የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ለዚህ ሳምንት ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡- ፊል. 3:17–21፣ ፊል. 4:4–13, 19።
የመታሰቢያ ጥቅስ፡ “በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና
ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ እንጂ በአንዳች
አትጨነቁ” (ፊል. 4:6)።
በዚህ ሳምንት ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ሰዎች የጻፈውን መልዕክት በተመለከተ
ስናደርግ የነበረውን ጥናታችንን እንጨርሳለን። ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ሰዎች
የጻፈው ደብዳቤ ለየዕለት ኑሮአችን ጠቃሚ በሆኑ ትምህርቶች፣ ምክሮች እና
አባባሎች የተሞላ ነው። ጳውሎስ ከእነዚህ አባባሎች ውስጥ ብዙዎቹን በመልዕክቱ
የመጨረሻ ቁጥሮች ላይ አካቷቸዋል። የጳውሎስ መልዕክቶች ከኢየሱስ አስተምህሮዎች
ጋር ተመሳሳይ ናቸው። ኢየሱስ ተከታዮቹን በእምነት የተሞላ አስደሳች ሕይወት እንዴት
መኖር እንደሚችሉ አስተምሯቸዋል። ጳውሎስም በሐሴት የተሞላ ክርስቲያናዊ ሕይወት
እንዴት መኖር እንዳለብን ይነግረናል።
ብዙ ጊዜ በህይወታችን ውስጥ የማንፈልጋቸው ነገሮች ይከሰታሉ። ሆኖም
ልንጨነቅ ወይም ተስፋ ልንቁርጥ አይገባም። መጽሐፍ ቅዱስ ጸንተን እንድንቆምና
ችግሮቻችንን ለመፍታት የሚረዱንን ብዙ ጠቃሚ መርሆዎችን ይሰጠናል። ስለዚህ
መጨነቅ አይገባም። እግዚአብሔር በሚሰጠን የከበረ ሰላም መሞላት እንችላለን። እርሱ
አሁንም ሆነ የወደፊቱን ህይወታችንን ይቆጣጠራል። የሚያስፈልገንንም ሁሉ ይሰጠናል።
ከሁሉም በላይ ተስፋ ወይም ሰላም እንዲሰጡን በመንግስታት ወይም
በመሪዎቻቸው ላይ መደገፍ አያስፈልገንም። ክርስቲያኖች በመሆናችን የሰማይ ዜጎች
ነን። የእግዚአብሔር መንግሥት ዜጎች በመሆናችንም እርሱ ብዙ በረከቶችን ይሰጠናል።
እግዚአብሔርም ደግሞ እኛ እንድናገለግለው ይጠብቅብናል።
*የሳምንቱን ትምህርት በማጥናት ለሰንበት ይዘጋጁ።
ጳውሎስ ይኖር የነበረው በክፉ ዘመን ነበር። እኛም እንዲሁ ነን። ጥያቄው
ዙሪያችንን ብዙ ክፋት ከቦን ሳለ፣ እንዴት መኖር ወይም መመላለስ አለብን? የሚለው ነው።
ፊል. 3:17-19ን ያንብቡ። ጳውሎስ ስለ መልካም እና መጥፎ አርአያዎች ይናገራል።
እነዚህ መልካም እና መጥፎ አርአያዎች ምንድናቸው? መልካሙን ከመጥፎው ለይተን
እንዴት ማወቅ እንችላለን?
ጳውሎስ ሃሳባቸውን ባይደግፈውም እንኳን ሰዎቹን ይወዳቸዋል። ጳውሎስ
ስለነሱ ያነባል! ጳውሎስ እነዚህ ሰዎች የግል ጠላቶቹ እንዳልሆኑ መናገሩን ያስተውላሉ?
ጳውሎስ በእርግጥ “የክርስቶስ መስቀል ጠላቶች” እንደሆኑ ተናግሯል (ፊል. 3፡18)።
ጳውሎስ አዳኝ የሚያስፈልጋቸው ኃጢአተኞች መሆናቸውን ተረድቷል (ኤፌ. 2፡11-14ን
ያንብቡ)። ሁላችንም እንደነሱ ስለሆንን ኢየሱስ ያስፈልገናል። ኢየሱስ የሚያስፈልገን
መሆኑ ደግሞ ሁላችንም አንድ ያደርገናል።
ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ሰዎች ስለ መጥፎዎቹ ሳይሆን ስለ መልካም አርአያዎች
እንዲያስቡ ነግሯቸዋል። ጳውሎስ አንባቢዎቹ እንደ እሱ የሚኖሩትን ሰዎች በጥንቃቄ
እንዲመለከቱአቸው ይፈልጋል። ከዚያም የፊልጵስዩስ ሰዎች እንደነዚህ ሰዎች መኖር
ነበረባቸው። ጳውሎስ ለሮሜ ሰዎች በጻፈው ደብዳቤ ላይ ተመሳሳይ ነገር ተናግሯል።
“ነገር ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ እናንተ የተማራችሁትን ትምህርት የሚቃወሙትን፣
መለያየትንና ማሰናከያን የሚያደርጉትን ሰዎች እንድትመለከቱ እለምናችኋለሁ፥ ከእነርሱ
ዘንድ ፈቀቅ በሉ” በማለት ያሰጠነቅቃል (ሮሜ 16፡17)። ጳውሎስ በሮም የነበሩት እነዚህ
ሐሰተኛ አስተማሪዎች ሊታመኑ አይችሉም ይላል። “እንዲህ ያሉት ለገዛ ሆዳቸው እንጂ
ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ አይገዙምና፥ በመልካምና በሚያቆላምጥ ንግግርም ተንኮል
የሌለባቸውን ሰዎች ልብ ያታልላሉ” (ሮሜ 16፡18)።
በእርግጥ ፍጹም የሆነው ምሳሌአችን ኢየሱስ ብቻ ነው። ደግሞም ልንከተላቸው የሚገቡን
መልካም አርአያዎች የሆኑ ክርስቲያኖችም አሉ። አሁን ደግሞ ስለራስዎ ህይወት ያስቡ።
ለሌሎች ሰዎች ምን ዓይነት ምሳሌ ነዎት?
ጳውሎስ የሰማይ ዜጋ ስለመሆን የሚናገረው ምንድን ነው? ፊል. 3:20, 21ን ያንብቡ።
ጳውሎስ ስለ መስቀሉ ጠላቶች ይናገራል። “መጨረሻቸው ጥፋት ነው፥ ሆዳቸው
አምላካቸው ነው፥ ክብራቸው በነውራቸው ነው፥ አሳባቸው ምድራዊ ነው” ይላል (ፊል.
3፡19)። ክርስቲያኖች የሰማይ ዜጎች ስለሆኑ፣ የሚያስቡት በሰማይ ስላለው ነገር ነው።
ኢየሱስ ክርስቶስ ንጉሣችን ነው። ጳውሎስ ኢየሱስ “የተዋረደውን (ደካማ) ሥጋችንን
ይለውጠዋል” በማለት ይናገራል (ፊል. 3፡21)። ይህ እስኪሆን ድረስ በበሽታ፣ በህመም
እና በሞት ልንሰቃይ እንችላለን።
የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ። ኢየሱስ ስለሚሰጠን አዲስ አካል ምን ያስተምሩናል?
ኢዮ. 19፡25-27
ሉቃ. 24፡39
1ኛ ቆሮ. 15፡42-44
1ኛ ቆሮ. 15፡50-54
ቆላ. 3፡4
በመጨረሻም ኢየሱስ ሞትን ይሽረዋል። ሞት የመጨረሻው ጠላታችን ነውና (1
ቆሮ. 15:26)። ይህ ቃል ተስፋ ይሰጠናል። ኢየሱስ ለሞት ዳርቻ አድረጎ፣ አዲስ አካል
ይሰጠናል (ፊል. 3: 21)።
ስለዚህ ለጳውሎስ የሰማይ ዜጎች መሆናችን የዘላለም ሕይወትንና የትንሣኤን
ተስፋ ያካትታል። ትንሣኤ ኢየሱስ በዳግም ምጽዓቱ ታማኝ ተከታዮቹን ከሞት
የሚያስነሣበት ጊዜ ነው። ያኔ ሙሉ በሙሉ አዲስ ህይወት ይኖረናል። ይህንን አዲስ
ሕይወት በአእምሯችን ማሰብ እንኳን አንችልም!
እንደ ክርስቲያኖች ለምናምንባቸው ነገሮች ሁሉ የዘላለም ሕይወት ተስፋ እጅግ አስፈላጊ የሆነው
ለምንድን ነው? ይህ ሕይወት ከዚህ ይልቅ የበለጠ ዋጋ ያለው ነገር ምን ሊሰጠን ይችላል?
ፊል. 4:4-7ን ያንብቡ። ጳውሎስ በእነዚህ ጥቅሶች ላይ የሚናገረው ሰላም የሚመጣው ከየት ነው? የምናገኘውስ እንዴት ነው?
ጳውሎስ በድጋሚ ለቤተ ክርስቲያን አባላት በሰላምና በአንድነት የመኖርን
አስፈላጊነት ይናገራል (ፊል. 4፡1-3)። ከዚያም ጳውሎስ በጌታ ደስ መሰኘት ወደሚለው
አዲስ ርዕስ ይገባል (ፊል. 4፡4-7)።
ከተከሰቱ በኋላ ወዲያውኑ ስለሚፈቱ ችግሮች ምን ያህል ይጨነቃሉ? ብዙ
ጊዜ ነገሮች ስናስባቸው ከእውነታው ይልቅ የከፉ ይመስላሉ። ስለዚህ ኢየሱስ ስለ
እነርሱ እንዳንጨነቅ ነግሮናል (ማቴ. 6፡25-34ን እና ማቴ. 10፡19ን ያንብቡ)። ጴጥሮስ
በሚያስጨንቀን ነገር ሁሉ በኢየሱስ ላይ መታመን እንደምንችል ይነግረናል። ኢየሱስ
ይጠነቀቅልናል (1 ጴጥ. 5፡7)። ችግሮች በዓለም ላይ እየከፉ ሲሄዱ፣ እኛ ግን በተስፋ
መሞላት አለብን። እነዚህ ችግሮች የኢየሱስ ምጻት እጅግ መቃረቡን የሚያሳዩ ምልክቶች
ናቸው (ማቴ. 24:33ን፣ ሉቃ. 21:28ን እና ያዕ. 5:8ን ያመሳክሩ)። ለጭንቀትና ፍርሃት
መፍትሄው ምንድነው? መፍትሄው በእምነት መጸለይ ነው (ፊል. 4፡6, 7)። በእርግጥ
በኢየሱስ ማመንና ጸሎታችንንም እንደሚሰማ መተማመን አለብን። በተጨማሪም
ምንም እንኳን ጸሎታችን ተመልሶ ባንመለከትም፣ ምላሽ እንዳገኘ አድርገን በመቀበል
መኖር ይገባል። በምስጋና መንፈስ መጸለይ አለብን። እኛም ጸሎታችንን እንዲመልስልን
እግዚአብሔርን በሙሉ ልባችን ልንጠይቀው ይገባል። አንዳንድ ጊዜ ለጸሎታችን ምላሽ
ማግኘት እጅግ የሚያስፈልግበት ወቅት አለ (የሚከተሉትን ምሳሌዎች ያንብቡ፡- ሉቃ.
1፡13፣ ፊል. 1፡19፣ 1 ጢሞ. 5፡5፣ ያዕ. 5፡16)። እግዚአብሔር ተስፋ የገባልንን ነገሮች
መጠየቅ አለብን (1 ዮሐ. 5፡14)። ያኔ ጸሎታችን እንደሚመለስ እርግጠኞች መሆን
እንችላለን። ከዚያም ማረፍ እና ሰላም ማግኘት እንችላለን። እግዚአብሔር እንደነዚህ
አይነት ጸሎቶችን እንደሚቀበል እናውቃለን።
የሚከተሉት ጥቅሶች የእግዚአብሔርን ሰላም እንድናስተውል የሚረዱን እንዴት ነው? መዝ.
29:11፣ ኢሳ. 9:6፣ ሉቃ. 2:14፣ ዮሐ. 14:27 እና 1 ቆሮ. 14:33።
ምድራዊው ሕይወት የእግዚአብሔርን ሰላም ሊሰጠን አይችልም።
የእግዚአብሔር ሰላም የሚገኘው፣ በእግዚአብሔር የዘላለም ሕይወት ስጦታ ላይ
ባለን ተስፋ ነው (ሮሜ 5፡1፣ 6፡23)። ምንም እንኳን ሙሉ በሙሉ ባናስተውለውም፣
ይህ ሰላም በተስፋ ይሞላናል (ፊል. 4፡7)። የእግዚአብሔር ሰላም የሕይወታችንን
እያንዳንዷን ክፍል ሁሉ እንደሚለውጥ እናውቃለን!
የእግዚአብሔርን ሰላም ማግኘት ማለት ምን ማለት ነው?
እግዚአብሔር ልናስተውለው ከምንችለው በላይ የሆነ ሰላም ይሰጠናል። ይህ
ሰላም ደግሞ “ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል” (ፊል. 4፡7)።
መንፈሳዊ ሕይወታችንን መጠበቅ አለብን። በፊል. 4: 7 ላይ “ይጠብቃል” የሚለው ቃል
የመጣው “ፍሩሬዎ” ከሚለው የግሪክኛ ቃል ነው። በግሪክ ቋንቋ ይህ ቃል ከተማን
በቡድን ከጠላቶች የሚጠብቁ ወታደሮችን ለማመልከት ጥቅም ላይ ውሏል (2 ቆሮ. 11፡
32ን ከሐዋ. 9፡24 ጋር ያመሳክሩ)።
በልባችን ውስጥ ሰላም የመኖሩ ሌላው እጅግ አስፈላጊው ክፍል የእግዚአብሔርን
ሕግ መታዘዝ ነው። “ሕግህን ለሚወድዱ ብዙ ሰላም ነው፥ ዕንቅፋትም የለባቸውም”
(መዝ. 119:165)።
ፊል. 4:8, 9ን ያንብቡ። በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ ጳውሎስ ለአንባቢዎቹ ምን ምክር
ይሰጣል?
በፊል. 4: 8, 9 ላይ ጳውሎስ አእምሯችንን በስድስት አስፈላጊ ነገሮች እንድንሞላ
ይነግረናል። ጳውሎስ የእሱን ምሳሌ እንድንከተል ያደፋፍረናል። በተጨማሪም በዝርዝሩ
ውስጥ ስላካተታቸው ነገሮች ስለ እያንዳንዳቸው ይናገራል። ስለሚከተሉት ነገሮች
እንድናስብ ያበረታታናል፡-
1. እውነተኛ የሆነውን፡- ኢየሱስ ብዙውን ጊዜ ትምህርቱን የሚጀምረው “እውነት
እላችኋለሁ” በማለት ነበር። መላው አዲስ ኪዳን እውነት ለእግዚአብሔር እጅግ
አስፈላጊ እንደሆነ ይነግረናል (ሐዋ. 26:25ን፣ ሮሜ 1:18ን፣ 1 ቆሮ፣ 13:6ን፣ 2 ቆሮ. 4:2ን፣
ኤፌ. 4:15ን፣ 1 ጢሞ. 3:15ን፣ ያዕ. 1:18ን፣ 1 ጴጥ. 1:22ን እና 1 ዮሐ. 2:21ን ያንብቡ)።
2. ጭምትነት (ሐቀኝነት) ያለበትን፡- ኢየሱስን ስለምንወደውና እርሱ እውነት ስለሆነ፣
ሁልጊዜ ሐቀኛ መሆን አለብን (ከ1 ጢሞ. 3: 8, 11 እና ከቲቶ 2: 2 ጋር ያመሳክሩ)።
3. ጽድቅ (ትክክል) የሆነውን፡- እግዚአብሔር ሁልጊዜ ትክክል የሆነውን ስለሚያደርግ
ቅዱስ ነው።
4. ንፁህ የሆነውን፡- ሀሳባችንና ባህሪያችን ንጹህ መሆን አለባቸው። የእግዚአብሔርን
ቅዱስ ሕይወት በእምነት እንቀበላለን። ሕይወቱም ንጹሕ ያደርገናል (1 ዮሐ.3፡3ን
ያንብቡ።)
5. ተወዳጅ የሆነውን (ፍቅር ያለበትን)፡- ይህ ቃል በተፈጥሮ ውስጥ ስለምናየው
ውበት ይናገራል። እግዚአብሔር በምድር ላይ ብዙ ውብ ነገሮችን ፈጥሮአል።
6. መልካም የሆነውን፡- መልካም ሰው ደግ፣ ተንከባካቢ እና አፍቃሪ ነው።
እንዲሁም ሁልጊዜ አመስጋኝ ልንሆንባቸው ስለሚገቡን ነገሮች አስቡ።
(ፊል. 4:10–13, 19) ፊል. 4:10–13, 19ን ያንብቡ። ጳውሎስ ደስተኛ እንድንሆን ምን ምክር ይሰጠናል?
አስቸጋሪ ጊዜያት በሚከሰቱበት ጊዜ፣ በእርግጥ አስፈላጊ ስለሆኑ ነገሮች ማሰብ
እንጀምራለን። ረሃብ፣ ህመም፣ ስቃይ እና ማጣት እግዚአብሔር ለሚሰጠን በረከቶች
አመስጋኞች እንድንሆን ይረዱናል። ስናዝን ወይም ስንቸገር በእግዚአብሔር ላይ ያለን
እምነት እንድንጸና ያደርገናል (ፊል. 4፡12)።
እንዲሁም የሚበቃ ወይም ከምንፈልገው በላይ ሲኖረን ሁሉንም ነገር በቅጽበት
ልናጣ እንደምንችል ሁልጊዜ ማስታወስ አለብን (ምሳ. 23፡5ን ያንብቡ)። ኢዮብም ሆነ
ጳውሎስ ስንወለድ ወደ ዓለም ከእኛ ጋር ምንም ነገር እንዳላመጣን ይነግሩናል። ስንሞትም
ከእኛ ጋር ወደ መቃብር የምንወስደው ምንም ነገር የለም (ኢዮ. 1፡21፣ 1 ጢሞ. 6፡7)።
መጽሐፍ ቅዱስ አስደሳች ሕይወት መኖር እንድንችል አስደናቂ ተስፋዎችን
ይሰጠናል። ጥቂቶቹን እንመልከት፡-
•መዝ. 23፡1፡- “እግዚአብሔር እረኛዬ ነው፥ የሚያሳጣኝም የለም”።
•ማቴ. 6፡32፡- “ይህ ሁሉ እንዲያስፈልጋችሁ የሰማዩ አባታችሁ ያውቃልና”።
•1 ጴጥ. 5:7:- “እርሱ ስለ እናንተ ያስባልና የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ
ጣሉት”።
•ፊል. 4፡19፡- “አምላኬም እንደ ባለ ጠግነቱ መጠን በክብር በክርስቶስ ኢየሱስ
የሚያስፈልጋችሁን ሁሉ ይሞላባችኋል”።
በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ከሁሉ የላቀውን ይህን ተስፋ ይሰጠናል፡- “ኃይልን
በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ” (ፊል. 4፡13)። እግዚአብሄር እንዲረዳንና ኃይሉን
እንዲሰጠን ብቻ ሳይሆን፣ እርሱ የሚበጀንን እንዲያደርግልንም ልንጠይቀው ይገባል።
እግዚአብሔር የሚከተሉትን ነገሮች እንዲሰጠን እና የተስፋ ቃሎቹንም እንዲፈጽምልን
ልንጠይቀው እንችላለን፡-
•ቤተሰባችንን እና ጓደኞቻችንን እንዲያድናቸው (1 ጢሞ. 2፡3, 4)።
•እምነታችንን ለማካፈል ድፍረት እንዲኖረን (ራዕ. 22፡17)።
•ይቅር እንዲለን (1 ዮሐ. 1፡9)።
•የእግዚአብሔርን ህግ ለመታዘዝ ኃይል እንዲኖረን (ዕብ. 13፡20, 21)።
•የሚጠሉንንና የሚጎዱንን ሰዎች መውደድ እንድንችል (ማቴ 5፡44)።
•ችግሮቻችንን ለመፍታት ጥበብ እንዲሰጠን (ያዕ. 1፡5)።
•መጽሐፍ ቅዱስን እንድናስተውል ጥበብ እንዲሰጠን (ዮሐ. 8፡32)።
“እግዚአብሔር የሚያስፈልገንን ነገር ሁሉ ያውቃል፤
ይሰጠናልም። አምላክ በሀብት የተሞላ ጎተራ አለው። ከዚያ የምንፈልገውን ሁሉ
ይሰጠናል። ታዲያ ለምንድነው የበለጠ በእርሱ የማንተማመነው? እግዚአብሔር ለልጆቹ
የከበሩ ተስፋዎችን ሰጥቷቸዋል። እግዚአብሔርን ብንታዘዝ ተስፋዎቹን ይፈጽምልናል።
እግዚአብሔር ያለብንን ችግር ሁሉ ያስወግዳል፤ መፍታትም ይችላል። እርሱ ደካማውን
ሰው ብርቱ ያደርገዋል። ፍርሃታችንን ሁሉ ሊያስወግድልን ይችላል። ማንኛውንም
መልካም ነገር እንድናደርግ ሊረዳን ይችላል።
“ስለዚህ ወደ ራሳችን ልንመለከት አይገባም። ስለ ውድቀታችን የበለጠ ባሰብን
ቁጥር፣ የበለጠ እየደከምን እንመጣለን። ያኔ ችግሮቻችንን ለመፍታት አቅም እናጣለን።”-
ኤለን ጂ. ዋይት፣ አውቀው ዘንድ፣ ገጽ 224።
1. እግዚአብሔር ጸሎቶቻችሁን የመለሰበትን ጊዜአቶች አስቡ። እነዚህ ተሞክሮዎች
እግዚአብሔር ጸሎቶቻችሁን የመለሰበትን ጊዜአቶች አስቡ። እነዚህ ተሞክሮዎች
ስለ እግዚአብሔር ሰላም ምን አስተማሯችሁ? እግዚአብሔር እንዲመልስላችሁ
ስለምትጠብቋቸው ጸሎቶችስ? እየጠበቃችሁ ሳለስ እግዚአብሔር በልባችሁ
ሊሰጣችሁ ቃል የገባላችሁ የሰላም ተስፋ እንዴት ሊሰማችሁ ይችላል?
2. መልካም ሀሳቦችን ስለማሰብ ፊል. 4: 8ን ያንብቡ። እያሰባችሁ ጊዜአችሁን
መልካም ሀሳቦችን ስለማሰብ ፊል. 4: 8ን ያንብቡ። እያሰባችሁ ጊዜአችሁን
የምታሳልፉባቸው አንዳንድ መልካም ነገሮች ምንድናቸው ናቸው? እነዚህ ነገሮች
እምነታችሁን የሚያጸኑት እንዴት ነው? ከጌታ ጋርስ ያላችሁን ግንኙነት እንዴት
ያጠነክሩታል?
3. ከላይ ያለውን ከኤለን ጂ. ዋይት የተወሰደውን ጽሑፍ ደግመው ያንብቡት።
ከላይ ያለውን ከኤለን ጂ. ዋይት የተወሰደውን ጽሑፍ ደግመው ያንብቡት።
ስለሚከተሉት አረፍተ ነገሮች ያሰላስሉ፡- “ስለ ውድቀታችን የበለጠ ባሰብን ቁጥር፣
የበለጠ እየደከምን እንመጣለን። ያኔ ችግሮቻችንን ለመፍታት አቅም እናጣለን።”
ታዲያ ችግሮቻችንን ለመፍታት ምስጢሩ ምንድን ነው?