የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

የትንቢት ስጦታ



4ኛ ሩብ ዓመት 2026



መስከረም፣ ጥቅምት፣ ኅዳር፣ ታኅሣሥ 2019 ዓ.ም.

መደበኛ እትም

Sep 26 - Dec 25




አዘጋጅ: ኤለን ጂ ዋይት ጽሑፎች ባለአደራ ተቋም (ድርጅት)

ትርጉም: እንግዳው ብርሃኑ



© 2026 የሰባተኛው ቀን አድቬንቲስት® አጠቃላይ ጉባኤ። ሁሉም መብቶች በሕግ የተጠበቁ ናቸው። ከሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት® አጠቃላይ ጉባኤ በቅድሚያ የጽሑፍ ፍቃድ ሳይገኝ በማንኛውም ሰው ወይም አካል የትኛውም የጎልማሶች የሰንበት ትምህርት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ (መደበኛ እትም) ክፍል ሊስተካከል፣ ሊቀየር፣ ሊሻሻል፣ ሊተረጎም፣ ሊባዛ ወይም ሊታተም አይችልም። የሰባተኛው ቀን አድቬንቲስቶች® አጠቃላይ ጉባኤ ክፍል ቢሮዎች በልዩ መመሪያዎች የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያን ለመተርጎም ሥልጣን ተሰጥቷቸዋል። የእነዚህ ትርጉሞች የቅጂ መብት እና ህትመታቸው የጠቅላላ ጉባኤው ሆነው ይቆያሉ። «የሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት» እና «አድቬንቲስት» የሚሉት ቃላቶች እና የነበልባል አርማው የሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት® የተመዘገቡ አጠቃላይ የመለያ ምልክቶች ናቸው፤ እናም ከጠቅላላ ጉባኤው ያለ ቅድመ ፈቃድ ጥቅም ላይ ሊውሉ አይችሉም።

የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ የተዘጋጀው በሰባተኛ ቀን አድቬንቲስቶች ጠቅላላ ጉባኤ የጎልማሶች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ ቢሮ ነው። የመምሪያዎቹ ዝግጅት የተደረገው፣ የጠቅላላ ጉባኤ አስተዳደር ኮሚቴ (ADCOM) ንዑስ ኮሚቴና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያዎች አሳታሚ በሆነው የሰንበት ትምህርት ህትመቶች ቦርድ አጠቃላይ አመራር ነው። የታተመው መምሪያ የጸሐፊውን(ዎችን) ሃሳብ ብቻ የሚወክል ሳይሆን፣ ነገር ግን የዓለም አቀፍ የግምገማ ኮሚቴ ግብአት እና የሰንበት ትምህርት ህትመቶች ቦርድን ይሁንታ የሚያንፀባርቅ ነው።

4ኛው ሩብ ዓመት

ከመስከረም 16-ታኅሳስ 16/2019 ዓ ም

መደበኛ እትም



በኢትዮጵያ አድቬንቲስት ማተሚያ ቤት ታተመ



አዳምና ሄዋን ከእግዚአብሔር ጋር የነበራቸውን ግንኙነት ኃጢአት ሲያወድመው እግዚአብሔር ራሳቸውን ያጥፉ ብሎ እጁን ታጥቦ አልተዋቸውም። ሁለቱንም “የት ናችሁ?” እያለ ሊፈልጋቸው መጣ (ዘፍ 3:9)። ዓለምን ከኃጢአቷ ስለሚያድነው አዳኝ መወለድ ትንቢት ተናገረ (ዘፍ 3:15)። ከውድቀት በኋላ በዚያው በኤደን ውስጥ ትንቢት ኢየሱስን ከፍ ከፍ በማድረግ ኃጢአተኞችን ብቸኛ ተስፋቸው ወደ ሆነው ወደ እርሱ አመላከታቸው።

በዚህ ሩብ ዓመት የትንቢትን ስጦታ እናጠናለን። ይህ እግዚአብሔር በጥበቡ ለሰዎች ፈቃዱንና መንገዱን ለመግለጥ ለወደቀው የሰው ዘር ያዘጋጀው መንገድ ነው። ይህን ያደረገው ከርሱ ጋር ፊት ለፊት ለመነጋገር ስላልቻሉ ነበር። ይህ የተለየ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ በ1ኛ ቆሮንቶስ 12፣ በ1ኛ ቆሮንቶስ 14፣ በኤፌሶን 4 እና በሮሜ 12 ላይ በሚገባ (በገሃድ) ተቀምጧል። መንፈስ ቅዱስ “እርሱ እንደሚፈቅድ ለእያንዳንዱ ለብቻው በማካፈል” (1ኛ ቆሮንቶስ 12:11) ይህንን እና ሌሎችንም መንፈሳዊ ስጦታዎች የሚስጥ ታላቁ አቀባይ ነው። እግዚአብሔር ከውድቀት በኋላ በኤደን እንዳደረገው ሁሉ የመንፈስ ስጦታ የተሰጣቸው ቃል አቀባዮችም ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ግንኙነት ለመመለስ እና ለማደስ በዘመናት ሁሉ መንፈሳዊ መልዕክቶችን ሲያውጁ ኖረዋል።

እግዚአብሔር ነቢያትን እንዴት እንደሚጠራና እውነተኝነታቸውን (ሀቀኝነታቸውን) እንዴት እንደሚፈትን (እንደሚመረምር) እንማራለን። በብሉይ ኪዳንና በአዲስ ኪዳን ነቢያት መካከል ተመሳሳይነትና ልዩነት እንመለከታለን። ራእይና መገለጥ በህይወታቸው ላይ የነበረውን ስራም ለማስተዋል እንሞክራለን። አንዳንድ ነቢያት ሲናገሩ ሌሎቹ ደግሞ ጻፉ፣ የቀሩትም ደግሞ ሁለቱንም አደረጉ (ተናገሩም፣ ጻፉም)። እነዚህንና ሌሎችንም መለኮታዊ የመገናኛ ዘዴዎችን እና ተጽዕኖአቸውን፣ እንዲሁም እነዚህ ነቢያት ያመጡአቸውን በመታዘዝ የሚገኙ በረከቶች እንመለከታለን።

እግዚአብሔር የትንቢትን ስጦታ ለአምስት ወሳኝ ዓላማዎች ይጠቀመዋል፦ (1) ለወደቀው የሰው ዘር ራሱን፣ እውነቱንና ፈቃዱን ለመግለጥ፣ (2) ስለ ወሳኝ ክስተቶችና ድርጊቶች ምክርና ማስተዋል ለመስጠት፣ (3) የክርስቶስን አካል፣ ቤተ ክርስቲያንን፣ ለተልኮዋ ለማስታጠቅ (ለማዘጋጀት)፣ (4) ለተከታዮቹ መንፈሳዊ ማደፋፈሪያ ለመስጠት፣ (5) ኃጢአተኞችን ቀስቅሶ ወደ ንስሐ ለመጥራት። በተጨማሪም የትንቢት መንፈስ በዘመን መጨረሻ ላይ የምትገኘው የቅሬታዋ ቤተ ክርስቲያን ካሏት ከሁለቱ ልዩ መለዮቿ አንዱ ነው (ራዕይ 12:7: ራዕይ 19:10)።

እግዚአብሔር የጠፋውን የሰው ዘር ወደ ቤቱ ለመምራት ግድ ስለሚለው በዘመኑ መጨረሻ ላይ መንፈስ ቅዱስን ያወርዳል (ኢዩኤል 2:28-31)። የሰባተኛ ቀን አድቬንቲስቶች፣ ከሌሎች ጋር በመሆን፣ የቤተ ክርስቲያኗ መስራች የሆነችው ኤለን ጂ ዋይት ዘመናዊ የትንቢት መንፈስ ስጦታ ተሰጥቷታል ብለው የሚያምኑበት በቂ (ጥሩ) ምክንያት አሏቸው።

የትንቢትን ስጦታ ከቃሉ ጋር ከማጥናታችን በተጨማሪ ዓርብ ኤለን ጂ ዋይት ስለ ትንቢታዊ አገልግሎት ያላትን አስተያየት የምንመለከተው ለዚህ ነው። ቤተ ክርስቲያናችን ግሩም ስጦታ ተቀብላለች። ታዲያ እንዴት ነው የምንጠቀምበት?

ሲጀመር ጀምሮ (ከህጻንነታችን ጀምሮ) ሲነገረን ለመስማት እንድንችል ሆነን ነው የተፈጠርነው። ታድያ የእግዚአብሔር ነቢያት የሚነግሩንን ነገር መስማት ምንኛ ጠቃሚ ነው!

ይህ የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት የተዘጋጀው ሲሊቨር እስፕሪንግ፣ ሜሪላንድ፣ ዩናይትድ ስቴትስ በሚገኘው የኤለን ጂ ዋይት ጽሑፎች ባለ አደራ ተቋም አገልግሎት ቡድን ነው።

ድርጅቱ (ተቋሙ) የኤለን ጂ ዋይትን ትንቢታዊ አገልግሎት እና ጽሑፎቿን በማካፈል የሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተ ክርስቲያን ኢየሱስ ክርስቶስንና ቃሉን ከፍ ከፍ ለማድረግ የምታደርገውን ተልዕኮ (ሚሽን) ይደግፋል።




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA Union SSL