የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ዘፍ. 9:18–11:9፣ ሉቃ. 10:1፣ ማቴ. 1:1–17፣ ሉቃ. 1:26–33፣ መዝ. 139:7–12፣ ዘፍ. 1:28፣ ዘፍ. 9:1.
የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ “እግዚአብሔር በዚያ የመላውን ዓለም ቋንቋ ስለ ደበላለቀ የከተማይቱ ስም ባቤል ተባለ። ከዚያም እግዚአብሔር ሰዎቹን በምድር ሁሉ በተናቸው።” (ዘፍ. 11፡9)።
ከ
ጥፋት ውሃ በኋላ፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊው ዘገባ ትኩረቱን ከአንድ
ግለሰብ (ኖኅ) አንሥቶ ወደ ሦስቱ ልጆቹ ማለትም “ሴም፣ ካምና
ያፌት” ላይ ያደርጋል። የከነዓን አባት ለሆነው ካም የተሰጠው ልዩ
ትኩረት (ዘፍ. 10፡6፣15)፣ የተስፋይቱ ምድር የሆነችውን “ከነዓን” (ዘፍ. 12፡
5)፣ ይኸውም በእርሱ አማካይነት ሕዝቦች ሁሉ እንደሚባረኩ (ዘፍ. 12፡3)
ተስፋ የተደረገውን አብርሃማዊ ጽንሰ ሀሳብ ያስተዋውቃል።
ይሁን እንጂ መስመሩ በባቤል ግንብ አማካይነት ተሰበረ (ዘፍ. 11፡1-9)።
እግዚአብሔር ለሰው ልጆች የነበረው ዕቅድ አሁንም በድጋሚ ተፋለሰ።
በረከት ተብሎ የታሰበው የሕዝቦች ዳግም ውልደት ለሌላ እርግማን ምክንያት
ሆነ። ሕዝቦች የእግዚአብሔርን ቦታ ለመያዝ ባደረጉት መፍጨርጨር ግንባር
ፈጠሩ። እግዚአብሔርም የፍርድ ምላሽ ሰጣቸው። ይህን ተከትሎ በተፈጠረው
ግራ መጋባትና ውዥንብር ሕዝቡ በምድር ዙሪያ እንዲበተን ሆነ (ዘፍ. 11፡8)።
ይህ ክስተት እግዚአብሔር ቀደም ሲል “ምድርንም ሙሏት” (ዘፍ. 9፡1) ሲል
የተናገረውን ዕቅድ ወደ ፍጻሜ ያመጣ ነበር።
በመጨረሻ፣ ሰው በክፋት የተሞላ ቢሆንም እግዚአብሔር ግን ክፉውን
ወደ በጎ ይቀይራል። እርሱ እንደ ሁልጊዜውም የመጨረሻ ቃል አለው። ካም
በአባቱ ድንኳን የደረሰበት እርግማን (ዘፍ. 9፡21-22) እና በባቤል ግንብ
እርግማን የተቀበለው ሕዝብ (ዘፍ. 11፡9) ውሎ አድሮ የአምላካዊው በረከት
ተቋዳሽ ሆነ።
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፍ. 9፡18-27። ይህ ዕንግዳ ታሪክ ምን መልእክት ይዟል?
ኖኅ በወይን እርሻው ያደረገው ነገር፣ አዳም በኤደን የአትክልት ስፍራ
ያደረገውን ያስተጋባ ነበር። ሁለቱ ታሪኮች የጋራ ጭብጥ ይዘዋል፡ ከፍሬው
መብላትና እርቃን መሆን--እርቃንን መሸፈን--እርግማን--በመጨረሻም
በረከት መቀበል። ኖኅ ከአዳማዊ ሥሩ ጋር ዳግመኛ ትስስር ቢፈጥርም፣
በሚያሳዝን ሁኔታ ያው የውድቀት ታሪክ ይቀጥላል።
የወይን ፍሬውን ማብላላትና ወደሚያሰክር መጠጥነት መቀየር፣ የቀደመው
አምላካዊ የፍጥረት ሥራ አካል አልነበረም። ኖኅ ራሱን መግዛትና መቆጣጠር
ስለ ተሳነው ዕርቃኑን ተኛ። ካም የአባቱን እርቃነ ሥጋ “አየ” በሚል የቀረበው
አገላለጽ፣ ሔዋን የተከለከለውን ዛፍ ፍሬ--አየች--(ዘፍ. 3፡6) ወደሚለው
ይጠቁመናል። ካም የአባቱን ምስጢራዊ አካል እንደው በአጋጣሚ ብቻ
አለማየቱን ይህ በሁለቱ መካከል ያለ መመሳሰል ፍንጭ ይሰጠናል። ለአባቱ
ችግር ቅንጣት ታክል መፍትሔ ለመፈለግ እንኳ ሳይሞክር ወሬውን ለማዳረስ
ወጣ። በአንጻሩ፣ ካም ዕርቃኑን ትቶት የሄደውን አባታቸውን ለመሸፈን
ወንድሞቹ ያሳዩት ፈጣን ምላሽ፣ የካምን ድርጊት ያለማወላወል ያወገዘ ነበር።
በዚህ ስፍራ የቀረበው ጉዳይ በአብዛኛው ወላጅን ስለ ማክበር ይመለከታል።
የቀደመውን ታሪክ የሚወክሉትን ወላጆች አለማክበር በወደፊት ሕይወት
ላይ መሰናክል ይፈጥራል (ጥቅሶቹን ያስተያዩ፡ ዘፀ. 20፡12 እና ኤፌ. 6፡2)።
በመሆኑም እርግማኑ በካም ብሎም በልጁ ከንዓን የወደፊት ሕይወት ላይ
ተጽእኖ ይኖረዋል።
ዘረኝነት የተጸናወተውን ንድፈ ሀሳብ ለማቀንቀን ይህን ጥቅስ ጥቅም ላይ
ለማዋል መሞከር፣ ግዙፍ የመንፈሳዊ አስተምህሮ ህጸጽ ከመሆኑ በተጨማሪ
ሥነ ምግባራዊ ወንጀልም ነው። ትንቢቱ በተለይ የካም ልጅ በሆነው ከነዓን
ላይ የተወሰነ ነበር። ይህን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ዘገባ በብዕሮቹ ያሰፈረው ጸሐፊ፣
አንዳንዶቹ የከነዓናውያን ምግባረ ብልሹ ልማዶች ወደ አእምሮው ሳይመጡ
እንዳልቀሩ ይታመናል (ዘፍ. 19፡5-7፣ 31-35)።
ከስያሜው አኳያ ብንሄድ፣ “ካና” ከተሰኘ ግስ የወጣው “ከነዓን”—
“በቁጥጥር ስር ማስገዛት” የሚል ፍቺ አለው። ይህ ደግሞ እርግማኑ የበረከት
ተስፋ ጭምር መያዙን ያሳያል። የሴም ዝርያ የሆኑት የእግዚአብሔር ሕዝቦች
ወደ ተስፋይቱ ምድር ገብተው እየመጣ ለነበረው መሲሕ መንገድ ያዘጋጁት
ከነዓንን በቁጥጥር ስር በማስገባት ሲሆን፣ የያፌት ግዛት ደግሞ “በሴም
ድንኳኖች” ይሰፋል (ዘፍ. 9፡27)። ይህ እስራኤል ለዓለም የምታካፍለውን
የመዳን መልእክት አቅፎ ከያዘው፣ አምላካዊው ኪዳን ወደ ሁሉም ሕዝቦች
ከሚስፋፋበት የትንቢት ሁኔታ ጋር ይያያዛል (ዳን. 9፡27፣ ኢሳ. 66፡18-20፣
ሮሜ 11፡25)። የካም መረገም፣ በጌታ የቀረበላቸውን ደኅንነት የሚቀበሉትን
ማናቸውንም የካምም ሆነ የከነዓን ዘሮች ጨምሮ እንደውም ለሁሉም ሕዝቦች
በረከት ይሆናል።
የግዙፉ ጥፋት ውሃ “ጀግና” የሆነው ኖኅ፣ በወይን ጠጅ ተረታ ማለት
ነው? ይህ እኛ ሁላችን ምን ያህል እንከን እንደማያጣን እና አምላካዊው
ጸጋ በየጊዜው የሚያስፈልገን ስለመሆኑ ምን ሊነግረን ይገባል?
ኖኀ ለቅድመ ጥፋት ውሃ እና ድኅረ ጥፋት ውሃ ሥልጣኔ እንደ አገናኝ ድልድይ
ሆኖ ያገለግላል። ለዚህም በእርሱ ዘመን ዙሪያ የነበረውን ክስተት የሚያወሱ
መረጃዎች ግንዛቤ ይሰጡናል። በመጨረሻዎቹ ሁለት ጥቅሶች የምናገኘው
ታሪክ (ዘፍ. 9፡28-29) ከኋለኛው የአዳም ትውልድ ዘመን ጋር ያስተሳስረናል
(ዘፍ. 5፡32)። አዳም የሞተው የኖኅ አባት፣ ላሜህ 56 ዓመት ሲሞላው ስለነበር፣
ኖኅ ስለ አዳም የተነገሩ ታሪኮችን በትክክል ሰምቷል ተብሎ ይታመናል። ይህን
ታሪክ ደግሞ ከጥፋት ውሃ በፊትም ሆነ በኋላ ላሉ ትውልዶቹ ሊያስተላልፍ
ይችላል።
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፍ. ምዕ. 10። የዚህ የዘር ሐረግ በመጽሐፍ
ቅዱስ መስፈር ዓላማው ምንድን ነው? (ሉቃ. 3፡23-38)
መጽሐፍ ቅዱሳዊው የዘር ሐረግ ሦስት ተግባሮች አሉት። በመጀመሪያ-በተጨባጭ ከኖሩና ከሞቱ እንዲሁም ቀኖቻቸው በትክክል ከተቆጠሩ
ሰዎች ጋር ዝምድና ለሚፈጥሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ክስተቶች ታሪካዊ ባህሪያት
አጽንኦት ይሰጣል። ሁለተኛ--ከጥንት ጀምሮ ጸሐፊው እስከሚገኝበት ዘመን
ያለውን ተያያዥነት ያሳያል፣ ደግሞም ቀደም ብሎ ከነበረው ጸሐፊ ጋር ግልጽ
ትስስር ይፈጥራል። ሦስተኛ፡--የሰውን ዘር ደካማነት፣ የኃጢአት እርግማን
ያስከተለውን አሳዛኝ ውጤት እና በቀጣይ ትውልዶች ላይ ያስከተለውን ገዳይ
ውጤት ያስታውሰናል።
እዚህ ላይ የ “ካም”፣ “ሴም” እና “ያፌት” የዘር ሃረግ ምደባ ግልጽ የሆኑ
መመዘኛዎችን እንደማይከተል ልብ ማለቱ ተገቢ ነው። ወደ ግብፅ የወረደው
የያዕቆብ ቤተሰብ ቁጥር 70 ነበር (ዘፍ. 46፡27) እንዲሁም በእስራኤል የምድረ
በዳ ጉዞ 70 የእስራኤል አለቆች ነበሩ (ዘፀ. 24፡9)። በ70ዎቹ የቤተሰብ አባላት
እና በ70ዎቹ አለቆች መካከል ያለው የጥምረት ጽንሰ ሀሳብ፣ እስራኤል እንደ
ሕዝብ ያላትን ተልዕኮ ይጠቁማል። “ልዑል ለአሕዛብ ርስታቸውን በሰጠ ጊዜ፣
የሰውንም ዘር በለያየ ጊዜ፣ በእስራኤል ልጆች ቁጥር ልክ፣ የአሕዛብን ርስት
ድንበር ለየ” (ዘፀ. 32፡8)።
ይህ መረጃ በአዳም እና በኃይማኖት አባቶች መካከል ያለውን ቀጥተኛ
ግንኙነት ያሳየናል። እነዚህ ሁሉ ከአዳም አንስቶ ታሪካቸው በተጨባጭ
የተዘገበና በገሃድ የኖሩ ሰዎች ናቸው። የኃይማኖት አባቶች ከእነዚያ
ጥንታዊ ክስቶች ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት የነበራቸውና በግል ምስክር ሆነው
እንዳለፉባቸው በተጨማሪ እንድናስተውል ይረዳናል።
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ማቴ. 1፡1-17። እነዚህ ሁሉ ሰዎች ምን
ያህል የታሪክ አካል እንደነበሩ አስመልክቶ ይህ ምን ያስተምረናል?
ሰዎቹ በተጨባጭ ኖረው ያለፉ መሆናቸውን ማወቅና ማመን
ለእምነታችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድነው?
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፍ. 11፡1-4። የ“ምድር ሁሉ” (1962 ትርጉም) ሕዝቦች አንድነት ለማምጣት ከፍተኛ ጉጉት የነበራቸው ለምንድን ነው?
“ምድርም ሁሉ” የሚለው ሐረግ ከጥፋት ውሃ በኋላ በሕይወት የነበሩትን
ጥቂት ሰዎች ያመለክታል። ሰዎቹ የተሰባሰቡበት ምክንያት በግልጽ
ተጠቁሟል፡ ሰማይ የሚደርስ ግንብ ለመገንባት (ዘፍ. 11፡4)። እንደውም
እውነተኛ ዓላማቸው የራሱን፣ ፈጣሪ የሆነውን አምላክ ስፍራ መውሰድ ነው።
የሕዝቡ ሃሳብና ተግባር የተገለጠበት መንገድ በፍጥረት ዘገባ ቀርቦ የነበረውን
አምላካዊ ሃሳብና ድርጊት ያስተጋባ ነበር። “ተባባሉ” (ጥቅሶቹን ያስተያዩ፡
ዘፍ11፡3-4 እና ዘፍ. 1፡6፣ 9፣ 14 ወዘተ)፣ “እንሥራ” (ዘፍ. 11፡3-4 እና ዘፍ.
1፡26)። ዓላማቸው ግልጽ ሆኖ ቀርቧል፡ “‘ለስማችን መጠሪያ እንዲሆን’”
(ዘፍ. 11፡4)። ይህ ደግሞ ለእግዚአብሔር አምላክ ብቻ ጥቅም ላይ የሚውል
መግለጫ ነው (ኢሳ. 63፡12-13)።
በአጭሩ የባቤል ግንበኞች ፈጣሪ የሆነውን አምላክ የመተካት የተዛባ ምኞት
አንጸባርቀው ነበር። (የዚህ ጎትጓች ማን እንደሆነ እናውቅ የለ? ኢሳ. 14፡
14)። የጥፋት ውሃ ትውስታ ለዚህ ፕሮጀክታቸው ትልቅ ሚና እንደ ነበረው
ምንም ጥርጥር የለውም። እግዚአብሔር ዳግመኛ ምድር ላይ የጥፋት ውሃ
እንደማያመጣ ኪዳን ቢገባም፣ እነርሱ ግን ከሌላ የጥፋት ውሃ ለመትረፍ ግዙፍ
ግንብ ገነቡ። ከባቤል (ባቢሎን) ከተማ ግንባታ ጋር በተያያዘ፣ ምንም እንኳ
ከጥቅም ውጭ ቢሆንም፣ የጥፋት ውሃ ትውስታ በባቢሎናውያን ባህል ውስጥ
ተጠብቆ ቆይቷል። ይህ ወደ ሰማይ ለመድረስና የአምላክን ስፍራ ለመንጠቅ
የሚደረግ ጥረት በእርግጥም ቀንደኛውን የባቢሎን መንፈስ ያሳያል።
የባቤልን ግንብ ታሪክ፣ በተመሳሳይ በዳንኤል መጽሐፍ አስፈላጊ ጭብጥ
ሆኖ የምናገኘው ለዚህ ነው። የባቤልን ግንብ ታሪክ ስለሚያስተዋውቀው
ሰናዖር (ዘፍ. 11፡2) የቀረበው ማጣቀሻ፣ በዳንኤል መጽሐፍ መጀመሪያ ላይ
ናቡከደነፆር የየሩሳሌምን ቤተ መቅደስ ዕቃዎች ያመጣበትን ቦታ ለማመልከት
እንደገና ተጠቅሷል (ዘፍ. 1፡2)። በመጽሐፉ ውስጥ ከሚገኙ ሌሎች በርካታ
መልእክቶች መካከል፣ ናቡከደነፆር የወርቁን ምስል ያቆመበት ክፍል በዚያው
“ሜዳ” መሆኑ፣ ምናልባት በአእምሮ ላይ ያለውን ተጽእኖ በግሩም ሁኔታ
የሚያሳይ ምሳሌ ሆኖ እናገኘዋለን። ምንም እንኳ እንደ ባቤል ሁሉ ይሄኛውም
ሙከራ ቢሰናከልም፣ ነገር ግን የምድር ሕዝቦች በእግዚአብሔር ላይ
ግንባር በመፍጠር በአንድ ላይ ለመሰባሰብ የሚያደርጉትን ሙከራ ዳንኤል
የጨረሻውን ዘመን አስመልክቶ በተሰጠው ራእይ ተመልክቷል (ዳን. 2፡43፣
ዳን. 11፡43-45--ያስተያዩ፡ ራእ. 16፡15-16)።
ታላቁ የሰው ልጆች ዓላማ “አምላክ ለመሆን” መፍጨርጨር
ነው--ሲል አንድ ያለፈው ምዕተ ዓመት ዝነኛ ዓለማዊ፣ ፈረንሳዊ
ጸሐፊ ተናግሯል። ከኤደኗ ሔዋን ጀምሮ (ዘፍ. 3፡5) በዚህ
አደገኛ ውሸት የምንማረክበት ጉዳይ ምንድን ነው?
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፍ. 11፡5-7 እና መዝ. 139፡ 7-12። እግዚአብሔር ለምን ወደዚህ ምድር ወረደ? ለዚህ መለኮታዊ ምላሽ ያነሳሳው ክስተት ምንድን ነው?
ሰዎቹ ወደ ላይ እየወጡ የነበረ ቢሆንም፣ አምላክ ግን ወደ እነሱ መውረድ
ነበረበት። የእግዚአብሔር መውረድ የእርሱ የበላይነት ማረጋገጫ ነው።
እግዚአብሔር ሁሌም ከሰብዓዊው አቅምና ግስጋሴ በላይ ነው። እርሱ
ወዳለበት ለመውጣትና በሰማይ ለመገናኘት የሚደረግ ማንኛውም ሰብዓዊ
ሙከራ ከንቱ መጃጃል ነው። የሱስ ወደዚህ ምድር የመጣበት ምክንያት እኛን
ለማዳን መሆኑ አያጠያይቅም። እርሱ እኛን ሊያድን የሚችልበት ሌላ አንዳች
መንገድ አልነበረም።
“ሰዎቹ ይሠሩ የነበሩትን ከተማና ግንብ ለማየት” (ዘፍ. 11፡5) በሚል
እግዚአብሔር የተናገረው ቃል በእጅጉ ምጸታዊ ነው። እግዚአብሔር ያን
ለማየት መምጣት የማያስፈልገው ቢሆንም (መዝ. 139፡7-12 ያስተያዩ፡ መዝ.
2፡4) ሆኖም ግን አደረገው። ይህ ጽንሰ ሀሳብ እግዚአብሔር ከሰው ልጆች ጋር
ላለው መስተጋብር አጽንኦት ይሰጣል።
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ሉቃ. 1፡26-33። ይህ፣ እግዚአብሔር ወደ
እኛ ስለመውረዱ ምን ያስተምረናል?
የእግዚአብሔር መውረድ የጽድቅ በእምነት መርኅን እና የአምላካዊውን ጸጋ
ሂደትም እንዲሁ ያስታውሰናል። ለእግዚአብሔር የትኛውንም ሥራ ብንሠራም
እንኳ፣ እኛን ለመገናኘት መምጣቱ የግድ ይሆናል። እኛን ወደ እርሱ እና
ወደ መቤዠት የሚያመጣን ለእግዚአብሔር የምናደርገው ነገር አይደለም።
ይልቁንም እኛን የሚያድነን እግዚአብሔር ወደ እኛ የሚያደርገው እንቅስቃሴ
ነው። እንዲያውም በዘፍጥረት ከአንዴም ሁለቴ ስለ “መውረድ” የሚናገር
ሲሆን፣ ይኸውም በስፍራው እየሆነ የነበረው ነገር ምን ያህል እንዳሳሰበው
የሚያመላክት ይመስላል።
በጥቅሱ መሠረት ጌታ ሥር የሰደደ አንድነታቸውን ወደ ፍጻሜ ለማምጣት
ፈለገ። ምክንያቱም የወደቀ ማንነታቸው ሊያመራ የሚችለው ወደ ባሰ ክፉ
ድርጊት ብቻ በመሆኑ ነው። ግንባር የፈጠረ ሴራቸውን ወደ ፍጻሜ በማምጣት
ቋንቋቸውን ለማደበላለቅ የመረጠው በዚህ የተነሣ ነበር።
“የባቤል ገንቢዎች እቅድ በሐፍረት እና በሽንፈት ተጠናቀቀ። የኩራታቸው
ሐውልት የሞኝነታቸው ማስታወሻ ሆነ። ይሁን እንጂ ሰዎች ያለማቋረጥ ይህን
ተመሳሳይ መስመር በመከተል በራሳቸው እየታመኑ--የእግዚአብሔርን ሕጐች
አለመቀበላቸውን ገፍተውበታል። ይህ መርኅ ሰይጣን በሰማይ ውስጥ
ሊተገብረው የሞከረ ሲሆን ቃየንም መሥዋእቱን ባቀረበበት ወቅት ይኸው
መርኅ ገዝቶታል።” (የኃይማኖት አባቶችና ነቢያት፡ ገጽ 131)
ሌላውን ዓይነት ከመጠን ያለፈ መኩራራት ወይም ግብዝነት
ተከትሎት የሚመጣውን የውድቀት ምሳሌ በባቤል ታሪክ እንዴት
መመልከት እንችላለን?
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፍ. 11፡8-9፣ ዘፍ. 9፡1 ከሚከተለው ጋር ያስተያዩ፡ ዘፍ. 1፡28። እግዚአብሔር ሕዝቡን በምድር መበተኑ መዋጀት ያስገኘው ለምንድን ነው?
እግዚአብሔር “ ‘ብዙ ተባዙ ምድርንም ሙሏት’ ” (ዘፍ. 9፡1፣ ዘፍ. 1፡28) ሲል
ለሰው ልጆች ያለውን ዕቅድ እና በረከት አመለከተ። የባቤል ግንበኞች ግን
ከአምላካዊው ዕቅድ በተቃራኒ እንደ አንድ ዓይነት ሕዝብ በአንድ ላይ ለመጣበቅ
መረጡ። ከተማዋን ለመገንባት የፈለጉበት አንዱ ምክንያት “በምድር ላይ
እንዳንበተን” (ዘፍ. 11፡4) ከሚል እሳቤ ነበር። ምናልባት አንድ ላይ መሆናቸው
ከመለያየታቸውና ከመበታተናው ይልቅ ኃይለኛ እንደሚያደርጋቸው ስላሰቡ፣
በየቦታው ለመበታተን ፈቃደኞች ሳይሆኑ እንዳልቀሩ ይታመናል። ደግሞም
በአንድ በኩል ሲታይ ትክክል ነበሩ።
የሚያሳዝነው የተባበረ ኃይላቸውን ለበጎ ሳይሆን ለክፋት ሊጠቀሙበት
መፈለጋቸው ነበር። “ ‘ለስማችን መጠሪያ እንዲሆን’ ” ብለው መነሣታቸው፣
በውስጣቸው ያለውን እብሪትና መታበይ በጉልህ ያንጸባርቃል። ሰዎች
እግዚአብሔርን በግልጽ በመቃወም ለራሳቸው “ስም መጠሪያ” ለማቆም በሚፈልጉ
ጊዜ፣ መጨረሻው መልካም ሊሆን እንደማይችል እርግጠኞች መሆን እንችላለን።
በመሆኑም እግዚአብሔር ፍጹም እምቢተኝነታቸው ላይ ፍርድ በመስጠት
እነሆ “በምድር ሁሉ ላይ በታተናቸው” (ዘፍ. 11፡9)። በዚህም እንዲደርስባቸው
ያልፈለጉት ነገር ደረሰባቸው።
በጣም የሚገርመው፣ “የእግዚአብሔር በር” የሚል ፍቺ ያለው ባቤል--ባላል
ከተሰኘው ግስ ጋር ዝምድና አለው። ባላል “ድብልቅልቅ” (ዘፍ. 11፡9) የሚል
ትርጉም አለው። ወደ እግዚአብሔር “ደጅ” ለመድረስ ስለ ፈለጉ እና ራሳቸውን
እንደ አምላክ ስለቆጠሩ፣ መጨረሻቸው መደበላለቅና ከቀድሞው በጣም ባነሰ
አቅም መወሰን ሆነ።
“የባቤል ሰዎች ከእግዚአብሔር የተነጠለ መንግሥት ለመመስረት ቆርጠው
ነበር። ይሁን እንጂ ከመካከላቸው ጌታን የሚፈሩ የተወሰኑ ሰዎች ቢኖሩም
በከሃዲዎች አስመሳይነት ተታለው በወጥመዳቸው ገብተዋል። ለእነዚህ
ታማኞች ሲል ብቻ ጌታ ፍርዱን በማዘግየት ሰዎች የራሳቸውን እውነተኛ ባህሪ
እንዲያንፀባርቁ ጊዜ ሰጣቸው። ሁኔታው እየሰከነ ሲመጣ የእግዚአብሔር
ልጆች ታማኝ ያልሆኑት ህዝቦች ከሚከተሉት የተሳሳተ አካሄድ ሊመልሷቸው
ጥረት ቢያደርጉም ነገር ግን
ሰማይን በሚዳፈረው እንቅስቃሴያቸው ገፍተውበት ነበር። የሚሠሩት ሥራ
ታልፎ ቢሆን ኖሮ ዓለምን ገና በጨቅላነቷ ሞራል ዐልባ ባደረጓት ነበር።
የእነርሱ የትብብር መንፈስ የተመሰረተው በአመፅ ላይ ነው፤ ራስን ከፍ
አድርጐ ለማሳየት
በሚቋቋም አገዛዝ ውስጥ እግዚአብሔር ምንም ዓይነት ድርሻ ወይም ክብር
አይሰጠውም ነበር።”--(የኃይማኖት አባቶች እና ነቢያት፡ ገጽ 130)
ለገዛ ራሳችን “ስም ማስጠሪያ” የማቆም መሻት እንዳይኖር
ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ያለብን ለምንድን ነው?
ኤለን ጂ. ኋይት፣ “የባቤል ግንብ” ገጽ፡ 125-132--የኃይማኖት
አባቶችና ነቢያት።
“በዚህ ቦታ ላይ ከተማ ለመመስረት እና በከተማዋ ውስጥ ደግሞ ዓለምን
የሚያስደምም ከፍታ ያለው ማማ ለመሥራት ወሰኑ። እነዚህ ተግባራት ሕዝቡ
ተበታትኖ እንዳይሰፍር ለማድረግ የታለሙ ነበሩ። እግዚአብሔር ሰዎች በምድር
ዙሪያ እንዲሰራጩ እና እንዲቆጣጠሩት ያዘዘ ቢሆንም እነዚህ የባቤል ገንቢዎች
ግን ማኀበረሰባቸውን በአንድ አካል ውስጥ አዋህደው ለመያዝ እና መላው
ምድርን የማቀፍ አቅም ያለው ንጉሣዊ ቤተሰብ ለመመሥረት ቆርጠው ነበር።
በመሆኑም ከተማቸው የዓለም አቀፍ ኢምፓየር መዲና ስለምትሆን ሞገሷ
የዓለምን አድናቆት እና ክብር ከማግኘቱም ባሻገር ለመሥራቾቹ ዝናን ያጎናፅፋል።
እስከ ሰማይ የሚደርሰው እፁብ ድንቅ ማማ የገንቢዎቹን ኃይል እና ብልሀት
የሚያሳይ ሐውልት ሆኖ እንዲቆምና የእነርሱንም ዝና በቅርብ ላሉ ትውልዶች
እንዲያስተላልፍ የታለመ ነበር።
“በሰናዖር ሜዳ ላይ የሚኖሩ ሰዎች እግዚአብሔር በምድር ላይ ድጋሚ ጐርፍ
እንደማይልክ የገባውን ቃል ኪዳን አያምኑም ነበር። አብዛኞቹ የእግዚአብሔርን
ሕልውና የማይቀበሉ እና የጎርፉ መንስኤ ተፈጥሮአዊ ክስተት ነው ብለው
የሚያምኑ ነበሩ። ሌሎች ደግሞ ልዕለ ኃያል የሆነ አካል እንዳለ በመቀበል፤
የጐርፍ ጥፋት ከመምጣቱ አስቀድሞ የነበረውን ዓለም ያወደመው እርሱ እንደሆነ
የሚያምኑ ሲሆን ልክ እንደ ቃየን ሁሉ የእነርሱም ልብ በእግዚአብሔር ላይ ሸፈተ።
ግንቡ ከሚገነባበት ዓላማዎች አንዱ ሌላ የጎርፍ መጥለቅለቅ ቢኖር ደኅንነታቸውን
ለማስጠበቅ እንዲችሉ ነበር። የግንባታው መዋቅር የጐርፍ ውሃ ከሚደርስበት
ከፍታ በላይ እንዲሠራ በማድረግ ከማንኛውም አደጋ እርቀናል የሚል አስተሳሰብ
ያዙ። ወደ ደመና ክልል ለመውጣት ስለሚችሉም የጎርፉን መንስኤ ለማረጋገጥ
ተስፋ አደረጉ። አጠቃላዩ እንቅስቃሴ ዓላማው የእቅድ አውጪዎቹን ክብር
ይበልጥ ለማሞገስ እና የመጪ ትውልዱን አዕምሮ ከእግዚአብሔር በማራቅ ወደ
ጣኦት አምላኪነት ለመምራት ነው።” (የኃይማኖት አባቶችና ነቢያት፡ ገጽ፡ 127128)።
1. ለገዛ ራሳቸው ስም ማስጠሪያ ለማትረፍ በሚጥሩ ሰዎች ላይ
ሊመጣ የሚችለውን ችግር፣ ከታሪክ አልፎ ተርፎም ከዚህ ምን
ዓይነት ምሳሌ እናገኛለን?
2. እንደ ቤተ ክርስቲያን፣ ሳናስተውለውም እንኳ ቢሆን፣
የራሳችንን የባቤል ግንብ ለመሥራት ከመፈለግ አደጋ ማምለጥ
የምንችለው እንዴት ነው? አንዳንዴ ብዙም ልብ ሳንል ይህን
ለማድረግ የምንጥርባቸው መንገዶች ምንድን ናቸው?