የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ዘፍ. 6:13–7:10፣ 2ጴጥ. 2:5–9፣ ዘፍ. 7፣ ሮሜ 6:1–6፣ መዝ. 106:4፣ ዘፍ. 8፣ ዘፍ. 9:1–17።
የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ “ ‘ልክ በኖኅ ዘመን እንደሆነው የሰው ልጅ መምጣትም እንደዚሁ ይሆናል’ ” (ማቴ. 24፡37)።
“እ
ግዚአብሔር አምላክ የሰው ዐመፅ በምድር ላይ የበዛና የልቡም
ሐሳብ ዘወትር ወደ ክፋት ብቻ ያዘነበለ መሆኑን ተመለከተ”
(ዘፍ. 6፡5)። “ተመለከተ” የሚለው ግስ አንባቢውን ወደ
እያንዳንዱ የቀደመ አምላካዊ የፍጥረት ሥራ ቅደም ተከተል ይመልሰዋል።
ሆኖም እግዚአብሔር አሁን የሚመለከተው “መልካም” (ቶቭ) ሳይሆን
“ክፋት”(ራኣ) (ዘፍ. 6፡5) ነው። በመሆኑም አሁን “ክፋት” የተሞላውን ዓለም
ሲመለከት እግዚአብሔር ምድርን በመፍጠሩ የተጸጸተ ይመስላል።
ይህም ሆኖ፣ እግዚአብሔር የተሰማው የጸጸት ስሜት የደኅንነት አላባዎችንም
ያካተተ ነበር። “አዘነ” (ናክሃም) የሚለው የዕብራይስጥ ቃል “እግዚአብሔር
በረገማት ምድር ከልፋታችንና ከጉልበታችን ድካም ያሳርፈናል” በሚለውና
መጽናናት የሚል ፍቺ ባለው የኖኅ (ኖሃክ) ስም ውስጥ አስተጋብቷል። ስለዚህ
እግዚአብሔር ለዚህ ክፋት የሚሰጠው ምላሽ ሁለት ገጽታዎች አሉት። በሰዎች
ላይ ውድመት ሊያደርስ የሚችል የፍትሕ ስጋት እና ሰዎችን ወደ ደኀንነት
ጎዳና የሚመራ የመጽናናትና የምኅረት የተስፋ ቃል።
ይህ ሁለቱን በአንድ የያዘ “ድርብ ድምፅ” በቃየን እና በአቤል/ሴት ቀደም ሲል
ተሰምቶ የነበረ ሲሆን፣ በሴት (በእግዚአብሔር ወንዶች ልጆች) እና በቃየን
(በሰዎች ወንዶች ልጆች) የዘር ሃረጎች መካከል በነበረው ልዩነት ተደግሞ
ነበር። አሁንም እንደገና እግዚአብሔር በኖኅ እና በተቀረው ሰብዓዊ ዘር
መካከል ያለውን ልዩነት ሲያቀርብ በድጋሚ እንሰማዋለን።
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፍ. 6፡13-7፡10። ከዚህ አስደናቂ የቀደመ የሰው ልጅ ታሪክ ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን?
እንደ ዳንኤል ሁሉ ኖኅ የዓለምን ፍጻሜ የሚተነብይ ነቢይ ነው። “መርከብ”
(ቴቫህ) የተሰኘው የዕብራይስጥ ቃል (ዘፍ. 6፡14) እስራኤልን ከግብፅ
የሚያድነው ህጻኑ ሙሴ ተደብቆ በዓባይ ላይ የሰፈፈበትን ቅርጫት
ለማመልከት ጥቅም ላይ የዋለ፣ እምብዛም ያልተለመደ ተመሳሳይ የግብፅ
የውሰት ቃል ነው (ዘፀ. 2፡3)።
እንዲሁም አንዳንዶች አጠቃላዩ የመርከቡ አወቃቀር ከማደሪያው ታቦት ጋር
የሚመሳሰል መሆኑን ተመልክተዋል (ዘፀ. 25፡10)። መርከቡ የሰው ልጆች
በሕይወት እንዲተርፉ እንደሚያስችል ሁሉ፣ የእግዚአብሔር በሕዝቡ መካከል
መገኘት ምልክት የሆነው የምስክሩ ታቦትም (ዘፀ. 25፡22) እርሱ ለሕዝቦቹ
ደኅንነት የሚሠራውን ሥራ ያመላክታል።
“ኖኅም ሁሉን እግዚአብሔር እንዳዘዘው አደረገ” (ዘፍ. 6፡22) የሚለው ሃረግ
የዝግጅት ሂደቱን መጠናቀቅ ያሳያል። የኖኅን ድርጊት በሚያመለክተው ክፍል
ውስጥ የተጠቀሰው “አደረገ” (አሳህ) የሚለው ግስ፣ እግዚአብሔር ትእዛዝ
በሰጠው ክፍል ውስጥ የሚጀምረው “ሥራ” (አሳ) (ዘፍ. 6፡14) የተሰኘ ግስ፣
አምስት ጊዜ (ሥራ፣ አብጅ፣ ሥራት፣ አብጅላት፣ ሥራት) ተደጋግሞ ቀርቧል
(ዘፍ. 6፡14-16)። ይህ በእግዚአብሔር ትእዛዝ እና በኖኅ ምላሽ መካከል
የሚስተዋል መስተጋብር፣ ኖኅ--እግዚአብሔር እንዲያደርግ (አሳህ) ለነገረው
ነገር የነበረውን ፍጹም መታዘዝ ያሳያል። እንዲሁም ይህ አባባል የማደሪያው
ድንኳን ከሚገነባበት ዐውድ ጥቅም ላይ መዋሉ ትኩረት የሚስብ ነው (ዘፀ.
39፡32፣ 42 ዘፀ. 40፡16)።
“እግዚአብሔር ለኖኅ የመርከቡን ትክክለኛ ርዝመት፣ ወርድና ከፍታ
ከማሳወቁ በተጨማሪ ስለ ግንባታው ዝርዝር የሆነ መመሪያ ሰጥቶት ነበር።
ሰብዓዊው ማስተዋል ያንን ግዙፍ፣ ጠንካራና ብቃት የነበረውን መርከብ
ንድፍ ለማውጣትና
ለመተግበር አይሆንለትም ነበር። በመሆኑም እግዚአብሔር የመርከቧ ንድፍ
አውጪ--ኖኅ ደግሞ የግንባታው ባለሙያ ነበር።” (የኃይማኖት አባቶችና
ነቢያት፡ ገጽ 95)።
አሁንም በመርከቡ እና በማደሪያው ድንኳን መካከል ያለው ተመሳሳይነት
የጋራ የመዋጀት ተግባራቸውን ያረጋግጣል። በመሆኑም የኖህ ታዛዥ መሆን
የእግዚአብሔር የማዳን እቅድ አካል ሆኖ ተገልጿል:: ኖኅ የዳነው እግዚአብሔር
ያዘዘውን ለማድረግ የሚያስችል እምነት ስለነበረው ብቻ ነው (ዕብ. 11፡7)።
ኖኅ ራሱን በመታዘዝ የሚገልጥ ብቸኛውና ታላቅ ቦታ የሚሰጠው፣ ከንቱ
ያልሆነ እምነት ቀደምት ምሳሌ ነበር (ያዕ. 2፡20)።
ባጭሩ፣ ምንም እንኳ ኖኅ “በእግዚአብሔር ፊት ሞገስ” ቢያገኝም (ዘፍ.
6፡8)፣ ለአምላካዊው ፈቃድ በታማኝነት እና በመታዘዝ መመላለሱ፣ ለዚህ
ለእርሱ አስቀድሞ ለተሰጠው ጸጋ ምላሽ ነበር። ይህ በእኛ በሁላችንም መሆን
የለበትም?
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ 2ጴጥ. 2፡5-9። ለምንድን ነው የኖኅ
ቤተሰቦች ብቻ የዳኑት? ዓለምን ስለ መጪው ፍርድ በማስጠንቀቅ
ረገድ ስለሚኖረን ሚና ከኖኅ ታሪክ ምን ትምህርት እናገኛለን?
“ሥራ”፣ “አብጅ” በሚል የተተረጎመውና የኖኅን ድርጊት የሚያመላክተው አሳ የተሰኘው የዕብራይስጥ ግስ፣ በአምላካዊው የፍጥረት ሥራም እንዲሁ ቁልፍ ቃል ሆኖ እናገኘዋለን (ዘፍ. 1:7፣ 16፣ 25፣ 26፣ 31፣ ዘፍ. 2:2)። ኖኅ እግዚአብሔርን በመታዘዝ የወሰዳቸው እርምጃዎች ከእግዚአብሔር የፍጥረት ሥራ እርምጃዎች ጋር ይመሳሰላሉ። የጥፋት ውሃ እግዚአብሔር የሰውን ልጅ ለመቅጣት ሲል ያመጣው መአት ሳይሆን እኛን ለማዳን ጭምር ያደረገው መሆኑን ከዚህ ተያያዥነት ያለው ቃል መውሰድ እንችላለን። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፍ. ምዕ. 7። ስለ ጥፋት ውሃ የሚሰጠው ገለጻ የፍጥረት ዘገባን ያስታውሰናል የምንለው ለምንድን ነው? በሁለቱ ክንውኖች መካከል ስላለው ተመሳሳይነት ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን?
የጥፋት ውሃ ታሪክን የሚሸፍነውን መልእክት በትኩረት ስናነብ ከፍጥረት
ታሪክ ጋር ተዛምዶ ያላቸውን አያሌ ቃላቶችና አገላለጾች እናገኛለን፡ “ሰባት”
(ዘፍ. 7:2፣3፣ 4፣ 10--ከሚከተሉት ጥቅሶች ጋር ያስተያዩ፡ ዘፍ. 2:1–3)፣
“ወንድ እና ሴት” (ዘፍ. 7፡2፣3፣9፣16--ከሚከተለው ጥቅስ ጋር ያስተያዩ፡ ዘፍ.
1፡27)፤ “ከየወገኑ” (ዘፍ. 7፡14--ከሚከተሉት ጥቅሶች ጋር ያስተያዩ፡ ዘፍ. 1፡
11፣12፣21፣24፣25)፤ “ከዱር እንስሳት”፣ “ከወፎች”፣ “ከሚሳቡ ፍጡራን” (ዘፍ.
7፡8፣ 14፣21፣23--ከሚከተሉት ጥቅሶች ጋር ያስተያዩ፡ ዘፍ. 1፡24፣ 25)፤
በመጨረሻም፡ “የሕይወት እስትንፋስ” (ዘፍ. 7፡15፣22--ከሚከተለው ጥቅስ
ጋር ያስተያዩ፡ ዘፍ. 2፡7)።
የጥፋት ውሃ ታሪክ ምንባብ በተወሰነ መልኩ የፍጥረት ሥራ ታሪክን
ይመስላል። እነዚህ የፍጥረት ታሪክን የሚያስተጋቡ ክስተቶች የሚፈጥረውም
ሆነ የሚያጠፋው አምላክ እርሱ አንድ መሆኑን ይገልጡልናል (ዘዳ. 32፡39)።
ሆኖም እነዚህ አስተጋቢ ክስተቶች የተስፋ ቃል መልእክትም ይዘዋል፡ የጥፋት
ውሃ--ከእነዚያ ውሆች ወደ አዲስ ሕልውና የሚያመራ አዲስ ፍጥረት ይወጣ
ዘንድ ታስቦ የተደረገ ነው።
የውሆች እንቅስቃሴ የተስተዋለበት ይህ የፍጥረት ክስተት፣ በዘፍ. 1
የተገለጸውን የፍጥረት ሥራ በተጨባጭ እየቀለበሰ መሆኑን ያሳያል።
ከጠፈር በላይና ከጠፈር በታች ያለውን ውሃ እንደለየ ከሚናገረው (ዘፍ. 1፡
7) መልእክት በተቃራኒ፣ የጥፋት ውሃው ከየድንበሩ ባሻገር በፈነዳበት ወቅት
መልሶ መገናኘቱን ያሳያል (ዘፍ. 7፡11)።
ይህ ሂደት እርስ በርሱ የሚጋጭ ዓይነት መልእክት ይዟል፡ እግዚአብሔር
አምላክ ቀጣይ አዲስ ፍጥረት ወደ ሕይወት ጎዳና እንዲመጣ ያደርግ ዘንድ
እነሆ አስቀድሞ የነበረውን ማጥፋት ነበረበት። አዲስ ምድር የመፍጠሩ ሥራ
የቀድሞውን አሮጌ ምድር ማስወገድ ይጠይቅ ነበር። የጥፋት ውሃ ክስተት
በዘመን መጨረሻ ፍጻሜ የሚያገኘውን የዓለም መዳን አስቀድሞ ያሳየ ነው፡
“ከዚህ በኋላ አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር አየሁ፤ የመጀመሪያው ሰማይና
የመጀመሪያይቱ ምድር ዐልፈዋልና፤ ባሕርም ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም”
(ራእ. 65፡17)።
እንደ አዲስ ለመፈጠር ከውስጣችን መወገድ ያለበት ነገር ምንድን
ነው? (ሮሜ 6:1–6)።
ዘፍ. 7፡22-24--የጥፋት ውሃው ያስከተለውን ሁሉን ያጥለቀለቀ መጠነ ሰፊ
ውጤት ሲገልጽ “ሕይወት ያላቸውን ፍጡራን ሁሉ ከምድር ገጽ አጠፋ” (ዘፍ.
7፡23)፣ “ውሃውም ምድርን ሸፍኖ መቶ አምሳ ቀን ቆየ” (ዘፍ. 7፡24) ይላል።
ከዚህ ሁሉ ድምሰሳና ተስፋ አስቆራጭ ሁናቴ ባሻገር “እግዚአብሔር ኖኅን…
አሰበ” (ዘፍ. 8፡1)። በጥቅሱ የቀረበው ሐረግ የጥፋት ውሃን በሚሸፍኑት
ጥቅሶች መሃል ለመሃል መዋሉ፣ ይህ ጽንሰ ሀሳብ የጥፋት ውሃ ታሪክ ዋና
መልእክት መሆኑን ያመለክታል።
ጥቅሱን ያንብቡ፡ ዘፍ. 8፡1። እግዚአብሔር ኖኅን “አሰበ” ማለት
ምን ማለት ነው?
“አሰበ” (ዛካር፡ አስታወሰ) ማለት እግዚአብሔር አልረሳውም ነበር የሚል ፍቺ
ያለው ሲሆን፤ ጉዳዩ ከአእምሮ ጂምናስቲክም ያለፈ ነው። “እግዚአብሔር
አሰበው” የሚለው አነጋገር ከመጽሐፍ ቅዱስ ዐውድ ሲታይ የተስፋ ቃል
ፍጻሜን የሚያመለክት ሲሆን፣ አልፎ አልፎ መዳንን ለመግለጽ ጥቅም ላይ
ሲውል ይታያል (ዘፍ. 19፡29)። ተከስቶ ከነበረው የጥፋት ውሃ ዐውድ
“እግዚአብሔር አሰበው” ማለት “ዝናቡ መዝነቡን አቆመ” (ዘፍ. 8፡2) ስለዚህ
ኖኅ ውሎ አድሮ መርከቢቱን ለቅቆ ይወጣል (ዘፍ. 8፡16) እንደ ማለት ነው።
ምንም እንኳ ኖኅ ከመርከቧ ስለሚወጣበት ሁናቴ ገና ቀጥተኛ ትእዛዝ
ያልተሰጠው ቢሆንም፣ እርሱ ግን በራሱ ተነሳሽነት ሁኔታውን ለመፈተሸ
በማሰብ በመጀመሪያ ቁራ፣ በመቀጠል ደግሞ ርግብ ላከ። በመጨረሻ ርግቧ
ሳትመለስ ስትቀር “ኖኅ በመርከቡ ላይ ያለውን ክዳን አንሥቶ ተመለከተ፣
የመሬቱም ገጽ እንደ ደረቀ አየ” (ዘፍ. 8፡13)።
የኖኅ ባህሪ በተግባራዊ አስተምህሮዎች የበለጸገ ነበር። በአንድ በኩል፣ ምንም
እንኳ እርሱ በቀጥታ ሲናገር ባይደመጥም በእግዚአብሔር ላይ መታመን
እንዳለብን ግን ያስተምረናል። በሌላ በኩል ደግሞ እምነት የማሰብንና
የመፈተሸ እሴትን እንደማይክድ እንመለከታለን። እምነት የተማርነው ነገር
እውነት መሆኑን የማሰብ፣ የመፈለግ እና የማየት ሀላፊነትን አይገድብም።
ሆኖም ኖኅ ከመርከቧ የሚወጣው እግዚአብሔር በመጨረሻ ያን እንዲያደርግ
ሲነግረው ብቻ ነው (ዘፍ. 8፡15-19)። ይህ ማለት፣ ከመርከቧ መውጣቱ
ምንም ችግር እንደማያስከትል ቢያውቅም፤ ኖኅ ግን አሁንም በእግዚአብሔር
በመታመን ከመውጣቱ በፊት የእርሱን ምልክት ይጠባበቅ ነበር። “አሁንም
ኖኅ በመርከቧ ውስጥ ሆኖ አምላካዊውን ትእዛዝ እየተጠባበቀ በትዕግሥት
ቆየ። በመጨረሻ መልአኩ ከሰማይ ወርዶ ግዙፉን የመርከቢቱን በር ከከፈተ
በኋላ እንዲወጡ አዘዛቸው። ኖኅና ቤተሰቡ በምድር ላይ ህይወት ያለውን
ነገር በሙሉ የራሳቸው ያደርጉ ዘንድ ተነገራቸው።”--(የኃይማኖት አባቶችና
ነቢያት፡ ገጽ 110)።
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፍ. 19፡29፣ መዝ. 106፡4። “እግዚአብሔር
አሰበው” (አስታወሰው) ማለት ፍቺው ምንድን ነው? ይህ እውነት
ለእኛ ያለው ትርጉም ምን ይመስላል? ለመሆኑ እግዚአብሔር
እርስዎን “እንዳሰቦት” ያሳዮት በምን መልኩ ነው?
እነሆ የተስፋው ቃል ፍጻሜ የሚያገኝበት ጊዜው አሁን ነው። “ ‘ካንተ ጋር
ግን ቃል ኪዳን እመሠርታለሁ። አንተና ወንዶች ልጆችህ፣ ሚስትህና የልጆችህ
ሚስቶች ከአንተ ጋር ወደ መርከቧ ትገባላችሁ’ ” (ዘፍ. 6፡18)። ከመለኮታዊው
ምድርን የማጥፋት ስጋት በንጽጽር (ዘፍ. 6፡17) የቀረበው ይህ ቃል ኪዳን፣
እነሆ የሕይወት ተስፋ ነው።
ጥቅሱን ያንብቡ፡ ዘፍ. 8፡20። ኖኅ ከመርከቧ እንደወጣ
በመጀመሪያ ምን አደረገ? ለምን?
አዳም እና ሔዋን ከስድስቱ የፍጥረት ቀናት በኋላ ወዲያውኑ በሰንበት
እግዚአብሔርን እንዳመለኩ ሁሉ፣ ኖኅም ከጥፋት ውሃ በኋላ፣ በራሱ የሌላ
ፍጥረት ክስተት ከሆነው ከመርከቧ እንደወጣ፣ ወዲያውኑ እግዚአብሔርን
አመለከ። ይሁን እንጂ በእነዚህ በሁለቱ የአምልኮ ተግባራት መካከል ልዩነት
አለ። ጌታን በቀጥታ ያመልኩ ከነበሩት ከአዳምና ሔዋን በተቃራኒ ኖኅ
መሥዋዕት ማቅረብ ነበረበት። መሠዊያን አስመልክቶ በቅዱሳት መጻሕፍት
ለመጀመሪያ ጊዜ የተጠቀሰው በዚህ ስፍራ ነው። ኖኅ ያቀረበው “የሚቃጠል
መሥዋዕት” (ኦላህ) ሲሆን፣ ይህ መሥዋዕት እጅግ ጥንታዊና ዘወትር ይቀርብ
የነበረ ነው። ለኖኅ ይህ የምስጋና መሥዋዕት ሲሆን (ያስተያዩ፡ ዘኁ. 15፡1-11)፣
ላዳነው አምላክ ምስጋናውን ለመግለጽ ያቀረበው ነበር።
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፍ. 9፡2-4። የጥፋት ውሃ በሰዎች አመጋገብ
ላይ ተጽእኖ ያሳደረው እንዴት ነበር? ከአምላካዊ ገደቦች
በስተጀርባ ያለው መሠረታዊ መርኅ ምንድን ነው?
የጥፋት ውሃው ካስከተለው ተጽእኖ የተነሣ እንደ ቀድሞው የእፅዋት ምግብ
ማግኘት የማይቻል ሆኖ ነበር። ስለዚህ ሰዎች የእንስሳትን ሥጋ ለምግብነት
እንዲያውሉ እግዚአብሔር ፈቀደላቸው። ይህ የአመጋገብ ለውጥ በሰዎች እና
በእንስሳት መካከል ከነበረው የቀደመ የሥነ ፍጥረት ሁናቴ አንጻር ግንኙነቱ
እንዲቀየር አድርጓል። በፍጥረት ታሪክ የሰው ልጆችና እንስሳት አንድ ዓይነት
የዕፅዋት አመጋገብ ከመጋራታቸው አኳያ አንዱ ለሌላው ስጋት አልነበረም።
ነገር ግን በድኅረ ጥፋት ውሃ ዓለም፣ እንስሳትን ለምግብነት መግደል አስፈሪና
አስደንጋጭ ግንኙነትን ጠየቀ (ዘፍ. 9፡2)። ሰዎችና እንስሳት እርስ በርስ
መበላላት ከጀመሩ በኋላ፣ በኤደን ከነበራቸው ግንኙነት ፈጽሞ የተለየ ዝምድና
ለመፍጠራቸው ምንም ጥርጥር የለውም።
ይሁን እንጂ እግዚአብሔር የሥጋ መብልን የፈቀደው ሁለት ገደቦችን
በማስቀመጥ ነበር። በመጀመሪያ ደረጃ ሁሉም እንስሳት ለምግብነት ተስማሚ
አልነበሩም። የመጀመሪያው ገደብ የፍጥረት ሥርዓት አካል በነበሩት “ንጹሕ
እና እርኩስ” እንስሳት መካከል ያለውን ልዩነት የገለጸ ነበር (ዘፍ. 8፡19-20 /
ያስተያዩአቸው፡ ዘፍ. 1፡21፣24)።
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፍ. 8፡21-9፡1። እግዚአብሔር ሕይወትን ጠብቆ ለማቆየት ያሳየው ቁርጠኝነት አንደምታው ምንድን ነው? አምላካዊው በረከት ያን ቁርጠኝነት የፈጸመው እንዴት ነበር?
እግዚአብሔር ሕይወትን ጠብቆ ለማቆየት የነበረው ቁርጠኝነት የጸጋ ተግባር
እንጂ የሰው ልጅ ብቃት ውጤት አልነበረም። ሰው ወደ ክፋት ያዘነበለ ሆኖ
ሳለ፣ እግዚአብሔር ግን በምድር ላይ ሕይወትን ጠብቆ ለማቆየት ወሰነ (ዘፍ.
8፡21)። “ምድር እስካለች ድረስ” ብሎ ዘፍ. 8፡22 ቃል በቃል በመናገር-ወቅቶች ይፈራረቃሉ፣ ሕይወትም ይቀጥላል። ባጭሩ እግዚአብሔር በፍጥረቱ
ተስፋ አልቆረጠም።
እንዲያውም ስለ አምላካዊው በረከት የሚናገረው የሚከተለው ጥቅስ ወደ
መጀመሪያው የፍጥረት ሥራው ይመልሰናል (ዘፍ. 1፡22፣ 28፣ ዘፍ. 2፡3)።
ጌታ የሰው ልጅ በአዲስ ጅማሮ ወደፊት የሚገሰግስበትን ዕድል እየሰጠ ነበር።
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፍ. 9፡8-17። የቀስተ ደመና ትርጓሜ
ምንድን ነው? ይህ “የኪዳን ምልክት” (ዘፍ. 9፡13) ሌላኛው
የኪዳን ምልክት ከሆነው ሰንበት ጋር የሚዛመደው እንዴት ነው?
“ኪዳኔን እመሠርታለሁ” የሚሉት ቃላት ለሦስት ጊዜ ተደጋግመው
መቅረባቸው (ዘፍ. 9፡9፣11፣17) የቀደመው አምላካዊ የተስፋ ቃል ጡዘት ላይ
መድረሱንና ፍጻሜውን ያመለክታሉ (ዘፍ. 6፡18)። የመጀመሪያውን የስድስት
ቀን የፍጥረት ሥራ ዘገባ ተከትሎ የሚመጣው ይህ ክፍል፣ ከሰባተኛው ቀን
ማለትም የሰንበትን ቀን ከሚሸፍነው ክፍል ጋር ይመሳሰላል። በጥቅሱ ውስጥ
እንደሚስተዋለው “ቃል ኪዳን” ለሰባት ጊዜ ያህል ተደጋግሞ የቀረበው
ሰንበትን በሚያስተጋባ መልኩ ነው። እንደ ሰንበት ሁሉ ቀስተ ደመና የቃል
ኪዳኑ ምልክት ነው (ዘፍ. 9:13-14፣ 16--ያስተያዩ፡ ዘጸ. 31:12-17)። በተጨማሪ
ልክ እንደ ሰንበት፣ ቀስተ ደመናም ዩኒቨርስ አቀፍ መዳረሻ ስላለው ትግበራው
መላውን ምድር አካታች ነው። ሰንበት በየትኛውም ስፍራ ለሚገኝ ማንኛውም
ሰው የአምላካዊው ሥነ ፍጥረት ምልክት እንደሆነ ሁሉ፣ የጥፋት ውሃ ዳግመኛ
እንደማይመጣ የተሰጠው የተስፋ ቃልም ለየትኛውም ስፍራና ለማንኛውም
ሰው ጭምር ነው።
በሚቀጥለው ጊዜ ቀስተ ደመናን ሲያዩ እግዚአብሔር ስለ ሰጠን
የተስፋ ቃል አሰብ ያድርጉ። በእነዚህ ተስፋዎች ላይ እምነት
መጣል የምንችለው ለምንድን ነው? የተስፋ ቃሎቹን ልናምናቸው
እንደምንችል ቀስተደመናው እንዴት ሊያሳየን ይችላል?
ከጥፋት ውሃ በፊት የነበሩ ሕዝቦችን አስተሳሰብና ባህሪ
ከዘመናችን ሰዎች አስተሳሰብና ባሕሪ ጋር ማነጻጸር በተለይ ትምህርት ሰጭ
ነው። የሰው ልጅ ክፋት አገር ያወቀው ጸሐይ የሞቀው እውነታ እንጂ አዲስ
ክስተት አይደለም። እስቲ በእነርሱና በእኛ ዘመን መካከል ያለውን መመሳሰል
እንመልከት፡
“ከጥፋት ውሃ አስቀድሞ በነበሩ ሰዎች ላይ አምላካዊው ቁጣ እንዲወርድ
ያደረጉ ኃጢአቶች እነሆ ዛሬም አሉ። እግዚብሔርን መፍራት ከሰዎች ልብ
ውስጥ ተወግዶአል፤ ሕጉም እንደ ከንቱ ነገር ተቆጥሮአል፣ ተንቋል። በጥንቱ
ዓለም ተንሰራፍቶ የነበረው ሥር የሰደደ ዓለማዊነት ከዛሬው ትውልድ ጋር
ተመጣጣኝ እንጂ የሚያንስ አይደለም።… ከጥፋት ውሃ በፊት የነበሩት ሕዝቦች
በመብላታቸውና በመጠጣታቸው አልተኮነኑም… ኃጢአት የሆነባቸው እነዚህን
ስጦታዎች ሲወስዱ ሰጪውን አለማመስገናቸውና መሻታቸውን መግዛት
ተስኖአቸው በስግብግብነት ጌታ የሚፈልግባቸው የከበረ ደረጃ ላይ መድረስ
አለመቻላቸው ነው። እነዚህ ሰዎች ትዳር እንዲይዙና ቤተሰብ እንዲመሰርቱ
ሕጉ ይደግፋል፣ ያበረታታቸውማል። ጋብቻ እግዚአብሔር ከመሠረታቸው
የመጀመሪያዎቹ ተቋሞች አንዱ እንደመሆኑ ትዳር አምላካዊ ትእዛዝ ነው።
እግዚአብሔር በጋብቻ ሕግ ዙሪያ የተለየ መመሪያዎችን ሰጥቶአል። በመሆኑም
ትዳርን በቅድስና መያዝና ውበቱን መጠበቅ አንዱና ዋንኛው መመሪያ ቢሆንም
ነገር ግን እነዚህ ሕጎች በመጣሳቸው ጋብቻ የታለመለትን ዓላማ ስቶ የስሜት
መገልገያ መሣሪያ ሆነ። ከጥንቱ ትውልድ ድርጊቶች ጋር ተመሳሳይነት ያላቸው
ሁናቴዎች ዛሬም ይስተዋላሉ። ሕጋዊ የሆነው ነገር የተቀመጠለትን ገደብና
ልክ አልፎአል… ማጭበርበር፣ ሙስና እና ሌብነት ከፍ ባለው እንዲሁም
በዝቅተኛው ስፍራ የተወገዙ አይደሉም። የመገናኛ ብዙሃን የሚያወጧቸው
ጭካኔ የተሞላባቸው የግድያ ወንጀል ታሪኮች ሰብዓዊው ፍጡር የተሰጠው
የማመዛዘን ተፈጥሮ ከአእምሮው ተደምስሶአል የሚያሰኙ ናቸው። እነዚህ
የዐመጻ ተግባራት በእጅጉ የተለመዱ ክስተቶች ከመሆናቸው የተነሳ በብዙዎች
ዘንድ አስተያየት ወይም አግራሞት የመፍጠራቸው አንደምታ ውሱን ሆኗል።
የሕገ-አልበኝነት መንፈስ መላውን አገራት እያጥለቀለቀ ይገኛል። ከጊዜ ወደ
ጊዜ በዓለም ላይ እንደ ወረርሽኝ እየተዛመቱ ያሉ፤ እንዲህ ተብለው ሊገለጹ
የማይችሉ፤ የፍትዎት እሳትና ሕገ-አልበኝነት፤ አንዴ ከቁጥጥር ውጪ ከወጡ
ምድርን በወዮታና በውድመት ይሞሏታል። በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ስለ
ጥንቱ ዓለም የቀረበው ስዕላዊ መግለጫ የዛሬው ዘመናዊ ማኅበረሰብ በፍጥነት
እያመራበት ያለውን አቅጣጫ በተጨባጭ ያሳያል። ዛሬ በዚህ ዘመን እንኳ
እራሳቸውን ክርስቲያን ብለው በሚጠሩ ማኅበረሰቦች ምድር ላይ የጥንቱ
ዓለም ኃጢአተኞች የጠፉበት ዓይነት አስከፊ ወንጀሎች ይፈጸማሉ።”—
(የኃይማኖት አባቶችና ነቢያት፡ ገጽ 104-106)።
1.ከጥፋት ውሃ በፊት የነበረው ኅብረተሰብና የእኛ የጋራ ባሕሪያት ምንድን ናቸው? እነዚህ የጋራ ባሕሪያት ስለ እግዚአብሔር ጸጋ ማለትም በዚህ ሁሉ ውስጥ ዓለምን መውደዱንና የምድርን ሕዝብ ለማዳን ዛሬም እጁ የተዘረጋች ስለ መሆኗ ምን ያስተምሩናል? 2.አንዳንዶች በኖኅ ዘመን የደረሰው የጥፋት ውሃ በአንድ አካባቢ ብቻ የተፈጸመ ድርጊት ነበር ብለው ይሞግታሉ። ይህ እውነት ቢሆን ኖሮ፣ በተለያየ አካባቢ ዝናብ ሲጥል የሚወጣው እያንዳንዱ ቀስተ ደመና እርሱን ለምን ውሸታም አላደረገውም?