የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

የትንቢት ስጦታ



4ኛ ሩብ ዓመት 2026


መስከረም 30 - ጥቅምት 6

3ኛ ትምህርት

Oct 10 - 16




የብሉይ ኪዳን ነቢያት



ሰንበት ከሰዓት በኋላ

ለዚህ ሳምንት ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፦ ያዕቆብ 5:17፣18፣ 1ኛ ነገስት 19:1-16፣ 1ኛ ነገስት 22:1-14፣ ዘፀአት 15:20፣ 2ኛ ነገስት 22:11-14፣ ኤርምያስ 14:1-15።


የመታሰቢያ ጥቅስ፡“ኢዮሳፍጥም ቆመና በይሁዳና በኢየሩሳሌም የምትኖሩ ሆይ ስሙኝ፣ በአምላካችሁ በእግዚአብሔር እመኑ ትጸኑማላችሁ በነብያቱም እመኑ ነገሩም ይሰለላችኋል አለ” (2ኛ ዜና 20:20)።

GPS (ጂፒኤስ) ለተጓዦች ከየት ተነስተው ወዴት እንደሚሄዱ በማመልከት ይረዳቸዋል። እንዲያውም በመንገዳቸው ላይ ሊያጋጠማቸው ስለሚችል እንቅፋት (አደጋ) ያስጠነቅቃቸዋል። ወደ ሰማይ ለሚጓዙ መንፈሳዊ መንገደኞችም ለአሁን እና ለወደፊቱ ሰማያዊ GPS (ጂፒኤስ) ያስፈልጋቸዋል። እግዚአብሔር እንደዚህ ያደረገበት አንዱ መንገድ የብሉይ ኪዳንን ነቢያት አገልግሎት በመጠቀም ነበር። በስድ ንባብ፣ በምክር፣ በትንቢቶች፣ በግጥሞች (ቅኔዎች) እና በመዝሙሮች አማካኝነት በብዙ ደርዘን የሚቆጠሩ ነቢያት የእግዚአብሔርን መልዕክት ለህዝቡ አደረሱ።

የዚህ ሳምንት ትምህርት ብሉይ ኪዳን እነዚህን ነቢያት እንዴት እንደሚገልጻቸው ለመረዳት ያግዘናል። በእነዚህ የእግዚአብሔር አገልጋዮች የትንቢት መንፈስ እንዴት እንደተከሰተ እናያለን። እነዚህ ሰዎች እንደ ሁላችንም ደካማ ሰብአዊ ፍጡራን ናቸው። እንደ ሁላችንም ፍርሃት፣ ቁጣና ተስፋ መቁረጥ ሊያጠቃቸው የሚችሉ ሰዎች ናቸው። እንደሁላችንም ኑሮ ለእነርሱም ቀላል አልነበረም። በግድድሮሽና በመከራ የተሞላ ነበር።

ታዲያ የጌታ አገልጋዮች የተባሉትን የእነዚህን ሰዎች ሕይወት(ኑሮ) በመርመር ምን ልንማር እንችላለን? *የዚህን ሳምንት ትምህርት ለጥቅምት 7 ሰንበት ለመዘጋጀት ያጥኑ።

ጥቅምት 1
Oct 11

የነቢያት ሰብአዊነት


ባለፈው ሳምንት እንዳየነው ብርቱ ተቃውሞ ቢነሳበትም እግዚአብሔር ኤልያስን በእስራኤል ውስጥ ታላቅ ስራ እንዲሰራ ተጠቀመበት። እግዚአብሔር እርሱን በመጠቀም የሰራው ስራ ግሩም ነበረ። ነገር ግን...... ምን? ያዕቆብ በያዕቆብ 5:17-18 ኤልያስን እንዴት እንዳቀረበው ይመልከቱና ያሰላስሉ። “እንደኛ የሆነ ሰው ነበር..” ሲል ምን ማለቱ ነው?



ኤልያስ በቀርሜሎስ ተራራ ላይ አስገራሚ ስኬት አግኝቶ ነበር (1ኛ ነገስት 18)። እግዚአብሔር በተለየ ኃይል ተጠቀመበት። በብሉይ ኪዳን ታሪክ ከሆኑት ተአምራት ሁሉ በጣም አስገራሚ ተአምራት መካከል አንዱ ነበር። ኤልያስ ሲናገር ከሰማይ እሳት በገሃድ ወረደ ይላል (1ኛ ነገስት 18:38)። እንደዚህ አይነት ነገር ከሆነ በኋላ ይህ የእግዚአብሔር ሰው በጣም መደሰት ነበረበት ብሎ መገመት አያዳግትም። 1ኛ ነገስት 19:1-16ን ያንብቡ። ስለ እግዚአብሔር ነቢያት ስሜታዊ ሁኔታ ይህ ምንን ያሳየናል?



“ይበቃኛል! አሁንም አቤቱ እኔ ከአባቶቼ አልበልጥምና ነፍሴን ውሰድ” (1ኛ ነገስት 19:4)። ከባድ የድብርት አይነት የደረሰበት ይመስላል። ለምን? በቀርሜሎስ ተራራ ላይ የሆነውን ለመድገም ቀላል ሊሆን አይችልም። ቢሆንም አንድ የሆነ ነገር እየተካሄደ ያለ ይመስላል።

ምናልባት የሚከተለው ንግግሩ ፍንጭ ሊሰጠን ይችል ይሆናል። “ለሰራዊት ጌታ ለእግዚአብሔር እጅግ ቀንቻለሁ፣ የእስራኤል ልጆች ቃል ኪዳንህን ትተዋልና መሰዊያዎችህንም አፍርሰዋልና ነቢያትህንም በሰይፍ ገድለዋልና እኔም ብቻዬን ቀርቻለሁ፤ ነፍሴንም ሊወስዱ ይሻሉ” (1ኛ ነገስት 19:10)። አገልግሎቴ አልተሳካም እያለ እሮሮ የሚያሰማ ይመስላል። የቻለውን ሁሉ ቢያደርግም የሕዝቡን ክህደት ሊያስወገድ አልቻለም። ችግሩን እርሱ ራሱ ሊያስወገድ የሚችል ይመስል። በመጨረሻ የሆነ ቢሆን ከዚህ ላይ የምናየው ይህ የእግዚአብሔር ሰው ሰብአዊ መሆኑንና ድክመቱን ነው። በሌላ አነጋገር ኤልያስ “እንደ እኛ የሆነ ሰው ነበር።” በእርስዎ ጥረትና ሙከራ አንዳንዴ ስኬት አልባ እንደሆኑ የሚሰማዎት ለምን ይሆን? ተስፋ በቆረጡ ጊዜ ሊረዳዎት የሚችሉ የትኞቹ የቃሉ ተስፋዎች ናቸው?

ጥቅምት 2
Oct 12

እውነተኛ ነቢያትን ለይቶ ማወቅ


በእስራኤል የቀድሞ ታሪክ ውስጥ ሀሰተኛ ነቢያት መኖራቸው የታወቀ ነበር (ዘዳ 18:20)። ታዲያ የእርሱ እውነተኛ ነቢያት እነማን እንደሆኑ እንዲያውቁ እግዚአብሔር ህዝቡን ያለ መመሪያ አልተዋቸውም።

የእግዚአብሔርን ራእይና አነሳሽነት የሚቀበሉት መልዕክተኞች፣ ባለስልጣናት ዘንድ ጥላቻ ቢሰነዘርባቸውም እንኳን መልእክቱን በታማኝነት፣ በትክክለኛነትና በሀቀኝነት ያስተላለፋሉ። 1ኛ ነገስት 22:1-14ን ያንብቡ። ይህ ጥቅስ ታማኝ ነቢያት እንዴት እንደሚሰሩ እንዴት ያስረዳዎታል?



አንድ ንጉስ ስለ አንድ ነቢይ “ክፉ እንጂ መልካም ትንቢት አይናገርልኝምና እጠላዋለው” (1ኛ ነገስት 22፡8) የሚለው አነጋገር የንጉሡን ማንነት፣ ከዚያም በበለጠ የነብዩን ማንነትም በግልጽ ያሳያል። ንጉሳዊ ሞገስ ባያገኝ እንኳን ነቢዩ እውነትን ከንጉሱ ፊት ለመናገር ደፈረ።

ሚክያስ የተገለጸለትን እውነት በድፍረት እየተናገረ በአራት መቶ ሃሰተኛ ነቢያት መካከል ብቻውን ቆመ። ያን አሉታዊ መልእክት ለመቀየር ከንጉሡ አክሃብና ከዚያች ክፉ ሚስቱ ከኤልዛቤል ከባድ ተጽዕኖ ቢመጣበትም (1ኛ ነገስት 22:13፣14)፣ ሚክያስ የእግዚአብሔርን እውነት ተናገረ። መልእክቱ ተቀባይነት ይኑረው አይኑረው የእርሱ ጉዳይ አልነበረም። 1ኛ ሳሙኤል 9:3-14ን ያንብቡ። ታማኝ ነቢያትን ሌሎች ሰዎች ምን ግምት እንደሚሰጧቸው ከእነዚህ ቁጥሮች ምን ይረዳሉ?



በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የነቢያትን አኗኗር የሚያስረዱ አያሌው ምሳሌዎች ይገኛሉ። ይህንን ስናይ ሳኦልን አባቱ ቂስ የጠፉ አህዮችን እንዲፈልግ ልኮት ነበር። አብሮት የነበረው አሽከሩ እንዲህ አለ፦ “አንድ የእግዚአብሔር ሰው በዚህች ከተማ አለና እርሱም የተከበረ ሰው ነው” በማለት አህዮቹን መፈለጋቸውን እንዳይተው ሳኦልን መከረው (1ኛ ሳሙኤል 9:6)። እዚህ ላይ ስለ ሳሙኤል የተሰጠው መግለጫ ከእግዚአብሔር ነቢያት ዘንድ የሚጠበቀውን የህይወት (የኑሮ) ጥረት ያመለክታል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እውነተኛ ነቢያት በከፊል ይእርሱን ባህሪ በሕይወት ምሳሌነታቸው እንዲያሳዩ የተመረጡ “የእግዚአብሔር ሰዎች” ተብለው ተገልጽዋል። በሌላ በኩል ደግሞ “የእግዚአብሔር ሰዎች” የተባሉት ነቢያትም ቢሆን እንከን የለሽ ሰብዓዊያን ናቸው ማለት አይደለም። ከእነዚህ እጅግ ከተከበሩ “የእግዚአብሔር ሰዎች” መካከል እንኳን እንከን የለሽ የሆነ ማንን ያውቃሉ?

ጥቅምት 3
Oct 13

የነቢያት ሥራ


1ኛ ሳሙኤልን 8:4-22ና ዘሌዋውያን 8:10-13ን ያንብቡ። ከነገስታትና ከካህናት ጋር በነበራቸው ግንኙነት የነቢያት ስራ ምን ነበረ?



ነቢያት ከነገስታት ጋር የነበራቸው ግንኙነት አንዳንድ ጊዜ የሚያስደስት በሌላ ጊዜ ደግሞ የማያስደስት ነበር። እስራኤላውያን ንጉስ ይሰጠን ብለው ሲጠይቁ (1ኛ ሳሙኤል 8:4-22)” እንደ አህዛብ የሚፈርድልን ንጉስ አድርግልን” አሉ (1ኛ ሳሙኤል 8:5)። ይህ የእግዚአብሔር ሕዝብ በዘመናት ሁሉ የገጠማቸውን ችግር የሚያሳይ ሃይለኛ ምሳሌ ነው፣ በአካባቢያቸው እንዳሉት ህዝቦች ለመሆን መፈለግ። እግዚአብሔር በነብዩ በኩል ቢያስጠነቅቃቸውም (1ኛ ሳሙኤል 8:11-18) የጠየቁት ጥያቄ የሚያደርስባቸውን ጉዳት አልተገነዘቡም። ማስጠንቀቂያ ቢሰጣቸውም በጠየቁት መሰረት በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ የእስራኤል የመጀመሪያው ንጉስ ተብሎ የሚታወቀውን ሳኦልን ሳሙኤል አነገሰላቸው።

1ኛ እና 2ኛ ነገስት፣ 1ኛ እና 2ኛ ዜና የተባሉት የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት የእስራኤልንና የይሁዳን ነገስታት የአገዛዝ አይነቶች መዝግበዋል (ዘግበዋል)። ቃሉ እንደሚያስረዳው በእግዚአብሔር ፊት መልካም ከሠሩት ይልቅ ክፉ የሠሩት ነገስታት በቁጥር ይበልጣሉ። ከነቢያት ተግባራት አንዱ ታማኝ ያልሆኑትን ነገስታት የእግዚአብሔርን ህግ ወደ መታዘዝ መመለስ ነበር። ውጤቱ ታዲያ የእግዚአብሔርን ህዝብ ያሳሳቱት ነገስታት እነዚህን ነቢያት አስፈራሯቸው፣ እንዲያውም አንዳንዴ ጉዳት ወይም ሞት አደረሱባቸው (1ኛ ነገስት 18:4-19፣ 2ኛ ዜና 24:20-22)።

ነቢያት ደግሞ ከካህናት ጋር ግንኙነት ነበራቸው። ሙሴ አሮንን እና ልጆቹን የመጀመሪያዎቹ የእስራኤል ካህናት አድርጎ ሾማቸው (ዘሌ 8:10-13)። ካህናት በነቢያት አማካይነት ከእግዚአብሔር ተግሳጽ የተቀበሉባቸው ጊዜያት ነበሩ።

አንድ የማይረሳ ምሳሌ የኤሊ ቤተሰብ በሙሉ ስለ ብልሹ ተግባራቸው የገጠማቸው ተግሳጽ ነበር (1ኛ ሳሙኤል 2:27-36)። እነዚህ የተለየ መብት የተሰጣቸው ሰዎች ሀላፊነታቸውን ስላበላሹ ብርቱ ተግሳፅ ደረሰባቸው።

ነቢያት የሕዝቡ መምህራን ነበሩ (2ኛ ዜና 34)። ለካሕናቱ፣ ለነገስታቱና ለህዝቡ የእግዚአብሔርን መልዕክት አቀባዮች ነበሩ (ሕዝቅኤል 22:26፣ ኤርምያስ 5:31)። በብሉይ ኪዳን ተደጋግሞ እንደታየው የእግዚአብሔርን እቅድ በአካባቢው ላሉት ህዝቦች ያስታውቁ ነበር (ኢሳያስ 60:1-3፣ ኢሳያስ 62:1፣2)። እግዚአብሔር የሰጣቸውን መልዕክት ማስተላለፍ ብቻ ሳይሆን ነቢያት አንዳንድ ጊዜ መልዕክቱን በጽሑፍ እንዲያስቀምጡ እና እንዲያቆዩ ይታዘዙ ነበር (2ኛ ዜና 13:22)። ነቢያት የፈለገውን ያህል ሰው ቢሆኑም፣ በሰው ሁሉ ላይ የሚገኘው ድክመት ቢኖርባቸውም፣ የጸሎት እና የቃሉ ወንዶችና ሴቶች፣ እንዲሁም የእግዚአብሔርና የህዝቡ አገልጋዮች ነበሩ (ኤርምያስ 42:4፣ 2ኛ ነገስት 22:15-17)።

ጥቅምት 4
Oct 14

ሴቶች ነቢያት


የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ። ዘፀአት 15:20፣ መሳፍንት 4:4፣ 2ኛ ነገስት 22:14፣ነህምያ 6:14። እነዚህ ጥቅሶች ደግሞ ነቢያት ስለሚጫወቱት ሚና ምን ያስተምሩናል?



እግዚአብሔር ሴቶችን ለነቢይነት እንደጠራ የሚያረጋግጥ በመጽሐፍ ቅዱስ በቂ መረጃ አለ። (ኒቪአህ የሚለውን የዕብራይስጥ ቃል አጠቃቀምን (ዘፀ 15:20) እና ፕሮፈቲስ የሚለውን የግሪክ ቃልም ይመልከቱ (ሉቃ 2:36))። በሚክያስ 6:4 ላይ ወድ ሕዝቡ የተላኩ ተብለው ከተወሱት መካከል ከሙሴና ከአሮን ጋር ሚርያም አብራ ተወስታለች። ሚርያም እስራኤላውያን ቀይ ባህርን ከተሻገሩ በኋላ የድል መዝሙር የዘመረች ነቢይ ተብላ እውቅናን አግኝታለች (ዘፀ 15:20፣21ን ያንብቡ)። ነገር ግን በሙሴና በኢትዮጵያዊት ሚስቱ ላይ የነበራት የሚያሳፍር አስተያየት እንደሚያስረዳው ይህች ነቢይት እንደ ወንዶች ነቢያት ባልደረቦችዋ ሁሉ ያለ እንክን አልነበረችም። ነቢይቱ ለዚህ ስህተቷ ተገቢውን ቅጣት ተቀብላለች (ዘሁ 12:1-10)።

የእስራኤላውያን ፈራጅ በነበረችው የዲቦራ ታሪክ ውስጥ የሌላ ነቢይ ስራ መመልከት እንችላልን (መሳ 4:1-4)።

እንዲያውም ዲቦራ ከእግዚአብሔር ራእይ እንደተቀበለች በቂ መረጃ አለ (መሳ 4:4-9፣14:22)። የእግዚአብሔርን ጣልቃ መግባት እውቅና ለመስጠት የዘመረችው የድል መዝሙር በዚያን ጊዜ ለነበረው ለህዝቡ ታሪክ ታላቅ ስነ-መለኮታዊ ትርጉም አለው (መሳ 5:2-31)። 2ኛ ነገስት 22:11-14ን ያንብቡ። ንጉስ ኢዮስያስ ወደ ሕልዳና ለምን ላከ? ይህ በሕዝቡ ላይ የተጫወተችውን ሚና እንዴት ያስረዳናል?



የንጉሱ ኢዮሲያስ ከፍተኛ ባለስልጣናት “ነቢይቱን” ሕልዳናን አማከሩ። ይህን ያደረጉት “የሕጉን መጽሐፍ” ከነበቡ በኋላ ነው (2ኛ ነገ 22:14፣ 2ኛ ዜና 34:22፣ 2ኛ ነገስት 22:28)። “የሕጉ መጽሐፍ” የተባለው ዘዳግም እንደነበረ ይታመናል። “የሕጉ መጽሐፍ” ሲነበብለት ንጉሡ ልብሱን ቀደደ (2ኛ ነገ 22:11)። ይህ ጉዳይ አንገብጋቢ ጉዳይ ነበረ። ንጉሡም የተመለከተው በዚያ መልኩ ነበር። ሰዎችም በቀጥታ ወደ ሕልዳና የሄዱት ለዚህ ነበር። በይሁዳ ላይ ስለሚያንዣብበው ፍርድ መልዕክት ተቀብላ ነበር። ኢዮስያስ ያደረገው ተሀድሶ በሕልዳና መልእክት ላይ የተመሰረተ ነበር። በሕዝቡ ላይ ያንዣበበው ቅጣትም ሳይደርስ ቀረ። ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ነቢያት በእግዚአብሔር ቢጠሩም ቅሉ ጸጋ የሚያስፈልጋቸው ኃጢአተኞች ነበሩ። ታዲያ ከእነዚህ ታሪኮች ምን አይነት ተስፋ እናገኛለን?

ጥቅምት 5
Oct 15

ሐሰተኛ ነቢያት


እግዚአብሔር ያደረገውን ቢያደርግ ሰይጣን ምንጊዜም ተጻራሪ የሆነ ማስመሰያ ነገር አለው። በነቢያትም እንደዚሁ ነው። እስራኤል እውነተኛና ሃሰተኛ ነቢያት አጋጥሟታል። ቁልፉ (ወሳኙ) ነገር ልዩነታቸውን ከማወቅ ላይ ነው። ኤርምያስ 14:1-15ን ያንብቡ። እዚህ ላይ የምናየው ምንድነው? በስሙ “ነቢያት” ነን እያሉ የሚናገሩትን እግዚአብሔር እንዴት ያያቸዋል?



በኤርምያስ 14 ላይ እግዚአብሔር በኤርምያስ በኩል የፍርድ መልእክት ላከባቸው። ፍርዱም የሚከሰተው በሰይፍ (ጦር)፣ በረሃብ እና በቸነፈር ነበር። በጊዜው የነበሩ ሀሰተኛ ነቢያት የኤርምያስን መልዕክት አስተባባሉ። ኤርምያስ በግልጽ ስም ይሰይማቸዋል። “እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፦ ነቢያቱ ውሸት በስሜ ትንቢት ይናገራሉ፤ አላክኋቸውም፥ አላዘዝኋቸውም፥ አልተናገርኋቸውም፤ የውሸቱን ራእይ ምዋርትንም ከንቱንም ነገር የልባቸውንም ሽንገላ ይሰብኩላችኋል” (ኤርምያስ 14:14)። የመልእክታቸው ምንጮች የሚያመልኳቸው ሀሰተኛ “አማልክት” ስለሆኑ ሀሰተኛ ነቢያት ብልሹ ናቸው (ኤርምያስ 23:13፣14)። እግዚአብሔር እንዲህ ሲል ያስጠነቅቃል፦ “አልላኳቸውም፣ አላዘዝኳቸውም፣ አልተናገርኳቸውም” (ኤርምያስ 14:14)። “ትንቢትን በሐሰት በሚናገሩ፥ የልባቸውንም ሽንገላ በሚናገሩ በነቢያት ልብ ይህ የሚሆነው እስከ መቼ ነው?” (ኤርምያስ 23:26)። ሕዝቅኤል “ከገዛ ልባቸውም ትንቢት የሚናገሩትን መስክርባቸው” ተብሎ ነበር (ሕዝቅኤል 13:2)።

ሀሰተኛ ነቢያት አብዛኛውን ጊዜ የብዙሃንን አስተያየት ይከተላሉ። በ1ኛ ነገስት 22 የሆነው እንዲሁ ነው። አራት መቶ ነቢያት በአክዓብ ትዕዛዝ ተሰበሰቡ። ሬማት ዘገለዓድን እንዲዋጋ በአንድ ድምጽ መከሩት (1ኛ ነገስት 22:6)። አክዓብ የይሁዳ ንጉስ ኢዮሳፋጥን አማከረ። እዮሳፋጥ ወደ ጦርነት ከመዝመቱ በፊት ነብዩን ሚክያስን እንዲጠይቅ መከረው። ሚክያስን ሊጠራ የሄደ መልእክተኛ- “እነሆ ነቢያት ሁሉ በአንድ አፍ ሆነው ለንጉሡ መልካምን ይናገራሉ፣ እንደ ቃላቸው እንዲሆን መልካም እንድትናገር እለምንሃለሁ አለው” (1ኛ ነገስት 22:13)። በሚክያስ ላይ የነበረበት ተጽዕኖ በሀሰተኞቹ ነቢያት ላይ ከነበረው ተጽዕኖ አያንስም ነበር። ሚክያስ ግን የብዙኀንን አስተያየት አልተከተለም። በዚያ ፈንታ እግዚአብሔር የሚናገረውን እስኪያዘው ጠበቀ (1ኛ ነገስት 22:14)። ነቢይ ቢሆንም ባይሆንም የብዙኀንን ሀሳብ መከተል ምንጊዜም ቀላል ነው። ባህል ምን ያህል ብልሹ መሆን እንድሚችል ከግምት ውስጥ በማስገባት ብዙሃንን መከተል የማይበጀው ለምንድነው?

ጥቅምት 6
Oct 16

እንከን የለሽ ባትሆንም ፈቃደኛ ነበረች


የእግዚአብሔር መልእክተኛ መሆን ቀላል አለመሆኑን በብሉይ ኪዳን ነቢያት ህይወት አይተናል። የመጽሐፍ ቅዱስ ነቢያት የገጠማቸው ችግር ኤለን. ጂ ዋይትንም ገጥሟታል። ባለፈው ዓርብ እንዳየነው እግዚአብሔር ጥሪ በመጣላት ጊዜ ወጣት (ልጅ)፣ አይነ-አፋርና ባለ ሙሉ ጤና ያልሆነች ነበረች። ጥሪዋ በሁለተኛ ራዕይ ሲረጋገጥላትም እንዳመነታች እንዲህ ብላ ጽፋለች፦

“ከአንድ ሳምንት በኋላ ጌታ ሌላ ራዕይ በመስጠት የማልፍባቸውን ፈተናዎችም አሳየኝ። የገለጠልኝን ለሌሎች እንድናገር አዘዘኝ። ተቃውሞ እንደሚገጥመኝም ነገረኝ። የመንፈስ መታወክም እንደሚደርስብኝ አስጠነቀቀኝ።......ራዕዩ በጣም ረበሸኝ። ጤነኛ አልነበርሁም። በእድሜዬ የአስራ ሰባት ዓመት ልጅ ነበርኩ። ሸክሙ ለሌላ ሰው እንዲሰጥ ከልቤ ጸለይኩ። ነገር ግን የተቀበልኩት ብርሃን `የነገርኩሽን ለሌሎች አካፍይ` የሚል ነበር። ወደ ዓለም ለመውጣት አልደፈርሁም። በራሴ ላይ ምንም አይነት መተማመን አልነበረኝም። ሞትን ተመኘሁ። ከተሸከምኩት መልዕክት ይልቅ መሞት ቀልሎ ታየኝ” (መንፈሳዊ ስጦታዎች መጽሃፍ 2 ገጽ 35፣36)።

ኤለን ሐርመን ዋይት ጥሪዋን ከመቀበል ይልቅ ብትሞት እንደፈለገች ልብ ብላችኋል? ከብዙ ጸሎትና ከሌሎች አማኞች ማደፋፈር በኋላ እድሜዋን በሙሉ ለጌታ ስራ ለማዋል ወሰነች (መንፈሳዊ ስጦታዎች መጽሃፍ 2 ገጽ 38)።

ለሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተ ክርስቲያንና ስለ ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተ ክርስቲያን ከማንም የበለጠ ተሰሚ ድምጽ ሆነች። ቢሆንም ኤለን ሐርመን ዋይት እንደ ማንኛውም ሰው የራሷ የሆነ የግል ጉድለት፣ የጤና ችግር፣ የቤተሰብ ግድድሮሽና ከሌሎች ጋር ያለመግባባት ችግር ነበረባት። ነገር ግን ከሰብአዊ እንከኖቹ መካከል ትልቅ ትምህርት እናገኛለን። እግዚአብሔር ለማገልገል ፈቃደኛ ከሆኑ እንከን ያላቸውንም ሰዎች ይመርጣል።

በመንፈስ ቅዱስ መሪነት የኤለን ጂ ዋይት ትንቢታዊ አገልግሎት አማኞን አበረታታ፣ ከመጽሐፍ ቅዱሳው እውነት ጋር አስተዋወቃቸው። በ1860 ዓ ም ለጋዋን 7ኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተ ክርስቲያን በማደራጀትና ቤተ ክርስቲያኗ የሦስቱን መላእክት መልዕክት በዓለም ዙሪያ እንድታደርስ ወሳኝ ሚና ተጫውታለች። በ1863 ዓ ም እነዚህን አማኞች የሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተ ክርስቲያንን እንዲቆረቁሩ እግዚአብሔር ረዳቸው። በሚከተሉት አስርት ዓመታት 7ኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተ ክርስቲያን ዓለም አቀፍ የሆነውን የጤናና የትምህርት አሰጣጥ መዋቅሮችን እንድትመሰርት የኤለን ጂ ዋይት ትንቢታዊ ድምጽ ታላቅ ተጽዕኖ አሳድሯል።

ነገር ግን የአገልግሎቷ ከሁሉም የሚበለጠው አስተዋጽኦ ጽሑፎቿ ነው። ጠቅላላ ጽሑፏ በግምት አንድ መቶ ሺህ ገጽ ይሆናል። የኤለን ዋይት በመንፈስ ቅዱስ ምሪት የተጻፉ ጽሑፎቿ ዛሬም በዓለም ዙሪያ መናገራቸውን ይቀጥላሉ።




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA Union SSL