የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ለዚህ ሳምንት ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡- ፊል. 2:1-8፣ ሮሜ 8፡3።
የመታሰቢያ ጥቅስ፡ “በአንድ አሳብ ተስማሙ፥ አንድ ፍቅር
አንድም ልብ አንድም አሳብ ይሁንላችሁ” (ፊል. 2:2)።
አንድ ስንሆን ጠንካራ እንሆናለን። እንደ ቤተ ክርስቲያን አንድ መሆን እንዳለብን
እናውቃለን። ማወቅ ግን መሆን አይደለም። አንድ ለመሆን እንጥር ይሆናል።
አንዳንዴ ይሳካልናል። ሌላ ጊዜ ደግሞ ሊያቅተን ይችላል። ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ
ሰዎች አንድነታቸው እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ ነግሯቸዋል። ለዚህ ነው ጳውሎስ “በአንድ
አሳብ ተስማሙ፥ አንድ ፍቅር አንድም ልብ አንድም አሳብ ይሁንላችሁ” ያለው (ፊል. 2:2)።
የጳውሎስ የአንድነት አስተምሮ ምንጩ ኢየሱስ ነው። ስለዚህ ጉዳይ
በአዲስ ኪዳን ውስጥ በሁሉም ቦታዎች እናነባለን። የአለመግባባት መንፈስ የት ነው
የተጀመረው? በሰማይ በአንድ መልአክ ልብ ውስጥ ነው የጀመረው። ያ መልአክ
ሉሲፈር ነበር (ኢሳ. 14፡12-14)። ሌሎች መላእክትም የእግዚአብሔርን ሕግና መንግሥት
ለመቃወም ከሉሲፈር ጋር ተባበሩ። ከዚያም በኤደን አዳምና ሔዋን የእግዚአብሔርን
ሕግ ለመቃወም ሉሲፈርን ተባበሩ (ዘፍ. 3፡1-6)።
በዚህ ሳምንት መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ቤተ ክርስቲያን ሰላምና አንድነት
የሚያስተምረውን እንመለከታለን። በተጨማሪም ስለዚህ ጉዳይ ከኢየሱስ የምንማረውን
ትምህርት እናጠናለን።
*የሳምንቱን ትምህርት በማጥናት ለሰንበት ይዘጋጁ።
በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አለመግባባትን የፈጠረው ምን ነበር? ጳውሎስ ችግሩን የሚፈታው ምንድን ነው አለ? ፊል. 2:1-3ን ያንብቡ።
እርግጥ ነው በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የነበረው ችግር ጳውሎስን አሳዝኖታል።
በፊልጵስዩስ የነበረችውን ቤተ ክርስቲያን የመሠረታት ጳውሎስ ስለነበር፣ ቤተ
ክርስቲያኗን በጣም ይወዳት ነበር። አዎን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የነበረው ግጭት
ልቡን አቁስሎታል። በሮም እንደነበሩት የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ራስ ወዳድ ወይም
ትዕቢተኞች እንዳይሆኑ ጳውሎስ የፊልጵስዩስን ሰዎች ያስጠነቅቃቸዋል (ፊል. 1፡16)።
እነዚህ መሪዎች የበለጠ የሚጨነቁት ፊተኛ ወይም ታዋቂ ለመሆን ነበር። የኢየሱስን
ወንጌል ለመደገፍ ደንታ አልነበራቸውም።
ጳውሎስ ራስ ወዳድ የሆነ ልብ እንዳይኖረንና ትዕቢት እንዳያጠቃን ያስጠነቅቀናል
(ገላ. 5፡20)። በተጨማሪም ያዕቆብ “ቅንዓትና አድመኛነት ባሉበት ስፍራ በዚያ ሁከትና
ክፉ ስራ ሁሉ አሉ” ይላል (ያዕ. 3፡16)። የሚታበዩ ሰዎች ራሳቸውን ከሚገባቸው በላይ
አስፈላጊ እንደሆኑ አድርገው ያስባሉ። ለዚህም ነው ጳውሎስ ለገላትያ ሰዎች በጻፈው
ደብዳቤ ላይ “እርስ በርሳችን እየተነሣሣንና እየተቀናናን በከንቱ አንመካ” የሚለው (ገላ.
5: 26) ። ጳውሎስ እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ማድረግ ስላለብን ነገሮች ይዘረዝራል፡-
1. የኢየሱስን ምሳሌ መከተል፡- ጳውሎስ በልብ ውስጥ ያሉ ኃጢአቶችን ድል
ለመንሳት የኢየሱስ ሕይወት እንዴት ያለ ሁነኛ ምሳሌ እንደሆነ ያሳያል።
2. ፍቅር፡- ኢየሱስ የእግዚአብሔርን ፍቅር ገልጦልናል። እርሱም “እኔ እንደ ወደድኋችሁ
እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ ትእዛዜ ይህች ናት” ይለናል (ዮሐ. 15፡12)።
3. ከመንፈስ ቅዱስ ጋር መተባበር፡- መንፈስ ቅዱስ የቤተ ክርስቲያን አባላትን ልብ
ለልብ እንዲቀራረቡ ይረዳቸዋል። የቀደመችው ቤተ ክርስቲያን ይህንን የጠበቀ
ህብረት ተለማምዳ ነበር (ሐዋ. 2፡42፣ ከ2 ቆሮ. 13፡14 ጋር ያነጻጽሩ)።
4. ትሁት ልብ፡- ኢየሱስ በህይወቱ ፍቅርንና ይቅር ባይነትን አሳይቷል (ማቴ. 9:36ን፣
ማቴ. 20:34ን እና ማር. 1:41ን ያንብቡ)። የመልካሙን ሳምራዊ (ሉቃ. 10፡33) እና
የጠፋውን ልጅ (ሉቃ. 15፡20) ስዕላዊ ታሪኮች በመጠቀም ስለ ፍቅርና ይቅርታ
አስተምሯል።
5. ርኅራኄ፡- ኢየሱስ በምድር ሲመላለስ ርኅሩኅ ነበር። የተከታዮቹም ሕይወት
ርኅራኄን ሊያሳይ ይገባዋል (ሉቃ. 6፡36)።
6. ሰላም እና አንድነት፡- ጳውሎስ “በክርስቶስ ኢየሱስ የነበረ ይህ አሳብ በእናንተ
ዘንድ ደግሞ ይሁን” እንዳለው እንዲሁ ልናደርግ ይገባል (ፊል. 2፡5)።
የሃይማኖት መሪዎች ባህሪና ድርጊት አስፈላጊ መሆናቸውን ያስተምሩ ነበር።
ነገር ግን ኢየሱስ መልካም ባህሪ ሰውን ንፁህና የዋህ አያደርገውም አለ። ክፉ ነገሮች
የሚመነጩት በልብና በአእምሮ ውስጥ ነው። ይህንን ትምህርት ስለ ባለጠጋው ወጣት
በተናገረው ታሪክ ውስጥ እናያለን። ይህ ወጣት በህይወት ዘመኑ ሁሉ ሕጉን እንደጠበቀ
ለኢየሱስ ነገረው። ስለዚህ ኢየሱስ ባለጠጋውን ወጣት በልቡ ውስጥ ያለውን ነገር
ያሳየው ዘንድ ፈተነው። ኢየሱስ ባለጠጋውን ወጣት ያለውን ሁሉ እንዲሸጥ፣ ገንዘቡን
ለድሆች እንዲሰጥ እና እንዲከተለው ጠየቀው። በተጨማሪም ኢየሱስ “ከልብ
ክፉ አሳብ፥ መግደል፥ ምንዝርነት፥ ዝሙት፥ መስረቅ፥ በውሸት መመስከር፥ ስድብ
ይወጣልና” አላቸው (ማቴ. 15:19)።
በቤተ ክርስቲያን ሰላምና አንድነት እንዲኖር ምን ማድረግ አለብን? ፊል. 2:3, 4ን
ያንብቡ።
የጳውሎስ ምክር ልባችንን ከትዕቢት ማጥራትን ያካትታል። እኛ ከሌሎች ሰዎች
ይልቅ የበለጠ አስፈላጊ ነን ብለን ማሰብ የለብንም። ደግሞም ለራሳችን ብቻ ሳይሆን
ለሌሎች ሰዎች ፍላጎትም ልንጠነቀቅ ይገባል። ከማድረግ ይልቅ መናገር ይቀላል፤
አይደለም እንዴ? ነገር ግን እነዚህን አስፈላጊ መርሆዎች ብንከተል፣ ግንኙነታችንን ሁሉ
ለማሻሻል ይረዱናል። ማድመጥንም መማር አለብን። ብዙ ጊዜ ስንነጋገር፣ እኛ ብቻ
ማውራት እንፈልጋለን። ነገር ግን ሌላው የሚናገረውን ለመረዳት መጀመሪያ ማዳመጥ
አለብን። ሌሎች እንዲረዱአችሁ ከመጠበቃችሁ በፊት፣ እነሱን ለመረዳት ሞክሩ።
አስቀድመን ካዳመጥን ብዙ ግጭቶችንና አለመግባባቶችን ማስወገድ እንችላለን።
ሁልጊዜ ላንስማማ እንችላለን። ሆኖም አስቀድመን ስናዳምጥ እና ሌላውን ሰው ለመረዳት
ስንሞክር፣ በግንኙነታችን እና በቤተ ክርስቲያናችን ጤናማ ተግባቦትንና መተማመንን
ማዳበር እንችላለን።
ጳውሎስ በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ስለሚመጣው አንድነት ይናገራል (ኤፌ.
4፡3)። ይህ አንድነት የሚያስተሳስር ሰላም እንዲኖረን ያደርጋል (ኤፌ. 4፡3)። በቤተ
ክርስቲያን ውስጥ የምንጠላላ ከሆነ፣ ይህንን ለማርገብ መንፈስ ቅዱስ ይረዳናል።
መንፈስ ቅዱስ ሰላምን ያመጣል። በተጨማሪም ጳውሎስ ስለ ኢየሱስ እና ስለ እምነታችን
አስተምህሮዎች መስማማት እንደሚያስፈልገን ተናግሯል (ኤፌ. 4፡13)። ኢየሱስንና
አስተምህሮውን ስናውቅ፣ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እውነት ተመሳሳይ ግንዛቤ ይኖረናል።
ይህ ግንዛቤ ሲኖረን፣ ቤተ ክርስቲያን አንድ ትሆናለች።
በዓለም ዙሪያ ያሉ ብዙ ኩባንያዎች ኮምፒውተሮችን ከሰው አእምሮ ጋር ለማገናኘት እየሞከሩ ነው። ልሂቃን ኮምፒውተሮችን በመጠቀም ሃሳባችንን ለመለወጥ ይፈልጋሉ። ከእነዚህ ፈጠራዎች መካከል አንዳንዶቹ ሰዎች በሽታን ይቆጣጠሩ ዘንድ ይረዷቸዋል ብለው ተስፋ ያደርጋሉ። በእርግጥም ጥሩ ሀሳብ ነው አይደል? ነገር ግን እነዚህ ኮምፒውተሮች የሰውን አእምሮ መጥፎ በሆኑ መንገዶች ለመቆጣጠር ጥቅም ላይ ሊውሉ እንደሚችሉ ያስቡ። በብዙ መንገዶች አእምሯችን ልክ እንደ ኮምፒውተር ነው የሚሰራው - የተሻለ ነው እንጂ። በየቀኑ አዳዲስ መረጃዎች፣ እውቀቶች እና ሀሳቦች ወደ አእምሯችን ይገባሉ። ይህም መረጃ ሀሳባችንን እና ባህሪያችንን ሊቀይረው ይችላል። ቴሌቪዥን በብዛት ስንመለከት፣ ሰዎች ምን እንደሚያደርጉ እና እንደሚያስቡ እናያለን። ብዙም ሳይቆይ እንደ ተዋናዮቹ ማሰብ እና ማድረግ እንጀምራለን። በተወሰነ መልኩ ሀሳባቸው በአእምሯችን ውስጥ “የተተከለ” ይመስላል። ኢየሱስ መንፈስ ቅዱስ አእምሮአችንን እንዲቆጣጠረው እንድንፈቅድለት ይፈልጋል (ሮሜ 8፡6)። አዎን መንፈስ ቅዱስ እንዲቆጣጠረን መፍቀድ እንችላለን። ያለዚያ የሰው ሃሳብ ይቆጣጠረናል (1 ቆሮ. 2፡11, 12)። አስተማሪያችን ማን ይሆን? ምንስ እየተማርን ነው? “እንደ ክርስቶስ ኢየሱስ ማሰብና ማድረግ” ማለት ምን ማለት ነው? (ፊል. 2:5ን ያንብቡ)
ዞሮ ዞሮ ምን ማሰብ እንዳለብን የምንወስነው እኛ ነን። ግን ልባችንን መለወጥ
አንችልም። ሊለውጠን የሚችለው እግዚአብሔር ብቻ ነው። መንፈስ ቅዱስ በልባችን
ላይ “ንቅለ ተከላ” እንደሚያደርግ ሐኪም ነው። በልባችን ውስጥ ያለውን እናይ ዘንድ
እንዲረዳን መንፈስ ቅዱስ የሚጠቀመው ኃይለኛ መሣሪያ መጽሐፍ ቅዱስ ነው።
“የእግዚአብሔር ቃል ሕያው ነውና፥ የሚሠራም፥ ሁለትም አፍ ካለው ሰይፍ ሁሉ
ይልቅ የተሳለ ነው፥ ነፍስንና መንፈስንም ጅማትንና ቅልጥምንም እስኪለይ ድረስ
ይወጋል፥ የልብንም ስሜትና አሳብ ይመረምራል” (ዕብ. 4:12)። ያለ መንፈስ ቅዱስ
እርዳታ ትክክለኛ ማንነታችንን ማወቅ አንችልም። የገዛ ልባችን ያታልለናል (ኤር. 17፡
9)። “ማታለል” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል “አኮቭ” ነው። ይህ ቃል
እንድንሰናከልና እንድንወድቅ የሚያደርግ ጎርባጣ መንገድ ማለት ነው። መጽሐፍ ቅዱስ
ይህንን ቃል የሚጠቀመው የራሳችንን ሐሳብ ልናምነው እንደማንችል ለማስረዳት ነው።
መጀመሪያ ልባችንና አእምሮአችን መለወጥ አለበት። “የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም
በጎና ደስ የሚያሰኝ ፍጹምም የሆነው ነገር ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ
በልባችሁ መታደስ ተለወጡ እንጂ ይህን ዓለም አትምሰሉ” (ሮሜ 12፡2)።
መሐመድ አሊ “በምድር ላይ ምርጡ ቦክሰኛ እኔ ነኝ” በማለት በጉራ ተናግሯል።
በጎርጎርዮስ አቆጣጠር በ1963 አሊ የአለም አቀፍ የቦክስ ሻምፒዮናን አሸነፈ። ከስድስት
ወራት በፊት አሊ “ከማንም በላይ ምርጡ እኔ ነኝ” የሚል ሪከርድ የሆነ አልበም ሰርቶ
ነበር። በእርግጥ አሊ በጣም ጥሩ ቦክሰኛ ነበር። ሆኖም እሱ ክርስቲያኖች ሊከተሉት
የሚገባ ምሳሌ አይደለም፤ በተለይ እንደ ኢየሱስ ማሰብ የሚፈልጉ ከሆነ። ኢየሱስ
ፍጹምና ኃጢአት የሌለበት ነበር። ኢየሱስ “ከኃጢአት በቀር በነገር ሁሉ እንደ እኛ
የተፈተነ ነው እንጂ፥ በድካማችን ሊራራልን የማይችል ሊቀ ካህናት የለንም” (ዕብ.
4:15)። ኢየሱስ በሃሳቡ አልበደለም። ይሁን እንጂ ኢየሱስ “ከተቀበለው መከራ መታዘዝን
ተማረ” (ዕብ. 5:8)። ምንም እንኳን መታዘዝ ቀላል ባልነበረበትም ጊዜ፣ ኢየሱስ ሁልጊዜ
አባቱን ታዘዘ።
ፊል. 2፡5-8ን ያንብቡ። ጳውሎስ በእነዚህ ውብ እና አስደናቂ ጥቅሶች ውስጥ ምን
እያለን ነው? እኛንስ ምን ያስተምሩናል? ይህንን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት በሕይወታችን
ውስጥ የምንተገብረው እንዴት ነው?
ኢየሱስ እግዚአብሔር ነው። እርሱ ግን ሰው ሆነ። ከዚህም በላይ ኢየሱስ
አገልጋይ ሆነ። በፊል. 2፡5-8 “አገልጋይ” የሚለው ቃል የመጣው “ዱሉ” ከሚለው
ቃል ነው። በእንግሊዘኛ ቋንቋ “ዱሉ” ማለት ባሪያ ማለትም ነው። ኢየሱስ ሰው እና
አገልጋይ ከሆነ በኋላ፣ ራሱን ስለ ኃጢአታችን መስዋዕት አድርጎ ሰጠን! ጳውሎስ በፃፈው
በሌላኛው ደብዳቤ ላይ “በእንጨት የሚሰቀል ሁሉ የተረገመ ነው ተብሎ ተጽፎአልና
ክርስቶስ ስለ እኛ እርግማን ሆኖ ከሕግ እርግማን ዋጀን” ይላል (ገላ. 3፡13)። የፈጠረን
አምላክ በመስቀል ላይ ሞተልን። ስለዚህ እርሱ አዳኛችን ነው። ያድነን ዘንድ ደግሞ
ኢየሱስ ስለ እኛ የተረገመ መሆን ነበረበት።
ጳውሎስ የሚናገረውን ማስተዋል የምንችለው እንዴት ነው? በእነዚህ ጥቅሶች
ላይ እንድናደርግ የሚነግረንን እንዴት ልንተገብረው እንችላለን? እንደ ኢየሱስ ልባችንን
ከትዕቢት ነፃ በማድረግ፣ ህይወታችንን ሌሎችን ለማገልገል አሳልፈን ለመስጠት ፈቃደኞች
መሆን የምንችለው እንዴት ነው? በተጨማሪም ኢየሱስ እንዲህ ብሏል:- “ከእናንተም
የሚበልጠው አገልጋያችሁ ይሆናል። ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳል፥ ራሱንም
የሚያዋርድ ሁሉ ከፍ ይላል” (ማቴ. 23:11, 12)። እነዚህ ቃላት በፊል. 2፡5-8 ያለውን
የጳውሎስን መልዕክት የበለጠ እንድናስተውል ይረዱናል።
ኢየሱስ ሰው ለመሆን የተወው ምን ነበር? ሮሜ 8:3ን፣ ዕብ. 2:14-18ን እና ዕብ. 4፡15ን ያንብቡ።
የእግዚአብሔር ልጅ የሆነው ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስ እርዳታ የሰው ልጅ ሆነ።
ይህ እንዴት ሊሆን ቻለ? ዘላለማዊ የሆነው አምላከ እንዴት ሟች ሊሆን ቻለ? ይህ ጳውሎስ
“እግዚአብሔርንም የመምሰል ምሥጢር ያለ ጥርጥር ታላቅ ነው” (1 ጢሞ. 3፡16) ያለው
ነው። የአምልኮ ሕይወታችን ምስጢርም ይሄው ነው።
በፊል. 2 ላይ ጳውሎስ ኢየሱስ ከእኛ እንደ አንዱ ይሆን ዘንድ ስላደረጋቸው
ነገሮች ሰፋ አድርጎ ይናገራል።
1. “እርሱ በእግዚአብሔር መልክ” ይኖር ነበር (ፊል. 2፡6)። “በእግዚአብሔር መልክ”
የሚለው ሀረግ ‘ሞርፌ’ ከሚለው የግሪክ ቃል የመጣ ነው። ‘ሞርፌ’ ኢየሱስ
እግዚአብሔር መሆኑን ያሳያል (ከዮሐ. 1፡1 ጋር ያነጻጽሩ)።
2. “ሰማይን ለመተው መረጠ” (ፊል. 2፡7)። “የባሪያን መልክ ይዞ … ራሱን ባዶ አደረገ”
(ፊል. 2:7)። እግዚአብሔር የሆነው ኢየሱስ ሥልጣኑንና ክብሩን ትቶ ሰው ሆነ።
ኢየሱስ ሰይጣን ኃጢአት እንድንሠራ ሲፈትነን የሚሰማን ስሜት ይገባዋል።
3. “ራሱን አዋረደ” (ፊል. 2፡8)። ኢየሱስ ሰው መሆን ብቻ ሳይሆን አገልጋይ ሆነ።
ኢየሱስን ከሉሲፈር ጋር ያነጻጽሩ። ኢየሱስ ለማገልገል መጣ፣ ነገር ግን ሉሲፈር
የበላይ ለመሆን ፈለገ።
4. “ለሞትም ይኸውም የመስቀል ሞት እንኳ የታዘዘ ሆነ” (ፊል. 2፡8)። ኢየሱስ
ይኖርበት በነበረው ዘመን እጅግ አስከፊው ሞት በመስቀል ላይ መሰቀል ነበር።
ኢየሱስ ይህን ሞት ሊሞት መረጠ። እግዚአብሔር አብ እና ኢየሱስ የመስቀሉን ሞት
አስቀድመው “የሰላም ምክር” በማድረግ አቅደውት ነበር (ዘካ. 6፡13)። ኢየሱስ
በመስቀል ላይ ከመሞቱ ከብዙ መቶ አመታት በፊት አብ እና ኢየሱስ እቅዳቸውን
ለእስራኤላውያን ገልጸውላቸዋል። በዓላማ ላይ ተሰቅሎ የነበረው እባብ የኢየሱስ
ሞት ምሳሌ ነበር። ሙሴ ይህን እባብ ከናስ ሠርቶ በምድር ላይ ከፍ አድርጎ በዓላማ
ላይ ሰቀለው። ይህ እባብ ኢየሱስ ወደዚህ ምድር መጥቶ የሚሰራውን የማዳን ሥራ
ያሳይ ነበር (ዘኁ. 21፡9፣ ዮሐ. 3፡14)። ጳውሎስ “እኛ በእርሱ ሆነን የእግዚአብሔር
ጽድቅ እንሆን ዘንድ ኃጢአት ያላወቀውን እርሱን ስለ እኛ ኃጢአት አደረገው”
በማለት ገልጾታል (2 ቆሮ. 5:21)።
“የኢየሱስ ተማሪዎች መሆን አለብን። ከአዳኛችን ምን
እንማራለን? ልባችን በትዕቢት እንዲሞላ ያስተምረናልን? እኛ ድንቅና ከሌሎች የተሻልን
መሆናችንን እንማራለንን? በጭራሽ! ኢየሱስ ባስተማረን ቁጥር፣ ልባችንን ከትዕቢት
እንዲጸዳ እናደርገዋለን። ሊታወቅ የሚገባውን ሁሉ እንደምናውቅ ማሰብ የለብንም።
እግዚአብሔር ክህሎቶችንና መክሊቶችን ሰጥቶናል። እነዚህን ስጦታዎች ለርሱ ክብር
እንዴት እንጠቀምባቸዋለን? እግዚአብሔር ለውጦን ዘላለማዊ ሰውነት ሲሰጠን፣
በምድር ላይ የተማርናቸውን መልካም ነገሮች አንረሳቸውም። ይህንን እውቀት ይዘን
ነው ወደ ሰማይ የምንሄደው። በዚያም ከኢየሱስ ጋር ለዘላለም እንኖራለን። ስለ ኢየሱስ
እና ስለ ማዳን ስራው ለዘላለም እናጠናለን።”—ኤለን ጂ. ዋይት፣ ጽሑፍ 36፣ 1885።
1. ስለ እግዚአብሔር ፍቅር ምን ተምረዋል? የእግዚአብሔር ፍቅር ተጨባጭ
ስለ እግዚአብሔር ፍቅር ምን ተምረዋል? የእግዚአብሔር ፍቅር ተጨባጭ
መሆኑን የሚያሳይ ምን ተሞክሮ አለዎት? በክፍላችሁ ስለ እግዚአብሔር ፍቅር
የተማራችሁባቸውን የተለያዩ መንገዶች ተነጋገሩ።
2. ኢየሱስ “የባሪያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ” ሲል ምን
ኢየሱስ “የባሪያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ” ሲል ምን
ማለቱ ነው? (ፊል. 2:7) ከሮሜ 8፡3 ጋር በማነጻጸር ተወያዩበት። እነዚህ
ሁለት ጥቅሶች የሚያመሳስላቸውና የሚያለያያቸው ምንድነው? ሁለቱም ጥቅሶች
ስለ ኢየሱስ ምን ያስተምሩናል?
3. በዚህ ሳምንት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሰላምና አንድነት እንደሚያስፈልግ
በዚህ ሳምንት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሰላምና አንድነት እንደሚያስፈልግ
አጥንተናል። ቤተ ክርስቲያንዎን ሰላምና አንድነት እንዳይኖራት የሚያደርጓት
ችግሮች ምንድን ናቸው? ጳውሎስ ችግር ሲያጋጥመን ሊረዱን የሚችሉ አንዳንድ
ጠቃሚ ምክሮችን ሰጥቶናል:- “ለወገኔ ይጠቅማል በማለት ወይም በከንቱ ውዳሴ
ምክንያት አንድ እንኳ አታድርጉ፥ ነገር ግን እያንዳንዱ ባልንጀራው ከራሱ ይልቅ
እንዲሻል በትሕትና ይቍጠር” (ፊል. 2:3)። እንደ ቤተ ክርስቲያን ይህ ምክር
ችግሮቻችንን ለመፍታት እንዴት ሊረዳን ይችላል?