የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ሰማይ እና ምድርን ማስታረቅ
በፊልጵስዩስ እና በቆላስይስ ስለ ኢየሱስ መማር



1ኛ ሩብ ዓመት 2026


የካቲት 21 - 27

10ኛ ትምህርት

Feb 28 - Mar 6




በኢየሱስ ሙሉ መሆን



ሰንበት ከሰዓት በኋላ

ለዚህ ሳምንት ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡- ቆላ. 2: 1-7፣ ኢሳ. 61:3፣ ቆላ. 2:11-23።


የመታሰቢያ ጥቅስ፡ “እንግዲህ በመብል ወይም በመጠጥ ወይም ስለ በዓል ወይም ስለ ወር መባቻ ወይም ስለ ሰንበት ማንም አይፍረድባችሁ። እነዚህ ሊመጡ ያሉት ነገሮች ጥላ ናቸውና፥ አካሉ ግን የክርስቶስ ነው” (ቆላ. 2: 16, 17)።

ሰዎች ሰንበትን ለምን እንደምትጠብቁ ይጠይቋችኋል? ምናልባት የዚህን ሳምንት መሪ ጥቅስ እንደ “ማስረጃ” በመጠቀም ሰንበትን መጠበቅ አያስፈልግም ይሉ ይሆናል። ነገር ግን ቆላ. 2: 16, 17 የሚናገረው ስለ አራተኛው ትእዛዝ አይደለም።

ጥቅሱ የሚያተኩረው በቤተ ክርስቲያን ስላሉት የሐሰት አስተምህሮዎች ነው። እነዚህ የሐሰት ትምህርቶች ምን ነበሩ?

በመጀመሪያ የሐሰት ትምህርቶቹ የሰው ሐሳቦች እንጂ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት አይደሉም (ቆላ. 2፡8)። በተጨማሪም የሐሰት ትምህርቶቹ የአይሁድን በዓላት ማክበርንና መገረዝን የሚያካትቱ ነበሩ። መገረዝ የወንድ ብልት ሸለፈትን መቁረጥ ሲሆን አንድ ሰው የእግዚአብሔር መሆኑን ያሳያል። በተጨማሪም የሐሰት ትምህርቶቹ የአይሁድን የመንጻት ሥርዓትና የምግብ ደንቦችን ያካትቱ ነበር (ቆላ. 2:16, 21)። የሐሰት አስተማሪዎቹ የሃይማኖት ሰዎች ነበሩ። ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እውነት የሚጠነቀቁ ነበሩ።

ሆኖም ስለ ኢየሱስ የሚናገረውን መልካሙን የምሥራች (ወንጌል) አላስተዋሉትም ነበር። ይህም ለምን እንደሆነ በዚህ ሳምንት እናያለን። በተጨማሪም መሪ ጥቅሱ ሰባተኛውን ቀን ሰንበት ስለመጠበቅ እንደማይናገር እንማራለን። *የሳምንቱን ትምህርት በማጥናት ለሰንበት ይዘጋጁ።

የካቲት 22
Mar 1



የእግዚአብሔር ጥበብ እና እውቀት (ቆላ. 2፡1-7)


ኢዮብ “ነገር ግን ጥበብ የምትገኘው ወዴት ነው? የማስተዋልስ ስፍራ ወዴት ነው?” ሲል ይጠይቃል (ኢዮ. 28:12)። ጳውሎስ ደግሞ በኢየሱስ ነው ሲል ይመልሳል።

“የተሰወረ የጥበብና የእውቀት መዝገብ ሁሉ በኢየሱስ ነው” (ቆላ. 2:3፤ ከ1 ቆሮ. 1:30 ጋር ያስተያዩ)። ኢየሱስ ካለን፣ ሁሉም ነገር አለን። ኢየሱስ “ወደ መረዳት ባለ ጠግነት ሁሉ እንድንደርስ፣ የእግዚአብሔርንም ምሥጢር እንድናውቅ” ይረዳናል (ቆላ. 2፡2)።

እግዚአብሔር እኛን በኢየሱስ ለማዳን ያለውን ምሥጢር (ዕቅድ) ያሳየናል። ቆላ. 2:1-7ን ያንብቡ። ጳውሎስ ለቆላስይስ ቤተ ክርስቲያን መልእክቱን የጻፈበት ምክንያት ምንድነው?



“ፓራክሌቶሲን” የሚለው የግሪኩ ቃል “መበረታታት” ወይም “መጽናት” (ቆላ. 2፡2) ማለት ነው። ጳውሎስ የቤተ ክርስቲያን አባላትን የሐሰት ትምህርቶች የሚያስከትሉትን አደጋ እንዲገነዘቡ መርዳት ይፈልጋል። በተጨማሪም ጳውሎስ ቤተ ክርስቲያንን በክርስቲያናዊ ፍቅር አንድ እንዲሆኑ ይፈልጋል። ጳውሎስ የጻፈው ደብዳቤ እነዚህን ነገሮች ለማድረግ እንደሚረዳ ያምናል። ጳውሎስ የቆላስይስ ቤተ ክርስቲያን አባላትን “ስለ ሥርዓታቸውና በክርስቶስም ስላላቸው የእምነታቸው ጽናት” ያመሰግናቸዋል (ቆላ. 2፡5)። ቤተ ክርስቲያኗ ጠንካራ አመራር እንዳላት በማወቁ ደስ ብሎታል። ብዙ ጊዜ ሰዎች የቤተ ክርስቲያን አመራር ትኩረቱ ሥራው ብቻ እንጂ አምልኮ አይደለም ብለው ያስባሉ። ጳውሎስ ግን የቤተ ክርስቲያን አመራር እና አምልኮ የተቆራኙ መሆናቸውን ተረድቷል። ጳውሎስ የቤተ ክርስቲያን አምልኮ የሚመራበት ትክክለኛ መንገድ እንዳለ ያምናል (1 ቆሮ. 11ን ያንብቡ)። ለዚህም ነው ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ እና ለቲቶ የቤተ ክርስቲያን መሪዎችን እንዴት መምረጥ እንዳለባቸው በጥንቃቄ ይነግራቸው የነበረው (1 ጢሞ. 3፣ ቲቶ 1)። ጠንካራ መሪዎች ቤተ ክርስቲያን እንድታድግ ይረዳሉ።

እንዲሁም ጠንካራ መሪዎች የእግዚአብሔርን ጥበብና የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ያከብራሉ፤ ይህንንም ለሌሎች ሰዎች ያካፍላሉ።

የጳውሎስ ባልደረቦች ትክክለኛውን አስተምህሮ ለቆላስይስ ቤተ ክርስቲያን ተናግረዋል። ለዚህም ነው የቆላስይስ ቤተ ክርስቲያን በእምነት የጠነከረችው።

እምነታቸውንም በመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ይደግፉ ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ስንከተል፣ ከሐሰት ትምህርቶች እንጠበቃለን። ከዚህ በፊት ጠንካራ አመራር መንፈሳዊ ሕይወትዎ አብዝቶ እንዲያድግ ያደረገው እንዴት ነው? ጠንካራ መንፈሳዊ አመራር የአምልኮ ልምምድዎን ወደ ተሻለ ደረጃ የለወጠው እንዴት ነው?

የካቲት 23
Mar 2

በኢየሱስ ማደግ (ኢሳ. 61:3)


ለቆላስይስ ሰዎች የተጻፈው ደብዳቤ የሚናገረው የክርስቲያን ሕይወትን እንዴት መኖር እንዳለብን ነው፡- “እንግዲህ ጌታን ክርስቶስ ኢየሱስን እንደ ተቀበላችሁት በእርሱ ተመላለሱ” ይላል (ቆላ. 2፡6)። እውነትን ስንቀበል፣ የምንቀበለው አስተምህሮዎችን ብቻ ሳይሆን ትክክለኛ አካል ያለውን ኢየሱስን ነው። እንዲሁም ኢየሱስን ስንቀበል፣ ትምህርቶቹን ሁሉ እንቀበላለን (ኤፌ. 2፡20ን ያንብቡ)።

በተጨማሪም ኢየሱስን ስንቀበል፣ ለእኔነት እንሞታለን። ሕይወታችንንም ሙሉ በሙሉ ሕያው ለሆነው ለኢየሱስ እናስረክባለን።

ኢየሱስ ሕያው የሆነ ቃል ነው። ሕያው ቃል (ኢየሱስ) ደግሞ ከተጻፈው ቃል ከመጽሐፍ ቅዱስ ሊለይ አይችልም። በእርግጠኝነት ኢየሱስን ማወቅ የምንችለው በመጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ በኢየሱስ እንዴት መኖር እንዳለብን ያስተምረናል። በምናደርገው በእያንዳንዱ ነገር እና በእያንዳንዱ ምርጫችን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት እና መንፈስ ቅዱስ እንዲመሩን መፍቀድ አለብን።

በቆላ. 2፡7 ላይ ጳውሎስ ክርስቲያኖችን ከእፅዋት ጋር የሚያነጻጽር ምሳሌያዊ ቃል ተጠቅሟል። “ሥር ሰዳችሁ በእርሱ ታነጹ” ይላል። ኢየሱስን እንደ ግል አዳኛችን ስንቀበለው፣ ከእርሱ ጋር እንጣበቃለን። ትምህርቶቹንም ተቀብለን እንተገብራቸዋለን።

ከዚያም “በእርሱ እናድጋለን (እንታነጻለን)” (ቆላ. 2፡7)። ኢሳ. 61:3ን፣ ማቴ. 3:10ን፣ ሉቃ. 8:11-15ን እና 1 ቆሮ. 3፡6ን ያንብቡ።

እነዚህ ጥቅሶች በእጽዋት የተመሰለውን ቃል በተሻለ ሁኔታ እንድንረዳ የሚያግዙን እንዴት ነው? ይህ ምሳሌ እንደ ክርስቲያን ስለ እምነታችን ምን ያሳየናል?



ጳውሎስ ክርስቲያኖች ሊሆኑ ስለሚችሉት ሁለት ዓይነት ዕፅዋት ተናግሯል።

የመጀመሪያው ተክል “በመልካም ዛፎች” እና “እግዚአብሔር ለክብሩ በተከላቸው የጽድቅ ዛፎች” (ኢሳ. 61: 3) የተመሰሉ ክርስቲያኖችን ይመስላል። እነዚህ ክርስቲያኖች በጌታ ሁልጊዜ የሚያድጉ ናቸው። ኢየሱስንና ትምህርቱን አጥብቀው ይይዛሉ። ሁለተኛው ተክል ሰው ሠራሽ ነው። ተክሉ እውነተኛና ሕያው ይመስላል። ነገር ግን ሕይወት አልባ ወይም የሞተ ነው። የሰውን ትምህርት እንዲሁም ሰው ሰራሽ ህግጋቶችንና ሃሳቦችን ስንከተል፣ እንደ ባሪያዎች እንሆናለን (ቆላ. 2፡8)። ኢየሱስ ከኃጢአት ባርነት ነፃ አውጥቶናል። ሆኖም እኛ እንደገና ባሪያዎች ልንሆን እንችላለን (ገላ. 5፡1ን ከሐዋ. 15፡10 ጋር ያስተያዪ)።

የሐሰት ትምህርቶችን ስንቀበል፣ ኢየሱስን እንቃወማለን። ለምን? ምክንያቱም የሐሰት ትምህርቶች ስለ ኢየሱስ ከሚናገረው ወንጌል ይለዩናል። የሐሰት ትምህርቶችን ስንቀበል፣ ከመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ይልቅ የሰዎችን ሐሳብ እየተቀበልን ነው (ገላ. 1፡ 6-9ን ያንብቡ)። በአዲስ ኪዳን ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖች ይህንን ስህተት የመሥራት አደጋ ተጋርጦባቸው ነበር። እኛም ደግሞ ካልተጠነቀቅን፣ የዚህ አደጋ ሰለባ እንሆናለን።

የካቲት 24
Mar 3

በመስቀል ላይ የተቸነከሩ (ቆላ. 2፡11-15)


ጳውሎስ የቆላስይስ ሰዎች እንዲገነዘቡት የፈለገው የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ምንድነው? ቆላ. 2፡11-15ን ያንብቡ።



ሰዎች ሰባተኛውን ቀን ሰንበት ላለመጠበቅ ቆላ. 2፡11-15ን እንደ ምክንያት ሲጠቀሙ ምን ያህል እናያለን?

ሁለት ማብራሪያዎች እነዚህን ጥቅሶች ለመረዳት ያግዙናል። በመጀመሪያ በብሉይ ኪዳን “የሚቃወሙን በትእዛዛት የተጻፉ” ነገሮች ነበሩ (ቆላ. 2፡14)። እነዚህን ነገሮች ጲላጦስ በኢየሱስ መስቀል ላይ ካንጠለጠለው ጽሑፍ ጋር ማነጻጸር እንችላለን (ማቴ. 27:37፣ ዮሐ. 19:19, 20)። ሁለተኛ ስለ መባ የሚናገረው የሙሴ ህግ በመስቀል ላይ ተቸንክሯል (ዘዳ. 31፡24–26ን ያንብቡ)። በዐውዱ ካሉት ሌሎች ጥቅሶች ጋር ስንመለከተው፣ ቆላ. 2፡14 የሚናገረው ስለ መስዋዕት ህግ ነው።

በተጨማሪም ጳውሎስ “በክርስቶስ መገረዝ፥ . . . በእርሱ ሆናችሁ ደግሞ ተገረዛችሁ” ይላል (ቆላ. 2፡11)። መገረዝ ማለት የወንድ ብልት ሸለፈትን መቁረጥ ማለት ነው። ጳውሎስ መገረዝን እንደ ምሳሌያዊ አነጋገር ተጠቅሞ፣ እግዚአብሔር ኃጢአት እንድንሰራ የሚያደርገንን “የሥጋን ሰውነት መግፈፉን” ያሳየናል (ቆላ. 2፡11)። ጳውሎስ ይህን የልብና የአስተሳሰብ መለወጥ ከጥምቀት ጋር ያስተሳስረዋል። ስንጠመቅ አሮጌው ሰውነታችን ከኢየሱስ ጋር ይሞታል። ከዚያም አዲስ ሰው ሆነን እንነሳለን (ቆላ. 2፡11, 12)። ጳውሎስ “እናንተም በበደላችሁ . . . ሙታን በሆናችሁ ጊዜ፥ ከእርሱ ጋር ሕይወትን ሰጣችሁ። በደላችሁን ሁሉ ይቅር አላችሁ” በማለት ይገልጻል (ቆላ. 2:13)።

“በእኛ ላይ የነበረውን የሚቃወመንንም በትእዛዛት የተጻፈውን የዕዳ ጽሕፈት ደመሰሰው” የሚለውን እንደገና ይመልከቱ (ቆላ. 2፡14)። እነዚህ ቃላት ህጋዊ ትዕዛዛት የሚል ትርጉም ካለው የግሪክ ቃል የተወሰዱ ናቸው። እነዚህ ትዕዛዛት ከመንግስት ወይም ከቤተክርስቲያን ሊሰጡ ይችላሉ። ጳውሎስ ይህንን የግሪክ ቃል በሌላ ቦታ አንድ ጊዜ ብቻ የተጠቀመው ሲሆን ያውም ስለ መስዋዕት ህግ ለመናገር ነው (ኤፌ. 2፡14, 15)።

ይህ ህግ በአይሁዶች እና አይሁዶች ባልሆኑ መካከል የነበረ የጥል (የመለያየት) ግድግዳ ነው። በቆላስይስ 2 ውስጥ ጳውሎስ በኤፌሶን የተናገረውን ተመሳሳይ ሃሳብ እንድንረዳ ይፈልጋል። አይሁዳዊ ያልሆኑ ክርስቲያኖች ስለ እንስሳት መባ የሚናገረውን የሙሴን ሕግ ስለመጠበቅ ከእንግዲህ ወዲህ መጨነቅ አያስፈልጋቸውም ነበር። በተጨማሪም መገረዝ ወይም የመንጻት ሕጎችን መጠበቅ አያስፈልጋቸውም ነበር።

ስለዚህ ጳውሎስ እግዚአብሔር አሥርቱን ትእዛዛት በመስቀል ላይ ቸንክሯቸዋል እያለ እንዳልሆነ እንመለከታለን። በሌላ ቦታ ጳውሎስ ኃጢአት አሥርቱን ትእዛዛት መተላለፍ እንደሆነ ተናግሯል (ሮሜ 7፡7)።

የካቲት 25
Mar 4

ጥላ ወይስ አካሉ? (ቆላ. 2:16–19)


በቆላ. 2፡16–19 ውስጥ ስላሉት ሰው ሰራሽ ህጎች ያንብቡ። የእነዚህ ደንቦች ችግር ምንድን ነው?



ቆላ. 2፡16-19 በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ስላለው ችግር ብዙ መረጃ ይሰጠናል።

ችግሩ አይሁዳዊ በሆኑ ክርስቲያኖች እና አይሁዳዊ ባልሆኑ አባላት መካከል ነበር (ቆላ. 2፡13)። የቆላስይስ ቤተ ክርስቲያን አባላት በአብዛኛው አይሁዳውያን አልነበሩም።

አይሁዳዊ የሆኑ ክርስቲያኖች አይሁዳዊ ያልሆኑ ክርስቲያኖችን ሰው ሰራሽ ሕጎችን መከተል አለባችሁ ብለዋቸው ነበር። ነገር ግን ጳውሎስ እነዚህ ህጎች (ደንቦች) አስፈላጊ አይደሉም አላቸው።

ቆላ. 2፡16 የአይሁድ ህጎችን ዝርዝር ይሰጠናል። ብዙ አይሁዶች ቤተ ክርስቲያንን ከተቀላቀሉ በኋላ እነዚህን ህጎች መጠበቃቸውን ቀጥለው ነበር። ከእነዚህ አይሁዶች መካከል አንዳንዶቹ መላእክትን የሚያመልኩ ወይም በትዕቢት የተሞሉ ነበሩ። ኢየሱስ በምድር ላይ ሲያገለግል በነበረበት ጊዜ፣ የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎችን በልባቸው ውስጥ ስለነበረው ትዕቢት አስጠንቅቋቸው ነበር (ማቴ. 6: 1, 5, 7, 16ን ያንብቡ)።

ስለዚህ ጳውሎስ በቆላስይስ ቤተ ክርስቲያን ያያቸው ችግሮች አዲስ አልነበሩም። እንዲያውም ጳውሎስ በሌሎች ቦታዎች ባሉ አብያተ ክርስቲያናትም ተመሳሳይ ችግሮችን ተመልክቷል።

ዛሬ ብዙ ክርስቲያኖች ቆላ. 2፡16ን በተሳሳተ መንገድ ስለሚረዱት በጥንቃቄ እንመልከተው። በቆላ. 2:16 “እንግዲህ” የሚለው ቃል ጳውሎስ አስቀድመን ባነበብናቸው ጥቅሶች ውስጥ ያለውን ሃሳቡን እየቋጨ እንደሆነ ይነግረናል። ጳውሎስ ክርስቲያኖች መገረዝ እንደማያስፈልጋቸው ተናግሯል። አይሁዶች ይገረዙ የነበሩት የእግዚአብሔር መሆናቸውን ለማሳየት ነበር። ጳውሎስ መገረዝ ሳይሆን ዋናው ነገር አዲስ ልብ ነው እያላቸው ነበር (ቆላ. 2፡11–15)።

በተጨማሪም ጳውሎስ በቆላ. 2፡16 ላይ ስለ ምግብና መጠጥ ተናግሯል። እነዚህ ነገሮች የሚናገሩት ስለ መብል እና መጠጥ ቁርባን ነው። እስራኤላውያንም ወደ ቤተ መቅደሱ ያመጡአቸው ነበር።

በቆላ. 2፡16 ጳውሎስ ስለ ልዩ ልዩ በዓላት ተናግሯል። እነዚህ በዓላት ሆሴ. 2፡11ን እንድናስታውስ ይረዱናል። እንዲሁም ሆሴ. 2፡11 ስለ ተቀደሱ ጉባኤዎች፣ ሃይማኖታዊ በዓላት እና ሰንበታት ይናገራል (በተጨማሪም ዘሌ. 23:11, 24, 32ን ያንብቡ)። ጳውሎስ እነዚህ ሁሉ ህግጋት እና በዓላት “ሊመጡ ያሉት ነገሮች ጥላ ናቸውና” በማለት ይነግረናል (ቆላ. 2፡17)። እነዚህ በዓላት የኢየሱስን የወደፊት ሥራ የሚያሳዩ ነበሩ (1 ቆሮ. 5፡7ን እና 1 ቆሮ. 15፡23ን ያንብቡ)። እግዚአብሔር ሰንበትን በኤደን የጀመረው ኃጢአት ሳይከሰት በፊት ወይም የመጀመሪያው የኃጢአት መስዋዕት ሳይቀርብ ነበር። ስለዚህ ኢየሱስ በመስቀል ላይ ከሞተ በኋላ የሰንበት ትእዛዝ አልተሻረም።

የካቲት 26
Mar 5

ገደቦች እና ህግጋት (ቆላ. 2፡20–23)


ጳውሎስ ለቆላስይስ ቤተ ክርስቲያን ምን ምክርና ማስጠንቀቂያ ሰጠ? ቆላ. 2፡20- 23ን ያንብቡ።



ጳውሎስ ስለ እንስሳት መስዋዕት የተጻፉ ህግጋትን መፈጸም አያስፈልገንም ብሏል። እነዚህ ነገሮች ኢየሱስ መጥቶ የሠራቸውን ሥራዎች የሚያመለክቱ ነበሩ።

ኢየሱስ በመስቀል ላይ ከሞተ በኋላ፣ እነዚህ ህግጋት አስፈላጊ አልነበሩም።

ስለዚህ ክርስቲያኖች (አይሁዳዊ ክርስቲያኖችን ጨምሮ) እነዚህን ህግጋት መከተል አያስፈልጋቸውም ነበር። እነዚህ ህግጋት ከእንግዲህ ወዲህ እንደማያስፈልጉ ለማሳየት፣ እግዚአብሔር ለሕዝቡ የሚታይ ምልክት ሰጥቷቸዋል። ምልክቱም የቤተ መቅደሱን መጋረጃ የቀደደው የሰማይ እጅ ነው። ይህ መጋረጃ ቅድስተ ቅዱሳኑን ከቅዱሱ ክፍል የሚለይ ነበር። አስፈላጊነታቸው ካከተመ በኋላ እነዚህን ስለ እንስሳት መስዋዕት የተጻፉ ህግጋትን ብንፈጽምስ? ያን ጊዜ እኛ የዚህ ምድር ዜጎች እንጂ የእግዚአብሔር መንግሥት አካል እንዳልሆንን እናሳያለን።

እኛ “ጽድቅ የሚኖርባትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንደ ተስፋ ቃሉ እንጠብቃለን” (2 ጴ. 3፡13)። ያን ጊዜ እግዚአብሔር ሁሉንም ነገር አዲስ እንደሚያደርገው ቃል ገብቷል።

የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች በሙሴ ህግጋት ላይ ተጨማሪ ሰው ሰራሽ ደንቦችን ጨምረውባቸው ነበር (ማር. 7፡1–13ን ያንብቡ)። እነዚህ ደንቦች ሁሉ ከባድ ሸክም ሆኑ።

የክርስቲያኖች እምነት እንዲያድግ አስተዋጽኦ አልነበራቸውም። አንዳንድ ክርስቲያኖች ከሌሎች ሰዎች ይልቅ የተሻለ ስሜት እንዲሰማቸው የሚያደርጓቸውን ነገሮች ማድረግ ይወዳሉ። ያ በራሱ መጥፎ ነው። ይባስ ብሎ እነዚሁ ሰዎች በሚያደርጓቸው የተለዩ ነገሮችና በሚከተሏቸው ደንቦች የዘላለም ሕይወትን ማግኘት እንደሚችሉ ያስቡ ይሆናል።

ቀደም ባሉት ጊዜያት ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥልቅ ተመራማሪዎች የመንፈስ ቅዱስን ሥራ ለመሥራት በመሞከር ተሳስተዋል። በሌሎች ሰዎች ሕይወት ውስጥ የመንፈስ ቅዱስን ቦታ ተክተው ነበር። እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥልቅ ተመራማሪዎች መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረውን ለሰዎች ለመንገር ሞክረዋል። ያ ግን የእግዚአብሔር ስራ ነው። ኢየሱስ እውነት ነው። እርሱም ጳውሎስንና ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎችን ምን ማለት እንዳለባቸው ይመራቸው ነበር። ኢየሱስ “ለእኛ” እና “በእኛ ውስጥ” ይሰራል። ኢየሱስ በመስቀል ላይ ለእኛ የሠራልን ሥራ ምንድነው? ኢየሱስ አሁን በእኛ ውስጥ የሚሠራው ሥራ ምንድነው? አሁን በእኛ ውስጥ የሚሠራው ሥራ በመስቀል ላይ በሠራልን ሥራ ላይ የተመሰረተው ለምንድነው?

የካቲት 27
Mar 6


ተጨማሪ ሀሳብ


“በአዲስ ኪዳን ዘመን፣ ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የነበረውን አመኔታ ለማጥፋት ሞክረው ነበር። ይህንን እንዴት አደረጉት? በሰው ሰራሽ ደንቦችና ሃሳቦች በመተካት ነበር። ዛሬም ሰይጣን ተመሳሳይ ነገር ለማድረግ ይሞክራል።

ሰዎች የተሳሳቱ ሀሳቦችን እንዲቀበሉ ለማድረግ ይሞክራል። ለዚያም ነው ለብዙ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ምንም ዘይት እንደሌለው መብራት የሆነባቸው። እነዚህ ሰዎች ግራ የሚያጋቧቸውን የሐሰት ትምህርቶች ይቀበላሉ። ከዚያም የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት በተሳሳተ መንገድ ይረዱታል። እነዚህ የተሳሳቱ ሐሳቦች ደግሞ፣ መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር ለእኛ የሰጠን መልዕክት መሆኑን ሰዎች እንዳያምኑበት ያደርጋሉ። ሰዎች እነዚህን የተሳሳቱ ሀሳቦች ሲቀበሉ፣ መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት መቆጣጠር ወይም የተሻለ ማድረግ አይችልም። ሰዎች ሙታን ከእኛ ጋር መነጋገር እንደሚችሉ ሲያምኑ፣ የእግዚአብሔርን ህግ በእኔነት ይተኩታል። የፈለጉትን ማድረግ እንደሚችሉ ያምናሉ - ኃጢአት መስራትን ጨምሮ። መተላለፍ አርነት እንደሆነ፣ ለእግዚአብሔርም መልስ መስጠት እንደማያስፈልጋቸው ያምናሉ።

“ክርስቲያኖች እነዚህን ነገሮች ከሚያስተምሩ ሰዎች ጋር ይገናኛሉ። ሐዋርያው ጳውሎስ የቆላስይስ ቤተ ክርስቲያንን ከእነዚህ የሐሰት አስተማሪዎች እንዲጠበቁ አስጠንቅቋቸዋል። ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ከሙታን ጋር መነጋገር እንደምንችል ያስተምራል ይላሉ። ነገር ግን እነዚህን ትምህርቶች መቀበል የለብንም። ክርስቲያኖች ለመጽሐፍ ቅዱስ እውነት የጸና አቋም ሊኖረን ይገባል። በኢየሱስ ላይ ማተኮር አለብን። ከእርሱ አስተምህሮ ጋር የማይስማሙትን ሁሉንም ሃሳቦች መቃወም አለብን። ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እውነት ልናሰላስል ይገባል። መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ድምጽ ወይም ቃል እንደሆነ ልናምን ይገባል።

መጽሐፍ ቅዱስን ስናነብ፣ እግዚአብሔር ይናገረናል። ያን ጊዜ ከእግዚአብሔር የሚገኘውን ጥበብ እናውቃለን፣ እንማራለንም።”—ኤለን ጂ. ዋይት፣ የሐዋርያት ሥራ፣ ገጽ 474, 475።


የመወያያ ጥያቄዎች




1. ጳውሎስ “በእርሱ የመለኮት ሙላት ሁሉ በሰውነት ተገልጦ ይኖራልና። ለአለቅነትና ጳውሎስ “በእርሱ የመለኮት ሙላት ሁሉ በሰውነት ተገልጦ ይኖራልና። ለአለቅነትና ለሥልጣንም ሁሉ ራስ በሆነ በእርሱ ሆናችሁ ተሞልታችኋል” ይላል (ቆላ. 2፡9, 10)። እነዚህ ነገሮች ምን ማለት ናቸው? በተጨማሪም ዮሐ. 1:1ን፣ ዕብ. 1:3ን እና 1 ጴጥ. 3፡22 ያንብቡ።

2. ብዙ ክርስቲያኖች ቆላ. 2፡14-16ን በመጠቀም 7ኛውን ቀን ሰንበት ከእንግዲህ ብዙ ክርስቲያኖች ቆላ. 2፡14-16ን በመጠቀም 7ኛውን ቀን ሰንበት ከእንግዲህ ወዲህ መጠበቅ እንደማያስፈልገን ለማሳየት ይሞክራሉ። ይህንን ለማለት እነዚህን ጥቅሶች መጠቀም ምን ዓይነት ችግሮችን ያስከትላል?

3. ከላይ በተጠቀሰው ጽሑፍ፣ ኤለን ጂ. ዋይት “መጽሐፍ ቅዱስን ስናነብ፣ ከላይ በተጠቀሰው ጽሑፍ፣ ኤለን ጂ. ዋይት “መጽሐፍ ቅዱስን ስናነብ፣ እግዚአብሔር እየተናገረን እንደሆነ” ማመን አለብን ብላ ጽፋለች። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያለንን እምነት ከሚያዳክም ከማንኛውም ሰው ወይም ነገር ራሳችንን መጠበቅ ያለብን ለምንድን ነው?




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA Union SSL