የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

የትንቢት ስጦታ



4ኛ ሩብ ዓመት 2026


ኅዳር 26 - ታኅሣሥ 2

11ኛ ትምህርት

Dec 5 - 11




በወሳኝ ጊዜያት ትንቢታዊ መገለጦች



ሰንበት ከሰዓት በኋላ

ለዚህ ሳምንት ጥናት እነዚህን ጥቅሶች ያንብቡ። 2ኛ ጴጥ 2፡5, መሳ 4፡4-16, 1ኛ ነገስት 18፡21,38,39, ኢሳ 59፡1-4, ነህ 9፡30, ራዕይ 1፡1-3።


የመታሰቢያ ጥቅስ፡”በእውነት ጌታ እግዚአብሔር ምሥጢሩን ለባሪያዎቹ ለነቢያት ካልነገረ በቀር ምንም አያደርግም” (አሞጽ 3፡7)።

ከውድቀት በኋላ ሰው በኢየሱስ በኩል የሚገኘውን የዘላለም ህይወት በመሻት ፋንታ ጊዜያዊ ደስታን የመምረጥ ዝንባሌ አደረበት። እግዚአብሔር ይህን አሳዛኝ ነገር ያውቃል። ቢሆንም ይወደናል፣ ለድነታችንም ይሰራል።

ስለዚህ ነው በታሪክ ወሳኝ እጥፋቶች ላይ፣ እግዚአብሔር በትንቢታዊ ስራው አማካይነት፣ ለሕዝቡ በሚያስገርም ሁኔታ የሰራው። ነገር ግን ጥረቶቹ በተደጋጋሚ ተቀባይነት ካጡ ፍርድ እንደሚያስከትሉ በግልጽ ተነግሯል።

እግዚአብሔር አንድን ነገር ከማድረጉ በፊት ሁልጊዜ በነቢያቱ አማካኝነት ድርጊቱን አስቀድሞ ያስታውቃል (አሞጽ 3፡7)። ሰዎች ንስሃ ከገቡ ይቅር ለማለት የፈጠነ ነው።

ዛሬም ቢሆን በተመሳሳይ መንገድ ከእኛ ጋር መነጋገሩን ይቀጥላል። ስለዚህ ከምዕተ ዓመታት በፊት እንዳደረገው ሁሉ እግዚአብሔር በዘመኑ መጨረሻ ለሚኖሩት ህዝቡም መናገር አለበት ቢባል አግባብ አለው።

የዚህ ሳምንት ጥናት በድነት ታሪክ ውስጥ እግዚአብሔር ለሕዝቡና ለሰፊው ዓለም ፈቃዱን ግልጽ ለማድረግ ነቢያትን የተጠቀመባቸውን ወሳኝ ጊዜያት ወደ ኋላ ዘወር ብሎ ይመለከታል። በአድቬንቲስት እንቅስቃሴ ዋና ጊዜያቶች የኤለን ጂ ዋይት በመንፈስ ቅዱስ የተመራ አገልግሎት ያለውን ሚና እንመረምራለን። *የዚህን ሳምንት ትምህርት ለታኅሳስ 3 ሰንበት ለመዘጋጀት ያጥኑ።

ህዳር 27
Dec 6

የጥፋት ማስጠንቀቂያ


እግዚአብሔር የሰውን ዘር ሊታደግ ይፈልጋል። ከውድቀት በኋላ እንኳን እግዚአብሔር ከአዳምና ከሄዋን ጋር ግንኙነቱን መቀጠል ፈለገ። ለተወሰነ ጊዜ ሰው “በእግዚአብሔር ስም መጠራት ተጀመረ” (ዘፍ 4፡26)። ትውልድ ትውልድን እየተተካ ሲሄድ ከእግዚአብሔር ጋር የሚራመዱት ሰዎች ቁጥር እየቀነሰ ሄደ። እግዚአብሔርን የሚከተሉት ስለ መልካምነቱ (ስለ ቸርነቱ) መሰከሩ፣ በዙሪያቸው የሚሰራውን ኃጢአት አወገዙ፣ ኃጢአታቸው ስለሚያስከትለው ጥፋት አስጠነቀቋቸው።

ነገር ግን በኖህ ዘመን የምድር ነዋሪዎች ኃጢአት እጅግ ከመጠን ስላለፈ እግዚአብሔር ሊያጠፋቸው ወስነ (ዘፍ 6፡5-7)። የጽድቅ ሰባኪ የሆነው ኖህ (2ኛ ጴጥ 2፡5) ለሚሰሙት ሁሉ ጥፋት እንደተቃረበ አስጠነቀቃቸው። ማስጠንቀቂያውን ሰምተው ንስሃ የሚገቡት እንዲጠለሉበት እግዚአብሔር ኖህን መርከብ እንዲሰራ አዘዘው። ዕብ 11፡7፤ 2ኛ ጴጥ 2፡5፤ ዘፍ 6፡9ን ያንብቡ።። ኖህ በምን መንገዶች ነው “የጽድቅ ሰባኪ” የሆነው?



የውሃ ጥፋት በሰው ዘር ታሪክ ውስጥ ወሳኝ ቦታ አለው። በብሉይ ኪዳን እና በአዲስ ኪዳን ውስጥ ተደጋግሞ ተጠቅሷል። የሰውን ክፋት ዝቅጠትና የእግዚአብሔርን አስገራሚ ጸጋ ከፍተኛነት በጉልህ ያሳያል። በኃጢአተኞች ላይ በሚያስተላለፈው ፍርድና መዳንን ለመቀበል ለሚፈልጉ በሚያደርገው መታደግ የእግዚአብሔር ጽድቅ በይፋ ይታያል።

“ብልሽት በሞላበት ዓለም ማቱሳላ፣ ኖህና ሌሎችም የእግዚአብሔር ዕውቀት እንዳይጠፋና የግብረ ገብነትን ውድቀት ለማገድ ተግተው ይሰሩ ነበር። የጥፋት ውሃ ከመምጣቱ 120 ዓመታት ቀደም ብሎ የውሃ ጥፋት እንደሚመጣ እና መርከብ መስራት እንዳለበት እግዚአብሔር በመልአኩ በኩል ለኖህ ገለጠለት። መርከቡን በሚሰራበት ጊዜ ሁሉ ክፉዎችን ለማጥፋት እግዚአብሔር የውሃ ሙላት እንደሚያወርድ ኖህ ይሰብክ ነበር። መልእክቱን አምነው የሚናዘዙና ንስሃ የሚገቡ ሁሉ ከጥፋት እንደሚድኑ ነገራቸው” (ኤለን ጂ ዋይት፣ አበውና ነቢያት ገጽ 92)።

እግዚአብሔር ስለ ጥፋት ውሃና ማስጠንቀቂያውን የሚሰሙ እንደሚድኑ ብቻ ሳይሆን ምድርን እንደገና በውሃ እንደማያጠፋ ለኖህና ለፍጥረት ሁሉ ቃል ኪዳን ገባ (ዘፍ 9፡8-17)። እያንዳንዱ ቀስተ ደመናው የመዳንን ቃል ኪዳንና ተስፋ ያሳያል። ቀስተ ደመና ባዩ ቁጥር በዚያ ውስጥ ስለሚገኘው ቃል ኪዳን ያስቡ። እግዚአብሔር ቃል ኪዳኑን እንደማያፈርስ ማወቅዎ የሚያጽናናዎት ለምንድር ነው?

ህዳር 28
Dec 7

አንዲት እናት በእስራኤል ውስጥ


እስራኤሎችን ከግብጽ ባርነት ነፃ ካወጣቸው በኋላ እግዚአብሔር የከነዓንን ምድር ሰጣቸው። ህጉንና ትእዛዙን ከጠበቁ እጅጉን እንደሚባረካቸው ቃል ኪዳን ገባላቸው። ቃል ኪዳናቸውን ካፈረሱ ደግሞ ስቃይና ጥፋት እንደሚደርስባቸው አስጠነቀቃቸው (ዘዳ 27፡30)። እያሱ ከሞተ በኋላ እስራኤላውያን ቃል ኪዳናቸውን አፈረሱ። ታዲያ በጎረቤት ህዝቦች ሲጨቆኑ ወደ እግዚአብሔር ጮኹ። ጩኸታቸውን ሰምቶ “እግዚአብሔር መሳፍንትን አስነሳላቸው፣ ከማረኩአቸውም እጅ አዳናቸው”(መሳ 2፡16)። ደግሞ ቃል ኪዳናቸውን እንዲያድሱና በጣላቶቻቸው ላይ እንዲያይሉ የሚያደፋፍሯቸውን ነቢያትን ላከላቸው። መሳ 4፡4-16ንና መሳ 5፡1-5ን ያንብቡ። ዲቦራ ለእስራኤላውያን ምን አደረገች?



የእግዚአብሔርን መልዕክት ለእስራኤላውያን የጦር ሰራዊት መሪ፣ ለባራቅ በማድረስ ዲቦራ ወሳኝ ሚና ተጫወታለች። ዲቦራ ባራቅ ጦርነቱን እንዲጀምር እንዲህ ስትል ምልክት ሰጠችው፦ “እግዚአብሔር ሲሣራን በእጅህ አሳልፎ የሚሰጥበት ቀን ዛሬ ነውና ተነሣ፤ እነሆ፥ እግዚአብሔር በፊትህ ወጥቶአል አለችው። ባራቅም አሥር ሺህ ሰዎች ተከትለውት ከታቦር ተራራ ወረደ” (መሳፍንት 4፡14)።

የእስራኤል ፈራጅ (ዳኛ) እንደመሆኗ መጠን ዲቦራ ዋና ሰው ነበረች። መሪነቷና በእግዚአብሔር ተስፋ የነበራት እምነት ጠላቶቻቸውን ሲዋጉ እስራኤላውያንን አበረታታቸው። ምንም እንኳን በመጀመሪያ ፈራ ተባ ቢልም (ቢያመነታም) የባራቅ የጦር መሪነት ብቁነትና ፈቃደኝነቱ በጣም ጠቃሚ ነበር። ነገር ግን የጦርነት ድል የተገኘው በእርሱ ምክንያት አልነበረም።

ነቢይት የነበረችው የዲቦራና የጦር ሰራዊቱ ዋና አዛዥ ባራቅ ታሪክ ዋናው ቁም ነገር ከዚህ ላይ ነው። ያን አስገራሚ ድል ሲቀዳጁ ዳኛዋ ዲቦራና የጦር ስራዊቱ ጠቅላይ አዛዥ ባራቅ ስላገኙት ድል እግዚአብሔርን አከበሩ። እውነተኛ መንፈሳዊ መሪ ማለት እንዲህ ነው።

የዲቦራ ትንቢታዊ አገልግሎት የሚያሳየው በችግር እና በጭቆና ጊዜ የእግዚአብሔርን ታማኝነት ነው። እግዚአብሔር መልዕክቱን ለባራቅ እንድታስተላልፍ ሲናገር በቂ የጦር ኃይል የለንም ወይም እስራኤላውያን ደካማ ናቸው ብላ አልተከራከረችም። በዚያ ፋንታ መልእክቱን ለባራቅ በእርግጠኛነት አስተላልፋለች። መጠራጠሩን ትቶ በእግዚአብሔር ቸርነት ላይ እንዲተማመን አደፋፈረችው። ሁኔታዎች ተስፋ የሚያስቆርጡ በሚመስሉበት ጊዜ በእግዚአብሔር ላይ መተማመንን የምንማረው እንዴት ነው?

ህዳር 29
Dec 8

ለንስሃ ጥሪ


መሳፍንት 2፡16-19ን ያንብቡ። እዚህ ላይ የምናየው ምን አይነት ዝንባሌ ወይም አቅጣጫ ነው?



እስራኤል ንጉስ እንዲሰጣቸው በጠየቁት መሰረት (1ኛ ሳሙ 1፡8) የመሳፍንት ዘመን አከተመ (አለፈ)። ይህ ለውጥ ግን ንጉሡንና የሕዝቡን መሪዎች ለመምከር፣ ለማረምና ለመገሰጽ የነቢያትን አስፈላጊነት በበለጠ ወሳኝ አደረገው።

በአክአብ ጊዜ የፍርድ መልእክት እንዲያስተላልፍ እግዚአብሔር ኤልያስን ላከው። “የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ትታችሁ በኣሊምን የተከተላችሁ፥ አንተና የአባትህ ቤት ናችሁ እንጂ እኔ አይደለሁም” (1ኛ ነገሥት 18፡18)። ንስሐ በመግባት ፋንታ አክአብ ኤልያስን ሊያስገድል ሞከረ። እግዚአብሔር ግን ኤልያስን ጠበቀው (1ኛ ነገስት 18፡ 10-12)። በረሃቡ ሶስተኛ ዓመት ኤልያስ ለአክአብ ሲገለጥ የድርቁ ምክንያት አንተ ነህ በማለት አክአብ ኤልያስን ከሰሰው (1ኛ ነገ 18፡17)።

ኤልያስ በእግዚአብሔር እና በብኤል ነቢያት መካከል የሚደረገውን ተጋድሎ እንዲመሰክሩ (እንዲመለከቱ) እስራኤልን በሙሉ ሰበሰበ (1ኛ ነገ 18፡19)። የኤልያስን አዋጅ በ1ኛ ነገስት 18፡21፣ 38 እና 39 ያንብቡ። ምን ተከሰተ?



ከሰማይ የወረደው መለኮታዊ እሳትና የኤልያስ ትንቢታዊ መልዕክት አንድ ላይ ተጨምረው ሕዝቡን ስለነኩት ሕዝቡ ንስሃ ገባ። እስራኤላውያን ሙሉ በሙሉ ራሳቸውን ለእግዚአብሔር ለመስጠት ዳተኞች እንደነበሩ ሁሉ ዛሬም የእግዚአብሔርን ፈጣሪነት እና አዳኝነት በማያምን ባህል መካከል እንኖራለን። የእግዚአብሔር መልክተኞች ሆነን ሌሎች ለእርሱ ታማኝ እንዲሆኑ በመጎስጎስ ፈንታ እስራኤላውያን እንዳደረጉት ሁሉ እኛም የራሳችንን ፈላጎቶች በመከተል ከጥሪያችን ወደ ኋላ እናፈገፍጋለን።

የራሳችንን ምኞት መከተል ስብራት፣ ስቃይና ከዚያም መሞት እንደሚያስከትል እግዚአብሔር አስጠንቅቆናል። ድምጹን ብንከተል (ብንሰማ) ግን “እግዚአብሔርም ሁልጊዜ ይመራሃል፤ ነፍስህንም በመልካም ነገር ያጠግባል አጥንትህንም ያጠናል፤ አንተም እንደሚጠጣ ገነት፥ ውኃውም እንደማያቋርጥ ምንጭ ትሆናለህ” ይላል (ኢሳይያስ 58፡11)። ስጋዊ ተፈጥሮአችን ሳናውቀው እንኳን እንድናምጽ ይገፋፋናል። በስጋዊ ተፈጥሮአችን እንዳንወድቅ ምን አይነት ምርጫዎችን ማድረግ ይገባናል?

ህዳር 30
Dec 9

በስደት ተስፋ


“የአባቶቻቸውም አምላክ እግዚአብሔር ለሕዝቡና ለማደሪያው ስላዘነ ማለዳ ተነሥቶ በመልእክተኞቹ እጅ ወደ እነርሱ ይልክ ነበር” (2 ዜና 36፡15)።

ለማጽናናት፣ ለመገሰጽና ለማስጠንቀቅ እግዚአብሔር ከኤልያስ በኋላ ለህዝቡ አያሌ ነቢያትን ልኮላቸው ነበር። የእስራኤል እና የይሁዳ መንግስታት ግን በኃጢያት ከመዝቀጣቸው የተነሳ እግዚአብሔር ከሰዶምና ከጎሞራ ጋር አነፃፀራቸው (ኢሳ 1፡ 9,10)። የእግዚአብሔር ሕዝብ ትእቢተኞች፣ ስግብግቦችና ጣኦት አምላኪዎች ሆኑ። ሰራተኞቻቸውን፣ መበለቶቻቸውን፣ ደሃ አደጎችንና መጻተኞችን ጨቆኑ (ለውድቀታቸው እግዚአብሔር የሰጠውን መልስ በኢሳይያስ 58 ላይ ይመልከቱ)። በመጨረሻ በአሦራውያን እንዲማረኩ እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ ፈረደባቸው (2ኛ ነገ 24 እና 25)።

እግዚአብሔር ህዝቡን ቢቀጣም በስደት አገር ብቻቸውን አልተዋቸውም። ለወደፊቱ ተስፋ እንዲኖራቸው እንደ ሕዝቅኤልና ዳንኤል ያሉ ነቢያት ላከላቸው። ኢሳያስ 59፡1-4ንና ነህምያ 9፡30ን ያንብቡ። ለዘመናት ሁሉ አግባብነት ያለው ሀሳብ እዚህ ላይ ምን እየተባለ ነው?



የእስራኤል እና የይሁዳ መንግስታት በታሪካቸው ዘመን በሙሉ የኃጢአታቸውን ዋጋ ሲያጭዱ ኖረዋል። ከእግዚአብሔር ፊታቸውን በማዞራቸው የደህንነት ጥበቃው ሲለያቸው የቁጣውን ፍርድ ተቀብለዋል። ጭቆናንና ጣኦት አምላኪነትን ባይታገስም ወደ ስደት የላካቸው መጀመሪያ እንደተሳሳቱ አይደለም። ንስሐ እንዲገቡና ወደ እርሱ እንዲመለሱ ነብያቱን ደጋግሞ ላከባቸው (ላከላቸው)። ህዝቡ ግን መስማት አልፈለጉም። እንዲያውም ሕዝቡ ወደ እርሱ እንዲመለሱ እግዚአብሔር ያሳየው የትዕግስት ርዝመት ዘመን ሲታይ እጅግ ያስገርማል። ለብዙ ምእተ አመታት ከነቢያት ላይ ነቢያት እየላከ ከማስጠንቀቂያ ላይ ማስጠንቀቂያ ደርድሮላቸው ነበር። ወደ እርሱ እንዲመለሱ ደጋግሞ ተማፀናቸው።

ኢየሱስ ራሱ እንዲህ አለ፦ “ኢየሩሳሌም ኢየሩሳሌም ሆይ፥ ነቢያትን የምትገድል ወደ እርስዋ የተላኩትንም የምትወግር፥ ዶሮ ጫጩቶችዋን ከክንፎችዋ በታች እንደምትሰበስብ ልጆችሽን እሰበስብ ዘንድ ስንት ጊዜ ወደድሁ! አልወደዳችሁምም” (ማቴዎስ 23፡37)።

በስደት ላይ ሳሉ እንኳን እግዚአብሔር ህዝቡን ያለ ተስፋ አልተዋቸውም። በተደጋጋሚ ውድቀታቸው ጊዜ እንኳን “ለጽዮን ታዳጊ ይመጣል፥ በያዕቆብም ዘንድ ከኃጢአት ለሚርቁ፥ ይላል እግዚአብሔር” (ኢሳይያስ 59፡20)። እስራኤል ከእርሱ ፊቷን ከእርሱ ስታዞር እንኳን የእግዚአብሔርን ታማኝነት እስቲ ይመልከቱ። ታዲያ ይህን የእግዚአብሔርን ፍቅራዊ ባህሪ በራስዎ ህይወት ላይ ሲከሰት እንዴት አይተዋል? እግዚአብሔር ይህን ያህል ታጋሽና አፍቃሪ ባይሆን ኖሮ ምን ይበጅዎ ነበር?

ታህሣሥ 1
Dec 10

በመጠበቂያ ጊዜ የተላከ ነቢይ


ራዕይ 1፡1-3ን ያንብቡ። ዮሐንስ የተጠራው ምን እንዲያደርግ ነበር?



ቀደምት ክርስቲያኖች የክርስቶስን የመመለስ ተስፋ በጉጉት ይጠባበቁ ነበር። ሐዋርያው ዮሐንስ ክርስቶስ ወደ ደመናት ሲያርግ ሲያይ በዚያው ሁኔታ እንደሚመለስ መልአኩ ነገረው (የሐዋ 1፡10,11)። አሁን የቀደምቷ ቤተ ክርስቲያን አባላት አንድ የማያውቁት ነገር ገጠማቸው። አዎን፣ ኢየሱስ እመለሳለሁ ብሏል። ነገር ግን መቼ?

ዮሐንስ በጳጥሞስ ደሴት ተግዞ ሳለ ስለ ክርስቶስ ዳግም መመለስ ተስፋ ጻፈ። “እነሆ፥ ከደመና ጋር ይመጣል፤ ዓይንም ሁሉ የወጉትም ያዩታል፥ የምድርም ወገኖች ሁሉ ስለ እርሱ ዋይ ዋይ ይላሉ። አዎን፥ አሜን” (ራእይ 1፡7)። የዘመኑን መጨረሻ ስለሚያሳዩ ምልክቶች ዮሐንስ ሰፋ ያለ መልዕክት ተቀበለ። ለሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት ማደፋፈሪያና ተግሳጽም ተቀበለ (ራዕይ 2፡3)። ራዕዩ የፍርድ (ራዕ 14፡ 6-12)፣ የዓለም መጨረሻ (ራዕ 20) እና የምድር መታደስን መልዕክቶች ያካተተ ነበር (ራዕ 21፡22)።

ዮሐንስ “እኔ ወንድማችሁ የሆንሁ ከእናንተም ጋር አብሬ መከራውንና መንግሥቱን የኢየሱስ ክርስቶስንም ትዕግሥት የምካፈል ዮሐንስ ስለ እግዚአብሔር ቃልና ስለ ኢየሱስ ምስክር ፍጥሞ በምትባል ደሴት ነበርሁ” ሲል እራሱን ያስተዋወቃል (ራእይ 1፡9)። መጠባበቅ ከሚያስከትል ጭንቀት ብቻ ሳይሆን የእግዚአብሔርን ቃል ከማወጅ እና የኢየሱስ ክርስቶስን ምስክርነት ከመያዝ የተነሳ መከራን መቀበል ምን እንደሆነ አወቀ።

በመላው ራዕይ መጽሐፍ ውስጥ ዩሐንስ እንዲያይና ያየውንም እንዲጽፍ ታዝዞ ነበር። “ይህንም ያየሁትና የሰማሁት እኔ ዮሐንስ ነኝ” (ራዕ 22፡8)። ዮሐንስ በዘመኑ መጨረሻ ስለሚሆነው ክስተት ትንቢታዊ ምስክር ነበር። በራዕይ የተገለጠለትን በጊዜው ለነበሩት አብያተ ክርስቲያናት እንዲነግር ታዝዞ ነበር (ራዕ 22፡16)። በምድር ታሪክ ወሳኝ ወቅት የኢየሱስን የመጀመሪያውን መምጣት ያበሰረውን መጥምቁ ዮሐንስን ያስታውሰናል (ዮሐ 1፡6-8)።

እኛም እንደ ዮሐንስ እንድንመሰክር ተጠርተናል። የክርስቶስን ምስክርነትም ልንጠብቅ ይገባናል (ራዕ 19፡10)። በነቢያት በኩል ስለ እርሱ የሰጠውን ምስክርነት ራዕይ ላንቀበል እንችላለን። ነገር ግን በህይወታችን ስለ እርሱ ስራ እየመሰከርን እና የመዳናችንን ምልክቶች ተግተን እየጠበቅን የክርስቶስን መመለስ በትዕግስት መጠበቅ እንችላለን። ስለ ተሰጠን ብርሃን ሁሉ እስቲ ያስቡ። እጅግ ብዙ ስለተሰጠን ብቻ በለያችን የወደቁ ኃላፊነቶች ምንድር ናቸው?

ታህሣሥ 2
Dec 11

ትንቢታዊ ድምጽ


እግዚአብሔር ምንጊዜም ከሰዎች ጋር የሚገናኘው በነቢያቱ አማካኝነት ነው። ይህ በተለይ ወሳኝ በሆኑ የታሪክ ጊዜያት የተለመደ ነገር ነው። ታዲያ እግዚአብሔር በመጨረሻው ዘመን የሚኖረውን ሕዝቡን እንዲያነጋግር መጠበቅ አግባብ አይደለም?

በጥቅምት 22/1844 ዓ ም ሚለራውያን የተባሉት ክርስቲያኖች “ታላቁ ተስፋ መቁረጥ” የተባለው ክስተት ሲደርስባቸው ተስፋ ለቆረጡት አማኞች መልዕክት እንድታስተላልፍ ኤለን ሃርመንን (ዋይትን) ለትንቢታዊ አገልግሎት በመጥራት መልእክት ሰጣት። የመጀመሪያ ራዕዩዋ እነርሱን ማጽናናት ነበር።

ሌላኛው ወሳኝ እጥፋት የነበረው የአድቬንቲስት የህትመት ስራ ሲጀምር እና ሰንበትን አክባሪ የነበሩ አድቬንቲስቶች በይፋ ሲደራጁ ነበር። እነዚህ ሰንበትን አክባሪ አማኞች በ1860ዎቹ ውስጥ በህትመትና በወንጌላዊ ስራቸው አማካይነት ቁጥራቸው ወደ ብዙ ሺሆች አድጎ ነበረ። የሦስቱን መላዕክት መልዕክት በሚገባ ለማድረስ መደራጀት ነበረባቸው (ራዕይ 14፡6-12)። የመደራጀትን ሀሳብ አንዳንዶቹ ሲቃወሙ የመደራጀትን ትክክለኛነት እንድትደግፍ እግዚአብሔር ኤለን ጂ ዋይትን ተጠቀመ። ግንቦት 21/1863 ዓ ም የሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተ ክርስቲያን በይፋ ተወለደች።

በዚሁ ዓመት በአማኞቹ መካከል የጤና ተሃድሶን ለማደፋፍር እግዚአብሔር የትንቢትን ስጦታ ተጠቀመ። አብዛኛዎቹ 7ኛ ቀን አድቬንቲስቶች ጥሩ ጤንነት አልነበራቸውም ወይም ጤናማ ኑሮ አይኖሩም ነበር። በ1863ና በ1865 ዓ ም ኤለን ጂ ዋይት በተቀበለቻቸው ሁለት አጠቃላይ የጤና ራእዮች አማካይነት የጤና ጉዳያቸው ተቀየረ። ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስቶች የጤናና የጤነኛ አኗኗር ጥብቅ ደጋፊዎች ሆኑ።

ከ1870ዎቹ እስከ 1890ዎቹ ኤለን ጂ ዋይት የአድቬንቲስት የትምህርት ስርዓትን ለማቋቋም ትልቅ መሳሪያ ሆነች። የተሟላ ወይም ሁሉን አካታች የትምህርት ፍልስፍናዋ (የተግባር፣ የቀለምና መንፈሳዊ ትምህርት) ቀስ ብቀስ ተቀባይነት በማግኘት ስራ ላይ ዋለ። ስለዚህ የትምህርት ፍልስፍና እንዲህ ብላለች:-”እውነተኛ ትምህርት ማለት አንድን የዕውቀት ዘርፍ ከማጥናት በላይ ነው። አሁን ላለው ለዚህ ዓለም ኑሮ ክመዘጋጀትም በላይ ነው። የሰውን ሙሉነት የሚያካትትና ሰው እድሜ ልኩን የሚከታተለው መሆን አለበት። አካላዊ፣ አእምሮአዊና መንፈሳዊ እድገት ተጣጥመው የሚጎለምሱበት ትምህርት ነው” (Education page 13)።

በ1880ዎቹ ላይ የሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተ ክርስቲያን በድነት ላይ ያላት የስነ-መለኮት ትምህርት ሚዛናዊ እንዲሆን ወሳኝ ሚና ተጫውታለች። አድቬንቲስቶች ለሕግ በሚሰጡት የተለዬ ማዕቀፍ ውስጥ የእግዚአብሔር ጸጋና ጽድቅ በእምነት ማዕከላዊነት ላይ አጽንዖት ሰጠች። ከ1901 እስከ 1903 ድረስ የቤተ ክርስቲያኗን አለማቀፍ ተልዕኮ በተሻለ ሁኔታ ተፈጻሚነት እንዲኖረው ለማድረግ የድርጅቱን መዋቅር ለማሻሻል ረድታለች።

በአጭሩ ያለ ኤለን ጂ ዋይት አገልግሎት ዛሬ የምናውቀው የሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ድርጅት አይኖርም ነበር። በወሳኝ ወቅቶች የእግዚአብሔር መልክተኛ ነበረች።




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA Union SSL