐፍ ቅዱስ ሁሉ ለትምህርትና ለተግሳጽ
ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር ደግሞ ይጠቅማል ሲል ቃሉን በጠቅላላ
ማለቱ ነው እንጂ እያንዳንዱ ምንባብ ማለቱ አይደለም።” G. W. Knight III, The
Pastoral Epistles: A Commentary on the Greek Text (Grand Rapids, MI:
Eerdmans, 1992), p. 445.
ነገር ግን መነሻው መጽሐፍ ቅዱስ የሆነውን በመንፈስ ቅዱስ የመነሳሳት ሂደት
የምናስተውለው እንዴት ነው? መገንዘብ ያለብን ትንቢታዊ መነሳሳት ነቢያት
በመንፈስ ቅዱስ እርዳታ መለኮታዊ መልዕክት የሚያስተላልፉበት ሂደት መሆኑን
ነው። ያ እርዳታ መልእክቱን በመቀበል ብቻ የተወሰነ ሳይሆን መልዕክቱን ለተቀባዮቹ
ግልጽ በሆነ መንገድ ማስተላለፍንም ያካተተል።
የእግዚአብሔር መልዕክት በራእይ እና በህልም አማካይነት መጣ (ዘሁ 12:6፣ኢሳ
6:1፣8)። እግዚአብሔር የአይን ምስክሮችን (1ኛ ዮሐ 1:1-3)፣ በመንፈስ ምሪት
የተደረገ ታሪካዊ ምርምርን (ሉቃ 1:1-3) እና በአዕምሮ ውስጥ የተፈጠሩ መለኮታዊ
ተጽዕኖዎችንም ተጠቅሟል (2ኛ ጴጥ 1:21)። መንፈስ ቅዱስ የተጠቀመበት መንገድ
ምንም ቢሆን ነቢያትና የመጽሐፍ ቅዱስ ደራሲዎች ሁሉ ለሌሎች ለማጋራት
የተቀበሉት እውነተኛ መልዕክት እንጂ ግምታዊ መልዕክት አይደለም። ይህ ማለት
ምንም እንኳን መልእክተኞቹ መልእክቶቹን ለመግለጽ የራሳቸውን ቃላት ቢጠቀሙም
የእግዚአብሔር መልእክቶች በምንም መንገድ በመልእክተኞቹ መደፍጠጥ ወይም
መዛባት የሌለባቸው ናቸው።
ትንቢታዊ መልዕክቶችን ለመጀማሪያዎቹ አድማጮች የማስተላልፍ ተግባር
በቃል (2ኛ ጴጥ 1:19-21)፣ በጽሑፍ (ዮሐ 20:30፣ 31)፣ ወይም በትይንት መልክ
(በመግለጫ) ሊሆን ይችላል (ሕዝ 4:1-8)።
መጽሐፍ ቅዱስ እንዴት በመንፈስ ቅዱስ ምሪት እንደተጻፈ ወይም በመንፈስ
ቅዱስ መነሳሳት በአጠቃላይ እንዴት እንደሚሰራ ብዙ ጥያቄዎች ሊኖሩ
ቢችሉም፣ ደግሞ እንዴት እንደተጻፈም ሙሉ በሙሉ ባናስተውልም፣
መጽሐፍ ቅዱስ በመንፈስ ቅዱስ ምሪት የተጻፈ የእግዚአብሔር ቃል
መሆኑን ማመን እጅግ አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድር ነው?
2ኛ ጴጥ 1:18-21ን ያንብቡ። በእግዚአብሔር ነቢያት በቃል ብቻ የተላለፉት መልዕክቶች በጽሑፍ እንደሰፈሩት መልዕክቶች ሁሉ በመንፈስ ቅዱስ ምሪት የተሰጡ ለመሆናቸው ምን ማረጋገጫ አለን?
እግዚአብሔር አዳምንና ሄዋንን ከመውደቃቸው በፊት (ዘፍ 2:16፣17) እና
ከወደቁም በኋላ (ዘፍ 3:9-19) አነጋግሯቸዋል። በሁለቱም ጊዜያት ቃላቱን በትክክል
አስተውለዋል። ድምጹ በሲና (ዘፀ 20:20)፣ እንዲሁም በኢየሱስ ጥምቀትና መለወጥ
(ማቴ 3:17፤ ማቴ 17:5) በደንብ ተሰምቷል። ሰዎች ሲያነጋግሩን ንግግራቸውን
በተሳሳተ መንገድ ልንተረጉመው እንችላለን። እግዚአብሔር በሚናገርበት ጊዜ ግን
የመረጃ መዛባት ወይም ማታለል አይኖርም።
መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔር ለሙሴ እንደተናገረ እና ´እኔ እግዚአብሔር ነኝ´”
እንዳል ያረጋግጣል (ዘፀ 6:2)። አያሌ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች የእግዚአብሔርን
ድምጽ እንደ ሰሙ ይናገራሉ። ለምሳሌ ኢሳያስ (ኢሳ 8:1፣11)፣ ሕዝቅኤል (ሕዝ 3:16፣
6:11) እና ኤርምያስ (ኤር 1:4፣9:11) የእግዚአብሔርን ድምጽ ሰምተዋል። እነዚህን
እና ሌሎች ተመሳሳይ ክስተቶችን ለመካድ መሞከር የነቢያቱን ሀቀኝነትና የመጽሐፍ
ቅዱስን ተአመንነት ወደ መጠራጠር ያመራል።
እግዚአብሔር ግልጽ በሆነ በሰው ቋንቋ የገለጠላቸውን መልዕክት ነቢያትም
ግልጽ በሆነ በራሳቸው ቋንቋ ለአድማጮቻቸው አስተላልፈዋል። ለምሳሌ ኖህ
እውነተኛ የእግዚአብሔር ነቢይ እና “የጽድቅ ሰባኪ” ነበር (2ኛ ጴጥ 2:5)። ነገር ግን
የትኛውንም የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል አልጻፍም። ቢሆንም በወቅቱ ለነበረው ህዝብ
መልዕክቱን በቃሉ አስተላለፈ። መልእክቱ እንደተፃፉት የነቢያት መልእክቶች ሁሉ
በመንፈስ ቅዱስ በመነሳሳት የተሰጠ ነበር።
ናታንን፣ ኤልያስን፣መጥምቁ ዮሐንስንና ኤልሳዕን ጨምሮ ሌሎች አያሌ
ነቢያትም የመጽሐፍ ቅዱስን ክፍል አልጻፉም። ነገር ግን መልዕክታቸውን በቃል
አስተላልፈዋል።
ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱስ? ወንጌል ኢየሱስ በምድራዊ አገልግሎቱ ወቅት “ጎንበስ
ብሎ በጣቱ በምድር ላይ ፃፈ” ሲል ወንጌል ዘግቧል (ዮሐ 8:6)። ይህን ነበር
ያደረገው። ኢየሱስ ሌላ ነገር መጻፉን የሚያሳይ ሌላ ምንም አይነት መረጃ የለም።
ነገር ግን “እንደ ባለስልጣን ሆኖ (ማቴ 7:29) በቃሉ አስተምሯል፣ ሰብኳልም።
ከአዳማጮቹ መካከል አንዳንዶች እንዲህ ሲሉ መስክረውለታል። “እንደዚህ ሰው
ማንም ከቶ አልተናገረም” (ዮሐ 7:40፣46)። ኢየሱስ በዋነኝነት የእግዚአብሔርን
መልዕክቶች በቃል አስተላላፊ ነበር። ቢሆንም ከመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት አንዱንም
አለመጻፉ የመልዕክቱን ስልጣንና እውነት አይቀንስበትም።
እግዚአብሔር መጽሐፍ ያልጻፉ ነቢያት እንዳሉት ማወቁ ምንኛ አስገራሚ
ነገር ነው። ታዲያ እነዚህ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ጽህፈታቸው
ያልተካተተ ነቢያት መልዕክት ክብደት ወይም ሀቀኝነት የሚኖረው
ለምንድነው?
አንዳንድ የታወቁ ንግግሮች በሰዎች ህይወት ላይ ጥልቅ ተጽዕኖ ከማሳደራቸው
አልፎ ታሪክንም ቀይረዋል። እነዚህ ንግግሮች ባይዘገቡ ኖሮ እነዚህ ንግግሮች ከጊዜ
ጋር ይረሱ ነበረ ወይም ይዘበራረቁ ነበር። ስለዚህ ጽሑፍ በቃል የተነገረውን ቋሚ
አድርጎት ይኖራል። መልእክቱም በዘመናት ሁሉ ተላላፊ ይሆናል።
እስራኤላውያን ግብጽን እንደለቀቁና አማሌቃውያንን እንዳሸነፉ ብዙም ሳይቆይ
እግዚአብሔር ሙሴን “ይህን ለመታሰቢያ በመጽሐፍ ጻፈው” አለው (ዘፀ 17:14)።
የመጀመሪያ 5ቱን የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍትና መዝሙር 90ን ከጻፈው ሙሴ
ጀምሮ መንፈስ ቅዱስ 66 መጻሕፍትን የሚያካትተውን መጽሐፍ ቅዱስን እንዲጽፉ
መንፈስ ቅዱስ ነቢያትን መራቸው።
ዘፀ 17:14፣ዮሐ 20:30፣31፣1ኛ ቆሮ 10:11 እና ራዕ 1:19ን ያንብቡ።
እግዚአብሔር የሰጣቸውን መልዕክቶች እንዲጽፉ ነብያቱን ከጠየቀበት
ምክንያቶች መካከል ጥቂቶቹ ምንድን ናቸው?
የተለያዩ የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት የጸሐፊዎቹን የስነ ጽሑፍ ዘዴና ችሎታ
ያሳያሉ። ቢሆንም በሚመጣው ሳምንት ጥናት እንደምንወያየው ይህ የፀሐፊዎቹ
የግል የአፃፃፍ ዘዴና ችሎታ የመልእክቶቹን በመንፈስ ቅዱስ ተገፋፍቶ የመጻፋቸውን
ደረጃ በምንም አይነት አይቀንሰውም። አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ከሌሎቹ
ይልቅ ዛሬ ለህይወታችን በበለጠ ወቅታዊ ናቸው። ይህም ቢሆን የአንዱ የመጽሐፍ
ቅዱስ ክፍል ከሌላው ይልቅ በመንፈስ የተፃፈ አያደርገውም።
አንዳንድ ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች በመጀመሪያ በቃል ያስተላለፉትን
መልዕክት በኋላ ራሳቸው ጽፈውታል፣ ወይም በሌላ በሚያምኑት ሰው አጽፈውታል።
ሙሴ ሊሞት ሲቀርብ ለእስራኤላውያን የተናገረውን የመጨረሻውን ንግግር በዘዳግም
መጽሐፍ ውስጥ ዘግቦታል። አራቱ ወንጌሎች ኢየሱስ በዚህ ምድር በነበረ ጊዜ
ከሰበካቸው ስብከቶች ብዙዎቹን መዝግበው ይዘዋል።
ነገር ግን ነቢያት በመንፈስ ቅዱስ ያልተሰጡ ምንጮችን (የሐዋ 17:18፣ 1ኛ ቆሮ 15:53፣
ቲቶ 1:12) እና የሰይጣንን ቃላት ሳይቀር የጠቀሱበት ጊዜ አለ (ዘፍ 3:1-5፣ማቴ 4:1-11)።
ማስታወስ ያለብን ነገር ቢኖር ነቢያት የሌሎች ሰዎችን ምኞትና ስሜት እንደዘገቡ
ሁሉ የራሳቸውን ሰብአዊ ስሜትም መዘገባቸውን ነው።(ዳን 8:27፣ ራዕይ 22:8፣9ን
ይመልከቱ)። በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ልንከተላቸው የሚገቡንን መልካም
ምሳሌዎች ሲዘረዝር ልናስወግዳቸው የሚገቡ መጥፎ ምሳሌዎችንም ያካትታል (1ኛ
ቆሮ 10:1-11)።
መጽሐፍ ቅዱስን ስናነብ መገንዘብ ያለብን ፍፁም በሆነ ቋንቋ ባይጻፍም
የዘመናትን ፈተና የሚያልፍ የማይወድቅ መልዕክት መያዙን ነው።
መጽሐፍ ቅዱስ የተለያዩና የዳበሩ የቃላት ስዕሎችና ምሳሌዎች አሉት። ለምሳሌ
በብሉይ ኪዳን የሚገኘው የአበው የመሰዊያዎች የመስዋእት ስነ ስርዓት፣ የሙሴ
የመገናኛው ድንኳን፣ የኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ፣ እነዚህ ሁሉ የክርስቶስን በመስቀል
ላይ ያደረገውን የቤዛነት መስዋዕትና በሰማይ የሚያካሄደውን ይክህነት አገልግሎት
የሚያሳዩ ስዕላዊ ቃላት ናቸው (ዕብ 8:1-6)።
በዳንኤል ትንቢቶች ውስጥ የዓለም መንግስታትና ሃይላት በታላቁ ምስል በተለያዩ
ክፍሎች (ዳንኤል 2:31-35)፣ በተለያዩ እንስሳትና ቀንዶች (ዳንኤል 7 እና 8) እና
በሁለት ነገስታት (ዳንኤል 11) ተገልጸዋል። በራዕይ ዮሐንስም ተመሳሳይ ምስሎች፣
ለምሳሌ በምዕራፍ 13 በተገለጹት ሁለት አራዊት(አውሬዎች) ቀርበዋል።።
ኢየሱስ ራሱ ሲያስተምር እራሱን በህይወት እንጀራ (ዮሐ 6:35፣41-58)፣ የዓለም
ብርሃን (ዮሐ 8:12፣9:5) እና እውነተኛ የወይን ግንድ (ዮሐ 15:1-8) መስሏል።
በዘሪው ምሳሌና (ማቴ 13:1-9፣18-23) በሌላም ብዙ ምሳሌዎች (ማቴ 13:24-52፣
ወዘተ) ኢየሱስ የመንግስቱን ተፈጥሮ እና አስተዳደግ በምሳሌዎች አስረድቷል።
ሕዝቅኤል 4:1-8ን ያንብቡ። እግዚአብሔር በቃሉ ከመናገሩም
በላይ አንዳንድ መልእክቶቹን በትይንት (drama) ያቀረበው ለምን
ይመስሎታል?
በሕዝቅኤል 4:1-8 ላይ እግዚአብሔር ነብዩን ትንሽ የኢየሩሳሌም ምስል
ሰርቶ መጀመሪያ የእስራኤልን ቤት በመወከል በምስሉ ላይ ለ390 ቀናት በግራ
ጎኑ እንዲጋደምባት፣ ከዚያም የይሁዳን ቤት በመወከል በቀኝ ጎኑ ለ40 ቀናት
እንዲጋደምባት ባዘዘው ክፍል ግልጽ የሆነ ትይንታዊ አቀራረብ ይታያል። ሌላው
ምሳሌያዊ ትይንት ደግሞ እስራኤል በመንፈሳዊ ሁኔታ ለእግዚአብሔር ታማኝ
አለመሆኗን ለማሳየትን ሆሴዕን ጎሜር የተባለችውን ገላሞታ እንዲያገባ ያዘዘበት
ክስተት ው (ሆሴዕ 1:2-9)።
የሕዝቅኤልና የሆሴዕ ትይንታዊ ልምምዶች ዛሬ ስናያቸው ያስደነግጣሉ።
አላማውም ያው ነበር። ለእኛ ብቻ ሳይሆን በዘመኑ ለነበሩ ሰዎችም አስደንጋጭ
እንዲሆኑ የታቀዱ ትይንቶች ነበሩ። እነዚህ ነቢያት ያሰሟቸውን ማስጠንቀቂያዎች
ሕዝቡ በግልጽ ችላ ሲላቸው (2ኛ ዜና 36:15-21ን ይመልከቱ)። የመጨረሻው
መለኮታዊ ምህረት ድርጊት ሕዝቡን ወደ እውነተኛ ንስሐ ለመምራት መልዕክቱን
በእንዲህ አይነት ትይንታዊ መንገድ ማቅረብ ነበር። የዚህ ዓይነት አቀራረብ
እግዚአብሔር የገለፀላቸውን ማስጠንቀቂያዎች ምን ያህል ከልብ ሊቀበሉ
እንደሚገባቸው ሊያስረዷቸው ይገባ ነበር።
ዛሬስ እኛ ከሎዶቂያዊነታችን እንድንነቃ ምን አይነት ትይንታዊ መልዕክት
የሚያስፈልገን ይመስልዎታል? (ራዕይ 3:14-18ን ይመልከቱ)
7ኛ ቀን አድቬንቲስቶች ኤለን ጂ ዋይት መለኮታዊ መነሳሳት ተቀብላለች ብለው
ያምናሉ። ጽሑፎቿ፣ ኑሮዋና አገልግሎቶቿ የእውነተኛ ነቢይን መስፈርት ያሟላሉ።
የመንፈስ ቅዱስ መነሳሳቷ የመጽሐፍ ቅዱስ ነቢያት ካገኙት ጋር አንድ ቢሆንም
ጽሑፏን ግን ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር አታወዳድርም። እንዲያውም በአንጻሩ ኤለን
ጂ ዋይት መጽሐፍ ቅዱስን ሁል ጊዜ ከፍ ከፍ ታደርጋለች። ታዲያ እግዚአብሔር
ትንቢታዊ ራዕይ እንዴት እንደሰጣትና ሂደቱንስ እንዴት ታየዋለች?
በአንደኛ ደረጃ፣ ኤለን ጂ ዋይት መጽሐፍ ቅዱስ ፍጹም ኃይል ያለውና የማይሳሳት
የእግዚአብሔር መገለጥ መሆኑን ታምናለች። መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔርን
እውነትና እግዚአብሔር ለወደቀው የሰው ዘር ያለውን የመዳን እቅድ ይገልጣል።
በዚያ ሂደት አሁን እንደምንማረው ያን መልዕክት ለማስተላለፍ ነቢያቱን ይጠቀማል።
በሁለተኛ ደረጃ፣ የመነሳሳት ሂደት በመለኮታዊና በሰብአዊ ፍጡራን መካከል
ያለውን ግንኙነት የሚመለከት ነው። እግዚአብሔር መልዕክቱን ሲሰጥ ነቢይ ደግሞ
መለኮታዊ መልእከቱን የራሱን ወይም የራሷን ቃል በመጠቀም ለሰዎች ያስተላልፋል
ወይም ታስተላልፋለች። ኤለን ጂ ዋይት እንዲህ ብላለች፦ “በመንፈስ ቅዱስ የተነሳሱት
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያሉ ቃላት ሳይሆን የጻፍዋቸው ሰዎች ናቸው። መንፈስ
ቅዱስ የሰራው፣ ሰው በፃፋቸው ቃላት ላይ ሳይሆን በፀሐፊው ላይ ነው። መንፈስ
ቅዱስ በፀሐፊው ውስጥ አድሮ ባስተሳሰቡ ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል። መለኮታዊ ሀሳብና
ፈቃድ ከሰብአዊ ሀሳብና ፍቃድ ጋር ተዋህዶ የሰው ንግግር የእግዚአብሔር ቃል ሆነ”
(ምርጥ መልዕክቶች 1ኛ መጽሐፍ ገጽ 21)።
ራዕዮችንና ትንቢታዊ ህልሞችን በሚመለከት ኤለን ጂ ዋይት “የሀሳብ
በመንፈስ ቅዱስ መነሳሳትን” የመለኮታዊ መገለጥና ሰብአዊ የኑሮ ተሞክሮ ውህደት
እንደሆነ ተረድታለች። እንዲህ ብላለች፦”መጽሐፍ ቅዱስ በሰዎች ቋንቋ ከተገለጹ
እግዚአብሔር ከሰጣቸው እውነቶቹ ጋር የሰብአዊውንና መለኮታዊውን ጥምረት
ያቀርባል።” (ምርጥ መልዕክቶች 1ኛ መጽሃፍ ገፅ 25)። መልእክተኛው መልዕክቱን
እንዲያስተውል ለማድረግ እግዚአብሔር የተለያዩ መንገዶችን ተጠቅሟል። እነዚህም
ስዕላዊ አቀራረብን እና ቃላትንና የነቢዩን ህዋሳት በሙሉ የያዙ ሀሳቦችን ያካትታሉ።
የኤለን ጂ ዋይት ልምምድም ከመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ልምምድ ጋር ይመሳሰላል።
በሦስተኛ ደረጃ፣ ኤለን ጂ ዋይት ሰብዓዊ ልምምዶቿና ግንኙነቶቿ በሙሉ
በመንፈስ ቅዱስ የተነሳሱ (የተገፋፉ) አለመሆናቸውን አስገነዘባለች። “ተራ ንግግሮች
መነገር፣ በአእምሮ ውስጥ ተራ ሀሳቦች መመላለስ፣ እና ተራ ደብዳቤዎች በሰራተኞች
መካከል ተጽፈው ተራ መልዕክቶችን ማካፈል ያለባቸው ጊዜያቶች አሉ። የዚህ
ዓይነት ቃላትና የዚህ አይነት መረጃ በእግዚአብሔር መንፈስ ልዩ መነሳሳት የተሰጡ
አይደሉም” ብላለች (ምርጥ መልዕክቶች 1ኛ መጽሃፍ ገጽ 39)።
የእሷን ጽሑፎች ስናነብና ከጽሑፎቿና ልምምዶቿ ጋር ግንኙነት ስንፈጥር፣
በተለይም ደብዳቤዎቿንና ማስታወሾቿዋን ስናነብ ይህን ልዩነት መገንዘብ አስፈላጊ
ነው።
ኤለን ጂ ዋይት ስለ ራእይና በመንፈስ ቅዱስ ስለ መነሳሳት ያላትን ማስተዋል
ማወቅ፣ ምክሯን ስናነብ ጽንፍ ከመያዝ በመከላከል ምክሮቿን በጥንቃቄና በመረዳት
እንድናነብ ይረዳናል።