የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

የትንቢት ስጦታ



4ኛ ሩብ ዓመት 2026


መስከረም 16 - 22

1ኛ ትምህርት

Sep 26 - Oct 2




ፈጣሪ ተናገረ



ሰንበት ከሰዓት በኋላ

ለዚህ ሳምንት ጥናት እነዚህን ጥቅሶች ያንብቡ፥ ዘፍ 1:27፣ 28፣ ዘፍ 3:1-8፣ ሉቃስ 15:11-12፣ ዘፍ 3:14-24፣ ዘፀ 19:16-22 እና ዮሐ 10:27-30።


የመታሰቢያ ጥቅስ፡“ከጥንት ጀምሮ እግዚአብሔር በብዙ ዓይነትና በብዙ ጎዳና ለአባቶቻችን በነቢያት ተናግሮ፥ ሁሉን ወራሽ ባደረገው ደግሞም ዓለማትን በፈጠረበት በልጁ በዚህ ዘመን መጨረሻ ለእኛ ተናገረን” (ዕብ 1:1፣2)።

ዘመናዊ ጥበብ በሩቅ ካሉት ዘመዶቻችንና ወዳጆቻችን ጋር እንድንተያይ ይረዳናል። ይህ መልካም ነው። ነገር ግን በአካል ፊት ለፊት መተያየት እንዴት እጅግ በጣም ይሻላል! በአካል ስንገናኝና ሰላምታና መሳሳም ስንቀያየር እንዲያው አንድ የተለየ ነገር ይፈጠራል።

በዚህ ሳምንት ሰዎች የተፈጠሩት ከፈጣሪያቸው ጋር የፊት ለፊት ግንኙነት እንዲኖራቸው ሆነው እንደሆነ እንመለከታለን። ነገር ግን ይህንን የቅርብ ግንኙነት ከብዙ ጊዜ በፊት ኃጢያት አበላሸው (አወደመው)። ከውድ ፍጡራኑ ጋር የነበረውን ይህን ግንኙነት ለማደስ እግዚአብሔር ለእኛ የሚናገርበትን ዘዴ ፈጠረ። በግልጽ የሚታወቁት ዋና መገናኛዎቹ ነቢያት በመባል የሚታወቁት በጥንቃቄ የተመረጡት መልእክተኞቹ ናቸው። እነዚህ ነቢያት አብዛኛውን ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ጽሑፍን ትተዋል፣ ነገር ግን ሁሉም አይደሉም።

የእግዚአብሔር ዋና ዕቅድ ኃጢአት ያበላሸውን የእርሱን ምስል በእኛ ላይ መመለስ (ማደስ) ነው። የደህንነት ዕቅድ ይኸው ነው። ይህ እድሳት ፍፁም የሚሆነው “ጽድቅ የሚኖርባቸው አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር” ሲፈጠሩ ነው (2ኛ ጴጥ 3:13)። እስከዚያ ድረስ አሁንም ቢሆን በነቢያቱ አማካኝነት እግዚአብሔር ይናገረናል። *የዚህን ሳምንት ትምህርት ለመስከረም 23 ሰንበት ለመዘጋጀት ያጥኑ።

መስከረም 17
Sep 27

በኤደን የነበረው ግንኙነት


ዘፍጥረት ምዕራፍ አንድና ምዕራፍ ሁለት የፍጥረትን ታሪክ ይተርካሉ። እግዚአብሔር ውብ ዓለም ፈጠረና የፍጥረት ሁሉ ቁንጮ የሆኑትን አዳምንና ሄዋንን አስቀመጠበት። “በእግዚአብሔር አምሳል ስለ ተፈጠሩ” (ዘፍ 1:27)። በምድር ሁሉ ከተፈጠረው ፍጥረት ሁሉ ይለያሉ። ይህ ስለ እነርሱ የተባለው ነገር ስለ ወፎችም ሆነ ስለ ሌሎች ፍጡራን አልተባለላቸውም። ስለዚህ የተሟላና የተትረፈረፈ ኑሮ እንዲኖሩ፣ በተለያየ መንገድ ፍቅርን እንዲቀበሉና ከእግዚአብሔር ከራሱ ጋር እየተነጋገሩ ከእርሱ ጋር እንዲራመዱ ሆነው ተፈጠሩ።

ደግሞ “ሰው ብቻውን ይኖር ዘንድ መልካም አይደለም” በማለት ሄዋንን ለአዳም እንደፈጠረለት ዘፍ 2:18-23 ላይ እናነባለን። ከመጀመሪያም ሰዎች ማህበራዊ ኑሮ እንዲኖሩ ተፈጠሩ። ብቸኝነት ጎጂ ሲሆን ሰዎች ከሰዎች ጋር ሲገናኙ አካላዊና አእምሮአዊ ደህንነት እንደሚያገኙ የህብረተሰብ ሳይንስ አጥኚዎች (sociologists) ያስተምራሉ።

ስለዚህ ሄዋን ከተፈጠረች በኋላ አዳም “ይህች አጥንት ከአጥንቴ ስጋም ከስጋዬም ናት፣ እርሷም ከወንድ ተገኝታለችና ሴት ትባል” ማለቱ አያስገርምም (ዘፍ 2:23)። የተሟላ ግንኙነትና መግባባት እንዲኖራቸው ተደርጎ በመጀመሪያ በአንድ ወንድና በአንዲት ሴት መካከል የተመሠረተው ታዋቂው የጋብቻ ተቋም እግዚአብሔር ለሰዎች የሰጠው የመጀመሪያው ህብረሰባዊ ተቋም ነው። ስለዚህ ሰይጣን ለማጥፋት ከሚፈልጋቸው አንዱና ዋነኛው ነገር የተመሰረተውን የቤተሰብ ተቋም መሆኑ ሊያስገርም አይገባም። ዘፍ 1:27፣28፣ ዘፍ 2:15-17 እና ዘፍ 3:9ን ያንብቡ። በኤደን ገነት በእግዚአብሔር እና በሰዎች መካከል ምን አይነት ግንኙነት ነበር?



አዳምና ሄዋን ከእግዚአብሔር ጋር ፊት ለፊት ይገናኙ ነበር። አስተዋይ ፍጡራን ስለ ነበሩ ከእግዚአብሔር ጋር ተገናኝተው መመሪያውን ያስተውሉ ነበር። ለእግዚአብሔር ግሩም ገነት መጋቢዎች (ተጠንቃቂዎች) ስለ ነበሩ ህያው ለሆኑ እፅዋትና እንስሳት ሲጠነቀቁ እውቀታቸውና ችሎታቸው እየዳበረ ሄደ። “ቀኑ በመሸ ጊዜ” ከእግዚአብሔር ጋር የተለየ ጊዜ ያሳልፉ ነበር (ዘፍ 3:8)። በእግዚአብሔር የፈጣሪነት ስራ የተለየ ቦታ ያለው ሰንበት በተለይ በእግዚአብሔርና በልጆቹ መካከል የተለየ የመገናኛ ቀን ነበረ (ዘፍ 2:2፣3 ዘፀ 20:8-11)። በዚህች ቀን የመጀመሪያ ወላጆቻችን የእግዚአብሔርን ጥንቃቄና ፍቅር በተለየ ሁኔታ ይለማመዱ (ይቀበሉ) ነበር። ዛሬ ከኤደን በብዙ ሺህ ዓመታት ርቀን ለምንገኘው ለእኛ ከኃጢአት በፊት የነበረውን ሁኔታ ለመገመት ያዳግተናል። ቢሆንም ዛሬ እንኳን ተፈጥሮ እግዚአብሔር ዓለምን መጀመሪያ ሲፈጥረው ወደ ነበረው የዓለም ሁኔታ ዙሮ ያመላክታል?

መስከረም 18
Sep 28

ከእግዚአብሔር መደበቅ


እግዚአብሔር ፍቅር ስለሆነ (1ኛ ዮሕ 4:8) “ሮቦት” ሰው አልፈጠረም። ፍቅር ምርጫን ያካትታል። አዳምና ሄዋን ማፍቀር እንዲችሉ ስለተፈለገ ከምርጫ ፈቃድ ጋር ተፈጠሩ። አለዚያ ፍቅርን፣ እውነተኛ ፍቅርን፣ መስጠት አይችሉም ነበር።

ስለዚህ አዳምና ሄዋን ፈጣሪያቸውን የመታዘዝ ወይም ያለመታዘዝ ምርጫ ነበራቸው። የዚህ የነጻ ምርጫ እውነታ ክፉና በጎ ከምታስታውቀው ዛፍ ፍሬ እንዳይበሉ በተሰጣቸው ትዕዛዝ ውስጥ ይገኛል (ዘፍ 2:15-17ን ይመልከቱ)። መጀመሪያውኑ የነፃ ምርጫ ካልነበራቸው አትብሉ ብሎ ለምን ያስጠነቀቃቸዋል?

“የመጀመሪያ ወላጆቻችን ንጹሃንና ቅዱሳን ሆነው ቢፈጠሩም ያለመሳሳት ችሎታ የሌላቸው ሆነው አልተፈጠሩም። ነጻ የሞራል ወኪሎች አድርጎ ፈጠራቸው። የባህሪውን ጥበብና ቸርነት የሚያስተውሉ ፍጡራን ነበሩ። ፍትህን የሚጠባበቅ መሆኑንም ያውቁ ነበር። ለመታዘዝ ወይም ላለመታዘዝ ሙሉ ነጻነት ነበራቸው። ከእግዚአብሔር እና ከቅዱሳን መላእክት ጋር ግንኙነት ነበራቸው። የምርጫ ነፃነት ከሌላቸው መታዘዛቸው የውዴታ ሳይሆን የግድ ይሆን ነበር (ኤለን.ጂ ዋይት፣ አበውና ነቢያት ገፅ 48፣49)። ትእዛዙን ከጣሱ በኋላ አዳምና ሔዋን ለምን ከፈጣሪያቸው ለመደበቅ ሞከሩ? (ዘፍ 3:1-8ን ከኤርምያስ 23:34 እና ከዕብራውያን 4:13 ጋር ያነፃፅሩ)።



ዘፍጥረት ምዕራፍ 3 የአዳምንና የሔዋንን አስከፊ ውድቀት ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። በሔዋን እና በእባቡ (በሰይጣን) መካከል ከተከሰተው ታሪካዊ ውይይት በኋላ የመጀመሪያ ወላጆቻችን ከተከለከሉት “ክፉንና በጎን ከምታሳውቀው ዛፍ ፍሬ” እንዲበሉ ተፈተኑ። ሰይጣን የቃላትን፣ የስሜትንና የመጎምጀትን ኃይላት መሣሪያ አድርጎ ተጠቅሞ ሄዋንን እንድትበላ አሳመናት። እርሷም በተራዋ አዳምን አሳመነችና ሁለቱም የእግዚአብሔርን ትዕዛዝ ጣሱ። ሔዋን ዛፉ “ለመብላት ያማረ፣ ለአይንም እንደሚያስጎመጅ፣ ለጥበብም መልካም እንደሆነ አየች” (ዘፍ 3:6)። “እንደ እግዚአብሔር መልካምንና ክፉን የምታውቁ ትሆናላችሁ” የሚለውን የሰይጣንን ተስፋ ለመቋቋም የማይቻል መስሎ ታየ (ዘፍ 3:5)።

እንደ እውነቱ ከሆነ የሰይጣን ስብከት በሀሰት (በስህተት) የተሞላ ነበር። ሰይጣን አለመታዘዛቸው የሚያስከፍለውን ዋጋ ደበቃቸው። የእግዚአብሔርን ትእዛዝ እንደ ጣሱ ወዲያው “የሁለቱም ዓይኖች ተከፈቱ።” “እራቁታቸውን” መሆናቸውን አዩ። የፈጣሪያቸውን “አምሳል” የሚያሳየው “የብርሃንና የክብር ሸማ ከላያቸው ተገፈፈ (መዝ 104:1፣2)። እግዚአብሔር የሰጣቸውን ጸጋ መልበስ አቆሙ (ከእግዚአብሔር መደበቅ የሚቻል ይመስል)። አዳምና ሄዋን ከፈጣሪያቸው መደበቃቸው አያስገርምም። የህሊና ወቀሳ ሲሰማን ከእግዚአብሔር ፊት እንኮበልላለን። ኃጢአት ከሰሩ በኋላ ከእግዚአብሔር ለመደበቅ የፈለጉበት የእርስዎስ የሀፍረት የኑሮ ተሞክሮ (ልምምድ) ምን ነበር?

መስከረም 19
Sep 29

እግዚአብሔር ሰብዓዊን ፍጡር ፈለገ


እግዚአብሔር የወደቁትን ልጆቹን ለመፈልግ የመጀመሪያውን እርምጃ ሲወስድ በዘፍጥረት 3:9፣10 እንመለከታለን። እግዚአብሔር አዳምና ሄዋን እንደ ነበሩ ያውቅ ስለነበረ “የት ነህ” የሚለው ጥያቄ መልስ ለማግኘት የተጠየቀ ጥያቄ አልነበረም። ምን እንዳደረጉም ያውቅ ነበር። በመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት እና በእግዚአብሔር መካከል የነበረውን ግንኙነት ኃጢያት አቋረጠው። እግዚአብሔር በቅጽበት የወሰደው እርምጃ ከልጆቹ ጋር ግንኙነትን እንደገና ለመመስረት፣ ከእነርሱ ጋር ለመገናኘትና ተስፋ ቆርጠው ሳሉ በልባቸው ተስፋ ለማሳደር ነበር። እንዲያውም ኳራ የሚለው የዕብራይስጥ አንቀጽ “ጠራ” የሚለው በዘፍጥረት 3:9 የተጠቀሰው አብዛኛውን ጊዜ የሚውለው እግዚአብሔር ከሕዝቡ ጋር ግንኙነትን ለመመስረት የሚወስደውን እርምጃ ለመግልጽ ነው። ሉቃስ 15:11-32ን ያንብቡ። ይህ ምሳሌ በዘፍጥረት 3:9፣10 የሆነውን ጉዳይ እንዴት ያንፀባርቃል?



እግዚአብሔር አዳምንና ሄዋንን ፍለጋ መሄዱ ቅድመ ሁኔታ የማይጠብቀውን የእግዚአብሔርን ፍቅር ያሳያል። እግዚአብሔር በእኛ ላይ ተስፋ አይቆርጥም (ሉቃስ ምዕራፍ 15ን ይመልከቱ)። ስንደበቅ እንኳን አይገቡ ገብቶ ግንኙነቱን እንደገና ለመመስረት ይጥራል። ክርስቶስ ከመሰቀሉ በፊት ሶስት ጊዜ ሲክደው ጴጥሮስን “ ዘወር ብሎ አየው” (ሉቃስ 22:61)። ያለ ቃል እንኳን ለጴጥሮስ “ተናግሮ” ወደ ከዳው ወዳጁ ለመድረስ ፈለገ።

በዘፍጥረት 3:11-14 ላይ ኃጢአት እንዴት የአዳምንና የሔዋንን ግንኙነት በድንገት እንደቀየር ልብ በሉ። የየራሳቸውን ኃጢአት በመናዘዝ ፈንታ እርስ በእርሳቸው መወነጃጀል ጀመሩ። አዳም ሄዋንን ሲወነጅል በተዘዋዋሪ እግዚአብሔርን መወንጀሉ ነው። ምክንያቱም የሰጠው እርሱ ነበረና። “ከእኔ ጋር እንድትሆን የሰጠኸኝ ሴት እርሷ ከዛፉ ሰጠችኝና በላሁ” (ዘፍ 3:12)። ሔዋን ደግሞ በበኩሏ ላለመታዘዝዋ እባቡን ወንጀለች። “እባብ አሳሳተኝና በላሁ”(ዘፍ 3:13) ስትል አመካኘች።ስለ መሳሳታቸው ሲጠየቁ ሁለቱም ላደረጉት ነገር ሃላፊነትን አልተቀበሉም። አሁንም በዚህ ጉዳይ ከስድስት ሺህ አመታት በኋላ ብዙም ለውጥ የለም።

ኃጢአት የሰው ዘርን በሙሉ መበከሉ የማይካድ ነገር ነው። መልካም ለማድረግ እየፈለገ ተቃራኒውን ሲያደርግ ጳውሎስ የገጠመውን ትግል ሲዘረዝር በሮሜ 7:15-24 እንዲህ ይላል፦ “የማደርገውን አላውቅምና የምጠላውን ያንን አደርጋለሁና ዳሩ ግን የምወደውን እርሱን አላደርግም።” በዚህ የማይስማማ ማን ነው?

ጳውሎስ የተናገረው በጣም ጥልቅ ነው። ማድረግ እንደማይገባን የምናውቀውን ነገር የምናደርግ ሁላችንም ደካሞች ሰዎች ነን። ይህ እውነታ ያልደረሰበት ማን ነው?

ጳውሎስ ብቸኛው ተስፋችን “በኢየሱስ ክርስቶስ በጌታችን” ነጻ መውጣት ነው ይላል (ሮሜ 7:25)። በራሱ አምሳል ቀርጾን ኃጢያት ካደረሰው ከባድ ውድመት ሊያወጣን ወደሚችል ወደ ኢየሱስ ሊመራን እግዚአብሔር እኛን መፈለጉን የሚቀጠልበት ምክንያት ይህ ነው።

መስከረም 20
Sep 30

ከአትክልቱ ቦታ ተባረሩ


የአዳምና የሔዋን ኃጢያት ካስከተላቸው እጅግ አስከፊ ከሆኑት ዋና ውጤቶች አንዱ ከእግዚአብሔር መለየት ነበር። ከአትክልት ቦታው ከመባረራቸውም በላይ ከዚያ በኋላ ከእግዚአብሔር ጋር ፊት ለፊት መነጋገራቸው ተቋርጠ። ስለዚህ አስቸጋሪ ልምምድ ነቢዩ ኢሳይያስ እነዚህን የማይረሱ ቃላት ጻፈ፦ “በደላችሁ በእናንተና በአምላካችሁ መካከል ለይታለች፣ እንዳይሰማም ሃጥያታችሁ ፊቱን ከእናንተ ስውሮታል (ኢሳያስ 59:2)።

እንደ እውነቱ ከሆነ አዳምና ሄዋን አሁንም የእግዚአብሔር ልጆች ናቸው። ነገር ግን ከኃጢአት ውጤት ማምለጥ ስለማይችሉ ኤደንን ለቀው መሄድ ነበረባቸው። ካለመታዘዛቸው በኋላ ሁሉም ነገር ተቀየረ። ኃጥያት በብዙ መንገዶች ሰብአዊ ፍጡርን ቀይሯል (ዘፍጥረት 3:14- 24ን ይመልከቱ)። ነገር ግን ከእግዚአብሔር ጋር የነበረንን ግንኙነት በተለየ መንገድ የቀየረው እንዴት ነው? (ደግሞ ዘጸአት 19:16-22ን ይመልከቱ)።



ኃጢአት መገመት በማንችላቸው መንገዶች የሰውን ሕይወት ሙሉ በሙሉ ቀይሮታል። ምክንያቱም እኛ የምናውቀው የኃጢአትን ዓለም ብቻ ነው። ከኃጢአት የተነሳ ምድር “ስለተረገመች” እሾህንና አሜኬላን ማብቀል ነበረባት። ሰው መሰቃየት እና “በፊቱ ወዝ እንጀራውን መብላት” ነበረበት። በመጨረሻም መሞትና ወደ መሬት መመለስ ሆነበት። ከሃጢያት ማሳሰቢያዎች ሁሉ እጅግ ሃይለኛው ሞት ነው። ወዲያውም በኃጢአት ምክንያት ከእግዚአብሔር ጋር ፊት ለፊት የመነጋገር መብታችንን ተቀማን።

ቢሆንም ኃጢአት ያደረሰውን ጥፋት ለማረም መፍትሄ የሚሆን ተስፋ ተሰጣቸው። የመጀመሪያ ወላጆቻችን እግዚአብሔርን በቀጥታ ማየትና መስማት ቢከለከሉም ለጊዜውና ለወደፊቱ የሚሆን ተስፋ ይዘው ኤደንን ለቀው ወጡ። እግዚአብሔር የመጀመሪያውን እርምጃ በመውሰድ የመታደግ እቅዱን አስረዳቸው። የሆነው ሁሉ እንዳለ ሆኖ “የመጀመሪያው የወንጌል ተስፋ” የተባለው ዘፍጥረት 3:15 ለእነርሱና ለእኛ በተስፋ የታጨቀ ነበር። የተስፋው መድህን ከሃጥያት ጋር ጠላትነት ፈጥሮ ለሰው ዘር የወደፊት መዳን ተስፋን አስጨበጠ። የአትክልት ቦታውን ከመልቀቃቸው በፊት ለአዳም እና ለሄዋን እግዚአብሔር ያለበሳቸው ልብስ ለወደፊት መዳናቸው ምሳሌያዊ ነበር። ለወደፊት በሚሆነው በኢየሱስ ሞትና ትንሣኤ አማካኝነት ከእግዚአብሔር ጋር የነበረው ግንኙነት መታደስ (መመለስ) ነበረበት (ዮሐ 14:1-3)። ስህተት ከሰሩ በኋላ ምን ተሰማዎት? የህሊና ወቀሳ? ሀፍረት? እራስን መፀየፍ? ውጤቱስ ምን ነበር? በእግዚአብሔር ላይ ያለዎት እምነትና የወንጌሉ ተስፋ እምነትዎን በጭራሽ እንዳይተው እንዴት ረዳዎት?

መስከረም 21
Oct 1

የእግዚአብሔር አፈ-ንጉሶች


የእግዚአብሔር አፈ-ንጉሶች (አፈ-ቀላጢዎች አፈ-ቀላጢዎች) ኃጥያት ከገባ በኋላ እግዚአብሔር ለሰው ዘር እንዴት እንደተናገረ (እንደሚናገር) የሚቀጥሉት ጥቅሶች እንዴት ያስረዳሉ? እነዚህን ጥቅሶች ያንብቡ (ዕብ 1:1-2፣ ሮሜ 19:20፣ ዘሁ 12:6፣ 2ኛ ጢሞ 3:16፣17፣ዮሐ 14:7-9፣ ዮሐ 10:27-30)



ኃጢአት ቢኖርም እንኳን እግዚአብሔር ከወደቁት ሰብአዊያን ጋር በተለያዩ መንገዶች መነጋገሩን ቀጠለ። እግዚአብሔር ራሱን ከሚገልጽበት መንገድ አንዱ ተፈጥሮ ነው። ተፈጥሮ ግሩም የሆነውን ስራውን ለመግለጽ ኃይለኛ መሳሪያ ነው። ሳይንቲስቶች በዩኒቨርስ አስገራሚነትና “ቀላል” የተባለችው ህያው ፍጥረት ሳትቀር የተወሳሰበች በመሆኗ እጅግ ይደነቃሉ። ተፈጥሮ ደግሞ ኃጢአት ያስከፈለውን ከባድ ዋጋ ታሳያለች። ዋናው ግልጽ ማስረጃ ህያው የሆነ ፍጡር ሁሉ ሟች መሆኑ ነው።

እግዚአብሔር ለሰብዓውያን የሚናገርበት ሌላኛው መንገድ ደግሞ ቃል-አቃባይ (አፈ-ንጉስ) አድርጎ በመረጣቸው በነቢያት በኩል ነው። ለምሳሌ እግዚአብሔር ፈቃዱን ለእርሱ ህዝብ ለመግለጥ ለኖህ፣ ለአብርሃም፣ ለሙሴና ለዳንኤል በመናገር ለሕዝቡ ያለውን ፈቃድ ገለጸ። የእግዚአብሔር ትንቢታዊ መልእክቶች ዋናው ፍሬ ሀሳብ እርሱ አሁንም ልጆቹን እንዳልረሳና ከእነርሱ ጋር እንደሆነ ለማሳሰብ ነው። ምንም እንኳን አንዳንዶቹ ነቢያት ዛሬ ቅዱስ ቃል ሆኖ የመጣልንን ጽሑፍ ቢጽፉም ሌሎቹ ደግሞ ከመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት አንዱንም አልፃፉም።

ቢሆንም አብዛኞቹ የነቢያት ቃላት በቅዱሳት መጻሕፍት አማካይነት ተላልፈዋል (2ኛ ጢሞ 3:16፣17)። መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔርን እራሱን ይገልፃል። ማንነቱን፣ ወሰን የሌለውን ፍቅሩንና ህይወታችንን እንዴት እንደሚመራ የምንረዳው በቃሉ አማካኝነት ነው።

በተጨማሪም በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ማንነታችንን፣ ከየት እንደመጣን እና ወዴት እንደምንሄድ እንረዳለን። እግዚአብሔር ለህይወታችን ያለውን ዕቅድም የምንረዳው በዚያው በቃሉ አማካኝነት ነው።

ነገር ግን ከሁሉም በበለጠ ግልጽ በሆነ መንገድ የሚናገረን ራሱ በመጽሐፍ ቅዱስ በተነገረለት በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ነው። እግዚአብሔር አዳምንና ሄዋንን ለማግኘት ፍለጋ እንደ ሄደ ሁሉ ክርስቶስም “የጠፋውን ሊፈልግና ሊያድን መጣ” (ሉቃስ 19:10)። ኢየሱስ “እኔን ያየ አብን አይቷል” አለ (ዮሐ 14:9)። ኢየሱስ በህይወቱ፣ በሞቱና በትንሣኤው ለአዳም እና ለሄዋን በኤደን የሰጠውን ተስፋ አሟላ። በእርሱ በኩል የዘላለም ህይወት እናገኝ ዘንድ መጣና በእኛ ፋንታ ሞተልን።

ኢየሱስ ወደ ሰማይ ካረገ በኋላ መንፈስ ቅዱስ እኛን “ወደ እውነት ሁሉ መምራቱንና የሚመጣውን ሁሉ ለእኛ መናገሩን” ይቀጥላል (ዮሐ 16:13)። የኢየሱስ ፍቅሩ፣ ባህሪውና መስዋዕትነቱ የእግዚአብሔር አብን ማንነት ለእኛ በመግለጡ ምን ያህል መጽናናት ያገኛሉ?

መስከረም 22
Oct 2

ኤለን ኤለን. ጂ ዋይት


የእግዚአብሔር ከሰዎች ጋር ግንኙነት መፍጠር በመጽሐፍ ቅዱስ ጊዜ ብቻ የተወሰነ አይደለም። በሚቀጥሉት ሳምንታት እንደምንመለከተው እግዚአብሔር ሳያቋርጥ ክርስቶስ ዳግም እስኪመለስ ድረስ ለሰው ዘር ይናገራል።

ኤለን ጉልድ ሃርሞን (ዋይት) እና መንትያ እህቷ ኤልሳቤት እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ህዳር 26 ቀን 1827 ዓም ጎርሃም በምትባል ከተማ በሜይን ጠቅላይ ግዛት ተወለዱ። ኢዮንስ ሃርሞንና ሮበርት ለተባሉት ወላጆቻቸው ከነበሩአቸው 8 ልጆች መካከል የመጨረሻዎቹ ነበሩ። ከጥቂት ዓመታት በኋላ ሮበርት ሃርሞን የባርኔጣ ንግዱን ለማዳበር ፈልጎ ቤተሰቡን ፖርትላንድ ወደ ምትባል በሜይን ጠቅላይ ግዛት ወደምትገኝ ከተማ ይዞ ሄደ። ኤለን በዘጠኝ አመቷ አካላዊ፣ ስሜታዊና ህብረተሰባዊ ተፅዕኖ ያስከተለ የአካል ጉዳት ደረሰባት።

ከቤቱ አጠገብ በነበረ መናፈሻ ቦታ (ፓርክ) ሳለች አንዲት የተናደደች የትምህርት ቤት ጓደኛዋ ድንጋይ ወርውራ ፊቷን መታችት። ኤለን ለብዙ ሳምንታት ራሷን ስታ ሰነበተች። ይህ አደጋ ትምህርቷን እንድታቋርጥ ከማስገደዱም በላይ የእድሜ ልክ የጤና እክል ተወባት። ይህ አደጋ በኤለን ላይ ስለ መልኳ ያለመመቸትን ስሜት አሳደረባት። ከሰዎች ጋር የነበራትን ማህበራዊ ግንኙነት ቀነሰባት።

ወጣቷ ኤለን ስለ መንፈሳዊ መዳረሻዋ ማሰብ የጀመረችው በዚህ እርግጠኝነት በሌለበት አውድ ውስጥ ሆና ነበር። እግዚአብሔርን ትፈራ ስለነበር ለሰማይ ብቁ አይደለሁም የሚል ስሜት አደረባት። የሃርሞን ቤተስብ ስለ ክርስቶስ ዳግም መምጣት የሚያስተምረውን ሚለራዊ መልዕክት ሲቀበል ደግሞ ፍርሃቷ እየጨመረ ሄደ። በ1842 ዓም በጥልቅ ተጠምቃ የሜቶዲስት ቤተ ክርስቲያን አባል ከሆነች በኋላ እንኳን የእግዚአብሔር ፍቅር ይገባኛል ብላ አላመነችም ነበር። “ለዘላለም ጠፍቻለሁ” ብላ ታምን ነበር (የኤለን ዋይት የሕይወት ታሪክ ገፅ 29፣ 20-31ን ይመልከቱ)።

በእንዲህ አይነት አስጨናቂ አሳብ ውስጥ እያለች ስለ እግዚአብሔር ያላትን ሀሳብ ለመለወጥ የረዳትን ሁለት ህልሞች አየች። ነገር ግን የእግዚአብሔርን ጸጋና ፍቅር ማስተዋል የጀመረችውና የተሰማት ሊቫይ ስቶክተን የተባለ የሜቶዲስት ሰባኪን ከተዋወቀች በኋላ ነበር። በጨነቃት ጊዜ እግዚአብሔር እንደተናገራት ተሰማት። በኋላ “አሁን እምነት ልቤን ማረከው። ለእግዚአብሔር መግለጫ የሌለው ፍቅር ተሰማኝ። ለሃጢያቴ ይቅርታ እንደተቀበልኩ መንፈሱ መሰከረልኝ። ስለ አብ ያለኝ አስተያየት ተቀየረ። አሁን ዓይናችሁን ጨፍናችሁ በግድ ታዘዙልኝ የሚል ጨካኝ ገዢ ሳይሆን ቸርና ገር ወላጅ ሆኖ ታየኝ። ጥልቅ በሆነ ፍቅር ከልቤ ወደድኩት” ብላ ጽፋለች (የኤለን ዋይት የሕይወት ታሪክ ገፅ 39)።

ዋይት “የሙታንን ሁኔታ” አስተምህሮም አስተዋለች። በገሃነም ለዘላለም ሲቃጠሉ መኖር እንደሌለ ቀስ በቀስ እየገባት ሄደ። በተከታታዮቹ ሳምንታት እንደምናጠነው ኤለን ዋይት ኢየሱስን በሙሉ ልቧ በጥልቅ ከመውደዱም በላይ እድሜ ልኳን አገለገለችው።




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA Union SSL