የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ለዚህ ሳምንት ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡- ዮሐንስ 20፡21-22፣ ማቴ. 28፡ 16-20፣ ዮሐ. ራዕ. 14፡6-7፣ ዘዳ. 7፡6፣11፣12፣ ዮሐ. ራዕይ 7፡9-10።
መግቢያ ጥቅስ፡- “እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ፣ በወልድና በመንፈስ
ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ
ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።” ማቴ. 28፡19-20
እግዚአብሔር የተልእኮ አምላክ መሆኑን የሚያወሳው መሪ ሀሳብ በመላው
ቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ ይገኛል። ይህ ኃሳብ የሰው ልጅን ታሪክ የሚያስተሳስር
ክር ሲሆን እግዚአብሔር ለፍጥረታቱ ያለውን ዓላማ ይገልፃል። በተጨማሪም
የእግዚአብሔርን መልክ በወደቁት ልጆቹ ውስጥ እንደገና መመለስ ላይ በማተኮር
መለኮታዊ መገለጥን ያጠነክራል (ከቆላ. 3፡9፣ 10፣ 1 ዮሐንስ 3፡2 ጋር ያነፃፅሩ)።
የእግዚአብሔር ተልእኮ የእግዚአብሔርን ቃል ማየትና መረዳት እንድንችል
የሚያግዝ መነሻ ሆኖም ሊያገለግል ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስን ስናነብ ሆን ብሎ ወደ
እኛ እየቀረበ ያለውን አምላክ መለየት እንችላለን። በኃጢአት ምክንያት የተፈጠረው
መለያየት እንዳለ ሆኖ (ኢሳ. 59፡2)፣ በተልእኮው ውስጥ እግዚአብሔር “ሁሉንም አዲስ”
እስከሚያደርግበት የክብር ጊዜ ድረስ ከሰው ልጆች ጋር የተበላሸውን ግንኙነት ማደሱን
ይቀጥላል (ራዕ. 21፡5)።
በዚህ ውስጥም እግዚአብሔር ተፈጥሮውን እና አላማውን እንድንረዳው ራሱን
ሊገልጥልን መርጧል፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ ከእርሱ ጋር እውነተኛ እና ዘላቂ ግንኙነት
ሊኖረን ይችላል። በሌላ አነጋገር፣ እርሱን ማወቅ ብቻ ሳይሆን ከእርሱ ጋር ያለንን
ልምምድ፣ ፍቅሩንና ማዳኑን ለሌሎች እናካፍላለን።
ስለዚህ እግዚአብሔር በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ ተልእኮው ምን እንደሆነ
መሠረታዊ ነገሮችን ይሰጠናል።
ለጥቅምት 3 ሰንበት ለመዘጋጀት የዚህን ሳምንት ትምህርት ያጥኑ።
በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ ያለው የእግዚአብሔር ተልእኮ ኢየሱስን ብቸኛው
የመዳኛ መንገድ አድርጎ ከፊት እና ከመሃል ያስቀምጣል። ክርስቶስ ራሱ እንዲህ ሲል
ተናግሯል:- “እኔ መንገድ፣ እውነትና ሕይወት ነኝ። በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም”
(ዮሐንስ 14፡6)። ነገር ግን ኢየሱስ የሥላሴን የተልእኮ ማዕከልነትም እንድንረዳ ይረዳናል።
ክርስቶስ ያደረጋቸው ነገሮች ሁሉ ከሰማይ አባቱ ወይም ለሰማይ አባቱ ነበር
(ዮሐንስ 4:34፤ ዮሐንስ 5:30፤ ዮሐንስ 12:45 ይመልከቱ)። ሆኖም፣ የኢየሱስ ተልእኮ
የጀመረው ወደ ዓለም ሲመጣ እንዳልሆነ ሁልጊዜ ማስታወስ አለብን። ዓለማችን
ሳይፈጠር እንኳ ከአብ ተቀብሎታል (ከኤፌ. 1፡4፣ 1ጴጥ. 1፡20 ጋር ያነፃፅሩ)።
ስለዚህ፣ እግዚአብሔር የምድራችንን መሰረት ከመጣሉ በፊት ለሰው ልጆች
እንዴት እንደሚደርስ አቅዶ ነበር፤ ይህን አላማ ለመፈጸምም ሆን ብሎ በሰው ልጅ ታሪክ
ውስጥ ገባ።
ወልድ ዓለምን ፈጠረ (ዮሐ. 1፡3)። እናም “በዘመኑ ፍጻሜ” (ገላ. 4፡4)
እግዚአብሔር ልጁን ወደዚህ በመላክ ፍቅሩን አሳየን (ዮሐ. 3፡16, 17)። ወልድ መጥቶ
በመስቀል ላይ ሞቶ ሞትን ድል ነሳው። ከዚያም፣ ከአብ የተላከው፣ መንፈስ ወደዚህ
መጣ (ዮሐ. 14፡26፣ ዮሐ. 16፡7)፣ ዓለምን ወቀሰ (ዮሐ. 16፡8-11)። እና ዛሬም የአብንና
የወልድን ተልእኮ በማበረታታትና የእግዚአብሔርን ሕዝብ ለተልእኮው መላኩን
ቀጥሏል (ዮሐንስ 14፡26፤ ዮሐንስ 16፡13፣ 14)።
ዮሐንስ 20:21፣ 22ን ያንብቡ። ተልዕኳችን ከአብ፣ ከወልድ እና ከመንፈስ
ቅዱስ መምጣቱን መረዳታችን ተልእኳችንን እንዴት ሊቀርጽ ይገባል?
ምንም እንኳን “ሥላሴ” የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ባይገኝም በተልእኮ
ላይ ያተኮሩ የሥላሴ ማስረጃዎች ብዙ ናቸው። ለምሳሌ፣ ከትንሣኤ በኋላ ክርስቶስ
ለደቀ መዛሙርቱ ተገልጦ “እነሆም፥ አባቴ የሰጠውን ተስፋ እኔ እልክላችኋለሁ፤ እናንተ
ግን ከላይ ኃይል እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ ቆዩ” አላቸው (ሉቃስ 24፡
49)። እዚህ ላይ የመለኮትን ተልእኮ እውነታ በአንድ አረፍተ ነገር ውስጥ እናገኘዋለን፡
- እነርሱም የአብ የተስፋ ቃል፣ የወልድ የተስፋ ቃል ፍጻሜ ማረጋገጫ እና የተስፋው
ቃል እራሱ የመንፈስ ቅዱስ መምጣት ናቸው (ሉቃስ 3፡16፤ የሐዋርያት ሥራ 1፡4፣ 5፣ 8)
ከዚህ የምንማረው ተልዕኮው የእኛ እንዳልሆነ ነው፤ ተልዕኮው የሥላሴ ነው።
ስለዚህ አይወድቅም።
አብ፣ ወልድ እና መንፈስ ቅዱስ ነፍሳትን በማዳን ሥራ ውስጥ
ይሳተፋሉ። ይህ ሐሳብ ሊያጽናናን የሚገባው ለምንድነው?
ማቴዎስ 28:16-20ን ያንብቡ። በዚህ ክፍል ውስጥ የትኞቹን የደቀ መዝሙርነት ገጽታዎች ማየት እንችላለን?
ማቴዎስ 28፡16-20 በተለምዶ ታላቁ ተልእኮ በመባል የሚታወቀውን መጽሐፍ
ቅዱሳዊ አደራ ያውጃል (ማቴ. 28፡18-20)፣ በዚህም ኢየሱስ ተከታዮቹ እንዲሄዱ
እና ደቀ መዛሙርት እንዲያፈሩ፣ እንዲያስተምሯቸው እና ወደ ህብረት እንዲቀላቀሉ
እንዲያነሳሷቸው አዟል (በተጨማሪ ማርቆስ 16:15-16፤ ሉቃስ 24:44-49፤ ዮሐንስ
20:21-23፤ ሐዋ. ሥራ 1:8ን ይመልከቱ)።
የማቴዎስ 28:16-20ን መሠረታዊ ክፍሎች በአራት ቀላል ነጥቦች ውስጥ ማየት
ይቻላል:- (1) ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ከእርሱ ጋር ለመሆን ወደ ገሊላ እንዲሄዱ አዘዛቸው
(ማቴ. 28:16-17)፤ (2) ኢየሱስ ሥልጣኑንና ሉዓላዊነቱን በማወጅ ወደ እነርሱ መጣ (ማቴ.
28:18)፤ (3) ከዚያም ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ለአንድ የተለየ ተግባር ማለትም ደቀ
መዛሙርት የማፍራቱን (የማድረጉን) ተልዕኮ ሰጣቸው። እና በመጨረሻ፣ (4) ኢየሱስ ከደቀ
መዛሙርቱ ጋር እስከ መጨረሻው እንደሚሆን ቃል ገባላቸው (ማቴ. 28፡20)።
ደቀ መዛሙርት የማድረጉ ሥራ የታላቁ ተልእኮ ዋና ትኩረት እና የተልእኮ ዋና
ተግባር ነው። በመጀመሪያው የግሪክ ቋንቋ የማቴዎስ ወንጌል 28፡19 መጀመሪያ ቃል
በቃል እንዲህ ይላል፣ “ስለዚህ ሄዳችሁ ደቀ መዛሙርት አድርጉ።” “ስለዚህ” የሚለው ቃል
ተልእኮው መሠረት ያደረገው ቀደም ብሎ በተናገረው ማለትም የትንሣኤው ድል ውጤት
በሆኑት በኢየሱስ ኃይል፣ ሥልጣንና ሉዓላዊነት ላይ መሆኑን ይገልፃል (ማቴ. 28:18)።
በታላቁ ተልእኮ ውስጥ ስልጣንን የሚገልፀው ብቸኛው የተግባር ግሥ “ደቀ
መዛሙርት አድርጉ” የሚለው ብቻ መሆኑን ማስመር አስፈላጊ ነው። ሁሉንም ማስተማር፣
ማጥመቅ እና የኢየሱስን ትምህርቶች ለአለም ሁሉ ማካፈል የደቀ መዝሙርነት ባህሪያት ናቸው። እዚህ ላይ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ወደ አንድ ዓላማ እየመራቸው ነው፡- ደቀ
መዛሙርት ወደ ማድረግ። ይህ በእርግጥም በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ ካሉት ታላላቅ
የተልእኮ ምንባቦች አንዱ ነው። የሚያበቃው ኢየሱስ ከተከታዮቹ ጋር ቀጣይነት ባለው
መልኩ እንደሚገኝ በገባው ቃል ኪዳን ነው።
በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ታላቁ ተልእኮ የታሰበው በዚያ ጊዜ ለተሰበሰቡት
የመጀመሪያዎቹ ደቀ መዛሙርት ብቻ አይደለም። ደቀ መዛሙርት የማድረጉን አዲስ
ተልእኮ ለመፈጸም ብቻቸውን ወደ “አሕዛብ ሁሉ” መሄድ አይችሉም። ስለዚህ ተልእኮው
ሁሉን አቀፍ ነው። የኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ ተከታይ ሁሉ ደቀ መዛሙርት በማድረጉ
ሥራ መካፈል አለበት። በተጨማሪም፣ የሚተላለፈው መልእክት ማለትም የኢየሱስ
ክርስቶስ ዘላለማዊ ወንጌል— ያለ ምንም የቦታ፣ ማህበራዊ ወይም የጎሳ ውሱንነቶች
ለዓለም ሁሉ የታሰበ ነው።
ተልእኮው “ደቀ መዛሙርት ማድረግ” ነው። ይህ ጌታችን የሰጠን ኃላፊነት
በአኗኗራችንና ለሌሎች በምናደርገው አገልግሎት ላይ ምን ተጽዕኖ ያሳድራል?
በተጠራንበት ነገር ላይ የበለጠ ለመሳተፍ ምን ማድረግ እንችላለን?
ራእይ 14:6-7ን ያንብቡ። የመጀመሪያው መልአክ ባቀረበው “ዘላለማዊ ወንጌል” ላይ የትኞቹን የአምላክ ተልእኮ ገፅታዎች እንመለከታለን?
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ዘላለማዊ” እና “ወንጌል” የሚሉት ቃላት የተገናኙበት
ብቸኛው ቦታ ይህ ነው። ወንጌል በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ለሁሉም የተሰጠ የጸጋ
ወንጌል ነው። ወደ እኛ ዓለም የመጣው “ጸጋንና እውነትን” (ዮሐንስ 1፡14) ሊያሳየን
ነው። ኃጢአት የሌለበት ሕይወትን ኖረና የኃጢአታችንን እዳ ሊሸከም ምትክ መስዋዕት
ሆኖ በመስቀል ላይ ሞተ (ኢሳ. 53፡4-5፤ 1 ጴጥ. 3፡18)። ከዚያም ተነሥቷል፤ ወደ ሰማይ
ተመልሷል፤ አብ ከፍ አድርጎታል፤ ዛሬ በሰማያዊው መቅደስ ስለ እኛ ይማልዳል (ራዕ.
1:18፣ ሐዋ. 2:33፣ ዕብ. 7:25)። በቅርቡ ታላቁን የተስፋ ቃሉን ይፈጽማል—በግርማና
በክብር ይመለሳል፤ በመጨረሻም ከሺህ ዓመቱ በኋላ የእግዚአብሔርን መንግሥት
በምድር ላይ ለመመስረት ይመጣል (ዮሐ. 14:1-4፣ ሐዋ. ሥራ 1:11፣ ራእይ 21:1-4)።
እነዚህ ሁሉ የዘላለሙ ወንጌል አስፈላጊ እውነታዎች ናቸው።
ቢሆንም፣ ይህ መልእክት ዘላለማዊ መሆኑ አስደናቂ ነው። ሊያድነን የሚችል
አንድ ወንጌል ብቻ ነው። የእግዚአብሔር ተልእኮ ሙሉ በሙሉ እስኪፈጸም ድረስ
እንደዚያው ይቆያል። መቼም ሌላ ወንጌል አይኖርም። አታላይ ትምህርቶች ይመጣሉ
ይሄዳሉ (ኤፌ. 4:14)፣ ነገር ግን የመዳን መልእክት፣ የዘላለም ወንጌል፣ የማይለወጥ ነው፤
እናም አምነው በመታዘዝ የሚኖሩት ዋጋ ያገኛሉ (ዘዳ. 5፡33፣ ሮሜ. 2፡6)።
ለመጀመሪያዎቹ ደቀ መዛሙርት የተሰጠው ተመሳሳይ ተልእኮ ለእኛም ዛሬ
ተሰጥቶናል። በሁሉም ቦታ ሰዎችን ለክርስቶስ ደቀ መዛሙርት የማድረጉን ሥራ መቀጠል
አለብን። ግን ምን ዓይነት ደቀ መዛሙርት? ጥሩ፣ ታማኝ፣ ሙሉ በሙሉ ራሳቸውን
የሰጡ፣ አፍቃሪ ሰዎች? እነዚህ ባህሪያት አስፈላጊ ናቸው፤ ግን በቂ አይደሉም። ሁሉንም
መጽሐፍ ቅዱሳዊ የደቀ መዝሙርነት ባህሪያት የሚያሳዩ ደቀ መዛሙርትን ልናፈራ
ይገባናል (ሉቃስ 9፡23፤ ዮሐ. 13፡34-35፣ 2 ቆሮ. 5፡17)፤ ዋና ዓላማችንም ለጌታችን
ለኢየሱስ ዳግም ምጽአት መዘጋጀትና ሌሎችን ማዘጋጀት ይሁን።
“የፍርዱ ሰዓት መድረስ አዋጅ (ራእ. 14:6-7) የክርስቶስ ዳግም ምጽዓት
እንደቀረበ የሚገልጽ ማስታወቂያ ነው። ይህ አዋጅ ደግሞ ዘላለማዊ ወንጌል ይባላል።
ስለዚህ የክርስቶስን ዳግም ምጽዓት መስበክና በቅርቡ እንደሚመጣ መናገር የወንጌል
መልእክት ዋነኛ ክፍል እንደሆነ ተመልክቷል።”—Ellen G. White፣ Christ’s Object
Lessons፣ ገጽ 227, 228
የፍርዱ ጽንሰ-ሐሳብ በመጀመሪያው መልአክ መልእክት ውስጥ ካለው
“ከዘላለም ወንጌል” ጋር የተገናኘው እንዴት ነው? ወንጌል የፍርድ
ሃሳብ ማዕከል መሆን ያለበት ለምንድነው?
በታሪክ ውስጥ፣ እግዚአብሔር ሁልጊዜ ባህሪውን በታማኝነት የሚወክሉ እና
በታዛዥነት ዓላማውን የሚከተሉ ሰዎች አሉት። የእግዚአብሔር ሰዎች የተጠሩ እና
የጸጋው ተካፋዮች እንዲሆኑ ግብዣውን የተቀበሉ ናቸው። ሁሉም የእግዚአብሔርን
ተልእኮ ለማስፈጸም መሳሪያዎች ነበሩ፤ አሁንም ናቸው።
ዘፍጥረት 12:1-3 እና ዘዳግም 7:6፣11-12ን ያንብቡ። እግዚአብሔር
በብሉይ ኪዳን ለሕዝቡ የነበረው የመጀመሪያ ዓላማ ምን ነበር?
አምላክ ከአብርሃምና ከዘሮቹ ጋር የገባው ቃል ኪዳን የተለየ ዓላማ ነበረው።
የተፈጠሩት፣ የተጠሩት እና የተለዩት የእግዚአብሔር ተልዕኮ ወኪሎች እንዲሆኑ ነበር—
በረከቱን ለአሕዛብ ለማስተላለፍ (ከዘዳ. 28፡10፣ ኢሳ. 49፡6 ጋር ያነፃፅሩ)። ሆኖም
ከእግዚአብሔር ጋር በቃል ኪዳን ግንኙነት ውስጥ የገቡት በእምነት እና በታዛዥነት
ቅድመ ሁኔታ ላይ በመመስረት ነው (ዘፍ. 22:16-18፤ ዘጸ. 19:5-6፤ ዘዳ. 28:1-2፤ 2
ዜና 7፡14)። ይህ በዙሪያ ያሉትን ህዝቦች ወደ እስራኤል የመሳብ ሂደት፣ በብሉይ ኪዳን
የእግዚአብሔር “ተልዕኮ ስልት” ነበር።
በአዲስ ኪዳንም የእግዚአብሔር ተልዕኮ ይቀጥላል። ከሙታን የተነሳው ጌታ እና
አዳኝ አሁን የታደሰ “የተልእኮ ስልትን” አስጀመረ (ማቴ. 28፡18-20፣ ሐዋ. ሥራ 1፡8)።
ያም የክርስቶስ ደቀ መዛሙርትን የያዘችው ቤተ ክርስቲያን ዓለም ወደ እርሷ እንዲመጣ
ከምትጠብቀው ከጥንቷ እስራኤል በተቃራኒ በተልእኮ ወደ ዓለም ሁሉ የምትሄድበት
ነው። ተልእኮው የመነጨው ከቤተ ክርስቲያን አይደለም። በተቃራኒው፣ ቤተ ክርስቲያን
ያለችው እግዚአብሔር አሁንም የሚፈጸም ተልእኮ ስላለውና ቤተ ክርስቲያኒቱን ያንን
ሥራ ለመፈፀም እየተጠቀመባት ስለሆነ ነው።
ሆኖም፣ አንድ ጥያቄ ይቀራል። የቤተ ክርስቲያን ተልእኮ ምንድን ነው? ቤተ ክርስቲያንን
ወደ መኖር ከጠራው ጋር ተመሳሳይ ነው፡- “የሰው ልጅ የጠፉትን ሊፈልግና ሊያድን መጥቶአልና”
(ሉቃስ 19፡10)። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ማናችንም ብንሆን ማንንም ማዳን ባንችልም፣ ሌሎችን
ማዳን ወደሚችለው ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ መጠቆም እንችላለን፤ አለብንም።
“የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ተልዕኮ የሚጠፉ ኃጢአተኞችን ማዳን ነው።
የእግዚአብሔርን ፍቅር ለሰዎች ለማሳወቅና በዚያ ፍቅር ውጤታማነት ለክርስቶስ
ለመማረክ ነው።”—Ellen G. White, Testimonies for the Church, vol. 3, p.
381። እንዴት ያለ ታላቅ ኃላፊነት ነው!
ተልእኮ ለቤተ ክርስቲያን እንደ አየር (እስትንፋስ) ነው። አየር ከሌለን
እንሞታለን። ያለ ተልእኮ ቤተ ክርስቲያን ትሞታለች። የቤተ ክርስቲያናችንን
ሕይወት ለማስቀጠል በግል ምን ማድረግ እንችላለን?
ራእይ 7:9-10ን ያንብቡ። ይህ ጥቅስ ስለ እግዚአብሔር ተልእኮ ሰፊ መልክዓ ምድራዊ ድንበር ምን ይነግረናል?
የዚህ ሳምንት ትምህርት በታላቁ ተልዕኮ ውስጥ ደቀ መዛሙርት የማድረጉን
ማዕከላዊነት እና የዘላለም ወንጌልን መልእክት የሚያጎሉ ሁለት ወሳኝ ጥቅሶችን ዳስሷል።
የሚገርመው፣ ሁለቱም ጥቅሶች ቢያንስ አንድ የጋራ ነጥብ አላቸው፡- የተልእኮው
“ድንበር”። “እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ ደቀ መዛሙርቴ አድርጓቸው” (ማቴ. 28:19)፣
“በምድርም ለሚኖሩ ለሕዝብ፣ ለነገድ፣ ለቋንቋ ሁሉ” (ራእይ 14:6)።
በሌላ አነጋገር፣ የክርስቶስ ወንጌል ለሁሉም አይነት ሰዎች፣ ለሁሉም ቋንቋዎች
እና ህዝቦች መድረስ አለበት። የወንጌል ተጽእኖ የዳኑትን በአንድ ታላቅ ወንድማማችነት
አንድ ሊያደርግ ይገባል። አንድ ምሳሌ ብቻ አለን፤ እርሱም ክርስቶስ ነው። እውነትን
በኢየሱስ ውስጥ እንዳለ ከተቀበልን ብሔራዊ ጭፍን ጥላቻና ምቀኝነት ይፈርሳል፣
የእውነትም መንፈስ ልባችንን አንድ ያደርገዋል።
ኢየሱስ፣ “ምስክሮቼ ትሆናላችሁ” ሲል (የሐዋርያት ሥራ 1:8) በአእምሮው ሦስት
የተለያዩ መልክዓ ምድሮችን እያሰበ ነበር።
ቀጠና 1፡ “ ‘በኢየሩሳሌም ምስክሮቼ ትሆናላችሁ።’ ” በዚያን ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ
ለኢየሩሳሌም በጣም ቅርብ ነበሩ። ስለዚህ፣ ኢየሱስ “እግዚአብሔር ያደረገልዎትን ነገር
ቅርብዎ ለሆኑ ሰዎች ማካፈል ጀምር” እያለ ነው። ተልዕኮው የሚጀምረው ከቤት፣
ከቤተሰብ፣ ከጎረቤትና ከጓደኞች ነው። ይህ ዋናው የተልዕኮ ቦታ ነው።
ቀጠና 2: በመቀጠልም “ ‘በይሁዳና በሰማርያ’ በማለት ተናግሯል። ተልዕኳችን ራቅ
ቢሉም በተወሰነ መልኩ ቅርባችን የሆኑትንም ይነካል። በዚህ ቡድን ውስጥ እኛ የምንናገረውን
ተመሳሳይ ቋንቋ የሚናገሩ ሰዎች አሉ፤ እንደ እኛ አይነት ባህል ያላቸው፣ ግን እኛ የምንናገረውን
ተመሳሳይ እውነታ የማይኖሩ ወይም የማይጋሩ። ይህ የእኛ ተጨማሪ የተልእኮ ቦታ ነው።
ቀጠና 3፡ ከዚህ ባሻገር፣ ክርስቶስ እንዲህ ይላል፡- “‘እስከ ምድር ዳርቻም’”።
የእግዚአብሔር ተልእኮ ከሁሉም ቦታዎች፣ ብሄሮች፣ ህዝቦች፣ ቋንቋዎች እና ጎሳዎች
የተውጣጡ ግለሰቦችን እንድንደርስ ይጠራናል። ይህ የእኛ ዋናው የተልእኮ ቦታ ነው።
ግድድሮሽ፡ በየእለቱ ስለምትኖሩበት ማህበረሰብ ጸልዩ። እግዚአብሔር በእነርሱ
መካከል ያስቀመጠዎት በምክንያት ነው።
በተጨማሪም፡- በአካባቢዎ ያሉትን ሕዝቦች መረጃዎች (በአካባቢዎ ምን ዓይነት
ሰዎች እንደሚኖሩ) ዘር፣ ሃይማኖት፣ ሽማግሌ፣ ወጣት፣ ድሀ፣ ሀብታም፣ የሚናገሩአቸው
ቋንቋዎች ወዘተ አጥኑ። የእርሱን ፍቅር ለእነርሱ የምታደርሱበትን መንገድ እንዲያሳያችሁ
እግዚአብሔርን ጠይቁት።
ለአሕዛብ ሁሉ ምስክር ፡- “‘እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ’ የሚሉ
የአዳኙ ቃላት ለተከታዮቹ ዓለም አቀፋዊ ተልዕኮ መስጠቱን ያመለክታሉ። የፀሀይ ጨረሮች
ወደ ሩቅ የአለም ማዕዘኖች ዘልቀው እንደሚገቡ እግዚአብሔርም የወንጌል ብርሃንን
በምድር ላይ ላለ ነፍስ ሁሉ እንዲደርስ ይፈልጋል። የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን የጌታችንን
ዓላማ የምታከናውን ከሆነ በጨለማ እና በሞት ክልል እና ጥላ ውስጥ ለተቀመጡት
ሁሉ ብርሃን ይፈነጥቃል፤ የቤተ ክርስቲያኒቱ አባላት በአንድነት ከመሰብሰብና ከኃላፊነት
ከመሸሽ ይልቅ ወደ ሁሉም አገሮች በመሄድ የክርስቶስን ብርሃን አብርተው ቢሆን ኖሮ
ይህ ‘የመንግሥት ወንጌል’ በፍጥነት ወደ ዓለም ሁሉ ይዳረስ ነበር።
“ከሀገሮች ሁሉ የመቄዶንያ ጥሪ እየጮኸ ነው፡- “መጥታችሁ እርዱን” እያሉ ነው።
እግዚአብሔር በፊታችን የሥራ መስክ ከፍቶልናል። መላዕክት ከሰዎች ጋር ሲተባበሩ
ነበር። የእግዚአብሔር ምሪት በፊታችን እየሄደ ነው፤ እናም መለኮታዊ ሀይል ከሰው ጥረት
ጋር እየተባበረ ነው። የጌታን ሥራ የማያዩ ዓይኖች ዕውሮች ናቸው፥ የእውነተኛውን እረኛ
ጥሪ የማይሰሙ ጆሮዎች መስማት የተሳናቸው ናቸው። አንዳንዶች የእግዚአብሔርን
ጥሪ ሰምተው ምላሽ ሰጥተዋል። ሕይወት ሰጪውን መልእክት ለማወጅ በመፈለግ
እያንዳንዱ የተቀደሰ ልብ አሁን ምላሽ ይስጥ። ወንዶችና ሴቶች በትህትና እና በታማኝነት
ከእግዚአብሔር የተሰጣቸውን፣ የተሾሙበትን ሥራ ከሠሩ፣ መለኮታዊው ኃይል ብዙዎችን
ወደ እውነት በመመለስ ይገለጣል። የጥረታቸውም ውጤት አስደናቂ ይሆናል።” Ellen G.
White, The Advent Review and Sabbath Herald, November 14, 1912.
1. ቤተ ክርስቲያን በማህበረሰቡ ውስጥ ያላትን ተአማኒነት የሚወስነው የክርስቶስ
አካል የሆንነው እኛ ተልእኮውን ስንፈፅም በራሳችን ህይወት የእግዚአብሔርን ፍቅር
በምንገልጽበት መጠን ነው። ለዚህ ግድድሮሽ እርስዎ በግል ምን ምላሽ ይሰጣሉ?
2. ቤተ ክርስቲያንዎ አድቬንቲስት ባልሆኑ ጎረቤቶቿ የምትታየው እና የምትስተዋለው
እንዴት ነው? ይህን እንዴት ያውቃሉ? ግንዛቤያቸው አዎንታዊ ከሆነ የበለጠ
ለማጠናከር ምን ማድረግ ይችላሉ? አሉታዊ ከሆነ፣ ለመለወጥ ምን ማድረግ ይችላሉ?
3. “ዘላለማዊውን ወንጌል” ለአለም የምናደርገው ተልዕኮ ማእከል አድርጎ መፅናት
በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድነው? ታላቁ ተስፋችን ኢየሱስ በመስቀል ላይ
ባደረገልን ድንቅ ሥራ ላይ ካላማከለ ምን አይነት ተስፋ ልንናገር እንችላለን?