የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ዘፍጥረት


የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 2ኛ ሩብ ዓመት 2022

ከግንቦት 6 – 12

8ኛ ትምህርት

May 14 - May 20




ቃል ኪዳኑ



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ዘፍ. 22፣ ዕብ. 11:17፣ ዘሌዋ. 18:21፣ ዮሐ. 1:1–3፣ ሮሜ 5:6–8፣ ዘፍ. 23–25፣ ሮሜ 4:1–12።


የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ “በዚህ ጊዜ አብርሃም ሸመገለ፤ ዕድሜውም ገፋ፤ እግዚአብሔርም አብርሃምን በሁሉም ነገር ባረከው” (ዘፍ. 24፡1)።

በ መጨረሻ እግዚአብሔር ቃል በገባው መሠረት ሣራ ለአብርሃም “በሽምግልናው” (ዘፍ. 21፡2) ወንድ ልጅ ወለደችለት፤ ሕፃኑንም ይስሐቅ ብሎ ሰየመው (ዘፍ. 21፡1–5)። ይሁን እንጂ የአብርሃም ታሪክ ገና ያልተጠናቀቀ እንደመሆኑ፣ ወሳኝ ነጥብ ላይ የሚደርሰው ልጁን መሥዋዕት ለማድረግ ወደ ሞሪያ ተራራ በሚወጣ ጊዜ ይሆናል። የሆነ ሆኖ፣ ይስሐቅ “በዘሩ” (ዘፍ. 22፡17-18) አማካይነት ሕዝቦችን ለመባረክ ቃል መግባቱን በሚያመለክተው አውራ በግ ተተካ (ዘፍ. 22፡13)። እርግጥ ነው-- ያ ዘር የሱስ ነበር (ሐዋ. 13፡23)። በመሆኑም በዚህ አስገራሚ (በአንድ መልኩ አስጨናቂ) ታሪክ አብዛኛው የደኅንነት ታሪክ ተገልጦአል።

በዚህ ስፍራ የቱንም ዓይነት ጥልቅ መንፈሳዊ ትምህርቶች ቢቀርቡም፣ የአብርሃም ቤተሰብ በጉዳዩ ሳይናወጥ እንዳልቀረና የእርሱ የወደፊት ሁናቴ ብዥታ ውስጥ ሳይገባ እንዳልቀረ ይታመናል። ሣራ የሞሪያው መሥዋዕት ከቀረበ በኋላ የሞተች ሲሆን (ዘፍ. 23) ይስሐቅም ያለ ትዳር አጋር ብቻውን ቀርቶ ነበር።

ከዚያም ይስሐቅ ቀና የወደፊት ሁናቴ ይከተለው ዘንድ አብርሃም ተነሳሽነቱን ወሰደ። የልጁን ጋብቻ ከርብቃ (ዘፍ. 24) ጋር ያቀናጀ ሲሆን፤ ርብቃ ሁለት ወንዶች ልጆች ወልዳለታለች (ዘፍ. 25፡21-23)። እንዲሁም አብርሃም ራሱ ብዙ ልጆች የወለደችለትን ኬጡራ አገባ (ዘፍ. 25፡1-6)። በዚህ ሳምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን አብርሃምን እስከ ህይወቱ ፍጻሜ እንከተለዋለን (ዘፍ. 25፡7-11)።

ግንቦት 7
May 15

የሞሪያ ተራራ


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፍ. 22፡1-12፣ ዕብ. 11፡17። የዚህ ፈተና ትርጉም ምን ነበር? ከዚህ አስደናቂ ክንውን ምን ዓይነት መንፈሳዊ ትምህርቶች ማግኘት እንችላለን?



ዘፍ. 22 የሥነ መለኮት ምሑራንን ብቻ ሳይሆን ፈላስፎችንና አርቲስቶችን ጭምር ያስደመመ፣ በዓለም አቀፉ ሥነ ጽሑፍ በከፍተኛ ደረጃ የሚመደብ ነው። ይሁን እንጂ የአምላካዊውን ፈተና ፍቺ ለመረዳት አስቸጋሪ ነው። ይህ መለኮታዊ ትእዛዝ ኋላ ላይ የተሰጠውን ሰው መሥዋዕት አድርጎ የማቅረብ ክልከላ የሚቃረን (ዘሌዋ. 18፡21) ከመሆኑም በላይ፣ እግዚአብሔር በይስሐቅ በኩል ከሰጠው አምላካዊ ዘላለማዊ ቃል ኪዳን በተጻራሪ የሚሠራ ይመስላል (ዘፍ. 15፡5)።

ታዲያ እግዚአብሔር ይህን እንዲያደርግ የጠራበት ዓላማ ምን ነበር? እንዲህ በሆነ ኃይለኛ መንገድ ለምን ፈተነው?

“ፈተና” (በዕብራይስጥ ኒሳህ) የተሰኘው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽንሰ ሀሳብ ሁለት ተቃራኒ ሀሳቦችን ያካትታል። አንደኛው የፍርድን ጽንሰ ሀሳብ የሚጠቅስ ሲሆን፣ ይኸውም በሚፈተነው ሰው ልብ ውስጥ ያለውን ነገር ለማወቅ ነው (ጥቅሶቹን ያስተያዩ፡ ዘዳ. 8፡2 እና ዘፍ. 22፡12)። ሁለተኛው የአምላካዊውን ጸጋ ዋስትና ለሚፈተነው ሰው ያመጣል (ዘፀ. 20፡18-20)።

በዚህ ጉዳይ፣ አብርሃም በእግዚአብሔር ላይ ያለው እምነት “የወደፊት” ትውልዱን አደጋ ላይ እስከ መጣል ያደርሰዋል። ይህም ሆኖ በእግዚአብሔር ላይ እምነት ስላለው፣ ለማስተዋል የቱንም ያህል አስቸጋሪ ቢሆንም እርሱ የጠየቀውን ሁሉ ያደርጋል። ደግሞስ በማናየው ወይም ሙሉ በሙሉ ባልገባን ነገር ላይ እምነት ካልጣልን--እምነት ምንድን ነው?

እንዲሁም መጸሐፍ ቅዱሳዊው እምነት አቅማችንን ሁሉ ለእግዚአብሔር ስለ መስጠትና ለእርሱ መሥዋዕት አድርጎ ስለ ማቅረብ ብቻ አይደለም። በእርግጥ ይህ የራሱ ሚና አለው (ሮሜ 12፡1)። ነገር ግን በጎነቱ ለእኛ የማይገባ መሆናችንን በማስተዋል፣ ባለን አቅም እርሱን ማመንና ጸጋውን መቀበል ይኖርብናል። ይህ እውነት ተከትሎ በመጣው ነገር በድጋሚ ተረጋገጠ። ሁሉም የአብርሃም ሥራዎች፣ በርካታ በቅንአት የተሞሉ ተግባሮቹ፣ ከልጁ ጋር ያደረገው በህመም የተሞላ ጉዞ፣ ሌላው ቀርቶ ለመታዘዝና የገዛ አካሉን ክፋይ መሥዋዕት አድርጎ ለእግዚአብሔር ለማቅረብ የነበረው ዝግጁነት የቱንም ያህል አስተማሪ ቢሆንም፣ ሊያድነው ግን አልቻለም። ለምን? ምክንያቱም ጌታ ራሱ ለእርሱ ብቸኛ የመዳን ተስፋ ወደሆነው የሱስ የሚያመላክተውን የአውራ በግ መሥዋዕት አቅርቦ ነበር።

በዚህ ወቅት አብርሃም የአምላካዊውን ጸጋ ምንነት ሳያስተውል እንዳልቀረ ይታመናል። ምንም እንኳ የአብርሃም ተግባራት ብርቱ ምሳሌ እንደሆኑበት፣ እንደ እርሱ ለእግዚአብሔር አብልጠን እንድንሠራ ብንጠራም፣ ነገር ግን የሚያድነን የገዛ ሥራችን ሳይሆን ይልቁንም እግዚአብሔር ስለ እኛ የሠራው ሥራ ነው (ያስተያዩ፡ ኤፌ. 3፡8 እና ሮሜ 11፡33)። በሞሪያ ተራራ ላይ የተስተዋለው የአብርሃምና የይስሐቅ ታሪክ፣ ስለ እምነትዎና እምነትዎን እንዴት እንደሚገልጹ አስመልክቶ በግል ምን ይነግሮታል?

ግንቦት 8
May 16

እግዚአብሔር ያዘጋጃል


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፍ. 22፡8፣ 14፣ 18። እግዚአብሔር እንደሚያዘጋጅ የገባውን ቃል የፈጸመው እንዴት ነበር? ምን አዘጋጀ?



ይስሐቅ ስለ መሥዋዕቱ እንስሳ አባቱን ሲጠይቀው አብርሃም “ ‘ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚሆነውን በግ እግዚአብሔር ራሱ ያዘጋጃል’ ” (ዘፍ. 22፡8) የሚል አስደናቂ መልስ ሰጠው። ሆኖም የዕብራይስጡ ግስ “እግዚአብሔር እራሱን እንደ መሥዋዕቱ በግ ያቀርባል” የሚል አንደምታ ሊኖረው ይችላል። “ያዘጋጃል” (ይርኤሎ) የሚለው ግስ “ራሱን ያቀርባል” (ወይም ቃል በቃል “ራሱን ያያል”) የሚል ፍቺ ሊኖረው ይችላል።

በዚህ ስፍራ እያየን ያለነው ጌታ ራሱ እየተሠቃየና የኃጢአታችንን ቅጣት በራሱ እየከፈለ እንደነበረ የሚያሳየውን የደኅንነትን ዕቅድ መሠረታዊ ነጥብ ነው። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዮሐ. 1፡1-3 እና ሮሜ 5፡6-8። በዚህ ስፍራ ማለትም በሞሪያ ተራራ በምሳሌነት የተተነበየው መሥዋዕት በመስቀል ላይ የሆነውን ነገር እንድንገነዘብ የሚረዳን እንዴት ነው?



ከመስቀሉ ትዕይንት አያሌ ዘመናት ቀደም ብሎ “በቁጥቋጦው መካከል ቀንዶቹ የተጠላለፉበት” የመሥዋዕት በግ (ዘፍ. 22፡13) በቀጥታ የሱስን የሚያመላክት ነበር። እርሱ በዚህ ስፍራ “የታየ” ሲሆን፣ አብርሃም ቆየት ብሎ “በእግዚአብሔር ተራራ ይታያል” ሲል ክስተቱን ገልጾአል። ዘፍ. 22፡ 14 [1962 ትርጉም])። የሱስ ራሱ “አባታችሁ አብርሃም ቀኔን ለማየት ተስፋ በማድረግ ተደሰተ፤ አየም፤ ሐሴትም አደረገ” (ዮሐ. 8፡56) ሲል በዚህ ስፍራ የተስተዋለውን የአብርሃም አባባል በማስተጋባት እርሱ የተናገረውን ትንቢታዊ ቃል አመልክቷል።

“እግዚአብሔር አብርሃም ልጁን እንዲሠዋለት ያዘዘው አእምሮውን በወንጌል ተጨባጭ እውነታ ለመማረክ እና እምነቱን ለመፈተን ነበር። በዚያ በጽልመት በተዋጠ አስፈሪ የፈተና ወቅት በነበሩት ቀናት ውስጥ ያሳለፈው መከራ እግዚአብሔር አምላክ የሰውን ልጅ ለማዳን ሲል የሚከፍለው መስዋዕትነት ምን ያህል ግዙፍ እንደሆነ ከራሱ ልምድ እንዲረዳው ለማስቻል ነበር።”-የኃይማኖት አባቶችና ነቢያት፡ ገጽ 169-170)። በዚህ ስፍራ የተፈጸመው ነገር--በመስቀል ላይ የሆነውን እና እግዚአብሔር ለእኛ ሲል የተቀበለውን መከራ የበለጠ እንድንረዳ የሚረዳን እንዴት ነው? ለተደረገልን ነገር የእኛ ምላሽ ምን መሆን አለበት?

ግንቦት 9
May 17

የሣራ ሞት


በዘፍ. 22፡23 የርብቃን መወለድ ዜና የምንሰማ ሲሆን፣ ይህ ዜና ወደፊት በይስሐቅና ርብቃ መካከል የሚኖረውን ጋብቻ ታሳቢ ያደረገ ነው (ዘፍ. 26)። እንደዚሁም የአብርሃም ሚስት ሣራ ሞት እና ቀብር ዘገባ (ዘፍ. 23)፣ የወደፊቱን ከኬጡራ ጋር የሚኖረውን ጋብቻ ከግምት ያስገባ እንደሆነ እናያለን (ዘፍ. 25፡1–4)።

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፍ. 23። የሣራ ሞትና ቀብር ታሪክ እግዚአብሔር ለአብርሃም በገባው የተስፋ ቃል ፍጻሜ ላይ ምን ሚና አለው?



ከይስሐቅ መሥዋዕት ታሪክ በኋላ የሣራ ሞት መነገሩ፣ የልጇን ሕይወት ሊቀጥፍ ይችል በነበረው በዚህ ክስተት ተጎድታ ሊሆን እንደሚችል ይጠቁማል። ቀደም ሲል ከእርሱ ጋር ባደረገችው ጉዞ እና አልፎ አልፎ ሊከሰት በሚችል የእምነት መንሸራተት፣ ሣራም እንዲሁ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከባሏ ጋር “ፈተና” ውስጥ ነበረች (ዘፍ. 12፡11-13)።

ሣራ የተለየ አንደምታ ባላቸው ወይም ሊረብሹአት በሚችሉ ጉዳዮች እጆቿን አጣጥፋ ቁጭ የምትል ዓይነት ሴት አልነበረችም (ዘፍ. 16፡:3–5፣ ዘፍ. 18:15፣ ዘፍ. 21:9-10)። የእርሷ አለመኖርና ዝምታ፣ እንዲሁም ከዚያ አስገራሚ ክስተት በኋላ የምትሞትበት የጊዜ ሁናቴ፣ ከአካላዊ መገኘቷ ይልቅ ለክስተቶቹ ያላትን ጠቀሜታ ይበልጥ ይናገራል። የሣራ እርጅና የተጠቀሰው (ዘፍ. 23፡ 1) የአብርሃምን የሸምግልና ዕድሜ ለማስተጋባት (ዘፍ. 24፡1) እንደ መሆኑ ለታሪኩ ያላትን አስፈላጊነት ያሳያል።

በመሠረቱ በብሉይ ኪዳን ዕድሜዋ የተጠቀሰላት ብቸኛ ሴት ሣራ ብቻ ስትሆን፣ ይህ ደግሞ ከተጨባጩ እውነታ በኋላ በታሪኩ ውስጥ ያላትን ተሳትፎ ያሳያል። አብዛኛው የምዕራፉ ክፍል በሣራ ሞት ዙሪያ ሳይሆን፣ በምትቀበርበት መሬት ግዢ ላይ ትኩረት ማድረጉ ከተስፋይቱ ምድር ጋር ያለውን ግንኙነት አጉልቶ ያሳያል። እንደ ተጠበቀው የሣራ “በከነዓን ምድር” መሞት (ዘፍ. 23፡2)፣ እግዚአብሔር ምድሪቱን እንደሚወርሱ የገባውን ቃል ኪዳን ያጸና ነበር። ከአብርሃም የዘር ግንድ በተስፋይቱ ምድር የሞተችና የተቀበረች የመጀመሪያ ሰው ሣራ ናት። አብርሃም “ ‘ለአገሩ እንግዳ፤ ለሰዉ ባዳ’ ” (ዘፍ. 23፡4) መሆኑ አብልጦ ስላሳሰበው፣ ለኬጢ ልጆች ያቀረበው ጥብቅ ሙግት የእርሱ ፍላጎት የመቃብር ቦታ ለማግኘት ብቻ እንዳልሆነ ያሳያል። እርሱን በዋነኝነት የሚያሳስበው በመሬቱ ላይ በቋሚነት የመኖሩ ጉዳይ ነው።

ጥቅሱን ያንብቡ፡ ዘፍ. 23፡6። ይህ ሁኔታ አብርሃም ስለነበረው መልካም ስም ምን ይነግረናል? እንደዚያ እንዲያደርግ ጌታ የተጠቀመበት መሆኑን ለመረዳት ይህ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

ግንቦት 10
May 18

ሚስት ለይስሐቅ


ዘፍ. 24 ሣራ ከሞተች በኋላ ስለ ተፈጸመው የይስሐቅ ጋብቻ ይነግረናል። ሁለቱ ታሪኮች ተዛማጅነት አላቸው። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፍ. 24። አብርሃም ልጁ ከከነዓናውያን ሴት አንዷን እንዳያገባ በእጅጉ አሳስቦት የነበረው ለምንድን ነው?



አብርሃም ሚስቱን ለመቅበር መሬቱን ለመያዝ እንደፈለገ ሁሉ፣ እግዚአብሔር ዘሮቹ ይህችን ምድር እንደሚወርሱ በገባው ቃል ኪዳን መሠረት አሁን ይስሐቅ ከተስፋይቱ ምድር ውጪ እንደማይቀመጥ አጥብቆ እየተናገረ ነው (ዘፍ. 24፡ 7)። በተጨማሪም ይስሐቅ የእርሱን ሙሽራ ወደ ሣራ ድንኳን ለማምጣት የወሰደው እርምጃ እንዲሁም በርብቃ አማካይነት “ከእናቱ ሞት ተጽናና” (ዘፍ. 24፡67) በሚል መነገሩ፣ መለስ ብሎ የሣራን ሞት የሚያመለክት ሲሆን፣ ይህም ይስሐቅ እናቱን በሞት በማጣቱ ተሰምቶት የነበረውን ሥቃይ ያመለክታል።

ታሪኩ ጸሎት እና የጸሎት ምላሽን በሰፊው ያካተተ ከመሆኑም በላይ በአምላካዊው በቸርነት የተሞላ መግቦት እና በሰብዓዊው ነጻነት ዙሪያ የበለጸገ ነው። “በሰማይና በምድር አምላክ በእግዚአብሔር…” (ዘፍ. 24፡3) የሚሉት አብርሃም የተናገራቸው ቃላት ከሁሉ አስቀድሞ ለእግዚአብሔር ፈጣሪ አምላክነት ዕውቅና የሰጠና (ዘፍ. 1፡1፣ ዘፍ. 14:19) ራሱን መሲሑን ጨምሮ ከአብርሃም ዘር መወለድን በቀጥታ የሚመለከት ነው። “ ‘መልአኩን’ ” እና “ ‘የሰማይ አምላክ እግዚአብሔር’ ” (ዘፍ. 24፡7) በሚል የቀረበው ማጣቀሻ፣ ቀደም ሲል ይስሐቅን ከመታረድ ወደ ታደገው የእግዚአብሔር መልአክ ያመለክታል (ዘፍ. 22፡11)። መላውን ዩኒቨርስ የሚቆጣጠረው እግዚአብሔር አምላክ፣ ይስሐቅን ለመታደግ ጣልቃ የገባው የጌታ መልአክ፣ በዚህ የጋብቻ ጥያቄ ከፊት ይቀድማል።

ልጅቷ ለእግዚአብሔር ጥሪ ምላሽ ላትሰጥ የምትችልበት ዕድል ሊኖር ከመቻሉ አኳያ አብርሃም ጉዳዩን ክፍት አድርጎ ይተወዋል። እርሱ ኃያል አምላክ ቢሆንም፣ ነገር ግን ሰዎች እንዲታዘዙት አያስገድዳቸውም። ምንም እንኳ እግዚአብሔር ለርብቃ ያለው እቅድ ኤሊዔዘርን እንድትከተል ቢሆንም፣ የመምረጥ ነፃነቷ እንደተጠበቀ ነው። ይኸውም ይህች ልጅ መምጣት የማትፈልግ ከሆነ ልትገደድ አትችልም።

ስለዚህ እግዚአብሔር ለእኛ ለሰዎች የሰጠንን የመምረጥ ነጻነት ይኸውም እርሱ ስለማይደፈጥጠው በታላቅ ምስጢር የተሞላ ነጻነት እነሆ ሌላ ምሳሌ በዚህ ስፍራ እንመለከታለን። ይሁን እንጂ ሰብዓዊው ፍጡር ተጨባጭ የመምረጥ ነጻነቱን ለአያሌ አስከፊ ውሳኔዎች ቢጠቀምበትም፣ ነገር ግን በስተመጨረሻ የእግዚአብሔር ፍቅር እና መልካምነት አሸናፊ እንደሚሆን አሁንም ልበ ሙሉ መሆን እንችላለን።

የሁሉም የበላይ እግዚአብሔር ሆኖ ሳለ፣ ነገር ግን ሁሉም ነገር እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ገቢራዊ አለመሆኑን ማወቃችን ሊያጽናናን የሚችለው እንዴት ነው? ለምሳሌ እንደ ዳን. ምዕ. 2 ያሉ ትንቢቶች ይህን ነጥብ የሚያረጋግጡልን እንዴት ነው?





ግንቦት 11
May 19

ሚስት፡ ለአብርሃም


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፍ. 24፡67-25፡8። በአብርሃም ሕይወት ውስጥ ክንውን ያገኙት የእነዚህ የመጨረሻ ክስተቶች ትርጉም ምንድን ነው?



ሣራ ከሞተች በኋላ አብርሃም እንደገና አገባ። ልክ እንደ ይስሐቅ ከሣራ ሞት በኋላ እርሱም ተጽናና (ዘፍ. 24፡67)። የሣራ ትውስታ ከልጁ አእምሮ እንዳልጠፋ ሁሉ፣ በርሱም ልብ እንደነበር ይታመናል (ዘፍ. 24፡67)። ሆኖም የአዲሷ ሚስቱ ማንነት በግልጽ አይታወቅም። የታሪክ ጸሐፊው የኬጡራን ስም ሳይጠቅስ፣ የኬጡራን ልጆች ከአጋር ልጆች ጋር ማገናኘቱ (አንዳንዶች እንደሚሉት) አጋር ልትሆን እንደምትችል ያሳያል። በተጨማሪም አብርሃም ለአጋር ልጅ ያደረገውን በተመሳሳይ ለኬጡራ ልጆች መድገሙን ማሳየቱ ጠቃሚ ነው። በሣራ፣ በልጁ እና በእነርሱ መካከል ግልጽ ልዩነት በማስቀመጥ፣ እነዚህ ልጆቹ ሊያሳድሩ የሚችሉትን ማንኛውንም ዓይነት መንፈሳዊ ተጽእኖ ለማስገወድ ራቅ ወዳለ ስፍራ ይሰዳቸዋል።

አብርሃም “ያለውን ሀብት ሁሉ ለይስሐቅ አወረሰው” (ዘፍ. 25፡5) “ለቁባቶቹ ልጆች ግን በሕይወት እያለ ስጦታ አደረገላቸው” (ዘፍ. 25፡6)። “ቁባቶቹ” በሚል የተቀመጠው አመዳደብ ኬጡራ ልክ እንደ አጋር ቁባት እንደ ነበረች ያመለክታል። በዚህም ኬጡራ ከአጋር በተመሳሳይ ተገልጻ እንመለከታለን። በዘፍ. 25፡1-4፣ 12-18 አብርሃም ከኬጡራ የወለዳቸው ልጆች እና የእስማኤል ልጆች ስም ዝርዝር መቅረቡ ትኩረት የሚስብ ነው። አብርሃም ስድስት ወንዶች ልጆችን ከሰጠችው ከኬጡራ ጋር ከተጋባ በኋላ የተጠቀሰው የዘር ሃረግ ዓላማ፣ ሁለቱን ልጆቹን (ይስሐቅና እስማኤል) ጨምሮ እርሱ የብዙ ሕዝብ አባት እንደሚሆን እግዚአብሔር የገባለትን ኪዳን ወዲያውኑ ለማቅረብ ሊሆን ይችላል። ሁለተኛው የዘር ሐረግ ደግሞ ልክ በያዕቆብ እንደሚሆነው( ዘፍ. 35፡2226)--12 ነገዶችን ያቀፈውን (ያስተያዩ፡ ዘፍ. 17፡20) የእስማኤልን የትውልድ ሀረግ የሚመለከት ነው። የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን በእስማኤል ሳይሆን በይስሐቅ የዘር ሃረግ (ዘፍ. 17፡21) ተጠብቆ የሚዘልቅ ይሆናል። ቅዱሳት መጻሕፍት ይህን ግልጽ አድርገው ያስቀምጣሉ።

በሁለቱ የትውልድ ሐረጎች መሃከል የዋለው የአብርሃም ሞት ዘገባ (ዘፍ. 25፡7-11) የእግዚአብሔርን በረከትም ይመሰክራል። እግዚአብሔር ከብዙ ዓመታት ቀደም ብሎ አብርሃም “ ‘በመልካም ሽምግልና ’ ” (ዘፍ. 15፡15 [1962 ትርጉም]) እንደሚሞት የገባው ቃል ኪዳን መፈጸሙን ያሳያል (ያስተያዩ፡ መክ. 6፡3)

በመጨረሻ፣ ጌታ--በቅዱሳት መጻሕፍት እምነቱ በታላቅ ምሳሌነት ለቀረበው ታማኝ አገልጋዩ አብርሃም የጸጋ ቃሉን ጠብቆ ቆየ--ጽድቅ በእምነትን አስመልክቶ በብሉይ ኪዳን ከቀረቡት እጅግ ምርጡ ምሳሌ ባይሆንም (ሮሜ 4፡1-12)።

ግንቦት 12
May 20


ተጨማሪ ሀሳብ


አብርሃም እግዚአብሔር ዕቅዶቹን የሚያጋራው (ዘፍ. 18፡17) እጅግ የተለየ ነቢይ ስለ ነበር፣ ፈጣሪ አምላክ የአብርሃም ሰብዓዊ ክልል ውስጥ በመግባት በተወሰነ ደረጃም ቢሆን በልጁ መሥዋዕትነት የሚገኘውን ደኅንነት አጋራው።

“ይስሐቅ ስለ ዓለም ኃጢአት መሥዋዕት የሚሆነው የእግዚአብሔር ልጅ ምስል ነበር። ለሰው ልጅ የተዘጋጀውን የደኅንነትን ወንጌል እግዚአብሔር በአብርሃም ላይ ጫነ። ይህን ለማድረግ፣ እና እውነትን ለእርሱ በተጨባጭ ለማሳየት ብሎም እምነቱን ለመፈተን--ተወዳጁን ልጁን ይስሐቅን መሥዋዕት አድርጎ እንዲያቀርብለት ጠየቀው። አብርሃም የወደቀውን ሰብዓዊ ዘር የመቤዠትን ዕቅድ በጥልቅ ይረዳ ዘንድ በዚያ ልብ የሚሰብር ሐዘንና ሥቃይ ባጠላው አስፈሪ ጽልመታዊ ፈተና ውስጥ ማለፍ ነበረበት። ዘላለማዊው አምላክ ሰውን ከውድመት ለመታደግ ሲል ራሱን ክዶ የገዛ ልጁ እንዲሞት አሳልፎ መስጠቱ፣ ሊነገር የማይቻል መሆኑን አብርሃም ከገዛ ልጁ ተሞክሮ እንዲማር ተደረገ። አብርሃም ልጁን እንዲሠዋ የተሰጠውን መለኮታዊ ትእዛዝ በማክበር የጸናበትን የአዕምሮ ሥቃይ የሚተካከል ምንም ነገር የለም”—Ellen G. White, Testimonies for the Church, vol. 3, p. 369.

“አብርሃም ዕድሜው በመግፋቱ ምክንያት ብዙም ሳይቆይ እንደሚሞት ቢጠበቅም ነገር ግን የተስፋውን ቃል ለልጁ በማስተላለፉ ረገድ አንድ ተግባር ብቻ ይቀረው ነበር። ይስሐቅ የእግዚአብሔርን ቃል በመጠበቅ እና የተመረጡ ሕዝቦች አባት በመሆን እርሱን እንዲወርሰው ከሰማይ የተመረጠ ቢሆንም ነገር ግን ገና ሚስት አላገባም ነበር። የከነዓን ነዋሪዎች ለጣኦት አምልኮ የተጋለጡ ሲሆኑ እግዚአብሔር ደግሞ በሕዝቦቹ እና በእነዚያኞች መካከል ጋብቻ ከተመሠረተ የጣኦት አምልኮን እንደሚያስከትል ስለሚያውቅ ይከለክል ነበር። አብርሃም በልጁ ዙሪያ ያሉ ብልሹ ተጽዕኖዎች የሚኖራቸው ውጤት ያስፈራው ነበር… በአብርሃም አእምሮ ውስጥ ለልጁ የምትሆን ሚስት የመምረጡ ጉዳይ ወሳኝነቱ ከፍተኛ ነበር። ሊድረው የሚፈልገው ከእግዚአብሔር የማታርቀውን ሴት ነው።… ይስሐቅ በአባቱ ብልሀት እና ስሜት በመተማመን በሚስት መረጣው ዙሪያ እግዚአብሔር አመራር እንደሚሰጥ ይገባው ስለነበር ጉዳዩን ለአባቱ ተወለት።”--የኃይማኖት አባቶችና ነቢያት፡ ገጽ 189-190።


የመወያያ ጥያቄዎች



1.አብርሃም ይስሐቅን ለመሠዋት ስለ ነበረው ፈቃደኝነት በክፍል ውስጥ ተወያዩ። ይህ ዘገባ የሚገልጠውን የተለየ ዓይነት እምነት በዐይነ ህሊናዎ ለመሳል ይሞክሩ። በዚህ ታሪክ በጣም የሚያስደንቀው፣ በተመሳሳይ የሚያስጨንቀው ምንድን ነው? 2.የመምረጥ ነጻነትን በተመለከተስ? እምነታችን ከዚህ ተጨባጭ እውነታ ውጪ ትርጉመ ቢስ የሆነው ለምንድን ነው? የመምረጥ ነፃነትን አስመልክቶ በመጽሐፍ ቅዱስ ምን ዓይነት ምሳሌዎች አሉን? ሰዎች ይህን ነጻነታቸውን ተጠቅመው የተሳሳተ ምርጫ ቢያደርጉም፣ በመጨረሻ አምላካዊው ፈቃድ የሚፈጸመው እንዴት ነው?




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA union SSL