የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ሰማይ እና ምድርን ማስታረቅ
በፊልጵስዩስ እና በቆላስይስ ስለ ኢየሱስ መማር



1ኛ ሩብ ዓመት 2026


ጥር 16 - 22

5ኛ ትምህርት

Jan 24 - 30




በሌሊት የሚያበሩ ከዋክብት



ሰንበት ከሰዓት በኋላ

ለዚህ ሳምንት ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡- ፊል. 2:12, 13, 15-17፣ 2 ጢሞ. 1:5።


የመታሰቢያ ጥቅስ፡ “በመጥፎና በጠማማ ትውልድ መካከል ያለ ነቀፋ የዋሆችም ነውርም የሌለባቸው የእግዚአብሔር ልጆች እንድትሆኑ ሳታንጐራጉሩ ክፉም ሳታስቡ ሁሉን አድርጉ” (ፊል. 2:14, 15)፡፡

እግዚአብሔር ለዕብራውያን ሕጎቹን እንዲታዘዙ ነግሯቸዋል:- “(ሥርዓቴንና ፍርዴን) ጠብቁአት አድርጉአትም፤ ይህችን ሥርዓት ሁሉ ሰምተው በእውነት ይህ ታላቅ ሕዝብ ጠቢብና አስተዋይ ሕዝብ ነው በሚሉ በአሕዛብ ፊት ጥበባችሁና ማስተዋላችሁ ይህ ነውና” (ዘዳ. 4:6)።

ከብዙ መቶ ዓመታት በኋላ፣ ኢየሱስ “እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ። በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትሰወር አይቻላትም” በማለት ተናግሯል (ማቴ. 5:14)። ብርሃን መሆን የምንችለው እንዴት ነው? ከኢየሱስ ጋር ግንኙነት ሊኖረን ይገባል። እርሱ “ለሰው ሁሉ የሚያበራው እውነተኛው ብርሃን ” ነው (ዮሐ. 1፡9)። በተጨማሪም ዮሐ. 8:12ን እና ፊል. 2:9-11ን ያንብቡ።

ኢየሱስ ብርሃኑን ለሁሉም ይሰጣል። እኛ ግን አስቀድመን ህይወታችንን ለእርሱ መስጠት አለብን። ለዚህም ነው ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ሰዎች በጻፈው ደብዳቤ ላይ ያለው መልዕክት ዛሬም ለእኛ እጅግ አስፈላጊ የሆነው። *የሳምንቱን ትምህርት በማጥናት ለሰንበት ይዘጋጁ።

ጥር 17
Jan 25



እግዚአብሔር በልባችን እንዲኖር እና በህይወታችን እንዲሰራ መፍቀድ (ፊል. 2:12, 13)


ጳውሎስ ኢየሱስ ፍጹም ምሳሌያችን ነው ይላል። ኢየሱስ በልቡ ኩራት አልነበረበትም። እግዚአብሔርም ለህይወቱ ያዘጋጀውን እቅድ ታዘዘ። ጳውሎስ የፊልጵስዩስ ሰዎች ወንጌልን ከተቀበሉ በኋላ ስላሳዩት ታዛዥነት አመስግኗቸዋል (ሐዋ. 16:13-15, 32, 35ን ያንብቡ)። መታዘዛቸውንም እንዲቀጥሉ ነግሯቸዋል።

ጳውሎስ አሁንም የኢየሱስን ምሳሌ እንዴት እንደምንከተል ያመለክተናል።

ለመዳን ወደ ኢየሱስ እንመጣ ዘንድ መስቀሉ እንዴት እንደሚያስተምረን ይገልጻል። ጳውሎስ “በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ የራሳችሁን መዳን ፈጽሙ” ሲል ምን ማለቱ ነው? ፊል. 2:12, 13ን ያንብቡ።



በፊል. 2፡12, 13 ላይ ጳውሎስ ስለ ወንጌል አዲስ ወይም የተለየ አስተምህሮ አልሰጠንም። በፊልጵስዩስ የሚገኘው መልካሙ የምሥራች፣ ጳውሎስ በሮሜ መጽሐፍና በሌሎች መልእክቶቹ ውስጥ የጠቀሰው ነው። ስለ አንድ ርዕስ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስናጠና፣ መከተል ያለብን አስፈላጊ መርህ አለ። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ርዕሰ ጉዳዩ የሚናገረውን ሁሉ ማጥናት አለብን። የዚህ ሳምንት ርዕሳችን እግዚአብሔር የሚያድነን እንዴት ነው የሚል ነው። ይህን ርዕስ በተሳሳተ መንገድ መረዳት ቀላል ነው። ስለዚህ ለመረዳት የሚያስቸግር ርዕስ ስናጠና፣ ከላይ የተጠቀሰውን አስፈላጊ መርህ መከተል አለብን ምክንያቱም ርዕሱን በደንብ እንድናስተውል ይረዳናልና። ሮሜ 3:23, 24ን፣ ሮሜ 5:8ን እና ኤፌ. 2፡8-10ን ያንብቡ። እግዚአብሔር እንዴት እንደሚያድነን እነዚህ ጥቅሶች ምን ያስተምሩናል?





እግዚአብሔር በፍቅሩና በምህረቱ እንደሚያድነን ምንም ጥያቄ የለውም።

ራሳችንን ማዳን አንችልም። የራሳችን መልካም ባህሪ ሊያድነን አይችልም። ማመን መቻላችን ራሱ የርሱ ስጦታ ነው። ይህንን ስጦታ የምናገኘው መንፈስ ቅዱስ በልባችን ውስጥ ሲሰራ ነው። መንፈስ ቅዱስ እንድናምን ይረዳናል። እግዚአብሔር አዲስ ልብ ሲሰጠን፣ ባህሪያችን ይለወጣል። ህጉንም መታዘዝ እንችላለን። የእግዚአብሔር መንፈስ ትክክለኛውን ነገር ለማድረግ እንድንመርጥ ይረዳናል። በተጨማሪም ኃጢአትን እምቢ እንድንል መንፈስ ቅዱስ ይረዳናል።

እግዚአብሔር በልባችን እንዲኖር ስንፈቅድለት፣ ሕይወታችንን ይለውጠዋል።

ከዚያም እግዚአብሔርን “በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ (በአክብሮት)” መታዘዝ እንችላለን (ፊል. 2፡12)። ፊል. 2:12 እግዚአብሔርን ልንፈራው ይገባል ማለት ነው? በጭራሽ! እግዚአብሔር የእኛና ከእኛ ጋር መሆኑን ማስታወስ አለብን። እርሱ ሁልጊዜ ይጠነቀቅልናል። ስለዚህ እርሱን ልናከብረውና ልንታዘዘው ይገባናል (መዝ. 2፡11ን ያንብቡ።)

ጥር 18
Jan 26



በሌሊት የሚያበሩ ከዋክብት (ፊል. 2:15, 16)


በፊል. 2፡14 ላይ ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ሰዎች የለገሰው ምክር “ሳታንጐራጉሩ ክፉም ሳታስቡ ሁሉን አድርጉ” የሚል ነው። ሁላችንም የበኩላችንን ጥረት ሳናደርግ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሰላምና አንድነት ሊኖር አይችልም። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሰላምና አንድነት የሚኖረው ከኢየሱስ ጋር ግንኙነት ሲኖረን ነው። በተጨማሪም የእግዚአብሔር ቃል የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስ መታዘዝ አለብን። ያኔ የኢየሱስ ሁነኛ ምስክሮች መሆን እንችላለን። እኛም “በዓለም እንደ ብርሃን እንታያለን” (ፊል. 2፡15)። መጽሐፍ ቅዱስን በቀላሉ ለመረዳት በተዘጋጀው የእንግሊዝኛው ትርጉም “በሌሊት እንደሚያበሩ ከዋክብት” እናበራለን ይላል። ከመንገድ መብራቶች እና ከተማዎች ስንርቅ፣ በሌሊት በሰማይ ላይ ያሉ ከዋክብትን በግልጽ እናያቸዋለን። የጠቆረው ሰማይ ከዋክብትን ደምቀው እንዲያበሩ ያደርጋቸዋል። ሕይወታችንም እንዲሁ ነው። በዙሪያችን ያለው ክፋት ይህችን ምድር ጨለማ ስፍራ ያደርጋታል። በዙሪያችን ያለው ክፋት ሲበዛ፣ ልክ እንደ ደማቅ ከዋክብት እናበራለን። ሌሎች በዙሪያችን ካሉ እግዚአብሔርን ከማያውቁ ሰዎች እጅግ የተለየን መሆናችንን ያያሉ። ጳውሎስ እንደ እግዚአብሔር ልጆች ምን መሆን እንዳለብን ይናገራል? እኛስ ምን ማድረግ አለብን? ፊል. 2:15, 16ን ያንብቡ።



የእግዚአብሔር ልጆች ስለሆንን የተቀደሰ ሕይወት መኖር አለብን። ያን ጊዜ “ያለ ነቀፋ የዋሆችም ነውርም የሌለባቸው የእግዚአብሔር ልጆች እንሆናለን” (ፊል. 2፡15)።

ኢዮብ የኖረው በዚህ መልኩ ነበር (ኢዮ. 1:1, 8ን፣ 2:3ን፣ 11:4ንና 33:9ን ያንብቡ)። የዋህ ሰው ንፁህ ልብ አለው። እንዲህ ያለ ሰው ማንንም አይጎዳም። ለዚህም ነው ኢየሱስ በእምነታችን ምክንያት ለሚያሳድዱን “እንደ ርግብ የዋሆች በመሆን” ማንንም አትጉዱ የሚለን (ማቴ. 10:16)። ጳውሎስ “ለክፉም የዋሆች እንድትሆኑ እወዳለሁ” ሲል ከክፉ ነገር ራቁ ማለቱ ነው (ሮሜ 16፡19)። የዜና አውታሮቻችን ብዙ ጊዜ አሰቃቂ ዘገባዎችን እና ታሪኮችን ያሳዩናል። ስለዚህ ዳዊት የተናገረው ዛሬም ልንከተለው የሚገባ ጠቃሚ መመሪያ ነው፡- “በዓይኔ ፊት ክፉን ነገር አላኖርሁም” ይላልና (መዝ. 101፡ 3)። እንደ እግዚአብሔር ሕዝቦች የተለየን ለመሆን መፍራት የለብንም። እምነታችን ከክፉ ነገር ይለየናል። በጨለማ ሰማይ ውስጥ እንደሚያበሩ ብርሃናት ማብራት አለብን (ፊል. 2፡15)። ይህንን ማድረግ የምንችልበት ብቸኛው መንገድ ክፋትን በመቃወምና እግዚአብሔርን በመታዘዝ ነው (ፊል. 2፡16)። ምርጫዎቻችን የምንኖረው ለኢየሱስ ወይም ለዚህ ሕይወት እንደሆነ ያሳያሉ (ፊል. 2፡16ን፣ ከ1 ቆሮ. 9፡24-27 ጋር ያስተያዩ)። “መንጻት” ያለባቸው የሕይወትዎ ክፍሎች የትኞቹ ናቸው?

ጥር 19
Jan 27

ህያው መስዋዕት (ፊል. 2:17)


ፊል. 2:17ን፣ 2 ጢሞ. 4:6ን፣ ሮሜ 12:1, 2ን እና 1 ቆሮ. 11፡1ን ያንብቡ። እነዚህ ጥቅሶች ምን ያስተምሩናል?





ጳውሎስ ለኢየሱስ መሞትን እንደማይፈራ አስቀድሞ ተናግሯል (ፊል. 1፡20- 23)። አሁን ደግሞ ጳውሎስ “በእምነታችሁ መሥዋዕትና አገልግሎት ተጨምሬ ሕይወቴ እንኳ ቢፈስ፥ ደስ ብሎኛል” ይላል (ፊሊ. 2፡17)። ይህ ምሳሌአዊ አነጋገር በብሉይ ኪዳን ጊዜ ይቀርብ ከነበረው የመጠጥ ቁርባን የተወሰደ ነው። የእግዚአብሔር ሕዝቦች ዘይትን፣ ወይንን ወይም ውኃን ለእግዚአብሔር መስዋዕት አድርገው ያፈሱ ነበር (ዘፍ. 35:14ን፣ ዘጸ. 29:40ን እና 2 ሳሙ. 23:15-17ን ያንብቡ)። ይህ መስዋዕት በአዲስ ኪዳን ማርያም የፈጸመችውን ድርጊት እንድናስታውስ ይረዳናል። ማርያም እጅግ ውድ የሆነ ሽቱ በኢየሱስ ራስና እግር ላይ አፈሰሰች (ማር. 14፡3-9፣ ዮሐ. 12፡3)። በእርግጥ የማርያም ስጦታ እውነተኛ የመጠጥ ቁርባን አይደለም። ሆኖም ስጦታዋ ኢየሱስን ምን ያህል እንደምትወደው ያሳየናል። ስለዚህ የማርያም ስጦታ ኢየሱስ ለኃጢአታችን በመስቀል ላይ ላቀረበው መስዋዕት ፍጹም የሆነ ምሳሌ ነው። ጳውሎስ እግዚአብሔርን በማገልገል ላይ እያለ ቢሰዋ ደስ ይለው ነበር። ሕይወቱም ለእግዚአብሔር እንደ መስዋዕት “ይፈሳል”።

በብሉይ ኪዳን ጊዜ፣ የእግዚአብሔር ህዝቦች ሌሎች ስጦታዎችን የሚያቀርቡት ከመጠጥ ቍርባን ጋር ነበር (ዘኍ. 15፡1-10፣ 28፡1-15ን ያንብቡ)። ስለዚህ የጳውሎስ ሕይወት የፊልጵስዩስ ሰዎች ከሚያቀርቡት ስጦታ ላይ እንደሚጨመር የመጠጥ ቁርባን ነበር።

ስጦታቸው ሕይወታቸው ነበር። የፊልጵስዩስ ሰዎች እግዚአብሔርን ለማገልገል ሙሉ ሕይወታቸውን ሰጥተው ነበር። ሕያው መስዋዕት ነበሩ (ሮሜ 12፡1)። የመጀመሪያዎቹ ክርስቲያኖች ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ እምነታቸውን ያካፍሉ ነበር (ሐዋ. 5፡42)። መስማት ለሚፈልጉ ሁሉ ወንጌልን ተናገሩ። መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ሰዎችን ወደ ቤታቸው ይጋብዟቸው ነበር (ሐዋ. 12:12፣ 1 ቆሮ. 16:19፣ ቆላ. 4:15፣ ፊልሞና 1:1, 2)። ለምን እንዳመኑ ከመጽሐፍ ቅዱስ ምክንያታቸውን ያቀርቡ ነበር (ሐዋ. 17፡11፣ 18፡26፣ 1 ጴጥ. 3፡15)። የአድቬንቲስት እምነት ፈር ቀዳጆችም እንዲሁ ያደርጉ ነበር። እነሱ ቄሶች ሁሉንም ሥራ እንዲሠሩ አይጠብቁም ነበር። ወንጌልን ለጎረቤቶቻቸው ያካፍሉ ነበር። እምነታቸውንም እንዲሁ። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ያካሂዱ ነበር። ቄሱ ተመልሶ ሲመጣ ያጠምቃቸው ዘንድ ሰዎችን ያዘጋጁ ነበር። ባጭሩ የአድቬንቲስት እምነት ፈር ቀዳጆች ሕያው መስዋዕት ነበሩ። እነሱ ያደረጉትን ማድረግ የለብንምን?

ጥር 20
Jan 28

ጢሞቴዎስ መልካምነቱን አሳይቷል (2 ጢሞ. 1:5)


ጳውሎስ ጢሞቴዎስ መልእክቱን ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች እንዲልክ እንደረዳው አስቀድሞ ነግሮናል (ፊል. 1፡1)። አሁን ደግሞ ጳውሎስ ጢሞቴዎስ በአገልግሎቱ በጣም እንዳገዘው ይነግረናል። ጢሞቴዎስ ስለ ኢየሱስ በተለያዩ ከተሞችና ቦታዎች ወንጌልን ሰበከ (2 ጢሞ. 4:5)። ጳውሎስ ጢሞቴዎስን ወደ መቄዶንያ ልኮት ነበር (1 ተሰ. 3፡2፤ የሐዋ. 18፡5ን ከሐዋ. 19፡22 ጋር ያነጻጽሩ)። እንዲሁም ወደ ቆሮንቶስ ብዙ ጊዜ ይልከው ነበር (1 ቆሮ. 16፡10)። ጢሞቴዎስ ከጳውሎስና ከሲላስ ጋር በተሰሎንቄ ሠርቷል (1 ተሰ. 1፡1፣ 2 ተሰ. 1፡1)። በኋላ ላይ ደግሞ ከጳውሎስና ከሲላስ ጋር በኤፌሶን አገልግሏል።

ጳውሎስ “እንደ እርሱ ያለ … ማንም የለኝምና” ይላል (ፊል. 2፡20)። ጢሞቴዎስ በብዙ መልኩ ከጳውሎስ ጋር ተመሳሳይ ነበር። ጢሞቴዎስ ኢየሱስን ይወደው ነበር።

መልካሙን የምሥራች ለሰዎች ለማካፈል በትጋት ይሠራ ነበር። ለፊልጵስዩስ ሰዎች ይጠነቀቅ ነበር። ጳውሎስ ስለ ጢሞቴዎስ ብዙ ጥሩ ነገሮችን የሚናገረው ለምን ይመስልዎታል? ፊል. 2፡19-23ን ያንብቡ። ጳውሎስ ስለ እሱ ሌላ ምን ተናገረ? 1 ቆሮ. 4:17ን እና 2 ጢሞ. 1:5ን ያንብቡ።



ጳውሎስ ጢሞቴዎስ “ከእኔ ጋር ሆኖ ለወንጌል እንደ አገለገለ መፈተኑን ታውቃላችሁ” ይላል (ፊልጵስዩስ 2፡22)። ጢሞቴዎስ ለጳውሎስ እምነት የሚጣልበት ሰው መሆኑን አሳይቷል። ጳውሎስ ጢሞቴዎስ ምን ያህል በትጋት እንደሠራ ተመልክቷል።

ስለዚህ ጳውሎስ በጢሞቴዎስ ሊተማመን እንደሚችል ያውቅ ነበር (ሮሜ 5፡4፣ 2 ቆሮ. 2፡9፣ 2 ቆሮ. 9፡13)።

በህይወት ውስጥ የሚገጥሙን አስቸጋሪ ጊዜያት ፈተናዎቻችን ናቸው። እነዚህ ተሞክሮዎች እኛ ማን እንደሆንንና በልባችን ውስጥ ምን እንዳለ ለሌሎች ያሳያሉ።

ኤለን ጂ. ዋይት እንዲህ ትላለች፡- “የምንፈተንባቸው ገጠመኞች ይኖሩናል። አንዳንዶቹ እንድንናደድ ወይም እንድንበሳጭ ያደርጉናል። ሆኖም አእምሮአችንን ልንስት አይገባም።

የይቅርታና የፍቅር መንፈስ ሲኖረን፣ በልባችን ውስጥ እንደ ኢየሱስ እንሆናለን። ስለዚህ ሰዎች ሲሰድቡን ወይም ሲጎዱን መበሳጨት የለብንም። በፍቅር ቃላት ልንመልስላቸው ይገባል። ክፉ ለሆኑብን ሰዎች ፍቅርን ማሳየት አለብን። ያኔ የኢየሱስ መንፈስ በልባችን ውስጥ እንደሚኖር ለሁሉም እናሳያለን።”—ኤለን ጂ. ዋይት፣ የቤተክርስቲያን ምክሮች፣ ጥራዝ 5፣ ገጽ 344። ስለሚጎዷችሁ ወይም ስለሚያበሳጯችሁ አንዳንድ ነገሮች ያስቡ። በቁጣ ገነፈሉ ወይስ በደስታ ታገሱ? አስቸጋሪ ገጠመኞች እንደ ኢየሱስ ለመሆን እንዴት ያስተምሩዎታል?

ጥር 21
Jan 29

እንደ አፍሮዲጡ የሆኑትን ሰዎች አክብሩ (ፊል. 2፡25-30)


ጳውሎስ ስለ አፍሮዲጡ ምን አለ? አፍሮዲጡ ጠንካራ ክርስቲያን ሠራተኛ መሆኑን የሚያሳይ ምን ነገር አደረገ? ለምላሹ ፊል. 2:25-30ን ያንብቡ።



ጳውሎስ ስለ አፍሮዲጡ ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች ከጻፈው መልእክት ውጭ በሌላ ቦታ ላይ አልተናገረም። ጳውሎስ ከተናገራቸው ቃላት ስለ አፍሮዲጡ ብዙ እንማራለን። አፍሮዲጡ የተባለው የግሪክ ሴት አማልክት ለሆነችው ለአፍሮዳይት ክብር ነው። የአፍሮዲጡ ስም ክርስቲያን ከመሆኑ በፊት የሐሰት አማልክትን ያመልክ እንደነበር ያሳየናል። አፍሮዲጡ ከጳውሎስ ጋር አብሮ እንደሠራ እናውቃለን። ይህም የሆነው በፊልጵስዩስ ሊሆን ይችላል። ጳውሎስ አፍሮዲጡን ከወታደር ጋር ያመሳስለዋል (ከፊል. 1፡27 ጋር ያነጻጽሩ)። እርግጥ ነው፣ አፍሮዲጡ መልካሙን የምሥራች ለማካፈል “ተጋድሏል”። አንዳንድ ጊዜ ልክ እንደ ወታደር አደጋ ይጋረጥበት ነበር። ሆኖም ለጌታ መስዋዕት ለመሆን አልፈራም ነበር (ፊል. 2፡30)። የፊልጵስዩስ ቤተ ክርስቲያንም የእነሱ መልእክተኛ ይሆን ዘንድ አፍሮዲጡን መርጣ ነበር። አፍሮዲጡ ጳውሎስን በእስር ቤት ጎብኝቶ የሚያስፈልገውን ሁሉ አሟላለት (ፊል. 2፡25)። በተጨማሪም የፊልጵስዩስ ሰዎች አፍሮዲጡ ለጳውሎስ ገንዘብ እንዲወስድለት ሰጡት (ፊል. 4፡18)። እነዚህ የገንዘብ ስጦታዎች አስፈላጊ ነበሩ። የሮም እስረኞች የራሳቸውን ምግብ፣ ልብስ፣ ብርድ ልብስና ሌሎች ቁሳቁሶችን መግዛት ነበረባቸው። ያለዚያ እነዚህን ነገሮች እንዲያሟሉላቸው በቤተሰቦቻቸው እና በጓደኞቻቸው ላይ ጥገኛ ይሆኑ ነበር (ከሐዋ. 24፡23 ጋር ያስተያዩ)። ጳውሎስ በሮም ለሁለተኛ ጊዜ የነበረውን የእስር ቆይታ ሊያገባድድ ተቃርቦ ሳለ፣ ጢሞቴዎስን ከክረምት በፊት እንዲመጣና ጳውሎስ በጢሮአዳ የተወውን በርኖስ (ኮት) እንዲያመጣለት ጠየቀው (2 ጢሞ. 4: 21, 13)። ጳውሎስ በቀዝቃዛው የድንጋይ ወኅኒ ቤት ውስጥ ይህ ወፍራምና የሱፍ ኮት ያስፈልገው ነበር። በተጨማሪም ጳውሎስ ደብዳቤውን ወደ ፊልጵስዩስ እንዲወስድለት አፍሮዲጡን ጠየቀው (ኤለን ጂ. ዋይት፣ የሐዋርያት ሥራ፣ ገጽ 479ን ያንብቡ)። በፊልጵስዩስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ችግሮች ነበሩ (4ኛ ትምህርትን ያንብቡ)።

ስለዚህ ጳውሎስ አፍሮዲጡን ሊልከው ከሚፈልገው ጊዜ አስቀድሞ ቶሎ ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች መልሶ ላከው። ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ሰዎች አፍሮዲጡን በጌታ ደስታ እንዲቀበሉት ነገራቸው (ፊል. 2፡29)። ጳውሎስ የፊልጵስዩስ ሰዎች በእስር ቤት ውስጥ በመሆኑ ስለ እሱ እንዳይጨነቁ ማረጋገጥ ፈለገ። በተጨማሪም አፍሮዲጡ የኢየሱስን ምሳሌ ስለ ተከተለ የፊልጵስዩስ ሰዎች እንዲያከብሩት ነገራቸው (ፊል. 2፡6-11፤ ከሉቃ. 22፡25-27 ጋር ያስተያዩ)። “አክብሩ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል በአዲስ ኪዳን ውስጥ ጥቂት ጊዜ ብቻ ጥቅም ላይ ውሏል፡- (1) ለሮማዊው ወታደር (ሉቃ. 7፡2)፣ (2) በበዓል ላይ ለነበሩት እንግዶች (ሉቃ. 14:8) እና (3) ለኢየሱስ (1 ጴጥ. 2:4, 6)።

አፍሮዲጡ በዚህ ልዩ ቡድን ውስጥ ተካትቷል። በሙሉ ልቡ ጌታን አገልግሏልና።

ጥር 22
Jan 30


ተጨማሪ ሀሳብ


“እግዚአብሔር ለእያንዳንዱ ሰው የመጨረሻውን ፈተና የሚሰጥበት ጊዜ በቅርቡ ይመጣል። ሰዎች የአውሬውን ምልክት እንድንቀበል ሊያስገድዱን ይሞክራሉ። በእምነታቸው ደካማ የሆኑ ሰዎች ምልክቱን እንዲቀበሉ ለሚያስገድዷቸው መሪዎች ይታዘዛሉ። ቀስ በቀስ እነዚህ ሰዎች የሰውን ሀሳብ እና ህግጋት ይከተላሉ። ስድብን፣ እስራትን እና ሞትን ይፈራሉ። ስለዚህ የአውሬውን ምልክት በቀላሉ ይቀበላሉ። . . .

“በዚያን ጊዜ ኢየሱስን ከልባቸው የሚያገለግሉት እነማን እንደሆኑ እንመለከታለን። የኢየሱስ እውነተኛ ተከታዮች ከእርሱ ጋር ይቆማሉ። ከእነዚህ ተከታዮች መካከል ብዙዎቹ ለእግዚአብሔር ለመቆም ይፈሩ የነበሩ ናቸው። ብዙም ድፍረት አልነበራቸውም። አሁን ግን ከኢየሱስ እና ከእውነት ጎን መሆናቸውን ያስታውቃሉ።

እጅግ ደካማ እና ፈሪ የነበሩ አባላት እንደ ንጉሥ ዳዊት ደፋር ይሆናሉ። እነዚህ አባላት እግዚአብሔርን ሙሉ በሙሉ ያገለግላሉ። ነገሮች እየከፉ በሄዱ ቁጥር፣ የእግዚአብሔር ሕዝቦች ይበልጥ እንደ ከዋክብት ደምቀው ያበራሉ። ሰይጣን ይዋጋቸዋል፣ ይጎዳቸዋልም። ይሁን እንጂ የእግዚአብሔር ታማኝ ተከታዮች ተጋድሎውን በኢየሱስ ስም ያሸንፋሉ።”—ኤለን ጂ. ዋይት፣ የቤተክርስቲያን ምክሮች፣ ጥራዝ 5፣ ገጽ 81, 82።


የመወያያ ጥያቄዎች




1. “ቀስ በቀስ የሰውን ሃሳብና ህግጋት ስለሚከተሉት” ከላይ ስለተጠቀሱት ሰዎች “ቀስ በቀስ የሰውን ሃሳብና ህግጋት ስለሚከተሉት” ከላይ ስለተጠቀሱት ሰዎች ያስቡ። እነዚህ ሰዎች የሚከተሏቸው የሰው ሀሳቦች እና ደንቦች ምን ይሆናሉ ብለው ያስባሉ? ይህ ማስጠንቀቂያ ለመላው ቤተ ክርስቲያን ጭምር ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው?

2. እግዚአብሔር “ያከበሩኝን አከብራለሁ” ይላል (1 ሳሙ. 2፡30)። እግዚአብሔር “ያከበሩኝን አከብራለሁ” ይላል (1 ሳሙ. 2፡30)። እግዚአብሔርን የምናከብረው በምን አይነት መንገዶች ነው? እግዚአብሔርን ማክበር ለእርሱ ክብር ወይም ምስጋና ከመስጠት ጋር ተመሳሳይ ነው? (ራዕ. 14፡ 7)? መልስዎን ያብራሩ።

3. ጳውሎስ “በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ የራሳችሁን መዳን ፈጽሙ” በማለት ጳውሎስ “በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ የራሳችሁን መዳን ፈጽሙ” በማለት ጽፏል (ፊል. 2፡12)። ለእግዚአብሔር መኖር ማለት በመልካም ባህሪያችን የእግዚአብሔርን ፍቅር እና ይቅርታ ለማግኘት መሞከር ነውን? ለመልስዎ ምክንያቶችን ይስጡ።




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA Union SSL