የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

የእግዚአብሔር ተልዕኮ የእኔ ተልዕኮ



4ኛ ሩብ ዓመት 2023



ጥቅምት፣ ህዳር፣ ታህሣሥ 2016 ዓ.ም.

መደበኛ እትም

Sep 30 - Dec 29




አዘጋጅ : የግሎባል ሚሽን ማዕከል ሥራ መሪዎች (ዳይሬክተሮች)

ትርጉም : በረከት ፈለቀ እና ብሩክ ፈለቀ



ይህ የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ የሚዘጋጀው በሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተ ክርስቲያን ዋና መስሪያ ቤት በሆነው በጄኔራል ኮንፍራንስ ውስጥ ሆኖ የጎልማሶች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያን በሚያዘጋጀው ቢሮ ነው። መምሪያዎቹ የሚዘጋጁት የጄኔራል ኮንፍራንስ አስተዳደር ኮሚቴ ንዑስ ኮሚቴ በሆነውና የመጽሐፍ ቅዱስ መምሪያዎችን በሚያሳትመው የሰንበት ትምህርት ሕትመት ቦርድ ነው። የታተመው መምሪያ በውስጡ ዓለም አቀፋዊ የሆነ የምዘና ኮሚቴ ሀሳቦችንና የሰንበት ትምህርት ሕትመት ቦርድን ማረጋገጫ ስለሚያንጸባርቅ የአዘጋጁን (የአዘጋጆችን) ሀሳብ ብቻ የሚወክል አይደለም።

በኢትዮጵያ አድቬንቲስት ማተሚያ ቤት ታተመ
4ኛ ሩብ ዓመት
መስከረም 19-ታህሳስ 19፣ 2016 ዓ.ም

ማውራት አቁሙና አንድ ነገር ማድረግ ጀምሩ!


ከዓመታት በፊት ከአድቬንቲስት መጽሄቶች መካከል አንዱ ላይ ስለ አንድ አሰቃቂ ረግረጋማ ስፍራ (አረንቋ) ታትሞ ነበር። በዚህ በኩል ሰዎች በሚያልፉበት ጊዜ አንዳንዶቹ በዚህ አረንቋ ተይዘው ይቀሩ ነበር። የሞት ጣር ለቅሶአቸውም በአቅራቢያ በሚገኙ ጎረቤቶች ዘንድ ይሰማ ነበር። ነገሩ በጣም አሰቃቂ ነበር።

የአገሩ ህዝብም የመንደር ሸንጎን ሰበሰበ። በእርግጥም አያሌ የመንደሩ ሰዎች ተሰበሰቡ። ለችግሩ መንስኤ ይሆናሉ የተባሉ የተለያዩ ሀሳቦችና ትንታኔዎች እንዲሁም ይሆናሉ የተባሉ አንዳንድ የመፍትሄ ሃሳቦች በፅሁፍ ቀረቡ። ነገር ግን በተደጋጋሚ ከመሰብሰብና ከመወያየት በቀር ምንም የተደረገ ነገር አልነበረም። ለብዙ ዓመታት ውይይቱ ቀጠለ። የተለያዩ ሰዎች ይህንን ርዕሰ ጉዳይ በመጠቀም የመመረቂያ ጽሁፋቸውን ጻፉ። የኮሌጅ መምህራንም በእንግድነት ተጋብዘው ወደዚህ ቦታ እንዲመጡ ተደርገው ነበር። በዚህ ስብሰባ ላይ በመቀመጥ ረጅም ሰዓታትን መስዋዕት ላደረጉ ሰዎች ምግብ ይዘጋጅ ዘንድ የቦታ ሽያጭ ተከናውኖ ገንዘብ ተሰብስቦ ነበር። በስተመጨረሻም የጠፉና እየሞቱ ያሉ ሰዎች ጩኸት እየተካሄዱ ያሉ ውይይቶችን እንዳያደናቅፍ ለማድረግ ድምጽ የማያሰማ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ለመገንባት ገንዘብ ተሰበሰበ። ነገር ግን በችግር ውስጥ የነበሩትን ለመርዳት ማንም ምንም ነገር አላደረገም ነበር። ማንም ሰው በዚህ አረንቋ ውስጥ ተጨማሪ ሰዎች ገብተው እንዳይጠፉ ለማስቆም ምንም ሙከራ አላደረገም ነበር። እንዲሁ ዝም ብለው ያወሩ ነበር።

ቤተ ክርስቲያን በአጠቃላይና የሰንበት ትምህርት የጥናት ቡድናችሁ በተለይ በዚያ መንደር እንዳሉ ሰዎች መሆን የለባችሁም። አብረን የምንጸልይበትን፣ የምናሰላስልበትን፣ የምንነጋገርበትን እና የምንወያይበትን ጊዜ እንወደዋለን። ነገር ግን ከዚህ አልፈን በዙሪያችን ላሉ ሰዎች የሆነ ነገር ለማድረግ ልንናፍቅ ይገባል። በማህበረሰቦቻችን ብሎም በዙሪያችን ባለው ዓለም ልዩነትን መፍጠር ይገባናል። ስራው እንዲያልቅና ኢየሱስም ተመልሶ እንዲመጣ እንሻለን።

የዚህ ሩብ ዓመት የጎልማሶች የሰንበት ትምህርት የመፅሐፍ ቅዱስ ጥናት ትኩረት ያደረገው ወጥተን ሌሎችን ለመድረስ የሆነ ሥራ እንድንሰራ በማድረግ ላይ ነው።

እጅግ አስደማሚ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችን እናጠናለን። አስደናቂ ተሞክሮዎችንና ምሳሌዎችን እናነባለን። ጎረቤቶቻችንን እንድንደርስ የሚያግዙንን (በተለይም ምንም ዓይነት የክርስትና የኋላ ታሪክ የሌላቸውን) የተለያዩ ዋቢ ፅሁፎችን በመጥቀስ እንማራለን። ነገር ግን እነዚህ ነገሮች የተለያዩ መንገዶችን የሚሰጡንና የሚያነቃቁን መንገዶች ብቻ ሊሆኑ ይችላሉ። የእያንዳንዱ ትምህርት እውነተኛው ትኩረትና ልብ የሚገኘው በየሳምንቱ ሃሙስ ላይ በቀረበው ትምህርት ላይ ሲሆን ትምህርቱም ወጥተን የሆነ ተግባር እንድናደርግ የሚገዳደረን ነው።

እናንተ ተግባራዊ ልታደርጓቸው የምትችሉአቸውን ስነ መለኮታዊ ምልከታዎችን በማጋራት ለመስራት የምትጠቀሙባቸውን መንገዶችንና እሳቤዎችን እናጋራችኋለን።

በእያንዳንዱ ትምህርት ሐሙስ ቀን ላይ ደግሞ መሻሻል ስላለበት ነገር ግድድሮሽ/ ጥያቄ እንሰጣችኋለን። ሃሳቡም የሚጀምረው ቀለል ከሚለው ነገር ነው። የሩብ ዓመቱ እየገፋ ሲሄድም የጥያቄዎቹ ክብደት ቀስ በቀስ እየጨመረ ይሄዳል። ግቡ እያንዳንዳችን ግድድሮሹን እንድንወስድ፣ መንፈስ ቅዱስ እንዲመራን እንድንጸልይ፣ የተማርነውን ተግባራዊ እንድናደርግ እና በሚቀጥለው ሰንበት ያለፈው ሳምንት እንዴት እንዳለፈ ለመወያየት ጥቂት ደቂቃዎችን እንድናሳልፍ ነው። ይህ የመመካት ጊዜ ሳይሆን ስላለፈው እና ስላልተሳካው ነገር በጥሩ ሁኔታ የማጋራት ጊዜ መሆን አለበት። ስናጋራ ቡድኑ ሃሳቦችን ያመነጫል። የጸሎት ዝርዝሮች ያድጋሉ (የግልም የጋራም)።

በመጨረሻ፣ ይህ ሩብ ዓመት ሲታወስ እንዲታወሱ የምንፈልገው ያገኘናቸውን መልካም ሀሳቦች፣ አሳታፊ ታሪኮች ወይም ጥልቅ ሥነ-መለኮታዊ ጽንሰ- ሐሳቦች አይደለም። እነዚህ በብዛት ሊኖሩ ይችላሉ። ነገር ግን ይህን ሩብ ዓመት መለስ ብለን ስንመለከተው መንፈስ ቅዱስ የትህትና ጥረታችንን ወስዶ የተልእኮ ተአምራትን ለስሙ ክብር የሰራበት ጊዜ እንዲሆን ምኞታችን ነው።

የግሎባል ሚሽን ማዕከላት በ1980 በጠቅላላ ጉባኤ የተቋቋሙ ሲሆን የሚሠሩት በአድቬንቲስት ሚሽን የጠቅላላ ጉባኤ ጽሕፈት ቤት መሪነት ነው። በአሁኑ ጊዜ ስድስት ማዕከሎች አሉ። ዓላማቸው ቤተ ክርስቲያን አዳዲስ ቡድኖችን በዋና ዋናዎቹ ክርስቲያን ባልሆኑ የዓለም ሕዝቦች መካከል እንድትጀምር መርዳት ነው።

ይህ ጽሑፍ በሚጻፍበት ጊዜ የእነዚህ ማዕከላት ዳይሬክተሮች (ፔትራስ ባሃዱር፣ ሪቻርድ ኤሎፈር፣ ክሌበር ጎንካልቭስ፣ ክሊሞንድ ሻሜሩዲን፣ ዳግ ቬን እና ግሬግ ዊትሴት) ከጋሪ ክራውስ (የአድቬንቲስት ሚሽን ዳይሬክተር)፣ ሆሜር ትሬካርቲን (የአለም አቀፍ የወንጌል ተልዕኮ ማዕከላት ጡረታ የወጣ ዳይሬክተር) እና ጄፍ ስኮጊንስ (የአለም አቀፋዊ ተልእኮ እቅድ ዳይሬክተር) ጋር በመተባበር ይህንን የመጽሐፍ ቅዱስ ማጥኛ አዘጋጅተዋል።

ለበለጠ መረጃ፣ እባክዎ ወደ www.GlobalMissionCenters.org ይሂዱ።




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA Union SSL