የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

የእግዚአብሔር ተልዕኮ የእኔ ተልዕኮ



4ኛ ሩብ ዓመት 2023


ህዳር 8 - 14

8ኛ ትምህርት

Nov 18 - 24




በችግር ላይ ያሉትን በወንጌል መድረስ



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሳምንት ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ሉቃ 5፡17-26፣ ዮሐንስ 5፡1-9፣ ዘዳ. 10:19፣ ዘሌ. 23፡22፣ ማቴ. 25፡34-40፣ ዮሐንስ 15፡13።


መግቢያ ጥቅስ፡- “ንጉሡም መልሶ፦ እውነት እላችኋለሁ፥ ከሁሉ ከሚያንሱ ከእ ነዚህ ወንድሞቼ ለአንዱ እንኳ ስላደረጋችሁት ለእኔ አደረጋችሁት። ይላቸዋል” (ማቴ. 25፡40)

ሉቃስ 5፡17-26 እግዚአብሔር የተቸገሩትን እንዴት እንደሚረዳቸው ብዙ ምሳሌዎችን ይሰጣል። አንዳንድ ጊዜ እግዚአብሔር እኛን ለመርዳት ሌሎችን ይጠቀማል ወይም ሌሎችን ለመርዳት እኛን ይጠቀማል። ይህ ሥራ ፈታኝ ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን ትልቅ ሽልማቶችን ያመጣል። የተቸገሩትን በመርዳት የኢየሱስ ክርስቶስን አገልግሎት ምሳሌነት እየተከተልን ነው። አንዳንድ ጊዜ እርዳታ የሚያስፈልገው ማን እንደሆነ መንገር ቀላል ነው፤ በሌሎች ጊዜያት ደግሞ ለማወቅ አስቸጋሪ ነው።

ሁኔታው ምንም ይሁን ምን፣ የኋላ ታሪካቸው ምንም ይሁን ምን፣ ለተቸገሩ ሰዎች ሁሉ የእግዚአብሔር ረዳቶች እንድንሆን ተጠርተናል።

መጽሐፍ ቅዱስ ከማናውቃቸው ሰዎች ጋር እንድንቀራረብ ያበረታታናል፤ እናም እንዲያምኑን ካደረግን በኋላ ኢየሱስን እንዲያገኙ ለመርዳት የተሻሉ መንገዶችን መማር እንችላለን።

በዚህ ሳምንት ትምህርት “የተቸገሩትን በወንጌል መድረስ” የሚለው ርዕሳችን፣ እግዚአብሔር ችግረኞችን በማንኛውም መንገድ የመድረስ እቅድ እንዳለው ያሳያል።

ፍላጎታቸው አካላዊ፣ ስሜታዊ፣ ገንዘብ ነክ ወይም ማህበራዊ ማለትም አንዳንዶች ከማህበረሰባቸው ወይም ከቤተሰባቸው የተገለሉ ሊሆኑም ይችላሉ። ፍላጎቱ ምንም ይሁን ምን ለመርዳት የምንችለውን ለማድረግ ዝግጁ መሆን አለብን። ይህ የክርስትና ኑሮ ማዕከል እና ተልእኮው ማካተት ያለበት ዋና አካል ነው። *ለህዳር 15 ሰንበት ለመዘጋጀት የዚህን ሳምንት ትምህርት ያጥኑ።

ህዳር 9
Nov 19

የወዳጆች እምነት


በወንጌል ውስጥ የሚገኘው ይህ ኃይለኛ ታሪክ የተወሰኑ ሰዎች ችግረኛውን ምናልባትም ወዳጃቸውን ወደ ኢየሱስ ለማምጣት ምን እንዳደረጉ ይገልጻል። የተቸገሩትን ለማገልገል መደረግ ስላለበት ጥረት እዚህ ከተፈጠረው ነገር መማር እንችላለን።

ሉቃስ 5፡17-26ን ያንብቡ (በተጨማሪም ማቴ. 9፡1-8፣ ማርቆስ 2፡3-12 ይመልከቱ)። ከዚህ ታሪክ ስለ ተልእኮ እና አገልግሎት ልንወስዳቸው የምንችላቸው አንዳንድ ትምህርቶች ምንድን ናቸው?



እነዚህ ሰዎች እሱን ወደ ኢየሱስ በማምጣት ጓደኛቸውን የመንከባከብ ኃላፊነት ወሰዱ። እግዚአብሔር እንደዚህ ሰው ጓደኞች እንድንሆን እየጠራን ነው - ችግረኞችን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ እንድንመራ። ይህ ሥራ እምነትን፣ ተግባርን፣ ትዕግስትን፣ እና አስፈላጊ ከሆነ፣ ባልተጠበቀ መንገድ ለመሄድ ፈቃደኛ መሆንን ይጠይቃል። ሰዎቹ ወደ ኢየሱስ መጡ፤ ነገር ግን እንቅፋት አጋጠማቸው። ረዳት የሌለውን ወዳጃቸውን በተለመደው መንገድ ወደ ኢየሱስ ማምጣት አልቻሉም። ተስፋ አልቆረጡም፣ ይልቁንም ሰውየውን ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ የሚያደርሱበት አዲስ መንገድ አገኙ። ጓደኛቸውን ከጣራው ላይ ማውረድ! እንደ ሉቃስ አነጋገር ኢየሱስ ያደረጉትን ነገር ተቀብሏል (ሉቃስ 5፡20 ይመልከቱ)።

የኢየሱስ ፍላጎት ረዳት የሌላቸውን ጓደኞቻችንን ወደ እርሱ እንድናመጣ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስን የሚሰቃዩትን ማንም ይሁኑ ማን ይቅር ለማለት እና ለማዳን የሚፈልግ ታላቅ ሐኪም ብሎ ይጠራዋል።

ኤለን ጂ. ኋይት አቅመ ደካሞችን እንድንረዳ ትሞግተናለች፡- “ሥራችሁ እንዲነገራችሁ አትጠብቁ። ዓይናችሁን ክፈቱ እና በዙሪያችሁ ያሉትን እዩ፤ ከድሆች እና ከተቸገሩት ጋር ተዋወቁ። ራሳችሁን ከእነርሱ አትደብቁ፣ ፍላጎታቸውንም መዝጋት አትፈልጉ። በያዕቆብ ላይ እንደተፃፈው ነውር የሌለበትን እውነተኛ አምልኮ ይዘዋል የተባሉትን ማድረግ የሚወድ ማነው? በታላቁ የድነት እቅድ ውስጥ ለመርዳት የሚችሉትን ሁሉ ለማድረግ የሚጨነቁ እነማን ናቸው?”— Testimonies for the Church, vol. 2, p. 29

ኢየሱስ ራሱ ረዳት የሌላቸውን እንዴት መርዳት እንዳለብን አሳይቷል እና እኛንም እንድንረዳ እየጠራን ነው። በመጀመሪያ ጓደኞቻቸው እንሆናለን፤ ከዚያም ስለ ፍላጎታቸው እንማራለን፤ እና በመጨረሻም፣ እርሱ ብቻውን ሊረዳቸው ወደሚችለው ወደ ኢየሱስ እንመራቸዋለን። በዚህ ታሪክ ውስጥ ያሉት ወንዶች ያደረጉት ይህን ነው፤ ራሳችንን ባገኘንበት በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ እንዲሁ ማድረግ አለብን። ሰዎችን እርሱ ብቻ ሊያድናቸው ወደሚችለው ወደ ኢየሱስ እንዲጓዙ እርዷቸው።

አሁን እርዳታ የሚያስፈልገው በአካባቢዎ ያለ ማን አለ? ምን ሊያደርጉላቸው አስበዋል?

ህዳር 10
Nov 20

የክርስቶስ ዘዴ ብቻ


የሚከተሉት ታሪኮች ለችግረኞች ስለሚደረጉ አገልግሎቶች ምን ያስተምሩናል? ዮሐንስ 5፡1-9



ማርቆስ 1፡23-28



ኤለን ጂ. ኋይት የኢየሱስን አገልግሎት በተለይም የተቸገሩትን እንዴት ማገልገል እንዳለብን ባለ አምስት ደረጃ መንገድ አስቀምጣለች፡- “የክርስቶስ ዘዴ ብቻውን ሰዎችን በመድረስ እውነተኛ ስኬት ያስገኛል። አዳኙ መልካማቸውን በመፈለግ ከሰዎች ጋር ተቀላቀለ፤ ርኅራኄን አሳያቸው፤ ፍላጎቶቻቸውን አሟላ፤ እናም መተማመናቸውን አገኘ።

ከዚያም ‘ተከተሉኝ’ አላቸው።”— The Ministry of Healing, p. 143

በመጀመሪያ፣ ከአቅመ ደካሞች ጋር መቀላቀል፣ እነሱን ለማወቅ ጊዜ ማሳለፍ እና ለእነሱ መልካም ለማድረግ በማሰብ ፍላጎታቸውን መረዳት አለብን። ኢየሱስ በውሃ ቦታ ላይ ለሽባው ያደረገውን ይመልከቱ። ኢየሱስ እዚያ ነበር፣ “ከብዙ በሽተኞች፣ ዕውሮች፣ አንካሶች፣ ሽባዎች” (ዮሐንስ 5፡3) መካከል።

ሁለተኛ፣ ርኅራኄ ማሳየት አለብን። ይህ በአንዳንድ ሁኔታዎች ፈታኝ ሊሆን ይችላል ምክንያቱም አንዳንድ ጊዜ ሰዎች እምነትን ለማግኘት ደግነትን እንደ አንድ ዘዴ አድርገው ከተጠቀሙ በኋላ ስለሚጎዱ(ስለሚያጭበረብሩ) ነው። ቢሆንም፣ እግዚአብሔር በምላሹ ምንም ሳንጠብቅ እንድንራራ እየጠራን ነው።

ሦስተኛው እርምጃ ፍላጎታቸውን ማሟላት ነው። ይህ ከቃላት ያለፈ ነገርን ይጨምራል። የጓደኛን ወይም የእንግዳውን ሰው ፍላጎት ለማሟላት እርምጃ መውሰድን ይጠይቃል። ኢየሱስ ሽባውን አነጋግሮ ምን እንደሚፈልግ ጠየቀ ከዚያም ተአምር ሠራለት። “ርኩስ መንፈስ” በያዘው ሰው ታሪክ ውስጥ ኢየሱስ ሁኔታውን ሙሉ በሙሉ በመቆጣጠር ረዳት የሌለው ሰው ለራሱ ማድረግ የማይችለውን አድርጓል።

አራተኛው እርምጃ መተማመንን ማግኘት ነው፤ ሰዎችን ስናገለግል፣ ስንረዳቸው፣ በእኛም ሆነ በምንነግራቸው ነገሮች ላይ እምነት መጣልን ይማራሉ፣ ስለዚህም ስለ ኢየሱስ ስንነግራቸው ለማዳመጥ ይበልጥ ክፍት ይሆናሉ። ኢየሱስ በአካል እነሱን መፈወስ ብቻ አልፈለገም፤ ይልቁንም በእርሱ የዘላለም ሕይወት እንዲኖራቸው ፈለገ (ዮሐንስ 10፡10)።

የመጨረሻው እርምጃ እነርሱን ወደ ኢየሱስ መምራት ነው፣ ይህ ድርጊት ከእርስዎም ሆነ ከሚረዱት ሰው እምነትን የሚጠይቅ ነው።

በአጠቃላይ ኢየሱስ ያደረጋቸውን ተአምራት ማድረግ ላንችል እንችላለን። ግን አሁንም እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ማገልገል የምንችልባቸው መንገዶች የትኞቹ ናቸው?

ህዳር 11
Nov 21

ስደተኞች


ከስደተኞች ጋር የተያያዘው ርዕስ በተለይም ዛሬ በጣም ብዙ ስደተኞች ስላሉ በጣም አነጋጋሪ ሆኗል። በጦርነትም ይሁን በተፈጥሮ አደጋዎች፣ ወይም የተሻለ ኢኮኖሚያዊ የወደፊት ተስፋ ለማግኘት በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ከመኖሪያ ቤታቸው ተፈናቅለው እርዳታ ያስፈልጋቸዋል።

በማቴዎስ 2፡13-14 ኢየሱስ ስደተኛ ነበር። ከሄሮድስ እጅ ለማምለጥ ምድራዊ ወላጆቹ ዮሴፍና ማርያም በሌሊት ከቤተልሔም ሸሽተው ወደ ግብፅ ለመሄድ ተገደው ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ በግብፅ ስለነበሩበት ሁኔታ ምንም የሚናገረው ነገር የለም፤ ነገር ግን ፈተናዎች እንዳሉት መገመት ከባድ አይደለም፤ ምናልባትም በዛሬው ጊዜም ስደተኞች የሚያጋጥሟቸው አይነት አንዳንድ ተግዳሮቶችን ሳይጋፈጡ አይቀሩ ይሆናል።

እንዲያውም የኢየሱስ ቤተሰብ በባዕድ አገር ጥገኝነት እንደጠየቁት በመጠኑም ቢሆን ብዙ ሙስሊሞች፣ ቡዲስቶች፣ ሂንዱዎች፣ ክርስቲያኖች እና ሃይማኖተኛ ያልሆኑ ሰዎች ዛሬም በተለያዩ አገሮች ጥገኝነት እየጠየቁ ነው።

በጥቅሉ ሲታይ ከራሳችን ባህልና የቋንቋ ቡድን ከመጡ ግለሰቦች ጋር መወዳጀት ይቀላል፤ ምክንያቱም ብዙ ነገሮችን ስለምንጋራ ነው። ከኛ የተለየ መልክ ያላቸውና ቋንቋችንን ከማይናገሩ፣ ሃይማኖታዊ እሴቶቻችን ከማይጋሩና ተመሳሳይ ምግብ ከማይመገቡ ስደተኞች ጋር የጋራ መግባባት መፍጠር የበለጠ ፈታኝ ነው። ወንጌሉ ከጎሳ፣ ከሀገር እና ከባህላዊ ምቾት ክልላችን እንድንወጣ እና ከእኛ ምንም ያህል ቢለያዩም የተቸገሩትን እንድንደርስ ጥሪ ያቀርብልናል።

ዘዳግም 10:19፣ መዝሙር 146:9፣ ሮሜ 12:13፣ እና ዘሌዋውያን 23:22ን ያንብቡ። በነዚህ ጥቅሶች ውስጥ ልናስታውሰው የሚገባን አስፈላጊ ጭብጥ ምንድን ነው?



ስደተኞችን እንዴት ማገልገል እንችላለን? አስቸጋሪ ነው፤ ምክንያቱም በአንዳንድ አገሮች ከእነዚህ ሰዎች ጋር መቀላቀል ወይም እነርሱን መርዳት በፖለቲካዊ እይታ ትክክል ላይሆን ይችላል። ነገር ግን በጣም አስቸጋሪ ጊዜያት ያለፉ እና የእኛ እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን እነዚህን ሰዎች ለማገልገል የምንችለውን ማድረግ አለብን። ስለዚህ በምንችለው ደረጃ መርዳት አለብን።

በጸሎት ይጀምሩ፣ ከዚያም ስለ ስደተኞች መረጃ ይፈልጉ። በብዙ ቦታዎች ለእነሱ እንክብካቤ የሚያደርጉ ድርጅቶች አሉ። ከድርጅቶቹ ውስጥ ከአንዱ ጋር መስራት መጀመር ትችላላችሁ፤ ወይም ምናልባት በአካባቢያችሁ የሚገኘው የቤተክርስቲያን ሰንበት ትምህርት ቡድን የስደተኞች አገልግሎት ሊጀምር ይችላል።

ምንም እንኳን መጠኑ አነስተኛ ቢሆንም፣ እርስዎ የሚያውቋቸውን ስደተኞች ለመርዳት ምን ማድረግ ይችላሉ?

ህዳር 12
Nov 22

ተጎጂዎችን መርዳት


በአለማችን ውስጥ ያሉትን ጎጂ ነገሮች ያልቀመሰ ማን አለ? በሀብት እና በቁሳቁስ ተከበን ብንኖር፣ ወይም በድህነት ብንኖር - አስቸጋሪ ነገሮችን ከማየት አንፃር ልዩነት የለም። ሰዎች እየተጎዱ፣ እየተሰቃዩ፣ እየታገሉ ናቸው። ቁሳዊ ሀብት ብቻውን ደስታን ወይም ሰላምን ሊሰጥ እንደማይችል ለመረዳት በምዕራቡ ዓለም በየዓመቱ ለጭንቀት መድኃኒቶች የሚወጣውን ከፍተኛ የገንዘብ መጠን ማየት ብቻ በቂ ነው። “የእግዚአብሔር መንፈስ በእኔ ላይ ነው፥ ለድሆች ወንጌልን እሰብክ ዘንድ ቀብቶኛልና፤ ልባቸው የተሰበረውን እንድፈውስ፥ ለታሰሩትም ነጻነትን ለዕውሮችም ማየትን፥ የተገፉትንም ነጻ አወጣ ዘንድ ልኮኛል” (ሉቃስ 4፡18) ይህ ኢየሱስ ስላደረገው ነገር እና እኛም በዙሪያችን ለተቸገሩ ሰዎች ማድረግ ስላለብን ነገር ምን ያስተምረናል?



ኢየሱስን መቼ እንደሚቀበሉ ባናውቅም የሁሉንም ሰዎች ፍላጎት እንድናሟላ እግዚአብሔር እየጠራን ነው። እነርሱን በወንጌሉ መድረስ የተልእኮአችን መሠረት ቢሆንም ስለሚያስፈልጋቸው ብቻ የተቸገሩትን መርዳት አለብን። እኛ የምንረዳቸው ኢየሱስን እንደ ጌታችን ስለተቀበልን ነው፤ እርሱም እንድናደርገው የጠራን ይህንን ነው።

እንደ ኢየሱስ የሁሉንም ሰዎች ፍላጎት ለማሟላት መሞከር ልንከተለው የሚገባን መጽሐፍ ቅዱሳዊ መመሪያ ነው። የረዳቸው ሰዎች ሁሉ እርሱን እንደተቀበሉት ወይም እንዳልተቀበሉት የምናውቀው ነገር የለም።

ሌሎችን በእውነት ለመርዳት ፍላጎታቸውን ማወቅ አለብን። እያንዳንዱ ባህል ጓደኛን እንዴት መያዝ እንዳለበት የሚያሳይ የራሱ መንገድ አለው። በህንድ ውስጥ ጎብኝዎችን ሲቀበሉ ምግብ ወይም መጠጥ ማቅረብ የተለመደ ነው። በዚያ ሀገር የሚወደውን ሰው በሞት ያጣውን ጓደኛ ከማጽናናት ይልቅ ለማያውቁት ሰው ገንዘብ መስጠት ቀላል ነው። ጓደኛዎ የሚያስፈልገው ከገንዘብ ወይም ከሥጋዊ ነገሮች በላይ ሊሆን ይችላል። ብዙ ጊዜ በከባድ ችግር ወቅት የርህራሄ ድጋፍዎ የበለጠ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል።

ለወዳጆቻችን የኢየሱስ እጅ ለመሆን በመጀመሪያ ለእነርሱ ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር በማሳየት ይጀምራል፤ ከዚያም እርዳታ ለመስጠት ከመሞከር በፊት በመጀመሪያ ፍላጎታቸውን መረዳት ወሳኝ ነው። ኢየሱስን ለመከተል ዝግጁ መሆናቸውን ባያውቁም የሚያስፈልጋቸውን እርዳታ አቅርቡላቸው።

ማቴዎስ 25:34-40ን ያንብቡ። በዚህ ጥቅስ ውስጥ ለእኛ የሚሰጠን መልእክት ምንድን ነው?

ህዳር 13
Nov 23

ከፍ ያለ ፍቅር


ሁላችንም እንደምናውቀው ፍላጎቶች መቼም አያልቁም። ሌሎችን ለመርዳት ፈቃደኛ ከሆኑ ብዙ እድሎች ያገኛሉ። የቅርብ ወዳጆችም ሆኑ በሩቅ ያሉ ስደተኞች፣ በችግር ላይ ያሉ ስላሉ በምንችለው ጊዜ ለመርዳት የምንችለውን ማድረግ አለብን።

ኢየሱስ በምድራዊ አገልግሎቱ በሙሉ ራሳቸውን መርዳት የማይችሉትን ረድቷል። በአንዳንድ ሁኔታዎች፣ እሱ ቅድሚያውን ወስዶ ወደተቸገሩት ሄደ፤ በሌሎች ሁኔታዎች ሽባውን ወደ ኢየሱስ ለማምጣት ከጣሪያው ላይ እንዳወረዱት ሰዎች ጓደኞች ቅድሚያውን የወሰዱበት ጊዜ አለ።

“ነፍሱን ስለ ወዳጆቹ ከመስጠት ይልቅ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም።” (ዮሐንስ 15፡13) በአገልግሎታችን ላይ ይህን መሠረታዊ መርህ ለሌሎች ተግባራዊ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?



አንድ የሚሲዮናውያን ቤተሰብ በትሪንዳድ እና ቶቤጎ ለስድስት ዓመታት አገልግሏል። የመጀመሪያዎቹን ሶስት አመታት የኖሩት በብዛት በሂንዱ እና በሙስሊም ማህበረሰብ ውስጥ ነበር። ብዙ ሂንዱዎች ለዓመታዊ የምስጋና አገልግሎት ሲጠሯቸው ክርስቲያኖች ግብዣቸውን ውድቅ በማድረጋቸው ቅሬታ ያቀርቡ ነበር። አንድ ቀን እነዚህ ክርስቲያኖች በአዲስ የሂንዱ ጓደኛ የምስጋና አገልግሎት ላይ ተገኙ። ይህን ያደረጉት የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል ነው፡- ጓደኞቹ ወደ ልዩ በዓላቸው ሲጠሩት ጎበኘ። እንደውም ሂንዱይዝም እንግዶች ወይም ጓደኞች ወደቤት ሲመጡ በረከቶችን እንደሚያመጡ ያስተምራል።

ለአንድ ሰው በረከት በመሆን በዚህ ሳምንት ጓደኛ ማፍራት ለመጀመር እንሞክር። በመጀመሪያ፣ የአካባቢውን አውድ፣ ማህበረሰብ፣ መንደር ወይም ከተማ ይቃኙ። እዚያ የሚኖር ስደተኛ ያውቃሉ? በመንገድዎ ላይ ስለሚኖሩ ሰዎችስ? ሁሉንም ያውቋቸዋል? ሁኔታዎ ምንም ይሁን ምን ከማያውቁት ሰው ጋር ጓደኝነት መመሥረት ቀላል ሥራ አይደለም። እንጸልይ እና እርዳታ ለማግኘት እግዚአብሔርን እንለምን። እሱ ሁሉንም ያውቃል እና ጓደኛ የምታደርጉትን እንግዳ ያውቃል። ያስታውሱ፣ ዓላማው ወደ እግዚአብሔር በመምራት መርዳት እንድንችል ጓደኛቸው መሆን ነው።

ግድድሮሽ፡- በአገርዎ ስለሚኖሩ የውጭ አገር ዜጎች ወይም ክርስቲያን ያልሆኑ ሰዎች ለማወቅ ይሞክሩ። Joshuaprojects.org በባህልዎ ውስጥ ያልተደረሱ ቡድኖችን ለመቃኘት ጥሩ ቦታ ነው።

ከፍ ያለ ግድድሮሽ፡- በእርስዎ የተፅዕኖ መስክ ውስጥ የሆነን ሰው ይለዩ። የሚከተሉትን ጥያቄዎች ከመለሱ በኋላ አዘውትረው ለግለሰቡ መጸለይ ይጀምሩ።

• ኢየሱስ ባሳየኝ የወዳጅነት ምሳሌ መሠረት ይህ ሰው ባልንጀራዬ ነው? • የእሱን ወይም የእሷን ፍላጎት አውቃለሁ? • ፈውስ እንዲያገኝ/እንድታገኝ እሱን ወይም እሷን ወደ ኢየሱስ ልመራ የምችለው እንዴት ነው?

ህዳር 14
Nov 24


ተጨማሪ ሀሳብ


አርተር ዋይት የፃፈውን፣ “ጥቂት ቀናት በሎንግ ፖይንት” እና ኤለን ጂ. ኋይት የፃፈችውን “የአውስትራሊያ ቆይታዬ፡ 1891-1900” ከሚለው መጽሐፍ ውስጥ፣ ጥራዝ. 4፣ ገጽ 100-104ን ያንብቡ።

የወንጌል ጸሓፊዎች ሰዎችን ለማዳን ሲል ኢየሱስ ከሌሎች ባህሎች ጋር ድልድዮችን የገነባባቸውን ምሳሌዎች ዘግበዋል (ማቴ. 8፡28-34፣ ማር. 5፡1-20)።

በተመሳሳይ፣ እኛ ደግሞ ከሌሎች ባህሎች የመጡ ሰዎችን እንድናፈራ እና እንድናገለግል ተጠርተናል። የክርስቶስ ሞት ዘር፣ ዜግነት፣ ሀብት፣ ወይም የኋላ ታሪክ ሳይለይ ለሁሉም ሰው ነው። ይህ መቼም ልንረሳው የማይገባ ነጥብ ነው። “እርሱም የኃጢአታችን ማስተስሪያ ነው፥ ለኃጢአታችንም ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን ለዓለሙ ሁሉ ኃጢአት እንጂ።” (1ኛ ዮሐንስ 2፡2)።

“ወንዶችና ሴቶች ሊረዷቸው የሚችሏቸውን ሰዎች አግልለው . . . ለቤተሰባቸው ብቻ ያላቸውን ፍቅር ሲገልጹ የአምላክን ንድፍ እያሟሉ አይደለም።”

“ጌታ ከቤታችን ውጭ ለሌሎች መልካም እንድናደርግ ሲነግረን፣ ለቤት ያለን ፍቅር ይቀንሳል ማለት አይደለም፤ ለሌሎች ርህራሄ እንድናሳይ ስለጠራን ለዘመዶቻችን ወይም ለአገራችን ያለን ፍቅር ይቀንሳል ማለት አይደለም። እኛ ግን ፍቅራችንን እና ርኅራኄን በአራት ግድግዳዎች ውስጥ ገድበን ሌሎች ከእኛ ጋር መደሰት እንዳይችሉ አምላክ የሰጠንን በረከት መከለል የለብንም።”— Ellen G. White, The Advent Re- view and Sabbath Herald, Oct. 15, 1895

ከሌላ ባህል ለመጡ ወይም ረዳት አልባ ለሆኑና ከእኛ ምቾት ክልል ውጪ ላሉ ሰዎች በረከት እንድንሆን የተሰጠን ኃላፊነት ከራሱ ከኢየሱስ ክርስቶስ የተሰጠ ለድርድር የማይቀርብ ኃላፊነት ነው (ሐዋ. 1፡8፣ ማር. 11፡17)።


የመወያያ ጥያቄዎች




1. የእርስዎ ምቾት ክልል ምንድን ነው? እና አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ከእሱ ውጭ ለመውጣት ፈቃደኛ መሆን ያለብዎት ለምንድን ነው?

2. ኢየሱስ “ ሆዳምና ሰካራም፣ የቀረጥ ሰብሳቢዎችና የኃጢአተኞች ወዳጅ” (ማቴ. 11:19) ተብሎ በተጠራበት ወቅት የተከሰተው ሁኔታ አንድምታ ምንድን ነው? ኢየሱስ እንዲህ እንዲባል ያደረገው ምን ነበር? ስለ ተልእኮስ ምን ያስተምረናል?

3. አንድ ክርስቲያን አማኝ ያልሆኑ ሰዎችን ደስታ መካፈል ያለበት እስከ ምን ድረስ ነው? ክርስቲያኖች የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ መርሆች ሳይጥሱ ይህን ማድረግ የሚችሉት እንዴት ነው?




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA Union SSL