የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ሰማይ እና ምድርን ማስታረቅ
በፊልጵስዩስ እና በቆላስይስ ስለ ኢየሱስ መማር



1ኛ ሩብ ዓመት 2026


መጋቢት 5 - 11

12ኛ ትምህርት

Mar 14 - 20




ከሌሎች ጋር አብሮ መኖር



ሰንበት ከሰዓት በኋላ

ለዚህ ሳምንት ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡- ቆላ. 3:18, 19፣ ምሳ. 22:6, 15፣ ቆላ. 3:22–25፣ ቆላ. 4፡2-4።


የመታሰቢያ ጥቅስ፡ “ለእያንዳንዱ እንዴት እንድትመልሱ እንደሚገባችሁ ታውቁ ዘንድ ንግግራችሁ ሁልጊዜ፥ በጨው እንደ ተቀመመ፥ በጸጋ ይሁን” (ቆላ. 4፡6)።

የቅርብ ግንኙነት ያላቸው ሰዎች አብረው በሚኖሩበትና በሚሰሩበት ጊዜ፣ እርስ በእርሳቸው ችግር ሊገጥማቸው ይችላል። አንዳንድ ጊዜ ሊጨቃጨቁ ወይም ላይስማሙ ይችላሉ። ስለዚህ በግንኙነቱ ውስጥ ያለ እያንዳንዱ ሰው ተስማምቶ ለመኖር የተቻለውን ሁሉ ማድረግ ይጠበቅበታል። እርግጥ ነው እጅግ የቀረበ ግንኙነት ያለን ከቤተሰብ አባላት ጋር ነው። ቤት አንዳንድ ጊዜ “የቤተሰብ ንግድ (ጉዳይ)” ተብሎ ይጠራል። ምክንያቱም ንግድና ቤትን ማስተዳደር የሚያመሳስላቸው ብዙ ነገሮች ስላሉ ነው። የቤተሰብ አባላት ስለሚያምኑባቸው ነገሮችና እቅዶቻቸው መስማማት አለባቸው።

ሁሉም ሰው እርስ በርሱ መግባባት አለበት። ቤትን የተሳካና ደስተኛ ለማድረግ ሁሉም የቤተሰብ አባላት የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል። ቤተ ክርስቲያንስ? ቤተ ክርስቲያን በእርግጥም ትልቋ ቤተሰብ ነች። ስለዚህ በቤተ ክርስቲያንም ስኬትና ደስታን ለማግኘት ጠቃሚ የሆኑ ተመሳሳይ መርሆዎች መከበር አለባቸው።

በዚህ ሳምንት መሪ ጥቅሳችን ላይ፣ ጳውሎስ የክርስቲያን ቤተሰብ በሚገባ ተስማምቶ ይኖር ዘንድ አንዳንድ ጠቃሚ መርሆዎችን ይሰጠናል። የክርስቲያን ቤት የመጽሐፍ ቅዱስን መርሆዎች መከተል ይኖርበታል። እርግጥ ነው ጳውሎስ በሚኖርበት ዘመን፣ የክርስቲያኖች ቤት ከሮማውያን ቤት የተለየ ነበር። በተጨማሪም ጳውሎስ በቤትም ሆነ ከቤት ውጭ ለሚኖረን ግንኙነት አጋዥ የሆኑ ሌሎች ጠቃሚ የመጽሐፍ ቅዱስ መርሆዎችን ሰጥቶናል። *የሳምንቱን ትምህርት በማጥናት ለሰንበት ይዘጋጁ።

መጋቢት 6
Mar 15

ባሎችና ሚስቶች (ቆላ. 3:18, 19)


አዲስ ኪዳን ለክርስቲያን ቤቶች ጥሩ ምክሮችን ያካትታል (ኤፌ. 5፡21–6፡9ን፣ ቆላ. 3፡18–4፡1ን፣ ቲቶ 2፡1–10ን እና 1 ጴጥ. 2፡18–3፡7ን ያንብቡ)። እነዚህ ምክሮች “የቤት መርሆዎች” ተብሎው ሲሰየሙ የቤተሰብ ራስ ማን እንደሆነ የሚናገሩ ብቻ አይደሉም። በተጨማሪም መርሆዎቹ ቤተሰቦች ግንኙነታቸውን ደስተኛና ጤናማ ለማድረግ የሚረዱ ምክሮችን ያካትታሉ። ቆላ. 3:18, 19ን ያንብቡ። ጳውሎስ በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ የሚሰጣቸው ምክሮች ምንድናቸው? በኤፌ. 5: 22–25, 33 ላይ ጳውሎስ የሚጨምራቸው ሌሎች ምክሮች ምንድናቸው?



ብዙ ባሎች “ሚስቶች ሆይ፥ ለባሎቻችሁ ተገዙ” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ይወዱታል (ቆላ. 3፡18)። ነገር ግን እነዚህ ሰዎች “ለጌታ እንደሚገባ” ታዘዟቸው የሚለውን የጥቅሱን ክፍል ይዘሉታል። አዲስ ኪዳን ሴቶች ወንዶችን ሁሉ መታዘዝ እንዳለባቸው በየትኛውም ቦታ አያስተምርም። በተጨማሪም አዲስ ኪዳን ሴቶች እንደ ባሪያዎች እንዲሆኑ ወይም ባሎቻቸው የሚፈልጉትን ወይም የሚጠይቁትን ሁሉ እንዲያደርጉ አያስተምርም። ጳውሎስ እያለ ያለው ሚስት በመጀመሪያ ለጌታ፣ ቀጥሎም ለባለቤቷ ታማኝ መሆን አለባት ነው (ኤፌ. 5፡22)። ባል የሚስቱን ስብዕና (ማንነት) በራሱ ቁጥጥር ስር ማድረግ የለበትም። እንዲሁም ትክክል ወይም ስህተት የሆነውን ሊወስንላት አይገባም። መጽሐፍ ቅዱስ እና መንፈስ ቅዱስ ለራሷ እንድትወስን ይረዷታል።

ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያንን ስለወደዳት ያድናት ዘንድ ነፍሱን አሳልፎ ሰጥቷል።

የኢየሱስ ፍቅር ባሎች ሚስቶቻቸውን እንዴት መውደድ እንዳለባቸው ያሳያል (ኤፌ. 5፡25)። ባሎች በሚስቶቻቸው ላይ መማገጥ የለባቸውም። የጋብቻ ቃል ኪዳናቸውን ማክበር አለባቸው። ባሎች ለሚስቶቻቸው በረከት የሚሆኑ ውሳኔዎችን ይወስናሉ።

ባል ሚስቱን በዚህ መንገድ ከወደዳት፣ እሱን እንድታከብር የታዘዘችውን ትእዛዝ እንድትፈጽም ይረዳታል (ኤፌ. 5፡33)።

ጤናማ በሆነ የክርስቲያን ትዳር ውስጥ ባልና ሚስት እንደ ባለትዳር ነገሮችን አብረው ያደርጋሉ። እንደ ባለትዳር ውሳኔዎችን አብረው ይወስናሉ፤ እቅዶችንም አብረው ያወጣሉ። አንዳንድ ጊዜ ልጆቻቸውን በውይይቶቻቸውና በእቅዶቻቸው ውስጥ ማካተት ይኖርባቸው ይሆናል። ነገር ግን ወላጆች በልጆቻቸው ፊት መጋጨት ወይም መጨቃጨቅ የለባቸውም። ባልና ሚስት መስማማት ባይችሉስ? መጽሐፍ ቅዱስ ምን ማድረግ እንዳለብን ይነግረናል። እቅዶቹ ከመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ጋር እስካልተጣረሱ ድረስ፣ ሚስት የባሏን ውሳኔ መቀበል አለባት። ይህ ምክር ለቤተሰቡ ሰላምን ያመጣል።

በተመሳሳይም ብዙ ባሎች ሚስቶቻቸው በጥበብ የተሞሉ ምክሮች የሰጡባቸውን ጊዜያቶች ሊያስታውሱ ይችላሉ። ባልና ሚስት አብረው በህብረት ሲሠሩ፣ ትዳራቸው በደስታ የተሞላ ይሆናል።

መጋቢት 7
Mar 16

ወላጆችና ልጆች (ምሳ. 22:6, 15)


ልጆች አስፈላጊ የቤተሰብ አባላት ናቸው። ልጆች ወላጆቻቸው እንደሚወዷቸው ማወቅ አለባቸው። ወላጆችም ልጆቻቸውን እግዚአብሔር እንደሚወዳቸው ማስተማር አለባቸው። እግዚአብሔር ልጆችን የሰማይ መንግሥት ዜጎች እንዲሆኑ ይፈልጋል።

ስለዚህ የቤተሰብ አምልኮ አስፈላጊ ነው። ቤተሰቦች በየዕለቱ ጧትና ማታ አብረው ማምለክ አለባቸው። ገና በለጋነታቸው ልጆች ቤትን በማጽዳትና ሌሎች ሥራዎችን በመስራት እንዲያግዙ ሊማሩ ይገባል። ከሁሉም በላይ ደግሞ “ልጆች ሆይ፥ ይህ ለጌታ ደስ የሚያሰኝ ነውና በሁሉ ለወላጆቻችሁ ታዘዙ” የሚለውን የጳውሎስን ምክር መታዘዝ አለባቸው (ቆላ. 3:20)። የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ። እነዚህ ጥቅሶች ልጆቻችንን ስለማሳደግ ወይም ስለማሰልጠን ምን ጠቃሚ የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎችን ያስተምሩናል? ምሳ. 22:6, 15



ማቴ. 19፡14



ዘዳ. 6:6, 7



ምሳ. 1:8, 9



ወላጆች ልጆቻቸውን እንዴት መኖር እንዳለባቸው ማሳየት አለባቸው።

በተጨማሪም ለልጆቻቸው የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ማስተማር አለባቸው። ወላጆች ልጆቻቸውን ጌታን እንዲከተሉ ሲያሠለጥኗቸው፣ ልጆች ለቤተሰብ፣ ለቤተ ክርስቲያን እና ለማህበረሰቡ በረከት ይሆናሉ። ጳውሎስ ወላጆችን በቁጣ እንዳያስተምሩና እንዳይቀጡ ያስጠነቅቃቸዋል። “አባቶች ሆይ፥ ልባቸው እንዳይዝል ልጆቻችሁን አታበሳጩአቸው” (ቆላ. 3:20)። ስለዚህ ወላጆች ልጆቻቸውን ሲያስተምሩና ሲቀጡ አፍቃሪ መሆን አለባቸው።

ከእናት ይልቅ አባት ልጆች የተሳካ መንፈሳዊ ሕይወት እንዲኖራቸው ትልቅ ድርሻ አለው።

ጥናቶች እንደሚያሳዩት ሁለቱም ወላጆቻቸው ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚሄዱ ከሆነ፣ ልጆቹም ሲያድጉ ወደ ቤተ ክርስቲያን መሄዳቸውን ይቀጥላሉ። አባታቸው በየሳምንቱ ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚሄድ ከሆነ፣ ልጆቹ ጎልማሳም ሆነው በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ይመላለሳሉ። ስለዚህ አባቶች በቤተሰባቸው ውስጥ ጠንካራ መንፈሳዊ መሪዎች እንዲሆኑ የተቻላቸውን ሁሉ ማድረግ አለባቸው።

መጋቢት 8
Mar 17

አብሮ መስራት (ቆላ. 3፡22-25)


ቆላ. 3፡22–25ን እና ቆላ. 4፡1ን ያንብቡ። ጳውሎስ በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ ለባሪያዎች ምን ምክሮችን ሰጥቷል? እነዚህ ጥቅሶች ከሰዎች ጋር አብሮ ለመሥራት የሚረዱ ምን ጠቃሚ መመሪያዎችን ያስተምሩናል?





ዛሬ ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ አንዳንድ ክፍሎችን ላለመቀበል ስለ ባርነት የተጻፉ ርዕሶችን እንደ ምክንያት አድርገው አንዳንድ ጊዜ ይጠቀማሉ። ነገር ግን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያለውን ስለ ባርነት የተጻፈውን ርዕስ ስናጠና፣ በብሉይም ሆነ በአዲስ ኪዳን ያለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ መዳሰስ አለብን። መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር ሰዎችን በራሱ አምሳል እንደፈጠራቸው ያስተምራል። የፈጠረንም ነፃነት ያለን እንድንሆን አድርጎ ነው። ለዚህም ነው የሙሴ ህግ እስራኤላውያን ለዘላለም ባሪያዎች እንዳይሆኑ ያዘዘው (ዘዳ. 15፡12)። አንድ ሰው ከስድስት ዓመት በላይ ባሪያ ሊሆን አይችልም ነበር።

አንድ ሰው የተበደረውን ገንዘብ ሁሉ ለመክፈል መስራት የሚጠበቅበት ቢበዛ ስድስት ዓመት ነበር (ዘጸ. 21፡2–6፣ ዘሌ. 25፡39–43)። በአዲስ ኪዳን ዘመን የነበረው ባርነት በእኛ ዘመን ካለው ባርነት ጋር ተመሳሳይ አልነበረም። ባለፉት ጥቂት መቶ ዓመታት የነበረው ባርነት በቃላት ለመግለጽ የሚዘገንን ወንጀል ነው።

በአዲስ ኪዳን ዘመን፣ ቤተ ክርስቲያን የሮምን ህግ መከተል ነበረባት። የሮም ሕግ ዜጎቿ ባሮች እንዲኖሯቸው ይፈቅድ ነበር። ሆኖም የሮም ሕግ ለባሮችም ብዙ መብቶችን ወይም ፈቃዶችን ይሰጣቸው ነበር። እነዚህ መብቶች መደበኛ ዜጎች ያደርጓቸው የነበረውን ብዙ ተመሳሳይ ነገሮችን ለማድረግ ፈቃድና ህጋዊ ስልጣንን ያካትቱ ነበር።

ክርስቲያኖች በአዲስ ኪዳን ዘመን ባርነትን ለማጥፋት ቢሞክሩ ኖሮ፣ ጥረታቸው እግዚአብሔር እንዲሠሩ የሰጣቸውን ሥራ ይጎዳው ነበር። እንደ ቤተ ክርስቲያን አባል፣ ባሪያ መጀመሪያ ለእግዚአብሔር ታማኝ መሆን ነበረበት። ክርስቲያን ጌቶችም ለባሪያዎቻቸው ፍትሃዊና ደግ መሆን ነበረባቸው። ጳውሎስ ጌቶችን “እናንተ ደግሞ በሰማይ ጌታ እንዳላችሁ ታውቃላችሁ” ይላቸዋል (ቆላ. 4፡1)። በተጨማሪም ጳውሎስ የቤተ ክርስቲያን አባል ለነበረው ለፊልሞና፣ አናሲሞስን ከእንግዲህ እንደ ባሪያው አድርጎ እንዳይቆጥረው ነግሮታል። በእርግጥ አናሲሞስ ባሪያ ነበር። ነገር ግን አናሲሞስና ፊልሞና ክርስቲያኖች ነበሩ። ስለዚህ ጳውሎስ ፊልሞናን አናሲሞስን እንደ ወንድሙ እንዲወደው ነግሮታል (ፊልሞና 1፡16)። በብሉይም ሆነ በአዲስ ኪዳን የእግዚአብሔር ሰዎች የአምላክ ባሪያዎች ወይም አገልጋዮች ተብለው እንደሚጠሩ ያውቃሉ? (መዝ. 34:22ን፣ ሉቃስ 17:10ን እና 1 ጴጥ. 2:16ን ያንብቡ) ይህም ኩሩ ልብ እንዳይኖረን እናስታውስ ዘንድ ሊረዳን ይገባል። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የተፈጸሙትን አንዳንድ ነገሮች ላንወዳቸው ወይም ላንስማማባቸው እንችላለን። ባርነት አንዱ ምሳሌ ነው።

ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ የሚለውን መቀበል አለብን። ይህንን ካላደረግን፣ ከመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ይልቅ የራሳችንን ሐሳብ እናስበልጣለን። በመጀመሪያ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ አንድ ርዕሰ ጉዳይ የሚናገረውን ሁሉንም ነገር እንመልከት። ከዚያም መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ጉዳዩ ምን እንደሚል በደንብ ማስተዋል እንችላለን።

መጋቢት 9
Mar 18

አንዱ ለሌላው መጸለይ (ቆላ. 4:2-4)


ቆላ. 4:2-4ን ያንብቡ። እነዚህ ጥቅሶች ስለ ጸሎት ምን ጠቃሚ መርሆዎችን ያስተምሩናል? ጳውሎስ ሰዎች እንዲጸልዩለት የጠየቀው ስለምንድነው?



እርዳታ ለሚያስፈልገው ሰው ልንናገራቸው ከምንችላቸው እጅግ አስፈላጊ ቃላት መካከል አንዳንዶቹ “እየጸለይኩልህ ነው” የሚሉት ናቸው። ጸሎት ሰማይ ከእኛ ጋር የሚነጋገርበትና የሚገናኘት መንገድ ነው። “ከእግዚአብሔር እቅድ ውስጥ አንዱ ክፍል የምንለምናቸውን ነገሮች ለኛ መስጠት ነው። እግዚአብሔር የሚሰጠን ስለምንጠይቀውና በእምነት ስለምንጸልይ ነው። እርሱን ካልጠየቅነው፣ እነዚህን ነገሮች አንቀበላቸውም።” —ኤለን ጂ. ዋይት፣ ታላቁ ተጋድሎ፣ ገጽ 525።

ጳውሎስ ስለ ጸሎት ሲናገር የተጠቀማቸውን ቃላት ልብ ይበሉ፡- “ትጉ፣” “ሁልጊዜ የነቃችሁ ሁኑ”፣ “ነቅታችሁ ጠብቁ” እና “እግዚአብሔርን ማመስገን አትርሱ” (ቆላ. 4፡2)። እነዚህ ቃላት የጳውሎስ ጸሎት የእምነት ጸሎት እንደሆነ ይነግሩናል (ቆላ. 4፡2)። በሌላ ቦታ ጳውሎስ “ዘወትር (ሁልጊዜ)” እንድንጸልይ (ኤፌ. 6፡18) እና “ሳናቋርጥ እንድንጸልይ” (1 ተሰ. 5፡17) ይነግረናል። በተጨማሪም “እንዴት እንድንጸልይ እንደሚገባን አናውቅምና፥ ነገር ግን መንፈስ ራሱ በማይነገር መቃተት ይማልድልናል” ይላል (ሮሜ8፡26)። ቆላ. 4:3ን እንደገና ያንብቡ። በዚህ ጥቅስ ውስጥ ጳውሎስ “እግዚአብሔር የቃሉን ደጅ ይከፍትልን ዘንድ ስለ እኛ ጸልዩ” ይላል። እምነትህን እንድታካፍል እግዚአብሔር የሚከፍትልህ “በር” ምን ይመስልሃል?





እንዲሁም ጳውሎስ መናገር የሚገባውን ቃል እንዲሰጠው ጸልዮአል። አንዳንድ ጊዜ የጳውሎስን ደብዳቤዎች ስናነብ፣ ጳውሎስ ምን መናገር እንዳለበት እንዳልተጠራጠረ ወይም እንዳልተጨነቀ እናስብ ይሆናል። እዚህ ላይ ግን ስለ ኢየሱስ የሚናገረውን ወንጌል ሁሉም ሰው እንዲረዳው አድርጎ ይሰብክ ዘንድ እንዲጸልዩለት ጠይቋል (ቆላ. 4፡4)። ጳውሎስ የንጉሱን ቤት ጨምሮ በሮም መንግሥት ውስጥ ላሉ ትልቅ ስልጣን ለነበራቸው መሪዎች መልእክቱን መስበክ በጣም አስፈላጊ እንደሆነ ተረድቶ ነበር።

“ለመጸለይ ሁልጊዜ መንበርከክ አያስፈልገንም። ብቻችሁን ስትሆኑ፣ ስትራመዱና የየዕለት ስራችሁን ስትሰሩ፣ ከአዳኛችሁ ጋር የመነጋገርን ልምድ ጀምሩ።

ይረዳችሁ ዘንድ በልባችሁ ጸልዩ። ሁልጊዜም በዚህ መንገድ ጸልዩ። ኃይልና እውቀት እንዲኖራችሁ ጸልዩ። እያንዳንዱ እስትንፋሳችሁ ጸሎት ይሁን።”—ኤለን ጂ. ዋይት፣ የፈውስ አገልግሎት፣ ገጽ 510, 511።

መጋቢት 10
Mar 19



እንዴት እንደምትኖሩ ተጠንቀቁ (ቆላ. 4:5, 6)


እንዴት እንደምትኖሩ ተጠንቀቁ (ቆላ. 4:5, 6) እንደ ክርስቲያን ልናውቀው የሚገባን ዋናው የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት የትኛው ነው? እርግጥ ነው ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ኃጢአታችን መሞቱ ነው። እርሱ ከኃጢአት ጋር በምናደርገው ተጋድሎ እናሸንፍ ዘንድ ብርታት ይሰጠናል። በኢየሱስ ስናምን፣ የዘላለምን ሕይወት ማግኘት እንችላለን። ይህንን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት በራሳችን ልንማረው አንችልም። እግዚአብሔር ስለዚህ ጉዳይ ሊነግረን ይገባ ነበር። እግዚአብሔር ይህንን እውነት ቃሉ በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስና በልጁ በኢየሱስ አሳይቶናል። ስለ እውነት፣ እውቀትና ጥበብ ብዙ የምናውቀው፣ እግዚአብሔር እነዚህን ነገሮች በቃሉ ስለገለጸልን ነው። እግዚአብሔር ብዙ እውቀትንና ጥበብን ይሰጠናል። አምላክ ሕይወታችን በዚህ እውቀትና ጥበብ መሞላቱን እንዲያሳይ ይፈልጋል። ቆላ. 4:5, 6ን አንብበው የሚከተሉትን ጥያቄዎች ይመልሱ። ጳውሎስ ጠቢብ ለመሆን መጠንቀቅ ያለብን በየትኞቹ ጊዜያት ነው ይላል? ይህስ የሆነው ለምን ይመስላችኋል?





የሚያሳዝነው ክርስቲያን ብንሆንም፣ አንዳንድ ጊዜ የክርስቲያን ባህሪ የለንም! ጳውሎስ እስራኤላውያን በክፉ ባህሪያቸው ምክንያት ሌሎች ሰዎች እግዚአብሔርን እንዲነቅፉት (እንዲሰድቡት) እንዳደረጓቸው ይናገራል፡- “በእናንተ ሰበብ የእግዚአብሔር ስም በአሕዛብ መካከል ይሰደባል” ( ሮሜ 22:4)። ባህሪያችን ትልቅ ተጽእኖ አለው። ስለዚህ በኢየሱስ የማያምኑትን ጨምሮ፣ ለሁሉም ሰው ደግ መሆን አለብን (ቲቶ 2፡5ን እና 2 ጴጥ. 2፡2ን ያንብቡ)። የክርስቲያን ቤት ሰዎች ኢየሱስን በእኛ ውስጥ እንዲመለከቱት ሊረዳቸው ይችላል። በተጨማሪም ሰዎች ቢያበሳጩን እንኳን፣ መታገሥና ደግ መሆን አለብን። ያኔ እምነታችን ትክክለኛ መሆኑን ያያሉ።

በቆላ. 4፡6 ላይ ጳውሎስ ስለምንናገራቸው ቃላት “ለእያንዳንዱ እንዴት እንድትመልሱ እንደሚገባችሁ ታውቁ ዘንድ ንግግራችሁ ሁልጊዜ፥ በጨው እንደ ተቀመመ፥ በጸጋ ይሁን” በማለት ይናገራል (ቆላ. 4:6)። በዚህ ጥቅስ ውስጥ ጳውሎስ ስለምንናገራቸው ቃላት የሰጠን ምክር ሦስት ክፍሎች አሉት። በመጀመሪያ ንግግራችን መልካም ከመሆን የላቀ መሆን አለበት። ንግግራችን በእግዚአብሔር ፍቅር የተሞላ መሆን አለበት።

ሁለተኛ የምንናገራቸው ነገሮች ለሰዎች የሚጠቅሙ መሆን ይኖርባቸዋል።

ሦስተኛ ምን እንደምንናገር እናውቅ ዘንድ የመንፈስ ቅዱስ እርዳታ ያስፈልገናል። በትክክለኛው ጊዜ መናገር የሚገባንን ትክክለኛውን ቃል ሊሰጠን የሚችለው መንፈስ ቅዱስ ብቻ ነው። በተጨማሪም መንፈስ ቅዱስ የሰዎችን አእምሮና ልብ ለእነሱ የምናካፍለውን መልእክት ይሰሙ ዘንድ ያዘጋጃቸዋል። ስለ ንግግሮቻችሁና ድርጊቶቻችሁ አስቡ። በኢየሱስ ላይ ስላላችሁ እምነት ለሌሎች ሰዎች ምን መልእክት ይሰጣሉ?

መጋቢት 11
Mar 20


ተጨማሪ ሀሳብ


“ሁሉም የቤተሰቡ አባላት ቤተሰብን ደስተኛ ለማድረግ የበኩላቸውን መወጣት እንዳለባቸው ሊገነዘቡ ይገባል። አንዱ የቤተሰብ አባል ሌላኛውን የቤተሰብ አባል ሊቃወመው አይገባም። ሁሉም የቤተሰብ አባላት እርስ በርስ መበረታታት አለባቸው። አፍቃሪ፣ ታጋሽና ደግ መሆን አለባቸው። ንግግራቸው ለስላሳ መሆን አለበት። የሚያደናግር ነገር መናገር የለባቸውም። ሁሉም በቤት ውስጥ እናታቸውን ለመርዳት የበኩላቸውን ማድረግ አለባቸው።

“ሁሉም የቤተሰብ አባላት አብረው መስራት እንደሚጠበቅባቸው መረዳት አለባቸው። እድሜያቸው ስድስት ዓመትና ከዚያ በላይ የሆኑ ሁሉም ልጆች በቤት ውስጥ በሚደረጉ ስራዎች መርዳት እንዳለባቸው መገንዘብ አለባቸው።”—ኤለን ጂ. ዋይት፣ የአድቬንቲስት ቤት፣ ገጽ 179፣ 180።

“ደስተኛ ለመሆን ከፈለግን ኢየሱስን ወደ ልባችን እና ወደ ቤታችን እንዲገባ መፍቀድ አለብን። በምንችለው መንገድ ሁሉ ጎጇችንን ቤት እንዲሆን ማድረግ አለብን።

ቤት በምድር ላይ ትንሿ ሰማይ መሆን አለባት። ቤት ፍቅራችንን የምንገልጽበት እንጂ የምንደብቅበት መሆን የለበትም። ደስታችን እርስ በርስ ባለን ፍቅር ላይ የተመረኮዘ ነው።

. . . ስለ ራሳችን ደስታ ብቻ ማሰብ የለብንም። የቤተሰቦቻችን አባላት ለሚያደርጉልን ነገር ሁሉ ምን ያህል እንደምንወዳቸው ለማሳየት እያንዳንዱን አጋጣሚ መጠቀም አለብን። እነሱን ለማስደሰትና ስራቸውን ለማቅለል እንጥራለን። ሲያዝኑ ልናበረታታቸው እንችላለን። ምን ያህል እንደምንወዳቸው ለማሳየት ትንንሽ ነገሮችን ማድረግ እንችላለን።

በቤተሰብ ውስጥ የሚጀምረው ፍቅር እያደገ ይሄዳል። ይህንን ፍቅር የቤተሰባችን አባላት ላልሆኑት ሰዎች እናሳያለን። ይህ ፍቅር የኛንም ሆነ የሌሎች ሰዎችን ህይወት እጅግ አስደሳች ለማድረግ ይረዳናል። ሰዎችን እንረዳቸው ዘንድ የምንችላቸውን ትንንሽ ነገሮች ካላደረግን፣ ሌሎች ሰዎች በሕይወታቸው የመረረ ሀዘን እንዲሰማቸው እናደርጋለን።”— ኤለን ጂ. ዋይት፣ የቤተ ክርስቲያን ምክሮች፣ ጥራዝ 3፣ ገጽ 539፣ 540።


የመወያያ ጥያቄዎች




1. ያገቡ ከሆኑ፣ የትኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ግንኙነትዎን ለማሻሻል ያገቡ ከሆኑ፣ የትኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ግንኙነትዎን ለማሻሻል ይረዱዎታል? ላላገቡ ሰዎችስ ምን ምክር ሊለግሱ ይችላሉ? ትዳር ምንጊዜም ለሚያመጣቸው ተግዳሮቶች በተሻለ ሁኔታ መዘጋጀት የሚችሉት እንዴት ነው?

2. ህይወትዎን በጥንቃቄ መኖር (በጥበብ መመላለስ) ስለሚለው ሃሳብ ያሰላስሉ ህይወትዎን በጥንቃቄ መኖር (በጥበብ መመላለስ) ስለሚለው ሃሳብ ያሰላስሉ (ቆላ. 4፡5)። ስለ አካሄድዎ ስለተጠነቀቁበት ጊዜ ያስቡ። ይህንን በጥንቃቄ ካልኖሩበት ጊዜ ጋር ያነጻጽሩት። ከእያንዳንዱ የህይወት ተሞክሮ ምን ተምረዋል?




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA Union SSL