የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ለዚህ ሳምንት ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ። 1 ነገሥት 11፡1-6፤ ማቴ. 4:23-25፤ ማቴ. 15:22-28፤ ማርቆስ 7:24-30፤የሐዋ. ሥራ 10:34-35፤ ማቴ. 8፡10።
መግቢያ ጥቅስ፡- “በዚያን ጊዜ ኢየሱስ መልሶ፦ አንቺ ሴት፥ እምነትሽ ታላቅ
ነው፤ እንደወደድሽ ይሁንልሽ አላት። ልጅዋም ከዚያች ሰዓት ጀምሮ ዳነች።”
(ማቴዎስ 15:28)።
ከመጀመሪያው፣ የጠፉትን ልጆቹን የፈለገው ይህ አፍቃሪ አምላክ ነው (ዘፍ. 3:9)፤
ይህ አፍቃሪ አምላክ አሁንም በከተሞች ውስጥም ጭምር የጠፉትን ለመድረስ
እየፈለገ ነው (ራዕ. 14፡6-12 ይመልከቱ)። እ.ኤ.አ. በ2018 የተባበሩት መንግስታት
የቅርብ ግኝቱን ያሳተመ ሲሆን በዚህም 55 በመቶው የፕላኔቷ ህዝብ በከተሞች ውስጥ
እንደሚኖር እና ይህም በ2050 ወደ 68 በመቶ እንደሚያድግ ይተነብያል (እስከዛ
የምንቆይ ከሆነ)። ሌላ ምንም አማራጭ የለንም፤ በከተሞች ውስጥ ላሉት መመስከር
አለብን።
ሆኖም ብዙዎቹ የእግዚአብሔር ሰዎች ዮናስ ለአንድ ከተማ እንዲመሰክር
በተጠራ ጊዜ እንዳደረገው ያደርጋሉ፡- ሰበብ በማስቀመጥ ራሳቸውን ከሥራው ገሸሽ
ያደርጋሉ። “በመጽናትና መጻሕፍት በሚሰጡት መጽናናት ተስፋ ይሆንልን ዘንድ
አስቀድሞ የተጻፈው ሁሉ ለትምህርታችን ተጽፎአል።” (ሮሜ. 15:4) ይህም ስለ ዮናስ
የተጻፈውን ይጨምራል።
በዚህ ምድር በነበረበት ጊዜ ኢየሱስ በእስራኤል ከተሞች ያሉትን ብቻ ሳይሆን
በባዕድ አገር ያሉትንም አገልግሏል። ማለትም ከተመረጡት ከአይሁድ ሕዝብ ውጭ
የሆኑትንም ሰዎች አገልግሏል።
በዚህ ሳምንት ወደ ጢሮስ እና ሲዶና ክርስቶስን ስለነበረው ተልእኮ የሚናገረውን
የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ በማጥናት ዛሬ በህይወታችን ላይ ተግባራዊ ለማድረግ
የምንችላቸውን ትምህርቶችን እንቀስማለን።
*ለታህሳስ 6 ሰንበት ለመዘጋጀት የዚህን ሳምንት ትምህርት ያጥኑ።
ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ከጌንሴሬጥ ወጥተው (ማቴ. 14፡34) “ወደ ጢሮስና
ወደ ሲዶና አገር” (ማቴ. 15፡21) እንደሄዱ እናነባለን። ከገሊላ ወደ እነዚህ አረማዊ ቦታዎች
የወሰዳቸው ለምንድነው? ደቀ መዛሙርቱን በገሊላ በቀላሉ ሊማሩት ያልቻሉትን በሌላ
ስፍራ እንዲማሩ በዚህ የመስክ ጉዞ ወደ እነዚህ የውጭ አገር ድንበሮች መርቷቸዋል።
ደቀመዛሙርቱን የከተማ ሰዎችን ጨምሮ ለሁሉም ሰዎች እንዲደርሱ የሚጠይቀውን
ጥሪ እንዲፈፅሙ ለማዘጋጀት የሚያግዙ ትምህርቶችን ማስተማር ፈልጎ ነበር።
መሳፍንት 3:1-6፣ 1 ነገሥት 5:1-12፣ እና 1 ነገሥት 11:1-6ን ያንብቡ።
እነዚህ ጽሑፎች የእነዚህን ከተሞች የኋላ ታሪክ ትንሽ እንድንረዳ
የሚረዱን እንዴት ነው?
መሳፍንት 3፡1-6 ላይ እነዚህ የጥንት ህዝቦች እግዚአብሔር የእስራኤላውያንን
እምነት ለመፈተሽ እንደተጠቀመባቸው እንመለከታለን። እንደ አለመታደል
ሆኖ፣ የእግዚአብሔር ሰዎች ቢያንስ በዚህ ታሪክ ያንን ፈተና ወድቀዋል ፡- “ሴት
ልጆቻቸውንም አገቡአቸው፥ እነርሱም ሴቶች ልጆቻቸውን ለወንዶች ልጆቻቸው
ሰጡ፥ አማልክቶቻቸውንም አመለኩ።” (መሳ. 3፡6)። ስለዚህ፣ ገና ከጅምሩ፣ እነዚህ
ሰዎች ለእስራኤል እንቅፋት ነበሩ።
በ1ኛ ነገሥት 5፡1-11 ላይ በሲዶናውያን እና በዕብራውያን መካከል ያለውን የጠበቀ
ግንኙነት ማየት እንችላለን። ምንም እንኳን በአንድ ደረጃ፣ ኢኮኖሚያዊ ትስስሩ ለጋራ
ጥቅም ቢሆንም፣ ዕብራውያኑ አሁንም በንግድ አጋሮቻቸው ጣዖት አምልኮ አሉታዊ
ተጽዕኖ እንደደረሰባቸው ምንም ጥርጥር የለውም።
1ኛ ነገሥት 11፡1-6 ላይ ይህ ተጽእኖ በመጨረሻ ምን ያህል አሉታዊ እንደነበረ
ይገልፅልናል፡- ንጉሥ ሰሎሞን የሲዶናዊቷን ልዕልት አገባ፣ እርሷም አሳተችው።
“ሰሎሞንም የሲዶናውያንን አምላክ አስታሮትን፥ የአሞናውያንንም ርኵሰት ሚልኮምን፥
ተከተለ” (1ኛ ነገ. 11፡5)።
የጣዖት አምልኳቸውና አረማዊነታቸው በተመረጠው ህዝብ ላይ አሉታዊ
ተጽእኖውን ያሳረፈ ቢሆንም ኢየሱስ አሁንም ደቀ መዛሙርቱን ወደ እነዚህ ቦታዎች
አምጥቷቸዋል። አድሏዊነታቸውን እና ጭፍን ጥላቻቸውን በመጋፈጥ ድንበር ዘለል የሆነውን
የከተማ የወንጌል ሥራ ተልዕኮን አስጀምሯቸዋል፤ በዚህም ለተከታዮቹ ለሁሉም ባህሎች
እና ብሄረሰቦች ገጣሚ የሆነ የተሟላ የከተማ የወንጌል ሥራ ተልእኮ ሞዴልን አስቀምጧል።
የአድቬንቲስት የከተማ የወንጌል ሥራ አገልጋዮችን ብዙ ተግዳሮቶች
ያጋጥሟቸዋል፣ ከእነዚህም መካከል የጤና እና የአካባቢ ጉዳዮችን ይገኙበታል። ሌሎች
ደግሞ የኑሮ ውድነት፣ ዘረኝነት፣ ጭፍን ጥላቻ፣ ብሔርተኝነት እና የእምነት ነፃነት እና
ሃሳብን የመግለጽ ገደቦች ናቸው። እነዚህ እንቅፋቶች ቢኖሩም ለከተሞች መስራት አለብን።
በከተማ የወንጌል ሥራ አገልግሎት የሚሳተፉትን ለመርዳት እርስዎ
ምን ማድረግ ይችላሉ?
ምንም እንኳን ውጫዊ እና ውስጣዊ ፈተናዎች ቢኖሩም፣ ኢየሱስ ለከተሞች ለሚሰጠው ተልዕኮ ጥሪውን በጸጋ አቀረበልን።
ማቴዎስ 9:35–38ን ያንብቡ። ባገኘንባቸው ቦታዎች ሁሉ ይህ ስለ ብዙሃኑ ተልእኮ ምን ያስተምረናል?
ኢየሱስ በከተሞች ውስጥ ላሉት ለብዙ ሰዎች ርኅራኄ አሳይቷል። ኢየሱስ ስለ ኢየሩሳሌም እንዴት እንዳለቀሰ ሉቃስ 19፡41 ይገልጻል።
ኢየሱስ ለልጆቹ፣ በከተሞች ለሚኖሩ "ፊት ለሌላቸው ብዙሃን" እንኳን ያለውን የፍቅር ጥልቀት ላንረዳ እንችል ይሆናል። ለዚህም ነው በማቴዎስ 9፡38 ላይ ኢየሱስ
አነሳሳችን እና ልባችን የእርሱን እንዲመስል እንድንጸልይ የሚነግረን።
ማቴዎስ 4:23–25ን ያንብቡ። ኢየሱስ አገልግሎቱን ሲጀምር ሕዝቡ ከየትኞቹ መልክዓ ምድራዊ ቦታዎች ይመጡ ነበር?
በማቴዎስ 4:25፣ ኢየሱስን የተከተሉት ብዙ ሰዎች ከገሊላ፣ ከአሥሩ የዲካፖሊስ ከተሞች በምስራቅ፣ ከኢየሩሳሌም፣ እና ከይሁዳ ወደ ደቡብ ይመጡ ነበር።
ከሰማርያ በተጨማሪ የቀሩት የትኞቹ ክልሎች ናችው? የፊንቄ ክፍል የሆነው የጢሮስና የሲዶና የባሕር ዳርቻ በሜድትራንያን ባሕር እና ከገሊላ በስተ ሰሜን ምዕራብን ያካትታል።
ኢየሱስ ለምን ወደዚህ አካባቢ እንደሄደ እንለመለከታለን። ይህ የጢሮስ እና የሲዶና ክልል ጉዞ ከኢየሱስ ባህላዊ ተልእኮ ጉዞዎች ውስጥ አንዱ ነው።
“ከፈሪሳውያን ጋር ከተገናኘ በኋላ፣ ኢየሱስ ከቅፍርናሆም ወጥቶ ገሊላን ተሻግሮ በፊንቄ ድንበር ላይ እስከ ተራራማው አገር ድረስ ዘለቀ።
ወደ ምዕራብ ሲመለከት የጥንቶቹ የጢሮስና የሲዶና ከተሞች፣ የአረማውያን ቤተ መቅደሶቻቸው፣ ግርማ ሞገስ የተላበሱ ቤተመቅደሶቻቸውና የንግድ ገበያዎቻቸው
እንዲሁም በመርከብ የተሞሉትን ወደቦች ተዘርግተው ማየት ችሏል።”—Ellen G. White፣ የዘመናት ምኞት፣ ገጽ. 399.
የሰዎች "ዕጹብ ድንቅ የሆኑት ቤተ መንግሥቶቻቸውና የንግድ ሥራዎቻቸው" ምን ያህል ከንቱ እንደሆኑ እንዲያዩ መርዳት የምንችለው እንዴት ነው? ኢየሱስ የሚያስፈልጋቸውስ ለምንድን ነው?
የመጽሐፍ ቅዱስ ሊቃውንት የማቴዎስ ወንጌል በተለይ ለአይሁድ አንባብያን
የተጻፈ እና የማርቆስ ወንጌል ደግሞ የተጻፈው በዋነኝነት የአሕዛብ ተደራሲያንን በማሰብ
ነው ብለው ያምናሉ። የወንጌል መልዕክቶችን ስናጠና ይህን ልዩነት ማወቅ ጠቃሚ ነው።
ማቴዎስ 15፡22-28ን እና ማርቆስ 7፡24-30ን ያንብቡ። ይህቺ ሴት
ከተገለፀችባቸው መገለጫዎች አንፃር ምን ልዩነቶችን ታያላችሁ?
ማቴዎስ ይህችን እናት ዜግነቷን እና ዘሯን በመጠቀም እንዴት እንደ ገለጻት
ልብ ይበሉ፡ ከነዓናዊት። ማርቆስ ይህችን እናት “ግሪካዊት” ወይም “አሕዛብ” በማለት
ተጨማሪ ቃላትን እንዲጠቀም በመንፈስ ቅዱስ ተመራ ከዚያም ተጨማሪ ማብራሪያን
እንዲህ ይሰጣል፡- “በትውልድ ሲሮፊኒቃዊት” ወይም “የፊንቄ ሶርያዊት” - ይህ ቃል
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ጥቅም ላይ የዋለው እዚህ ስፍራ ላይ ብቻ ነው።
ይህ በማቴዎስ 15 ላይ ያለው ታሪክ የኋላ ታሪካቸውን እና ስለዓለም ያላቸውን
አተያይ ከግምት ውስጥ በማስገባት የመጀመሪያዎቹ ተደራሲያን ላይ እንዴት ተጽእኖ
እንደፈጠረባቸው ያስቡ። የማቴዎስ አንባቢዎች ይህቺን እናት እንደ ተናቀች አረማዊ
አድርገው ይመለከቷታል። ይህ የመጣው የአይሁድ ሕዝብ ከነዓናውያን እንደ ጣዖት
አምላኪ ሕዝብ ቡድን ከነሱ ጋር ካላቸው ታሪካዊ ልምድ ሲሆን ክፉ አኗኗራቸውና
ልማዳቸው ለሕዝባቸው ለረጅም ጊዜ እንቅፋት ሆኖባቸው ስለቆየ ነበር። የክርስቶስ
ደቀ መዛሙርት እንኳ ይህች ሴት እምነት ሊኖራትና የአምላክ መንግሥት አካል ልትሆን
እንደምትችል አላሰቡም ነበር!
በማርቆስ 7፣ የማርቆስ ተደራሲያን ከማቴዎስ አንባብያን ምላሽ የተለየ ምላሽ
ይኖራቸዋል። አህዛብ የነበሩት ሰዎች አይሁዶች ለከነዓናውያን እንዳነበራቸው አይነት
አመለካከት አልነበራቸውም። ይልቁንም አሕዛብ ይህቺን ሴት የሚያውቁት፣ “ግሪካዊና፣
በትውልዷ ሲሮ-ፊንቄያዊት” መሆንዋን ነው። ኢየሱስ ከእነርሱ ውስጥ አንዱን ፈወሰ!
ለአህዛብ፣ ይህች ሴት ዘርዋ እና የኋላ ታሪኳ ምንም ይሁን ምን የልጇ እጣ ፈንታ
ያሳሰባት፣ ጌታ እንዲፈውስላት የምትፈልግ ተወዳጅ እናት ነች።
“ክርስቶስ ለሴቲቱ ጥያቄ ወዲያውኑ ምላሽ አልሰጠም። ይህቺን የተናቀ ዘር
ተወካይ ሴት አይሁዶች በሚያዩበት አይን ተቀበላት። እርሱ እንደዚያ ያደረገው
አይሁዳውያን እንዲህ ዓይነቱ ጉዳይ ሲገጥማቸው በቀዘቀዘና ልባዊ ባልሆነ መንገድ
እንደሚያስተናግዱ ለደቀመዛሙርቱ ለማሳየት ሲሆን እነርሱ ተመሳሳይ ነገር ሲገጥማቸው
እርሱ በኋላ እንዳደረገው ማለትም ልመናዋን አይቶ እንደራራላትና የፈለገችውን እንደሰጣት
እንዲያደርጉ ፈልጎ ነው።” —Ellen G. White፣ The Desire of Ages፣ ገጽ. 400.
1 ዮሐንስ 2:2ን ያንብቡ። በእግዚአብሔር ፊት ሁላችንም አንድ
እንደሆንን ይህ ጥቅስ ምን ይነግረናል?
በወንጌል ባልተደረሱት ከተሞች ሰፈር ውስጥ ብዙ ተስፋን የሚናፍቁ ሰዎች
አሉ። በክርስቶስ ዘመን የነበሩ የአምላክ ሕዝቦች እንደ ጢሮስና ሲዶና ላሉ የባዕድ አገር
ከተሞች የመሲሑን ተስፋ እንዳያመጡ ያደረጋቸው ምንድን ነበር? የአምላክ ሕዝቦች
በመጀመሪያው ምጽአት የተነገረውን ትንቢት ተስፋ የሚናፍቁትን ጎረቤቶች እንዳያዩ
ብሔረተኝነት፣ ኩራት እና ጭፍን ጥላቻ አሳወሯቸው። ዛሬ በከተሞች ውስጥ፣ ኢየሱስ
ክርስቶስ ህዝቡ የዳግም ምጽአቱን “የተባረከ ተስፋ” እንዲካፈሉ የሚፈልጋቸው ብዙ
ወገኖች አሉ (ቲቶ 2፡13)። ኢየሱስ ዜግነታቸው ወይም ዘራቸው ምን እንደሆነ ግድ
እንደማይሰጠው ሁሉ እኛም ልክ እንዲሁ ልንሆን ይገባናል።
የሐዋ. ሥራ 10:9-16፣28፣34-35ን ያንብቡ። በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት
የተሰጠንን ትምህርት እንዴት ጠቅለል አድርጋችሁ ትገልፁታላችሁ?
ጴጥሮስ ምሳ ለመብላት እየተጠባበቀ ሳለ በምግብ ጠረጴዛው ልብስ ላይ ንጹሕ
ያልሆኑ እንስሳትና አእዋፋትን የሚያሳይ ራእይ ታየው። በዚህ ራእይ ውስጥ ሦስት ጊዜ
ተነስቶ እንዲበላ ተነገረው። እግዚአብሔር የጴጥሮስን ሃይማኖታዊ ኩራት እና በአሕዛብ ላይ
ያለውን ጭፍን ጥላቻ ለመጋፈጥ እነዚህን ራእዮች ተጠቅሟል። ከጊዜ በኋላ ጴጥሮስ ይህን
እውነት ተረዳ:- “ከዚያም ጴጥሮስ አፉን ከፍቶ እንዲህ አለ:- “ጴጥሮስም አፉን ከፍቶ እንዲህ
አለ፦ እግዚአብሔር ለሰው ፊት እንዳያደላ ነገር ግን በአሕዛብ ሁሉ እርሱን የሚፈራና ጽድቅን
የሚያደርግ በእርሱ የተወደደ እንደ ሆነ በእውነት አስተዋልሁ።” (የሐዋ.ሥራ 10:34-35)
ከዚህ ዳራ በመነሳት ከጢሮስ እና ከሲዶና ታሪኮች ስለምናገኛቸው ትምህርቶች
እስቲ እናስብ። ኢየሱስ ከእናቲቱ ጋር ያደረገውን ንግግር እንደገና ይመልከቱ። ደቀ
መዛሙርቱ ከዚህ የመስክ ጉዞ ከጴጥሮስ ራእይ ጋር በተያያዘ ምን ትምህርት አግኝተዋል?
እነዚህን ዛሬ በህይወታችን እና ክርስቶስ ከተሞችን በወንጌል ለመድረስ በሰጠን ተልዕኮ
ውስጥ ተግባራዊ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? የከተማ ነዋሪዎችን ፍላጎት እንዳናይ
ምን አይነት አድሎአዊነት ከልክሎን ይሆን?—የተልእኮአችንን ግንዛቤ ለማስፋት፣
እንዲሁም ጭፍን ጥላቻን፣ ብሄረተኝነትን፣ እና መንፈሳዊ ኩራታችንን ለመጋፈጥ እንችል
ዘንድ እግዚአብሔር በከተሞች ውስጥ ምን እድሎችን ሰጥቶናል?
ኢየሱስ ገና ሙሉ በሙሉ ላልተረዱት ደቀ መዛሙርት የእግዚአብሔር ታላቅ
የማዳን ዕቅድ ለአንድ ብሔር ወይም ዘር ብቻ ሳይሆን ለመላው የሰው ልጅ ቤተሰብ
መሆኑን በትዕግስት አስተማራቸው። የከተሞች ተልእኳችንን ለማጠናቀቅ መንፈስ
ቅዱስ ጭፍን ጥላቻን እና አድሎአዊነታችንን እንድናሸንፍ ሊረዳን ይችላል።
ገላትያ 2፡11-13 ያንብቡ። ከልጅነታችን ጀምሮ የተማርነውን ጭፍን
ጥላቻ ማስወገድ ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ይህ ምን ያስተምረናል?
በሉቃስ 18፡8፣ ኢየሱስ ይህንን ጥያቄ በአንድ ምሳሌው መጨረሻ ላይ ጠየቀ፡
- “ነገር ግን የሰው ልጅ በመጣ ጊዜ በምድር እምነትን ያገኝ ይሆንን?”። በዛሬ ጊዜ ያለን
የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እንደመሆናችን መጠን ኢየሱስ የሚፈልገውን ነገር ማየት
አለብን። በዚህ ታሪክ ውስጥ፣ ኢየሱስ በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ የሚያበራ እምነትን
እየፈለገ እንደሆነ እንመለከታለን።
ማቴዎስ 8:10፣ 13ን፣ ማቴዎስ 9:2፤ ማቴዎስ 20:29-34፤ማርቆስ
2:5፣ ማርቆስ 10:46-52፣እና ሉቃስ 18፡35-43ን ያንብቡ። በእነዚህ
ምንባቦች ውስጥ፣ ኢየሱስ እምነት እንዳለው የገለጸው ማንን ነው?
ይህ ዝርዝር ጨለማ በሆኑ ከተሞች ውስጥ እንኳን የሚያበሩ እምነት ያላቸውን
ሰዎች ያካትታል። በቅፍርናሆም ኢየሱስ እምነት ያላቸውን በርካታ ሰዎች ጎላ አድርጎ
ገልጿል። በማቴዎስ 8፡10፤13 ላይ፣ የተለወጠውን አረማዊ መቶ አለቃ ታላቅ እምነት ይዞ
እናየዋለን። ሽባ የሆነውን ጓደኛቸውን ወደ ኢየሱስ ለማምጣት ጣራውን የቀደዱ አራት
በእምነት የተሞሉ ወዳጆችን አግኝተናል (ማቴ. 9፡2፣ ማር. 2፡5)። በማርቆስ 10፣ ኢያሪኮ
ውስጥ እምነቱ የሚያበራውን የቀድሞውን ዓይነ ስውር በርጤሜዎስን አገኘነው።
በተመሳሳይም በአምላክ ሕዝቦች መካከል ታላቅ እምነት እንደሚኖር
እንጠብቃለን። ሆኖም በኢየሱስ የትውልድ ከተማ በሆነችው በናዝሬት፣ እምነት
ማነስ ወይም ደግሞ ፍጹም አለማመን የክርስቶስን አገልግሎት ገድቦት ነበር። በደቀ
መዛሙርቱ መካከል፣ ኢየሱስ ስለ እስራኤል “እናንተ እምነት የጎደላችሁ!” በማለት ብዙ
ጊዜ ተናግሯል፣ (ማቴ. 6:30፣ ማቴ. 8:26፣ ማቴ. 14:31፣ ማቴ. 16:8 ) በማቴዎስ 17፡17
ላይ ደግሞ ኢየሱስ “የማታምን ጠማማ ትውልድ ሆይ” ብሎ ጮኋል!
ዛሬ ልንወስድ የሚገባን ትምህርት ቢኖር እምነት ባልተጠበቁ ቦታዎች ማለትም
በባዕድ አገር ሰዎች፣ ጣዖት አምላኪዎችና የተለያየ ሃይማኖት ባላቸው ሰዎች መካከል
በሚገኙ ከተሞች ውስጥ እንደሚገኝ ነው። በትሕትና፣ ኢየሱስ እንዳደረገው ወደ
ከተማዎች ሄደን እውነቱን ሲሰሙ በኢየሱስ ላይ የሚያምኑትን መሻት አለብን። እና
እነሱ በእርግጥ በእዚያ ስፍራ ላይ አሉ።
ግድድሮሽ፡- በቅርብ እና በሩቅ ላሉት ያለዎትን ፍቅር ለማካፈል እንዲችሉ
የጠለቀ እምነት እንዲኖራችሁ ልባችሁን በጸሎት ክፈቱ።
ከፍ ያለ ግድድሮሽ፦ ኢየሱስንና ውድ የሆኑትን የሦስቱን መላእክት መልእክት እርስዎ
ያወቁት እንዴት ነው? በግል ሕይወትዎ ከኢየሱስ ያገኟቸውን ሦስት መንፈሳዊ በረከቶች
ይዘርዝሩ። እነዚህን ፅንሰ-ሀሳቦች ለሰንበት ትምህርት ቤት ክፍልዎ ለማካፈል ይዘጋጁ።
“አይሁዳውያን አረማውያን ብለው ከፈረጇቸው መካከል ከእስራኤል
መምህራን ይልቅ ስለ መሲሑ የተነገሩትን የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች በደንብ የተረዱ
ሰዎች ነበሩ። ከኃጢአት ለመታደግ አዳኝ ሆኖ መምጣቱን ተስፋ ያደረጉ አንዳንዶች
ነበሩ። ፈላስፋዎች የዕብራይስጥ አኗኗርን ምስጢር ለማወቅ ጥረት ያደርጉ ነበር። ነገር
ግን የአይሁዶች ጭፍን ጥላቻ የብርሃን መስፋፋትን አገደው።”—Ellen G. White፣
The Desire of Ages፣ p. 33.
“ኃያሉ አዳኝ ጌታ ኢየሱስ ስለ እነዚህ ነፍሳት ሞቶላቸዋል። ከቸልተኝነታቸው
ሊቀሰቅሳቸው፣ ርኅራኄአቸውን በማንቃት፣ ልባቸውን በማለስለስ፣ ለነፍሳቸው
የእውነትን ውበትና ኃይል መግለጥ ይችላል። ዋናው ሠራተኛ እግዚአብሔር ነው እንጂ
ውሱን የሆነው ሰው አይደለም። ነገር ግን በጨለማ ላሉ ሰዎች ብርሃንን የሚሰጥባቸው
ወኪሎች እንዲሆኑ ሰዎችን ይጠራል። እግዚአብሔር በሁሉም አብያተ ክርስቲያናት
ውስጥ ዕንቁዎች አሉት፣ እናም ሃይማኖተኞች ነን የሚሉትን ሰዎች የምንወቅስ ሳንሆን
ልክ ኢየሱስ እንዳደረገው በትሕትና እና በፍቅር እውነቱን የምናቀርብላቸው ልንሆን
ይገባናል። ሰዎች እግዚአብሔርን መምሰል እና መሰጠትን ይዩ፣ የክርስቶስን ባሕርይ
መምሰልን ይዩ፣ እናም ወደ እውነቱ ይሳባሉ። . . . የዓለም ቤዛ የሆነውን ኢየሱስን ከፍ
ማድረግ አለባቸው፤ የሕይወትንም ቃል ሊይዙ ይገባቸዋል።”—Ellen G. White፣ The
Advent Review and Sabbath Herald፣ January 17, 1893
1. እርስዎ እና ቤተክርስትያንዎ የምታውቁትን እውነት የማያውቁ ነፍሶችን ለመድረስ እድል
ሊሰጧችሁ የሚችሉ አንዳንድ በአካባቢዎ የሚታዩ ወሳኝ ፍላጎቶች ምንድን ናቸው?
2. ኤለን ጂ. ኋይት የሌሎች እምነት ተከታዮችን በተመለከተ ከላይ የተናገረችውን
ይመልከቱ፡- “እግዚአብሔር በሁሉም አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ እንቁዎች
አሉት፣ እናም ሃይማኖተኛ ነን በሚሉት ዓለም ላይ ወቀሳ መሰንዘር አይገባንም።
በሌላ አገላለጽ ሰዎችን በግላቸው ሳናንቋሽሽ ለሰዎች የአካሄዳቸውን ስሕተት እንዴት
ማሳየት እንችላለን?
3. “‘የሰው ልጅ በመጣ ጊዜ በምድር ላይ እምነትን ያገኝ ይሆንን?’” ( ሉቃስ 18፡
8) ኢየሱስ ይህን ወሳኝ ጥያቄ ሲጠይቅ ምን ማለቱ ነው? በማመን እና በአስተምህሮ
መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው? ትክክለኛ የእምነት አስተምህሮ ያላቸው ሰዎች
ክርስቶስ ሲመለስ እምነታቸው ከንቱ ሆኖ ሊገኙ የሚችሉት እንዴት ነው?