የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ዘፍጥረት


የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 2ኛ ሩብ ዓመት 2022

ከሚያዝያ 29 - ግንቦት 5

7ኛ ትምህርት

May 7 - May 13




ቃል ኪዳን ከአብርሃም ጋር



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ዘፍ. 15–19:29፣ ሮሜ 4:3-4፣ 9፣ 22፣ ገላ. 4:21–31፣ ሮሜ 4:11፣ ሮሜ 9:9፣ አሞጽ 4:11።


የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ “አብራምም ‘እግዚአብሔር አምላክ ሆይ፤ ያለ ልጅ የቀረሁ ስለሆንሁ፣ የቤቴ ወራሽ የደማስቆ ሰው ኤሊዔዘር ነው፤ ታዲያ ምን ትሰጠኛለህ?’ አለው” (ዘፍ. 15፡2)።

በ ዘፍ. 15 እግዚአብሔር ከአብርሃም ጋር የገባውን ኪዳን ሕጋዊ የሚያደርግበት ወሳኝ ሰዓት ላይ እንገኛለን። አብርሃማዊው ኪዳን እግዚአብሔር ከኖኅ ጋር ከገባው የሚቀጥል ሁለተኛው ኪዳን ነው። ልክ እንደ ኖህ ቃል ኪዳን ሁሉ፣ የአብርሃም ቃል ኪዳን ሌሎች ብሔራትንም ያካተተ ነው። ይህ እግዚአብሔር ከአብርሃም ጋር የገባው ኪዳን ውሎ አድሮ ለመላው ሰብዓዊ ዘር የተሰጠ ዘላለማዊ ኪዳን አካል ነው (ዘፍ. 17፡7፣ ዕብ. 13፡20)።

ይህ የአብርሃም ሕይወት ምዕራፍ በፍርሃትና ሳቅ የተሞላ ነው። አብርሃም ፈርቶ የነበረ ሲሆን (ዘፍ. 15፡1)፣ ሣራ (ዘፍ. 18፡15) እና አጋርም እንዲሁ (ዘፍ. 21፡17) ፈርተው ነበር። አብርሃም ሳቀ (ዘፍ. 17፡17)፣ ሣራም እንዲሁ ሳቀች (ዘፍ. 18፡12) በተመሳሳይ እስማኤልም ሲስቅ (ዘፍ. 21፡9) ይስተዋላል። እነዚህ ምዕራፎች የሰውን ስሜታዊነትና የልብ ሁናቴ ያስተጋባሉ። አብርሃም በእርክስና የወደቁት ሶዶማውያን ይድኑ ዘንድ ከልብ የመነጨ ፍላጎት ነበረው። ለሣራ፣ ለአጋርና ለሎጥ ተገቢውን ድጋፍና እንክብካቤ ያደርግ ነበር። አብርሃም ለሦስቱ እንግዶች ያደረገው ነገር ዕንግዳ ተቀባይነቱን ያስመሰከረ ነበር (ዘፍ. 18፡2-6)።

መኳንንት እና የሚከበር የሚል ፍቺ የነበረው አብራም የተሰኘ የቀድሞ ስሙ አሁን ወደ አብርሃም ይለወጣል። አብርሃም “የብዙ ሕዝቦች አባት” (ዘፍ. 17፡ 5) የሚል ፍቺ አለው። በዚህም፣ እግዚአብሔር ከአብርሃም ጋር በገባው ቃል ኪዳን ሊሠራ ስላቀደው ዩኒቨርስ አቀፍ ተፈጥሮ የተላበሰ አምላካዊ ዕቅድ፣ ተጨማሪ ፍንጮችን እንመለከታለን።

ሚያዝያ 30
May 8

የአብርሃም እምነት


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፍ. 15፡1-21 እና ሮሜ 4፡3፣4፣9፣22። አብርሃም በእምነት መኖር ምን ማለት እንደሆነ የገለጸው እንዴት ነው? እግዚአብሔር--አብራም እንዲያቀርብ ያዘዘው መሥዋዕት ምን ትርጉም አለው?



አብራምን አሳስቦት ስለነበረው የወራሹ ጉዳይ (ዘፍ. 15፡1-3) እግዚአብሔር የሰጠው የመጀመሪያ ምላሽ “ከአብራክህ የሚከፈል” (ዘፍ. 15፡4) ልጅ ወራሽህ ይሆናል የሚል ነበር። ነቢዩ ናታን የወደፊቱን መሲሐዊ ንጉሥ ዘር ለማመልከት ተመሳሳይ ቋንቋ ጥቅም ላይ አውሏል (2ሳሙ. 7፡12)። አብራም ከጥርጣሬና ፍርሃት ነጻ ሆኖ “እግዚአብሔርን አመነ” (ዘፍ. 15፡6)። ምክንያቱም የአምላካዊው ቃል ኪዳን ፍጻሜ የተመሠረተው በእርሱ ሳይሆን በእግዚአብሔር ላይ መሆኑን በማስተዋሉ ነው (ጥቅሶቹን ያስተያዩ፡ ዘፍ. 15፡ 6 እና ሮሜ 4፡5-6)።

ይህ አስተሳሰብ፣ በተለይ በዚያ ባህል ውስጥ በእጅጉ ያልተለመደ ነበር። ለምሳሌ በጥንት ግብፃውያን እምነት መሠረት የአንድ ሰው የጽድቅ ሥራ ይገመገም የነበረው፣ ጽድቅን ከምትወክለው ማት ከተባለች አማልክት ጽድቅ አኳያ በማነጻጸር ነበር።

ከዚያም እግዚአብሔር አብራም የሚፈጽመውን መሥዋዕታዊ ሥርዓት አቋቋመ። በመሠረቱ መሥዋዕቱ ክርስቶስ ስለ ኃጢአታችን መሞቱን ያመለክታል። ሰዎች የዳኑት በእነዚህ መሥዋዕቶች ተምሳሌትነት በቀረበውና የእግዚአብሔር ጽድቅ ስጦታ በሆነው በጸጋው ነው። ነገር ግን ይህ በዓይነቱ ልዩ የሆነ ሥርዓት ለአብራም የሚያስተላልፈው ጥብቅ መልእክት አለው። በመሥዋዕት የቀረቡትን እንስሳት ለመብላት የወረዱት አሞሮች (ዘፍ. 15፡ 9-11) ፍቺ--የአብራም ዘር “ ‘አራት መቶ ዓመት’ ” (ዘፍ. 15፡13) ወይም አራት ትውልድ (ዘፍ. 15፡16) በባርነት እንደሚሠቃይ የሚያመለክት ነው። ከዚያም አራተኛ ትውልድ የሆነው የአብርሃም ዘር “ ‘ወደዚህ ምድር ይመለሳል’ ” (ዘፍ. 15፡16)።

አብራም ያቀረበው መሥዋዕት የመጨረሻ ትዕይንት አስገራሚ ነው፡ “የሚንበለበል ፋና ታየ፤ በተከፈለውም ሥጋ መካከል ዐለፈ” (ዘፍ. 15፡17)። ይህ ዕንግዳ የሆነ አስደናቂ ክስተት እግዚአብሔር ለአብራም ዘር ምድሪቱን ለመስጠት የገባውን ቃል ኪዳን ለመፈጸም ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል (ዘፍ. 15፡18)።

“ ‘ከግብፅ ወንዝ ጀምሮ እስከ ታላቁ የኤፍራጥስ ወንዝ ድረስ’ ” (ዘፍ. 15፡18) በሚል የቀረበው የዚህች የተስፋይቱ ምድር ወሰን፣ የኤደንን የአትክልት ስፍራ ወሰኖች ያስታውሰናል (ያስተያዩ፡ ዘፍ. 1፡13-14)። በመሆኑም ይህ ትንቢት እስራኤላውያን ከባርነት ከመውጣታቸው እና ምድሪቱ ለእስራኤል መኖሪያ ከመሆኗም የላቀ ሥዕል ይዟል። በዚህ ትንቢት፣ የአብርሃም ዘሮች የከነዓንን ምድር ከመውረሳቸው ሩቅ አድማስ ባሻገር፣ በዘመን መጨረሻ የዳኑት የእግዚአብሔር ሕዝቦች ወደ ኤደን ገነት የሚመለሱበትን ጽንሰ ሀሳብ ያሳያል። ብቸኛ የመዳን ተስፋችን በሆነው በክርስቶስ እና በእርሱ ጽድቅ ላይ ትኩረት ማድረግ እንዳለብን መማር የምንችለው እንዴት ነው? መልካም ሥራችንን መቁጠር ብንሞክር ምን ይከሰታል?

ግንቦት 1
May 9

የአብራም ጥርጣሬዎች


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፍ. 16፡1-16። እግዚአብሔር ለአብራም ቃል ገብቶለት እያለ፣ ወደ አጋር ለመድረስ የመወሰኑ አንደምታ ምንድን ነው? ሁለቱ ሴቶች ሁለት የእምነት አመለካከቶችን እንዴት ይወክላሉ? (ገላ. 4፡21-31)



አብራም በተጠራጠረ ጊዜ (ዘፍ. 15፡2) ወንድ ልጅ እንደሚወልድ እግዚአብሔር በማያሻማ ሁኔታ አረጋግጦለታል። ሆኖም ከዓመታት በኋላ አብራም አሁንም ልጅ አልነበረውም። እግዚአብሔር ከገለጠለት የመጨረሻው ብርቱ ትንቢት በኋላም እንኳ አብራም እምነት ያጣ ይመስላል። ከሦራ ወንድ ልጅ አገኛለሁ ብሎ ተስፋ የማድረጉን ጉዳይ ያቆመ ይመስላል። ተስፋ መቁረጥ ስሜት ውስጥ የገባችው ሦራ በዚያን ዘመን በጥንታዊው የቅርብ ምሥራቅ አገራት የተለመደ የነበረውን ተግባር እንዲፈጽም፣ ማለትም ከአገልጋይዋ ጋር እንዲተኛ በመገፋፋት ተነሳሽነቱን ወሰደች። የሦራ አገልጋይ የነበረችው አጋር ለዚህ አገልግሎት ታጨች። አሠራሩ ውጤት የሚያመጣ ሆነ። የሚገርመው ይህ ሰብዓዊ ስልት በአምላካዊው ተስፋዎች ላይ ሊኖር ከሚችል እምነት በላቀ ውጤታማ መሰለ።

ሦራ ከአብራም ጋር የነበራትን ግንኙነት የሚገልጸው ክፍል፣ በኤደን የአትክልት ስፍራ የነበረውን የአዳምና ሔዋንን ታሪክ ያስተጋባል። ሁለቱ ጥቅሶች በርካታ የጋራ ጭብጦች (ሦራ እንደ ሔዋን ሁሉ ቀደም፣ ቀደም የምትል ሲሆን አብራም ደግሞ እንደ አዳም ለዘብተኛ ነበር) እንዲሁም ግሶች እና ሀረጎችም ይዘዋል (“የሚስቱን ቃል መስማቱ”፣ “መቀበሉ” “መስማማቱ”)። በእነዚህ ሁለት ታሪኮች መካከል ያለው መመሳሰል እግዚአብሔር በዚህ እርምጃ አለመስማማቱን ያሳያል።

ሐዋርያው ጳውሎስ በሥራ እና በጸጋ መካከል ያለውን ልዩነት ለማሳየት ይህን ታሪክ ይጠቅሳል (ገላ. 4፡23-26)። በሁለቱም ዘገባዎች ውጤቱ ተመሳሳይ ነው፡ ከአምላካዊው ፈቃድ ውጪ ያለው ሰብዓዊ ሥራ ሊያስገኝ የሚችለው ሽልማት መጨረሻው አጓጉል ነው። ይህ ድርጊት ገቢራዊ በሆነበት አጠቃላይ ሂደት ውስጥ እግዚአብሔር እንዳልነበረ ልብ ይሏል። ሦራ ስለ እግዚአብሔር ብትናገርም፣ ፈጽሞ እርሱን አታናግረውም። እግዚአብሔርም ቢሆን ሁለቱንም አያናግራቸውም። ይህ የእግዚአብሔር አለመገኘት ያልተለመደ ነበር--በተለይ ከቀደመው ምዕራፍ ብርቱ አምላካዊ መገኘት አኳያ።

ከዚያም እግዚአብሔር ለአጋር የተገለጠላት ቢሆንም፤ ይህ የሆነው ከአብራም ቤት ከኮበለለች በኋላ ነበር። ይህ ያልተጠበቀ ሁኔታ ሰው ከእርሱ ውጪ ለመሥራት ቢጥርም እንኳ፣ አምላካዊውን አብሮነት ይፋ ያደረገ ነበር። “የእግዚአብሔር መልአክ” (ዘፍ. 16፡7) የሚለው መግለጫ ብዙውን ጊዜ ጌታ ማለትም ያሕዌ (ዘፍ. 18፡1፣ 13፣22) የሚታወቅበት ነው (ዘፍ. 18፡ 1፣ 13፣ 22)። በዚህ ወቅት እግዚአብሔር ተነሳሽነቱን ወስዶ አጋር ወንድ ልጅ እንደምትወልድና ስሙንም እስማኤል እንደምትለው ነገራት። የስሙ ትርጓሜ እግዚአብሔር ሰምቶአልና (ዘፍ. 16፡11 [1962 ትርጉም]) ማለት ነው። የሚገርመው ይህ “ሰምቶአልና” በሚል ጽንሰ ሀሳብ የሚያበቃው ታሪክ፣ በታሪኩ መጀመሪያ ላይ አብራም የሦራን ቃል “ሰማ” (ዘፍ. 16፡3 [1962 ትርጉም]) በሚል ቀርቦ የነበረውን ያስተጋባል።

በዚህ ቦታ በአብራም የተስተዋለው ዓይነት እምነት ማጣት ለእኛ በጣም ቀላል የሆነው ለምንድን ነው?

ግንቦት 2
May 10

የአብራማዊው ኪዳን ምልክት


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፍ. 17፡1-19 አና ሮሜ 4፡11። የግርዘት ሥርዓት መንፈሳዊና ትንቢታዊ ትርጉም ምንድን ነው?



ቀደም ባለው ታሪክ እንደ ተመለከተው (ዘፍ. 16) የአብራም እምነት ማጣት ከእግዚአብሔር ጋር የነበረውን የእምነት ጉዞ እንዲቋረጥ አድርጓል። በዚያን ወቅት እግዚአብሔር ዝም ነበር ያለው። አሁን ለመጀመሪያ ጊዜ እግዚአብሔር አብራምን በድጋሚ ሲያናግረው እንመለከታለን። እግዚአብሔር እንደገና ከአብራም ጋር ግንኙነት በመፍጠር ከእርሱ ጋር ገብቶት ወደ ነበረው የቀደመ ኪዳን ይመልሰዋል።

አሁን ግን፣ የዚያን ቃል ኪዳን ምልክት ሰጠው። የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑራን በግርዛት ትርጉም ዙሪያ ለረጅም ጊዜ ሲወያዩ፣ ሲነጋገሩና ሲከራከሩ ኖረዋል። ነገር ግን የግርዛት ሥርዓት የደምን መፍሰስ የሚያካትት እንደመሆኑ (ዘፀ. 4፡ 25)፣ ለእርሱ ጽድቅ እንደተቆጠረለት በማመልከት፣ ይህ በመሥዋዕት ዐውድ መስተዋል ይችላል (ሮሜ 4፡11)።

እዚህ ላይ፣ ይህ በግርዘት የተመለከተ ቃል ኪዳን የመጀመሪያውን መሲሃዊ ትንቢት በሚያመለክት መልኩ መገለጹን መረዳት በጣም አስፈላጊ ነው (ያስተያዩ፡ ዘፍ. 17፡7 እና ዘፍ 3፡15)። በሁለቱ ጥቅሶች መካከል ያለው መመሳሰል እግዚአብሔር ለአብራም የገባው ኪዳን ከአካላዊው የሰዎች መወለድ በላቀ፣ ለምድር ሕዝቦች ሁሉ የደኅንነት መንፈሳዊ ተስፋ መያዙን ይጠቁማል። እንዲሁም “የዘላለም ኪዳን” (ዘፍ. 17፡7) ተስፋ ቃል የመሲሐዊውን ዘር ሥራ የሚያመለክት ሲሆን፣ ይኸውም የክርስቶስን መሥዋዕትነት በእምነት የራሳቸው አድርገው ለሚቀበሉ ሁሉ የዘላምን ሕይወት የሚያረጋግጥ ነው (ጥቅሶቹን ያስተያዩ፡ ሮሜ 6፡23 እና ቲቶ 1፡2)።

የሚገርመው ይህ የዘላለማዊ ኪዳን ተስፋ ቃል የአብራም እና ሦራ ስም መቀየርንም አካቷል። የአብራም እና ሦራ ስሞች የሚያመለክቱት በወቅቱ ይገኙ የነበሩበትን ሁኔታ ብቻ ሲሆን፣ አብራም “ስመ ጥር አባት” እንዲሁም ሦራ “የኔ ልዕልት” (የአብራም ልዕልት) የሚሉ ትርጉሞችን ይዘዋል። ስማቸው ወደ “አብርሃም” እና “ሣራ” መለወጡ የወደፊቱን ሁናቴ ያመላከተ ነበር፡ አብርሃም “የብዙ ሕዝቦች አባት” የሚል ፍቺ ያለው ሲሆን “ሣራ” ደግሞ “ልዕልቲቱ” (የሁሉም ልዕልት) የሚል ትርጉም ይዟል። ከዚህ በተጓዳኝ ይስሐቅ (ይሳቅ [እዚህ ላይ ዕብራይስጥኛው እና አማርኛው ተመሳሳይ ቃልና ፍቺ እንደሚጋሩ ልብ ይሏል]) የሚለው ስም የአብርሃምን ሳቅ የሚያስታውስ ሲሆን (በቅዱሳት መጻሕፍት የሰፈረው የመጀመሪያው ሳቅ፡ ዘፍ. 17፡17)፣ ይህ ሳቅ ጥርጣሬን ወይም ምናልባት፣ መገረምን ያመለክታል። ያም ሆነ ይህ፣ ምንም እንኳ ጌታ በግልጽ የሰጠውን የተስፋ ቃል ቢያምንም፣ አብርሃም በእምነት እና በመታመን ይኖር ዘንድ መታገል ነበረበት።

እንደ አብርሃም ሁሉ እኛም አንዳንዴ ከእንደዚያ ዓይነቱ አለማመን ጋር ትግል ውስጥ ብንገባም፣ በእምነታችን ጸንተን መቀጠል የምንችለው እንዴት ነው?

ግንቦት 3
May 11

የተስፋው ልጅ


የመጨረሻ ትዕይንት የሆነው ግርዘት ሁሉንም ያካተተ ነበር፡ እስማኤል ብቻ ሳይሆን በቅጥሩ የሚገኙ ሁሉ ተገረዙ (ዘፍ. 17፡23-27)። “በሙሉ” ወይም ኮል የተሰኘው ግስ አራት ጊዜ ተደጋግሞ ቀርቧል (ዘፍ. 17፡23፣27)። እንግዲህ ቃል ስለ ተገባለት ወንድ ልጅ ማለትም ስለ “ይስሐቅ” ማረጋገጫ ለመስጠት እግዚአብሔር ለአብርሃም የተገለጠው ከዚህ ሁሉን አካታች ታሪካዊ ዳራ አኳያ ነው።

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፍ. 18፡1-15 እና ሮሜ 9፡9። አብርሃም እንግዶችን በመቀበሉ (በእንግዳ ተቀባይነቱ) ዙሪያ ምን ትምህርት እናገኛለን? እግዚአብሔር ስለ አብርሃም እንግዳ ተቀባይነት የሰጠውን ምላሽ እንዴት ያብራሩታል?



ምንም እንኳ ለእንግዶቹ ባደረገው አቀባበል የታየበት አኳኋን፣ እግዚአብሔር ራሱ አብሯቸው እንደነበር የሚመስል ክስተት የተስተዋለበት ቢሆንም፣ ነገር ግን የእንግዶቹን ማንነት ይወቅ፣ አይወቅ በግልጽ የተቀመጠ ነገር የለም (ዕብ. 13፡2)። “ቀትር ላይ አብርሃም… ድንኳኑ ደጃፍ ተቀምጦ ሳለ” (ዘፍ. 18፡1) በዚያ ጭው ያለ ምድረ በዳ ዕንግዳ የመምጣቱ ጉዳይ እምብዛም ያልተለመደ ከመሆኑ አኳያ፣ ምናልባትም እነዚህን ሰዎች ለመገናኘት ሳይጓጓ እንዳልቀረ ይታመናል። ምንም አንኳ አብርሃም በወቅቱ የ99 ዓመት አረጋዊ ቢሆንም ነገር ግን ወደ ሰዎቹ ተነስቶ እንደ ሮጠ መጽሐፍ ቅዱስ (ዘፍ. 18፡2 [1962 ትርጉም]) ይነግረናል። ከእነዚህ ሰዎች አንደኛውን አዶናይ “ጌታዬ” (ዘፍ. 18፡3) ብሎ የጠራው ሲሆን፣ ይህ የመጠሪያ ማዕረግ እጅግ አልፎ አልፎ ለእግዚአብሔር ይውላል (ዘፍ. 20፡4፣ ዘፀ. 15፡17)። የሚበሉት ምግብ በፍጥነት እንዲዘጋጅላቸው አደረገ (ዘፍ. 18፡6-7)። ከዚያም የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ በትኩረት እየተከታተለ ሊያገለግላቸው አጠገባቸው ቆመ (ዘፍ. 18፡8)። አብርሃም ለእነዚያ ሰማያዊ እንግዶች ያሳየው ባህሪ አነቃቂ ዕንግዳ የመቀበል ተምሳሌት ሆኖ ይኖራል (ዕብ. 13፡2)። እንዲያውም ለእንግዶቹ ያሳየው አክብሮት የእንግዳ ተቀባይነትን ፍልስፍና ይዟል። ለሌሎች አክብሮት ማሳየትና ጥንቃቄ ማድረግ ከመልካም ሥነ ምግባር እና ባህሪ ያለፈ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ዕንግዳ ተቀባይነት ኃይማኖታዊ ግዴታ ስለ መሆኑ አጽንኦት ይሰጣል (ማቴ. 25፡35-40)። የሚገርመው ነገር እግዚአብሔር አበክሮ የሚታወቀው በለጋስነት እንግዶችን በሚቀበለው ሳይሆን፣ ለተራበው እና ለተቸገረው መጻተኛ በሚቸረው ወገን ነው።

በሌላ በኩል የመለኮታዊው ማንነት በሰብዓዊው ግዛት ጣልቃ መግባት፣ እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ያለውን ጸጋ እና ፍቅር ያመለክታል። ይህ አምላካዊ መገለጥ ሰማያዊ ቤቱን ትቶ የሰው አገልጋይ ለመሆን የሚመጣውን ክርስቶስ አስቀድሞ የገለጠ ነበር (ፈልጵ. 2፡7-8)። የእግዚአብሔር በዚህ ስፍራ መገለጥ ለተስፋ ቃሉ እርግጠኝነት ማስረጃ ነው (ዘፍ. 18፡10)። “ከበስተ ጀርባው” (ዘፍ. 18፡10) ራሷን የሸሸገችውን ሣራ እየተመለከተ የነበረው ጌታ በልቧ ውስጥ የነበረውን ሀሳብ ያውቅ ነበር (ዘፍ. 18፡12)። እርሷ እንደ ሣቀች ያውቅ የነበረ ሲሆን፣ “ሣቅሽ” የመጨረሻ ቃሉ ነው። የእርሷ ጥርጣሬ ቃሉን የሚፈጽምበት ስፍራ ይሆናል።

“እግዚአብሔር አበክሮ የሚታወቀው በለጋስነት እንግዶችን በሚቀበለው ሳይሆን፣ ለተራበው እና ለተቸገረው መጻተኛ በሚቸረው ወገን ነው።” በሚል በቀረበው ጽንሰ ሀሳብ ላይ በቂ ጊዜ ይውሰዱ። ይህን ጽንሰ ሐሳብ ማስታወስ ለእኛ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

ግንቦት 4
May 12

ሎጥ በሶዶም


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ከዘፍ. 18፡16 እስከ 19፡29። የአብርሃም ትንቢታዊ አገልግሎት ስለ ሎጥ በነበረው ኃላፊነት ላይ ተጽእኖ የነበረው እንዴት ነው?



አብርሃም ልጅ እንደሚኖረው ዳግመኛ በአምላካዊው የተስፋ ቃል ማረጋገጫ ተሰጥቶታል። ሆኖም በምሥራቹ ከመደሰት ይልቅ ነዋሪነቱ በሶዶም በሆነው ሎጥ ዕጣ ፈንታ ዙሪያ ከእግዚአብሔር ጋር የጋለ ውይይት ውስጥ ሲገባ ይታያል። አብርሃም እግዚአብሔር ፈቃዱን የሚገልጥለት ነቢይ ብቻ አይደም፣ ነገር ግን በእርክስና ስለ ወደቁ የሚማልድ ነቢይ ጭምር ነው። “በእግዚአብሔር ፊት እንደ ቆመ ነበር” (ዘፍ. 18፡22) የተሰኘው የዕብራይስጥ ሃረግ በጸሎት ላይ የሚውል ፈሊጣዊ አነጋገር ነው።

እንዲያውም አብርሃም የወንድሙ ልጅ የሚኖርባትን ሶዶም ከአምላካዊው ቁጣ ለማዳን እግዚአብሔርን ሲገዳደርና ከእርሱ ጋር ሲከራከር ይታያል። አብርሃም ከ50 አንስቶ ቁልቁል እስከ 10 የወረደ ሲሆን፤ 10 ጻድቅ ሶዶማውያን ብቻ ቢኖሩ እግዚአብሔር ሕዝቡን በታደገ ነበር።

ሁለቱ መላእክት ወደ ሎጥ መጥተው ስለሚመጣው ቁጣ ሲያስጠነቅቁት የነበረውን ታሪክ ስናነብ (ዘፍ. 19፡1–10)፣ ሕዝቡ ምን ያህል በኃጢአት ደዌ የተመታና ዕኩይ እንደነበረ ለመመልከት አንቸገርም። በዙሪያቸው እንደነበሩ አያሌ ህዝቦች ሁሉ፣ በእውነትም ስፍራው በእርክስና የተሞላ ነበር። በመጨረሻ ከምድሪቱ እንዲወገዱ የተደረጉበት አንዱ መንስዔ ይኸው ነው (ዘፍ. 15፡16)። “እነሆ የመጨረሻዋ የሰዶም ምሽት እየተቃረበች ነው። የምህረትን ጥሪ አሻፈረኝ ባለችው ከተማ ላይ የበቀል ደመና ጥላውን ቢያሳርፍም፤ ሰዎች ግን ይህን አላስተዋሉም ነበር። መላዕክት የማጥፋት ተልዕኳቸውን ለመፈጸም ወደ ቦታው ሲዳረሱ ሰዎች ግን ብልጽግናንና ደስታን ያልሙ ነበር። የመጨረሻዋ ቀን ልክ ከዚህ ቀደም መጥተው እንዳለፉት ሌሎች ቀናት ነበረች። በፍቅር የተሞላችና ደኅንነቷ የተጠበቀ የሚመስለው ሰዶም ላይ የምሽቱ ሰዓት እየተቃረበ ነበር። በውበቱ አቻ የሌለው የሚመስለው መልክአ ምድር ላይ ፈንጥቆ የነበረው የፀሐይ ጨረር አሁን መደብዘዝ ጀምሮአል። በዚህ ቀዝቀዝ ባለና የተረጋጋ በሚመስለው የምሽት ጊዜ፤ የከተማዋ ነዋሪዎች እና ፈንጠዝያ ወዳድ ህዝቦች ሰዓቷን በደስታ ለማሳለፍ በማሰብ ከአንዱ ቦታ ወደ ሌላው መመላለስ ጀምረዋል።”--የኃይማኖት አባቶችና ነቢያት፡ ገጽ 174።

በመጨረሻ እግዚአብሔር ያዳነው ሎጥን፣ ሚስቱንና ሁለት ሴቶች ልጆቹን ብቻ (ዘፍ. 19፡15) የነበረ ሲሆን፣ ይህ ቁጥር እጅግ ቢያንስ በሚል ከተቀመጠው 10 ጻድቅ ከግማሽ በታች ነበር። ማስጠንቀቂያውን ከቁም ነገር ያልቆጠሩት የሎጥ ሴት ልጆች ዕጮኛዎች፣ በከተማዋ ቀሩ (ዘፍ. 19፡14)።

በመጨረሻ ያቺ ውብ አገር ወደመች። የዕብራይስጡ ግስ ሃፋካ “ገለባበጠው” በዚህ ክፍል ብዙ ጊዜ የተጠቀሰ ሲሆን (ዘፍ. 19፡21፣ 25፣ 29) የሶዶምን ጥፋት ያመለክታል (ዘዳ. 29፡23፣ አሞጽ 4፡11)። ሀሳቡ አገሪቱ “ተገለባበጠች” የሚል እንደሆነ እንመለከታለን። የጥፋት ውሃ ድንግል የነበረውን ተፈጥሮ እንደ “ገለባበጠው” ሁሉ (ዘፍ. 6፡7) የሶዶም ውድመት በኤደን አትክልት ስፍራ የተመሰለውን መልክአ ምድር “የገለባበጠ” ነበር (ዘፍ. 13፡10)። የሶዶም ቅጣት በመጨረሻ ለሚደርሰው ውድመት ምሳሌ ነው (ይሁዳ 7)።

ግንቦት 5
May 13


ተጨማሪ ሀሳብ


“ሕጉና ኪዳናቱ”፡ ምዕራፍ 32 ገጽ፡ 410--የኃይማኖት አባቶችና ነቢያት (ክፍል 1) አብርሃም የሶዶምን ሕዝብ ወክሎ ለእግዚአብሔር ያቀረበው በትዕግሥት የተሞላ ጽኑ ልመና (ዘፍ. 18፡22–33)፣ ምንም እንኳ ተስፋ አስቆራጭ በሆነ የኃጢአት ሁኔታ ውስጥ ያሉ ቢመስሉም፣ ስለ ክፉዎች እንድንጸልይ ሊያበረታታን ይገባል። ከዚህም በላይ እግዚአብሔር ለአብርሃም ችክ ማለት በአጽኖት ስለ ሰጠው ምላሽና “አሥር” ጻድቃን እንኳ ቢገኙ ስለ እነርሱ ይቅር ለማለት ፈቃደኛ መሆኑን መግለጹ “አብዮታዊ” ፅንሰ ሀሳብ ነው ሲሉ ጌርሃርድ ሃስል ይናገራሉ፡

“ ‘ከኑግ ጋር የተገኘህ ሰሊጥ አብረህ ተወቀጥ’ እንዲሉ፣ በጥፋተኛ ማኅበረሰብ መሃል የሚኖረውን ጥፋተኛ ያልሆነ የማኅበረሰብ አባል በአንድ ላይ መጨፍለቅ የተለመደ በነበረበት በጥንቱ የወል አስተሳሰብ ላይ በእጅጉ አብዮታዊ ለውጥ በማምጣት፣ እነሆ ወደ አዲስ ዓይነት አስተሳሰብ እንዲለዋወጥ አድርጓል፡ የትሩፋን ጻድቅ ሕዝቦች መኖር ለአጠቃላዩ ሕዝብ ከጥፋት መትረፍ መንስኤ ሊሆን ይችል ነበር… ስለ ጻድቅ ትሩፋን ሕዝቦቹ ሲል ያሕዌ ከጽድቁ (ጽድቅ፡ በዕብራይስጥም ሆነ በአማርኛ አንድ ዓይነት ቃል እና ፍቺ አለው) የተነሣ የረከሰችውን ከተማ ይቅር ይል ነበር። ይህ አመለካከት ‘ለብዙዎች’ ደኅንነት በሠራው በያሕዌ አገልጋይ ትንቢታዊ ቃላት በስፋት ተገልጾአል።”—Gerhard F. Hasel, The Remnant: The History and Theology of the Remnant Idea From Genesis to Isaiah, 3rd edition (Berrien Springs, MI: Andrews University Press, 1980), pp. 150, 151. “ዛሬ በዙሪያችን ያሉ ነፍሶች ተስፋ ቢስ ሆነው በሰዶም የደረሰው ውድቀት ሲደርስባቸው ይታያል። የአንዳንዶች የምህረት ጊዜ እያበቃ ነው። በመሆኑም ምህረት ከሚሰጥበት ድንበር በየሰዓቱ እያለፉ ነው። ለመሆኑ ኃጢአተኛውን ከአስፈሪ ሁኔታ እንዲሸሽ የሚያስችሉት የሰብዓዊው የማስጠንቀቂያ ድምጾች የታሉ? ከሞት ሊመልሱ የተዘረጉት ሰብዓዊ እጆችስ? ስለሚጠፉት ግድ ብሎአቸው እግዚአብሔርን በትህትና እና በእምነት በመለማመን ላይ ያሉት ወገኖችስ የታሉ? የአብርሃም መንፈስ የክርስቶስ መንፈስ ነበር። በኃጢአተኛው ቦታ ሆኖ የሚማልደው ታላቁ አማላጅ እራሱ የእግዚአብሔር ልጅ ነው። ለሰብዓዊው ፍጡር ደኅንነት ዋጋ የከፈለው አዳኝ የሰውን ነፍስ ዋጋ ያውቃል።”-የኃይማኖት አባቶችና ነቢያት፡ ገጽ 152።


የመወያያ ጥያቄዎች



1. “የቃል ኪዳኑ ምልክት” ተብለው የተጠሩ ቀስተ ደመና እና ግርዘት ብቻ ናቸው። በሁለቱ ቃል ኪዳኖች መካከል ያሉ የጋራ ነጥቦችና ልዩነቶች ምንድን ናቸው?

2. ምንም እንኳ አብርሃም በእግዚአብሔር የተጠራ ቢሆንም እንዲሁም በእምነት መኖር ምን ማለት እንደሆነ አስመልክቶ በአዲስ ኪዳን ምሳሌ ሆኖ ቢቀርብም፣ አልፎ አልፎ አብርሃም መደናቀፍ ገጥሞት ነበር። ከእርሱ ምሳሌ የምንማረው ምንድን ነው? የማንማረውስ?

3. አንዳንድ ሰዎች እግዚአብሔር የጠፉትን ይቀጣል የሚለውን ጽንሰ ሀሳብ በመቃወም ይከራከራሉ። ለዚህ እንደ ምክንያት የሚያቀርቡት--እግዚአብሔር ፍቅር ነው የሚለውን መርኅ ይጻረራል የሚል ነው። ነገር ግን እኛ፣ አዎ፣ እግዚአብሔር የጠፉትን ይቀጣል ብለን የምናምን ከላይ ለቀረበው መከራከሪያ ምን ዓይነት ምላሽ እንሰጣለን?




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA union SSL