የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ዘፍጥረት


የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 2ኛ ሩብ ዓመት 2022

ከመጋቢት 24-30

2ኛ ትምህርት

Apr 2 - Apr 8




ውድቀት



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ዘፍ. 3፡2፣ 2ቆሮ. 11:3፣ ራእ. 12:7–9፣ ዮሐ. 8:44፣ ሮሜ 16:20፣ ዕብ. 2:14፣ 1 ጢሞቴ. 2:14-15


የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ“ ‘ በአንተና በሴቲቱ፣ በዘርህና በዘሯ መካከል፣ ጠላትነትን አደርጋለሁ፤ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፤ አንተም ተረከዙን ትቀጠቅጣለህ።” (ዘፍ. 3፡15)።

እ ግዚአብሔር በኤደን ለነበሩት ለመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን በሰጣቸው በእነዚያ ሁሉ ስጦታዎች መሃል እንዲህ የሚል ማስጠንቀቂያም አለ፡ “ ‘በአትክልት ስፍራው ውስጥ ከሚገኝ ከማንኛውም ዛፍ ፍሬ ትበላለህ። ነገር ግን መልካምና ክፉን ከሚያሳውቀው ዛፍ አትብላ፤ ምክንያቱም ከእርሱ በበላህ ቀን በእርግጥ ትሞታለህ’ ” (ዘፍ. 2፡16-17)። ምንም እንኳ መልካም የሆነውን ማወቅ የነበረባቸው ቢሆንም፣ ይህ መልካምና ክፉን ከሚያሳውቀው ፍሬ እንዳይበሉ የተሰጣቸው ማስጠንቀቂያ (ዘፍ. 2፡16-17) ክፉን ማወቅ እንዳልነበረባቸው ያሳየናል።

ይህ የሆነበትን ምክንያት በትክክል መረዳት እንችላለን--አይደል? እናም ከአለመታዘዝ ጋር ቁርኝት ያለው የሞት አደጋ (ዘፍ. 2፡17) ተፈጻሚነት ስለሚያገኝ--ይሞታሉ (ዘፍ. 3፡19)። ከፍሬው ደግመው እንዳይበሉ መከልከል ብቻ ሳይሆን ከኤደን የአትክልት ስፍራ መባረር ነበረባቸው (ዘፍ. 3፡24)። ምክንያቱም እንደ ኃጢአተኛ የዘላለም ሕይወት ሊሰጣቸው የሚችለውን ነገር ማግኘት የማይችሉ ይሆኑ ነበር (ዘፍ. 3፡22)።

ሆኖም፣ በዚህ አሳዛኝ ሁኔታ መሃል “የመጀመሪያው የወንጌል ተስፋ” በሚል የሚታወቀው በዘፍ. 3፡15 የሚገኘው የተስፋ ቃል መሰጠቱን እንመለከታለን። አዎ--ይህ ጥቅስ በመጽሐፍ ቅዱስ የቀረበውን የመጀመሪያ የወንጌል ተስፋ ቃል ይፋ ያደርግልናል። ውድቀት ቢከሰትም እንኳ እግዚአብሔር ማምለጫ መንገድ ስለ ማዘጋጀቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ለሰዎች ይነገራቸዋል።

መጋቢት 25
Apr 3

እባቡ


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፍ. 3፡1፣ 2ቆሮ. 11፡3፣ ራእ. 12፡7-9። እባቡ ማን ነው? እንዴት ሔዋንን ሊያስታት ቻለ?



ጥቅሱ “እባብ” በሚል ቃል ይጀምራል። “እባብ” የአረፍተ ነገሩ የመጀመሪያ ቃል መሆኑ፣ ቃሉ አጽንኦት ሊሰጠው እንደሚገባ የሃረጉ አገባብ ይጠቁማል። በተጨማሪ አንባቢው ማንነቱን አስቀድሞ ሊለይ በሚችል አግባብ የቀረበው “እባብ” የሚለው መስተአምራዊ አቀራረብ፣ የሚታወቅ ማንነት እንዳለው ይጠቁማል። በመሆኑም የዚህ አካል ተጨባጭ ማንነት በምዕራፉ የመጀመሪያ ቃል ተረጋግጦአል።

ቅዱሳት መጻሕፍት እባቡ የእግዚአብሔር ጠላት መሆኑን (ኢሳ. 27፡1) ለይተው በማቅረብ “ዲያብሎስ ወይም ሰይጣን” (ራእ. 12፡9) ብለው በግልጽ ይጠሩታል። በተመሳሳይ በጥንቱ ቅርብ ምሥራቅ አካባቢ እባብ የክፉ ኃይል መገለጫ ተደርጎ ይወሰድ ነበር።

“ሰይጣን የተነሳበትን ዕኩይ ዓላማ በትጋት ማከናወን ይችል ዘንድ ለመልዕክቱ ማስተላለፊያ እባብን መረጠ። እባብ በጣም ብልህና በምድር ካሉ ፍጥረታት ሁሉ የተዋበ ፍጥረት ነበር። ክንፎች የነበሩት ይህ ፍጡር ሲበር ያማረና ወርቃማ አንጸባራቂ ብርሐን ነበረው።” (የኃይማኖት አባቶችና ነቢያት፡ ገጽ 53) መጽሐፍ ቅዱስ ዲያብሎስን በየትኛውም ቅርጽ ቢገልጸውም፣ ስለ እርሱ የሚናገረው--ተራ ዘይቤያዊ አባባል አይደለም። በመጽሐፍ ቅዱስ ሰይጣን የተገለጸው ተጨባጭ ማንነት እንዳለው ተደርጎ እንጂ፣ ክፉ የሆነውን ነገር ለመግለጽ ወይም ሰብዓዊውን ጽልመታዊ ጎን ለማሳየት ሲባል ጥቅም ላይ የዋለ ተምሳሌታዊ ወይም የማይጨበጥ ምናባዊ ነገር አይደለም። እባብ ራሱን የእግዚአብሔር ጠላት አድርጎ አያቀርብም። እንደውም በተቃራኒው እባብ አምላካዊውን ቃል ይደግፍ ይመስል የእግዚአብሔርን ቃል በተደጋጋሚ ይጠቅሳል። በዚህም ገና ከመጀመሪያው አንስቶ ሰይጣን እግዚአብሔር የተናገረውን መጥቀስ ደስ የሚያሰኘው ነገር መሆኑን እናያለን። እንደውም ኋላ ላይ የእግዚአብሔርን ቃል--ቃል በቃል ሲጠቅስ መመልከት እንችላለን (ማቴ. 4፡6)።

እባቡ ወዲያውኑ ከሴቲቱ ጋር ሙግት ውስጥ እንዳልገባ እዚህ ላይ ልብ ማለት ተገቢ ነው። ይልቁንም ጌታ ነግሯቸዋል ብሎ ያመነውን በማንሣት “ ‘በእርግጥ እግዚአብሔር… ብሏል’ ” (ዘፍ. 3፡1) ሲል ይጠይቃታል። በዚህም ይህ ፍጡር ምን ያህል ተንኮለኛና አታላይ እንደነበር ገና ከጅምሩ መመልከት እንችላለን። ወደፊት የሚሆነውን እንደምንመለከተው፣ ይህም ሠርቶለታል። ሰይጣን በኤደን የነበረችውን ኃጢአት የሌለባትን ሔዋን ማታለል ከቻለ፣ እኛ ስንት እጥፍ ለሴራው የተጋለጥን ነን? ከእርሱ ማታለያዎች ለመጠበቅ ምርጥ መከላከያችን ምንድን ነው?

መጋቢት 26
Apr 4

የተከለከለው ፍሬ


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፍ. 2፡16-17፣ ዘፍ. 3፡1-6። በተጨማሪ ዮሐ. 8፡44 ይመልከቱ። እግዚአብሔር ለአዳም የሰጠውን ትእዛዝ እባቡ ለሴቲቱ ከተናገራቸው ቃላት ጋር ያነጻጽሩ። በሁለቱ ንግግሮች መሃል ያሉት ልዩነቶች ምንድን ናቸው? የእነዚህ ልዩነቶች ፍቺስ ምንድን ነው?



እግዚአብሔር ከአዳም ጋር ባደረገው ንግግር (ዘፍ. 2፡16-17) እና ሔዋን ከእባቡ ጋር ባደረገችው ንግግር መሃል ያሉትን መመሳሰሎች ልብ ይበሉ። ከእባቡ ሁኔታ መረዳት እንደሚቻለው እግዚአብሔርን የተካ እና ከእርሱ የበለጠ የሚያውቅ መስሎ የቀረበ ይመስላል። መጀመሪያ የጠየቃት ጥያቄ ሴቲቱ ምናልባት እግዚአብሔርን በተሳሳተ መንገድ አስተውላው እንዳይሆን የሚል ዐውድ ብቻ ያዘለ ይመስላል። ከዚያ ግን ሰይጣን በእግዚአብሔር ውጥን ላይ ግልጽ ጥያቄ ያነሣና፣ አልፎ ተርፎም እርሱን ወደ መቃወም ያመራል። የሰይጣን ጥቃት ሁለት ጉዳዮችን ማለትም ሞት እና መልካምና ክፉን ማወቅን ይመለከታል። እግዚአብሔር ከፍሬው ከበሉ መሞታቸው የተረጋገጠ መሆኑን በግልጽ እና በአጽኖት ቢናገርም (ዘፍ. 2፡17) ሰይጣን ግን የሰዎችን ሟች አለመሆን በሚያሳይ ዐውድ፣ በተቃራኒው እንደማይሞቱ ተናገረ (ዘፍ. 3፡4)። አዳም ከፍሬው እንዳይበላ እግዚአብሔር የከለከለው ቢሆንም (ዘፍ. 2፡17) ሰይጣን ግን ፍሬውን ከበሉ እንደ እግዚአብሔር እንደሚሆኑ በመንገር አበረታታቸው (ዘፍ. 3፡5)።

ሁለቱ የሰይጣን መከላከያ ነጥቦች ማለትም አለመሞት እና እንደ እግዚአብሔር መሆን፣ ከፍሬው ትበላ ዘንድ ሔዋንን አሳመኗት። ሴቲቱ እግዚአብሔርን ላለመታዘዝ እና ከፍሬው ለመብላት እንደ ወሰነች፣ ወዲያውኑ የአምላካዊው ሕልዎት ያከተመለትና በራሷ ብቻ የቆመች የሚመስል ሁናቴ በእርሷ መስተዋሉ እጅግ ያሳዝናል። መጽሐፍ ቅዱስ ይህን የተስተዋለባትን የባህሪ ለውጥ ይጠቅሳል። አሁን ሔዋን እግዚአብሔር በፍጥረት ወቅት የተናገረውን አባባል ቃል በቃል ለራሷ ወሰደች፣ እናም የተከለከለውን ፍሬ አስመልክቶ በደረሰችበት የግል ምዘና “መልካም… እንደሆነ… አየች” (ዘፍ. 3፡6)። ይህ አባባል እግዚአብሔር “መልካም እንደሆነ አየ” (ዘፍ. 1፡4 ወዘተ.) ሲል የፍጥረት ሥራውን አስመልክቶ የሰጠው የግምገማ ቃል ነበር።

እነዚህ ፈታኝ የሆኑ ሁለት ጉዳዮች ማለትም አለመሞት እና እንደ እግዚአብሔር መሆን፣ የጥንት ግብጻውያን እና ግሪካውያን ኃይማኖታዊ የማይሞት ባህሪ ጽንሰ ሀሳብ ሥረ መሠረቶች ናቸው። መለኮታዊ ባህሪ እንደሆነ ያምኑ የነበረው የአለመሞት ምኞታቸው፣ እነዚህ ሕዝቦች (ተስፋ ያደረጉትን) አለመሞትን ያገኙ ዘንድ መለኮታዊውን ማንነት እንዲፈልጉም አስገድዷቸው ነበር። ይህ አስተሳሰብ በአይሁድ--ክርስቲያን ባሕል በስውር ዘልቆ በመግባት ነፍስ አትሞትም የሚል እምነት እንዲወለድ ያደረገ ሲሆን፣ እነሆ ዛሬም በብዙ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ይገኛል።

በእኛ በሁላችንም ውስጥ አንድ የማይሞት ነገር አለ ብለው ዛሬ ስለሚያስተምሩ ስለ ሁሉም ዓይነት ቤተ እምነቶች አሰብ ያድርጉ። ስለ ሰው ተፈጥሮ እና በመቃብር ስለሚገኙ ሙታን ሁኔታ ያለን ግንዛቤ ለዚህ አደገኛ ማታለያ ብርቱ ጥበቃ ሊያደርግልን የሚችለው እንዴት ነው?

መጋቢት 27
Apr 5

ከእግዚአብሔር ፊት መሸሸግ


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፍ. 3፡7-13። አዳምና ሔዋን ከእግዚአብሔር ፊት መሸሸግ እንዳለባቸው የተሰማቸው ለምንድን ነው? እግዚአብሔር “የት ነህ?” የሚለውን ጥያቄ ለምን ጠየቀ? አዳምና ሔዋን ለፈጸሙት ድርጊት ሰበብ ለማቅረብ የሞከሩበት መንገድ ምን ይመስላል?



አዳምና ሔዋን ኃጢአት ከሠሩ በኋላ የእግዚአብሔርን ህልዎት ያንጸባርቅ የነበረውን የክብር ልብሳቸውን ስላጡ ራቁታቸውን እንደሆኑ ተሰማቸው (ጥቅሶቹን ያስተያዩ፡ መዝ. 8፡5፣ መዝ. 104፡1-2)። የእግዚአብሔር አምሳል በኃጢአት ተጎድቶ ነበር። “ሰፍተው አገለደሙ” (ዘፍ. 3፡7) የሚለው ጥቅስ በእንግሊዝኛው “made themselves coverings” በሚል ቀርቧል። ታዲያ በዚህ ሀረግ ውስጥ የምናገኘው “make” (ማድረግ) የተሰኘው ግስ እስከዚያን ጊዜ ድረስ እንደ ፈጣሪነቱ፣ ለእግዚአብሔር ብቻ ጥቅም ላይ የዋለ ቃል ነበር (ዘፍ. 1፡7፣ 16፣ 25 ወዘተ።) ኃጢአታቸውን ለመሸፋፈን ያደርጉ በነበረው ሙከራ፣ የእግዚአብሔርን ቦታ ተክቶ የመውሰድ የሚመስል ሁናቴ የተስተዋለባቸው ሲሆን፤ ሁናቴው ጳውሎስ ጽድቅ በሥራ በሚል የሚያወግዘው ድርጊት አካል ነበር (ገላ. 2፡16)።

በአቅራቢያቸው የነበረው እግዚአብሔር ከእነርሱ መልስ ለማግኘት ብሎ ሳይሆን ነገር ግን ትኩረታቸውን ለመሳብ ወይም አንድ ክስተት ገቢራዊ መሆኑን ለማመልከት “የት ነህ?” (ዘፍ. 3፡9) ሲል ጠየቀ። እግዚአብሔር በዘፍ. 4፡9 ተመሳሳይ ይዘት ያለው ጥያቄ ቃየንን ሲጠይቅ እንመለከታለን። በእርግጥ እግዚአብሔር የጥያቄዎቹን መልስ አስቀድሞ ያውቅ ነበር። ጥያቄዎቹ ጥፋት ለሠራው ወገን ጥቅም ሲባል የቀረቡ ሲሆን፣ ይኸውም በዳዩ በደሉን መገንዘብ እንዲችል ለመርዳትና ከዚያም አልፎ ተርፎ ግለሰቡን ወደ ንስሐ እና ደኅንነት ለመምራት ነበር። ሰዎች ኃጢአት ከሠሩበት ጊዜ ጀምሮ ጌታ እነርሱን ለማዳንና ለመቤዠት እየሠራ ነበር።

በእርግጥ አጠቃላዩ ሥዕላዊ አቀራረብ ዳኛው የጥፋተኛውን ቃል ከተቀበለ በኋላ (ዘፍ. 3፡9) ለሚሰጠው የፍርድ ውሳኔ በደለኛውን በማዘጋጀት (ዘፍ. 3፡ 14-19) የሚጀምረውን የፍርድ ምርመራ ጽንሰ ሀሳብ ያንጸባርቃል። ነገር ግን ይህን የሚያደርገው ግለሰቡን ውሎ አድሮ ወደ መዳን ሊመራው ወደሚችል ንስሐ ለማምጣት ጭምር ነው (ዘፍ. 3፡15)። ይህ በመላው መጽሐፍ ቅዱስ ጎልቶ የሚታይ ጽንሰ ሀሳብ ነው።

በመጀመሪያ ላይ፣ በኃጢአተኞች እንደ ተለመደው አዳምና ሔዋን፣ ሁለቱም ከቀረበባቸው ክስ ለማምለጥ አንዱ በሌላው ላይ ጣት ለመቀሰር ሞከረ። አዳም በእግዚአብሔር ለቀረበው ጥያቄ ሲመልስ በፈጣሪ የተሰጠችው ሴት (ዘፍ. 3፡12) እንዲበላ እንዳደረገችው ተናገረ። ይህ አዳም የሰጠው መልስ ጥፋቱ የእርሷ (እንዲሁም የእግዚአብሔር ጭምር) እንጂ የእርሱ አለመሆኑን የሚያሳይ አንደምታ ነበረው።

ሔዋን ደግሞ እርሷን ያሳሳታት እባቡ እንደሆነ ተናገረች። “አሳሳታት” (ዘፍ. 3፡13) በሚል የቀረበው የዕብራይስጥ ግስ፣ ለሰዎች ሐሰተኛ ተስፋዎች መስጠትና ትክክለኛውን ነገር እያደረጉ እንደሆነ አድርጎ ማሳመን ነው። (2 ነገሥ. 19:10፣ ኢሳ. 37:10፣ ኤር. 49:16)።

አዳም ሴቲቱ ፍሬውን እንደሰጠችው በመናገር በእርሷ ላይ ሲያመኻኝ (ጥቂት እውነት አለው)፣ ሔዋን ደግሞ እባቡ እንዳሳሳታት በመናገር በእርሱ ላይ አመኻኘች (ይህም ሌላ ጥቂት እውነት አለው)። ሆኖም በመጨረሻ ሁለቱም ጥፋተኞች ነበሩ።

ራሳቸው ለሠሩት ጥፋት በሌላው ላይ ለማላከክ መሞከር? ከዚህ ተመሳሳይ ወጥመድ ውስጥ መውደቅ ለእኛ ያን ያህል ቀላል የሆነው ለምንድን ነው?

መጋቢት 28
Apr 6

የእባቡ መጻኢ ዕድል


“ ‘በአንተና በሴቲቱ፣ በዘርህና በዘሯ መካከል፣ ጠላትነትን አደርጋሁ፤ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፣ አንተም ተረከዙን ትቀጠቅጣለህ’ ” (ዘፍ. 3፡15)። እዚህ ላይ ጌታ እባቡን ምን አለው? ጥቅሱ ምን ተስፋ ይዟል?



እግዚአብሔር ፍርዱን የሚጀምረው በእባቡ ነው። ምክንያቱም የዚህ ሁሉ ክስተት ወጣኝ እርሱ በመሆኑ ነው። እንዲሁም በዚህ ታሪክ ብቸኛ እርግማን የደረሰበት ፍጡር እባቡ ነው።

አሁን የፍጥረት ሥራ “ተገላቢጦሽ” በሚመስል ሁናቴ ላይ መድረሱን እንመለከታለን። ሥነ ፍጥረት ወደ ሕይወት፣ መልካሙን ወደ ማድነቅ እና ወደ ተትረፈረፈ የበረከት ጎዳና ይመራል። በአንጻሩ ፍርድ--ሞት እና እርግማን የማስከተሉን ያህል የደኅንነት ተስፋ እና ኪዳንም እንዲሁ ያስገኛል። ዐፈር እንዲበላና (ዘፍ. 3፡14) ራሱ እንዲቀጠቀጥ ከተፈረደበት በጽልመት የተሞላ ሥዕላዊ ትዕይንት ባሻገር--በትንቢት ቅርጽ የቀረበ የሰብዓዊውን ዘር የመዳን ተስፋ የሚያንጸባርቅ መልእክት ቀርቦ እናገኛለን። በአዳምና ሔዋን ላይ የእርግማን ቃል ከመነገሩ በፊት እንኳ ሳይቀር ጌታ የመዳን ተስፋ ሰጥቷቸዋል (ዘፍ. 3፡15)። አዎ--ኃጢአት ሠርተዋል። አዎ--በኃጢአታቸው የተነሣ ሥቃይ ይደርስባቸዋል። እንዲሁም ይህን ተከትሎ መሞታቸው የማይቀር ሐቅ ነው። ያም ሆኖ ግን፣ ውሎ አድሮ ተስፋ አለ--የመዳን ተስፋ!

የሚከተሉትን ሦስት ጥቅሶች ከዘፍ. 3፡15 ጋር ያስተያዩ፡ ሮሜ 16፡20፣ ዕብ. 2፡14፣ ራእ. 12፡17። የደኅንነት እቅድ እንዲሁም በብርሃን እና በጨለማ ኃይላት መካከል የሚደረገው ታላቁ ተጋድሎ በዚህ ጥቅስ የተገለጸው እንዴት ነው?



በዘፍ. 3፡15 እና በራእ. 12፡17 መካከል ያለውን መመሳሰል ልብ ይበሉ፡ --ዘንዶው (እባብ)፤ መቆጣቱ (ጠላትነት)፤ ልጆቿ (ዘሯ) እንዲሁም በኤደን የነበረችው ሴት (በራእ. 2፡17 የቀረበችው ሴት)። ወደ ኤደን የተዛወረው ውጊያ (ታላቁ ተጋድሎ) እስከ ዘመን ፍጻሜ ድረስ ይቀጥላል። የሆነው ሆኖ፣ ስለ ሰይጣን ሽንፈት የሚናገረው የተስፋ ቃል፣ ራሱ እንደሚቀጠቀጥ በሚገልጸው መልእክት አስቀድሞ በኤደን የተሰጠ ሲሆን፣ ይኸው ጭብጥ በመጨረሻ የሚደርስበትን መደምሰስ ይበልጥ ግልጽ አድርጎ በሚያሳየው የራእይ መጽሐፍ ተገልጾአል (ራእ. 20፡10)። ገና ከመጀመሪያው አንስቶ ሰብዓዊው ዘር ክፉን በማወቁ የተነሣ ለደረሰበት ዘግናኝ ውድቀት መውጫ መንገድ እንደሚኖር ተስፋ ተሰጥቶት ነበር። ይህ ደግሞ፣ እነሆ እኛ ሁላችንም ዛሬ ልንጋራው የምንችለው ተስፋ ነው።

ኃጢአት እና ክፋት በጀመረበት በዚያው በኤደን፣ ጌታ የደኅንነትን እቅድ መግለጥ መጀመሩን መመልከታችን አብልጦ የሚያጽናናን ለምንድን ነው?

መጋቢት 29
Apr 7

የሰው መጨረሻው


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፍ. 3፡15-24። ውድቀትን ተከትሎ በአዳምና ሔዋን ላይ ምን ደረሰ?



በግልጽ እንደሚታወቀው እግዚአብሔር በእባቡ ላይ የሰጠው ፍርድ እርግማን ሲሆን (ዘፍ. 3፡14)፣ በሴቲቱ እና በወንዱ ላይ የሰጠው ፍርድ ግን እርግማን አልነበረም። “እርግማን” የተሰኘው ቃል በዚህ ታሪክ ውስጥ በድጋሚና በብቸኝነት ጥቅም ላይ የዋለው ይህችን “ምድር” (ዘፍ. 3፡17) አስመልክቶ በተነገረው ላይ ነው። ይህ ማለት ከእባቡ በተቃራኒ እግዚአብሔር ለወንዱም ሆነ ለሴቷ ሌሎች እቅዶች ነበሩት። ለእባቡ ያልተሰጡ የተስፋ ቃሎች እነሆ ለእነርሱ ተሰጥተው ነበር።

የሴቲቱ ኃጢአት እርሷ ከእባቡ ጋር የፈጠረችውን ግንኙነት ተከትሎ የመጣ በመሆኑ፣ እግዚአብሔር በሴቲቱ ላይ ስለ ሰጠው ፍርድ የሚገልጸው ጥቅስ ከእባቡ ፍርድ ጋር የተያያዘ ነው። ዘፍ. 3፡16 ወዲያውኑ ዘፍ. 3፡15ን የሚከተል ብቻ ሳይሆን፣ ነገር ግን በሁለቱ ትንቢቶች መካከል ያለው መመሳሰል-ሴቲቱን አስመልክቶ በዘፍ. 3፡16 የቀረበው ትንቢት በዘፍ. 3፡15 ከቀረበው የመሲህ ትንቢት ጋር በተያያዘ ሊነበብ እንደሚገባ በግልጽ ያሳያል። ስለዚህ እግዚአብሔር ልጅ መውለድን ጨምሮ በሴቲቱ ላይ የሰጠው ፍርድ ከደኅንነት አዎንታዊ ምልከታ አኳያ ሊስተዋል ይገባል (1ጢሞቴ. 2፡14)።

ወንዱ እግዚአብሔርን ከማድመጥ ይልቅ የሴቲቱን ቃል በመስማቱ ምክንያት ኃጢአት በመሥራቱ፣ እነሆ ሰው የመጣበት ምድር ተረገመ (ዘፍ. 3፡17)። በውጤቱም የወንዱ ጥሮ ግሮ መኖር (ዘፍ. 3፡17-19) እልፍ ሲልም ወደ መጣበት “ ‘ዐፈር’ ” መመለስ (ዘፍ. 3፡19)--ፍጹም መሆን ያልነበረበት እና የቀደመው አምላካዊ እቅድ አካል ያልነበረ ነው።

ከዚህ ተስፋ አስቆራጭ የሞት ድባብ በተቃራኒ አዳም ፊቱን ወደ ሴቲቱ መልሶ፣ በእርሷ መውለድ የሕይወትን ተስፋ መመልከቱ ወሳኝና አስፈላጊ ነጥብ ነው (ዘፍ. 3፡20)። በሞት ፍርድ ውስጥም እንኳ የሕይወትን ተስፋ ይመለከታልና! እርግጥ ነው--እንደ ማንኛውም አፍቃሪ ወላጅ እግዚአብሔር ለእነርሱ ይመኝ የነበረው በጎውን ሁሉ እንጂ ክፉውን አልነበረም። ነገር ግን አሁን ክፋትን ስላወቁ እግዚአብሔር እነርሱን ከክፉ ለማዳን የተቻለውን ሁሉ ያደርጋል። ምንም እንኳ የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን ግልጽና ሐፍረት የለሽ አለመታዘዝ በእግዚአብሔር ፊት ቢያሳዩም፣ በፍርዶቹ መሃል--ለመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን የነበረው ተስፋ ሙሉ በሙሉ የተሟጠጠ አልነበረም። እነርሱ በገነት ውስጥ በእውነት የሚመላለሱ ከመሆናቸው አኳያ ፈጣሪ አምላክን፣ ቃሉን ወይም ለእነርሱ ያለውን ፍቅር የሚጠራጠሩበት አንዳች ምክንያት አልነበራቸውም። ምንም እንኳ “ዕውቀት” በራሱ ጥሩ እንደሆነ አድርገን የማሰብ አዝማሚያ ቢኖረንም፣ ይህ ሁል ጊዜ እንደታሰበው የማይሆነው ለምንድ ነው? ሳናውቃቸው በመቅረታችን የተሻለ ሊሆንልን የሚችሉ አንዳንድ ነገሮች ምንድን ናቸው?

መጋቢት 30
Apr 8


ተጨማሪ ሀሳብ


በ “ሕይወት ዛፍ” እና “መልካምና ክፉን መለየት የሚያስችለው የዕውቀት ዛፍ” መካከል ያለውን ግንኙነት ይመልከቱ። “በአትክልቱ ቦታ መካከል” (ዘፍ. 2፡9) የመገኘታቸው ተጨባጭ እውነታ ሁለቱንም እንደሚያዛምድ አስቀድሞ ተጠቅሷል። ነገር ግን ተመሳሳይ መልክአ ምድር በአንድ ከመጋራታቸው ባሻገር፣ የላቀ ነገር በሁለቱ መካከል አለ። እነዚህ ሰብዓዊ ፍጡራን መልካምና ክፉን መለየት ከሚያስችለው የዕውቀት ዛፍ ፍሬ ቀጥፈው በመብላታቸው እና እግዚአብሔርን ባለመታዘዛቸው ምክንያት ቢያንስ በዚህኛው ማንነታቸው ወደ ሕይወት ዛፍ መድረስ እንዳይችሉና ለዘላለም እንዳይኖሩ ተከለከሉ። ይህ ግንኙነት በጥልቅ መርኅ ላይ የተመሠረተ ነው። ሰሎሞን “ልጄ ሆይ፤ ትምህርቴን አትርሳ፤ ትእዛዛቴን በልብህ ጠብቅ፤ ቀኖችን ይጨምሩልሃል፤ ዓመቶችንም ያረዝሙልሃል፤ ሕይወት፣ ሀብትንና ሰላምን ያበዙልሃል” (ምሳ. 22፡2) ሲል ልጁን እንዳዘዘው ሁሉ፣ ሥነ ምግባራዊ እና መንፈሳዊ ምርጫዎች በሥነ ሕይወታዊው ማንነት ላይ ተጽእኖ አላቸው። ይህ ዝምድና “በከተማይቱ አውራ መንገድ መካከል” (ራእ. 22፡2) የሕይወት ዛፍ ብቻ በሚገኝባት በወደፊቷ ሰማያዊ የሩሳሌም ዳግመኛ የሚኖር ይሆናል። “እግዚአብሔር ሔዋንን ሲፈጥራት ከወንዱ በታች ወይም በላይ አላደረጋትም፣ ይልቁንም በሁሉም ነገር የእርሱ አቻ አደረጋት። ቅዱሶቹ ጥንዶች ተመሳሳይ የጋራ ፍላጎት ቢኖራቸውም ነገር ግን በአስተሳሰብም ሆነ በግብር ሁለቱም የየራሳቸው ግለሰባዊ ማንነት ነበራቸው። ነገር ግን ከሔዋን ኃጢአት በኋላ፣ ማለትም አምላካዊውን ቃል በመጀመሪያ የተላለፈችው እርሷ መሆኗን ተከትሎ፣ እርሱ የበላይዋ እንደሚሆን ጌታ ነገራት። ለባሏ መገዛት ነበረባት።

እናም ይህ የእርግማኑ አካል ነበር። በብዙ አጋጣሚዎች እርግማኑ የሴትን ልጅ ዕጣ ፈንታ እጅግ መራር እና በሸክም የተሞላ አድርጎታል። እግዚአብሔር ለወንዱ የሰጠውን የበላይነት በብዙ መልኩ አግባብ በጎደለው አምባገነናዊ መንገድ ተጠቅሞበታል። የትዬለሌው መለኮታዊ ጥበብ ለሰብዓዊው ዘር ሌላ የአመክሮ ጊዜ እና ፈተና በመስጠት እነሆ የመቤዠትን ዕቅድ ነደፈ።”—Ellen G. White, Testimonies for the Church, vol. 3, p. 484.


የመወያያ ጥያቄዎች



1.እግዚአብሔር በኤደን የነበረውን አዳም ፊት ለፊት ገጥሞ ጥያቄ ያቀረበለት ጥፋቱን ለማረጋገጥ ብቻ ሳይሆን እርሱን ወደ ንስሐ ለመምራት ጭምር ነበር። ተመሳሳይ መርኅ በቃየን (ዘፍ. 4፡ 9-10)፣ በጥፋት ውሃ (ዘፍ. 6፡5-8)፣ በባቤል ግንብ (ዘፍ. 11፡ 5)፣ እንዲሁም በሰዶም እና ገሞራ (ዘፍ. 18፡21) እናገኛለን። የፍርድ ምርመራ ጽንሰ ሀሳብ በእነዚህ ክስተቶች የተገለጸው እንዴት ነው?

2.ሔዋን መልካምና ክፉን ከሚያሳውቀው ዛፍ መብላቷ ጥበብ እንደሚሰጣት አድርጋ ለምን አሰበች? እኛም አምላካዊውን ቃል በግልጽ በመናቅ እግዚአብሔር ከሰጠን “የተሻለ” ነገር እንዳለ ተስፋ ከማድረግ ተመሳሳይ ስህተት መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው?




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA union SSL