የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

የእግዚአብሔር ተልዕኮ የእኔ ተልዕኮ



4ኛ ሩብ ዓመት 2023


ጥቅምት 17 - 23

5ኛ ትምህርት

Oct 28 - Nov 3




ተልእኮውን ለመግፋት የሚቀርቡ ሰበቦች



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሳምንት ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡- ዮናስ 1-4፤ ነህ. 11፡1፣ 2ነገ. 17፡5-6፤ መዝ. 24፡1፤ ያዕ. 1፤27፤ ኢሳ. 6፡1-8


የመታሰቢያ ጥቅስ፤ “ከዚያም የጌታ ድምጽ ‘ማንን እልካለሁ? ማንስ ይሄድል ናል?’ ሲል ሰማሁት። እኔም ‘እነሆኝ እኔን ላከኝ’ አልሁ።” (ኢሳ. 6፡8)

ለተልዕኮ የተጠራ ሁሉ እንደ አብርሃም አጉረምራሚ አልነበረም። ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ዮናስ ነው (ዮናስ 1-4ን ያንብቡ)። እግዚአብሔር የአሦር ዋና ከተማ ወደሆነችው ነነዌ ሄዶ የጩኸት ድምፅ እንዲያሰማ ዮናስን ጠራው። ይህች ከተማ የምትገኘው በአሁኑ ዘመናዊ አለም ኢራቅ ውስጥ ሲሆን ከኢየሩሳሌም 560 ማይል ርቀት ላይ ነው፤ ይህ የአንድ ወር ያክል የጉዞ ርቀት አለው። ዮናስ ለመሄድ እምቢ ከማለቱም ባሻገር በተቃራኒ አቅጣጫ ኮበለለ። ኢዮጴ ሲደርስ አሁን በደቡባዊ እስፔን ወደምትገኘው ወደ ተርሴስ የሚያስኬደውን የትራንስፖርት ግዢ አከናወነ። እንደ አየሩ ሁኔታ 2000 ማይልስ በመርከብ መጓዝ የወር ያክል ጉዞ ያስኬድ ነበር። የአሦር ንጉስን ፊት ለፊት ላለመጋፈጥ የወር ያክል የጉዞ ርቀት የሚወስድበትን የነነዌን ጉዞ በተቃራኒ አቅጣጫ ለመጓዝ መረጠ። ይህ የእግዚአብሔር ሰው ለምን ይህንን ያደርጋል?

የነነዌ ህዝብ በሙሉ በአመጻቸው፣ በክፋት ተግባራቸውና በእሥራኤልና ይሁዳ ላይ ጥቃት በመሰንዘር በጭካኔያቸው የታወቁ ነበሩ። ከዚህ የተነሣ ዮናስ ሄዶ ኃጢአተኝነታቸውን በጩኸት እንዲነግራቸው እግዚአብሔር ጠራው (ዮናስ 1፡2)። በዚህ ስፍራ ጥቅም ላይ የዋሉት ቃላት ልክ በአብርሃም ጊዜ እግዚአብሔር ለሰዶምና ገሞራ ከተጠቀማቸው ቃላት ጋር ተመሳሳይ ናቸው (ዘፍ 18፡20-21)።

ዮናስ ተልእኮውን ላለመፈጸም ካቀረበው ሰበብና አመለካከቱ ምን መማር እንችላለን? የዚህን ሳምንት ትምህርት አጥንተው ለጥቅምት 24 ሰንበት ይዘጋጁ።

ጥቅምት 18
Oct 29

የእኛ ሰበብ፡- ፍርሃት


ናሆም 1፡1፤ ናሆም 1፡1-4 እና 2ኛ ነገ. 17፡5-6፤ 2ኛ ነገ. 19፡32-37ን ያንብቡ። እነዚህ ጥቅሶች ስለ ነነዌ እና የአሦር ሕዝብ ከእስራኤል ጋር ስለነበራቸው ግንኙነት ምን የገለጡልን ነገር አለ? ይህ ግንኙነት ዮናስ ወደ ተርሴስ ለመኮብለል እንዲወስን ተፅዕኖ የፈጠረበት በምን መልኩ ነው?



ዮናስ ወደ ነነዌ መሄድን እንቢ እንዲል ካደረጉት ምክንያቶች አንዱ ፍርሃት ነው።

አሶራውያን የታወቁ ጠላቶቻቸው ሲሆኑ ነነዌ የመንግስቱ ዋና ከተማ ሆና ታገለግል ነበር።

“በተከፋፈለች ጥንታዊት እስራኤል ዘመን የአሶራውያን ግዛት ርዕሰ ከተማ የነበረችው የነነዌ ከተማ ከወቅቱ ታላላቅ ከተማዎች መካከል አንዷ ነበረች።… በጊዜያዊ የብልጽግናዋ ዘመን ነነዌ የወንጀል እና የክፋት ማዕከል ነበረች። የትንቢት መንፈስ የከተማዋን ባህሪ የገለጸው ‘በደም የተሞላችው ከተማ… ሀሰትና ዝርፊያ የተንሰራፋባት’ በሚል ነው። ነብዩ ናሆም የነነዌን ኗሪዎች ምስላዊ በሆነ አገላለፅ የሚያነጻጽረው ከጨካኝ እና በጣም ከተራበ አንበሳ ጋር ነው። ‘ክፋትህ ሁልጊዜ ያላለፈችበት ሰው ማን ነው’ በማለት ጥያቄውን ያነሳል (ናሆም 3፡19)።” Ellen G. White, Prophets and kings, p. 265

ነነዌ የምታስደንቅ ከተማ ናት። የታሪክ ጸሐፍት እንደሚናገሩት ሰናክሬም 1650 ጫማ በ794 ጫማ (503 በ242 ሜትር) የሆነውንና ቢያንስ ወደ 80 ክፍሎች የነበሩትን የሰሜን ምዕራብ ቤተመንግስትን መገንባትን ጨምሮ ከተማዋን በከፍተኛ ደረጃ አስፋፍቷል። ከዚህ በተጨማሪ ከ49 ማይልስ (65 ኪሎ ሜትር) ርቀት ላይ ውሃ ወደ ከተማዋ እንዲመጣ 18 ቦዮችን አስገነባ። መጠኑ ብቻ የሚያስፈራ ነበር።

ነገር ግን አሶርያውያንም ቢሆኑ ጨካኞች ነበሩ። ሰናክሬም ባቢሎንን ስለመውረሩ በሚናገረው ዘገባው ልጆችንና አዛውንትን ሳይለይ ጎዳናዎችን በነዋሪዎቹ ሬሳ መሙላቱን በኩራት ተናግሯል። በቁፋሮ ወቅት የተገኙት አጋዥ ምስሎች ወታደሮች ተጎጂዎችን ሲሰቅሉ ያሳያሉ። እነዚህ ሰዎች አልፈሃቸው ልትሄድ የፈለግካቸው ሰዎች አልነበሩም። እነርሱ በማይወዷቸው ሰዎች ላይ ጥቃት ከመሰንዘር እና ያለ ምክንያት በጭካኔ ከመግደል የማይመለሱ ሰዎች ነበሩ። በእርግጥም ዮናስ ብዛት ባላቸው የነነዌ ሰዎች መካከል ለመራመድ ሲያስብ በፍርሃት ሳይንቀጠቀጥ አልቀረም።

ይህ ሁሉ ቢሆንም እግዚአብሔር ያዘዛቸውን መመሪያዎች እንዳይፈጽም ፍርሃት እንቅፋት እንዲሆንበት በመፍቀዱ የዮናስን ታሪክ በነቀፌታ እናነባለን። እዚህ ላይ መረዳት ያልቻልነው ነገር ቢኖር እኛም ተመሳሳይ ነገር እንደምናደርግ ነው። ራሳችንን እግዚአብሔር እንዲቆጣጠር ከመፍቀድ ይልቅ ፍርሃት እንዲቆጣጠረን እንፈቅዳለን።

እግዚአብሔር አንድን ነገር እንድታከናውኑ ሲመራችሁ ከፍርሃት የተነሳ እንቢ ስላላችሁባቸው ሁኔታዎች ለጥቂት ደቂቃዎች እስቲ አስቡ።

ከዚህ የህይወት ተሞክሮ ምን ትምህርት አገኛችሁ?

ጥቅምት 19
Oct 30

የእኛ ሰበብ፡- የውሸት እይታዎች


ማዕበሉ በመጣ ጊዜ ዮናስ ችግሩ የመጣው በእርሱ ምክንያት እንደሆነ በመቀበል ራሱን ወቀሰ (ዮናስ 1፡1-12)። ይህ እርሱ ስለ አምላክ ወይም ስለ “አማልክት” የነበረው አመለካከት በዚያን ዘመን የነበረው ዓለም የነበረው ዓይነት አመለካከት እና ግንዛቤ እንደሆነ ያሳያል። የተለያዩ አማልክቶች በተለያዩ አገሮች እንደሚገዙ ያምኑ የነበረ ሲሆን ባህር አጋንንት የሚገዙበት የተረበሸ ዓለም ነው ተብሎ ይታመን ነበር። ባህር ላይ በሚቀዝፉ ሰዎች አመለካካት የእነዚህን መናፍስት ቁጣ ለማብረድ መስዋዕት ያስፈልግ ነበር።

ዮናስ ዕብራዊ ቢሆንም በዘመኑ በነበረው አመለካከት ተጽእኖ ሳያድርበት አይቀርም። አጋሮቻቸው ሲገዙ፣ የተመሰቃቀለው ባህር የአጋንንት ግዛት ስለመሆኑ ይታመን ነበር።

ዮናስ 2፡1-3 እና 7-10ን ያንብቡ። እነዚህ ጥቅሶች ዮናስ የእግዚአብሔርን ጥበቃ በምን መልኩ መረዳት እንደጀመረ ምን ይነግሩናል?



ዮናስ ህዝቡ ያህዌን አምላኬ ነው ብለው ከሚጠሩበት ክልል እየሸሸ ቢሆንም ወደ ባዕድ ባህሎች በሄደበት ጊዜም እንኳን ያህዌ አሁንም ሉአላዊ አምላክ እንደሆነ አስቸጋሪ በሆነ መንገድ ተማረ። ነፋሱና ማዕበሉ የእግዚአብሔር ናቸው። አሣውም የእርሱ ነው።

“ምድርና ሞላዋ የእግዚአብሔር ናቸው” (መዝ 24፡1)። የዮናስ ልብ በምድርና በባህር ሉአላዊ ወደሆነው አምላክ ተመለሰ። እርሱም ኃጢአቱን በመናዘዙ ዳነ።

እኛም ስለ አምላክና እርሱ ከእኛ ስለሚጠብቀው ነገር የተሳሳተ መረዳት ሊኖረን ይችላል። ከተለመዱ የተሳሳቱ መረዳቶች መካከል አንዱ እግዚአብሔር ለእኛ ያለው ፍላጎት በራሳችን ድነት ላይ እንድናተኩርና በዙሪያችን ካለው ከዓለም ክፋት ራሳችንን መለየት አለብን የሚለው መረዳት ነው። ምንም እንኳን “ከዓለም እርኩሰት ራሳችንን እንድንጠብቅ” መመሪያ ቢሰጠንም (ያዕቆብ 1፡27) ትኩረታችን መሆን ያለበት በችግር ውስጥ ላሉት የእግዚአብሔርን በረከቶችና ተስፋ ማምጣት ላይ ነው።

የእግዚአብሔርን የተልዕኮ ጥሪ እንዳንቀበል የሚያግደን ሌላው የተሳሳተ ግንዛቤ ስኬታችን በራሳችን ላይ የተመሰረተ መሆኑን ማመን ነው። ዮናስ ነነዌን ማዳን ከሚችለው መንገድ የበለጠ ነፍስን ማዳን አንችልም። ስለ ተልእኮው “የአዳኝ” አስተሳሰብ ሊኖረን ይችላል። እኛ የተጠራነው እንድናድን ሳይሆን በማዳን ሥራው ከእግዚአብሔር ጋር እንድንተባበር ነው። እግዚአብሔ እኛን እየለወጠ ስላለባቸው የተለዩ መንገዶች እያመሰገንነው ምስክርነት እንሰጣለን፣ ነገር ግን ሰዎችን ወደ ራሱ የሚስበው እግዚአብሔር ብቻ ነው። የእውነትን ዘር መዝራት እንችላለን፣ ነገር ግን ልብን መለወጥ የሚችል እግዚአብሔር ብቻ ነው። ብዙ ጊዜ የእኛን ሚና ከእግዚአብሔር ሚና ጋር እንናደበላልቀዋለን፤ ይህም ማንም ሰው እንዳይመሰክር ሰበብ እንዲያገኝ ለማድረግ በቂ ነው። አዎን፣ እግዚአብሔር ዮናስን ተጠቅሞበታል፣ ነገር ግን ነነዌን የቀየረው (የመለሰው) ዮናስ ሳይሆን እግዚአብሔር ብቻ ነው።

ለነፍሳት መመስከር በጣም ከባድ ነው። ይህንን ሰዎች በራሳቸው ሊያደርጉ ቢጥሩም አዳጋች ይሆንባቸዋል። በእኛ፣ በህይወታችንና በምስክርነታችን አማካይነት እግዚአብሔር ነፍሳትን እንዲማርክ መፍቀድን እንዴት መማር እንችላለን?

ጥቅምት 20
Oct 31

የኛ ሰበቦች፡ አለመመቸት


ዮናስ በአሳ ነባሪ ሆድ ውስጥ ያለፈበት ልምምድ (ዮናስ 2ን ተመልከቱ) አስደናቂ የሆነ የእግዚአብሔር ፍቅርና ምህረት ማሳያ ነው። የዮናስ ጸሎትም የእግዚአብሔርን የፍቅር መልእክት ሰይረዳው እዳልቀረ ያሳያል። ነገር ግን ምንም እንኳን ዮናስ ወደ ነነዌ ቢሄድም ከእግዚአብሔር ጋር አስደናቂ ግንኙነት ስለፈጠረ አሮጌ የአስተሳሰብ ልማዶች ወይም አመለካከቶች በቀላሉ ይለወጣሉ ማለት አይደለም።

ዮናስ 3ን ያንብቡ። ዮናስ በሚሰብክበት ጊዜ ህዝቡ በምን አይነት መንገድ ምላሽ ሰጡ? በዚህ ስፍራ ስለ ምስክርነት የምንማረው ምን ነገር አለ?



ዮናስ ስለ ነነዌ ሰዎች የነበረው አመለካከት ምንም ቢሆን እግዚአብሔር የነገረውን ነገር ሰብኳል፣ ውጤቱም የሚያስደምም ነበር። የነነዌ ሰዎች ልባቸው ተነክቶ ንስሃ ገቡ! አዎን፣ ዮናስ ማድረግ ያልፈለገውን ነገር ለማድረግ በብዙ ነገሮች ውስጥ ማለፍ ነበረበት፣ ነገር ግን ይህን በማድረጉ እግዚአብሔር ከበረ።

ስለዚህ፣ ዳተኛ ቢሆኑም እንኳን፣ መስዋዕትነትን ለመክፈል ፈቃደኛ በሆኑ ሰዎች ትከሻ የእግዚአብሔር ተልእኮ ወደ ፊት ይቀጥላል። የእኛ እሴቶች እግዚአብሔር ለጠፉት ለሚሰጠው ቅድሚያ ስፍራውን መልቀቅ አለባቸው። አንዳንድ ጊዜ ልክ እንደ ዮናስ ሁሉ እኛም ወደ ሌላ ሰው ወይም ቡድን እንዳንደርስ የሚያደርግ የጥላቻ ሃሳብን እናስተናግዳለን።

ጥላቻችንን መጋፈጥ ራስን ማዋረድን ይጠይቃል። ተልእኮውም ጊዜን እና የስሜት ሀይልን ይሻል። በሌሎች ላይ ያለንን ነገር ማፍሰስና በእውነት ለእነርሱ መጠንቀቅ ልፋት የሚጠይቅ ነገር ነው። የግል ኑሮአችንና የችግሮቻችን ጭንቀት ጫና እየፈጠረብን ባለው በዚህ ዘመን ለሌሎች የስሜት ድጋፍ ማድረግ እጅግ አድካሚ ሊሆን ይችላል።

በስተመጨረሻም በተልእኮው ውስጥ መሳተፍ ስለ ገንዘባችን ያለንን ስሜትና አጠቃቀም መለወጥን ይሻል። ለሌሎች ከመጠንቀቅ ወይም ሥነጽሁፍን ከመግዛት ወይም ለሚሲዮን ሥራ ጊዜን ነጻ ለማድረግ ለሚያስፈልግ አገልግሎት ወይም ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ገንዘብን ከመክፈል ጋር የተገናኘ ቢሆን ከተልዕኮ ጋር የተገናኙ ወጪዎች አሉ። የወጪው ዓይነት ምንም ዓይነት መልክ ቢኖረውም የተልዕኮ ሥራ መስዋዕትነትን ይጠይቃል።

መልካሙ ዜና ዮናስ ብቃት ባይኖረውም እግዚአብሔር የነነዌ ህዝቦች ወደ ንስሃ እንዲመጡ በሃይል ሰራ። የሚያሳዝነው ግን ይህንን የሰማያዊ ደስታን በረከት ዮናስ አልተቋደሰም። የእርሱን ፍቅር ለሌሎች ለማካፈል ምን መስዋዕት እንዲያደርጉ ወይም ለማድረግ እንዲዘጋጁ እግዚአብሔር እየጠየቀዎት ነው? በከፈሉት መስዋዕትነት አማካይነት ሕይዎትዎን ለማበልጸግ የገባልዎን ቃል እንደሚፈጽም ምን ያህል ከሙሉ ልብዎ ይተማመኑበታል?

ጥቅምት 21
Nov 01

የእኛ ስብከት፡- የምንጋፈጣቸው ያልተመቹ ሁኔታዎች


“ወደ እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ፀለየ፡- እግዚአብሔር ሆይ፤ በአገሬ ሳለሁ የተናገርሁት ይህን አልነበረምን? ፈጥኜ ወደ ተርሴስ ለመመኮብለል የተነሳሁትም ለዚሁ ነበር። አንተ ቸርና ሩህሩህ፤ ምህረትህ የበዛ፣ ከቁጣ የራቅህ አምላክ፤ ጥፋትንም ከማምጣት የምትመለስ እንደሆንህ አውቃለሁ” (ዮናስ 4፡2)። ዮናስ የጸለየው ምን ዓይነት ውብ ፀሎት ነው! አይደል? ዮናስ 4ን ያንብቡ። ይህ ሰው የነበረበት ችግር ምን ነበር?



ዮናስ በነነዌ ላይ የሰበከው የጥፋት ቀን ተፈጻሚ ሳይሆን ቀርቶ ከሚመለከት ይልቅ ሞትን እስኪመርጥ ድረስ እግዚአብሔር እንድናገር ለላከው ሕዝብ ጥልቅ ጥላቻ ነበረው። ዮናስ ነነዌ ቀጣይዋ ሰዶምና ገሞራ እንድትሆን ፈልጎ ነበር። በእነዚህ የተጣሉ ህዝቦች ላይ የእግዚአብሔር ፍርድ እንዲመጣባቸው ተስፋ አድርጎ ነበር። ይህ ሳይሆን በቀረ ጊዜ እርሱ ለዓለም የነበረው አመለካከት እየተናወጠበት ነበር። የእርሱ አለም እንድትገለባበጥ ከመፍቀድ ይልቅ ሞቱን ይመርጣል።

በዮናስ ታሪክ ውስጥ እግዚአብሔር ዮናስን ለሁለተኛ ጊዜ የገጠመው በስብከት ወይንም በንግግር ሳይሆን በህይወት ተሞክሮ አማካኝነት ነበር። የዓለም እይታዎች ተፈልገው የተፈጠሩ አይደሉም። አዲስ ወይም የተለየ ነገር ስለሰማንም የሚለወጡ አይደሉም። ስለ ዓለም ያሉን እይታዎች የሚፈጠሩትን ወይም የሚለወጡት በሕይወት ተሞክሮአችን ላይ ተመስርተው ነው።

እግዚአብሔር ለዮናስ የሰጠው አዲስ ልምምድ የራሱን የተዛባ የአለም አተያይ እንዲያውቀው ለመርዳት ነው። እግዚአብሔር ዮናስን ከጠራራ ፀሀይ ለመጠበቅ የሚያስችል በቂ ጥላ ያለው ተክል በአንድ ቀን ውስጥ ተአምራዊ በሆነ መንገድ አበቀለ።

ዮናስም ያመሰገነው ተአምሩን ያደረገውን አምላክ ሳይሆን ተክሉን ነበር። ይህንን እንደ ያልተገባ ተአምር ከመመልከት ይልቅ መልካም ስራውን ተከትሎ የመጣ ተገቢ እና የተገባው በረከት አድርጎ ቆጥሮታል። ተክሉ ሲደርቅ በሚያሳዝን መንገድ ዮናስ እየተናደደ ሄደ፤ በራሱ ላይ የነበረው መልካም ግምት ወረደ እናም ራሱን ለማጥፋት አሰበ።

ዮናስ በነነዌ ከነበሩት በሺሆች ከሚቆጠሩ ወንዶች፣ ሴቶችና ህጻናት እንዲሁም ከእንስሳት አብልጦ ለአንድ ተክል ዋጋ መስጠቱን ምን ያክል ሞኝነት እንደሆነ እንዲገነዘብ የሚያደርግ የተረጋጋ የእግዚአብሔር ድምጽ ተከትሎታል።

ታሪኩ በዮናስ ንስሃ የመግባት የመፍትሄ መንገድ ሲደመደም አናይም።

ይልቁንም ይህ ያላለቀ ታሪክ ለኛ ታሪክ ሆኖ ተቀምጦልናል። እግዚአብሔር ለክፉዎች፣ ለጉልበተኞችና በአለም ዙሪያ ላልደረስናቸው ሰዎች ስላለው ጭንቀት እኛ ምን እናደርጋለን?

ጥቅምት 22
Nov 02

እነሆኝ፣ እኔን ላከኝ


የዮናስ ታሪክ በጣም አስደናቂ ነው። የዮናስ ያልተገባ ምስክርነት የሳተ ቢሆንም አምላክ ነነዌን ማዳን መቻሉ የእኛ ሚና ልብን ሊወቅስና ሊመልስ ለሚችለው ለእግዚአብሔር መተላለፊያ መሆን ብቻ መሆኑን ያሳስበናል። እግዚአብሔር የሚፈልገው የእርሱን መመሪያ የሚከተሉ ፍቃደኛ እና ትሁት መልእክተኞች ብቻ እንድንሆን ነው።

ኢሳ 6፡1-8ን ያንብቡ። በዚህ ክፍል ውስጥ የተገለፀው ማዕከላዊ ሀሳብ ምንድር ነው?



ጥሪው አለ። እግዚአብሔር ፈቃደኛ የሆኑ ሰዎችን ይሻል። ለእርሱ አመራር በመገዛት፣ ድምጹንም በመስማት እና ከዚያም የሚነግረንን ማንኛውንም ነገር ለመታዘዝ በመምረጥ ለጥሪው ምላሽ መስጠት አለብን።

የዮናስ ታሪክ እግዚአብሔር ፍቅሩ በማይዳሰስበትና ድምጹ በማይሰማበት ቦታ ለሚኖሩ ሰዎች ያለውን ፍቅር ያሳያል። እግዚአብሔር ለነነዌ ሰዎች እንደራራላቸው ሁሉ ህንጻዎች ዛፎችንና አበባዎችን በተኩባቸውና የማያቋርጥ ጫጫታ ጸጥ ብሎ ማድመጥ እንዳይቻል በሚያደርግባቸው በዛሬዎቹ ከተማዎች ውስጥ ለሚኖሩ በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ነዋሪዎች ያዝናል። እግዚአብሔር ስለ ነነዌ እንዲህ አለ፡- “ቀኝና ግራቸውን ለማይለዩ” (ዮናስ 4፡1)። እግዚአብሔር የተስፋ መልእክቱን በህይወት የስራ መጨናነቅ እና በሕይወት አስቀያሚነት ለተጨናነቁ ሰዎች ለማድረስ ፈቃደኛ የሆኑ መልእክተኞችን ይፈልጋል።

ኢሳያስ “ማን ይሄድልናል?” የሚለውን ድምጽ ሰማ። የእርስዎ ምላሽ ምን ይሆን ይሆን?

ተግዳሮት፡- በባዶ ወረቀት ላይ ወይንም በፀሎት ደብተር ላይ አማኞች እንዳልሆኑ የሚያውቋቸውን 10 ሰዎች ስም ዝርዝር ይፃፉ። እነዚህን የእርስዎ “ደቀ መዛሙርት” እንላቸዋለን። ቢቻልዎ ስማቸውን ዘርዝረው ይፃፉ። ይህንን ዝርዝር በአጠገብዎ በማቆየት ለቀሪው ሩብ ዓመት ለእነዚህ 10 ደቀ መዝሙሮችዎ ይጸልዩ።

ለእነዚህ ለሚያውቁአቸው ሰዎች ጓደኛ መሆን እንዲችሉ እግዚአብሔር እንዲረደዎ ይጸልዩ። ከእነዚህ ከልተለመዱ ጓደኞቸዎ ጋር ጥልቅ፣ የቀረበና መተማመን ያለበትን ጓደኝነት መፍጠር እንዲችሉ ይጸልዩ። ጓደኝነታችሁ እየጠነከረ ሲሄድ ልዩ የሆኑ ፍላጎቶቻቸውን፣ ጉዳቶቻቸውንና ጭንቀቶቻቸውን ለማወቅ በጥንቃቄ ይመልከቱና ያድምጡ። እግዚአብሔር የሚያስፈልጋቸውን ነገር እንዲያሟላላቸው ይጸልዩላቸው። ተግዳሮት፡- በአቅራቢያዎ ያለ ከተማንና በሌላ የአለም ክፍል ውስጥ ያለ ከተማን ይምረጡ። በእያንዳንዱ ስፍራ ውስጥ ለሚኖሩ ሰዎች መፀለይን ይጀምሩ። እውነትን እንደምናውቀው--ስለ ክርስቶስ በቅርብ መገለጥ የሚገልጸውን እውነት የሚያጋሩ ጠንካራ አድቬንቲስቶች በዚያ ስፍራ እንዲነሱ እግዚአብሔርን ይጠይቁ።

ጥቅምት 23
Nov 03


ተጨማሪ ሀሳብ


ኤለን ጂ ኋይት በዙሪያቸው ላሉ ሰዎች ለመመስከር የኢየሱስን ጥሪ ለመከተል ልባቸው ለሚቸገሩ ሰዎች ጠንካራ ማስጠንቀቂያ አስቀምጣለች።

“ይህንን ሥራ ላለመስራት ሰበብ ለሚደረድሩ ሰዎች ሰበባቸው ከኃላፊነታቸው ነጻ አያደርጋቸውም። ይህንን ሥራ ላለመስራት ከመረጡ ክርስቶስ የሞተላቸውን ነፍሳትና እግዚአብሔር የሰጣቸውን ኃላፊነት ችላ እያሉ ስለሆነ በሰማይ መጽሐፍት ውስጥ ያልታመኑ (ሀኬተኛ) ባሪያዎች ተብለው ይመዘገባሉ። አንድ አገልጋይ የእርሱን እርዳታ ከሚሹ ሰዎች ራሱን ሲያርቅ ለሌሎች ብርታትና በረከት ለመሆን ጌታው እንደሰራ እየሰራ ነው ወይ? ከሰዎች ጋር የግል ግንኙነት ማድረግን ችላ የሚሉ ሰዎች ራስ ወዳድ ይሆናሉ።

ከዚህ የተነሣ የወንድሞቻቸውን መንፈሳዊ ሁኔታ ለመረዳትና ለእያንዳንዱ ሰው ምግቡን በጊዜው በመስጠት የእግዚአብሔርን መንጋ እንዴት መመገብ እንዳለባቸው ለማወቅ ከወንድሞቻቸው ጋር ግንኙነት የመፍጠር ልምምድ ያስፈልጋቸዋል። ይህንን ሥራ ችላ የሚሉ ሰዎች የግብረገብ እድሳት እንደሚያስፈልጋቸው ስለሚገልጡ የሥራውን ሸክም አለመሸከማቸውን ይመለከታሉ።” Ellen G. white, the Advent Review and Sabath Herald, August 30, 1892

እነዚህ ቃላት እግዚአብሔር በተልእኮው ላይ የሚያስቀምጠውን አስፈላጊነት የሚያጎሉ ጠንካራ ቃላት ቢሆኑም ያለ ተስፋ አልተተውንም። “ዮናስ በተሰጠው ሥራ ላይ ከባድ ሀላፊነት ተጥሎበት ነበር። ነገር ግን ሂድ ብሎ ያዘዘው ጌታ ባሪያውን ሊደግፈውና ክንውን ሊሰጠው ይችል ነበር። ነብዩ ያለ ጥርጥር ቢታዘዝ ኖሮ ከብዙ መራር ገጠመኞች መትረፍ በቻለ እና የተትረፈረፈ በረከት በተቀበለ ነበር። ነገር ግን ዮናስ ተስፋ በቆረጠበት ሰዓት ጌታ አልተወውም። በተከታታይ ባጋጠሙት ፈተናዎች እና ባልተለመዱ አስደናቂ በጎነቶች አማካይነት ነቢዩ በእግዚአብሔርና በሚያድነው በእርሱ ወሰን የለሽ ኃይል ላይ የነበረው መታመን መነቃቃት ነበረበት።” Ellen G. white prophets and kings, p. 266

ልክ እንደ ዮናስ በተልእኮው ውስጥ ላለመሳተፍ ሰበብ ለመስጠት ቀላል ሆኖ እናገኛዋለን። ለእነዚህ ሰበቦች መነሳሳታችን ከብዙዎች ምክንያቶች አንዱ ሊሆን ይችላል። ሆኖም የእኛ የተልእኮ ጥሪ ከዮናስ ጥሪ ያነሰና የተለየ አይደለም። ጥያቄው ለዚህ ምላሽ ለመስጠት የሚመርጡት እንዴት ነው?


የመወያያ ጥያቄዎች




1. በተልእኮ ላለመሳተፍ ምን አይነት ሰበቦችን ለመደርደር ተፈትነዋል? የእርስዎ ነነዌ ምንድነው?

2. እኛ እንደ ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስቶች ያለን እውነት ምን ያህል የከበረ እንደሆነ እስቲ ያስቡ። እነዚህ እውነቶች ስላሉዎ ምን ያህል እንደተባረኩ ያስቡ። በጣም የምትወዱትን ነገር ለሌሎች እንዳያጋሩ ወደ ኋላ የሚጎትትዎ ምን ነገር አለ?

3. ስለ መመስከር እና ተልእኮ ሊኖርዎ የሚችሉትን ፍርሃቶች በእግዚአብሔር ጸጋ ማሸነፍን መማር የሚችሉት እንዴት ነው?




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA Union SSL