የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ዘፍጥረት


የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 2ኛ ሩብ ዓመት 2022

ከሚያዝያ 1 – 7

3ኛ ትምህርት

Apr 9 - Apr 15




ቃየን ትቶት ያለፈው ቅርስ



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ዘፍ. 4፣ ዕብ. 11:4፣ ሚክ. 6:7፣ ኢሳ. 1:11፣ 1ቆሮ. 10:13፣ 1ዮሐ. 3:12፣ ዘፍ. 5፣ ዘፍ. 6:1–5።


የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ “ ‘መልካም ብታደርግ ተቀባይነትን አታገኝምን? መልካም ባታደርግ ግን፣ ኃጢአት በደጅህ እያደባች ናት፣ ልታሸንፍህ ትፈልጋለች፣ አንተ ግን ተቆጣጠራት’ ” (ዘፍ. 4፡7)

በ ዘፍጥረት መጽሐፍ እንደምናነበው የሰውን ውድቀት እና የአዳምና ሔዋንን ከኤደን መባረር ተከትለው ወዲያውኑ የሚመጡት ክስተቶች በአመዛኙ ውልደት እና ሞት ሲሆኑ፤ እነዚህ ሁሉም በቀደመው ምዕራፍ እግዚአብሔር የተናገራቸው ትንቢቶች ፍጻሜ ናቸው። ዘፍ. 3 እና 4 ተጓዳኝ ምዕራፎች እንደመሆናቸው አያሌ፡ የኃጢአት መግለጫዎች የሆኑ የጋራ ጭብጦች እና ቃላቶች ይዘዋል፡ (ጥቅሶቹን ያስተያዩ፡ ዘፍ. 3፡6-8 እና ዘፍ. 4፡8)፣ “ምድር የተረገመች” መሆኗ (ጥቅሶቹን ያስተያዩ፡ ዘፍ. 3፡17 እና ዘፍ. 4፡11) እና ከኤደን እንዲወጣ መደረጉ (ጥቅሶቹን ያስተያዩ፡ ዘፍ. 3፡24 እና ዘፍ. 4፡12፣16)።

የምዕራፎቹ ተጓዳኛዊ ፍሰት መንስዔ አዳምና ሔዋን ከወደቁ በኋላ እግዚአብሔር ሰጥቶአቸው የነበረውን ትንቢቶች ፍጻሜ ማጉላት ነው። አዳም ከተባረረ በኋላ የተስተዋለው የመጀመሪያ ክስተት በተስፋ የተሞላ ነበር። ሔዋን ስለ መሲሕ የሰማችው የትንቢት ቃል ፍጻሜ አድርጋ የተመለከተችው የበኩር ልጅ ተወለደ (ዘፍ. 3፡15)። በዚህም ልጁ በተስፋ የተሰጠው መሲህ ሊሆን ይችላል ብላ አሰበች። ቀጣይ ክስተቶች፡-- የቃየን ወንጀል፣ የላሜሕ በደል፣ የዕድሜ ጣሪያ ማሽቆልቆል፣ እንዲሁም የእርክስና መበራከት--እነዚህ ሁሉ በዘፍ. 3 የተነገረው የእርግማን ቃል ፍጻሜዎች ናቸው። ይህም ሆኖ ግን፣ ሁሉም ተስፋ አልጠፋም።

፡ ሚያዝያ 2
Apr 10

ቃየን እና አቤል


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፍ. 4፡1-2። ስለ ሁለቱ ወንዶች መወለድ ከእነዚህ ጥቅሶች ምን እንማራለን?



አዳም ከኤደን የአትክልት ስፍራ ከተባረረ በኋላ በመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊ የተመዘገበው የመጀመሪያው ክስተት ልጅ መውለድ እንደሆነ እንመለከታለን። በዘፍ. 4፡1 በቀረበው የዕብራይስጥ ሃረግ ውስጥ የምናገኘው “ጌታ” (ያህዌ) “ወንድ ልጅ” ከሚለው ጋር በቀጥታ የተሳሰረ ሲሆን፣ የዚህ ጥሬ ትርጉም፡ “ ‘ወንድ ልጅ አገኘሁ፤ በእርግጥም ጌታ ራሱ ነው’ ” የሚል ነው። ኢንተርናሽናል ስታንዳርድ ቨርዥን የተባለው የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ደግሞ፡ “ ‘ወንድ ልጅ--ጌታን ወለድኩ’ ” ይላል።

ይህ ጥሬ ትርጉም ሔዋን በዘፍ. 3፡15 ስለ መሲህ የተነገረውን ትንቢት ማስታወሷንና አዳኝዋ የሆነውን ጌታ እንደወለደች ማመኗን ይጠቁማል። “የአዳኙ መምጣት አስቀድሞ በኤደን የአትክልት ስፍራ ተነግሮ ነበር። አዳምና ሔዋን የተስፋውን ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ ሲሰሙ በፍጥነት ፍጻሜውን ለማግኘት ፈለጉ። አዳኝ እንደሚሆን በማሰብ የበኩር ልጃቸውን በደስታ ተቀበሉት።”—Ellen G. White, The Desire of Ages, p. 31. ቃየን የታሪኩን አብዛኛውን ክፍል መውሰዱ እሙን ነው። እርሱ የበኩር ልጅ ከመሆኑ ባሻገር ወላጆቹ “ያመልኩት” ነበር ብሎ መናገርም ይቻላል። በምዕራፉ እንደ ተመለከተው በአጠቃላዩ የዘፍጥረት መጽሐፍ ሲናገር የሚሰማው ብቸኛ ወንድም እርሱ ነው። ሔዋን ስለ ቃየን መወለድ በደስታ ስትናገር፣ በአንጻሩ አቤልን አስመልክታ የተናገረችውም ሆነ የተጻፈ ነገር የለም። ተራኪው “ደግሞም ወንድሙን አቤልን ወለደች” (ዘፍ. 4፡2) ብሎ ብቻ ዘግቧል። ቃየን የሚለው ስም ራሱ ቃናህ ከሚል የዕብራይስጥ ግስ የተገኘና “ማግኘት” የሚል ትርጉም ያለው ሲሆን፣ አንድ የከበረ እና ብርቱ ነገር ማፍራት ብሎም በእጅ ማድረግን ያመለክታል። በሌላ በኩል፣ የዕብራይስጡ ስም ሔቤል፣ በአማርኛ አቤል “ትነት” ወይም “እስትንፋስ” (መዝ. 144፡4) የሚል ፍቺ ያለው ሲሆን--የማይጨበጥ፣ ባዶ፣ ፍሬ ቢስ መሆንን ያመለክታል። ይኸው ተመሳሳይ ቃል--ሔቤል (አቤል) በመጽሐፈ መክብብ “ከንቱ” በሚል ተደጋግሞ ተጠቅሷል። ምንም እንኳ በእነዚህ አጠር ብለው በቀረቡ ጥቅሶች ከተነገረን በላይ መሄድ ባንፈልግም፣ ምናልባት የአዳምና ሔዋን ተስፋ እና እምነት ያረፈው በቃየን ላይ ብቻ ነበር። ምክንያቱም ወንድሙን ሳይሆን፣ እርሱን ተስፋ የተደረገው መሲህ አድርገው አምነው ነበር።

በሕይወታችን ውስጥ በትክክል “ሔቤል” ሆነው ሳለ፣ ነገር ግን ከሆኑት በላይ የላቁና ዋጋ ያላቸው አድርገን የምንመለከታቸው ነገሮች ምንድን ናቸው? አስፈላጊ በሆኑና ባልሆኑ ነገሮች መካከል ያሉትን ልዩነቶች ማወቅ ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?





ሚያዝያ 3
Apr 11

ሁለቱ መሥዋዕቶች


በቃየን እና አቤል መካከል ያለው ልዩነት በመጠሪያ ስማቸው የተንጸባረቀውን ማንነት ያገናዘበ አልነበረም። ይህ ደግሞ በተሰማሩበት የሥራ ዘርፍ ጭምር የታየ ነበር። ቃየን “ዐራሽ” (ዘፍ. 4፡2) እንደመሆኑ ብርቱ ልፋት በሚጠይቅ ሥራ ተጠምዶ ነበር። “የበግ እረኛ” (ዘፍ. 4፡2) የነበረው አቤል ደግሞ አሳቢነትና ርኀራኄ የሚጠይቅ ሥራ ይሠራ ነበር።

ቃየን ምድር የምትሰጠውን ፍሬ የሚያመርት ዐራሽ ገበሬ ነበር። አቤል ደግሞ የበጎች እረኛ። እነዚህ ሁለቱ የሥራ ዘርፎች የሁለቱን መሥዋዕቶች ተፈጥሮ (ቃየን ያቀረበውን የምድር ፍሬ መሥዋዕት እና አቤል ያቀረበውን የበግ መሥዋዕት) የሚገልጹ ብቻ ሳይሆን፣ ከሁለቱ መሥዋዕቶች ጋር ትስስርነት ያላቸውን ሁለት የተለያዩ ሥነ ልቦናዊ ዝንባሌዎችና አስተሳሰቦችንም ያሳያሉ። ቃየን በዕርሻ ሥራው ፍሬ “ለማግኘት” እየተጋ የነበረ ሲሆን፣ አቤል ግን የተቀበላቸውን በጎች በጥንቃቄ “ይጠብቅ” ነበር።

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፍ. 4፡1-5፣ ዕብ. 11፡4። እግዚአብሔር የአቤልን መሥዋዕት ሲቀበል፣ የቃየንን ግን ሳይቀበል የቀረው ለምን ነበር? በዚህ ስፍራ የሆነውን ነገር እንዴት እናስተውለዋለን?



“ደም ሳይፈስ የኃጢአት ሥርየት እንደሌለ ሁሉ እነርሱም [ቃየን እና አቤል] ከመንጋው በኩር የሆነውን መሥዋዕት አድርገው በማቅረብ ወደፊት ለበደላቸው ሥርየት እንደሚያመጣ ቃል በተገባው የክርስቶስ ደም ላይ ያላቸውን እምነት ማሳየት ነበረባቸው። ከዚህ በተጓዳኝ የመጀመሪያዎቹ የምድር ፍራፍሬዎች በምሥጋና ስጦታ ለጌታ መቅረብ ነበረባቸው።” (የኃይማኖት አባቶችና ነቢያት፡ ገጽ 70-71)

አቤል ከሚቃጠል የእንስሳ መሥዋዕት በተጨማሪ አምላካዊውን መመሪያዎች የተከተለ የምድር ፍሬዎችን መሥዋዕት ያቀረበ ሲሆን፣ ቃየን ግን ይህን ለማድረግ ችላ አለ። እርሱ ለመሥዋዕት የሚሆን እንስሳ አላመጣም፣ ይልቁንም “ከምድር ፍሬ” ብቻ ይዞ ቀረበ። ከወንድሙ አመለካከት በተቃራኒ የተስተዋለው ይህ ድርጊቱ ግልጽ አለመታዘዝ ነበር። ይህ ታሪክ ብዙውን ጊዜ ጽድቅ በእምነት (የአቤል እና የደም መሥዋዕቱ) ከማግኘት በተቃራኒ የሚደረግን ጽድቅ በሥራ (ቃየን እና የምድር ፍሬ መሥዋዕቱ) የማግኘት ዓይነተኛ ጉዳይ ተደርጎ ይታያል።

ምንም እንኳ የእነዚህ መሥዋዕቶች መንፈሳዊ አንደምታ እሙን ቢሆንም፣ ነገር ግን በራሳቸው የሚፈይዱት ምትሃታዊ ክስተት አልነበረም። መሥዋዕቶቹ ሁሌም ቢሆን ለኃጢአተኛው የመንፈስ ጽናት ብቻ ሳይሆን መዋጀትንም ወደ አቀረበው እግዚአብሔር አምላክ የሚያመላክቱ ምሳሌዎችና ምስሎች ብቻ ነበሩ።

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ሚክ. 6፡7፣ ኢሳ. 1፡11። በእነዚህ ጥቅሶች የቀረቡትን መርኅዎቸ በሕይወታችን እና አምልኮአችን ላይ ተግባራዊ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

፡ ሚያዝያ 4
Apr 12

የተፈጸመው ወንጀል


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፍ. 4፡3-8። ቃየን ወንድሙን እንዲገድል ያደረገው ሂደት ምን ነበር? በተጨማሪ ይህን ጥቅስ ያንብቡ፡ 1ዮሐ. 3፡12



በቃየን የታየው አጸፋዊ ምላሽ እጥፍ ነበር፡ “ክፉኛ ተናደደ፣ ፊቱም ጠቆረ” (ዘፍ. 4፡5)። የቃየን ንዴት ያነጣጠረው በእግዚአብሔር እና በአቤል ላይ ነበር። ቃየን የኢፍትሐዊነት ሰለባ እንደሆነ አድርጎ ስላሰበ በእግዚአብሔር ላይ የተናደደ ሲሆን፣ በአቤል ላይ የተናደደው በወንድሙ ስለቀና ነበር። በምን ቀና? በዚያ አንድ መሥዋዕት? በእነዚህ ጥቂት ጥቅሶች ከተገለጸው ጀርባ ቀደም ባሉት ጊዜያት አያሌ ነገሮች ሳይካሄዱ እንዳልቀሩ ለመገመት አያዳግትም። ጉዳዮቹ ምንም ይሁኑ ምን--ቃየን ያቀረበው መሥዋዕት ተቀባይነት ባለማግኘቱ ተጨነቀ።

በዘፍ. 4፡6 እግዚአብሔር ለቃየን ያቀረባቸው ሁለት ጥያቄዎች እርሱ ከነበረባቸው ሁለት ሁናቴዎች ጋር የተያያዙ ናቸው። እዚህ ላይ እግዚአብሔር ቃየንን አለመክሰሱን ልብ ይሏል። እንደ አዳም ሁሉ እግዚአብሔር ጥያቄዎችን የጠየቀው መልሱን ስለማያውቀው ሳይሆን፣ ነገር ግን ቃየን ወደ ራሱ እንዲመለከትና አሁን ያለበት ሁናቴ እንዲከሰት መንስዔ የሆነውን ነገር እንዲያስተውል ነው። ሰዎች በግልጽ ቢስቱም እንኳ ነገር ግን ሁል ጊዜም ቢሆን ጌታ የወደቁ ሕዝቦቹን ለመቤዥት ይፈልጋል። ከዚያም እግዚአብሔር እነዚህን ጥያቄዎች ከጠየቀው በኋላ አምላካዊ ምክር ሰጠው። በመጀመሪያ እግዚአብሔር ቃየንን “ ‘መልካም ብታደርግ’ ” ሲል ሰናይ ምግባር በእርሱ እንዲገለጥ ይነግረዋል። ይህ ወደ ንስሐ እንዲመጣና አመለካከቱን እንዲለውጥ የቀረበ ጥሪ ነው። ይህን ካደረገ ቃየን “ ‘ተቀባይነት’ ” እንደሚያገኝና ይቅር እንደሚባል ቃል ገብቶለታል። የእግዚአብሔር አነጋገር፡ ቃየን በእግዚአብሔር ፊት ተቀባይነት የሚያገኘው በራሱ ሳይሆን በእግዚአብሔር ሀሳብ መሠረት ከተጓዘ ብቻ ነው--የሚል አንደምታ አለው። በሌላ በኩል “‘መልካም ባታደርግ ግን፣ ኃጢአት በደጅህ እያደባች ናት፣ ልታሸንፍህ ትፈልጋለች፤ አንተ ግን ተቆጣጠራት’” (ዘፍ. 4፡7) ይለዋል። አምላካዊው ምክር የኃጢአትን ሥር የገለጠ ሲሆን፣ የሚገኘውም በራሱ በቃየን ውስጥ ነው። በዚህም ቃየን መሄድ ባለበት ቀና መንገድ ይሄድ ዘንድ እንደገና እየመከረው ነበር።

ሁለተኛው አምላካዊ ምክረ ቃል በደጁ ባደባውና ሊያሸንፈው “ ‘በሚፈልገው’ ” ኃጢአት ላይ ሊወስድ የሚገባውን ውሳኔ ይመለከታል፡ “ ‘አንተ ግን ተቆጣጠራት።’ ” ተመሳሳይ መርኅ በያዕቆብ መልእክት ሲስተጋባ ይታያል፡ “ነገር ግን እያንዳንዱ የሚፈተነው በራሱ ክፉ ምኞት ሲሳብና ሲታለል ነው” (ያዕ. 1፡14)። ወንጌል የኃጢአት ይቅርታ እንደምንቀበል ብቻ ሳይሆን፣ ነገር ግን በኃጢአት ላይ ባለ ድል እንደምንሆን ጭምር በመንገር የተስፋ ቃል ይሰጠናል (1ቆሮ. 10፡13)። በመጨረሻ፣ ቃየን ለሠራው ኃጢአት ከራሱ በቀር የሚያላክክበት ማንም አልነበረውም። ይህ በጥቅሉ ከእኛ ከሁላችንም ሁናቴ ጋር ተመሳሳይ አይደል?

ይህ አሳዛኝ ታሪክ ስለ የመምረጥ ነጻነት እና እግዚአብሔር እንድንታዘዘው የማያስገድድ አምላክ ስለ መሆኑ ምን ያስተምረናል?

ሚያዝያ 5
Apr 13

በቃየን ላይ የተሰጠው ቅጣት


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፍ. 4፡9-16። “ ‘ወንድምህ አቤል የት ነው?’ ” ብሎ እግዚአብሔር ለምን ጠየቀ? በቃየን ኃጢአት እንዲሁም “ ‘በምድር ላይ ኮብላይና ተንከራታች’ ” በመሆኑ መሃል ያለው ግንኙነት ምንድን ነው? (ዘፍ. 4፡12)



እግዚአብሔር ለቃየን ያቀረበው ጥያቄ፣ አዳምን ተጣርቶ “ ‘የት ነህ?’ ” ሲል በኤደን ያቀረበውን ጥያቄ ያስተጋባል። ይህ የተስተጋባ ድምጽ በኤደን በነበረው ኃጢአትና በአሁኑ ኃጢአት መካከል ያለውን ትስስር ያሳያል፡ ሁለተኛው ኃጢአት (የቃየን) የፊተኛው (የአዳም) ውጤት ነበር።

ሆኖም ቃየን፣ ከአዳም በተቃራኒ ኃጢአቱን አምኖ አይቀበልም። እንደውም ይክዳል። ምንም እንኳ አዳም በሌላ ላይ ለማላከክ ቢሞክርም መተላለፉን ግን አይክድም። በተቃራኒው ቃየን ስለ ሠራው ወንጀል እርሱን ፊት ለፊት በመጋፈጥ ምንም ጊዜ ያላጠፋውን እግዚአብሔርን ግልጽ በሆነ ድፍረት ይናገራል። እግዚአብሔር “ ‘ምንድነው ያደረግኸው?’ ” ብሎ ሦስተኛውን ጥያቄ ሲጠይቀው መልስ እንዲሰጠው አልጠበቀም ነበር። እርሱ ሁሉንም ነገር እንደሚያውቅ ቃየንን በማስታወስ የአቤል ደም ድምፅ ከምድር ወደ እርሱ እንደሚጮኽ (ዘፍ. 4፡10) ነገረው። ይህ ምስል እግዚአብሔር ግድያውን የሚያውቅ መሆኑንና በዚህ ዙሪያም ምላሽ እንደሚሰጥ አጽንኦት የሚሰጥ ነው። አቤል በምድር ላይ ነው ያለው። ይህ እግዚአብሔር ቀደም ሲል በአዳም ላይ ስለሚሆነው ከነገረው ነገር ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አለው (ዘፍ. 3፡19)። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፍ. 4፡14። ቃየን “ ‘ቃየን ከፊትህም እሸሸጋለሁ’ ” ብሎ የመናገሩ ትርጉም ምንድን ነው?



የአቤል ደም በምድሪቱ ላይ በመፍሰሱ ምክንያት እነሆ ምድሪቱ እንደገና ተረገመች (ዘፍ. 4፡12)። በውጤቱም ቃየን ከእግዚአብሔር ርቆ ተንከራታች ሆኖ እንዲኖር ተኮነነ። ቃየን የእግዚአብሔርን የፍርድ ቃል ሲሰማ ብቻ ለአምላካዊው ህልዎት አንደምታ እውቅና ሲሰጥ ይታያል። የእርሱ ጥበቃና አብሮነት የሌለበት ሁናቴ ለሕይወቱ አስግቶት ነበር። ቃየን በገዛ ወንድሙ ላይ ጭካኔ የተሞላው ግድያ ፈጽሞና ድርጊቱን ከቁም ነገር ሳይቆጥር ቀርቶም እንኳ፣ ጌታ አሁንም ምሕረቱን እየገለጠለት ነበር። “ቃየን ከእግዚአብሔር ፊት ወጥቶ” ከሄደ (ዘፍ. 4፡16) በኋላም እንኳ ጌታ የሆነ ዓይነት ከለላ አድርጎለት ነበር። ያደረገለት “ምልክት” (ዘፍ. 4፡15) ምን እንደሆነ በትክክል ባይነገረንም፣ ነገር ግን ምንም ይሁን ምን ያን ያገኘው ከእግዚአብሔር ጸጋ የተነሣ ብቻ ነው። “ ‘ከፊትህም እሸሸጋለሁ’ ፊት መሸሸግ ምን ማለት ነው? አሳዛኝ ሁኔታ ነው። እኛ እንደ ሁኔታ ማስወገድ የምንችልበት ” (ዘፍ. 4፡14)። ከእግዚአብሔር ይህ ለማንኛውም ሰው እንዴት ያለ ኃጢአተኝነታችን እንዲህ ያለውን ብቸኛው መንገድ ምንድን ነው?

ሚያዝያ 6
Apr 14

የሰው ልጅ እርክስና


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፍ. 4፡17-24። የቃየን ውርስ ምንድን ነበር? የእርሱ ወንጀል እየጨመረ ለሄደው የሰው ዘር እርክስና መንገድ የከፈተው እንዴት ነበር?



የቃየን አምስተኛ የልጅ ልጅ የሆነው ላሜሕ ከራሱ ወንጀል ዐውድ አኳያ የቃየንን ሲጠቅስ ይታያል። በቃየን ወንጀልና በላሜሕ ወንጀል መካከል ያለው ይህ ንጽጽር ትምህርት ሰጭ ነው። ቃየን ተመዝግቦ ስለሚገኝ ብቸኛ ወንጀሉ ዝምታን ሲመርጥ፣ ላሜሕ ግን ይባስ በዜማ እያዋዛ በመንገር የሚኩራራ ይመስላል (ዘፍ. 4፡23-24)። ቃየን የእግዚአብሔርን ምሕረት ሲጠይቅ፣ ላሜሕ ግን ይህን ስለማድረጉ የተመዘገበ ነገር አናገኝም። ቃየንን የሚገድል በእግዚአብሔር ሰባት ጊዜ የበቀል ቅጣት እንደሚቀበል መገለጹ እሙን ቢሆንም፣ የላሜሕ ገዳይ ግን ሰባ ሰባት ጊዜ ቅጣት ያገኘዋል ብሎ ራሱን ሲሸነግል ይታያል (ዘፍ. 4፡24)። ከላይ የቀረቡት ነጥቦች ላሜሕ ስለ በደለኝነቱ ከፍ ያለ ግንዛቤ እንደነበረው ፍንጭ ይሰጡናል።

በተጨማሪ ቃየን በአንድ ሚስት የተወሰነ ሲሆን (ዘፍ. 4፡17)፣ ላሜሕ ግን ከአንድ በላይ በማግባት አለሌነትን ያስተዋወቀ ሰው ነበር። በተለይ ይህን አስመልክቶ አምላካዊው ቃል፡ “ላሜሕ ሁለት ሚስቶች አገባ” (ዘፍ. 4፡17) ይለናል። ይህ እየተባባሰና እየተስፋፋ የሄደ ክፋት፣ በቀጣይ የቃየን ትውልድ ላይ ተጽእኖ ማሳደሩ ምንም ጥርጥር የለውም።

ይህን የቃየን ቤተሰብ የክፋት ክስተት ምዕራፍ ተከትሎ፣ ወዲያውኑ መጽሐፍ ቅዱስ ቃየናዊውን አካሄድ የሚጻረር አዲስ ኩነት ዘግቦ እንመለከታለን። “አዳም ደግሞ ሚስቱን አወቀ” (ዘፍ. 4፡25 [1962 ዕትም]) በውጤቱም ሴት ተወለደ። ሔዋን--በአቤል ፋንታ እግዚአብሔር “ሌላ ዘር ተክቶልኛል” [1962 ዕትም] ስትል ይህን ስም አወጣችለት።

እንደ እውነቱ ከሆነ ሴት የተባለው ስያሜ ታሪክ ከአቤል ይቀድማል። ሴት የተባለው ስም “አሺት” በመባል ከሚታወቀውና የመሲህን ትንቢት ከሚያስተዋውቀው “አደርጋለሁ” (ዘፍ. 3፡15) ከሚለው የዕብራይስጥ ግስ የመጣ ነው። መሲህአዊው ዘር በሴት የዘር ሀረግ የሚያልፍ ይሆናል። በመሆኑም ከሴት የሚጀምረው (ዘፍ. 5፡3) መጽሐፍ ቅዱሳዊው የመሲህ የዘር ሃረግ ዘገባ ሄኖክን (ዘፍ. 5፡21) እና ማቱሳላን አካትቶ በኖህ ይደመደማል (ዘፍ. 6፡8)።

“የእግዚአብሔር ወንዶች ልጆች” (ዘፍ. 6፡2) የሚለው ሐረግ እነዚህ ወገኖች የእግዚአብሔርን መልክ ጠብቀው እንዲያቆዩ (ዘፍ. 5፡1፣ 4) የታቀዱ መሆናቸው ያሳያል። በሌላ በኩል “የሰዎች ሴቶች ልጆች” (ዘፍ. 6፡2) የሚለው ሐረግ በእግዚአብሔር አምሳል የሚገኙትን ትውልዶች፣ በሰው አምሳል ከሚገኙት ጋር እያነጻጸረ አሉታዊ ትርጉም የሚሰጣቸው ይመስላል። እናም “በሰዎች ሴቶች ልጆች” ተጽእኖ ስር የወደቁት የእግዚአብሔር ወንዶች ልጆች “ከመካከላቸው የመረጧቸውን” ማግባታቸው (ዘፍ. 6፡2) ሰው እየሄደበት የነበረውን የተሳሳተ አቅጣጫ ይጠቁማል።

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፍ. 6፡1-5። ኃጢአት ምን ያህል እንደሚበክል የሚያሳይ እንዴት ያለ ብርቱ ምስክር ነው! ኃጢአትን ከሕይወታችን ለማጥፋት በእግዚአብሔር ኃይል የምንችለውን ሁሉ ማድረግ ያለብን ለምንድን ነው?

ሚያዝያ 7
Apr 15


ተጨማሪ ሀሳብ


“ሄኖክ አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር አደረገ” (ዘፍ. 5፡ 22) በሚል በተደጋጋሚ የቀረበው ሐረግ ከእግዚአብሔር ጋር የጠበቀ የዕለት ከዕለት ወዳጅነት መሥርቶ ነበር የሚል ፍቺ አለው። ሄኖክ ከእግዚአብሔር ጋር መሥርቶት የነበረው የግል ግንኙነት ከወትሮው በእጅጉ የተለየ ስለነበር እነሆ “እግዚአብሔር ወሰደው” (ዘፍ. 5፡24)። ይህ የመጨረሻ ሃረግ ለአዳም ዘር እንግዳ እና በዓይነቱ የተለየ ቢሆንም፣ “አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር” የሚያደርግ ማንም ሰው በቅጽበት በገነት የዳግም ሕይወት ባለቤት ይሆናል የሚል ጽንሰ ሀሳብን አይደግፍም። እዚህ ላይ በተጨማሪ ኖህ አካሄዱን ከእግዚአብሔር ጋር ማድረጉን (ዘፍ. 6፡9)፣ ሆኖም አዳምና ማቱሳላን ጨምሮ እንደማንኛውም ሰው መሞቱን መገንዘብ ያሻል። በተጨማሪ ለዚህ በዓይነቱ ልዩ የሆነ ጸጋ ይህ ነው የሚባል ምክንያት አለመሰጠቱን ልብ ይሏል።

“የጽድቅ ሰባኪ የሆነው ሄኖክ እግዚአብሔር የገለጠለትን ለህዝቡ ያሳውቅ ነበር። ጌታን ይፈሩ የነበሩ ወገኖች የሄኖክን መመሪያ እና ጸሎት በመሻት ይህን ቅዱስ ሰው ለመገናኘት ይተጉ ነበር። እግዚአብሔርን በይፋ ያገለግል የነበረው ሄኖክ የማስጠንቀቂያውን መልእክት ለሚሰሙ ሁሉ አምላካዊውን መልእክት ያስተላልፍ ነበር። የእርሱ አገልግሎት ለሴት ዝርያ ብቻ የተወሰነ አልነበረም። ቃየን ከእግዚአብሔር ፊት ሸሽቶ ለመኮብለል በሞከረበት ምድር ላይ የእግዚአብሔር ነቢይ በራእይ የተቀበላቸውን ድንቃድንቅ ትዕይንቶች ይፋ አድርጎአል። ‘እነሆ ጌታ ከእልፍ አእላፋት ቅዱሳኑ ጋር ይመጣል። ይህም በሰው ሁሉ ላይ ለመፍረድ እንዲሁም አመጸኞችን ሁሉ በክፋት መንገድ በሠሩት የዐመጽ ሥራና በክፋት በእርሱ ላይ ስለተናገሩት የስድብ ቃል ሁሉ አጥፊነታቸውን ይፋ ለማድረግ ነው’ ” (ይሁዳ 14-15)። (የኃይማኖት አባቶችና ነቢያት፡ ገጽ 87)


የመወያያ ጥያቄዎች



1.ቃየን ወንድሙን ለምን ገደለው? የሚከተለውን የኤሊ ዊዝል አስተያየት ያንብቡ፡ “ለምን እንዲህ አደረገ? ምናልባት ብቻውን ለመኖር ፈልጎ ይሆን? ብቸኛ ልጅ በመሆን ወላጆቹ ከሞቱ በኋላ ብቸኛ ሰው ሆኖ ለመቅረት? እንደ እግዚአብሔር አንድ ብቻ ለመሆንና ምናልባትም በእግዚአብሔር ፋንታ ብቻውን ለመሆን. . . እነሆ ቃየን አምላክ ለመሆን ግድያ ፈጸመ. . . ራሱን እንደ አምላክ የሚያደርግ ማንኛውም ሰው መጨረሻው ሰው መግደል ይሆናል።”—Elie Wiesel, Messengers of God: Biblical Portraits and Legends (New York: Random House, 1976), p. 58. በሰው ላይ ግድያ ባንፈጽምም እንኳ፣ የቃየንን ባህሪ ላለማንጸባረቅ እንዴት መጠንቀቅ እንችላለን?

2.ከውሃ ጥፋት አስቀድሞ ይኖሩ የነበሩ ሕዝቦችን የዕድሜ ዘመን (ዘፍ. 5) ከጥፋት ወዲህ ካሉ የኃይማኖት አባቶች ጋር ያስተያዩ። ይህን የሰው ልጅ የዕድሜ ዘመን ማሽቆልቆል እንዴት እናብራራለን? ይህ ማሽቆልቆል ዳርዊናዊውን የዘመናዊ ዝግመተ ለውጥ ንድፈ ሀሳብ እንዴት ይቃረናል?




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA union SSL