የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

የእግዚአብሔር ተልዕኮ የእኔ ተልዕኮ



4ኛ ሩብ ዓመት 2023


ጥቅምት 10 - 16

4ኛ ትምህርት

Oct 21 - 27




የእግዚአብሔርን ተልዕኮ ማካፈል



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሳምንት ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡- ዘፍጥረት 18፣ ያዕቆብ 5፡16፣ ሮሜ 8፡34፣ ዕብ. 7፡25፣ ዘፍ. 19፡1-29፣ ዘፍ. 12፡1-9።


መግቢያ ጥቅስ፡- “እርስ በርሳችሁ ትዋደዱ ዘንድ አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ። እኔ እንደ ወደድኋችሁ እናንተ ደግሞ እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ። እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፣ ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ ያውቃሉ።” (ዮሐንስ 13:34-35)

ከመጀመሪያው፣ አብርሃም እግዚአብሔር ለተልእኮው እንዲጠቀምበት ፈልጎ ነበር። ይህ እውነት ለምሳሌ በዘፍጥረት 18 ላይ እግዚአብሔር በሰዶምና በገሞራ ላይ ስለሚሆነው ነገር በማስጠንቀቁ ውስጥ ይታያል። “በእውነት ጌታ እግዚአብሔር ምሥጢሩን ለባሪያዎቹ ለነቢያት ካልነገረ በቀር ምንም አያደርግም” (አሞጽ 3:7)።

በሰዶምና በገሞራም ታሪክ ውስጥ “አገልጋዩ ነቢይ” አብርሃም ነበር።

አብርሃም ከቀኑ ሙቀት አርፎ ሳለ ሦስት መንገደኞችን አየ። “አብርሃም በእንግዶቹ ውስጥ ያየው የደከሙትን ሦስት መንገደኞች ብቻ ነበር፤ ከመካከላቸው እርሱ የሚያመልከው አንድ እንዳለ አላሰበም።”—Ellen G. White፣ Patriarchs and Prophets፣ ገጽ 138, 139

አብርሃም ግን ብዙም ሳይቆይ በአምላክ ተልእኮ ውስጥ በግል መሳተፍ ጀመረ።

በዚህ ምዕራፍ እንደተገለጸው የእሱ ተሳትፎ ስለ ሰዶምና ገሞራ ሰዎች መጸለይ እና መማለድ ነበር። ያም ማለት፣ በሆነ መንገድ፣ እነዚህ ሰዎች ከራሳቸው ባይሆንም መዳን ይችሉ እንደሆነ ለማየት ፈልጎ ነበር። በአንድ መልኩ፣ ተልዕኮ ማለት ያ ካልሆነ — ምንድን ነው?

በዚህ ምዕራፍ ውስጥ፣ ሶስት ታላላቅ የአብርሃም መንፈሳዊ ባህሪያት ተገልፀዋል፡ እንግዳ ተቀባይነት፣ ፍቅር እና ጸሎት— በተልእኮ ውስጥም በእጅጉ ሊረዱ የሚችሉ ባህሪያት ናቸው። ለጥቅምት 17 ሰንበት ለመዘጋጀት የዚህን ሳምንት ትምህርት ያጥኑ።

ጥቅምት 11
Oct 22

የእንግዳ ተቀባይነት ስጦታ


ዘፍጥረት 18:1-15ን ያንብቡ። አብርሃም ለእንግዶቹ የሰጠው ምላሽ ምን ዓይነት የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ አሳይቷል?



አብርሃም በቀን ሙቀት በድንኳኑ ደጃፍ ተቀምጦ ነበር። ይህ ባህሪ ያልተለመደ ነበር። በቀኑ በዚያ የበጋ ወቅት፣ ፀሐይ በከፍተኛ ደረጃ ላይ በምትገኝበት ጊዜ፣ ሁሉም ሰው ጥላ እና ንፋስ ይፈልጋል። ነገር ግን፣ ምናልባት አብርሃም የሚያልፍን ሰው ለመርዳት ሲል ሙቀቱን እየታገሠ ይሆን?

እዚያ እያለ ሶስት መንገደኞችን አየ። የእሱ ልምምድ የማያውቃቸውን እንግዶች ማስተናገድ ነበር። ለዚህም ነው ጥሪው ከአብርሃም የሆነው፤ በጽሑፉ ላይ ከድንኳኑ ደጃፍ ወደ እነርሱ ሮጠ ነው የሚለው። አብርሃም ወደ እርሱ ከመምጣታቸው በፊት እንኳ እነሱን ለማግኘት ቅድሚያውን ወሰደ የሚለው ነጥብ አስፈላጊ ነው።

“ቍራሽ እንጀራም ላምጣላችሁ፥ ልባችሁንም ደግፋ ከዚያም በኋላ ትሄዳላችሁ፤ ስለዚህ ወደ ባሪያችሁ መጥታችኋልና።” (ዘፍ. 18:4-5)።

አብርሃም ተልእኮውን ያውቅ ነበር፤ ይህም የጌታን እውቀት በአረማዊነት፣ በጣዖት አምልኮ እና በብዙ አማልክቶች አምልኮ በተዘፈቀ ዓለም ውስጥ ላሉ ሁሉ ማካፈል ነበር። በዚህ ክስተት ላይ እንደምናየው፣ ተልእኮውን ለመወጣት የተጠቀመው መንገድ እነዚህን በድንገት የመጡ እንግዶች በመልካም ሁኔታ ማስተናገድ ነበር።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ የአብርሃም “ታላቅ ቤተሰብ ከአንድ ሺህ የሚበልጡ ነፍሳትን ያቀፈ ነበር፤ ብዙዎቹ የቤተሰብ መሪዎች ነበሩ፣ እና ጥቂት ያልሆኑት ከአረማውያን የተመለሱ ናቸው። እንዲህ ያለው ቤተሰብ የመሪነት ቦታ ላይ ጠንካራ እጅ ያስፈልገዋል።

ደካማ፣ ወላዋይ ዘዴዎች በቂ አይሆኑም. . .። የአብርሃም ተጽዕኖ ከቤተሰቡ አልፏል። ድንኳኑን በተከለበት ቦታ ሁሉ የመሥዋዕቱንና የአምልኮውን መሠዊያ ተከለ። ድንኳኑ ሲወገድ መሠዊያው ይቀራል፤ ከአገልጋዩ ከአብርሃም ሕይወት ስለ አምላክ እውቀት ያገኙ ብዙ መንገደኛ ከነዓናውያን ለእግዚአብሔር መሥዋዕት ሊሰጡ በዚያ መሠዊያ አጠገብ ተቀመጡ።”—ኤለን. ጂ. ኋይት፣ ስነ-ትምህርት፣ ገጽ. 187.

ከመጀመሪያው ጀምሮ፣ ይህ ሰው እግዚአብሔር ለተልእኮ እንደጠራው፣ ወደ ተስፋይቱ ምድር መሄዱ ለመዝናናት ሳይሆን በዙሪያው ላሉት በረከት ለመሆን እና በዘሩ በኩል ደግሞ ለአለም በረከት ለመሆን እንደሆነ ተረድቷል።

በእኛ ሕይወት ውስጥ የትኞቹን የአብርሃም እንግዳ ተቀባይነትን ምሳሌ መከተል እንችላለን?

ጥቅምት 12
Oct 23

የአብርሃም ፍቅር ለሁሉም


ዘፍጥረት 18:16-33ን ያንብቡ። አብርሃም ነገድ፣ ዘር ወይም ሕዝብ ሳይለይ ለሰው ሁሉ ያለውን ታላቅ ፍቅር ያሳየው እንዴት ነበር?



ከዘፍጥረት 18 የተወሰደው ሁለተኛው የአብርሃም ባሕርይ ለሁሉም ሰው በግል ለማያውቃቸውም ሰዎች ጭምር የነበረው ፍቅር ነው። ይህ ለእያንዳንዳችን ትልቅ ትምህርት ነው። የሰዶምና የገሞራ ሰዎች ኃጢአተኞች ነበሩ፤ ከርሱ አኗኗር በጣም የራቁ፣ ነገር ግን ልቡ ዘር፣ ጾታ፣ ቋንቋ እና ሃይማኖት ሳይለይ ሁሉንም ሰው በማፍቀር የተሞላ ነበር።

እግዚአብሔር የሰዶምና የገሞራን ከተሞች ለማጥፋት ያደረገውን ውሳኔ ለአብርሃም ገለጠለት። “እግዚአብሔርም አለ፦ የሰዶምና የገሞራ ጩኸት እጅግ በዝቶአልና፥ ኃጢአታቸውም እጅግ ከብዳለችና፥እንግዲህስ ወደ እኔ እንደ መጣች እንደ ጩኸትዋ አድርገው እንደ ሆነ ወርጄ አያለሁ፤ እንዲሁም ባይሆን አውቃለሁ። ” (ዘፍ. 18:20- 21)።

አብርሃም በታላቅ ትሕትናና በአክብሮት እንዲህ ሲል ለእግዚአብሔር ልመና አቀረበ :- “ጻድቁን ከኃጢአተኛ ጋር ትገድል ዘንድ፥ ጻድቁም እንደ ኃጢአተኛ ይሆን ዘንድ፥ እንደዚህ ያለው አድራጎት ከአንተ ይራቅ። የምድር ሁሉ ፈራጅ በቅን ፍርድ አይፈርድምን?” ( ዘፍ. 18:25)

አብርሃም በፍቅሩ ጻድቃንን ብቻ ሳይሆን በእነዚህ ከተሞች ያሉትን ሰዎች ሁሉ ለማዳን ተስፋ አድርጓል። በእርግጠኝነት፣ አብርሃም በዚያ የሚኖሩ ሰዎች ምን ያህል ክፉ እንደሆኑ ያውቃል። ስለ እነዚያ ሰዎች እና ስለ ድርጊቶቻቸው ምን እንደሰማ ማን ያውቃል? እናም በሚቀጥለው ምዕራፍ እንደተገለጸው፣ ስለሎጥ እና ከቤቱ ውጭ ስለነበሩት አመፀኛ ሰዎች አስከፊ ታሪክ (ዘፍ. 19፡1-11 ይመልከቱ) ከሰማነው ተነስተን እነዚህ በጣም ክፉ ሰዎች ነበሩ።

አብርሃም ግን የእግዚአብሔርን ፍቅር ለራሱ በማወቅ ስለ እነርሱ ተማጸነ። አብርሃም የሰው ልጆች ሁልጊዜ በንስሐ ወደ እግዚአብሔር መመለስ እንደሚችሉ ያውቅ ነበር። ለአብርሃም፣ የእነዚህን ከተሞች ነዋሪዎች ማዳን ንስሐ እንዲገቡ ዕድል ይሰጣቸዋል።

በመጨረሻም፣ አብርሃም አምላክ ለሰው ልጆች ባለው ፍቅር ላይ በመመስረት ጥያቄውን አቀረበ። እርሱ ራሱ ለኃጢአተኞች ታላቅ ፍቅር ነበረው፤ እናም ሕይወት እስካለ ድረስ፣ የመዳን ተስፋ እንዳለ ያውቅ ነበር።

ለምንድነው የምልጃ ጸሎት በራሳችን የጸሎት ሕይወት ውስጥ በጣም አስፈላጊ የሆነው? ለተቸገሩ ሰዎች መጸለይ በመንፈሳዊ ህይወታችን እንድናድግ እና እግዚአብሔር ለኃጢአተኞች ያለውን ፍቅር የበለጠ እንድንለማመድ የሚረዳን እንዴት ነው?

ጥቅምት 13
Oct 24

የአብርሃም የጸሎት መንፈስ


ዘፍጥረት 18:23-32 እና ያዕቆብ 5:16ን ያንብቡ። ይህ የምልጃ ጸሎት ስላለው ኃይል ምን ያስተምረናል?



በአብርሃም እና በእግዚአብሔር መካከል ያለው ውይይት የምልጃ ጸሎት ምሳሌ ነው። አብርሃም በዚህ ምዕራፍ በእግዚአብሔር ፊት ስለ ሰዶምና ገሞራ ሰዎች አማላጅ ሆኖ ቀርቧል። በነርሱ ፋንታ ስለ እነርሱ ሲለምን ነበር፤ ይህም በተወሰነ መልኩ በአብ ፊት አማላጃችን የሆነውን ኢየሱስን ይመስላል። የዚህ ዘመን ተልዕኳችን የሚሳካው በዚህ አይነት ጸሎት ከቀጠልን ብቻ ነው።

አብርሃም የሰዶምን፣ የገሞራን እና ሌሎች በአቅራቢያው ያሉትን ከተሞች ነዋሪዎችን መውደድ ተምሯል። ጸሎቱ ቅን እና እውነተኛ የነበረው ለዚህ ነው። የሰዶምና የገሞራን ነገሥታት ካሸነፉ አንዳንድ ነገሥታት ጋር ተዋግቷል። ከአብርሃም ድል በኋላ፣ የሰዶም ንጉሥ ቤራ፣ አብርሃምን ከመልከጼዴቅ ጋር ሊገናኘው መጣ። ቤራ ሕዝቡን ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ ጠየቀ፡- “ሰዎቹን ስጠኝ፥ ከብቱን ግን ለአንተ ውሰድ አለው” (ዘፍ. 14፡21)። ይህ ንጉሥ ለሕዝቡ ያለውን ፍቅር የሚያሳይ ነው። የአብርሃም አንዱ ታላቅ ባሕርይ ፍቅር ስለሆነ የሰዶምና የገሞራን ነገሥታት ወደዳቸው፤ ስለ እነርሱና ስለ ሕዝባቸውም ጸለየ። “ለሚጠፉ ነፍሳት ያለው ፍቅር አብርሃም እንዲፀልይላቸው አነሳሳው።”—Ellen G. White፣ Patriarchs and Prophets፣ p. 140.

አብርሃም በጸሎቱ ትሁትና ፅኑ ነበር። 50 ጻድቃን በዚያ ከኖሩ ከተማይቱን እንደሚያድን እግዚአብሔር የመጀመሪያውን ልመና እንደተቀበለ፣ አብርሃም በዚያው ምልጃውን ቀጠለ።

ያለ ጸሎት፣ ያለ ምልጃ ጸሎት ተልእኳችን ስኬታማ ሊሆን አይችልም። ከአንድ ሰው ጋር ከተገናኘን በኋላ ምስክርነት ወይም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ከሰጠናቸው በኋላ ለነዚያ ሰዎች መጸለይ አለብን። እግዚአብሔር እኛ የተገናኘናቸውን ሰዎች ልብ በመንካት ለእነዚህ ጸሎቶች ትኩረት ይሰጣል። ጓደኞቻችንን ወይም ወዳጆቻችንን የሚለውጠው የእኛ ቃል ወይም አንደበተ ርቱዕነታችን አይደለም - መንፈስ ቅዱስ ነው።

በተሰማራንበት በማንኛውም የወንጌል ተልዕኮ ውስጥ ለእያንዳንዱ ሰው በግለሰብ ደረጃ መጸለይ ያለብን ለዚህ ነው።

ሮሜ 8፡34 እና ዕብራውያን 7፡25ን ያንብቡ። እነዚህ ጥቅሶች ኢየሱስ ስላደረገልን ነገር ምን ይነግሩናል? ለሌሎች ማድረግ ስላለብን የምልጃ ፀሎት እንድንረዳ ይህ እውነት የሚረዳን እንዴት ነው?

ጥቅምት 14
Oct 25

የአብርሃም ተልዕኮ


ዘፍጥረት 19:1-29ን ያንብቡ። የአብርሃም የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ፣ የፍቅር እና የጸሎት መንፈስ ምን ውጤት አስገኘ?



ጽሑፉ ሎጥ በሰዶም ከተማ ስላለው ቦታ አስገራሚ ፍንጭ ይሰጣል፡- “ሎጥ በሰዶም በር ተቀምጦ ነበር” (ዘፍ. 19፡1)። ይህ ማለት በከተማው ውስጥ ትልቅ ቦታ ያለው በእርግጠኝነትም የመንግስት መኮንን ነበር፤ ምክንያቱም በበሩ ላይ መቀመጥ የመኮንኖች፣ የዳኞች እና የነገሥታት መብት ስለሆነ ነው (2ሳሙ. 19: 8፣ ኤር. 38:7፣ ሩት 4:1)።

ዘፍጥረት 19 ከምዕራፍ 18 እና ከአብርሃም ጋር ያለው የመላእክት ታሪክ ትይዩ ነው ማለት ይቻላል። አብርሃም እና ሎጥ እያንዳንዳቸው በመግቢያው ወይም በበሩ ላይ ተቀምጠዋል (ዘፍ. 18:1፣ ዘፍ. 19:1)፤ አብርሃምና ሎጥ እንግዶችን በየማደሪያቸው እንዲያርፉ ጋብዘዋል (ዘፍ. 18፡3፣4፣ ዘፍ. 19፡2)። አብርሃም እና ሎጥ እያንዳንዳቸው ለጎብኚዎቻቸው ምግብ አዘጋጅተዋል (ዘፍ. 18፡4-8፣ ዘፍ. 19፡3)። ምንም አይነት ደካማ ጎን ቢኖረው፣ ሎጥ አንዳንድ ጥሩ ባህሪያት የነበሩት ይመስላል።

“እግዚአብሔርም በሰዶምና በገሞራ ላይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ከሰማይ እሳትና ዲን አዘነበ፤ እነዚያንም ከተሞች፥ በዙሪያቸው ያለውንም ሁሉ፥ በከተሞቹም የሚኖሩትን ሁሉ፥ የምድሩንም ቡቃያ ሁሉ ገለበጠ።” (ዘፍ. 19:24-25)።

በዚህ ዘገባ ጊዜ በሰዶምና በገሞራ ምን ያህል ሰዎች እንደነበሩ አናውቅም፣ ነገር ግን ከእነዚህ በሺዎች ከሚቆጠሩት ሰዎች መካከል አራቱ ብቻ ከተማይቱን ለቀው ሲወጡ የዳኑት ደግሞ ሦስቱ ብቻ ነበሩ። ከዘፍጥረት ጎርፍ ጋር ተመሳሳይ ነው። በዚያን ጊዜ ምን ያህል ሰዎች በሕይወት እንደነበሩ አናውቅም፣ ግን አብዛኞቹ እንዳልዳኑ እናውቃለን።

የዳኑት ጥቂት የሰዶም ነዋሪዎች ለኛ ተልእኮ መልዕክት አላቸው፡ ሁሉም አይድኑም። ሁሉም ሰው ኢየሱስን እና የእሱን የማዳን እቅድ እንዲቀበል እንፈልጋለን፣ ነገር ግን እያንዳንዱ ሰው ነጻ ምርጫ አለው። የእኛ ተግባር በተቻለ መጠን ብዙ ሰዎች ኢየሱስን እንዲመርጡ መጋበዝ ነው። ተልእኳችንን በምንፈጽምበት ጊዜ፣ እግዚአብሔር በመንፈስ ቅዱስ በኩል ይረዳናል፤ ነገር ግን ከማንም ፈቃድ ፈጽሞ አይቃረንም።

ነፃ ምርጫ ማለት በመጨረሻ፣ ምንም ብናደርግ፣ ምንም ያህል ብንጸልይ፣ መዳን በእያንዳንዱ ግለሰብ ምርጫ ላይ ይወሰናል ማለት ነው።

የወንጌል ሥራ በምንሠራበት ጊዜ የምንፈልገውን ውጤት ካላየን ተስፋ እንዳንቆርጥ መማር የምንችለው እንዴት ነው?

ጥቅምት 15
Oct 26

ለእግዚአብሔር ፈቃድ መገዛት


ዘፍጥረት 12:1-9ን ያንብቡ። እነዚህ ጥቅሶች ምንም እንኳን ከፊት ያለው መንገድ ግልጽ ባይመስልም ለእግዚአብሔር ፈቃድ ስለመገዛት ምን ያስተምራሉ?



ከአብርሃም ዋና ባሕርያት አንዱ ለእግዚአብሔር ፈቃድ መገዛቱ ነበር። አብርሃም ከእግዚአብሔር ጋር የነበሩት ልምምዶች ሁሉ መገዛቱን ያሳያሉ።

መጠራቱ፡- አብርሃም ከሰማይ ፈታኝ ጥሪ ተቀበለ፡- “እግዚአብሔርም አብራምን፡- ከአገርህ ከዘመዶችህም ከአባትህም ቤት ተለይተህ እኔ ወደማሳይህ ምድር ውጣ፤ አለው።” (ዘፍ.12፡1) ከሰማይ ድምፅ ሲሰማ፣ የመጀመርያው ምላሽ ቅዠት እንደሆነ በማሰብ ይህንን ድምጽ ችላ ማለት ሊሆን ይችላል። ወይም ለምሳሌ መሄድ አልፈልግም፤ እዚህ ተመችቶኛል” ብሎ መልእክቱን መቃወም ይችል ነበር። ‘እኔ የማሳይህ ምድር’ እንደ መድረሻ ቦታ እንግዳ የሆነ መግለጫ ሊመስል ይችላል! እርሱ ግን ጥሪውን ተቀበለ።

ፈቃዱን ለእግዚአብሔር ፈቃድ አስገዛና የአባቱን ቤተሰብና አገሩን ተወ፡ “አብራምም እግዚአብሔር እንደ ነገረው ሄደ” (ዘፍ. 12:4)።

የምድሪቱ ምርጫ፡ በሎጥ እና በአብርሃም አገልጋዮች መካከል ጠብ ተፈጠረ፤ አብርሃም ግን ከሥጋውና ከደሙ ጋር የሚዋጋ ሰው አልነበረም። ለእግዚአብሔር ፈቃድ ሲገዛ እንደገና ባረከው፡- “ሎጥ ከተለየው በኋላም እግዚአብሔር አብራምን አለው፦ ዓይንህን አንሣና አንተ ካለህበት ስፍራ ወደ ሰሜንና ወደ ደቡብ ወደ ምሥራቅና ወደ ምዕራብ እይ፤ የምታያትን ምድር ሁሉ ለአንተና ለዘርህ ለዘላለም እሰጣለሁና።” (ዘፍ. 13:14-15)

የሰዶምና ገሞራ ጥፋት፡- እግዚአብሔር የእነዚህን የሁለቱን ከተሞች ዕጣ ፈንታ ለአብርሃም በገለጠለት ጊዜ፣ አብርሃም በፍቅር ተሞልቶ ከተማዎቹን ለማዳን ሞከረ። በከተሞቹ ውስጥ አሥር ጻድቃን እንኳን ስላልነበሩ ከተሞቹ ጠፉ። አብርሃም ለእግዚአብሔር ፈቃድ በመገዛት በእነዚህ ከተሞች ላይ የተላለፈውን የእግዚአብሔርን ፍርድ ተቀበለ።

ጌታ አብርሃምን ሊጠቀምበት የቻለው በማንኛውም ሁኔታ ለእግዚአብሔር በመገዛቱ ነው። ዛሬም ቢሆን ከእኛ ጋር ተመሳሳይ መሆን አለበት።

ግድድሮሽ፡- በከተሞቻችን ውስጥ ወንጌልን በአግባቡ እና ውጤታማ በሆነ መንገድ በመስበክ ረገድ እንቅፋት ያጋጥመናል። እግዚአብሔር ጣልቃ እንዲገባልን መለመን አለብን።

በተጨማሪም፡- ከርስዎ ጋር በሚመሳሰል አስቸጋሪ ሁኔታ በቀጥታ የተጎዳን ሰው የሚያገኙበትን መንገድ ይፈልጉ። ለእሱ ወይም ለእሷ እንደምትጸልዩለት ይንገሩት/ሯት፣ እና ለመርዳት ምን ማድረግ እንደሚችሉ እንዲያሳይዎ አምላክን ይለምኑ።

ጥቅምት 16
Oct 27


ተጨማሪ ሀሳብ


“ለሚጠፉ ነፍሳት ያለው ፍቅር አብርሃምን እንዲፀልይላቸው አነሳሳው። የረከሰችውን ከተማ ኃጢአት ቢጸየፍም፣ ኃጢአተኞቹ እንዲድኑ ፈለገ።

ለሰዶም ያለው ጥልቅ ፍላጎት እኛ ንስሐ ላልገቡ ሰዎች ሊሰማን የሚገባውን ጉጉት ያሳያል። ኃጢአትን ልንጠላ ለኃጢአተኛውም ልናዝንለትና እና ልንወደው ይገባል።

በሰዶም ላይ እንደደረሰው አይነት አስከፊ ጥፋት ውስጥ እየገቡ ያሉ ተስፋ ያጡ ነፍሳት በዙሪያችን አሉ። በየቀኑ የአንዳንዶች የምህረት ጊዜ እየተዘጋ ነው። በየሰዓቱ አንዳንዶች ምህረት ሊደርስበት ከሚችለው ርቀው ያልፋሉ። እናም ኃጢአተኛው ከዚህ አስፈሪ ቅጣት እንዲሸሽ የማስጠንቀቂያ እና የልመና ድምጽ የት አለ? ከሞት ይመልሱ ዘንድ የተዘረጉት እጆች ወዴት ናቸው? በትህትና እና በፅኑ እምነት እግዚአብሔርን ስለ እርሱ የሚማፀኑት የት አሉ?

“የአብርሃም መንፈስ የክርስቶስ መንፈስ ነበር። የእግዚአብሔር ልጅ ራሱ በኃጢአተኛው ምትክ ታላቅ አማላጅ ነው። ለቤዛነት ዋጋ የከፈለለት እርሱ የሰውን ነፍስ ዋጋ ያውቃል። ነውር የሌለው ንፁህ ተፈጥሮ ብቻ ሊኖረው እንደሚችለው አይነት ጥላቻን ለክፋት በማሳየት፣ ክርስቶስ ወሰን የሌለው በጎነት ብቻ የሚፀንሰውን ፍቅር ለኃጢአተኛው አሳየ። በስቅለቱ ስቃይ ውስጥ እራሱ የአለምን ሁሉ የኃጢአት ሸክም ተሸክሞ ስለ ተሳዳቢዎቹ እና ገዳዮቹ ‘አባት ሆይ የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው።’ (ሉቃስ 23:34) ብሎ ጸለየ።”— Ellen G. White, Patriarchs and Prophets, p. 140

“አብርሃም እንደ ኃያል፣ ጥበበኛ እና አስተዋይ አለቃ ሆኖ በዙሪያው ባሉት አሕዛብ የተከበረ ነበር። በጎረቤቶቹ ላይ ተጽዕኖው መፍጠሩን አላቆመም። የእሱ ሕይወትና ባሕርይ፣ ከጣዖት አምላኪዎች ጋር ባለው ግልፅ ልዩነት፣ ለእውነተኛው እምነት ትልቅ አስተዋጽኦ አደረገ። ለአምላክ ያለው ታማኝነት የማያወላውል ነበር፤ የእሱ ወዳጅነትና ደግነት በራስ የመተማመን መንፈስና ወዳጅነትን የሚነሳሳ ሲሆን ያልወላወለ ታላቅነቱ እንዲያከብሩት ያስገድድ ነበር።”— Patriarchs and Prophets, pp. 133, 134


የመወያያ ጥያቄዎች




1. የተልእኮውን ጥሪ የፈጸመን ግለሰብ የሚያሳዩን ሌሎች የቅዱሳት መጻሕፍት ምሳሌዎች የትኞቹ ናቸው? ስለ መጥምቁ ዮሐንስስ? ስኬታማ ነበር ልንል እንችላለን?

2. ዘፍጥረት 19:30-36ን ያንብቡ። ይህ ከሰዶም ስለዳኑት ስለ አንዳንዶቹ ባህሪ ምን ይነግረናል?

3. ተልዕኮን ከመፈፀምና ከአገልግሎት አንፃር ከአብርሃም ሕይወት ሌሎች ምን አይነት ትምህርቶችን እናገኛለን?

4. ይህን ያሰላስሉ፡- በእርስዎ እይታ አብርሃም ለሰዶምና ገሞራ ያደረገው ምልጃ የተሳካ ነበር ወይስ አልነበረም?




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA Union SSL