የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ለዚህ ሳምንት ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ የሐዋርያት ሥራ 17; 1 ቆሮ. 2:2; ሮሜ 1፡18-25።
መግቢያ ጥቅስ፡- “ዓለሙንና በእርሱ ያለውን ሁሉ የፈጠረ አምላክ እርሱ የሰማይና
የምድር ጌታ ነውና እጅ በሠራው መቅደስ አይኖርም፤” (የሐዋርያት ሥራ 17፡24)።
ሉቃስ ጳውሎስ በአቴና ያደረገውን ሲገልጽ እንዲህ ጽፏል:- “ስለዚህም
በምኵራብ ከአይሁድና እግዚአብሔርን ከሚያመልኩ ሰዎች ጋር በየቀኑም
በገበያ ከሚያገኛቸው ጋር ይነጋገር ነበር።” (የሐዋርያት ሥራ 17:17)።
እርግጥ ነው፣ ጳውሎስ በሥጋና በደም ከሚዛመዱት ከአይሁዶች መካከል
መሥራት ይበልጥ ይመቸው ይሆናል። ጳውሎስ ግን በገዛ ወገኖቹ መካከል ብቻ
በመስራት ለመርካት ፈቃደኛ አልሆነም። ሌሎችንም እንዲደርስ ተጠርቷል።
ወይም ጳውሎስ በአመለካከታቸው የተሻሉ ከሆኑት “አምላክን ከሚፈሩ”
አሕዛብ ጋር አብሮ መሥራት ይችል ነበር። ‘የሚፈሩትን አምላክ’ ይኸውም መሲሑን
ኢየሱስን ማወቅ ቢያስፈልጋቸውም ጳውሎስ ሊነሳ የሚችልበት መጽሐፍ ቅዱሳዊ
መሠረት ነበረው።
ግን፣ እንደዚያ አላደረገም። ጳውሎስ በፍልስፍና ዝነኛ በሆነችው በአቴንስ
ከተማ በነበረበት ወቅት እዚያ ያሉትንም ሰዎች ለመድረስ ጥረት አደረገ። ከእነዚህ ውስጥ
ብዙዎቹ ከዕብራውያን እና ከቅዱስ ታሪካቸው የተለየ ዳራ እና ለማስተማር መሠረት
አድርጎ ሊነሳባቸው የማይችልበት አመለካከት ነበራቸው።
ጳውሎስ እነዚህን ሰዎች ለመድረስ ያደረገው ጥረት ምን ነበር? ካደረገው
ሙከራስ ምን እንማራለን?
*ለህዳር 29 ለሰንበት ለመዘጋጀት የዚህን ሳምንት ትምህርት ያጥኑ።
የሐዋርያት ሥራ 17:1-16ን ያንብቡ። ጳውሎስ በአቴንስ እንዴት ተገኘ? እዚያ ላገኘው ነገር ምን ምላሽ ሰጠ?
የአቴንስ ከተማ “ለጣዖታት የተሰጠች” ነበረች (ሐዋ. ሥራ 17፡16)። ጳውሎስ
ስለ ጣዖት አምልኮ የራሱን ሰዎች እና የእምቢተኝነታቸውን ታሪክ (ማለቂያ የሌለው
ማስጠንቀቂያ ቢሰጣቸውም) ስለሚያውቅ በአቴና ባገኛቸው ጣዖታት ተበሳጨ።
ጳውሎስ የተነሳሳው ስለ እውነተኛው አምላክ ካልተማሩ በኃጢአታቸው ለሚሞቱት
የአቴና ሰዎች ባለው ፍቅር እንደሆነ ጥርጥር የለውም።
ምንም እንኳን ጳውሎስ ካየበት ባነሰ ሁኔታ የሚታዩ ቢሆኑም ዛሬም ከተሞቻችን
በጣዖት የተሞሉ ናቸው። እናም በሚያሳዝን ሁኔታ፣ ብዙ አማኞች በከተማዋ ውስጥ
ለጣዖቶቿ ምንም ምላሽ ሳይሰጡ አልፈዋት ሊሄዱ ይችላሉ። ጳውሎስ ግን ለመንፈስ
ቅዱስ ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ ነበር። ጳውሎስ ወንጌል ለዓለም ሁሉ እንደሆነ ገና
ካልተረዱት አንዳንድ አማኞች በተቃራኒ እግዚአብሔር አቴናውያን ከሌሎች ሰዎች
ጋር እንዲድኑ እንደሚፈልግ ያውቃል። ዓለም ዓቀፋዊው ተልእኮ ጣዖት አምላኪ
አረማውያንን እንዲሁም የአቴንስ ጎዳናዎችን የሞሉ ፈላስፎችን ጨምሮ በወንጌል
ላልተደረሱት ሰዎች መውሰድ እንደሆነ ተረድቷል።
ስለዚህ ጳውሎስ እነዚህ ሰዎች ወደሚገኙበት የገበያ ቦታ መሄድን ያዘወትር
ነበር። የገበያ ቦታውን ተጠቅሞ የእነዚህን አረማውያን ልብ እና አእምሮ የመድረስ
ዘዴዎችን እያጠና ስለነበረ የመጀመሪያውን የግሎባል ሚሽን ጥናት ማዕከል አቋቋመ
ልንል እንችላለን።
ጳውሎስ አይሁዳውያንን ወይም ፈሪሃ አምላክ ያላቸው አሕዛብን በቀረበበት
መንገድ ወደ አቴናውያን መቅረብ እንደማይችል ያውቅ ነበር። እነዚህ መነሻቸው
የእስራኤል አምላክ ያልሆኑ ሰዎች ነበሩ። ይህ እምነት ለአይሁዶች እና ፈሪሃ አምላክ
ላላቸው አሕዛብ የቱንም ያህል ማዕከል ቢሆን ጳውሎስ በአቴንስ የገበያ ስፍራ ለገጠሙት
ሰዎች ምንም ትርጉም አልነበራቸውም። ስለዚህ ሙሉ በሙሉ አዲስ አቀራረብ አስፈለገ።
ዛሬ “የአይሁድ-ክርስቲያን” ቅርስ ተብሎ ከሚጠራው ታሪክ ጋር ምንም ዓይነት
ግንኙነት የሌላቸውን ሰዎች ለመድረስ ብዙ ጊዜ እንፈልጋለን። ስለዚህ ልክ እንደ ጳውሎስ
እኛም ከሁኔታዎች ጋር መላመድ አለብን። ለምሳሌ በቦነስ አይረስ ጥሩ ሊሠራ የሚችል
አቀራረብ በባንኮክ ውስጥ ምንም ፋይዳ ላይኖረው የችላል።
በማኅበረሰባችሁ ውስጥ ሰዎች የሚያመልኳቸው ምን ዓይነት ጣዖታት
አሉ? ታድያ ጣዖታቱ ምንም ዋጋ እንደሌላቸው የምትገልፁላቸው
እንዴት ነው?
በየትኛውም ቦታ ጳውሎስ ከእግዚአብሔር የተሰጠውን ተልእኮ ማለትም
ወንጌልን ይሰብክ ነበር። ስለዚህ በአቴንስ ውስጥ ለማድረግ የፈለገው ያንን ነበር።
የሐዋ. ሥራ 17:18-21ን ያንብቡ። በገበያ ቦታ የነበሩት አረማውያን ለጳውሎስ
ንግግርና ጥያቄ ምላሽ የሰጡባቸው አንዳንድ መንገዶች ምን ነበሩ?
በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ጳውሎስ ስለ ‘አዲስ አማልክት’ በመናገሩ
በገበያው ላይ በነበሩት ሰዎች ላይ ተጽዕኖ አሳድሯል (የሐዋ. ሥራ 17: 18)፤ ስለዚህ
ጳውሎስ ለሕጋዊ ክስ ሳይሆን አዲስ አስተምህሮውን ለመስማት የሕግና ሃይማኖታዊ
ጉዳዮች ወደሚደመጡበት ወደ አርዮስፋጎስ ወሰዱት። ለእነዚህ ሰዎች በጣም እንግዳ
የሚመስሉ ሃሳቦችን እያስተዋወቀ ቢሆንም እንኳ እንደ ጳውሎስ አይነት አንደበተ ርቱዕ፣
ግለት ያለውን እና አስተዋይ የሆነን ሰው ችላ ማለት ከባድ ነው።
የሐዋርያት ሥራ 17፡21 አቴናውያን ስለ አዳዲስ ሀሳቦች መናገር እና ማዳመጥ
ብቻ እንደሚፈልጉ ይናገራል። ሉቃስ በስንፍና እየከሰሳቸው ነበር? አይመስልም።
ምናልባትም ልምድ ያላቸው አሳቢዎችና ተከራካሪዎች መሆናቸውን እየጠቆመ ነበር።
ደግሞም ግሪኮች ተጽኖአቸው እስከ ዘመናችን የደረሰውን እንደ ሶቅራጥስ፣ ፕላቶ እና
አርስቶትል ያሉ ፈላስፎችን አፍርተዋል። አቴንስ ለብዙ መቶ ዘመናት የአዕምሯዊ እና
የፍልስፍና አስተሳሰብ ማዕከል ሆና ስትታይ የቆየች ናት። ምንም እንኳን ከእነዚህ
አስተሳሰቦች መካከል አንዳንዶቹ አምላክ የለሽ ባይሆኑም፣ ዛሬ እኛ አምላክ የለሽነትን
በምናስበው መንገድ ባይሆኑም፣ ብዙዎቹ ከፍልስፍና አስተሳሰባቸው የተነሣ ከክርስትና
ትምህርቶች በጣም የተለዩ ነበሩ። ለምሳሌ በኤፊቆሮስ እና ኢስጦኢኮች ፍልስፍና
ውስጥ እንደ መሲሁ ትንሣኤ ላለ ነገር ቦታ ማግኘት ከባድ ነው።
በአቴና፣ ጳውሎስ ከገማልያል በመማሩ ያገኘውን እውቀትና የመናገር ችሎታ
መንፈስ ቅዱስ ሊጠቀምበት እንደሚችል ጠብቆ ነበር። ነገር ግን እንደ እውነቱ
መንፈስ ቅዱስ የበለጠ የተጠቀመው ከአቴና ጎዳናዎች ላይ ያገኘውን ትምህርት ነበር።
“ከአድማጮቹ መካከል ጥበበኞች ምክሩን ሲያዳምጡ ተገረሙ። የጥበብ ሥራዎቻቸውን፣
ጽሑፎቻቸውንና ሃይማኖታቸውን እንደሚያውቅ ጠንቅቆ አሳይቷል።”— Ellen G.
White, The Acts of the Apostles, p. 237
ጳውሎስ ከእነዚህ ጣዖት አምላኪዎችና ፈላስፎች ጋር በአቴና ካጋጠመው
ነገር በኋላ፣ ለቆሮንቶስ ሰዎች እንዲህ ሲል ጽፏል:- “በመካከላችሁ ሳለሁ
ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር እርሱም እንደተሰቀለ ሌላ ነገር እንዳላውቅ
ቆርጬ ነበርና።” (1ቆሮ. 2፡2)። የምንሰብከው ለማንም ቢሆን ክርስቶስ
በመልዕክታችን ውስጥ ምን ያህል ማዕከላዊ መሆን እንዳለበት ከዚህ ምን
ትምህርት እናገኛለን?
ጳውሎስ የአቴናውያንን የሐሰት ሃይማኖት ወይም የሐሰት አማልክትን
እንዳላቃለለ ልብ ይበሉ። ባገኛቸው ጥቂት መልካም ነጥቦች ላይ አተኮረ።
የሐዋርያት ሥራ 17:22-23ን ያንብቡ። ጳውሎስ ለእነዚህ ሰዎች
ወንጌልን ለማድረስ ባደረገው ጥረት ውስጥ ምን እያደረገ ነበር?
“የአቴና ሰዎች ሆይ፥ እናንተ በሁሉ ነገር አማልክትን እጅግ እንደምትፈሩ
እመለከታለሁ።” (የሐዋ. ሥራ 17:22)። ጳውሎስ አረማውያንን እያመሰገነ ነበር!
ሃይማኖታቸው በሁሉም መንገድ የተሳሳተ ነበር፤ ሆኖም ጳውሎስ ለእርሱ ያላቸውን
ታማኝነት አመስግኗል፤ ለዚህም ምክንያቱ ለተሳሳተ መንፈሳዊነት እንኳ ቀናኢ መሆን
ለመንፈሳዊነት ግድ የለሽ ከመሆን የተሻለ ስለሆነ ነው።
ጳውሎስ በመቀጠል እንዲህ አለ:- “የምታመልኩትን እየተመለከትሁ ሳልፍ . . .”
(የሐዋ. ሥራ 17:23)። ጳውሎስ ስለ አቴንስ ሰዎች ሃይማኖት ያደረገውን ጥናት ሲገልጽ
ለሰዎቹ ያለውን አክብሮት አሳይቷል። ህዝቡ እንዴት መለወጥ እንዳለበት ሁሉንም
መልሶች ይዞ ራሱን እንደ ኤክስፐርት አድርጎ ወደ መፍትሔው እየቸኮለ አልነበረም። እንደ
እውነቱ ከሆነ እሱ በዚህ ርዕስ የተካነ(ኤክስፐርት) ነበር፤ እነዚህ ሰዎች የሚያስፈልጓቸው
መልሶችም ነበሩት፤ ነገር ግን እራሱን በዚህ መንገድ አላቀረበም። ወዲያው ተቀባይነቱን
እንዳያጣ ይህን ማድረግ ነበረበት። ይልቁንም ለህዝቡ የሚቆረቆርና መልካማቸውን
የሚሻ ሰው ተደርጎ ይታይ ነበር።
ጳውሎስ “ለማይታወቅ አምላክ” (የሐዋርያት ሥራ 17:23) በሚለው ጽሑፍ
ላይ አስተያየት ሲሰጥ የጋራ ጉዳይ ተደርጎ ሊወሰድ የሚችለውን አጋጣሚ ተጠቅሟል።
በአማልክት (ብዙዎቹ) ያምኑ ነበር፤ ይህም በጣም ጥሩ ጅምር ነበር (በዚያን ጊዜ የነበሩ
አንዳንድ ሰዎች አያምኑም ነበር)፤ ይህም ጥልቅ ለሆነ ውይይት መንገድ ይከፍታል።
ለማይታወቅ አምላክ የተሰጠ መሠዊያ በሚለው አሉታዊ ሐሳብ አላፌዘባቸውም።
ይልቁንም፣ ምናልባት ያላዩት ነገር እንዳለ በመገመት የማያውቁትን ነገር እንኳን እስከማምለክ
ለመሄድ ዝግጁ የነበሩትንና ለመንፈሳዊ ነገሮች በቂ ትኩረት የሰጡትን ሰዎች አደነቃቸው።
ተሳስተው ነበር? አዎን፤ ግን ይህ ሊስተካከል ይችላል። በመጀመሪያ አስፈላጊው
ነገር በተረዱት ነገር ቆራጥ መሆናቸው ነው። ከእንደዚያ አይነት ሰዎች ጋር መንፈስ
ቅዱስ አብሯቸው ሊሠራ በሚችልበት ሁኔታ መሆናቸውን ጳውሎስ ተገንዝቦ ነበር።
ጳውሎስ ትኩረታቸውን እንዲስብ የሚያደርግ የንግግር ነጥብን አገኘ።
ከምታገኟቸው ሰዎች ጋር ጠለቅ ያለ ውይይት ለማድረግ የሚያስችሉ
የትኞቹን ድልድዮች እና የጋራ ነጥቦች ማሰብ ይችላሉ?
አሁን ጳውሎስ በአቴንስ ያሉ ምሁራንን ትኩረት ስላገኘ አድማጮቹን ወደ
ሰማይ አምላክ መለሰ።
የሐዋርያት ሥራ 17:24-27ን ያንብቡ። ጳውሎስ እነዚህን ሰዎች ለማግኘት
ሲል እዚህ ጋ ምን ዓይነት አቀራረብን ተጠቀመ?
ለማይታወቅ አምላክ መሠዊያ እስከመሥራት ድረስ ለመንፈሳዊ ነገሮች በቂ
ትኩረት ለነበራቸው ሰዎች፣ የጳውሎስ ቃላት ትኩረት የሚስቡ ነበሩ፡- ፈጣሪ አምላክ
በቤተ መቅደሱ ውስጥ አይኖርም፤ ከሰዎች ምንም አያስፈልገውም፤ ይልቁንም የሰውን
ፍላጎት ያሟላል። አማልክቱ የማይገመቱ፣ ራስ ወዳዶች እና ጨካኞች በነበሩበት በግሪክ
አፈ ታሪክ ውስጥ ላለው ባህል፣ ጳውሎስ እንደገለጸው ዓይነት አምላክ የሚለው ሐሳብ
አስደናቂና ትኩረት የሚስብ ነበር። የአርዮስፋጎስ ሰዎች ዳዴ በማለት ወደ ፍቅር አምላክ
የመጀመሪያ ጉዞ ጀመሩ።
እውነታው ግን ይህ እነርሱ የማያውቁት አምላክ ሊታወቅ ይችላል! በእርግጥም
እርሱ መታወቅን ይፈልጋል።
ምናልባት ሉቃስ በዚህ ታሪክ ውስጥ ካካፈለን ጥቂት ቃላት ይልቅ ጳውሎስ በአርዮስፋጎስ ረዘም ላለ ጊዜ ተናግሮ ሊሆን ይችላል። ሉቃስ የጳውሎስን ንግግር
ጠቅለል አድርጎ መናገሩ ገፅን ለመቆጠብ መሆኑ አሳማኝ ይመስላል። ያ እውነት ከሆነ፣
እስካሁን ያነበብናቸው እያንዳንዱን ፅንሰ-ሀሳብ ጳውሎስ ምን አልባትም የበለጠ በዝርዝር
ተናግሯቸዋል። ከዚያም የጳውሎስን ንግግር ወደ ትናንሽ ጽንሰ-ሐሳቦች ስንከፋፍላቸው ፡-
1. ጳውሎስ በመጀመሪያ አሁን ያላቸውን መንፈሳዊ ግንዛቤ እና ቅንነት አመሰገነ።
2. በመቀጠል እምነታቸውን እንዳጠና እና ከተማረው ነገር የሚያከብራቸውን
አንዳንድ ነገሮች እንዳገኘ አሳየ።
3. ከዚያም በሃይማኖታቸው ላይ ባደረገው ጥናት እንዳልተረዱት ስላመነው አንድ
የተለየ ነገር ነገራቸው።
4. ከዚህም በኋላ እጅግ በጣም እንደሚፈልጉ የሚያውቀውን የእግዚአብሔርን ገጽታ
አካፈላቸው። ይህም እግዚአብሔር መኖሩን፣ እንደሚወዳቸው እና ሩቅ ያለመሆኑን
እውነታ ነው።
5. ጳውሎስ በንግግሩ መጨረሻ ላይ እስካሁን የማያውቁትን የዚህን አምላክ እውቀት
አለመቀበል ምን ማለት እንደሆነ አስጠንቅቋል።
ጳውሎስ ስለሚያምኑበት ነገር በሚያውቀው ነገር ላይ በመመስረት የቻለውን
ያህል ወሰዳቸው። እስከዚያ ድረስ ሊወስዳቸው ከቻለ ጥሩ እድገት እያሳየ ነበር።
ጳውሎስ ዓለም የተፈጠረች መሆኗንና ፈጣሪዋም እግዚአብሔር
እንደሆነ የገለፀበትን መንገድ ልብ ይበሉ (በተጨማሪ ሮሜ 1፡18-25
ይመልከቱ)። ለብዙዎች ቢያንስ መጀመሪያ ላይ እንዲህ አይነት ጥሩ
አቀራረብ አስፈላጊ የሆነው ለምንድነው? የተፈጠረው ዓለም እጅግ
ጠንካራ በሆነ ሁኔታ እግዚአብሔርን የሚያሳየው እንዴት ነው?
የሐዋርያት ሥራ 17:24-34ን ያንብቡ። ጳውሎስ ምሥክርነቱን የቀጠለው እንዴት ነበር?
በተጨማሪም ጳውሎስ ወደ አድማጮቹ ልብ የበለጠ ለመቅረብ ከነሱ መካከል
ከመጽሐፍ ቅዱሳዊው እውነት ጋር የሚቀራረብ ነገር የጻፉትን አንዳንድ ጸሐፊዎቻቸውን
መጥቀሱ አስገራሚ ነው። ይኸውም ከእምነታቸው ጋር ያለውን ትውውቅ ተጠቅሞ
የጋራ መግባቢያን በማግኘት ወደ ቀጣዩ እርምጃ ይዟቸው ሊሄድ በማሰብ ነው። ሌሎችን
በወንጌሉ ለመድረስ የሚያምኑትን ነገር ጠንቅቆ ማወቅ እና የጋራ ጉዳዮችን መፈለግ ሃይለኛ
ዘዴ እንደሆነ ጥያቄ የለውም።
በተጨማሪም ጳውሎስ ከእነርሱ ጋር ያለውን የጋራ መግባባት ተጠቅሞ ወደሚፈልገው
ቦታ ማለትም ወደ ኢየሱስ ትንሣኤና ትንሳኤው ለሁላቸውም ይዞ ወደመጣው ተስፋ ሀሳብ
ገባ። ሉቃስ ጳውሎስ ስለ ትንሣኤ ሲናገር ህዝቡ የሰጠውን ምላሽ ጽፏል። አንዳንዶች
በሃሳቡ ተሳለቁ፤ ሌሎች በዚህ ጉዳይ ላይ እንደገና ከጳውሎስ መስማት ፈለጉ፤ አንዳንዶቹም
አመኑ። በዚህ ታሪክ ውስጥ ዋናው ነገር ሁሉም በትክክል ማዳመጣቸው ነው። ይህ ደግሞ
ከመጀመሪያውም የጳውሎስ ተስፋ ነበር።
አንዳንድ ሰዎች ወንጌልን እንደማይቀበሉ እናውቃለን፣ ነገር ግን ከመቃወማቸው
በፊት፣ የሚቃወሙትን እንዲረዱ የተቻለንን ሁሉ ማድረግ አለብን። ጳውሎስ በአቴናውያን
መካከል በሚሠራበት ዘዴና የተማረውን ስልታዊ በሆነ መንገድ በመጠቀም እነርሱ
የማያውቁት ነገር ግን የፈጠራቸው አምላክ እንዳለ ከልባቸው ሰምተው እንደነበር
አረጋግጧል። የወደዳቸው እና በእነርሱ ዘንድ እንዲታወቅ የፈለገው ይህ አምላክ ነው።
ባለማወቃቸውም ምህረትን አደረገላቸው። የፍርድ ቀን ግን እየመጣ ነበር። እናም ይህ ሁሉ
የማይታመን መስሎ ከታየ፣ በክርስቶስ ትንሳኤ ውስጥ የተረጋገጠ ማስረጃ ነበር።
አሁን ሕዝቡ መልእክቱን በትክክል ሰምቶና ተረድቶ ስለነበር፣ መልእክቱን ሙሉ
በሙሉ ውድቅ ለማድረግ ወይም የበለጠ ለመመርመር ለራሳቸው መምረጥ ነበረባቸው።
አንዳንዶች ደግሞ በጥልቀት መርምረው የኢየሱስ ተከታዮች ሆኑ (ሐዋ. 17፡34)።
ግድድሮሽ፡ በጸሎት ለአንድ ለሚያውቁት ሰው እንዴት በተሻለ ሁኔታ መመስከር
እንደሚችሉ እንዲያውቁ እግዚአብሔር እንዲመራዎት ይጠይቁ።
ከፍ ያለ ግድድሮሽ፡- ወንጌልን-በጳውሎስ ግልጽነት እና አስተዋይነት—
ለማያምኑት ለማድረስ ማህበራዊ ሚዲያዎችን እንደ “አርዮስፋጎስ” ያስሱ።
ጳውሎስ በአርዮስፋጎስ ካጋጠመው ታሪክ ውስጥ ልንወስዳቸው
ከሚገቡን ዋና ዋና ነጥቦች አንዱ የማያምኑትን እንዴት መቅረብ እንዳለበት ያደረገው
ጥናት ሲሆን ይህም በአቴና የአማኞች ቡድን እንዲጀመር ያስቻለ ነው።
“በመንፈስ በተነካ ብዕር የተገለፀው የሐዋርያው ቃል፣ የአመለካከቱና የነበረው
ሁኔታ መግለጫ፣ የማይናወጥ መተማመኑን፣ በብቸኝነት እና በመከራ ውስጥ ያሳየውን
ብርታት፣ በአረማዊ አምልኮ ማዕከል በሆነ ቦታ ለክርስትና ያስገኘውን ድል በመመስከር
ለሚመጡት ትውልዶች ሁሉ መተላለፍ አለበት።
“የጳውሎስ ቃላት ለቤተ ክርስቲያን የእውቀት ሀብትን ይዘዋል። በቀላሉ ኩሩ
የሆኑትን አድማጮቹን የሚያናድድ እና እራሱን ወደ ችግር የሚያስገባ ነገር ሊናገር ይችል
ነበር። ንግግሩ በአማልክቶቻቸው እና በከተማው ታላላቅ ሰዎች ላይ ቀጥተኛ ጥቃት
ቢሆን ኖሮ የሶቅራጦስ ዕጣ ይደርሰው ነበር። ነገር ግን በመለኮታዊ ፍቅር በተወለደ ዘዴ፣
ለእነርሱ የማይታወቀውን እውነተኛውን አምላክ በመግለጥ አእምሯቸውን ከአረማውያን
አማልክት በጥንቃቄ ሳበ።” Ellen G. White, The Acts of the Apostles, pp. 240, 241.
ጳውሎስ ከሰዎች ጋር በቀጥታ በመገናኘቱ፣ ባህላቸውንና ሃይማኖታቸውን
በማጥናትና ለመንፈሳዊ ነገሮች ያላቸውን መሰጠት በማክበር በአቴንስ ውስጥ ትልቅ
ቦታ የሚሰጠውን ነገር ተጋፈጠ፤ ይህም ለቤተ ክርስቲያን የእውቀት ሀብት ነው።
አድማጮቹን ከማስቆጣት ተቆጠበ። ይህ በራሱ ትልቅ፣ በእግዚአብሔር አነሳሽነት
የተደረገ ስኬት ነበር። ይህ፣ እንደ ኤለን ጂ ዋይት አባባል፣ እኛ እንደ ቤተ ክርስቲያን በዚህ
ታሪክ ውስጥ ትኩረት ልንሰጥበት የሚገባን የእውቀት ሀብት ነው።
1. በአቴንስ የነበረውን የጳውሎስን ታሪክ እንደ አብነት በመጠቀም፣ በከተማ
ውስጥ አዲስ የወንጌል አገልግሎት ለመጀመር የመጀመሪያው እርምጃ ምንድን ነው?
2. እግዚአብሔርን ከማያውቁ ሰዎች ጋር በከተማው ውስጥ (እንዲሁም በሐቀኝነት፣
በየትኛውም ቦታ) ካሉ ሰዎች ጋር ድልድይ ለመሥራት አንድ ክርስቲያን ምን
ዓይነት ባሕርይ ሊኖረው ይገባል?
3. በዘመናዊው የጣዖት ዓይነቶች ብንበሳጭም፣ እነዚያን ጣዖታት በሚያመልኩ
ሰዎች መካከል አዲስ ሥራ ስንጀምር በተለይ በመጀመሪያ ማድረግ የሌለብን
ነገር ምንድነው?
4. ጳውሎስ ሕዝቡን የሚወዳቸውን አምላክ ካስተዋወቀ በኋላ ማቆም ይችል ነበር፤
እነሱም በጣም ደስ ይላቸው ነበር። ነገር ግን መስመሩን በማለፍ ስለ ትንሳኤው
ሲናገር የተታለለ መሰላቸው። ይህን ማድረግ ነበረበት? ለምን?