የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ለዚህ ሳምንት ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡- ሉቃስ 10፡25-37፣ 2 ጢሞ. 3:16፣
ያዕቆብ 2:17-22፣ ማቴ. 22:37-40፣ ገላ.5:14፣ ሚክያስ 6:6-8።
መግቢያ ጥቅስ፡- “እርሱም መልሶ፦ ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍ
ስህም በፍጹም ኃይልህም በፍጹም አሳብህም ውደድ፥ ባልንጀራህንም እንደ ራስህ
ውደድ አለው።” (ሉቃስ 10:27)
ሁላችንም ጥቅሱን እናውቀዋለን: “ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም
ነፍስህ በፍጹም ኃይልህ በፍጹም አሳብህ ውደድ” (ሉቃስ 10:27)። ነገር ግን
እግዚአብሔርን እንወዳለን ብለን እርሱን የማንታዘዝ ከሆነ ለእግዚአብሔር
ያለን ፍቅር የላይ ላይ ይሆናል። እግዚአብሔርን እንደምንወደው እናስባለን፤ ነገር ግን
ይህ ፍቅር በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ውስጥ የሚገለፀው እንዴት ነው? እግዚአብሔርን
መውደድ የልባችንን፣ የነፍሳችንን፣ የአካላችንን እና የአዕምሮአችንን ሙሉ ቁርጠኝነት
በየቀኑ ይጠይቃል። ማንም ሰው አምላክን እንደሚወድ ሊናገር ይችላል፤ ይህን ማድረግ
ግን የነቃ ጥረት ይጠይቃል።
እግዚአብሔርን መውደድ መልካም እና አስፈላጊ ቢሆንም እንኳን እግዚአብሔር
ሌሎችን እንድንወድ ይፈልጋል፤ ምክንያቱም ለሌሎች ያለን ፍቅር ለእግዚአብሔር
ያለንን ፍቅር ያሳያል፤ ይህም ሲገለፅ በኃይለኛ እና በጣም እውነተኛ በሆነ መንገድ
ነው። 1ኛ ዮሐንስ 4፡20 “ማንም፦ እግዚአብሔርን እወዳለሁ እያለ ወንድሙን ቢጠላ
ሐሰተኛ ነው፤ ያየውን ወንድሙን የማይወድ ያላየውን እግዚአብሔርን ሊወደው እንዴት
ይችላል?” ይላል። በተጨማሪም ጳውሎስ በገላትያ 5፡14 ላይ “ሕግ ሁሉ በአንድ ቃል
ይፈጸማልና፥ እርሱም፦ ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ የሚል ነው።” ይላል።
በዚህ ሳምንት ይህ ትምህርት በህይወታችን ውስጥ እንዴት እንደሚተገበር
እንማራለን።
*ለህዳር 8 ለሰንበት ለመዘጋጀት የዚህን ሳምንት ትምህርት ያጥኑ።
እኛ ማን ነን? ለምንድነው እዚህ ያለነው? ስንሞት ምን ይሆናል? የመጨረሻ
ዕጣችን ምንድን ነው? እነዚህ በብዙ መልኩ ሟች ፍጡራን ወይም ሟች መሆናቸውን
የሚያውቁ ፍጡራን የሚጠይቋቸው በጣም ወሳኝ ጥያቄዎች ናቸው። እናም በሉቃስ
ወንጌል ውስጥ፣ አንድ ሰው ከሁሉም በጣም አስፈላጊ የሆነውን ጥያቄ ወደ ኢየሱስ ይዞ
መጣ።
ሉቃስ 10:25ን ያንብቡ። ይህ ህግ አዋቂ ምን ጠየቀ? ይህንንስ ጥያቄ
ለምን ጠየቀ?
ጥያቄው የፈለገ ወሳኝ ቢሆንም መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስን ለመፈተን እንደ መጣ
በግልጽ ይናገራል። አንዳንድ ጊዜ አንዳንድ ሰዎች በጥርጣሬ፣ ባለማመንም ሊመጡ
እንደሚችሉ እና እንዲያውም ጥያቄያቸውን ከልባቸው ላይጠይቁ ይችላሉ፤ ነገር ግን
እነዚህም ሰዎች በእውነቱ ሊነኩ ይችላሉ። ኢየሱስ የሰውዬው የመጀመሪያ ዓላማ ከልቡ
እንዳልሆነ ቢያውቅም ከህግ አዋቂው ጋር የተገናኘው በዚህ መንገድ ነበር። ሆኖም ለህግ
አዋቂው እና ለታዳሚዎቹ፣ ይህ ጥያቄ ኢየሱስ የራሳቸውን ልብ እንዲመረምሩ ለማድረግ
እንደ እድል ተጠቀበመበት። ኢየሱስ የህግ አዋቂውን መነሻ ምክንያት ቢያውቅም እሱን
ችላ አላለውም።
ደግሞስ ከዚህ የበለጠ ምን ጥያቄ ሊኖር ይችላል? “የዘላለምን ሕይወት
እንድወርስ ምን ላድርግ?” ሀይማኖታዊ ስርአታችን ወይም ልምምዳችን ምንም ይሁን
ምን ከኋላቸው ይህ ወሳኝ ጥያቄ አለ። ከዚህ በተቃራኒ፣ ሕይወታቸው “ለትንሽ ጊዜ
ታይቶ እንደሚጠፋ እንፋሎት” (ያዕቆብ 4፡14) ተብሎ ለተገለጡ እንደኛ ላሉ ፍጡራን
ሌላ ምን ሊያሳስበን ይችላል? ከዘላለም ሕይወትና ከዘላለም ሞት ሌላ አማራጭ ምንድን ነው?
1 ቆሮንቶስ 15:30-32ን ያንብቡ። ጳውሎስ እዚህ ላይ የዘላለም
ሕይወትን አስፈላጊነት በሚያጎላ መልኩ ምን ተናገረ?
መነሻ ምክንያቱ አጠራጣሪ ቢሆንም የህግ አዋቂው አንድ ወሳኝ ጥያቄ ጠይቋል፤
ማንኛውንም እድል ለተልእኮ ለመጠቀም ሁልጊዜ በንቃት ይከታተል የነበረው ኢየሱስ
ነፍሳትን ለመድረስ ተጠቀመበት።
ሁኔታዎች ተስማሚ ባይሆኑም እንኳ ባገኘናቸው አጋጣሚዎች
ተጠቅመን መመስከር የምንችለው እንዴት ነው?
መጽሐፍ ቅዱስ ሕግ አዋቂው ኢየሱስን ሊፈትነው እንደመጣ ይነግረናል፤ ኢየሱስ
ግን ዓላማውን አውቆ ነበር። በእርግጥም እግዚአብሔር የልባችንን ፍላጎት እና ናፍቆት
ከእኛ በላይ ያውቃል። እኛ ደግሞ የሚጠይቁንን ሰዎች ልብም ሆነ ውስጣዊ ዝንባሌ
አናውቅም፤ እናውቃለን?
አንዳንድ ጊዜ የሌላ እምነት ተከታዮች ስለ እምነታችን ይጠይቁናል። ለምሳሌ፣
ሙስሊም ጓደኞቻችን ከኢየሱስ አምላክነት ጋር የተያያዙ ጥያቄዎችን ይጠይቁናል፣
ለምሳሌ፣ “ኢየሱስ አምላክ ነው ያለው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የቱ ጋ ነው?” ወይም
“ሥላሴ ሦስት አካላት ሲኖሯቸው አንድ አምላክ አለ ለምን ትላላችሁ?” ብለው ሊጠይቁን
ይችላሉ። እነዚህ ጥያቄዎች ቀስቃሽ ቢመስሉም ጥያቄዎችን የሚጠይቁት ሰዎች
ኢየሱስን ከልባቸው ፈልገውት ባዶነትም ተሰምቷቸው ሊሆን ይችላል። እኛ ልባቸውን
አናውቅም፤ የግድ ማወቅም አያስፈልገንም። የእነርሱ ጥልቅ ዓላማ ምንም ይሁን ምን
ሌሎችን በምንችለው ሁሉ ማገልገል አለብን።
ማቴዎስ 26:56ን፣ የሐዋርያት ሥራ 17:11ን፣ 1 ቆሮንቶስ 15: 3ን እና 2
ጢሞቴዎስ 3: 16ን ያንብቡ። እነዚህ ጥቅሶች በሉቃስ 10፡26 ላይ ኢየሱስ
ለህግ አዋቂው የሰጠውን ምላሽ እንድንረዳ የሚያግዙን እንዴት ነው?
አንዳንድ ጊዜ መልሶችን እንፈልጋለን ነገር ግን እነርሱን ለማግኘት አንንቀሳቀስም።
ኢየሱስ “በሕግ የተጻፈው ምንድር ነው? እንዴትስ ታነበዋለህ? አለው።” (ሉቃስ 10:26)። ኢየሱስ
የመማርን በጣም አስፈላጊ ገጽታ ጠቁሟል። ሌሎች የሚነግሩንን ብቻ ከመስማት ይልቅ
ለራሳችን ቅዱሳት መጻሕፍትን (የእግዚአብሔርን ቃል) ማንበብ አለብን። መልሶቹ ቀድሞውኑ
አሉ፤ መንፈስ ቅዱስ ደግሞ ምን ማድረግ እንዳለብን ሊያሳየን በልባችን ላይ ይሰራል።
እግዚአብሔር ቃሉን ሰጥቶናል። በዚህ መጽሐፍ ውስጥ፣ እንዴት መኖር
እንዳለብን፣ ሌሎችን እንዴት መያዝ እንዳለብን እና ‘የዘላለም ሕይወትን መወረስ’
ስለምንችልበት መንገድ ማወቅ ያለብንን እውነት ሁሉ እናገኛለን። በእርግጥ
የአስተማሪዎችና የአገልጋዮች ሚና አለ፤ ነገር ግን በመጨረሻ አስፈላጊ ለሆኑት እውነቶች
ወደ መጽሐፍ ቅዱስ መሄድ ይኖርብናል። “ቃልህ ለእግሬ መብራት ለመንገዴም ብርሃን
ነው” (መዝ. 119፡105)። ይህ ጥቅስ ግጥም ብቻ አይደለም፤ ወደ እግዚአብሔር ቃል
የሚያመላክት እና ለአማኙ ያለውን ጠቀሜታ የሚያሳስብ ቅዱስ እውነት ነው።
ኢየሱስ፣ ሥጋ የሆነው የእግዚአብሔር ቃል፣ ሁልጊዜ ሰዎችን ወደ
ተጻፈው ቃል ይጠቁማል። ይህ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ አስፈላጊነት ምን
ሊነግረን ይገባል? እንዲሁም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያለንን እምነት
የሚቀንስ ማንኛውንም ፍልስፍናዊ ወይም ሥነ-መለኮታዊ ሐሳብ
መቃወም ያለብን ለምንድን ነው?
ሉቃስ 10:27-28ን ያንብቡ። የሕግ አዋቂው ለራሱ ጥያቄ የሰጠው መልስ ምን ነበር?
ህግ አዋቂው ጥያቄውን የጠየቀ ሲሆን እሱ ራሱ መልሱን ሰጥቷል:- “ ጌታ አምላክህን
በፍጹም ልብህ ውደድ . . . ” እና “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” (ሉቃስ 10፡27)።
የኢየሱስ ምላሽ ምን ነበር? እርሱም፡- “እውነት መለስህ፤” አለው (ሉቃስ 10፡
28)። ሲቀጥልም ኢየሱስ “ይህን አድርግ በሕይወትም ትኖራለህ” በማለት በተግባር ላይ
እንዲያውለው ተገዳደረው(ሉቃስ 10፡28)።
ለአብዛኞቹ አማኞች ስለ ትምህርት እና እምነት ትክክለኛ መልስ መስጠት ያን
ያህል ከባድ አይደለም። ይልቁንም ተግዳሮቱ የሚያውቁትን በመሥራት እና ያመኑትን
መከተሉ ላይ ነው። ለመዳን በቂ እውቀት ቢኖራቸውም የሚያውቁትን ስላልታዘዙ ብዙ
ሰዎች ይጠፋሉ። ይህ ጉዳይ ያን ያህል አሳሳቢ ነው። እግዚአብሔርን እና ባልንጀራህን
ስለመውደድ ማወቅ ብቻ በቂ አይደለም። መተግበር አለብን!
ያዕቆብ 2:17-22ን ያንብቡ። እነዚህ ጥቅሶች ኢየሱስ ለሕግ አዋቂው
ከተናገረው ጋር የሚመሳሰሉት እንዴት ነው?
እግዚአብሔርን የምንወድ ከሆነ ቃሉን እናነባለን፣ እንጸልያለን፣ ትእዛዙን
እንጠብቃለን፣ እናም “በፍጹም ልባችን” ለድምፁ ታዛዥ እንሆናለን። ሌሎችን እወዳለሁ
ካልኩ፣ ነገር ግን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ስለሌሎች ግድ ከሌለኝ፣ ወይም መርዳት
ስችል የሌሎችን ፍላጎት ችላ ካልኩ፣ እምነቴ ምን ይጠቅማል? ክርስትና የተለያዩ
አስተምህሮዎች ስብስብ ብቻ አይደለም፤ የሕይወት መንገድ ነው።
“ወንድም ወይም እኅት ራቁታቸውን ቢሆኑ የዕለት ምግብንም ቢያጡ፥
ከእናንተም አንዱ፡— በደኅና ሂዱ፥ እሳት ሙቁ፥ ጥገቡም ቢላቸው፥ ለሰውነት ግን
የሚያስፈልጉትን ባትሰጡአቸው፥ ምን ይጠቅማቸዋል?” (ያዕቆብ 2:15-16)።
ለሌሎች ደህንነት ምን ያህል ያስባሉ? ቀጥሎ የተፃፈውን የጳውሎስን
ምክር ምን ያህል እንከተላለን? “እያንዳንዱ ለራሱ የሚጠቅመውን
አይመልከት፥ ለባልንጀራው ደግሞ እንጂ።” (ፊልጵ. 2፡4) በእግዚአብሔር
ጸጋ፣ ለሌሎች የበለጠ ማሰብን መማር የምንችለው እንዴት ነው?
ማቴዎስ 22:37-40ን ያንብቡ። እዚህ ላይ ኢየሱስ ራሱ የተናገረው በሉቃስ 10፡27-28 ላይ ለህግ አዋቂው ከሰጠው መልስ ጋር እንዴት ይመሳሰላል?
በማቴዎስ 22፡37-40 መሠረት፣ ኢየሱስ የዕለት ተዕለት የእውነተኛ እምነት
መግለጫ በእነዚህ ሁለት ትእዛዛት ላይ እንደሚንጠለጠል ግልጽ አድርጓል። ሉቃስ
10:27-28 ደግሞ አንድ ሰው እነዚህን ሁለት ነገሮች ቢያደርግ የዘላለም ሕይወት
እንደሚኖረው በግልጽ ይናገራል።
“ፍቅር በሰማይና በምድር ያለው የአምላክ መንግሥት መሠረታዊ መርህ ነው፤
እሱም የክርስቲያን ባሕርይ መሠረት መሆን አለበት። ቀጥ ብሎ እንዲቆም እና እንዲፀና
ሊያደርገው የሚችለው ይህ ብቻ ነው። ፈተናን እንዲቋቋም የሚያስችለው ይህ ብቻ
ነው።” Ellen G. White, Christ’s Object Lessons, p. 49
ገላትያ 5:14፣ ሚክያስ 6:6-8፣ እና 1 ዮሐንስ 4:20-21ን ያንብቡ።
እነዚህ ጥቅሶች ኢየሱስ የነገረንን የሚያጠናክሩት እንዴት ነው?
እንደ ጳውሎስ አነጋገር “ሕግ ሁሉ በአንድ ቃል ይፈጸማልና፥ እርሱም፡—
ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ የሚል ነው” (ገላ. 5፡14)። ለጳውሎስ አምላክን መውደድ
በተግባር ሊታይ የሚችለው ያንን ፍቅር ለሌሎች በምንገልጥበት ጊዜ ብቻ ነው። ምንም
እንኳን ጳውሎስ “ጻድቅ በእምነት ይኖራል” (ሮም 1:17) ብሎ ቢናገርም በእምነት መኖር
የተደበቀ፣ የማይታወቅ፣ ወይም የማይታይ ነገር አይደለም። ጳውሎስ፣ ሚክያስ እና
ዮሐንስ ተግባራችን የምንናገረውን እምነት እውነትነት እንደሚያሳዩ ግልጽ አድርገዋል።
ጳውሎስ በ1ኛ ቆሮንቶስ 13 ላይ፣ አንድ ሰው ትልቅ እውቀት አለኝ፣ ወይም ታላቅ
ስራ እሰራለሁ፣ ወይም ታላቅ እምነት አለኝ፣ ወይም ነፍሴን ለሌሎች አሳልፌ ሰጥቻለሁ
ብሎ ቢናገር ፍቅር ግን ከሌለው ያ ሰው “እንደሚጮኽ ናስ ወይም እንደሚንሽዋሽዋ
ጸናጽል” (1ኛ ቆሮ. 13፡1) ነው ይላል።
ከላይ ያለውን የኤለን ጂ. ኋይት ጥቅስ ይመልከቱ። ሰዎች በፍቅር
ብቻ እንዴት ጸንተው ሊቆዩ እንደሚችሉ እና ፈተናን እንደሚቋቋሙ
የምትናገረውን ያስተውሉ። ይህ ሐሳብ ሌሎችን የመውደድ ትእዛዝ
በሥራ የመዳን ሳይሆን በኢየሱስ ላይ ያለን እምነት መግለጫ መሆኑን
የሚያሳየው እንዴት ነው?
ኢየሱስ ሕግ አዋቂው ትክክለኛውን መልስ መስጠቱን ከገለፀ በኋላ “ይህን
አድርግ በሕይወትም ትኖራለህ” (ሉቃስ 10:28) አለው። በዚህም መንገድ የሰውየውን
ልብ ነክቶታል። ትክክለኛውን መልስ መስጠት ለጠበቃው ቀላል ነበር፤ ነገር ግን እነዚህን
ነገሮች ማድረግ ከ 2,000 ዓመታት በፊትም ዛሬም በጥያቄ ውስጥ ነው። ሕግ አዋቂው
ኢየሱስን ለማጥመድ እና እውቀቱን ለማሳየት ፈለገ። ቀጥሎም “ባልንጀራዬ ማን ነው?”
(ሉቃስ 10:29) ብሎ ጠየቀ።
ሉቃስ 10፡30-37ን ያንብቡ። በዚህ ታሪክ ውስጥ ኢየሱስ ሊል የፈለገውን
እንዴት ትገልፁታላችሁ?
በሌሎች ሰዎች በደል የደረሰባቸው ሰዎች በዙሪያችን አሉ? እነሱን ለመርዳት
የምንችለውን ሁሉ አድርገናል?
እውነት ነው አንዳንድ ጊዜ ፓስተሮች፣ ሽማግሌዎች እና አባላት እርዳታ
የሚያስፈልጋቸውን አይረዱም። አንዳንድ ጊዜ የሌላ እምነት ተከታዮች ከእኛ ይልቅ
በማህበረሰቡ ውስጥ ላሉ ሰዎች ደግ ሊሆኑ ይችላሉ። ስለ ደግነት ልንናገር እንችላለን፤
ሌሎች ግን እኛ ያላየናቸውን ሰዎች ፍላጎት ሊያሟሉ ይችላሉ። እምነታችን ትርጉም
የሚሰጠው የተቸገሩትን ስንረዳ እና ስንደርስላቸው ነው።
ኢየሱስ ከሦስቱ መካከል እርዳታ ለሚያስፈልገው ሰው በእውነት ባልንጀራ
የሆነው ማን እንደሆነ በመጠየቅ የደጉን ሳምራዊ ታሪክ ደምድሟል።
“ስለዚህ፣ ‘ባልንጀራዬ ማን ነው?’ የሚለው ጥያቄ ለዘላለም መልስ አግኝቷል።
ክርስቶስ ባልንጀራችን ማለት እኛ የምንገኝበት ቤተክርስቲያን አባል ብቻ እንዳልሆነ
አሳይቷል። ዘር፣ ቀለም ወይም የመደብ ልዩነት የለውም። ጎረቤታችን የኛን እርዳታ
የሚፈልግ ሰው ነው። ባልንጀራችን በጠላት የተጎዳ እና የቆሰለ ነፍስ ሁሉ ነው። ጎረቤታችን
የአምላክ ንብረት የሆነ ሁሉ ነው።” ኤለን ጂ. ኋይት፣ የዘመናት ምኞት ገጽ. 503።
ግድድሮሽ፡- ከእርስዎ የተለየ ለሆነ ሰው ወይም በግል ለማትወዱት ሰው በየቀኑ
መጸለይ ይጀምሩ።
በተጨማሪ ቢያንስ ሦስት የሚያውቋቸውን (አድቬንቲስቶች ያልሆኑ)
ስሞችን ይዘርዝሩ። ፍላጎቶቻቸውን ይለዩ (ስሜታዊ፣ አካላዊ፣
ማህበራዊ) እና እነዚህን ፍላጎቶች እንዴት በግል ማገልገል እንደሚችሉ
ያስቡበት። በሚቀጥለው ሳምንት ለእነርሱ ምን ማድረግ ይችላሉ?
የዘመናት ምኞት ከሚለው መጽሐፍ ውስጥ “ደጉ ሳምራዊ” የሚል
ርዕስ ያለውን ምዕራፍ ያንብቡ።
ዛሬ በዓለማችን ብዙ የተራቡ፣ የተቸገሩ እና የተገፉ ሰዎች አሉ። ምንም እንኳን
“ትንሽ” ቢመስልም የእርስዎን ድርሻ መወጣት ይችላሉ። ኢየሱስ ከመመለሱ በፊት
ሁሉንም የዓለም ችግሮች መፍታት አንችልም። እኛ ይህን ለማድረግ አልተጠራንም።
ነገር ግን እስከዚያው ድረስ የእኛ ሥራ እርስዎ የሚያውቁትን ሰው በቂ ምግብ የሌለውን
የመርዳት ያህል መሠረታዊ ሊሆን ይችላል፤ ወይም በዓለማችን ላይ ዛሬም ቢሆን
እውነተኛ ችግር የሆነውን ኢፍትሃዊነትን አልፎ ተርፎም ጭፍን ጥላቻን የሚጋፈጠውን
የቤተ ክርስቲያን አባል መርዳት ሊሆን ይችላል።
“ንጹሕ የሆነ ነውርም የሌለበት አምልኮ በአብ ዘንድ ይህ ነው፤ ወላጆች
የሌላቸውን ልጆች ባልቴቶችንም በመከራቸው መጠየቅ፥ በዓለምም ከሚገኝ እድፍ
ሰውነቱን መጠበቅ ነው።” ያዕ. 1፡26። በጎ ሥራ ክርስቶስ እንድናፈራ የሚፈልገው ፍሬ
ነው፤ እርሱም መልካም ቃል፣ ለድሆችና ለችግረኞች ርህራሄ ማሳየትና በጎነትን ማድረግ
ነው። ልቦች በተስፋ መቁረጥ ለተሞሉት ልቦች ሲራሩ፣ እጆች ለተቸገሩት ሲዘረጉ፣
የታረዙት ሲለብሱ፣ እንግዳው በጓዳህና በልብህ ውስጥ ቦታን ሲያገኝ፣ መላእክት በጣም
ቀርበዋል፤ ጥረትም በሰማይ ዘንድ ይታያል። እያንዳንዱ የፍትህ፣ የምህረት እና የቸርነት
ተግባር በሰማይ ዜማን ይፈጥራል። አብ ከዙፋኑ እነዚህን መሀሪዎች ተመልክቶ ከርሱ
ውድ ሀብቶች ተርታ ይቆጥራቸዋል። “እኔ በምሠራበት ቀን እነርሱ የእኔ ገንዘብ ይሆናሉ
ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር” ለችግረኞች የሚደረጉ መልካምነቶች ሁሉ ለኢየሱስ
እንደተደረገ ይቆጠራል። ድሆችን ስትረዱ፣ ለተቸገሩትና ለተጨቆኑት ስትራሩ፣ ወላጅ
አልባ ከሆኑት ልጆች ጋር ወዳጅነት ስትመሠርቱ፣ ከኢየሱስ ጋር ይበልጥ የቀረበ ዝምድና
ትፈጥራላችሁ።”—Ellen G. White፣ Testimonies for the Church፣ Vol. 2, ገጽ. 25.
1. እግዚአብሔርን እና ሌሎችን እንድንወድ የተሰጠው ትእዛዝ መዳን
በሥራ እንዳልሆነ መረዳታችንን እንዴት ማረጋገጥ እንችላለን?
ኢየሱስ ማን እንደሆነ እና በመስቀል ላይ ያደረገልንን ስናስብ
(ፊልጵ. 2፡5-8 ይመልከቱ)፣ መዳንን ለማግኘት የምናደርገው
ማንኛውም ነገር ትልቅ ስህተት የሚሆነው ለምንድነው? ገዳይ
ስህተት የሆነውን በሥራ መዳንን እና በህይወታችን በኢየሱስ
ያገኘነውን ድነት በተግባር መግለጥን እንዴት መለየት እንችላለን?
2. ከእኛ ለየት ባሉ ሰዎች ላይ ሊኖረን የሚችለውን አንዳንድ ጭፍን
ጥላቻ ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው?
3. በዚህ ሳምንት ትምህርት ውስጥ ከተጠኑት ጥቅሶች ሌላ፣ ምንም
ይሁኑ ማን ለሌሎች ደግነት ማሳየት አስፈላጊ ስለመሆኑ ምን ሌላ
መጽሐፍ ቅዱሳዊ ድጋፍ ልናገኝ እንችላለን?