የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ሰማይ እና ምድርን ማስታረቅ
በፊልጵስዩስ እና በቆላስይስ ስለ ኢየሱስ መማር



1ኛ ሩብ ዓመት 2026


ጥር 2 - 8

3ኛ ትምህርት

Jan 10 - 16




ሕይወት እና ሞት



ሰንበት ከሰዓት በኋላ

ለዚህ ሳምንት ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡- ፊል. 1:19-24, 27፣ 2 ቆሮ. 10:3-6።


የመታሰቢያ ጥቅስ፡ “ለእኔ ሕይወት ክርስቶስ፥ ሞትም ጥቅም ነውና” (ፊል. 1:21)።

ብዙ ጊዜ ሰዎች ሞት የሕይወት ተፈጥሯዊ ክፍል እንደሆነ ይናገራሉ። ያ ግን ስህተት ነው። ሞት እና ህይወት በጭራሽ የተለያዩ ናቸው። ሞት የሕይወት “ጠላት” ነው። የተገጨ መኪና ክፍሎቹ በአዲስ መኪና ውስጥ እንደማይገቡ ሁሉ፣ ሞትም የህይወት አንዱ ክፍል አንዲሆን “አልተደረገም”። ጳውሎስ ኢየሱስ የሞተው “በሞት ላይ ሥልጣን ያለውን ዲያብሎስን ለመሻር ነው። በሕይወታቸውም ሁሉ ስለ ሞት ፍርሃት በባርነት ይታሰሩ የነበሩትን ሁሉ ነጻ ያወጣቸዋል” በማለት ተናግሯል (ዕብ. 2:14, 15)።

ጳውሎስ ለኢየሱስ ለመሞት ዝግጁ ነበር። ስለ ወደፊቱም እርግጠኛ ነበር።

እስከዚያው ድረስ ግን ለጳውሎስ እጅግ ወሳኙ ነገር ኢየሱስን ማክበር ነበር። ጳውሎስ በተቻለ መጠን ለብዙ ሰዎች መልካሙን የምሥራች ለመስበክ ፈልጎ ነበር። ጳውሎስ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ብዙ ደብዳቤዎችን የጻፈበት አንዱ ምክንያት ይህ ሊሆን ይችላል። በደብዳቤዎቹ በሕይወት ዘመኑ በአካል ሊጎበኛቸው ከሚችላቸው በላይ ብዙ ሰዎችንና ቦታዎችን መድረስ ችሏል።

ህይወት አጭር ናት። የምንችለውን ያህል ለእግዚአብሔር መንግሥት ማገልገል አለብን። የአገልግሎታችን ዋንኛው ክፍል ሰላምና አንድነት ነው። እንደ ቤተ ክርስቲያን አባላት፣ በምናምንባቸው ነገሮች ላይ መስማማት አለብን። ያኔ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሰላምን እናገኛለን። በዚህ ሳምንት ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ሰዎች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሰላምና ስምምነት ለምን አስፈላጊ እንደሆነ የጻፈውን እንመለከታለን። *የሳምንቱን ትምህርት በማጥናት ለሰንበት ይዘጋጁ።

ጥር 3
Jan 11



ኢየሱስን አብዝቶ ማክበር (ፊል. 1:19, 20)


ፊል. 1:19, 20ን ያንብቡ። ጳውሎስ ፍርድ ቤት ሲቀርብ ምን ይደርስብኛል ብሎ ጠብቆ ነበር? ከእስር ቤት ከመውጣት የበለጠ አስፈላጊው ነገር ምንድን ነው ብሎ ያስብ ነበር?



ጳውሎስ የደረሰበትን ሥቃይ ከሌሎች ክርስቲያኖች የህይወት ተሞክሮ ጋር አነጻጽሮታል። “በድካም አብዝቼ፥ በመገረፍ አብዝቼ፥ በመታሰር አትርፌ፥ በመሞት ብዙ ጊዜ ሆንሁ። አይሁድ አንድ ሲጎድል አርባ ግርፋት አምስት ጊዜ ገረፉኝ። ሦስት ጊዜ በበትር ተመታሁ፤ አንድ ጊዜ በድንጋይ ተወገርሁ፤ መርከቤ ሦስት ጊዜ ተሰበረ፤ ሌሊትና ቀን በባሕር ውስጥ ኖርሁ። ብዙ ጊዜ በመንገድ ሄድሁ፤ በወንዝ ፍርሃት፥ በወንበዴዎች ፍርሃት፥ በወገኔ በኩል ፍርሃት፥ በአሕዛብ በኩል ፍርሃት፥ በከተማ ፍርሃት፥ በምድረ በዳ ፍርሃት፥ በባሕር ፍርሃት፥ በውሸተኞች ወንድሞች በኩል ፍርሃት ነበረብኝ፤ በድካምና በጥረት ብዙ ጊዜም እንቅልፍ በማጣት፥ በራብና በጥም ብዙ ጊዜም በመጦም፥ በብርድና በራቁትነት ነበርሁ።” (2 ቆሮ. 11:23–27)። በተጨማሪም ጳውሎስ “የቀረውንም ነገር ሳልቆጥር፥ ዕለት ዕለት የሚከብድብኝ የአብያተ ክርስቲያናት ሁሉ አሳብ ነው” ይላል (2 ቆሮ. 11፡28)። ጳውሎስ ከመሠረታቸው አብያተ ክርስቲያናት ጋር ምን አይነት ግንኙነት ነበረው? ጳውሎስ በኢየሱስ እንዲያምኑ ካደረጋቸው ሰዎች ጋር የነበረው ግንኙነት ምን ነበር? 1 ቆሮ. 4:14-16ን፣ 1 ተሰ. 2:10, 11ን፣ ገላትያ. 4:19ን፣ እና ፊል. 10ን ያንብቡ።



ኢየሱስ እኛን ለማዳን ያለውን ሁሉ ሰጠ። በተመሳሳይ መንገድ፣ ጳውሎስ ለቤተ ክርስቲያን አባላት፡- “እኔ ግን ስለ ነፍሳችሁ በብዙ ደስታ ገንዘቤን እከፍላለሁ፥ ራሴን እንኳ እከፍላለሁ (አሳልፌ እሰጣለሁ)” ብሏቸው ነበር። ኢየሱስ እንደኖረ በኖርን ቁጥር፣ አንዳንድ ሰዎች ላይወዱን ይችላሉ። ለዚህ ነው ጳውሎስ “በእውነትም በክርስቶስ ኢየሱስ እግዚአብሔርን እየመሰሉ ሊኖሩ የሚወዱ ሁሉ ይሰደዳሉ” (2 ጢሞ. 3፡12) በማለት ያስጠነቀቀን። ነገር ግን ለምናምነው ነገር መከራን ለመቀበል ፍቃደኛ ስንሆን፣ ሕይወታችን የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ግሩም በሆነ ሁኔታ ያሳያል (ከፊል. 1፡7 ጋር ያነጻጽሩ)። “ጳውሎስ በእስር ቤት ሆኖም ታጋሽና ደስተኛ ነበር። ድፍረቱና እምነቱ አስደናቂ ስብከት ነበር።”⎯ኤለን ጂ፣ ዋይት፣ የሐዋርያት ሥራ፣ ገጽ 464።

ጥር 4
Jan 12

ሞትም በረከት ነው (2 ቆሮ. 10:3-6)


ክርስቲያኖች በመሆናችን በመልካም እና በክፉ መካከል በሚደረገው ዓለም አቀፋዊ ተጋድሎ ተካፋዮች ነን። ይህ ተጋድሎ በዙሪያችን እየተካሄደ ነው። በእኛም ሕይወት ይካሄዳል። እኛም በየቀኑ የዚህ ተጋድሎ አካል ነን። እስከ ዕለተ ሞታችን ድረስም ተጋድሎው ይቀጥላል። ይህንን ተጋድሎ የምንጋፈጠው ለምንድን ነው? በዚህ ተጋድሎ የምንጠቀማቸው መሳሪያዎች ምንድን ናቸው? 2 ቆሮ. 10፡3-6ን ያንብቡ።



መልካምም ይሁኑ ክፉ፣ በጣም ኃይለኛ መንፈሳዊ መሳሪያዎች ሀሳቦች ናቸው።

ሰይጣን ሰዎችን ለማታለል የተሳሳቱ ሀሳቦችን ይጠቀማል። በተጨማሪም የሰይጣን “መሳሪያዎች” ክፉና አጸያፊ ቃላትን፣ ታማኝ አለመሆንንና ቃል ማጠፍን፣ ኃፍረትን፣ ፍርሃትን እና ሌሎች ብዙ መጥፎ ነገሮችን ያጠቃልላል። ክርስቲያኖች ሌሎች ሰዎችን ለመጉዳት ማንኛውንም ክፉ ነገር መጠቀም የለባቸውም፤ ፍቅርን፣ ምሕረትን፣ ሰላምን፣ ገርነትን፣ ታጋሽነትን፣ ቸርነትን እና መሻትን መግዛትን እንጂ። እጅግ ኃይለኛው መሣሪያችን መጽሐፍ ቅዱስ ነው። መጽሐፍ ቅዱስን በጥበብ መጠቀም አለብን፤ ለዚህም መንፈስ ቅዱስ ይረዳናል (ኤፌ. 6፡17)። አንድ ሰው የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት እንዲያምን ሊያደርግ የሚችለው እግዚአብሔር ብቻ ነው። እኛ የሱ መልክተኞች ነን።

እግዚአብሔር ሥራውን ለመስራት ይጠቀምብናል። ፊል. 1:21, 22ን ያንብቡ። በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ የጳውሎስን ሐሳብ እንዴት እንረዳዋለን? ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት በእግዚአብሔር እና በሰይጣን መካከል ያለውን ዓለም አቀፋዊ ተጋድሎ የበለጠ እንድናስተውለው የሚረዳን እንዴት ነው?



ዓለም አቀፋዊው ተጋድሎ መንፈሳዊ ውጊያ ነው። የምንዋጋው የሃሳብና የእምነት ጦርነትን ነው። ኢየሱስ በመስቀል ላይ ስለ እኛ ይህን ገድል አሸንፏል። ከኢየሱስ ጋር እስከተጣበቅን ድረስ፣ ብንሞትም እንኳን አንሸነፍም። ጳውሎስ በዚህ ምድር ሳለ የሚደርስበትን ማንኛውንም ነገር ሁሉ ተቀብሏል። ሕይወቱን ለእግዚአብሔር አደራ ሰጠ። በሰማያዊው የፍርድ አደባባይ የሱ ዳኛ ጌታ ነበር። እግዚአብሔር ፍትሃዊ ውሳኔ እንደሚሰጠው ታምኖ ነበር። ስለዚህ ጳውሎስ ስለ ወደፊቱ አልተጨነቀም ነበር።

እንደ ክርስቲያን ሰዎች የኛ “ባለዕዳዎች” ስለሆኑ ወይም “ስለተጋፉን” ለመብታችን መታገል የለብንም። መጋደል ያለብን ትክክለኛ ስለሆነው ነገር ነው።

በተጨማሪም በሁሉም ነገር እግዚአብሔርን መታዘዝ አለብን። ከክፉ ጋር በምናደርገው ተጋድሎ ማሸነፍ የምንችለው እግዚአብሔርን በመታዘዝ ብቻ ነው። ምሳሌያችን የሆነው ኢየሱስ በሁሉም ነገር እግዚአብሔርን ታዘዘ። ጳውሎስ ስለዚህ ጉዳይ በፊልጵስዩስ 2 ላይ የበለጠ ይናገራል። በመልካም እና በክፉ መካከል ያለው ዓለም አቀፋዊ ተጋድሎ፣ አሁን በህይወትዎ ውስጥ እየተካሄደ ያለው እንዴት ነው? ከክፉው ጋር ያለውን ተጋድሎ ኢየሱስ አሸንፏል። ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ተስፋ የሚሰጥዎት እንዴት ነው?

ጥር 5
Jan 13

በእግዚአብሔር ተስፋዎች መታመን (ፊል. 1:21-24)


ፊል. 1:21-24ን ያንብቡ። ጳውሎስ “ለእኔ ሞትም ጥቅም ነው” ሲል ምን ማለቱ ነው? (ፊል. 1:21)?





ብዙ ሰዎች ፊል. 1፡21-24ን በተሳሳተ መንገድ ይረዱታል። በእነዚህ ጥቅሶች፣ ጳውሎስ መኖርን ከመሞት ጋር ያነጻጽረዋል። ክርስቲያን የሚኖረው ለኢየሱስ ነው፤ ለእርሱም ሊሞት ይችላል። ለኢየሱስ ከሞትን፣ ያ ለእኛ “መልካም” ነው። ሰዎች ለኢየሱስ ለመሞት ዝግጁ መሆናችንን ሲመለከቱ፣ ሞታችን ስለ እምነታችን ኃይለኛ ስብከት ይሆናል (ፊል. 1፡21)። ስለዚህ ጳውሎስ ሲሞት ወዲያውኑ ወደ ሰማይ እንደሚሄድ እየተናገረ አይደለም። ስንሞት ምንም ነገር አናውቅም። ኢየሱስ እስኪያነቃቸው ድረስ ሙታን በመቃብር ውስጥ ያርፋሉ (መክ. 9:5ን እና ዮሐ. 5: 28, 29ን ያንብቡ)። ለዚህም ነው አልዓዛር ከሞተ በኋላ፣ ኢየሱስ “ወዳጃችን አልዓዛር ተኝቶአል፤ ነገር ግን ከእንቅልፉ ላስነሣው እሄዳለሁ” ያላቸው (ዮሐ. 11:11)።

ሰዎች እንደሞቱ ወዲያውኑ ወደ ሰማይ የሚሄዱ ቢሆንስ? ይህ ለምስኪኑ አልዓዛር ምን ሊመስል እንደሚችል በአእምሮዎ ያስቡ። በሰማይ ከአራት አስደሳች ቀናት በኋላ፣ አንድ መልአክ “መጥፎ” ዜና ይዞ ወደ አልዓዛር መጣ። “አዝናለሁ አልዓዛር።

ኢየሱስ ወደ ምድር እንድትመለስ እየጠየቀህ ነው። እዚህ መቆየት አትችልም!”

በእርግጥ ይህ ታሪክ ትንሽ ሞኝነት ሊመስል ይችላል፤ አይደለም እንዴ? ሆኖም ሰዎች ሲሞቱ ወደ ሰማይ ይሄዳሉ የሚለው አስተሳሰብ ለምን የተሳሳተ እንደሆነ እንድንገነዘብ ይረዳናል። ሞት ህልም የሌለበት እንቅልፍ ነው። ኢየሱስ በዳግም ምጽአቱ ተከታዮቹን ከዚህ እንቅልፍ ይቀሰቅሳቸዋል። ከዚያም ኢየሱስ በምድር ላይ በሕይወት ከሚቆዩት ተከታዮቹ ጋር ወደ ሰማይ ይወስዳቸዋል (1 ተሰ. 4:16, 17). በተጨማሪም ጳውሎስ:- “በመሥዋዕት እንደሚደረግ፥ የእኔ ሕይወት ይሠዋልና፥ የምሄድበትም ጊዜ ደርሶአል” ይላል (2 ጢሞ. 4: 6)። በእግዚአብሔርም ጸጋ ከሞት እንደሚነሳ ተናግሯል (ፊል. 3፡11)። ከዚያም ኢየሱስ ጳውሎስንና ሁሉንም የእግዚአብሔርን ህዝቦች በሰማይ ወደ አዘጋጀላቸው ቤት ይወስዳቸዋል (ዮሐ. 14:3፣ 1 ቆሮ. 2:9).

ጳውሎስ ለኢየሱስ ሊሞት ተዘጋጅቶ ነበር። ሆኖም በሕይወት መቆየቱ ለፊልጵስዩስ ሰዎች እንደሚሻል ያውቅ ነበር (ፊል. 1፡24)። ለኢየሱስ መኖር ወይስ ለእርሱ መሞት ይሻለናል? ይህን ጥያቄ መመለስ ቀላል አይደለም። ጳውሎስ “በእነዚህም በሁለቱ እጨነቃለሁ” በማለት ለመወሰን መቸገሩን ተናግሯል (ፊል. 1፡23)። ሁለቱም አማራጮች መልካም ሆነው ታይተውት ነበር (ፊል. 1፡23)።

ጥር 6
Jan 14



በአንድ መንፈስ ጸንታችሁ ቁሙ (ፊል. 1፡27)


ኢየሱስ ለተከታዮቹ ያቀረበው የመጨረሻ ጸሎት ስለ ሰላምና አንድነት ነበር። ኢየሱስ እንዲህ ሲል ጸለየ:- “አባት ሆይ፥ ዓለም ሳይፈጠር ስለ ወደድኸኝ የሰጠኸኝን ክብሬን እንዲያዩ እኔ ባለሁበት የሰጠኸኝ እነርሱ ደግሞ ከእኔ ጋር ይሆኑ ዘንድ እወዳለሁ” (ዮሐ. 17:24)። በተጨማሪም ኢየሱስ “ቅዱስ አባት ሆይ፥ እነዚህን የሰጠኸኝን እንደ እኛ አንድ እንዲሆኑ በስምህ ጠብቃቸው” ብሎ ጠየቀው (ዮሐ. 17:11)።

ደግሞም ኢየሱስ ተከታዮቹ አንድ ካልሆኑ ምን እንደሚፈጠር ተናግሯል። ሌሎች ሰዎች መልካሙን የምሥራች ላለማመን አለመግባባታችንን እንደ ምክንያት ሊጠቀሙበት ይችላሉ። በዮሐንስ 17 ላይ በጸለየው ጸሎት ኢየሱስ ሁለት ጊዜ ከእርሱና ከአብ ጋር ሊኖረን ስለሚገባው ሰላምና አንድነት ተናግሯል። በዚያን ጊዜ “አንተ እንደ ላክኸኝ ዓለም ያምናል፣ ያውቃልም” ይላል (ዮሐ. 17፡21, 23)። ፊል. 1:27ን ያንብቡ። ይህንን ጥቅስ ከዮሐ. 17፡17-19 ጋር ያነጻጽሩ። ኢየሱስም ሆነ ጳውሎስ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሰላምና አንድነት እንዲኖረን የሚነግሩን ምንድን ነው?



በፊል. 1: 27 ላይ “እንደሚገባ ኑሩ” የሚሉት ቃላት “ፖሊቲዮማይ” ከሚለው የግሪክ ቃል የተወሰዱ ናቸው። እነዚህ ቃላት እንደ እግዚአብሔር መንግሥት “ዜጋ መኖር” የሚል ትርጉም አላቸው። በማቴዎስ 5-7 ያለው የኢየሱስ ስብከት የእግዚአብሔር ልጆች እና የሰማይ መንግስት ዜጎች መሆን ማለት ምን ማለት እንደሆነ ይነግረናል።

የእግዚአብሔር ልጆች በልባቸው ውስጥ ትዕቢት የለባቸውም። የዋህ ናቸው። የተቀደሰ ሕይወትን ለመኖር ይራባሉ፣ ይጠማሉም። ይቅር ባይ ናቸው። ልባቸው ንጹህና የዋህ ነው። ሰላምን ያመጣሉ ወይም ያስታርቃሉ። ሌሎች ሰዎችን አይጣሉም ወይም አይጎዱም። ጠላቶቻቸውን ይወዳሉ። የሚረግሟቸውን ይመርቃሉ። እነሱን ለሚጠሉአቸው መልካም ያደርጋሉ። ባጭሩ በሚክ. 6:8 ላይ “ፍርድን ታደርግ ዘንድ፥ ምሕረትንም ትወድድ ዘንድ፥ ከአምላክህም ጋር በትሕትና ትሄድ ዘንድ” የሚለውን ይተገብራሉ።

ብዙ ጊዜ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አለመግባባት የሚፈጠረው ከትዕቢት የተነሳ ነው። “ትዕቢትና የዓለም ፍቅር ልባችንን ሲሞላ፣ የኢየሱስ መንፈስ ይለየናል።

ከዚያም ጠብና አለመግባባት ቤተ ክርስቲያንን ያዳክማታል።”—ኤለን ጂ. ዋይት፣ የቤተ ክርስቲያን ምክሮች፣ ጥራዝ 5፣ ገጽ 240, 241።

ጥር 7
Jan 15

ያለ ፍርሃት አንድ የሆነች ቤተ ክርስቲያን (ፊል. 1፡27-30)


ፊል.ስ 1:27-30ን ያንብቡ። እንደ ቤተ ክርስቲያን ሰላምና አንድነት ያለ ምንም ፍርሃት መልካሙን የምሥራች ለሌሎች እንድናካፍል የሚረዳን እንዴት ነው?



የሰይጣን አላማ አንዳችንን ከሌላችን መለያየት ነው። ያኔ ከእኛ ጋር የሚያደርገውን ተጋድሎ ማሸነፍ ይችላል። ኢየሱስ “ቤትም እርስ በርሱ ከተለያየ፣ ያ ቤት ሊቆም አይችልም” ብሎ ተናግሯል (ማር. 3፡25)። እንደ እግዚአብሔር የመጨረሻ ዘመን ቤተ ክርስቲያን፣ ሰላምና አንድነታችን የኢየሱስን ወንጌል እንድናውጅ ይረዳናል (ራዕ. 12፡17፤ 14፡6)። በዮሐንስ 17 ላይ ያለው የኢየሱስ ጸሎት፣ መጽሐፍ ቅዱስ በሰላምና በአንድነት እንድንኖር እንደሚረዳን ያስተምረናል (ዮሐንስ. 17፡17, 19)። እንደ ቤተ ክርስቲያን፣ በመጨረሻው ዘመን በምድር ላይ ላሉ ሁሉ የምናካፍለው የተለየ መልዕክት አለን።

ለዚህ ልዩ መልእክት ስኬት እና እንደ ቤተ ክርስቲያን ለምንሰራው ሥራ ሰላማችንና አንድነታችን አስፈላጊ ነው። አንድ ከሆንን የምንፈራው ነገር የለም (ፊል. 1፡28)።

ሰይጣን ተሸንፏል። ኢየሱስ በመስቀሉ ቀጥቅጦታል። ለእምነታችን ብንሞት እንኳን፣ ጽድቅን ካደረግን ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን የሚችል አንዳች ነገር የለም (ሮሜ 8፡ 36-39፣ 1ጴጥ. 3፡13)። ዲያብሎስ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ሊገታው አይችልም። ማቴ. 10:38ን፣ ሐዋ. 14:22ን፣ ሮሜ 8:17ን እና 2 ጢሞ. 3:12ን ያንብቡ። እነዚህ ጥቅሶች ስለ የትኛው አስፈላጊ ርዕሰ ጉዳይ ነው የሚናገሩት?





ይህች ምድር በኃጢአት ተሞልታለች። እንደ ኢዮብ “ምርጥ” ለሆነው እንኳን ሕይወት ከባድ ነው። ኢዮብ ቅዱስ ነበር። እግዚአብሔር ኢዮብ “ፍጹምና ቅን፥ እግዚአብሔርንም የሚፈራ፥ ከክፋትም የራቀ ነበረ” ብሎ ተናግሯል (ኢዮ. 1፡1)።

ይሁን እንጂ በአንድ ጀንበር ኢዮብንና ቤተሰቡን ከባድ አደጋ አጋጠማቸው። እንደ ኢዮብ በምድር ላይ ሕይወት ከባድ መሆኑን ያልተረዳ ማን አለ? መጥፎ ነገሮች መቼ እንደሚከሰቱ አናውቅም። በዚህ ምድር የሚኖር ሰው ሁሉ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ይሰቃያል። ከምንም ነገር ይልቅ ስለ ኢየሱስ መከራ ብንቀበል ይሻለናል። እንደ ክርስቲያን በመከራ ውስጥ ብናልፍ እንኳን ምን ተስፋ አለን?

ጥር 8
Jan 16




ተጨማሪ ሀሳብ


“ዛሬ ቤተ ክርስቲያናችን ብዙ የተለያዩ መንፈሳዊ ስጦታዎች አሏት። በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ይህን ያህል ልዩ ልዩ ስጦታዎች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አልነበሩም። በአዲስ ኪዳን ዘመን ቤተ ክርስቲያን ሰላምንና አንድነትን ለማጽናት የመንፈስ ቅዱስ ሥጦታዎች አስፈልጓት ነበር። ዛሬም ለሰላምና ለአንድነት እነዚህ ስጦታዎች ያስፈልጉናል! መጽሐፍ ቅዱስ በግልፅ እንደሚያሳየው ለመጨረሻው ዘመን ቤተ ክርስቲያን አባላት የእግዚአብሔር ዕቅድ በሰላምና በአንድነት እንዲተሳሰሩ ነው።

ኢየሱስ ዳግም ከመምጣቱ አስቀድሞ፣ በመጨረሻው ዘመን የቤተ ክርስቲያን መሪዎች እርስ በርሳቸው እንደሚስማሙ መጽሐፍ ቅዱስ ተስፋ ሰጥቶናል። በተጨማሪም በመጨረሻው ዘመን ጠቢብ የሆኑት የእግዚአብሔር ህዝቦች ማስተዋል ይኖራቸዋል።

ያን ጊዜ የእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ሰላምንና አንድነትን ትጎናጸፋለች። ነገሮችን በትክክል ከተረዳናቸው፣ እርስ በርሳችን እንስማማለን። . . . ይህ ፍጹም ሰላምና አንድነት በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚመጣበትን ጊዜ እየተጠባበቅን ነው። ይህ ጊዜ ገና አልደረሰም፤ ወደፊት ግን ይሆናል። ስለዚህ እግዚአብሔር የሰጠን መንፈሳዊ ስጦታዎች አንድ እስክንሆን ድረስ ሥራቸውን መቀጠል አለባቸው።”—አር. ኤፍ. ኮትሬል፣ “መግቢያ”፣ በኤለን ጂ. ዋይት፣ ቀደምት ጽሑፎች፣ ገጽ 140።


የመወያያ ጥያቄዎች




1. መንፈስ ቅዱስ ልባችንን በሰላምና በአንድነት መንፈስ እንዲሞላ ዛሬ በቤተ መንፈስ ቅዱስ ልባችንን በሰላምና በአንድነት መንፈስ እንዲሞላ ዛሬ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ምን መደረግ አለበት? በኤለን ጂ. ዋይት ጽሑፎች እግዚአብሔር ለቤተ ክርስቲያኑ ማስጠንቀቂያ እና ምክር ሰጥቷል። ይህንን ምክር መተግበር በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሰላምና አንድነት ይኖረን ዘንድ የሚረዳን እንዴት ነው?

2. ጳውሎስና የሞቱ ክርስቲያኖች አሁን ከኢየሱስ ጋር በሰማይ እንዳሉ የሚያምን ጓደኛ ጳውሎስና የሞቱ ክርስቲያኖች አሁን ከኢየሱስ ጋር በሰማይ እንዳሉ የሚያምን ጓደኛ አለህ እንበል። ለዚህ ጓደኛህ ስለ ሞት የሚናገረውን የመጽሐፍ አስተምሮ እንዴት ታስረዳዋለህ?

3. በዚህ ሕይወት ሰዎች የሚሠቃዩት ለምንድን ነው? በመልካምና በክፉው መካከል በዚህ ሕይወት ሰዎች የሚሠቃዩት ለምንድን ነው? በመልካምና በክፉው መካከል ያለው ዓለም አቀፋዊ ተጋድሎ የዚህን ጥያቄ መልስ ለማስተዋል የሚረዳን እንዴት ነው? በመስቀል ላይ ወደ ተሰቀለው ኢየሱስ ስንመለከት፣ እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ፍቅር እንመለከታለን። ይህ ፍቅር በመከራችን እንድንጸና የሚረዳን እንዴት ነው? በአስከፊ ጊዜአቶቻችን እንኳን በእግዚአብሔር መታመንን መማር ያለብን ለምንድን ነው?




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA Union SSL