የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ለዚህ ሳምንት ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ - ዘፍ. 3፡9-15፤ ዘፍ. 28፡15፤ ዘፀ. 29፡43፤ 45፤ ማቴ. 1፡18-23፤ ዮሐ. 1፡14-18፤ ዮሐ. 3፡16፤ ዮሐ. 14፡1-3።
የመታሰቢያ ጥቅስ፡- “እግዚአብሔር አምላክም አዳምን ጠርቶ ‘ወዴት ነህ?’ አለው፡፡” (ዘፍ. 3፡9)
ተልዕኮ መነሻውንና አላማውን የሚያገኘው ከእግዚአብሔር ከራሱ ብቻ ነው።
ይህ ተልዕኮ የተጀመረው አብርሃም ሲጠራ ጀምሮ አልነበረም (ዘፍ. 12፡1-4)፤
አልያም ዘጸአት ላይ አልነበረም (ዘፀ. 12፡31-42)፤ ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ
በነበረበት ጊዜም አልነበረም (ማቴ. 1፡18-25)፣ ወይንም በጳውሎስ የወንጌል ሥራ ጉዞ
ላይም አልነበረም (ሐዋ. 13፡4-14፣ 26)። ይህ ተልዕኮ የተጀመረው ከራሱ ከእግዚአብሔር
ዘንድ ነው፤ አጽናፈ አለምን ወደ መኖር ሲያመጣ እና ቆይቶም ሰብአዊ ዘርን ሲፈጥር
አንስቶ ማለት ነው (ዘፍ. 1፡26-27)።
በቅዱስ ቃሉ ውስጥ እግዚአብሔር ወዶና ፈቅዶ ሰዎችን ሲደርስ ወይንም
ከልጆቹ ጋር ለመሆን ሲፈልግ እናያለን። እርሱ አስቀድሞ ከአዳምና ከሄዋን ጋር
ግንኙነትን መስርቷል። ኃጢአት ከገባም በኋላ ተልእኮውን ቀጠለ፤ አሁንም ከሰብአዊ
ዘር ጋር በድጋሚ ግንኙነትን ሊመሰርት ይፈልጋል። በስተመጨረሻም የእግዚአብሔር ተልዕኮ ይፈጸማል (ራዕይ 21-22)። ዘላለማዊውን ወንጌል ለአለም ለማወጅ ሥራ
መነሳሳት ያለብን ከዚህ የተነሣ ነው (ራዕይ 14፡6-7)።
የትኛውም የተልእኮ ጥረት ማዕከል ማድረግ ያለበት ከፈጣሪያችን ጋር ባለን
ግንኙነት እና የተልእኮውን ባህሪና መገለጫ በትክክል መረዳት ላይ ነው። የእግዚአብሔርን
ተልእኮ ከመረዳታችን አስቀድሞ ግን የተልእኮው ጌታ የሆነውን እርሱን መረዳት በጣም
አስፈላጊ ነው።
የዚህን ሳምንት ትምህርት አጥንተው ለመስከረም 26 ሰንበት ይዘጋጁ።
እግዚአብሔር በመልኩና በአምሳሉ ፈጠረን። ፍጹማዊ አለምን ሰጠን፣ የእርሱ
አላማም የነበረው ከእርሱ ጋር ፍጹማዊ ግንኙነት እንዲኖረን፤ ግንኙነቱም በእርሱ የከበረ
ባህሪው ላይ ማዕከል ያደረገ እንዲሆን ነበር፤ እርሱም ፍቅር ነው። ፍቅር እውነተኛ መሆኑ
ይረጋገጥ ዘንድ እግዚአብሔር ሌላ የከበረ ስጦታ ሰጠን፡- ነፃ ፈቃድ--የትኛውን መንገድ
መርጠን መከተል እንዳለብን መምረጥ የመቻል ነጻ ፈቃድ። እርግጥ ነው፣ አለመታዘዝ
ስለሚያመጣቸው አደጋና መጥፎ መዘዞች እግዚአብሔር በግልፅ ለአዳምና ሔዋን
መመሪያ ሰጥቷቸው ነበር (ዘፍ 2፡16-17)። ሰይጣን በምላሹ ሔዋን ክፉውንና በጎውን
ከምታሳውቀው ዛፍ እንድትበላ በማባበል ቀረባት። ይህም ምንም አሉታዊ ውጤት
እንደሌለው አሳመናት። እንዲያውም በተቃራኒው “እንደ እግዚአብሔር እንደሚሆኑና
ክፉውንና በጎውን እንደሚለዩ” ነገራት (ዘፍ 3፤5)። የሚያሳዝነው ግን ሔዋን ፍሬውን
ለመብላት መረጠች፤ ለአዳምም ሰጠችው። እርሱም ተመሳሳይ ምርጫን አደረገ። ፍፁም
የሆነው ተፈጥሮ በኃጢአት ሰበብ ተበላሸ።
ያ ቅፅበታዊ ክስተት እግዚአብሔር አዲስ ሆኖ ለተፈጠረው ምድር አስቀድሞ
የነበረውን ዕቅድ ቀየረ። ከዚህ የተነሣ “አለም ከመፈጠሩ አስቀድሞ” (ኤፌ 1፡4) ተዘጋጅቶ
የነበረው የድነት ተልዕኮ አሁን ተግባራዊ መሆን ነበረበት።
ዘፍ. 3፡9-15ን ያንብቡ። እግዚአብሔር አዳምና ሔዋን ከወደቁ በኋላ
የተናገረው የመጀመሪያ ንግግር ምን ነበር? ያ ንግግር ዛሬም ከስነ
መለኮት አንፃር በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድር ነው?
በእርግጥም እግዚአብሔር የት እንደነበሩ በትክክል ያውቅ ነበር። አዳምና ሔዋን
የሆነውን ነገር በማየት ልባቸው በፍርሃት ራደ። ነገር ግን የኃጢአትን ገዳይነትና አስከፊነት
ፊት ለፊት በመጋፈጥ በደንብ መረዳት ነበረባቸው። ሰይጣንም ደግሞ መሸነፍ ነበረበት።
ስለዚህ እግዚአብሔር ተልዕኮውን፡- የድነት እቅዱን (ዘፍ 3፡14-15 ተመልከቱ)፣ “አለምን
ከራሱ ጋር የማስታረቅን” (2ቆሮ 5፡19) ብቸኛ ተስፋ ማቅረብ ጀመረ። ይህንን ችግር
ከመጋፈጣቸው እና የማስታረቅ ቃል ኪዳን ከመደረጉ አስቀድሞ እግዚአብሔር የወደቀውን
ሰብአዊ ዘር በመፈለግ የመምጣቱ እውነታ ላይ ትኩረት ልናደርግበት ይገባል። በሚታየው
ተስፋ የለሽ ሁኔታ ውስጥም እግዚአብሔር ለአዳም ባነሳው ጥያቄ ውስጥ ሁለት ጉዳዮችን
ነካ፡- ያም ስለ ወደቀው ማንነታችን እና ስለ ሚስዮናዊ ተፈጥሮው ነበር። ሁላችንም የጠፋን
ስለሆንን ድነት ያሻናል። እኛን ለማዳንና ከእኛ ጋር ለመሆን ቆርጦ ፈልጎ ያገኘን እርሱ ነው።
በታሪክ ሁሉ ውስጥ እግዚአብሔር “የት ነህ?” የሚለውን ጥያቄ
መጠየቁን ይቀጥላል። በግል ተሞክሮዎ ይህ ጥያቄ ለእርስዎ ምን
ማለት ነው? ለዚህ ጥያቄ ምን ብለው መለሱ?
ዘፍ 17፡7፤ ዘፍ 26፡3 እና ዘፍ 28፡15ን ያንብቡ። እግዚአብሔር በነዚህ ጥቅሶች ውስጥ ለአብርሃምና ለዘሩ የሰጠው ዋነኛ የቃል ኪዳን ትኩረት ምን ነበር?
በብሉይ ኪዳን ታሪክ እግዚአብሔር የራሱን እቅድ ለማሳካት በተልእኮው ጠባይ
መሰረት መተግበሩን ይቀጥላል። ለምሳሌ ከጥፋት ውኃ በኋላ የባቢሎን ሰዎች ወደ አንድ
ሥፍራ ተሰብስበው ከተማን ለመገንባት እና እስከ ሰማይ የሚደርስ ሰማይ ጠቀስ ህንፃ
ለመገንባት ወሰኑ። እግዚአብሔርም ጣልቃ ገባና በአለም ሁሉ ይበተኑ ዘንድ ለማድረግ
ቋንቋቸውን ደበላለቀ (ዘፍ 11፡1-9)። ከዚያ በኋላ ለመላው ዓለም የበረከቱ መተላለፊያ
መስመር እንዲሆን አብራምን በመጥራት (ኋላ አብርሃም የተባለውን) ተልዕኮውን አሰፋ
(ዘፍ 12፡1-3)። እግዚአብሔር ለአብርሃምና ለዘሩ የገባው ቃል ኪዳን እጥፍ ድርብ ነበር፣
ነገር ግን ከእነዚህ ሁሉ አንዱ ከፍ ብሎ ብቅ አለ። አያሌ ጊዜያት እግዚአብሔር እንዲህ
ብሎ ነግሮአቸው ነበር፡- “አምላካችሁ እሆናለሁ” “ከእናንተ ጋር እሆናለሁ።” “ከእናንተ
ጋር ነኝ” (ዘፍ 17፡7-8፤ ዘፍ 26፤3፤ ዘፍ 28፡1ን ተመልከቱ)።
ታሪክ ወደ ፊት ሲቀጥል ዮሴፍ ወደ ግብጽ የተወሰደ ቢሆንም እዚያ ሆኖ
ለህዝቦቹ መዳን እንደ መሳሪያ ሆኖ አገለገለ። በእያንዳንዱ የዮሴፍ ልምምድ እርምጃ፤
በህይወቱ እጅግ ፈታኝ የሆኑ ክስተቶች በገጠሙት ጊዜ እንኳን፣ “ጌታ እግዚአብሔርም
ከእርሱ ጋር” እንደነበር (ዘፍ 39፡2፣ 21፣ 23) መጽሐፍ ቅዱስ ያረጋግጣል። ከበርካታ
ትውልዶች በኋላ፣ ተልእኮው ይፈፀም ዘንድ፣ ህዝቦቹን ከግብፃውያን ባርነት ነፃ ያወጣ
ዘንድ እግዚአብሔር ሙሴን ወደ ፈርኦን ላከው። በሙሴ ጊዜም ለተልዕኮ ሲጠራው
እግዚአብሔር እንዲህ አለው፡- “እኔ ከአንተ ጋር እሆናለሁ” (ዘፀ 3፡12)። ከጊዜ ወደ ጊዜ
ያህዌ ከህዝቦቹ ጋር ለመሆን ያለውን ጥልቅ ናፍቆት አረጋገጠ።
ዘፀ 29፡43፣ 45ን አንብቡ። ከብሉይ ኪዳን ቤተ መቅደስ ዋና ዓላማዎች ውስጥ
አንዱ የነበረው ምን ነበር? እግዚአብሔር በተለያየ መንገድ ከልጆቹ ጋር አብሮ ለመሆን
ወሰነ። በመጨረሻ የእርሱ ግብ ማስፈጸሚያ የሆነውን ክርስቶስ ኢየሱስን ለማመልከት
አስቦና አቅዶ በሰጣቸው ስርአትና የቤተ መቅደሱ አሰራር አማካኝነት እግዚአብሔር
ከህዝቦቹ ጋር አብሮ ለመሆን ያለውን ናፍቆት ለሙሴ አረጋገጠለት። “የሚቃጠለው
መስዋዕትና የአይሁዳውያን የክህነት ሥራ በሙሉ የተቋቋመው የክርስቶስን ሞትና
የአማላጅነት ሥራ ለመጠቆም ነበር። እነዚህ ሁሉ ስርዓቶች ከክርስቶስ ጋር ካልተገኙ
በቀር ምንም ትርጓሜና መልካምነት የላቸውም።” Ellen G. White, the Advent Re-
view and Herald of the Sabath, December 17, 1872.
በህይወትዎ ውስጥ የእግዚአብሔርን ሀልዎት የተለማመዱት በምን
መንገድ ነው?
ፈጣሪ ባህርዩንና ዓላማውን ለዓለም ማቅረብ ባለባቸው ሰዎች አማካይነት
እንዴት እቅዱን መተግበር እንደጀመረ ብሉይ ኪዳን ያቀርብልናል። እግዚአብሔር
ያደረገው እያንዳንዱ ነገር የተደረገው በተልዕኮው እስትራቴጂ መሰረት ነበር። በነብዩ
ኢሳያስ በኩል እግዚአብሔር እንዲህ አለ፡- “እኔ አምላክ ነኝና፥ ሌላም የለምና የቀድሞውን
የጥንቱን ነገር አስቡ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ እንደ እኔም ያለ ማንም የለም። በመጀመሪያ
መጨረሻውን፥ ከጥንትም ያልተደረገውን እነግራለሁ፤ ምክሬ ትጸናለች ፈቃዴንም ሁሉ
እፈጽማለሁ እላለሁ።” (ኢሳ 46፡9-10)። ነገር ግን በአዲስ ኪዳን ውስጥ እግዚአብሔር
ከሰብአዊ ዘር ጋር ለመሆን ያለው መሻት አዲስ አቅጣጫ ያዘ። በክርስቶስ ሥጋ መልበስ
በኩል በኤደን ገነት ተስፋ ብቻ የነበረው እውነታ (ዘፍ 1፡15)።
ስለ ክርስቶስ ውልደት የተበሰረበትን ታሪክ ከማቴ. 1፡18-23 ላይ ያንብቡ፡
፤ ይህ ነገር ስለ እግዚአብሔር የሚነግረን ምን ጠቃሚ ሀሳብ አለ?
“እግዚአብሔር ከእኛ ጋር።” አማኑኤል። እግዚአብሔር በቤተ መቅደሱ ውስጥ
በሕዝቡ መካከል አድሯል፤ አሁን ደግሞ በናዝሬቱ ኢየሱስ አካላዊ መገኘት አማካኝነት
ከሕዝቡ ጋር ኖረ። በእርግጥም በኢየሱስ ውልደት በኩል እግዚአብሔር በማንነቱና
በተልእኮው አማካይነት በቀጣይነት ከእኛ ጋር ለመሆን ያለውን ፍላጎት ተጨባጭ
በሆኑ መንገዶች አቀረበልን። የእግዚአብሔር ልጅ ሙሉ በሙሉ ሰው እና ሙሉ በሙሉ
መለኮት ሆነ። እንዲህ በሚል ቃልም አረጋገጠልን፡- “መንገድ፣ እውነትና ህይወት እኔ
ነኝ፤ በእኔ ካልሆነ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም” (ዮሐ 14፡6)።
ዮሐ. 1፡14-18ን ያንብቡ። እግዚአብሔር ስለ እኛ ስላለው ተልዕኮ
ከክርስቶስ ስጋ መልበስ ምን መማር ይችላሉ?
እግዚአብሔር ተልዕኮውን ለመፈጸም ወደ ፊት በመንቀሳቀስ በኢየሱስ ክርስቶስ
አማካይነት በልጆቹ መካከል በሥጋ ተገኝቶ ነበር። ኢየሱስ ክርስቶስ ስጋ ለብሶ በልጆቹ
መካከል ከማደሩ የተነሣ እግዚአብሔር ከተልእኮው ጋር ወደ ፊት ተራመደ። “እኛም
ጸጋንና እውነትን ተሞልቶ ከአባቱ ዘንድ የመጣውን የአንድያ ልጁን ክብር አየን።” (ዮሐ
1፡14) በዚህም የብሉይ ኪዳን ትንቢቶችን የፈጸመ ሲሆን በመለኮታዊው ዕቅድ መሰረት
ከእኛ ጋር አንድ ሆነ፣ መለኮት በሰብአዊ ሥጋ ተገለጠ። በዚህም የብሉይ ኪዳንን ትንቢት
ፈፀመ። ከመለኮት እቅድ ጋር በመጣጣም በሰብአዊ ስጋው በኩል አምላክ እኛን ሆነ።
የተልዕኮው አምላክ አላማውን ለመፈጸም ሳያሰልስ እየቀጠለ ነበር።
እግዚአብሔር ለእኛ ያለው ፍቅር እጅግ ትልቅ ከመሆኑ የተነሣ የእኛን ሰብአዊነት
ለብሶ መምጣቱ ምን ማለት እንደሆነ ያስቡ። ለዚህ ፍቅር፣ በተላይ ለሌሎች ካለን ተልዕኮ
አንጻር፣ ምላሽ መስጠት ያለብን እንዴት ነው።
የኢየሱስ ህይወት እና አገልግሎት የእግዚአብሔር የመጨረሻው መገለጥ
ነው። እርሱ ማን እንደሆነ እና ተልዕኮውም ስለ ምን እንደሆነ ለመግለጥ ባለፉት
ዘመናት ከተጠቀመበት ከማንኛውም ሌላ ዘዴ ይልቅ እግዚአብሔር በሶስት ዓመታት
ውስጥ የበለጠ ራሱን መግለጥ ችሏል። ክርስቶስ “በመስቀሉ ደም አማካይነት ሰላምን
በመፍጠር የእግዚአብሔር ሙላት ሁሉ በእርሱ የሆነ…” (ቆላ 1፡15፤ 19-20) ፍጹም
የሆነ “የማይታየው አምላክ ምስል” ነው ። በክርስቶስ በኩል የእግዚአብሔር የተልዕኮው
ማንነት በሙላት ታወቀ። ኢየሱስ ራሱ ስለዚህ ተልዕኮው ሲናገር እንዲህ አለ፡- “የሰው
ልጅ የመጣው የጠፋውን ሊፈልግና ሊያድን ነው” (ሉቃስ 19፡10)።
ዮሐ. 3፡36ን ያንብቡና በጥንቃቄ ሃሳቡን ያሰላስሉ። እዚህ ጋ የእግዚአብሔር
ፍቅር እና ተልእኮ የሚመጋገቡት እንዴት ነው?
በኢየሱስ አገልግሎት ማብቂያ አካባቢ፣ የህይወቱ የመጨረሻ ሳምንት ላይ፣ የሰብአዊ ዘር የመጨረሻ እጣ ፈንታ አጣብቂኝ ውስጥ ገባ። በእነዚያ ቀናቶች የተከናወኑ ክንውኖች ከድሮ ጀምሮ ይጠበቅ የነበረውን ጉዳይ ከወደፊቱ ተስፋ ጋር አቆራኙ። ከግብፃውያን ጭቆና ነፃ መውጣታቸውን ያመለክት በነበረው የፋሲካ በዓል ወቅት ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ስጋን የለበሰው አምላክ፣ ከኃጢአት እስራት ነፃ ሊያወጣን ሕይወቱን አሳልፎ ሰጠ። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ፃፈ፡- “እኛ በእርሱ ሆነን የእግዚአብሔር ጽድቅ እንድንሆን፣ ኃጢአት የሌለበትን እርሱን እግዚአብሔር ስለኛ ኃጢአት አደረገው።” (2ቆሮ 5፤21) ማቴ. 28፤18-20 ያንብቡ። በታላቁ ተልዕኮ ውስጥ የምናገኘው ተስፋ ምንድነው? በእግዚአብሔር ተልዕኮ ውስጥ ስንሳተፍ መተማመኛ የሚያመጣልን እንዴት ነው?
የክርስቶስ ሞት የእርቅ ሂደቱ ማብቂያ ሳይሆን የሂደቱ ክፍል ነበር። ኢየሱስ
በትንሳኤው ኃጢአትን በማሸነፍ “በሰማይና በምድር ያለውን ሥልጣን በሙሉ” (ማቴ
28፡1) ተቀበለ። ከዚህ እውነታ በመነሳት ተከታዮቹ በሙሉ በመላው አለም ሌሎች ደቀ
መዛሙርትን ያፈሩ ዘንድ በመላክ ይህንን አስደናቂ የተስፋ ቃል ሰጣቸው፡- “እስከ ዓለም
ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።” (ማቴ 28፡2 አፅንዖት የተሰጠበት ነበር)።
በተልዕኮው ውስጥ ስትሳተፉ “ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር እሆናለሁ”
የሚለውን የኢየሱስን የተስፋ ቃል በህይወታችሁ ውስጥ እውን ሆኖ
የተመለከታችሁት እንዴት ነው?
ዮሐ. 14፡1-3ን ያንብቡ። በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ ካለው የፍጻሜ ዘመን መልእክት ጋር የተገናኘው በምን መንገድ ነው?
በክርስቶስ የምድራዊ አገልግሎቱ ጊዜ፣ እጅግ ክቡር ከነበሩ የተስፋ ቃሎች መካከል
አንዱ፣ የተባረከው ተስፋ፣ ፈጣሪያችን ዳግም ከኛ ጋር ለዘላለም ለመሆን ያለውን መሻት
በድጋሚ ያንፀባርቃል። ኢየሱስ “ሄጄም ስፍራ ካዘጋጀሁላችሁ በኋላ እኔ ባለሁበት እናንተም
ከእኔ ጋር እንድትሆኑ ልወስዳችሁ ዳግመኛ እመጣለሁ” በማለት አረጋግጧል (ዮሐ 14፡3)።
እንደ ሐዋርያው ዮሐንስ አገላለፅ ይህ የተስፋ ቃል በስተመጨረሻ እውን ይሆናል።
“ደግሞም እንዲህ የሚል ታላቅ ድምፅ ከዙፋኑ ሲወጣ ሰማሁ፣ “እነሆ፤ የእግዚአብሔር
ማደሪያ በሰዎች መካከል ነው፤ እግዚአብሔር ራሱም ከእነርሱ ጋር ይኖራል፣ እነርሱም ህዝቡ
ይሆናሉ፤ እግዚአብሔር ራሱም ከእነርሱ ጋር ይኖራል፤ አምላካቸውም ይሆናል” (ራእ 21፡3)።
“የድነት ሥራ ይፈፀማል። ኃጢአት ሞልቶ በተትረፈረፈበት ስፍራ የእግዚአብሔር
ፀጋ ሞልቶ ይትረፈረፋል። ሰይጣን የራሱ እንደሆነች የቆጠራት ምድር ራስዋ መቤዠትን
ማግኘት ብቻ ሳይሆን ከፍም ትላለች።… የእግዚአብሔር ልጅ ከሰብአዊ ዘር ጋር አብሮ
በሆነበት በዚህ ቦታ፣ የክብር ንጉስ በኖረበት፣ በተሰቃየበት እና በሞተበት በዚህ ስፍራ፣
ሁሉንም ነገር አዲስ በሚያደርግበት ጊዜ የእግዚአብሔር መቅደስ ከሰው ልጆች ጋር
ይሆናል…። የተዋጁት ፍጻሜ ለሌላቸው ዘመናት በእግዚአብሔር ብርሃን ሲራመዱ፣
ሊገለፅ ስለማይችለው ስጦታው--ስለ አማኑኤል፣ “እግዚአብሔር ከኛ ጋር” ስለሆነው
እርሱን ያወድሱታል።” Ellen G. White, The Desire of Ages, p. 26.
እዚህ ጋ የድነትን የተዋበ ምስል እናገኛለን። የተልዕኮው አምላክ በስተመጨረሻ
ከሰው ልጆች ጋር ለዘላለም ለመሆን ያለውን መሻት ይፈጽማል። የዚህ እውነታ አካል
መሆን ምን ያክል አስደማሚ እድል ነው!
ሳምንታዊው ተግዳሮት፡ - በዚህ ሩብ ዓመት በእግዚአብሔር ተልዕኮ ውስጥ ሆነ ብለው
(አስበውበት) እንዲሳተፉ ይጋበዛሉ። ይህ የተልዕኮው አምላክ በእኛ ህይወት ውስጥ በስራ ላይ
እንዳለ እንድናይ እድልን ይሰጠናል። የራሳችሁን ሃሳብ ለማንፀባረቅ ይህን አጋጣሚ በአግባቡ
በመጠቀም በየሳምንቱ የምትማሩትን ትምህርት ለማጋራት ተዘጋጁ። በተጨማሪም ይህ ተግዳሮት
በእግዚአብሔር ተልዕኮ ውስጥ መሳተፋችሁን የበለጠ እንድትጨምሩ ያደፋፍራችኋል።
ተግዳሮት፡ በቀጣዩ ሳምንት በየቀኑ እግዚአብሔር ተልእኮውን እንድትመለከቱ
አይኖቻችሁን ይገልጥ ዘንድ ጸልዩ።
በተጨማሪም፡ በህይወታችሁ አስቀድማችሁ የማታውቁትን ሰው ስም ተማሩ-
-ጎረቤታችሁ፣ የሥራ ባልደረባችሁ፣ ሱቅ ሻጭ፣ የአውቶቡስ ሹፌር፣ ወይንም ፅዳት
ሰራተኛ፣ ወዘተ ሊሆን ይችላል። በየዕለቱም ለእነዚህ ሰዎች ፀልዩላቸው።
“የድነት እቅድ ከአዳም ውድቀት በኋላ የተቀየሰና ከነገሩ መፈፀም
በኋላ የታሰበ አይደለም። “ላለፉት ረጅም ዘመናት ተሰውሮ የነበረው ምስጢር” መገለጥ
ነው (ሮሜ 16፡25)። … ይህ በዘላለማዊው ጊዜ ውስጥ የእግዚአብሔር ዙፋን መሠረት
የሆነውን መርህ መግለጥ ነው። ከጅማሬውም ሰይጣን እምነቱን እንደሚክድና የሰው
ልጆች በከሃዲው ማታለያ እንደሚወድቁ እግዚአብሔርና ክርስቶስ ያውቁ ነበር።
እግዚአብሔር ኃጢአት ይኖር ዘንድ አልፈቀደም ነበር፣ ነገር ግን የኃጢአትን መኖር
አስቀድሞ በመመልከት የሚያመጣውን አሰቃቂ አደጋ ለመመከት መንገድ አዘጋጀ።
ለአለም ያለው ፍቅር ታላቅ ከመሆኑ የተነሳ በርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ህይወት
ይኖረው ዘንድ እንጂ እንዳይጠፋ አንድያ ልጁን አሳልፎ ይሰጥ ዘንድ ቃል ገባ። ዮሐ 3፡16
“ Ellen G. White, The Desire of Ages, p. 22
“ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ ስራቸው ቀላል እንደ ሆነ አልነገራቸውም… ነገር ግን
ብቻቸውን ይታገሉ ዘንድ አልተዋቸውም። ከእነርሱ ጋር አብሮ እንደሚሆን አረጋገጠላቸው፤
በእምነት ወደፊት መራመድ ከፈለጉ ሁሉን ቻይ በሆነው ጥላ ውስጥ መንቀሳቀስ አለባቸው።
ቃሉን እስከታዘዙና ከእርሱ ጋር ተቆራኝተው እስከሰሩ ድረስ ሊወድቁ አይችሉም። ወደ
አለም ሁሉ ሂዱ ብሎ አዘዛቸው። ሰዎች ወደሚኖሩባቸው ሩቅ ስፍራዎች ሳይቀር እንዲሄዱና
እርሱም ከእነርሱ ጋር እንደሚሆን አረጋገጠላቸው። በማንኛውም ጊዜ ስለማልተዋችሁ
በእምነትና በድፍረት ስሩ፤ ስራችሁን እንድታከናውኑ እያገዝኋችሁ፣ እየመራኋችሁ፣
እያጽናናኋችሁ፣ እየቀደስኋችሁ፣ እየጠበቅኋችሁ፣ በምትናገሩት ንግግርም የሌሎችን ሀሳብ
ወደ ሰማይ እንዲያተኩር ታደርጉ ዘንድ እንድትችሉ ስኬትን እየሰጠኋችሁ ሁልጊዜ ከእናንተ
ጋር እሆናለሁ።” Ellen G. White, the Acts of the Apostles, p. 29
1. እግዚአብሔር ለወደቀው ሰብአዊ ዘር ያቀረባቸው የመጀመሪያ ቃላት “ምንድነው
ያደረግከው?” ወይንም “ለምን እኔን አልታዘዝክም?” የሚሉ ሳይሆኑ “ወዴት
ነህ?” ማለቱ ምን ማለት እንደሆነ እስቲ አስቡ። እግዚአብሔር ለእኛ እና እኛ
ለምንወዳቸው ሰዎች በሙሉ ያለውን አላማ በተመለከተ ይህ እውነት እንዴት
አድርጎ ያበረታታናል?
2. እግዚአብሔር እኛን ለማዳን በኢየሱስ ሆኖ ወደ አለም መምጣቱ ምን ማለት
እንደሆኑ አስቡ። በመስቀል ላይ የነበረው ክርስቶስ የእግዚአብሔር የመጨረሻው
የተልእኮ መገለጥ ነፀብራቅ ነው። ይህ ስለ እርሱ ባህሪ ምን ይነግረናል?
3. ተልእኮው የእግዚአብሔር የራሱ ነው። ስለዚህ ለዚህ ተግባር ሕዝብን ያስታጥቃል፣
አቅምም ይሰጣቸዋል። በዚህ እውነታ ብርሃን በኩል በአለም አቀፍ ደረጃ ያለውን
የወንጌል ሂደት ተግዳሮቶች ስንቃኝ ያለመብቃትና የፍርሃት ስሜቶችን መጋፈጥ
የምንችለው፣ እንዴት ነው?