የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

የእግዚአብሔር ተልዕኮ የእኔ ተልዕኮ



4ኛ ሩብ ዓመት 2023


ጥቅምት 3 - 9

3ኛ ትምህርት

Oct 14 - 20




የእግዚአብሔር ጥሪ ለተልዕኮ



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሳምንት ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ዘፍ. 11፡1-9፣ ዘፍ. 12፡1-3፣ ዳን. 9፡24-27፣ ማቴ. 1፡21፣ ዘፍ. 12፡10-13፡1፣ የሐዋርያት ሥራ 8፡1-4፣ የሐዋርያት ሥራ 1፡8።


መግቢያ ጥቅስ፡- “ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በወረደ ጊዜ ኃይልን ትቀበላላችሁ፥ በኢየሩሳሌምም በይሁዳም ሁሉ በሰማርያም እስከ ምድር ዳርም ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ።” (ሐዋ. 1፡8)።

እግዚአብሔር አንዳንድ ጊዜ ከምቾት ክልላችን አውጥቶ ምስክሮቹ ሊያደርገን ይችላል። አንዳንድ ጊዜ ይህ ለውጥ የእርሱን ዓላማዎች ለመፈጸም ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል፤ ለምሳሌ በባቢሎን ግንብ ወቅት የተበተኑት ሰዎችን መውሰድ እንችላለን። “ይህ መበታተን ምድር በሰዎች እንድትሞላ ምክንያት ሆነ፣ እናም ሰዎች የጌታ ዓላማ እንዳይፈፀም በተጉበት በዚያው መንገድ ተፈጸመ።”—Ellen G. White፣ Patriarchs and Prophets፣ p. 120። አብርሃምም ከሀገሩ ወደ ሌላ (ዘፍ. 12) ሀገር ሲሄድ ለምስክርነት ነበር። የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በራሳቸው ሰዎች መካከል ብቻ ከመስራት ይልቅ (ሐዋ. 3) ለሌሎችም ወደ መሥራት ሄደዋል (ሐዋ. 8፡1-4)። በሐዋርያት ሥራ 1፡8 ላይ ኢየሱስ የወንጌል ስርጭት መርህን አስቀምጧል፤ እነሱም ከአካባቢው ማለትም ከኢየሩሳሌም እና ከይሁዳ ይጀምራሉ፣ ከዚያም ወደ ሰማርያ እና በመጨረሻም እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ይሄዳሉ።

ነገር ግን አገራችንን ባንለቅም እግዚአብሔር አሁንም በዙሪያችን ላሉ ሰዎች እንድንደርስ ይፈልጋል። በእየሩሳሌም ያለችው ቤተ ክርስቲያን በስራዋ ረክታ ዝም ስትል ምእመናኑ ተበታተኑ። ስደት መጥቶ ሰዎች ቢሰቃዩም እነዚህ አሳዛኝ ክስተቶች የምሥራቹን በመላው ዓለም ለማዳረስ የሚረዱ መንገዶች ሆኑ። ለጥቅምት 10 ሰንበት ለመዘጋጀት የዚህን ሳምንት ትምህርት ያጥኑ።

ጥቅምት 4
Oct 15

ከምቾት ክልላችን አልፎ መንቀሳቀስ


ሌሎችን ለማግኘት፣ እግዚአብሔር ከእኛ ምቾት ቀጠና እንድንሻገር ይፈልጋል።

ከራሳችን ጎሳ ወይም ማህበረሰብ ጋር ብቻ የመቆየት ፍላጎት ራስ ወዳድነትን አልፎ ተርፎም ክፋትን ሊያስከትል ይችላል። ይህ አደጋ ከባቤል ታሪክ ከተወሰዱት ትምህርቶች አንዱ ነው።

ዘፍጥረት 11:1-9ን ያንብቡ። የህዝቡ አላማ ምን ነበር? ምን ሊያደርጉ ፈልገው ነበር? አምላክስ ለምን አከሸፈው?



ይህ በባቤል ግንብ ላይ ያሉ ሰዎች ታሪክ ታላቅ ምኞታቸውን ያሳያል። በዓለም ላይ የትም የማይገኝ ከተማና ግንብ ለመሥራት አስበው ነበር፤ “ስማችንን እናስጠራ ዘንድ እስከ ሰማይ የሚደርስ ግንብ” (ዘፍ. 11:4) እንሥራ ብለው ጀመሩ።

በፖለቲካ፣ በሥነ ጥበብ፣ በንግድ፣ በሃይማኖትም ዛሬም ቢሆን ሰዎች ተመሳሳይ ነገር ለማድረግ ምን ያህል ጊዜ ይፈልጋሉ? ስማቸውን በትልቁ ማስጠራት የሚፈልጉ አሉ። በመጨረሻም ጥረታቸው ምን ያህል ከንቱ እና ከንቱ ነው። (መክ. 2:1-11 ይመልከቱ)

መጽሐፍ ቅዱስ በዘፍጥረት 11፡4 ላይ እነዚህ ሰዎች ግንቡን ለመስራት የፈለጉት በምድር ላይ እንዳይበተኑ እንደሆነ ይናገራል። በራሳቸው ራስ ወዳድ ምክንያት አብረው መቆየት ፈልገው ነበር። እግዚአብሔር ግን ሌላ እቅድ ነበረው።

እነዚህ ሰዎችም ለዚህ ሥራ አንድ ሆነዋል። ነገር ግን “እግዚአብሔርም አለ፡ - እነሆ፥ እነርሱ አንድ ወገን ናቸው፥ ለሁሉም አንድ ቋንቋ አላቸው፤ ይህንም ለማድረግ ጀመሩ፤ አሁንም ያሰቡትን ሁሉ ለመሥራት አይከለከሉም።” (ዘፍ. 11፡6)። ይህ የህዝቡ ታላቅ እቅድ በእውነቱ ክፉ ነበር።

ቅዱሳት መጻሕፍት በግልጽ ባይናገሩም ኤለን ኋይት፣ እግዚአብሔር ምድርን ዳግመኛ በውኃ እንደማያጠፋት የገባውን ቃል አላመኑም ነበር (ዘፍ. 9፡14-15) ብላለች።

በእግዚአብሔር ቃል ላይ ከመታመን ይልቅ ለራሳቸው መጠበቂያ መገንባት አስበዋል። የመጨረሻው ዓላማቸው ምንም ይሁን ምን፣ እግዚአብሔር ኃሳባቸው ንፁህ እንዳልሆነ፣ ነገር ግን በራስ ወዳድነት ምኞት የተሞላ መሆኑን ያውቅ ስለነበር ዓላማቸውን እንዳያሳኩ ከለከላቸው። እርስዎ ምቾት ያለው ቡድን ወይም የጎሳ ማህበረሰብ አካል ነዎት? ዘርዎ ወይም የሀገርዎ ዜጋ ካልሆኑ ሌሎች ጋር መገናኘት(መሥራት) የሚችሉት እንዴት ነው?

ጥቅምት 5
Oct 16

ለአለም ሁሉ በረከት መሆን


ዘፍጥረት 12:1-3ን ያንብቡ። እግዚአብሔር ለአብራም የሰጠው መመሪያ የተልእኮ ጥሪ የሆነው በምን መንገድ ነው?



እግዚአብሔር አብራምን (በኋላ አብርሃም የተባለውን) አገሩንና ሕዝቡን ትቶ ወደ ሌላ አገር እንዲሄድ ጠየቀው። እግዚአብሔር በምድር ላይ ያለውን መለኮታዊ አላማ ለመፈጸም እንደ ተሽከርካሪ አብርሃምን የተጠቀመው በእቅድ ነው። አብርሃምም እንደ እግዚአብሔር ቃል ሄደ። እግዚአብሔር ለእርስዎ ያለው እቅድ፣ ለሌሎች በረከት ይሆኑ ዘንድ፣ ቤተሰብዎን እና ህዝብዎን ትተው እርሱን ለማገልገል ወደሚከፍትልዎ ቦታ እንዲሄዱ ሊሆን ይችላል።

የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ። እያንዳንዱ ጥቅስ ስለ እግዚአብሔር ቃል ኪዳን፣ ለእኛ ስለገባው ቃል ምን ይናገራል?

ዘፍ. 3፡15



ዘፍ.17፡19



ዘሁ. 24፡17



ኢሳ. 9፡6



ዳንኤል. 9፡24-27



ማቴ. 1፡21



ከላይ ከተጠቀሱት ጥቅሶች ውስጥ፣ እግዚአብሔር በኤደን ገነት ውስጥ አንድ ሰው ለኃጢአት ችግር መፍትሄ ሆኖ እንደሚመጣ የገባውን ቃል ሊፈጽም እንደነበረ ግልጽ ነው። ይህ መፍትሔ፣ መሲሑ ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ከአብርሃምና ከይስሐቅ ዘር (ከሣራ) የሚወጣ ነበር። ዕብራውያን 11፡9 ላይ ይስሐቅና ያዕቆብ እግዚአብሔር ለአብርሃም የገባው የበረከት ተስፋ ወራሾች እንደነበሩ ይናገራል።

አብርሃም ራሱ የተስፋው ዘር በእርሱ በኩል እንዴት እንደሚነሳ ምን ያህል እውቀት እንደነበረው ወይም እንደተረዳ በትክክል አናውቅም፣ ነገር ግን በእምነት ወጥቷል። “አብርሃም በተጠራ ጊዜ ርስት አድርጎ ወደሚቀበለው ስፍራ ለመውጣት በእምነት ታዘዘ። ወዴትም እንደሚሄድ ሳያውቅ ወጣ።” (ዕብ. 11:8)።

ለእኛ እንዴት ያለ ምሳሌ ነው! እርስዎ ወዴት እንደሚሄዱ “ሳያውቁ” እንዲወጡ በእግዚአብሔር ተጠሩ እንበል፤ ለዚህ ጥሪ እንዴትና ለምን ምላሽ ይሰጣሉ?

ጥቅምት 6
Oct 17

የአብርሃም ጥሪ


የእግዚአብሔርን ጥሪ ተከትሎ፣ አብርሃም እግዚአብሔር ወዳዘዘው ምድር ገባ። ሆኖም ፣ ከመጀመሪያው ጀምሮ ፣ ነገሮች ለእሱ በጣም ጥሩ ሆነው አልታዩም።

አምላክ እንዲሄድ ባዘዘው ቦታ ደረሰ፤ ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው “በዚያን ጊዜ ከነዓናውያን(በጭካኔያቸውና በዓመፅ የታወቁ) በምድር ላይ ነበሩ” (ዘፍ. 12:6)።

አብርሃም እዚያ ከደረሰ በኋላ ጌታ ተገለጠለትና “ይህችን ምድር ለዘርህ እሰጣለሁ” ያለው መሆኑ ምንም አያስደንቅም (ዘፍ. 12:7)። አብርሃም ማበረታቻው እንደሚያስፈልገው ምንም ጥርጥር የለውም።

ይሁን እንጂ ነገሮች አሁንም በተለይ ለእሱ በመልካም አልሄዱም፤ ቢያንስ በመጀመሪያ።

ዘፍጥረት 12:10-13:1ን ያንብቡ። ቀጥሎስ ምን ነገሮች አጋጠሙት? ይህ የእግዚአብሔር ሰውስ ምን አይነት ስህተትን ፈፀመ?



በራሱ አገር ውስጥ የነበረውን ምቹ እና ምናልባትም የበለጸገ ኑሮ ትቶ “ወዴት እንደሚሄድ ሳያውቅ” (ዕብ. 11፡8) መሄድ ለእሱ ምን ያህል ተስፋ አስቆራጭ ሆኖበት ይሆን! ካጋጠሙት የመጀመሪያ ነገሮች አንዱ ደግሞ ረሃብ ነበር! ይህ ረሃብ እጅግ የከፋ ከመሆኑ የተነሳ እግዚአብሔር እንዲኖርበት ከነገረው ቦታ ተነስቶ ሌላ ቦታ ሄደ። እና ከዚያ በኋላ ነገሮች የበለጠ እየባሱ ሄዱ። “አብርሃም በግብፅ በነበረበት ወቅት ከሰብዓዊ ድክመት ንፁህ እንዳልነበረ የሚያሳይ ፍንጭ አሳይቷል። ሣራ ሚስቱ መሆኗን ሲደብቅ በመለኮታዊ እንክብካቤ ላይ እምነት ማጣቱን፣ በሕይወቱ ውስጥ ብዙ ጊዜ ያሳየውንና ግሩም ምሳሌ ሆኖ የቆየበትን ያን ከፍተኛ እምነት እና ድፍረት ማጣቱን አሳየ። . . . በአብርሃም እምነት ማጣት ሳራ በታላቅ አደጋ ውስጥ ወደቀች። የግብፅ ንጉሥ ስለ ውበቷ ሲነገር ሚስት ሊያደርጋት አስቦ ወደ ቤተ መንግሥቱ እንድትወሰድ አደረገ። ነገር ግን ጌታ በታላቅ ምህረቱ በንጉሣዊው ቤተሰብ ላይ ፍርዶችን በመላክ ሣራን ጠበቃት።”—Ellen G. White፣ Patriarchs and Prophets፣ ገጽ. 130.

ማንም ሰው የተልእኮ ሥራ ቀላል ነው አላለም፣ እናም በመዋሸትና በማታለል፣ አብርሃም ነገሩን የበለጠ አባባሰው። እግዚአብሔር ግን የትዕግሥት አምላክ ስለሆነ አገልጋዬ አብርሃም ተሳሳተ ብሎ አልጣለውም። ብንሳሳትም ልክ እንደ አብርሃም በእምነት እና በመገዛት ከጌታ ጋር ከተጣበቅን፣ ስህተታችንና ኃጢያታችን ይቅር መባሉ ብቻ ሳይሆን ጌታ አሁንም ለተልእኮ ሊጠቀምብን እንደሚችል ማወቁ ምንኛ የሚያጽናና ነው።

አብራም በግብፅ ከነበረው ታሪክ ምን ትምህርት እናገኛለን?

ጥቅምት 7
Oct 18

የቀደመችው ቤተክርስቲያን እና የምቾት ክልሎች


የሐዋርያት ሥራ 8:1-4ን ያንብቡ። በቀደመችው ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የነበሩት ምዕመናን ከምቾት ክልላቸው እንዲበተኑ ያደረገው ምን ነበር?



እስከዚህ ጊዜ ድረስ፣ የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን በዋናነት በኢየሩሳሌም (ወይም በአይሁድ ግዛት ውስጥ እና በአይሁድ ሕዝብ መካከል) ነበረች። አጥባቂ አይሁዳዊና ፈሪሳዊ የነበረው ሳውል በትጋት ይሳተፍበት የነበረው ስደት በተጀመረ ጊዜ በኢየሩሳሌም ይገኙ የነበሩት የቤተ ክርስቲያን አባላት በመላው ይሁዳና በሰማርያ ተበታተኑ። ኢየሱስ በሐዋርያት ሥራ 1፡8 ላይ “በኢየሩሳሌም፣ በይሁዳም ሁሉ፣ በሰማርያም ሁሉ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ” ብሎ ተናግሮ ነበር። ይህ ቃል በሐዋርያት ሥራ 8፡4 እንደተገለፀው “የተበተኑት በሄዱበት ሁሉ ቃሉን በመስበካቸው” ተፈጸመ።

ቤተ ክርስቲያኒቱ ከኢየሩሳሌም መውጣት ከጀመረች በኋላም ቢሆን ይሰብኩ የነበረው በአይሁዳውያን ክልሎች ወይም በሌሎች ከተሞች ለሚገኙ የአይሁድ ሕዝቦች ነበር። የሐዋርያት ሥራ 11፡19 ቤተ ክርስቲያን እስከ ፊንቄ (ሊባኖስ) እና ቆጵሮስ ድረስ ተበታትኖ እንደነበር ይጠቁማል። ነገር ግን እስከዚህ ጊዜ ድረስ መልእክቱን ከአይሁዳውያን በስተቀር ለማንም አልሰበኩም። የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት እና የቀደመችው ቤተክርስቲያን ወደ አህዛብ ለመሄድ አላሰቡም፤ በዚህም አይሁዶች ብቻ ወደ ጌታ ይመጡ ነበር። አሁንም የቤተ ክርስቲያን ተልእኮ ምን መሆን እንዳለበት በጣም ጠባብ አመለካከት ነበራቸው።

የኢየሱስ ደቀ መዝሙር እና የቀደመችው ቤተክርስቲያን መሪ ከሆኑት አንዱ የሆነው ጴጥሮስ እንኳን ጳውሎስ ይህን ማድረግ ከጀመረ በኋላም የወንጌልን መልእክት ወደ አሕዛብ ለማድረስ አልፈለገም። ጴጥሮስ የተገረዙት ሐዋርያ (የአይሁድ ማለት ነው) እና ጳውሎስ የአሕዛብ ሐዋርያ በመባል ይታወቁ ነበር (ገላ. 2፡8)። መጀመሪያ ላይ፣ ጴጥሮስ ከአሕዛብ ጋር መታየት እንኳ አልፈለገም (ገላ. 2፡11-12)። ይሁን እንጂ አምላክ ጴጥሮስን ከምቾት ክልሉ አውጥቶ ልቡን ለወጠው። የወንጌል ተልእኮ ምን እንደሚያስፈጽም እና የኢየሱስ ሞት ለመላው ዓለም ምን ዓላማ እንዳለው መማር ጀመረ።

የሐዋርያት ሥራ 10:9-15፣ 28-29ን ያንብቡ። ጌታ ለጴጥሮስ የሰጠው መልእክት ምን ነበር? እኛስ በዘመናችን ይህን መሠረታዊ ሥርዓት በተልእኮ ሥራ ላይ ተግባራዊ ማድረግ የሚኖርብን እንዴት ነው?





ጥቅምት 8
Oct 19

ካሉበት መጀመር


የሐዋርያት ሥራ 1:8ን ያንብቡ። ኢየሱስ ወንጌልን በማካፈል ሥራ ውስጥ ምን መሠረታዊ መርህን አቅርቧል?



ለሌሎች የሚያካፍሉት መልካም ዜና እንዳላቸው ደቀመዛሙርት እንዴት ማካፈል እንዳለብን የሚያሳየው በኢየሱስ የተቀረፀው መርህ ይህ ነው። እውነትን ማካፈል ሌሎች ምን ያህል እንደተሳሳቱ ማሳመን ሳይሆን በዮሐ. ራእይ 14፡6-12 ባሉት ሦስቱ መላእክት መልእክቶች ላይ እንደተገለጸው ኢየሱስን ማካፈል ነው።

ነገር ግን በሐዋርያት ሥራ 1፡8 ውስጥ ባሉት የኢየሱስ ቃላት ውስጥ አንዳንድ መርሆች አሉ። በመጀመሪያ፣ “‘በኢየሩሳሌምም ምስክሮቼ ትሆናላችሁ’ ይላል። እንዳየነው (ቢደጋገምም) እኛ በአካል በምንኖርበት ቦታ የእርሱ ምስክሮች መሆን አለብን። ይህ የራሳችንን ቤት፣ ቤተክርስቲያናችንን፣ አካባቢያችንን እና ማህበረሰባችንን ሊያካትት ይችላል። በመጀመሪያ እኛ ባለንበት ቦታ፣ እሱ በመጀመሪያ ባኖረን አካባቢ- ቤት ወይም ስራ - እና ለእኛ ቅርብ ለሆኑ ሰዎች የእርሱ ምስክሮች መሆን አለብን። እነርሱም የቅርብ ቤተሰብ፣ የቤተ ክርስቲያን ሰዎች፣ የስራ ባልደረቦች፣ ጎረቤቶች እና ማህበረሰቡ ሊሆኑ ይችላሉ።

አንዳንድ ጊዜ ሰዎች የሱ ምስክሮች ለመሆን ወደ ሩቅ ሀገር እና ባዕድ ባህል መሄድ ብቻ ይፈልጋሉ። ዛሬ ግን በዙሪያቸው ላሉ ሰዎች አይመሰክሩም። ካለንበት ጀምረን ጌታ እንደሚመራን ከዚያ መንቀሳቀስ አለብን።

በመቀጠልም “በይሁዳም ሁሉ በሰማርያም እስከ ምድር ዳርም ድረስ” (የሐዋርያት ሥራ 1:8) እንደገና፣ ኢየሱስ መመስከር የባህል ድንበሮችን መሻገርን የሚያካትት እውነታ መሆኑን አረጋግጧል። ካለንበት ጀምረን ወደ ሌሎች አካባቢዎች ተንቀሳቅሰን ወደ ተለያዩ ማኅበራዊ፣ ብሔረሰባዊ እና ሃይማኖታዊ ቡድኖች እንድንደርስ ጥሪ ሊደረግልን ይችላል። የአንድ ብሔር ወይም የቋንቋ ሰዎች አባል ከሆንኩ ለመሻገር ከሚያጋጥሙኝ አነስተኛ የባህል እንቅፋቶች አንፃር ለእነሱ መመሥከር በጣም ቀላል ይሆንልኝ ይሆናል። በአንዳንድ የአለም አካባቢዎች በቤተክርስቲያኑ መዋቅር ውስጥ አንድ ጎሳ ወይም ነገድ ብቻ ነው የሚወከለው። ሆኖም፣ የኢየሱስ ታላቅ ተልእኮ እንደ እርሱ ምስክሮች፣ ከምቾት ክልላችን መውጣት እና ሀብታችንን ለእንደዚህ አይነት ሰዎች ማዋል ወሳኝ እንደሆነ ይነግረናል። የኢየሱስ መልእክትም ያስፈልጋቸዋል።

ተግዳሮት፡ ቤተ ክርስቲያኒቱ ለመድረስ ያልሞከረቻቸውን በማኅበረሰባችሁ ውስጥ ያሉ ልዩ ፍላጎት ያላቸውን ሰዎች ለይታችሁ ጻፉ።

በተጨማሪም፡ ልዩ ፍላጎት ላላቸው ሰዎች በተልዕኮ ለመሰማራት በቅርብ ጊዜ ውስጥ እድል እንዲያገኙ መጸለይ ይጀምሩ።

ጥቅምት 9
Oct 20


ተጨማሪ ሀሳብ


“የሐዋርያት ሥራ” ከሚለው መጽሐፍ ውስጥ “ታላቁ ተልእኮ” እና “እውነትን ፈላጊ” የሚል ርዕስ ያላቸውን ምዕራፎች ያንብቡ።

“ወደ ሰማይ ከማረጉ በፊት፣ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ ተልእኳቸውን ሰጣቸው። እርሱ የዘላለም ሕይወትን ሀብት ለዓለም የሰጠበት የፈቃዱ አስፈፃሚዎች እንደሚሆኑ ነገራቸው። እናንተ ለዓለም ስለ ከፈልኩት የመስዋዕትነት ሕይወቴ ምስክሮች ነበራችሁ፣ አላቸው። ለእስራኤል የደክምኩትን አይታችኋል። እና ምንም እንኳን ህዝቤ ህይወት እንዲኖረው ወደ እኔ ባይመጣም፣ ምንም እንኳን ካህናት እና ገዥዎች የፈለጉትን ቢያደርጉብኝም፣ ምንም እንኳን ቢክዱኝም፣ አሁንም የእግዚአብሔርን ልጅ የመቀበል ሌላ እድል አላቸው። ኃጢአታቸውን እየተናዘዙ ወደ እኔ የሚመጡትን ሁሉ እኔ በነጻ እንደተቀበልኩ አይታችኋል። ወደ እኔ የሚመጣውን ከቶ ወደ ውጪ አልጥለውም።

ለእናንተ ደቀ መዛሙርቴ ይህንን የምሕረት መልእክት አደራ እሰጣለሁ። ለሁለቱም ለአይሁዶች እና ለአሕዛብ—ለእስራኤል፣ በመጀመሪያ፣ ከዚያም ለሁሉም አሕዛብ፣ ቋንቋዎች እና ህዝቦች መሰጠት አለበት። የሚያምኑ ሁሉ ወደ አንድ ቤተ ክርስቲያን ይሰበሰባሉ።”— Ellen G. White, The Acts of the Apostles, pp. 27, 28

ታላቁ ተልእኮ ግልጽ ነው፡- “እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” (ማቴ. 28፡19)። ስለዚህ ወደሌሎች በተለይም ወደ ሌሎች አገሮች መሄድ እርግጠኛ ጉዳይ ነው።

“የወንጌል ተልእኮ የክርስቶስ መንግሥት መመሪያ ነው። ደቀመዛሙርቱ ለሁሉም የምሕረት ግብዣ በመስጠት ለነፍሶች በትጋት መሥራት ነበረባቸው። ሰዎች ወደ እነርሱ እስኪመጡ ድረስ መጠበቅ አልነበረባቸውም፤ መልእክታቸውን ይዘው ወደ ሰዎች መሄድ ነበረባቸው።”—ኤለን ጂ. ኋይት፣ የሐዋርያት ሥራ፣ ገጽ. 28.

“በዓለማችን ውስጥ ከምናስበው በላይ ለእግዚአብሔር መንግሥት የሚቀርቡ ብዙዎች አሉ። በዚህ የጨለማው የኃጢአት ዓለም ጌታ መልእክተኞቹን የሚመራባቸው ብዙ ውድ ዕንቁዎች አሉት። በየቦታው ከክርስቶስ ጎን የሚቆሙ አሉ። ብዙዎች ከምድራዊ ጥቅም ይልቅ የእግዚአብሔርን ጥበብ ይሸለማሉ እና ታማኝ ብርሃን አብሪዎች ይሆናሉ። . . . የጴጥሮስ አካሄድ በቀጥታ የእግዚአብሔርን እቅድ እንደሚፈጽም እና አድሎአዊነታቸው እና አግላይነታቸው ከወንጌል መንፈስ ጋር ፍጹም ተቃራኒ መሆኑን በማመን፣ ‘እንግዲያስ እግዚአብሔር ለአሕዛብ ደግሞ ለሕይወት የሚሆን ንስሐን ሰጣቸው’ በማለት እግዚአብሔርን አከበሩ። ስለዚህ ያለ ውዝግብ ጭፍኑ ጥላቻ ፈርሷል፣ በዘመናት ልማድ መሠረት የነበረው ማግለል ቀርቷል፣ እናም ወንጌል ለአህዛብ እንዲሰበክ መንገዱ ተከፍቷል።”—Ellen G. White፣ The Acts of the Apostles, pp. 140–142


የመወያያ ጥያቄዎች




1. “ተልዕኮ” የሚለውን ቃል በራስዎ ሕይወት ሲተገብሩት እንዴት ይገልፁታል?

2. በየቀኑ በአመለካከታችን እና በባህሪያችን ተልዕኳችንን መግለጽ የምንችለው በምን በምን መንገዶች ነው? በዕለት ተዕለት ተግባራችን ውስጥ የበለጠ ተልእኮ ተኮር መሆን የምንችለው እንዴት ነው?

3. ከእኛ የተለዩ ሰዎች ላይ ካለን ጭፍን ጥላቻ ለመገላገል ልባችንን መመርመርና ኃይሉን መሻት ምን ያህል አስፈላጊ ነው?




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA Union SSL