የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ለዚህ ሳምንት ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ዳን. 1:1-12፣ ዳንኤል. 6:1-9፣
አስቴር 2:1፣10፣ 20፣ አስቴር 3:1-15፣ አስቴር 4:1-14፣ አስቴር 9:1-12።
መግቢያ ጥቅስ፡- “እስከ ምድር ዳር ድረስ መድኃኒት ትሆን ዘንድ ለአሕዛብ
ብርሃን አድርጌ ሰጥቼሃለሁ” (ኢሳ. 49፡6)።
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከሚገኙት በጣም አበረታች ታሪኮች አንዱ የሆነውና
ስለ “ባህል አቋራጭ አገልግሎት” የሚናገረው ዘገባ በአስቴር መጽሐፍ ውስጥ
ይገኛል። ስለዚህ መጽሐፍ በብዙ ሺህ ዓመታት ውስጥ ተጽፏል፣ እናም እስከ ዛሬ
ድረስ ብዙ አይሁዶች በአስቴር 9፡26-31 መሠረት የፉሪም በዓልን ያከብራሉ።
አስቴር እና አጎቷ መርዶክዮስ በፋርስ ግዛት ዋና ከተማ በሆነችው በሱሳ
ይኖሩ የነበሩ አይሁዶች ነበሩ። ምክንያቱን ባናውቅም ወደ ይሁዳ ከተመለሱት ሌሎች
አይሁዶች በተለየ እነርሱ ከሌሎች ጋር በተማረኩበት ምድር ቀርተው ነበር።
ከዚያም አስቴር በእግዚአብሔር እርዳታ ንግሥት ሆነች። “ንጉሡም ከሴቶች
ሁሉ ይልቅ አስቴርን ወደደ፥ በዓይኑም ከደናግል ሁሉ ይልቅ ሞገስንና መወደድን
አገኘች፤ የመንግሥቱንም ዘውድ በራስዋ ላይ አደረገ፥ በአስጢንም ፋንታ አነገሣት።”
(አስቴር 2፡17)።
አስቴር በተወሰነ መልኩ እያንገራገረችም በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ውስጥ ትልቅ
ሚና መጫወት የቻለችው በዚህ መልኩ ነበር። ይህ ታሪክ በራሱ ልዩ በሆነ መንገድ
በባዕድ አገር የሚኖሩ የአምላክ ሕዝቦች እንዴት ለእውነት መመሥከር እንደሚችሉ
ያሳያል።
ለዚህ ሳምንት ጥናት እንዲረዳዎ ጊዜዎን አመቻችተው የአስቴርን መጽሐፍ
ያንብቡ።
*ለታህሳስ 13 ለሰንበት ለመዘጋጀት የዚህን ሳምንት ትምህርት ያጥኑ።
ወደ ባዕድ ባህል መሰደድ በጭራሽ ቀላል አይደለም። በመጀመሪያ በባቢሎናውያን
ከዚያም በፋርሳውያን ዘመን አይሁዳውያን ያጋጠሟቸውን ሁኔታዎች ለመረዳት ዛሬ
አስቸጋሪ ሊሆንብን ይችላል።
ማናችንም ብንሆን ለምሳሌ የእምነታችን መርሆዎች በተወሰነ ደረጃ የአገሪቱ
ህግ በሆነበት በአድቬንቲስት አገር ውስጥ አንኖርም። ነገር ግን ከመማረካቸው በፊት
የአይሁድ ህዝቦች የእምነታቸው መርሆዎች በሀገሪቱ ህግ ውስጥ በተቀመጡበት በገዛ
አገራቸው ይኖሩ ነበር።
በተወሰነ ደረጃ፣ ለእግዚአብሔር ታማኝ ለመሆን ምን ያህል ቀላል
እንደሚያደርገው ያስቡ። ለመሆኑ የሰባተኛው ቀን ሰንበትን ማክበር በሀገሪቱ ህጎች
ውስጥ ቢቀመጥ የሰባተኛውን ቀን ሰንበት ማክበር ምን ያህል ይቀል ይሆን?
በሌላ በኩል፣ በምድሪቱ ላይ የተደነገገው ህግ ምንም ይሁን ምን፣ ለእምነት
የሚመች ቢሆንም ታማኝነት ከልብ፣ ከውስጥ የመነጨ መሆን አለበት፤ አለዚያ ኃጢአት፣
ክህደትና ጥፋት እንደሚከተሉ ቅዱስ ታሪክ አሳይቶናል።
“ጌታም፦ ይህ ሕዝብ በአፉ ወደ እኔ ይቀርባልና፥ በከንፈሮቹም ያከብረኛል፥ ልቡ
ግን ከእኔ የራቀ ነው፥ በሰዎች ሥርዓትና ትምህርት ብቻ ይፈራኛልና” (ኢሳ. 29፡13)።
በአንጻሩ፣ ታማኝ ለመሆን ቆርጠው ለተነሱ ሰዎች፣ በጣም ምቹ ያልሆነ አካባቢ
እንኳን ከመታዘዝ ሊያግዳቸው አይችልም።
ዳንኤል 1፡1-12፣ ዳንኤል 3፡1-12 እና ዳንኤል 6፡1-9 ያንብቡ። እነዚህ
ዘገባዎች የተለያዩ ሁኔታዎችን ቢናገሩም የአምላክ ሕዝቦች በባዕድ አገር
ሲኖሩ ስለሚያጋጥሟቸው ፈታኝ ሁኔታዎች ምን ይናገራሉ?
ማንም ብንሆን፣ ወይም የትም ብንኖር፣ በተወሰነ ደረጃ በሀገሪቱ ህግ ወይም
በባህል፣ ወይም በሁለቱም እምነታችንን እና ምስክርነታችንን በሚፈትን አካባቢ
ውስጥ እንኖራለን። በዳንኤል ውስጥ የሚገኙት እነዚህ ዘገባዎች ሁልጊዜም “በደስታ”
የሚጠናቀቁ ቢሆኑም ሰዎች አስቸጋሪ በሆኑ ሁኔታዎች ውስጥም እንኳ ቢሆኑ ለአምላክ
ታማኝ ሆነው መቀጠል እንደሚችሉ ያሳያሉ። ከእነዚህ ታሪኮች ውስጥ አንዳቸውም ጥሩ
አጨራረስ ባይኖራቸው እንኳ፣ እነዚህ ሰዎች አሁንም ትክክለኛውን ነገር እንዳደረጉ
ምንም ጥርጥር የለውም።
በእርስዎ ባህል ውስጥ የሚያጋጥሟችሁ አንዳንድ የእምነት ፈተናዎች
ምንድን ናቸው? ለእነሱ ምላሽ የሚሰጡት እንዴት ነው?
ከባቢሎን መውደቅና ከሜዶ ፋርስ መነሳት በኋላ ብዙ አይሁዳውያን ቀስ በቀስ
ወደ ቅድመ አያቶቻቸው ምድር ተመልሰዋል። ግን ሁሉም አልተመለሱም። አንዳንዶቹ
ለዘመናት በኖሩበት ቦታ ቀርተዋል።
ይህንን ዳራ በልቡናችን ይዘን፣ የአስቴርን ታሪክ በተመለከተ ጥቂት አውድ
እናገኛለን። “በዚያም ዘመን ንጉሡ አርጤክስስ በሱሳ ግንብ በነበረው በመንግሥቱ
ዙፋን ላይ ተቀምጦ ሳለ፥” (አስቴር 1፡2)። ትረካው የሚጀምረው የፋርስ መንግሥት
በዚህ ንጉሥ ሥር እየነበረ ነው።
በምዕራፍ 1 ላይ ንግሥቲቱ አስጢን በንጉሡ ዘንድ ሞገስ አጥታለች፣ ይህም
ሌላ ንግሥት እንዲፈልግ አነሳሳው። አስቴር እና አጎቷ መርዶክዮስ ለመጀመሪያ ጊዜ
ወደታሪኩ የገቡት በዚህ አውድ ውስጥ ነበር።
አስቴር 2:1-9ን ያንብቡ። እነዚህ ጥቅሶች ስለ መርዶክዮስና አስቴር
ሁኔታ ምን ያስተምሩናል?
መርዶክዮስ የንጉሡ መኮንን እንደመሆኑ በቤተ መንግሥቱ በር ላይ የሚገኝ እና
በሱሳ ከተማ ከማደጎ ልጁ ወይም ከአጎቱ ልጅ ከአስቴር ጋር ይኖር የነበረ ይመስላል።
ከሥራው ሁኔታ እና ከሚኖሩበት ቦታ አንፃር በፋርስ ባህል ውስጥ ገብተው ነበር። ይህ
ቢያንስ አስቴር ወደ ንጉሱ እንድትቀርብ ከተመረጠችበት ምክንያት አንዱ መሆን አለበት፡
- “አስቴር ወደ ንጉሡ ቤት ወደ ሴቶች ጠባቂው ወደ ሄጌ ተወሰደች” (አስቴር 2፡8)።
አስቴር 2:10፣ 20ን ያንብቡ። እዚህ ምን እየሆነ ነበር? መርዶክዮስ
እንዲህ ያለ ትእዛዝ የሰጣትስ ለምን ነበር?
ጥቅሱ ለምን እንደሆነ በትክክል ባይናገርም ለመገመት አስቸጋሪ አይደለም።
በባዕድ ባህልና ሃይማኖት ውስጥ እንደጠላት እንዳይታዩ ስለቤተሰባቸው እና ስለ
ህዝባቸው ዝም በማለታቸው ጥበበኞች ሆነው ነበር።
ስለ እምነታችን አለመናገር ብልህነት ሊሆን የሚችልባቸውን ምን
ሁኔታዎች ሊያስቡ ይችላሉ? ወይስ መቼም ቢሆን ይህን ማድረግ
የለብንም? ከሌለብንስ ለምን?
በባዕድ አገር እንደመሆናቸው መርዶክዮስና አስቴር ፈጥኖም ይሁን ዘግይቶ
ለአምላክ ታማኝ ሆነው ከኖሩ ችግር ውስጥ ሊወድቁ ይችሉ ነበር። ይህም በመርዶክዮስ
ሁኔታ ታየ።
አስቴር 3:1-15ን ያንብቡ። እዚህ ምን ሆነ እና ለምን?
በአስቴር ምዕራፍ 3 ላይ፣ ንጉሥ አርጤክስስ ሐማን እንዳከበረው እና ታላቅ
ሥልጣን እንደሰጠው እንማራለን። ሁሉም በሃማ ፊት እንዲሰግዱ ተነገራቸው።
“መርዶክዮስ ግን አልተደፋም፥ አልሰገደለትም” (አስቴር 3:2)። መርዶክዮስ በዚህ
ሰው ፊት ያልተንበረከከበትን ምክንያት መጽሐፍ ቅዱስ አይናገርም። ለምን እንደሆነ
ግን እናውቃለን። ታማኝ አይሁዳዊ ነው። መርዶክዮስ ከዘፀአት ጀምሮ የሕዝቡ ጠላት
ለሆነው ለአጋግ ዘር አማሌቃዊ ክብር ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆነም (ዘዳ. 25፡19)። አንድ
ታማኝ አይሁዳዊ በአማሌቃዊ ፊት እንዴት ይንበረከካል? ወይስ ከጌታ በቀር ለማን
ይሰግዳል?
“በንጉሡም በር ያሉት የንጉሡ ባሪያዎች መርዶክዮስን፦ የንጉሡን ትእዛዝ
ለምን ትተላለፋለህ? አሉት።” (አስቴር 3፡3) እንዴት እንደ መለሰ በዝርዝር ባናውቅም፣
የሚቀጥለው ጥቅስ “መርዶክዮስ አይሁዳዊ መሆኑን ነግሮአቸው ነበር” (አስቴር 3፡4)
ይላል። በእርግጥም በዚህ ምላሽ፣ መርዶክዮስ ሰማይንና ምድርን የፈጠረውን አምላክ
አምላኪ እንደመሆኑ መጠን ማንኛውንም ኃጢአተኛ የሰው ልጅ ማምለክ እንደማይችል
ለማስረዳት አጋጣሚ አገኘ። መርዶክዮስ ስለ እምነቱ በተወሰነ ደረጃ መመሥከር ችሎ
እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም፤ ይህን እምነቱን አጥብቆ ከመያዙ የተነሳ ራሱንም ሆነ
ሌሎችን አደጋ ላይ ጣለ።
“ከዳንኤልና ከጓደኞቹ እንዲሁም ከመርዶክዮስ በባቢሎን ንጉሣዊ ፍርድ ቤቶች
የሞራል ጨለማ ውስጥ ደማቅ ብርሃን በራ።”— Ellen G. White፣ Advent Review
and Sabbath Herald፣ May 13, 1884
ሐማ የአይሁድን ሕዝብ ለማጥፋት በፈለገ ጊዜ ስለ እነርሱ የሰጠው መግለጫ
እንዲህ የሚል ነበር:- “አንድ ሕዝብ በአሕዛብ መካከል በመንግሥትህ አገሮች ሁሉ
ተበትነዋል፤ ሕጋቸውም ከሕዝቡ ሁሉ ሕግ የተለየ ነው፥ የንጉሡንም ሕግ አይጠብቁም።”
(አስቴር 3፡8)። ልማዱ የተለየና የንጉሡን ሕግ የማይታዘዝ ሕዝብ? ለማሳደድ የሚመች
መግለጫ ነበር።
አሁንም ቢሆን እንደ መርዶክዮስ ልንፈተን የምንችልባቸው መንገዶች
ምንድን ናቸው? ምንስ ምላሽ መስጠት አለብን?
አስቴር 4:1-14ን ያንብቡ። አስቴር አይሁዳዊት መሆኗን መግለጿ በዚህ ወቅት ተገቢ ሆኖ የተገኘው ለምን ነበር?
መርዶክዮስ አስቴርን እርዳታ በጠየቀ ጊዜ፣ ከአርጤክስስ ጋር ለብዙ ዓመታት
በትዳር ኖራለች፣ ነገር ግን በፋርስ ማንም ሰው ከንጉሡ ጥሪ ሳይደርሰው ወደ ንጉሣዊው
ዙፋን ሊመጣ እንደማይችል የሚገልጽ ሕግ ነበር። ይህንን ህግ የማያከብር ማንኛውም
ሰው ሊገደል ይችላል። አስቴር አደጋውን እያወቀች ሳትጠራ ወደ ንጉሱ ክፍል ሄደች።
መርዶክዮስ በእምነት የአስቴርን እምነት ለመቀስቀስ ፈልገ። የአስቴር መጽሐፍ
ልብ መርዶክዮስ ለአስቴር በላከው ቃል ውስጥ ይገኛል፡- “መርዶክዮስም አክራትዮስን፦
ሂድና ለአስቴር እንዲህ በላት አለው። አንቺ፦ በንጉሥ ቤት ስለ ሆንሁ ከአይሁድ ሁሉ
ይልቅ እድናለሁ ብለሽ በልብሽ አታስቢ። በዚህ ጊዜ ቸል ብትዪ ዕረፍትና መዳን ለአይሁድ
ከሌላ ስፍራ ይሆንላቸዋል፥ አንቺና የአባትሽ ቤት ግን ትጠፋላችሁ፤ ደግሞስ ወደ
መንግሥት የመጣሽው እንደዚህ ላለው ጊዜ እንደ ሆነ ማን ያውቃል?” (አስቴር 4:13 14)።
መርዶክዮስ ለሕዝቧ ያላትን ፍቅር ጥያቄ ውስጥ ሲያስገባ አስቴር እምነቷ
ተፈተነ። ከመርዶክዮስ በቀር አይሁዳዊት መሆኗን የሚያውቅ ማንም አልነበረም፤
እና አንድ ጊዜ በጉዳዩ ውስጥ ለመሳተፍ ከወሰነች በኋላ ህይወቷን አደጋ ላይ ለመጣል
አላመነታችም።
በአምላክ ላይ ያላት እምነት ጠንካራ ነበር፤ እናም ያለ አምላክ እርዳታ ስኬታማ
መሆን እንደማትችል ታውቃለች። ለመርዶክዮስ የሰጠችው መልስ እምነቷን ያሳያል:-
“ሄደህ በሱሳ ያሉትን አይሁድ ሁሉ ሰብስብ፥ ለእኔም ጹሙ ሦስት ቀን ሌሊቱንና ቀኑን
አትብሉም፥ አትጠጡም እኔና ደንገጥሮቼ ደግሞ እንዲሁ እንጾማለን፤ ምንም እንኳ ያለ ሕግ
ቢሆን ወደ ንጉሡ እገባለሁ፤ ብጠፋም እጠፋለሁ።” (አስቴር 4፡16)። መርዶክዮስ ይህንን
መረጃ በሱሳ ላሉ የአይሁድ ማኅበረሰብ ሁሉ ላከ እና እነሱ ሲጾሙና ሲጸልዩ አስቴር
ለአደገኛው ጊዜ እራሷን አዘጋጀች። “በሦስተኛውም ቀን አስቴር ልብሰ መንግሥትዋን
ለብሳ በንጉሡ ቤት ትይዩ በንጉሡ ቤት በውስጠኛው ወለል ቆመች፤ ንጉሡም በቤቱ
መግቢያ ትይዩ በቤተ መንግሥቱ ውስጥ በንጉሡ ዙፋን ላይ ተቀምጦ ንጉሡም ንግሥቲቱ
አስቴር በወለሉ ላይ ቆማ ባየ ጊዜ በዓይኑ ሞገስ አገኘች፤ ንጉሡም በእጁ የነበረውን
የወርቁን ዘንግ ለአስቴር ዘረጋላት፤ አስቴርም ቀርባ የዘንጉን ጫፍ ነካች።” (አስቴር 5:1-2)።
ከላይ እንደተገለጸው በዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ላሉ አይሁዶች ከጾም
ጋር ፀሎት እንዳለ የታወቀ ነው። ማለትም ለራሳቸው ቢሆንም ጸሎት
የእነርሱ ምላሽ ማዕከል ነበር። ከዚህ ምን ግልጽ ትምህርት ልንወስድ
እንችላለን?
ለሺህ ዓመታት የመጽሐፍ ቅዱስ ተንታኞች የአምላክ ስም በአስቴር መጽሐፍ
ውስጥ እንደማይገኝ አስተውለዋል። እንዲህ ያለ ክስተት የሚከሰትበት ብቸኛው
የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ነው። ይሁን እንጂ አይሁዳውያን ለእነርሱ በተደረገላቸው
ታላቅ መዳን የእግዚአብሔርን ድርጊቶች መገንዘብ ስለቻሉ ይህ መጽሐፍ በመጽሐፍ
ቅዱስ ውስጥ እንዲካተት በእግዚአብሔር ሕዝብ ተመርጧል።
በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ውስጥ የእግዚአብሔርን መገኘት አይተናል?
የእግዚአብሔር ድርጊቶች የተለመዱ፣ ተፈጥሯዊ ክስተቶችን ሊመስሉ ይችላሉ፤ እና
ለእነሱ ትኩረት ካልሰጠን የእግዚአብሔርን መገኘት አናስተውልም።
አስቴር 9:1-12ን ያንብቡ። የአስቴር ጥረት ምን ውጤት አስገኘ?
የፉሪም ተአምር በጣም ያልተለመደ መልክ የያዘ ነው። ተአምሩ የተለመዱ
በሚመስሉ ክስተቶች ተደብቋል። አይሁዶችን ለማጥፋት የወጣው ህግ አልተገለበጠም፤
ነገር ግን አዲስ ህግ ተፃፈ፤ ያም ህግ አይሁዶች እራሳቸውን እንዲከላከሉ አስቻላቸው።
በተጨማሪም፣ ሌላ ምን እንደተፈጠረ፣ እና እግዚአብሔር በእነዚህ ክንውኖች
ውስጥ እንዴት ሊሠራ እንደቻለ ያስተውሉ። ፋርሳውያን እግዚአብሔር ለአይሁዶች
ያደረገውን ነገር አስተውለዋል።
ውጤቱስ?
“ከምድር አሕዛብ ብዙ ሰዎች አይሁድ ሆኑ።” (አስቴር 8፡17)። ይህ፣ ጌታ የጠፉ
ነፍሳትን ወደ እርሱ እውቀት ለማምጣት እንዴት እንደሠራ የሚያሳይ ታላቅ ምሳሌ ነው።
የአይሁድ ሕዝብ መሪዎች የእግዚአብሔርን ሥራ ተገነዘቡ። አይሁዶች ራሳቸውን
ለመከላከል መብት ባገኙ ጊዜ የድላቸውን መታሰቢያ እና በዓል ለማክበር (ፉሪም
የሚባል) አመታዊ በዓልን አወጁ። በእነዚህ ቀናት አሁንም እንደ ባህል የእግዚአብሔርን
ማዳን በማሰብ በምስጋና ይውላሉ።
ግድድሮሽ፡ እግዚአብሔር ያደረገላችሁን ነገር በዚህ ሳምንት በጸሎታችሁ
ዝርዝር ውስጥ ላሉት ሰዎች ለማካፈል ድፍረት እንዲሰጣችሁ ጸልዩ።
ከፍ ያለ ግድድሮሽ፡ እግዚአብሔር ለእርስዎ የሚያደርገውን ልዩ ትናንሽ ነገሮች
(ወይም ትልልቅ ነገሮች) የሚመዘግቡበት ማስታወሻ ደብተር ይኑርዎትና መፃፍ ይጀምሩ።
እግዚአብሔር እነዚህን ነገሮች በትክክለኛው ጊዜ ወደ አእምሮዎ እንዲያመጣቸው እና
ለአንድ ሰው ማካፈል እንዲችሉ ይጸልዩ።
“የወንጌል ብርሃን ለፈነጠቀለት ለእያንዳንዱ ቤተሰብና ትምህርት ቤት፣
ወላጅ፣ አስተማሪና ሕፃን ሁሉ እስራኤል በነበረችበት ትልቅ ቀውስ ውስጥ ንግስት አስቴር
የተጠየቀችውና “ደግሞስ ወደ መንግሥት የመጣሽው እንደዚህ ላለው ጊዜ እንደ ሆነ ማን
ያውቃል?’ (አስቴር 4:14) የሚለው ጥያቄ ያስተጋባል።” ኤለን ጂ. ኋይት፣ ስነ ትምህርት፣ 263።
አስቴር የመርዶክዮስ ዘመድ የሆነች ቆንጆ አይሁዳዊት ልጅ ነበረች፣ ወላጆቿ
ከሞቱ በኋላ ወደ ቤቱ ወስዶ እንደ ራሱ ሴት ልጅ ወደዳት። እግዚአብሔር በፋርስ ምድር
ያሉትን የአይሁድ ሕዝብ ለማዳን በእሷ ተጠቅሟል።
“በጥንት ጊዜ ጌታ በተቀደሱ ሴቶች በኩል በሚያስደንቅ መንገድ ሠርቷል፣
ይህም እንደ ተወካዮቹ ሆነው እንዲቆሙ ከመረጣቸው ወንዶች ጋር በመተባበር
ሥራውን አደረጉ። ታላቅ እና ወሳኝ ድሎችን ለማግኘት ሴቶችን ተጠቅሟል። ከአንድ
ጊዜ በላይ፣ በድንገተኛ ጊዜ፣ ወደ ፊት አምጥቷቸው ለብዙ ሕይወት መዳን በእነርሱ
በኩል ተጠቅሟል። በንግሥት አስቴር፣ ጌታ ለሕዝቡ ታላቅ ማዳንን ፈጽሟል። ምንም
ኃይል ሊያድናቸው የማይችል በሚመስልበት ጊዜ አስቴርና ከእርሷ ጋር የነበሩ ሴቶች
በጾምና በጸሎት ፈጣን እርምጃ በመውሰድ በመጋፈጥም ለሕዝባቸው ድነትን አመጡ።
“በብሉይ ኪዳን ዘመን ከመንፈሳዊው ጉዳይ ጋር በተገናኘ የሴቶችን ስራ ማጥናት
ዛሬ በስራው ውስጥ ድንገተኛ ሁኔታዎችን ለመፍታት የሚያስችለንን ትምህርት ይሰጠናል።
በአስቴር ዘመን እንደነበሩት የእግዚአብሔር ሕዝቦች እንደዚህ ባለ ወሳኝ እና ታላቅ ደረጃ ላይ
ላንደርስ እንችላለን፤ ነገር ግን ብዙውን ጊዜ የተለወጡ ሴቶች ይበልጥ ዝቅ ባሉ ቦታዎች ላይ
ጠቃሚ ሚና ሊጫወቱ ይችላሉ። ብዙዎች ይህን ሲያደርጉ ቆይተዋል አሁንም ለማድረግ
ዝግጁ ናቸው።”— Ellen G. White, Daughters of God, pp. 45, 46
1. የአስቴር መጽሐፍ ያልተመለሱ ጥያቄዎችን ይተውልናል፤ በተለይ አስቴር በንጉሥ
ቤተ መንግሥት ውስጥ ስላላት ሚና፣ ምንም እንኳን እሷ ንግሥት ብትሆንም ማለት
ነው። እነዚህን ነገሮች ከእምነቷ ጋር እንዴት እናስታርቃቸዋለን?
2. “ብጠፋም እጠፋለሁ!” (አስቴር 4፡16) የሚሉት ታዋቂ የአስቴር ቃላቶች
በሞት ፊት እንኳን የታማኝነት ምሳሌ ሆነው ለሺህ ዓመታት አስተጋብተዋል። እነዚያ
የእርሷ ቃላት በራእይ 13 ላይ ያሉት ጉዳዮች እውን በሚሆኑበት በመጨረሻው
ዘመን የአምላክ ሕዝቦች የሚያጋጥሟቸውን ነገሮች የሚያንጸባርቁት እንዴት ነው?
3. በክፍልዎ ውስጥ በሰኞ ጥናቱ መጨረሻ ላይ, አንዳንድ ጊዜ እምነታችንን ስለ
አለመግለጽ የተጠየቀውን ጥያቄ ይመልከቱ። እኛ እንደዚህ አይነት ሁኔታ ውስጥ
ልንሆን የሚገባን ጊዜ አለ?