የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ለዚህ ሳምንት ጥናት እነዚህን ጥቅሶች ያንብቡ፦ዘፍ 15:6፣ ገላትያ 3:6-9፣1ኛ ነገስት 18:19-39፣ ኢሳያስ 53፣ ዳንኤል 2:46-48፣ማርቆስ 1:2-5፣ ማቴዎስ 11:1-6።
የመታሰቢያ ጥቅስ፡“የጌታን ድምጽ ማንን እልካለሁ? ማንስ ይሄድልናል?
ሲል ሰማሁ። እኔም እነሆ እኔን ላከኝ አልሁ” (ኢሳያስ 6:8)።
ነቢያት በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመናት በእግዚአብሔር ህዝብ ታሪክ ውስጥ ወሳኝ
ሚና ተጫውተዋል። አንዳንዴ በማህበረሰቡ ሕይወት ውስጥ ወሳኝ ባይሆን
እንኳን ሀይለኛ ቦታዎችን በመያዝ መዕከላዊ ሆነው ሰርተዋል።
ሆኖም ነቢይ መሆን አስቸጋሪ ጥሪ ነበር። ሕይወታቸው በሀዘን፣ በመገፋት፣
ባለመስተዋልና ተስፋ በመቁረጥ የተሞላ ነበር።
አብዛኛውን ጊዜ የእግዚአብሔር ነቢያት የነቢይነት ማዕረጋቸውን አሜን
ብለው በአንዴ አይቀበሉም ነበር። እንዲህ ማድረጋቸው ሊያስገርም አይገባም
(አይፈረድባቸውም)። ብዙ ነቢያትን መልዕክታቸውን ሊቀበሉ የሚገባቸው ሰዎች
በብርቱ ተቃውመዋቸዋል። የእግዚአብሔር ነቢያት አልተደመጡም፣ መሳለቅያ
ሆነዋል፣ ታስረዋል፣ ሌሎችም ደግሞ እንደ ዱር አራዊት ታድነዋል፣ ተወግረዋል፣
ብዙዎች ደግሞ የሰማዕትነት ዕጣ ደርሶባቸዋል።
ዛሬ፣ ወንጀል፣ ስስት (ስግብግብነት)፣ ኢ-ግብረገባዊነት፣ ብዝበዛና የተለያዩ
ሰይጣናዊ ተፅዕኖዎች ባጥለቀለቁት ትውልድ ውስጥ የነቢያት ድምጽ ችላ ተብሏል
ወይም በጭራሽ አዳማጭ የለውም። የእግዚአብሔርን ነቢያት ድምጽ እንድንሰማና
በነቢያት አማካኝነት የተሰጠው የተስፋ መልዕክት መልዕክተኞች እንድንሆን
ተጠርተናል።
ባለፈው ሳምንት በኤደን ከተከሰተው ውድቀት በኋላ እግዚአብሔር ከሰው ዘር
ጋር ግንኙነት እንደገና እንዳቋቋመ ተምረናል። ለወደቀው ዓለም ነዋሪዎች መልዕክቱን
እንዲያቀበሉ እግዚአብሔር ነቢያትን ጠራ።
*የዚህን ሳምንት ትምህርት ለመስከረም 30 ሰንበት ለመዘጋጀት ያጥኑ።
ከዘፍጥረት እስከ ዮሐንስ ራእይ ድረስ እግዚአብሔር የጸጋውን ጥሪ ተቀብለው
ታዛዥ የሆኑ ቅሬታዎች አሉት (ኤርምያስ 31:7፣31-34ን ይመልከቱ)። ለምሳሌ
ከባቤል መበተን ብዙ ዓመታት በኋላ እግዚአብሔር አብራምን (በኋላ አብርሃም
የተባለውን) መረጠ። የመረጠውም ለቤተሰቡ ብቻ ሳይሆን ለቀጣይ ትውልዶች
ሁሉ የእምነት ቃል ኪዳን ምሳሌ እንዲሆን ነው። በክህደትና በግብረገብ ብልሹነት
ቢከበብም አብርሃም ለእግዚአብሔር ጥሪ ታማኝ ሆኖ ተገኘ (ዘፍ 15:6-17)።
የአብርሃምን እምነት ለመፈተንና የእግዚአብሔርን ልጅ የወደፊት መስዋዕትነት
ለማስረዳት አብርሃም ልጁን ይስሃቅን ለመስዋዕትነት እንዲያቀርብ ተጠየቀ።
አብርሃም የእግዚአብሔርን ግልጽ ትእዛዝ ላለመታዘዝ ብዙ ምክንያቶች ሊሰጥ ሲችል
ነገር ግን በታማኝነት ታዘዘ። እግዚአብሔር ልጁን እንዳይገድል የአብርሃምን እጅ
ጨብጦ (ይዞ) በምትኩ በግ አዘጋጀ።
ነቢያት ሁሉ ከሚመጣ መአት ህዝቡን እንዲያስጠነቅቁ አልተጠሩም። ነገር ግን
ሕዝቡን ወደ ታማኝነት እንዲመልሱ፣ ከክህደት ህዝቡን እንዲያስጠነቅቁ፣ ሰዎች
ድሆችን እና ችግረኞችን እንዳይጨቁኑ እንዲነግሩ፣ ቃል ኪዳኑንና ውሉን እንዳይጥሱ
ለማስጠንቀቅ ሁሉም ነቢያት ተጠርተዋል።
ከሁሉም በበለጠ የተመረጡበት ዋና አላማ በመሲሁ የሚገኘውን የመዳን ተስፋ
እንዲገልጹ ነበረ። የማይሻረው የመጽሐፍ ቅዱስ ነቢያት ምስክርነትና በዘመናችን
የሚገኘው የመንፈስ ቅዱስ አነሳሽነት የሚመጣውን ጥፋት አውቀን (ተገንዝበን)
ሌሎችን ማስጠንቀቅ እንዳለብን ግድ ይሉናል። ነገር ግን የማስጠንቀቂያው ዋና ቁም
ነገር ኪዳኑን በታማኝነት ለጠበቁት ሁሉ የተሰጠው የክርስቶስ አዳኝነት የምስራች
ነው (ራዕይ 12:7)።
ዘፍ 15:6ን፣ ገላ 3:6፣9ን እና ዕብ 11:8ን ያንብቡ። በግልጽ እንከን
ያለው ሰው ቢሆንም በአብርሃም ሕይወትና ባህሪ ላይ ለእግዚአብሔር
አገልጋይነት ብቁ ያደረገው ምንድነው?
በአብርሃም እና በእኛ ጊዜ መካከል ብዙ ተመሳሳይ ነገሮች አሉ። በአብርሃም ዘመን
አህዛብነትና ጣኦት አምላኪነት አገር ፈትቶ እንደነበረ ሁሉ ዛሬም በዓለም ላይ ያሉት
ተፎካካሪ ርእሰ ሃሳቦች ሁሉ ክርስትናን ለማግለልና ለማጥፋት በርትተው ይጥራሉ።
ቃሉ “አብርሀም በእግዚአብሔር አመነ ጽድቅም ሆኖ ተቆጠረለት”
ይላል (ዘፍ 15:6)። በዚህ ጥቅስ ውስጥ የወንጌሉ ተስፋ እንዴት
በኃይል ተገልጾ ያዩታል? ይህስ በራስዎ ውስጥ ምን አይነት ተስፋ
ያሳድርብዎታል?
1ኛ ነገስት 18:19-39ን ያንብቡ። የነቢየነት ስራ እንዴት መስራት እንደሚችል ምን መማር እንችላለን?
የኤልያስ መጠራትና የአነጋገሩ ዘዴ የእግዚአብሔር መልእክተኛ መሆኑን
ያመለክታል። የእስራኤልን ክህደት ለማስቆም አመታት የሚያስቆጥር ድርቅ
እንደሚከተል እንዲነግረው እግዚአብሔር ኤልያስን ወደ አክዓብ ላከው። ሕዝቡ
ከጣዖት አምላኪነት ወደ መታዘዝ እንዲመለሱ እግዚአብሔር ይህን መከራ ተጠቀመ።
ንጉሱና ህዝቡ የችግራቸው ምንጭ ኤልያስ መሆኑን አምነው ሊገድሉት ፈለጉ።
ኤልያስ የበዓልን ነቢያት በቀርሜሎስ ተራራ ላይ ተጋፈጣቸው። ጣኦት
አምላኪ የሆኑትን እስራኤላውያን የሃሰት አማልክቶቻቸውን አውግዘው ወደ አምላክ
(ወደ ጌታ) እንዲመለሱ ኤልያስ መንፈሳዊ ተማጽኖ አቀረበላቸው። ርጫቸው ወደ
ህዝባዊ ክህደት እንደከተታቸው ያውቁ ነበር። አሁን ከሀሰት አማልክቶቻቸው የበላይ
የሆነውን የኤልያስን አምላክ ለመቀበል ዝግጁ ነበሩ። እንዲያውም እነዚያ ሀሰተኛ
አማልክት ህልውና አልነበራቸውም።
የክርስቶስ ዳግም ምጽአት ሲቀርብ ሰዎች “ከጣዖቶቻቸው” እንዲርቁና እና
ወደ አምላካቸው እንዲመለሱ የኤልያስን መልዕክት ለሰዎች ሁሉ እንድታውጅ
ቤተ ክርስቲያንን እግዚአብሔር አዝዟታል። እግዚአብሔር አሁንም በፈቀደው
መስመር ለተከታዮቹ መልዕክቱን ያስተላልፋል። ቃሉና የትንቢት መንፈስ ተግሳጽን፣
ማስጠንቀቂያ፣ ምክርንና፣ ማደፋፈርን ይለግሳሉ።
“የእውነት ጌታን የማምለክ መነቃቃት ከሚያስፈልጉንና አጣዳፊ ከሆኑት ነገሮች
ሁሉ የበላይነት አለው። ይህን መሻት ቀዳሚ ስራችን መሆን አለበት። እግዚአብሔር
ሊሰጠን ስለማይፈቅድ ሳይሆን እኛ ለመቀበል ስላልተዘጋጀን የጌታን በረከት ለመቀበል
ልባዊ ጥረት ማድረግ አለብን” (ኤለን ጂ ዋይት ምርጥ መልዕክቶች 1ኛ መጽሐፍ ገፅ
12:1)።
ሚልክያስ 4:5፣6ን ያንብቡ። እግዚአብሔርን በሚከተሉ ቤተሰቦች ላይ
የኤልያስ መልዕክት ምን አይነት ተጽዕኖ ይኖረዋል?
እውነተኛ መነቃቃት በልብ ውስጥ እና በቤተሰብ ውስጥ ይጀምራል። ቤተሰብ
የቤተ ክርስቲያን እና የህብረተሰብ መሰረት ነው። የቤተሰብ መነቃቃት በቤተ
ክርስቲያን፣ በህብረተሰብና በሀገር ሁሉ ላይ ሰማያዊ (አምላካዊ) ፍቅር ያሰራጫል።
በቤተሰቦቻችን፣ በልባችንና በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ ምን አይነት
ጣዖታት ይገኛሉ?
ከብሉይ ኪዳን አብይ ነቢያት መካከል አንዱ የሆነው ኢሳያስ የነቢይነት
አገልጋይነቱን የተቀበለው በቀጥታ ከእግዚአብሔር ነበር (ኢሳያስ 6:1-8)።
የእግዚአብሔር ቅዱስነትና ግርማ ሞገስ ስላስፈራው ኢሳያስ ብቁ አለመሆኑን
ተገነዘበ። በዚያች ቅጽበት ፍም የያዘ ሱራፌል ከሰማይ እየበረረ ወደ ኢሳይያስ መጥቶ
ሃጢያቱን “አስወገደለት”። በመቀጠል እግዚአብሔር እንዲህ ሲል ጠየቀ “ማንን
እልካለሁ ማንስ ይሄድልናል? (ኢሳያስ 6:8)።
የኢሳይያስ ጥሪ የመጣው በእስራኤል ታሪክ ውስጥ ወሳኝ በሆነ ጊዜ ነበር።
የራሱ ድክመት ቢኖረውም እስራኤልንና መሪዎቿን ከሃጥያታቸው ማስጠንቀቅ
በጣም አስፈላጊ ስራ ነበረ። የኢሳይያስ ትንቢቶች የእግዚአብሔርን ባህሪ፣ የሰብዓዊን
ማንነት እና የመዳንን ዕቅድ ለመግለጥ በጥልቀት የሚያስረዱ የእግዚአብሔር ቃል
ዋና ክፍል ነበሩ። እንዲሁም ስለ ክርስቶስ መሞት ብቻ ሳይሆን መሞቱ ለዓለም
ምን እንደሚያደርግ የሚናገረው ትንቢት የሚገኘው በታወቀው በኢሳይያስ 53ኛው
ምዕራፍ ውስጥ ነው።
ኢሳይያስ ምዕራፍ 53ን ያንብቡ። ከመስቀሉ በፊት አምስት ምዕተ
አመታት ቀድሞ የተጻፈው ይህ አስገራሚ ትንቢት የክርስቶስን ሞት
ለእኛ እንዴት በኃይል ያሳየናል? ስለ ትንቢታዊ ስጦታስ ይህ ትንቢት
ምን ያስተምረናል?
የኢሳይያስ ትንቢቶች የመሲሁን ሐሳብና ተልዕኮ አስቀድሞ ተናግረዋል (
ኢሳያስ 53:3-5)። “ለመታረድ እንደሚነዳ ጠቦት” እንዴት መስዋዕትነቱ ህዝቡን
ከኃጢአታቸው እንዳነጻቸው በሚገባ ተገልጿል። የክርስቶስ የቤዛነት ሞት ያለ
ጥርጥር በግልጽ ስለተፃፈ ለሰብዓዊ ዘር ሁሉ የማስተሰረይን መሰረት ያሳያል።
“እኛ ሁላችን እንደ በጎች ተቅበዝብዘን ጠፋን፣ ከእኛ እያንዳንዱ ወደ ገዛ መንገዱ
አዘነበለ፣ እግዚአብሔርም የሁላችንን በደል በእርሱ ላይ አኖረ” (ኢሳያስ 53:6)።
የኃጢአት ሁሉ-አቀፍነት ከዚህ ላይ ተገልጧል። የኃጢአት መፍትሄ የሆነው
የመስቀሉ ሁሉ-አቀፍነትም እንደዚሁ ተገልጧል። ምናልባት ከብሉይ ኪዳንም ሆነ
ከአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ይልቅ ይህ ምዕራፍ የመዳንን ዕቅድ በግልጽ እና በማያሻማ
ሁኔታ ያስረዳል።
የኢሳይያስ ትንቢታዊ ጥሪ ቀላል አልነበረም። ስለ መጥፊያቸው የተነገረው
ጥብቅ ማስጠንቀቂያ አስቂኝ ነገር መስሎ ታያቸው። ዛሬም ቢሆን ስለ ኃጢአት ዋጋ
ሲነገራቸው ብዙዎች ያሾፋሉ (ሮሜ 6:23)።
የኢሳይያስ ትንቢታዊ ድምጽ ለእርሱም ዘመን ሆነ ለእኛም ዘመን ግልጽ ነው
(ኢሳያስ 2:4ን፣ ኢሳያስ5:20ን ይመልከቱ)። የእየሩሳሌምን መደምሰስ ያመጣው
ፍትህንና ተሃድሶን ለማድረግ የህዝቡ ማመጽ ነበር። ያው ኃጢአት ክርስቶስ ሲመጣ
ጠማማና ክፉ ነዋሪዎች እንዲጠፉ ምክንያት ይሆናል።
ኢሳይያስ ምዕራፍ 53 ደግመው ያንብቡና ኢየሱስ ለእኛ የሚያደርግልን
በእነዚያ ቁጥሮች ውስጥ የሰፈሩትን ነገሮች ሁሉ ይመዝግቡ። ክርስቶስ
በሞቱ ያደረገልንን ሁሉ ነብዩ የገለጠውን ሲረዱ ለራስዎ ምን አይነት
ታላቅ ተስፋ ይሰማዎታል?
በዳንኤል ምዕራፍ 1 የሚገኘውን ዳንኤል በልጅነቱ በተማረው የጤና ህግ ጸንቶ እንደቆመ የሚተርከውን ታሪክ አብዛኞቹ ክርስቲያኖች ያውቃሉ (ዳንኤል 1:8)። የቤተ መንግስት ምግብ ሲቀርብለት በዚያ ፋንታ ቀላል የጥራጥሬና የፍራፍሬ ምግብ መመገብና ጥሩ ውሀ ብቻ መጠጣት መረጠ (ዳንኤል 1:12-16)። የሞትና የህይወት ጉዳይ ከሆነው በዳንኤል ምዕራፍ 6 ከቀረበበት ፈተና ጋር ሲነፃፀር ይህ ትንሽ ፈተና ነበር። ዳንኤል 2:46-48ን፣ ዳንኤል 4፡18ን፣ ዳንኤል 5፡13፣14ን፣ ዳንኤል 6:25-27ን ያንብቡ። እነዚህ ጥቅሶች በዙሪያው ለነበሩት ዳንኤል የመሰከረው ምስክርነት ምን አይነት እንደነበረ እንዴት ያሳያሉ?
ስለ ዳንኤል አምላክ ሃያልነት እነዚህ አረማውያን ይማራሉ። እነዚህ የተለያዩ
ታሪኮች ቢሆኑም የሚያስረዱት ሀሳብ አንድ ነው። በአኗኗራችን፣ በታማኝነታችንና
የእግዚአብሔር ኃይል በእኛ ውስጥ እና በእኛ በኩል ሲሰራ ሌሎች ስለ ሰማያዊ
አምላክ ሊማሩ ይችላሉ ሊማሩም ይገባቸዋል። “የአማልክት አምላክና የነገስታት
ንጉስ” መሆኑን ይገነዘባሉ።
በተጨማሪም የዳንኤል ተደጋጋሚ ትንቢቶች ስለ ፍርድ ስለሚተነብዩ በክርስቶስ
ዳግም ምጽአት ሲከናወን (የእግዚአብሔር ድል መደምደሚያ) “እግዚአብሔር ፈራጅ
ነው” የሚል ትርጉም ያለው የዳንኤል ስም ራሱ አግባብነት ያለው ነው። ለዘመናችን
ወቅታዊ ስለሆኑ ጽሑፎች በጥንቃቄ የተሞላ ጥናትና ትኩረት ያስፈልጋቸዋል።
የዳንኤል ትንቢቶች ጥቃቅን በሚመስሉ ነገሮች ሳይቀር የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት
ተግተን መጠበቅ እንዳለብን ያሳስቡናል።
ነብዩ ዳንኤል የመንግስታትን መነሳትና መውደቅ ከዚያም እግዚአብሔርን
ባለመታዘዛቸው የሚከፍሉትን ዋጋ በግልጽ አሳየ። በትንቢታዊ ራዕዮቹ ዳንኤል
የእግዚአብሔርን እቅድና በመጨረሻ የእግዚአብሔርን መንግስት ድል አድራጊነት
አሳየ (ዳንኤል 7:13፣14)።
ለምሳሌ ከክርስቶስ በፊት አምስት መቶ አመታት የተፃፈውን ዳንኤል 2ን ልብ
ይሏል። እነዚህን አራት ሀያላን መንግስታት መነሳትና መውደቅ በትክክል ተነበየ።
እኩሉ ብረት እኩሉ ሸክላ የነበሩትን በዘመናችን የሚገኙትን የአውሮፓ መንግታት
ሳይቀር በትንቢቱ አየ። “ብረቱ ከሸክላው ጋር ተደባልቆ እንዳየሆነ እንዲሁ ከሰው
ዘር ጋር ይደባልቃሉ ግን ብረት ከሸክላ ጋር እንደማይጣበቅ እርስ በእርሳቸው
አይጣበቁም” (ዳንኤል 2:43)።
ይህ ስለ አውሮፓ የሚያስገርም ትንቢት ነው። በመጋባትና በሌላ ሙከራዎች
ሊተባበሩ ቢሞክሩም ስላልተሳካላቸው የአውሮፓ ሀገሮች ሁሉ የራሳቸውን ባህል፣
ህግና ወግ ጠብቀው አሁንም የተለያዩ መንግስታት ሆነው ይገኛሉ። የሶቪየት ህብረትን
መውደቅ እንኳን የማንም መንግስት የስለላ ድርጅት ልተነቢይ አልቻለም። የዳንኤል
ትንቢት ግን የእግዚአብሔርን ነቢያት እንድናምን ሃይለኛ ምክንያት ነው።
በዳንኤል 2 የተነገረላቸው መንግስታት ታሪክ ሁሉ በትንቢቱ መሰረት እየተነሱ
ወደቁ። ቀጥሎ የሚመጣው የእግዚአብሔር መንግስት መሆኑን የሚናገረውን
ትንቢት ለማመን ታዲያ ይህ እንዴት ይረዳናል? (ዳንኤል 2:44)።
ማርቆስ 1:2-5ን ያንብቡ። የመጥምቁ ዮሐንስ አገልግሎት አላማው ምን ነበር?
የመጥምቁ ዮሐንስ አመጣጥ የኢሳያስ ትንቢት እንዲደርስ መሆኑን ማርቆስ ወንጌል ይነግረናል (ኢሳያስ 40:3)። ከልጅነት እስከ ጎልማሳነት የዮሐንስ አስተዳደግ በእግዚአብሔር ላይ በመተማመን የተመሰረተ ነበረ። የዮሐንስን ድምጽ በምድረ በዳ ሰይጣን ሲሰማ በሰብዓዊ ፍጥረት ላይ ያለውን የበላይነት አጣለሁ ብሎ ፈራ (ኤለን ዋይት፣ የዘመናት ምኞት ገፅ 224)። የዮሐንስ አድማጮች ክፋት መጋለጥ ሰይጣንን እንዲርድ (በፍርሃት እንዲንቀጠቀጥ) አደረገው። ሰይጣን በእስራኤል ላይ የነበረው የጠበቀ አያያዝ ስጋት ላይ ወደቀ። መጥምቁ ዮሐንስን ከአኗኗር ዘይቤና በመሲሁ ላይ ካለው ታማኝነቱ ሊያዛባው ቢሞክረም አልተሳካለትም። ማቴዎስ 11:1-6ን ያንብቡ። ሰባኪው በግዞት ሳለ ኢየሱስ ታማኝነቱን (እምነቱን) እንዴት አፀደቀለት?
ሰይጣን ኢየሱስን ፈትኖ ወደ ሃጥያት ሊያስገባው ስላልቻለ እና በምድረ በዳው
ተጋድሎ ስለተሸነፈ እጅግ ተበሳጨ። ከዚያ ዘዴውን ቀየረና የኢየሱስን የአክስት ልጅ
ዮሐንስን በእስር ቤት ውስጥ እንዲገባ አደረገ። ሰይጣን ይህን ያደረገው ዮሐንስን
ለማጥፋትና የመድኃኔ ዓለምን ልብ በሀዘን ለመውጋት ነበር። ነገር ግን ዮሐንስ
ከኢየሱስ የማበረታቻ ቃል ተቀበለ። የነበረበት ቦታ መጥፎ ቢሆንም እና ኢየሱስ
ስልጣን እያለው ለምን በእስር ቤት እንደቆየ ባያስተውልም ዮሐንስ ግን እስከ
መጨረሻው፣ እስከ ሞት ድረስ እንኳን ታማኝ ሆነ።
እኛም እንደ ጥንቱ ነቢያት ንስሀ እንድንገባ እና የእምነትና የክርስቶስን ፍጹም
ጻድቅነት መልእክት እንድናውጅ ተጠርተናል (ራዕይ 14:6-12)። በመጥምቁ
ዮሐንስ እንዳደረገው ሁሉ ሰይጣን የእኛንም የህይወታችንን ተልዕኮ ሊያጠራጥረን
ይሞክራል። በተለይ ነገሮች እንዳሰብነው ሳይሆኑ ሲቀሩ በክፉ ሴትና በደካማ
ሰው አማካኝነት እንደታሰረውና እንደተገደለው ዮሐንስ ህይወታችንን የሚመራው
እግዚአብሔር መሆኑን ካልረሳን ልንጨነቅ አይገባንም። ሰዎች ምንም ቢያደርጉን
በእምነት ከቀረብነው እግዚአብሔር ይመልስልናል። ፈቃዱን ለማድረግ ኃይል
እንደሚሰጠን ቃል ገብቶልናል (የሐዋርያት ሥራ 1:8)። በምንም ሁኔታ ላይ ብንሆን
ክርስትና ባለፈውና ክርስትና በሌለበት በአሁኑ ዘመን ለክርስቶስ መመስከር አለብን።
ዮሐንስ እስር ቤት እንደገባ ሁሉ እርስዎስ መጥፎ ነገር ለምን እንደደረሰቦት
ያላስተዋሉበት ጊዜ አጋጥሞት ያውቃል? ታዲያ በኢየሱስ ያለዎትን
እምነትና መተማመን እንዴት እንዳያዙ ቆዩ?
እግዚአብሔር ነቢያትን በሆነ ጊዜ ለሆነ አላማ ይጠራቸዋል። ለወቅቱ
የሚያስፈልገውን መልዕክት ይዘው ይመጣሉ። በዚህ አውድ 7ኛ ቀን አድቬንቲስቶች
ኤለን ጂ ዋይት ከእንደነዚያ አይነት ነቢያት አንዷ ነች ብለው ያምናሉ። ዘመናዊ
የትንቢት ስጦታ ተሰጥቷታል እንላለን። ከመጽሐፍ ቅዱስ ነቢያት መካከል
ባትመዘገብም በነቢይነት አገልግላለች (ስለዚህ ጉዳይ በትምህርቱ በሚመጣው ቀጣይ
ሃሳብ እንጠቅሳለን)። ኤለን ሃርመን ዋይት የመጀመሪያ መልእክቷን የተቀበለችው
በታኅሳስ ወር በ1844 ዓም ነበር። ጊዜው ሚለራውያን አድቬንቲስቶች በዳንኤል
8:14 በተዘገበው ትንቢት መሠረት ክርስቶስ ዳግም ይመጣል ብለው ከተጠባበቁት
ቀን ጥቂት ሳምንታት ቆይቶ ነው። “እስከ ሁለት ሺህ ሶስት መቶ ማታና ጠዋት ድረስ
ነው፣ ከዚያም በኋላ መቅደሱ ይነፃል።”
ዊሊያም ሚለር ትክክለኛውን ቀን ባይናገርም ተከታዮቹ ግን ጥቅምት 22/
1844 ክርስቶስ ዳግም ይመጣል ብለው ወሰኑ። መፅሀፍ ቅዱስ “መቅደሱ ይነፃል
ያለውን የመምጣቱ ቀን ይሆናል ብለው አመኑ። ይህ እምነት በሰሜን አሜሪካና
በሌላም የዓለም ክፍሎች በሚኖሩ በብዙ ሺህ በሚቆጠሩ ህዝብ ላይ እጅግ ከፍ
ያለ ጉጉት አሳደረ። በሰማይ ከሚገኘው አዳኛቸው ጋር በቅርቡ እንገናኛለን ብለው
አመኑ። ምጽአቱ መቃረቡን አምኖ ሚለር እራሱ የጉጉት ሲቃ ይዞት ነበር። ክርስቶስ
ግን ሳይመጣ ቀረ”። ሚለራያውያን “ታላቁ ተስፋ መቁረጥ” ተብሎ የሚታወቀው
ታሪካዊ ክስተት ደረሰባቸው።
ታዲያ እግዚአብሔር ለኤለን ሃርመን ዋይት የመጀመሪያውን መልዕክት
የገለጠላት ይህን በመሰለ ጊዜ ነበር። በተሳሳተ አተረጓጎም ተመርተው ብሳሳቱና ተስፋ
ቢቆርጡም እንኳን እግዚአብሔር አብሮአቸው እንዳለ በመግለጽ ሊያፅናናቸው
ይህን መልዕክት በእርስዋ በኩል ላከላቸው። ራዕይዋ ከዚህ ምድር ወደ ሰማያዊቷ
ኢየሩሳሌም የሚወስደውን መንገድ ያሳያል። በዚህ ጎዳና ላይ የምጽአቱ አማኞች ወደ
ቅድስት ኢየሩሳሌም ይጓዙ ነበር። “ከፊት ለፊታቸው ሆኖ በሚመራቸው በኢየሱስ
ላይ ዓይኖቻቸውን ከተከሉ ወደ ከተማይቱ በሰላም ይገባሉ” (ኤለን ጂ ዋይት
ትንቢታዊ ስጦታዎች መጽሃፍ 2 ገፅ 31)።
ራዕይዋ ታላቅ የምስራች ነበር። በግርግሩና በተስፋ መቁረጡ መካከል
እግዚአብሔር አዲስ እንቅስቃሴ መፍጠር ጀመረ። አሁንም በመዳን ጎዳና ላይ
እየመራቸው ነበር። ብቻ አይናቸውን በእርሱ ላይ “መትከል” አለባቸው። በግርግር
እና በተስፋ መቁረጥ መካከል ተስፋ መቁረጥ የለባቸውም።
ኤለን ጂ ዋይት የ 17 ዓመት ወጣት ሳለች ለትንቢታዊ አገልግሎት ተጠራች።
በተለይ መጀመሪያ ላይ የሄደችበት መንገድ ቀላል አልነበረም።
ስጦታዋ ቀስ በቀስ ተቀባይነት ቢያገኝም ኤለን ጂ ዋይት የእግዚአብሔር
መልእክተኛ ለመሆን ፈርታ ነበር። የእግዚአብሔር ነቢይ ታላቅ ክብርን የሚያቀዳጅ
ቀላል ስራ ሆኖ አያውቅም። ታዲያ ኤለን ጂ ዋይት የእግዚአብሔርን ጥሪ እሺ ብላ
ለመቀበል እንዴት ቻለች?
በሚቀጥለው ዓርብ እንደምንማረው የኤለን ጂ ዋይትን ሕይወት የሚያንፀባርቁት
የብሉይ ኪዳን ነቢያት የገጠማቸውን ግድድሮሽ እንመለከታለን።