የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

የእግዚአብሔር ተልዕኮ የእኔ ተልዕኮ



4ኛ ሩብ ዓመት 2023


ጥቅምት 24 - 30

6ኛ ትምህርት

Nov 4 - 10




ለተልዕኮው መነሳሳትና መዘጋጀት



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሳምንት ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ሉቃስ 24፡1-12፣ ሉቃስ 24:36- 49፣ የሐዋርያት ሥራ 1:12-26፣ ዕብ. 10:24-25፣ የሐዋርያት ሥራ 2:1-41፣ 1 ቆሮ. 11፡1።


መግቢያ ጥቅስ፡- “ከእናንተ ጋር ሳለሁ በሙሴ ሕግና በነቢያት በመዝሙራትም ስለ እኔ የተጻፈው ሁሉ ይፈጸም ዘንድ ይገባል ብዬ የነገርኋችሁ ቃሌ ይህ ነው።” (ሉቃስ 24፡44)

ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ሰዎች እንዲህ ሲል ጽፏል:- “አንዳንዶች ከቅንአትና ከክርክር እንኳ ሌሎች ግን ከበጎ ፈቃድ የተነሣ ክርስቶስን ይሰብኩታል፤ እነዚህ ወንጌልን መመከቻ ለማድረግ እንደ ተሾምሁ አውቀው በፍቅር ይሰብካሉ፥ እነዚያ ግን በእስራቴ ላይ መከራን ሊያመጡብኝ መስሎአቸው፥ ለወገናቸው የሚጠቅም ፈልገው በቅን አሳብ ሳይሆኑ ስለ ክርስቶስ ያወራሉ። ምን አለ? ቢሆንም በሁሉ ጎዳና፥ በማመካኘት ቢሆን ወይም በቅንነት ቢሆን፥ ክርስቶስ ይሰበካል ስለዚህም ደስ ብሎኛል።” (ፊልጵ. 1፡ 15-18) ።

ኃይለኛ ቃላት! “በማስመሰል ወይም በእውነት” ክርስቶስ ይሰበካል—ጳውሎስም የፈለገው ይህን ነው። ይሁን እንጂ ክርስቶስን የምንሰብክበት፣ የተልእኮው ሥራ፣ ለሌሎች የምሥራቹን የምንሰብክበት ዓላማ በፍቅርና ከእውነት የመነጨ መሆን ይኖርበታል እንጂ ከራስ ወዳድነት ምኞት፣ ከምቀኝነት ወይም ከጠብ ሊሆን አይገባም።

ታዲያ ክርስቶስን እንድንሰብክ የሚያነሳሱን አንዳንድ ምክንያቶች ምንድን ናቸው? ይህን ለማድረግ የምንዘጋጅባቸው አንዳንድ መንገዶችስ የትኞቹ ናቸው?

በዚህ ሳምንት በእነዚህ ወሳኝ የተልእኮ ክፍሎች ላይ መመሪያ ሊሰጡን የሚችሉትን አንዳንድ በጥንቷ ቤተ ክርስቲያን የተደረጉ ክስተቶችን እንመለከታለን። *ለህዳር 1 ሰንበት ለመዘጋጀት የዚህን ሳምንት ትምህርት ያጥኑ።

ጥቅምት 25
Nov 05

የምሥራቹን ለማካፈል


ሉቃስ 24:1-12 ያንብቡ። ስለ ክርስቶስ ከሞት መነሳት የሰሙት ሰዎች ምላሽ ምን ነበር?



ኢየሱስ ከሞተ በኋላ እሁድ ማለዳ ላይ፣ ሉቃስ በርካታ ሴቶች ወደ መቃብሩ እንደሄዱ ተናግሯል። ሰንበት ስላለፈ የኢየሱስን አስከሬን ለመቀባት ፈልገው ሽቱ ይዘው ነበር። የተዘጋ መቃብር እናገኛለን ብለው ሲጠብቁ መቃብሩ ባዶ ሆኖ በማግኘታቸው ደነገጡ። ምን ማድረግ እንዳለባቸው ግራ ተጋብተው እያሉ ሁለት የሚያብረቀርቅ ልብስ የለበሱ ሰዎች ሲታዩ የበለጠ ፈሩ። ይሁን እንጂ ሰዎቹ ለእነሱ መልእክት ነበራቸው፤ ኢየሱስ የተናገረውን በማስታወስ፣ ኢየሱስ እንደተናገረው በእርግጥ እንደተነሳ ለሴቶቹ ነገሯቸው። በዜናው በጣም ተደስተው ደቀ መዛሙርቱና ሌሎች ብዙ የኢየሱስ ተከታዮች ወደ ነበሩበት ተመለሱና ያዩትንና የሰሙትን ተናገሩ፤ ምክንያቱም ደስታቸው ሊገታ አልቻለም። በዚህም ስለ ክርስቶስ ያወቁትን ለሌሎች እያካፈሉ ነበር።

እርስዎ ሴቶቹ ምን ሊሰማቸው እንደሚችል መገመት ይችላሉ? በጣም የሚያስደንቅ ነገር አጋጥሟቸዋል፤ ይህም በእርግጥ በአድናቆት ሞልቷቸዋል፤ ነገር ግን ደቀ መዛሙርቱ የነገሯቸውን “ከንቱ ተረት” ብለው ጠሩት እና አላመኑአቸውም።

ቢሆንም ጴጥሮስ ሴቶቹን ማመን ወይም አለማመን እንዳለበት እርግጠኛ ስላልነበረ ራሱ ለማየት ወደ መቃብሩ ሮጠ።

ለጴጥሮስ- እና ለብዙዎቻችን- ሌላ ሰው ስለተናገረ ብቻ አንድን ነገር ለመቀበል እንቸገራለን። ጴጥሮስ ሴቶቹን ቢያዳምጣቸውም ራሱ እስኪያይ ድረስ ልምዳቸውን መካፈል አልቻለም። በመጀመሪያ ያጋጠመው ባዶ መቃብር ብቻ ነበር፤ እና ሉቃስ እንደፃፈው በቀላሉ “ለራሱ እየተደነቀ” ከዚያ ወጣ (ሉቃስ 24፡12)። በመቃብሩ ላይ ያጋጠመው ነገር ከሴቶቹ ጋር ተመሳሳይ አልነበረም።

ጴጥሮስ የሰጠው ምላሽ ምንም ይሁን ምን እነዚህ ሴቶች ስለ ኢየሱስ የሰሙትን ዜና ለሌሎች ማካፈል ፈለጉ። ኢየሱስ ያደረገላቸውን ለሌሎች ከማሳወቅ የበለጠ ለተልእኮ የሚያነሳሳ ምን አለ? ብቸኛ ተስፋችን በሆነው በኢየሱስ የመዳንን ምሥራች ከመስበክ የበለጠ ምን አነሳሽ ነገር ይኖራል?

እርግጥ ነው፣ ለሌሎች ከማካፈላችን በፊት ከአምላክ ጋር የግል ልምምድ ያስፈልገናል። በጣም የምንወደውን ለሌሎች ለማካፈል ያለን ፍላጎት ለተልእኮአችን መነሳሳት ወሳኝ አካል መሆን አለበት። ዞሮ ዞሮ እኛ እራሳችን የሌለንን ማካፈል አንችልም፤ እንችላለን?

በእግዚአብሔር መኖር እና በፍቅሩ ዙሪያ ያጋጠሟችሁ አንዳንድ ገጠመኞች ምንድን ናቸው? እነዚህ ጊዜያት በእርስዎ ዘንድ ውድ የሆኑት ለምንድን ነው? ምሥራቹን ለሌሎች እንዲሰብኩ የሚያነሳሱዎትስ እንዴት ነው?

ጥቅምት 26
Nov 06

ትንቢታዊ መሠረት


ሉቃስ 24:36-49ን ያንብቡ። እዚህ ምን ሆነ? ይህስ ለሐዋርያቱ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነገር የሆነው ለምንድን ነው?



በመጀመሪያ ደቀ መዛሙርቱ ያመኑት ከፍርሃት የተነሣ አለመሆኑ አስገራሚ ነው።

ከዚያም ኢየሱስን አይተው በእርግጥም ሕያው እንደሆነ ከተረዱ በኋላ ከደስታ የተነሣ አላመኑም (ሉቃስ 24፡41)። አንድ ነገር እውነት እንደሆነ ተሰምቶዎት ያውቃል? ይህ ደቀ መዛሙርቱ እና ሌሎቹም በላይኛው ክፍል ውስጥ የነበሩ ሰዎች ያጋጠማቸው ነበር።

ኢየሱስ የተዋቸው ይህን በማሳየት ብቻ ቢሆን ኖሮ ሲሄድ እምነታቸው ዘላቂ ላይሆን ይችል ነበር። ከጊዜ በኋላ የልምምዱ ኃይል ሊደበዝዝ ይችል ነበር፤ ሊረሱት ወይም መጠራጠር ሊጀምሩ ይችሉ ይሆናል። ስለዚህ ኢየሱስ ጠባሳዎቹን በማሳየት እና ከፊት ለፊታቸው ዓሣ በመብላት አላቆመም። ይልቁንም ወደ ቃሉ ወስዶ ስለ ሥራውና ስለ አገልግሎቱ የተፃፈውን ትንቢታዊ መሠረት አሳያቸው። ያም ማለት፣ ከእርሱ ጋር የነበራቸው ልምምድ ምንም ያህል ታላቅ ቢሆን፣ ኢየሱስ አሁንም እምነታቸው በእግዚአብሔር ቃል ላይ እንዲመሰረት ፈልጓል ማለት ነው።

“ከእናንተ ጋር ሳለሁ በሙሴ ሕግና በነቢያት በመዝሙራትም ስለ እኔ የተጻፈው ሁሉ ይፈጸም ዘንድ ይገባል ብዬ የነገርኋችሁ ቃሌ ይህ ነው” ( ሉቃስ 24: 44)።

እዚህም ለምሥክርነት ለተልዕኮ የሚሆን ኃይለኛ መነሳሻ እናገኛለን፡ ያም የእግዚአብሔር ቃል ነው። ኢየሱስ የደቀ መዛሙርቱን ተሞክሮ ለማጠንከር ለምን እንደሚሞትና ትንሣኤው ምን እንደሚያመለክት መረዳት እንደሚያስፈልጋቸው ያውቅ ነበር። እይታቸው ከፖለቲካዊ እና ምድራዊ መንግሥት ለኃጢአት ወደ ተሰጠው ታላቅ መፍትሄ እና በሞት ላይ ክርስቶስ ወደተቀዳጀው ድል እንዲሸጋገር ያስፈልግ ነበር። ወንጌል ለእስራኤል ፖለቲካዊ ሉዓላዊነትን ከማሳካት የበለጠ ነበር። ወንጌል ክርስቶስ በሰይጣን ላይ የተቀዳጀውን ድል በመግለፅ አንድ ቀን በዓለም ላይ ያሉ ክፋቶች በሙሉ እንደሚጠፉ፣ ምድር እንደ አዲስ እንደምትፈጠር እና አምላክ በሕዝቡ መካከል እንደሚሆን ዋስትና ሰጥቷል። ለዓለም የሚያካፍሏቸውን እነዚህን እውነቶች እንዲረዷቸው “አእምሮአቸውን ከፈተላቸው” (ሉቃስ 24:45)።

ከኢየሱስ ጋር ያሉን ልምምዶች ያለ ቃሉ መሰረት ሊጸኑ አይችሉም፤ ይህም ታሪክን የሚናገሩ ትንቢቶችን፣ የክርስቶስን የመጀመሪያ ምፅዓት እና ወደፊት ሁለተኛ ምጽዓቱን የሚናገሩ ትንቢቶችን ጨምሮ ማለት ነው። እነዚህን እውነቶች በደንብ ከተረዳን፣ ለተልእኮ ዝግጁ እና የተነሳሳን መሆን እንችላለን።

ስለ ክርስቶስ በተነገሩት ትንቢቶች፣ የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ምጽአቶቹ ላይ ምን ያህል መሰረት አላችሁ? በተለይ በመጨረሻው ዘመን፣ ትንቢቶቹን ጨምሮ በእግዚአብሔር ቃል ላይ መመሥረት ያለብን ለምንድን ነው? እና እነርሱን መረዳታችን በተለይ ለተልዕኮ አስፈላጊ የሆነው ለምንድነው?

ጥቅምት 27
Nov 07

መጠበቅ እና ተልዕኮ


ሉቃስ 24 የሚያበቃው ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲያርግ ነው (ሉቃስ 24፡50-53)።

የታሪኩ መጨረሻ ግን ይህ አይደለም። ፀሐፊው ሉቃስ የሐዋርያት ሥራን በመጻፍ ቀጥሎታል። ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከማረጉ ጥቂት ቀደም ብሎ፣ ለደቀ መዛሙርቱ ተልእኮ፣ የተስፋ ቃል እና በኢየሩሳሌም “ከላይ የሚመጣውን ኃይል” እንዲጠብቁ አስቸኳይ መመሪያ ሰጣቸው (ሉቃስ 24፡49፤ በተጨማሪም የሐዋርያት ሥራ 1፡4-8ን ይመልከቱ)።

ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን በኢየሩሳሌም፣ በይሁዳ፣ በሰማርያ እና ከዚያም አልፈው ምስክሮቹ እንዲሆኑ የሚያስችላቸውን አብ ለመላክ የገባውን የተስፋ ቃል (መንፈስ ቅዱስን) እስኪልክ ድረስ በኢየሩሳሌም እንዲቆዩ አዘዛቸው።

የሐዋርያት ሥራ 1:12-26ን ያንብቡ። በዚህ ቦታ ቁጥራቸው ወደ 120 የሚጠጉ ወንዶችና ሴቶች ደቀ መዛሙርት እየጠበቁ ሳሉ ምን እያደረጉ ነበር?



ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ግልጽ የሆነ ተልእኮ ሰጥቷቸዋል፡ ለዓለምም ምስክሮች እንዲሆኑ። ስለዚህ፣ እየጠበቁ ሳሉ፣ ለተልዕኳቸው በሁለት መንገድ ተዘጋጁ።

በመጀመሪያ፣ ሉቃስ በአንድነት ጸሎትና ልመና እንደቀጠሉ ይናገራል። ኢየሱስ የሰጣቸው ተልእኮ ምን እንደሆነ በአእምሯቸው ውስጥ ምንም ጥያቄ አልነበረም፣ እና እያንዳንዳቸው ያንን ተልእኮ ተቀብለዋል። ይህም በጸሎት እንዲተባበሩ አነሳስቷቸዋል።

ሉቃስ ሲጸልዩበት የነበረውን ጉዳይ አላካፈለም፣ ነገር ግን ተልእኮውን አንድ ላይ ለመፈጸም ጥበብን፣ ጥንካሬን እና ድፍረትን ለማግኘት ይጸልዩ እንደነበር የታወቀ ነው።

ምንኛ ድንቅ ምሳሌነት ነው!

እየጠበቁ ሳሉ ያደረጉት ሁለተኛው ነገር ለተልዕኳቸው ቁሳቁስ ማዘጋጀት ነበር። ይሁዳ ኢየሱስን እንዲገደል አሳልፎ ከሰጠው በኋላ የራሱን ሕይወት አጠፋ።

ይህ በአስራ ሁለቱ መካከል ክፍት ቦታ ትቶ ነበር። ስለዚህ እየጠበቁ፣ ደቀ መዛሙርቱ የእግዚአብሔርን ምሪት ፈለጉና ምትክ መረጡ። በዚህም ደቀ መዛሙርቱ ራሳቸውን እያደራጁ እና የተልእኮአቸውን አጀማመር እያቀዱ ነበር። እነዚህን ውሳኔዎች ሲያደርጉ, ጴጥሮስ የመሪነት ሚና ተጫውቷል። እርምጃውን ማንም አልተገዳደረም፤ ሁሉም የእግዚአብሔርን ጥበብ በውስጡ አዩ። እግዚአብሔር በመካከላቸው እየሰራ እና እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ ማስተዋል እና መተማመን ነበር። የጥበቃ ጊዜያቸው ስራ የመፍታት ሳይሆን በዓላማ እና በተልዕኮ የተደገፈ ተግባር ነበር።

የእግዚአብሔርን ታላቅ ተልእኮ ለመፈጸም እንዲረዳን የመንፈስ ቅዱስን መፍሰስ ስንጠብቅ፣ እርስ በርሳችን ለመበረታታት አንድ በመሆን (ዕብ. 10፡24-25)፣ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስን እንዲልክ መጸለይ አለብን። እንዲሁም ራሳችንን እና ቤተ ክርስቲያናችንን እግዚአብሔር ቅድሚያ ከሚሰጠው ማለትም የጠፉትን ከማዳን ሥራ ጋር ልናስተካክል ይገባናል። እምነታችንን ሳንጥል ጌታን መጠበቅን መማር የምንችለው እንዴት ነው? እየጠበቅን እያለን ደቀመዛሙርት በዚህ ቦታ እንዳደረጉት ጊዜያችንን በተሻለ መልኩ መጠቀም የምንችለው እንዴት ነው?

ጥቅምት 28
Nov 08

“እናንተ የሰቀላችሁት”


የሐዋርያት ሥራ 2 በበዓለ ሃምሳ የመንፈስ ቅዱስን መፍሰስ ዘግቧል። የኢየሱስ ተከታዮች እየጸለዩ ሳለ፣ በራሳቸው ላይ የእሳት ልሳኖች ታዩ። ቃል የተገባው የመንፈስ ቅዱስ ኃይል መሰጠቱን አውቁ።

የሐዋርያት ሥራ 2፡1-41ን ያንብቡ። በበዓለ ሃምሳ መንፈስ ቅዱስን በመቀበላቸው ምክንያት ደቀ መዛሙርቱ ምን ደረሰባቸው?



ደቀ መዛሙርቱ “መንፈስ ይናገሩ ዘንድ እንደ ሰጣቸው” በሌሎች ቋንቋዎች መናገር ጀመሩ (ሐዋ. ሥራ 2፡4)። እዚህ ጋ ወሳኙ ነገር እግዚአብሔር እያንዳንዱን ሰው የማያምኑትን እንዲጠቅም ማስታጠቁ ነው። በረከቱ ለራሳቸው ጥቅም ብቻ የታሰበ አልነበረም። ለመንግስተ ሰማያት ብቁ እንዲሆኑ ወይም በባዕድ ቋንቋ ንግድን በቀላሉ እንዲሰሩ ለማድረግ የተሰጠ በረከት አልነበረም። በረከቱ የተሰጠው የጠፉትን በመድረስ የእግዚአብሔርን ተልእኮ ለመፈጸም ነበር። ዛሬ እግዚአብሔር እያንዳንዱ አማኝ በግሉ የተሰጠውን ስጦታ የማያምኑትን የመድረስ ተልእኮ ላይ እንዲያውሉት ጥሪ ያቀርባል።

ስጦታዎች ተሰጥተውናል፤ የተሰጠንን ለሌሎች ለመድረስ ከመጠቀም የበለጠ ምን የተልእኮ ጥሪ አለ?

የመንፈስ ቅዱስ መፍሰስ ብዙዎቹ መሲሁን ባለመቀበላቸው ንስሐ እንዲገቡ አድርጓል፣ ምክንያቱም አንዳንዶቹ እርሱ ሲሞት በኢየሩሳሌም ነበሩ። እዚህ ጋ ያለውን ኃይል ያስቡ፡ ጴጥሮስ አንዳንዶቹን ክርስቶስን እንደሰቀሉት ከሰሳቸው። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው እነሱ ያደረጉትን ተረድተው “ወንድሞች ሆይ፣ ምን እናድርግ?” ብለው ተማፀኑ(የሐዋርያት ሥራ 2:37)።

ግን እነሱ እንኳን ይቅርታ ሊያገኙ ይችላሉ። ጴጥሮስ እንዲህ ብሏቸዋል:- “ንስሐ ግቡ፥ ኃጢአታችሁም ይሰረይ ዘንድ እያንዳንዳችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተጠመቁ፤ የመንፈስ ቅዱስንም ስጦታ ትቀበላላችሁ።” (የሐዋርያት ሥራ 2፡38)።

እነዚህ የኢየሱስ ተከታዮች ከመንፈስ ቅዱስ ጋር እና እርስ በርሳቸው በመስማማት ሰብከዋል—ኢየሱስን በመስቀል ተግባር ላይ በቀጥታ ተሳታፊ ለሆኑትም ጭምር ንስሐ መግባትንና የኃጢአትን ስርየት ሰበኩ። ይህ የወንጌል ኃይል ነው። ያ መልእክት ለተልእኮ ካላነሳሳን፣ ምን ሊያነሳሳን ይችላል? የተጠራነው ከኃጢአተኛ፣ ከወደቁ እና ከተበላሹ ሰዎች ጋር ለኃጢአተኛ፣ የወደቀ፣ የተበላሸ ዓለም ወንጌልን ለማዳረስ ነው። የእኛ ሥራ መፍረድ አይደለም፤ የእኛ ሥራ የኢየሱስን የማዳን ኃይል መመስከር ነው። በክርስቶስ ሞት ተባባሪ ከሆኑት መካከል አንዳንዶቹ መዳን ሊያገኙ መቻላቸው (1) እኛ ራሳችን እንድንበረታታ እና (2) ምንም ያህል መጥፎ ቢመስሉም ለሌሎች እንድንመሰክር የሚያበረታታን ለምንድን ነው?

ጥቅምት 29
Nov 09

የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ምስል


የሐዋርያት ሥራ 2፡41-47ን ያንብቡ። በዚህ ቦታ ምን አይነት የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ምስል አለ?



የሐዋርያት ሥራ 2 የሚያበቃው የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ምን እንደምትመስል የሚያምር ምስልን በማስቀመጥ ነው። የሐዋርያት ሥራ 2፡41 የተጠመቁትም “ተጨመሩላቸው” ይላል። ይህንንም በሒሳብ የአዳዲስ አማኞችን ቁጥር በነባር አማኞች ቁጥር ላይ በመጨመር አዲስ አባላት ያሉት ትልቅ ቡድን ተቋቋመ ብለን ልናነበው እንችላለን። ግን ያ ያልጠለቀና ግርድፍ ግንዛቤ ነው። በቃሉ ውስጥ የተደበቀው ነገር እነዚህ አዲስ የተጠመቁ አማኞች ከነባሮቹ ጋር እኩል ሆነው የቡድኑ አካል ሆነዋል የሚለው ኃሳብ ነው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የጥንቷ ቤተክርስቲያን ዋና ተግባር ደቀመዝሙርነት ነበር። አዳዲስ አባላት ሲጨመሩ በሦስት መንገዶች ደቀ መዝሙር ይሆኑ ነበር። በመጀመሪያ፣ በሐዋርያት ትምህርት እና ኅብረት መማራቸውን ይቀጥሉ ነበር። በዚህ ጽሑፍ ውስጥ “ትምህርት” እና “ኅብረት” የሚሉት ቃላት በቀጥታ ሲተረጎሙ “መመሪያ” እና “ሽርክና” የሚል ትርጉም አላቸው። የሐዋርያት ስብከት የተሳሳቱ እምነቶችን የተጋፈጠ ሲሆን ሰዎች እያዩና እያጋጠሟቸው ስለነበሩት ነገር አዲስ ማብራሪያ የሰጠ ነበር። ነገር ግን ያንን አዲስ እውነት በሕይወታቸው ውስጥ እንዴት መኖር እንደሚችሉ አላስተማራቸውም።

ይልቁንም እውነትን በህይወት ላይ መተግበሩ የህብረቱ አካል በመሆን ውስጥ ተከስቷል። አዲስ አማኞች በመንፈሳዊ ህይወት በበሰሉና በጠነከሩ ሐዋርያት አመራር ስር በመማር እንዲሁም በሌሎች አማኞች የእለት ተእለት ህይወት በመሳተፍ በጥንቃቄ እና በትኩረት ይሰለጥኑ ነበር።

ሰዎች ምን ማድረግ እንዳለባቸው የሚያስተምር ነገር ግን እንዴት እንደሚያደርጉት የማይገልፅ ስብከት ደካማ ነው። ነገር ግን፣ አንድ ሰው የድርጊት ይዘት ያላቸው መፃህፍትን ቢያነብ ወይም ነገሮችን እንዴት ማድረግ እንዳለበት የሚገልጹ ስብከቶችን ቢያዳምጥም፣ ሌሎች ሲያደርጉ አይቶ እነርሱን ማስመሰል መሞከርን የመሰለ ትምህርት የለም። ጳውሎስ ይህንን አውቆ ተከታዮቹ እርሱ ኢየሱስን እንደመሰለ እነርሱም እርሱን እንዲመስሉ አዘዛቸው (1 ቆሮ. 11፡1)። ሌሎች እርስዎን ማየት ሲችሉ እና ከክርስቶስ ጋር ያለዎትን ልምምድ በህይወትዎ ሲመለከቱ፣ በነሱም ላይ ተጽእኖ ያደርጋል።

ግድድሮሽ፡- ከሚያውቋቸው ሰዎች ውስጥ አማኝ እንዲሆን የምትመኙትን አንድ ሰው ያስቡ። ያ ሰው ከኢየሱስ ጋር የግል ልምድ እንዲኖረው በየቀኑ ይጸልዩለት።

በተጨማሪም እርስዎ እያስተማሩ እና ከኢየሱስ ጋር ግንኙነት እንዲፈጥር እየመሩ ያሉት ማንን ነው? እሱን ወይም እሷን ከሌሎች አማኞች ጋር ወደ ህብረት ለማምጣት መንገዶችን ይፈልጉ።

ጥቅምት 30
Nov 10


ተጨማሪ ሀሳብ


የተልእኮ ስራችን ኢየሱስ በህይወታችን ላደረገው እና እያደረገ ላለው ነገር ካለን ጥልቅ ፍቅር እና ምስጋና የተነሳ መሆን አለበት። ሌላ ማንኛውም ተነሳሽነት የተሳሳተ ነው። በቃሉ ውስጥ መጠመቅ እና ከቃሉ ጋር መስማማት ለስኬታማ አገልግሎት እና ለወንጌል ስርጭት ቁልፍ ነው።

“ሕይወታችን ከክርስቶስ ሕይወት ጋር መተሳሰር አለበት፤ ከሰማይ ከወረደው ሕያው መና ሁሌም አዲስና ማመንጨቱን ከማያቋርጠው ምንጭ ዘወትር ልንካፈል ከእርሱም ልንቀበል ይገባናል። ልባችን በምስጋና እና ውዳሴ እንዲሞላ በመፍቀድ ጌታን በፊታችን ካየነው በሃይማኖታችን ውስጥ ቀጣይነት ያለው ትኩስነት ይኖረናል። ከጓደኛ ጋር እንደምንነጋገር ጸሎታችን ከእግዚአብሔር ጋር የመነጋገርን መልክ ይይዛል። እርሱ ምሥጢሩን ይነግረናል። ብዙውን ጊዜ የኢየሱስን መገኘት የሚገልጽ አስደሳች ስሜት ወደ እኛ ይመጣል። ከሄኖክ ጋር እንዳደረገው ከእኛ ጋር ለመነጋገር ሲቃረብ ብዙ ጊዜ ልባችን በውስጣችን ይቃጠላል። ይህ በእውነት የክርስቲያን ልምምድ ሲሆን በህይወቱ ውስጥ ከኢየሱስ ጋር እንደነበረ እና ከእርሱም እንደተማረ ለሰዎች ሁሉ የሚያሳየው ቀለል ያለ አኗኗር፣ ትህትና፣ የዋህነት እና የልብ ትህትና ይታያል።” ኤለን ጂ. ኋይት፣ የክርስቶስ ተምሳሌታዊ ትምህርቶች፣ ገጽ 129፣ 130

“ራስን ባማከለ ህይወት ውስጥ እድገትም ሆነ ፍሬያማነት ሊኖር አይችልም።

ክርስቶስን እንደግል አዳኝ አድርጋችሁ ከተቀበላችሁ እራሳችሁን ትታችሁ ሌሎችን ለመርዳት ሞክሩ። ስለ ክርስቶስ ፍቅር ተናገሩ፣ [ለሌሎችም ስለ እነርሱ ሲል የራሱን ጥቅም ትቶ መሞቱን ተናገሩ]። . . .ለሌሎች የሚሰራውንና ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር ያለውን የክርስቶስን መንፈስ ስትቀበሉ ታድጋላችሁ፣ ፍሬም ታፈራላችሁ። . . . እምነታችሁ ይጨምራል፤ ግለታችሁም እየጠነከረ ይሄዳል፤ ፍቅራችሁም ፍጹም ይሆናል።” ኤለን ጂ. ኋይት፣ የክርስቶስ ተምሳሌታዊ ትምህርቶች፣ ገጽ 67-68


የመወያያ ጥያቄዎች




1. ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ሰዎች በላከው መልዕክት ላይ በምቀኝነት፣ በጠብ ወይም በራስ ወዳድነት ፍላጎት ክርስቶስ ስለመሰበኩ የተናገረውን እንዴት ተረዳችሁት? እኛ ራሳችን ይህን በማድረግ ጥፋተኛ እንዳልሆንን እንዴት ማረጋገጥ እንችላለን?

2. በእግዚአብሔር እና በፍቅሩ እርግጠኝነት ላይ የርስዎ የግል ተሞክሮ ምን ነበር? ማለትም ከራስዎ ተሞክሮ በመነሳት ስለ አምላክ መልካምነትና ፍቅር በቅንነትና በሐቀኝነት ለሌሎች መስበክ ይችላሉ? ምስክርነትዎ ምን ይሆን?

3. ጌታን ከመጠበቅ አንፃር ያጋጠመዎት ሁኔታ ካለ ምንድን ነው? እናም ያ ሁኔታ ስለመታመን እና በአጠቃላይ ስለ እምነት ምን አስተማረዎት?




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA Union SSL