የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ዘፍጥረት


የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 2ኛ ሩብ ዓመት 2022

ከግንቦት 13 – 19

9ኛ ትምህርት

May 21 - May 27




በሕገወጥ መንገድ የወንድሙን መብት የቀማው--ያዕቆብ



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ዘፍ. 25:21–34፣ ዘፍ. 28:10–22፣ ዘፍ. 11:1–9፣ ዘፍ. 29:1–30፣ ዘፍ. 30:25–32።


የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ “ዔሳውም፣ ‘ይህ ሰው ያዕቆብ መባሉ ትክክል አይደለምን? እኔን ሲያታልለኝ ይሁ ሁለተኛ ጊዜው ነው፤ መጀመሪያ ብኵርናዬን ወሰደብኝ፤ አሁን ደግሞ ምርቃቴን ቀማኝ’ አለ። ቀጥሎም፣ ‘ታዲያ ለእኔ ያስቀረኸው ምንም ምርቃት የለምን? ብሎ ጠየቀ።” (ዘፍ. 27፡36)።

አ ሁን ታምረኛውን ልጅ እና ቀጣይነት ያገኘውን፣ የተስፋው ዘር ትውልድ የሆነውን የይስሐቅ ቤተሰብ ታሪክ እንመረምራለን። ይሁን እንጂ፣ ታሪኩ መልካም ገጽታ ይዞ አይጀምርም። የልጁ የያዕቆብ በእንከን የተሞላ ባህሪ፣ በሁለቱ ወንድማማቾች መካከል ለሚነሣው የብኩርና መብት ፉክክር (ዘፍ. 25፡27-34) እና ያን ተከትሎ የሚገኘውን የይስሐቅ ምርቃት የመቀበል መብት ላይ በጉልህ ይታያል (ዘፍ. 27)። ያዕቆብ አባቱን አታልሎ ከታላቅ ወንድሙ በረከትን ስለሰረቀ ነፍሱን ለማዳን መሸሽ ይኖርበታል። በስደት እያለ እግዚአብሔር በቤቴል ፊት ለፊት ይገጥመዋል (ዘፍ. 28፡10-22)። ከዚያ በኋላ አታላዩ ያዕቆብ ራሱ መታለል ይደርስበታል። ያዕቆብ በወደዳት በራሔል (ዘፍ. 29) ፋንታ ታላቋ ሊያ ለያዕቆብ ትሰጠዋለች። ስለዚህ ያዕቆብ ሚስቶቹን ለማግኘት ለ14 ዓመታት ማገልገል ነበረበት።

ያም ሆኖ፣ በስደት ህይወቱ አምላካዊውን በረከት የሚቀበለው ያዕቆብ፣ 11 ወንዶች ልጆች ይወልዳል፣ እግዚአብሔርም ሀብቱን ያበዛለታል።

ይህም ሆኖ፣ በዚህ ታሪክ የቱንም ዓይነት ክስተት ብንመለከትና ሕዝቡ የቱንም ያህል ጊዜ ቢሰናከልም፣ እግዚአብሔር በአንድ ወይም በሌላ መንገድ እንዴት የገባውን ኪዳን እንደሚፈጽም ማየት እንችላለን።

ግንቦት 14
May 22

ያዕቆብ እና ዔሳው


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ዘፍ. 25፡21-34። የያዕቆብን እና የዔሳውን ስብዕና ያነጻጽሩ። ያዕቆብን ለይስሐቅ በረከት ብቁ ያደረጉት ባህሪያት የትኞቹ ናቸው?



ያዕቆብና ዔሳው ገና ከእናታቸው ማህጸን አንስቶ የተለያዩና እርስ በርሳቸው የሚገፋፉ እንደነበሩ እንረዳለን። ዔሳው ጎበዝ አዳኝ እና የበረሃ ሰው ሲሆን፣ ያዕቆብ ግን “ጭምት” እና ከድንኳን ሳይወጣ ሲያሰላስል የሚውል ዓይነት ስብዕና ነበረው። “ጭምት” የተኘው ቃል የተወሰደው “ታም” ከተሰኘው የዕብራይስጥ ግስ ሲሆን፣ ይህ ግስ በተመሳሳይ ለኢዮብ እና ለኖኅ ጥቅም ላይ ውሏል። “ነቀፋ የሌለበት” ለኢዮብ (ኢዮ. 1፡8) እና “ፍጹም” ለኖኀ (ዘፍ. 6፡ 9 [1962 ትርጉም])።

ይህ የባህሪ ልዩነት በኋለኛው ሕይወታቸው ይበልጥ በጉልህ መታየት ችሏል (ዘፍ. 27፡1-28፡5)። ዔሳው ደክሞትና ተርቦ ወደ ቤት ሲመጣ ያዕቆብ ምስር ወጥ እየሠራ ነበር። ለዔሳው ይበልጥ ትጉም የነበረው በዚያው ዕለት፣ ወዲያውኑ ሊያገኘው የሚችለው፣ የሚታይ እና አካላዊ እርካታ የሚሰጠው ምግብ እንጂ፣ ከበኵርነቱ ጋር ተያይዞ የሚመጣ ወደፊት የሚቀበለው በረከት አልነበረም (ያስተያዩ፡ ዕብ. 12፡16-17)

“ለአብርሃም የተሰጠውን እና ለልጁ የተረጋገጠለትን የተስፋ ቃል ይስሐቅ እና ርብቃ የምኞታቸውና የተስፋቸው ታላቅ ጉዳይ አድርገውት ነበር። ኤሳው እና ያዕቆብ እነዚህን የተስፋ ቃላት ያውቁ ነበር። በመወለዳቸው ያገኙት መብት ምድራዊ ሐብት ብቻ ሳይሆን ነገር ግን መንፈሳዊ ልህቀትን የያዘ ርስት በመሆኑ ታላቅ ጠቀሜታ እንዳለው ተምረዋል። ብኩርናን የተቀበለ የቤተሰቡ ካኅን ሲሆን በልጆቹ የዘር ሐረግ ደግሞ የዓለም አዳኝ ይመጣል።”--የኃይማኖት አባቶችና ነቢያት፡ ገጽ 198።

ያዕቆብ፣ ከወንድሙ በተቃራኒ፣ ለወደፊቱ በረከት የሚሰጠው መንፈሳዊ ትርጉም ትልቅ ዋጋ አለው። ሆኖም ኋላ ላይ በእናቱ ቆስቋሽነት (ዘፍ. 27) ያዕቆብ በግልጽ እና ሆነ ብሎ--ጭራሽ “ ‘እግዚአብሔር አምላክህ’ ” (ዘፍ. 27፡ 20) ብሎ የእግዚአብሔርን ስም ጠርቶ እስከ ማታለል ይደርሳል። ምንም እንኳ ይህን የሚያደርገው ለመልካም እንደሆነ ቢያውቅም፣ ሆኖም ዘግናኝ የማታለል ተግባር ይፈጽማል።

ይህን ተከትሎ የተከሰቱት ውጤቶች አሳዛኝ ነበሩ። ቀድሞውኑ የተዛባ ሁናቴ ውስጥ በነበረው ቤተሰብ ላይ ሌላ ተጨማሪ ችግር ታከለ። ያዕቆብ መልካምና የከበረ ዋጋ ያለው ነገር ይፈልግ የነበረ ሲሆን፣ ይህ ደግሞ የሚደነቅ ነበር (በተለይ ከወንድሙ አመለካከት አኳያ ሲነጻጸር)። ሆኖም ያን ለማግኘት ማታለልና ውሸት ተጠቀመ። “መልካም” የሆነው ነገር እንዲመጣ ብለን መጥፎ ከመሥራት ተመሳሳይ ወጥመድ መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው?

ግንቦት 15
May 23

የያዕቆብ መሰላል


ኤሳው ያዕቆብ የአባቱን በረከት እንደተቀበለ ሲያውቅ በወንድሙ እንደተታለ እና እንደተተካ ተረዳ (ዘፍ. 27፡36)፣ እናም ሊገድለው ፈለገ (ዘፍ. 27፡ 42)። በጭንቀት ውስጥ የወደቀችው ርብቃ ለሁለቱም ወንዶች ልጆች መጠፋፋት የሚያስከትለውን ይህን ወንጀል ለማስቀረት ፈለገች (ዘፍ. 27፡ 45)። ሰለዚህ በይስሐቅ ድጋፍ (ዘፍ. 28፡5) ያዕቆብ ወደ ቤተሰቦቿ ሸሽቶ እንዲሄድ አሳሰበችው (ዘፍ. 27፡43)። ያዕቆብ በስደት ጉዞው ኋላ ላይ ቤቴል “የእግዚአብሔር ቤት” ብሎ በሚጠራው ስፍራ በሕልሙ ከእግዚአብሔር ጋር የሚጋጠም ሲሆን፣ በዚያም ስለት ይሳላል።

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፍ. 28፡10-22 እና ከሚከተሉት ጋር ያስተያዩ--ዘፍ. 11፡1-9። ቤቴል ከባቤል እንዴት ይለያል? ያዕቆብ በቤቴል ያጋጠመውን ሁኔታ በባቤል ከተፈጸመው ነገር ጋር በማስተያየት--ከእግዚአብሔር ጋር ካለን ግንኙነት አኳያ ከዚህ ምን ትምህርት እናገኛለን?



ያዕቆብ ባየው በዚህ ሕልም አንድ ያልተለመደ ጫፉ ሰማይ የሚደርስ ከእግዚአብሔር ጋር የተያያዘ መሰላል አየ። ናትሳቭ የሚል ተመሳሳይ የዕብራይስጥ ግስ መሰላሉን ለመጥቀስ ጥቅም ላይ የዋለ ሲሆን (ዘፍ. 28፡12)፣ “ቆሞ”(ዘፍ. 28፡ 13) የነበረው ጌታ ደግሞ መሰላሉንም ሆነ ጌታን አንድ አድርጎ የሚያቀርባቸው ይመስላል።

በባቤል እሳቤ መሰላሉ ሰማይ ለመድረስ ከተደረገ ሙከራ ጋር የተያያዘ ነው። እንደ ባቤል ግንብ ሁሉ መሰላሉም “ወደ ሰማይ ደጃፍ” ይደርሳል ። ይሁን እንጂ የባቤል ግንብ ወደ አምላክ ለመድረስ የሚደረገውን ሰብዓዊ ጥረት የሚያመለክት ሲሆን፣ የቤቴል መሰላል ግን ወደ አምላክ መቅረብ የሚቻለው በሰው ጥረት ሳይሆን እግዚአብሔር ወደ እኛ ሲመጣ ብቻ እንደሆነ በጉልህ ይገልጻል። ያዕቆብ ተንተርሶ ተኝቶ ሕልም ያየበት “ድንጋይ”፣ ቤቴል--“የእግዚአብሔር ቤት” (ዘፍ. 28፡17--ያስተያዩ፡ ዘፍ. 28፡22) ምሳሌ ይሆናል። ይህ ደግሞ እግዚአብሔር ለሰው ልጆች የሚያከናውነው የማዳን ሥራ ማዕከል የሆነውን ቤተ መቅደስ ያመለክታል።

ያም ሆኖ፣ ያዕቆብ በእርሱ ላይ የሆነውን የአምልኮ መገለጫና አስፈሪ ክስተት በመንፈሳዊነቱና ምሥጢራዊነቱ ብቻ አልወሰነውም። ማለትም፣ በተጨባጭ፣ ውጫዊ በሆነ መንገድ ምላሽ ለመስጠት ፈለገ። በመሆኑም ያዕቆብ የእግዚአብሔርን በረከት ለማግኘት ሳይሆን፣ ቀደም ሲል ለሰጠው አምላካዊ ስጦታ የምስጋና ምላሽ ለመስጠት ሲል “ከዐሥር እጅ አንዱን” ለእግዚአብሔር ለመስጠት ይወስናል። እዚህ ላይ እንደ ገና፣ እስራኤል እንደ ሕዝብ ከመነሣቷ ከረጅም ዘመናት አስቀድሞ የአሥራትን ጽንሰ ሀሳብ እንመለከታለን።

ጥቅሱን በድጋሚ ያንብቡ፡ ዘፍ. 28፡22። “ከምትሰጠኝ ሀብት ሁሉ ከአሥር እጅ አንዱን ለአንተ እሰጣለሁ” (ዘፍ. 28፡22)። ያዕቆብ አሥራትንና ምንነቱን አስመልክቶ በዚህ ስፍራ ከሚናገረው ላይ ምን ጠቃሚ ነጥብ መውሰድ እንችላለን?

ግንቦት 16
May 24

እነሆ አታላዩ ተታለለ!


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፍ. 29፡1-30። እግዚአብሔር የላባን ማታለል እንዴትና ለምን ፈቀደ? ያዕቆብ ምን ዓይነት ትምህርቶች አገኘ?



ያዕቆብ መድረሻው እንደተቃረበ በመጀመሪያ የተመለከተው ድንጋይ ነበር። ምናልባትም ድንጋዩ የእግዚአብሔር መገኘት የሆነውን የቤቴል ድንጋይ የሚያመለክት ፍንጭ ሊሆን ይችላል (ዘፍ. 28፡18-19)። ለነገሩ ያዕቆብ ከራሔል ጋር እንዲገናኝ ዕድል የሚፈጥርለትም ይኸው ድንጋይ ነው። ራሔል በጎቿን እየነዳች ውሃ ለማጠጣት እየመጣች መሆኑን ያዕቆብ ቆመው ከነበሩት እረኞች ሲሰማ፣ ድንጋዩን ከጉድጓዱ አፍ እንዲያንከባልሉት አሳሰባቸው። ሆኖም እምቢተኝነታቸው፣ ያዕቆብ ብቻውን ድንጋዩን የሚያንከባልልበትንና ራሱን ከራሔል ጋር የሚያስተዋውቅበትን ዕድል ሰጠው (ዘፍ. 29፡11)። ራሔል ፈጥና ወደ ቤተሰቿ በመገስገስ ምላሽ ሰጠች። ይህ የያዕቆብና የራሔል የመጀመሪያ ግንኙነት ፍሬያማ ነበር፡ “ያዕቆብ ራሔልን… ወደዳት” (ዘፍ. 29፡18) ስለዚህ ያዕቆብ ራሔልን ለማግኘት ለላባ ያገለገለባቸው እነዚያ ሰባት ዓመታት እንደ “ጥቂት ቀን” ነበሩ (ዘፍ. 29፡20)።

ሆኖም ከእነዚህ ሰባት ዓመታት በኋላ ያዕቆብ ተታለለ። በሠርጉ ምሽት ያዕቆብ በአልጋው ላይ ያገኛት ታላቅ እህቷን ልያን እንጂ ራሔልን አልነበረም። ድግሱ የፈጠረውን ግርግር፣ የያዕቆብን ከመጠን ያለፈ ስሜታዊነትና ደካማነት ተጠቅሞ ላባ ይህን የማታለል ድርጊት ለመፈጸም አቀደ። የሚገርመው ያዕቆብ ለምን “አታለልኸኝ” (ዘፍ. 29፡25 [1962 ትርጉም] ሲል የተናገረው--ስርወ ቃል ያዕቆብ በአባቱ እና በወንድሙ ላይ ያደረገውን ነገር ለመጥቀስ ይስሐቅ ከተጠቀመው ጋር ተመሳሳይ ነው (ዘፍ. 27፡35)።

ይህ እሳቤ በዳይ፣ ተበዳይ የደረሰበትን እንዲቀምስ የሚያስገድደውን ማለትም “ዐይን በዐይን”፣ “ጥርስ በጥርስ” ከሚለው ሌክስ ታሊዮኒስ (የበቀል ሕግጋት) ጋር ተመሳሳይ መሆኑን ልብ ይሏል (ዘፀ. 21፡24--ያስተያዩ ዘፍ. 9፡6)። ያዕቆብ የማታለል ሰለባ መሆን ምን ማለት እንደሆነ አሁን ተረድቷል። የሚገርመው እግዚአብሔር በላባ ማታለል ስለ ራሱ ማታለል ያዕቆብን አስተማረው። ምንም እንኳ ያዕቆብ እንደ አታላይነቱ (ዘፍ. 27፡12) የመታለልን ምንነት ጠንቅቆ የሚያውቅ ቢሆንም፤ ነገሩ በእርሱ ላይ ሲደርስ ግን ተገረመ። ስለዚህ እንዲህ ሲል ጠየቀ፡ “ ‘ ለምን አታለልኸኝ?’” (ዘፍ. 29፡25)። ጥያቄው ማታለል ስህተት መሆኑን እንደሚያውቅ የሚያሳይ ነበር።

ያዕቆብ አታላይ ቢሆንም እርሱ ራሱ ተታለለ። “ፍትሕ” ሲነፈግ፣ ክፉ የሚሠሩ ነጻ ሲደረጉ ወይም ንጹሐን ሲሠቃዩ ስንመለከት፣ በእግዚአብሔር ላይ እምነት መጣልን እንዴት እንማራለን?

ግንቦት 17
May 25

የቤተሰብ መባረክ


ለያዕቆብ የመጨረሻዎቹ ሰባት የስደት ዓመታት ሸክም የነበሩ ሲሆን፣ ያም ሆኖ ግን በጣም ፍሬያማ ነበሩ። ያዕቆብ የእግዚአብሔር ሕዝቦች የዘር ግንድ ከሚሆኑት ዐሥራ ሁለት ልጆች መካከል ዐሥራ አንዱን ይወልዳል። ይህ የያዕቆብን ታሪክ ዋንኛ ክፍል የያዘ (ዘፍ. 25፡19-35፡26) ሲሆን፣ የሚጀምረውም ሆነ የሚያበቃው እግዚአብሔር “ማህጸኗን ከፈተ” በሚል ቁልፍ ሐረግ ነው። አባባሉ ልያን እና ራሔልን ይመለከታል። በየጊዜው ይህ ቁልፍ ሐረግ መውለድን ተከትሎ የሚጠቀስ ሲሆን፣ ይህም ውልደቶቹ የእግዚአብሔር ተአምራዊ ድርጊት ውጤቶች ለመሆናቸው ማስረጃ ነው።

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፍ. 29፡31-30፡22። በዚህ ስፍራ እየሆነ የነበረውን ነገር ትርጉም ዛሬ እንዴት እንረዳዋለን?



እግዚአብሔር የልያን ማህጸን ስለ ከፈተላት ሮቤል የተባለ ወንድ ልጅ ወለደች። ስሙ ራኣ የተሰኘ ግስ የሚይዝ ሲሆን “ማየት” የሚል ፍቺ አለው። እግዚአብሔር በያዕቆብ እንዳልተወደደች “አየ” (ዘፍ. 29፡31) ስለዚህ ሕፃኑ ለሥቃይዋ ማካካሻ ሆናት።

በተጨማሪ ለሁለተኛ ልጇ ሰማ--በዕብራይስጥ “ሻማ” የሚለውን ግስ የያዘውን ስምዖን የተባለውን ስም ሰጠችው። እግዚአብሔር የአጋርን ሥቃይ እንደ ሰማ ሁሉ (ዘፍ. 29፡33) የእርሷንም ውርደትና ህመም በጥልቀት ተመልክቶ ስለ ራራላት-እነሆ “ሰማት”። የልያ ልጅ ስም “ስምዖን”፣ ከአጋር ልጅ “እስማኤል” ስም ጋር የሚስማማ ሲሆን፣ ትርጉሙ “እግዚአብሔር ይሰማል” (ዘፍ. 16፡11) የሚል ነው። ልያ የመጨረሻ ልጇን ስትወልድ ይሁዳ ብላ የጠራችው ሲሆን፣ ትርጉሙ “ውዳሴ” ማለት ነው። ልያ እንደ ቀድሞው ሁሉ--ህመሟን ወይም ደግሞ በረከቷን አታወሳም። ይልቁንም ትኩረቷን በእግዚአብሔር ላይ በማድረግ ስለ ጸጋው ታወድሰዋለች።

የሚገርመው ልያ እንደ ገና መውለድ ሳትችል ስትቀር እግዚአብሔር ራሔልን “ዐሰባት” እናም ማህጸኗን ከፈተ (ዘፍ. 30፡22)። ተወዳጇ ሚስት ራሔል የመጀመሪያ ወንድ ልጇን ለማግኘት ሰባት ዓመት፣ ከያዕቆብ ጋር ከታጨች ደግሞ 14 ዓመታት መጠበቅ ነበረባት (ዘፍ. 29:18፣ 27--ያስተያዩ፡ ዘፍ. 30:25)። ህጻኑን “እግዚአብሔር እፍረቴን አስወገደልኝ፣ እግዚአብሔር ሌላ ወንድ ልጅ ጨምሮ ይስጠኝ” ስትል ዮሴፍ ብላ ጠራችው (ዘፍ. 30፡23-24)። ከእነዚህ ድርጊቶች መካከል አንዳንዶቹ የቱንም ያህል ስህተት ቢሆኑም፣ እርሱ ግን ሊቀበላቸውና፣ ከአብርሃም ዘር ታላቅ ሕዝብ ለመፍጠር ሊጠቀምባቸው ችሏል።

ሰብዓዊ ስህተቶችና ድካሞች ቢኖሩም፣ አምላካዊው ዓላማ በሰማይ እና በምድር ተፈጻሚነት እንደሚያገኝ ይህ ታሪክ እንዴት ይገልጽልናል?

ግንቦት 18
May 26

የያዕቆብ መሄድ


ብኩርናውን ለማግኘት አባቱን እና ወንድሙን ያታለለውን፣ ይስሐቅ ለታላቅ ልጁ ለመስጠት ያዘጋጀውን ምርቃት የሰረቀውን--ነገር ግን ላባንን በታማኝነት ያገለገለውን የያዕቆብን ታሪክ ተመልክተናል። ያዕቆብ በአማቱ እንደተታለለ በሚገባ ቢያውቅም--መተው ነገሬን ከተተው፣ እንዲሉ፣ ተወው። ከያዕቆብ ተፈጥሮ አኳያ እንዴት እንዲህ የሚተውና የተባለውን የሚቀበል ባህሪ እንዳሳየ ለመረዳት አስቸጋሪ ነው። ያዕቆብ ሊያምጽ ወይም ቢያንስ ላባን ሊጋተረውና ሊሞግተው ይችል ነበር። ነገር ግን ይህን አላደረገም። የቱንም ያህል ኢፍትሐዊ ቢሆንም ላባ የጠየቀውን ብቻ አደረገ።

ራሔል የመጀመሪያ ልጇን ዮሴፍን ስትወልድ፣ ያዕቆብ ላባን ለ14 ዓመታት “አገልግሎአል” (ዘፍ. 30፡26)። አሁን ግን ወደ ተስፋይቱ ምድር ለመመለስና ላባንን ትቶ ለመሄድ አሰበ። ያዕቆብ የገዛ ራሱ ቤት ጉዳይ (ዘፍ. 30፡30) አሳስቦት ነበር።

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፍ. 30፡25-32። እዚህ ላይ ምን እየሆነ ነው? ያዕቆብ ምን ዓይነት አመክንዮ እየተጠቀመ ነው? የላባን ምላሽ ምንድን ነው?



ከቤቱ ከወጣ ለቆየው ያዕቆብ ይህ ዙሪያ ጥምጥም ጉዞ ነበር። ያኔ መጀመሪያ፣ እንዲህ ለረጅም ዘመን ከአገሬ ርቄ እኖራለሁ ብሎ ላያስብ ቢችልም፣ ሆኖም ሁኔታዎች ለዓመታት ከገዛ አገሩ እንዲርቅ አደረጉት። አሁን ወደ ቤት የሚመለስበት ጊዜ ሲሆን--እነሆ ታላቅ ቤተሰብ አብሮት ይመለሳል። በያዕቆብ ተፈጥሮ ውስጥ የተስተዋለው ያልተለመደ ዓይነት ታዛዥነት፣ ምናልባት ያዕቆብ መቀየሩን ይጠቁማል። የእምነትን ትምህርት በቅጡ ተረድቷል። ይህ ማለት ያዕቆብ ለመንቀሳቀስ አምላካዊውን ምልክት እየተጠባበቀ ነበር። ያዕቆብ ለመንቀሳቀስ የወሰነው እግዚአብሔር ሲነግረው ብቻ ነው።

እግዚአብሔር እንደ “ ‘ቤቴል አምላክ’ ” ራሱን ለያዕቆብ ገልጦ፣ የላባንን ቤት ትቶ ወደ ተወለደበት ምድር ተመልሶ እንዲሄድ (ዘፍ. 31፡13) ያዘዘው ሲሆን፤ እዚህ ላይ እግዚአብሔር የተጠቀመው ቃል አብርሃም ቤተሰቡን ትቶ እንዲሄድ (ዘፍ. 12፡1) ከነገረው ጋር ተመሳሳይ ነው።

ያዕቆብ የሚሄድበት ጊዜ ላይ መድረሱን እንዲያስተውል የረዳው የላባ ወንዶች ልጆች እና የላባ አመለካከት ነበር (ዘፍ. 31፡1-2)። “ያዕቆብ ዔሳውን ሄዶ መጋፈጥ ባያስፈራው ኖሮ ይህንን አታላይ ዘመዱን ከረዥም ጊዜ በፊት ትቶት በሄደ ነበር። አሁን ደግሞ የእርሱን ሀብት እንደራሳቸው ሀብት አድርገው የሚመኙት የላባ ወንድ ልጆች ይህንን ምኞታቸውን በኃይል ለማሳካት ሊፈልጉ ስለሚችሉ አደጋ ተጋርጦበታል።”---የኃይማኖት አባቶችና ነቢያት፡ ገጽ፡215 ስለዚህ ቤተሰቡንና ንብረቱን ይዞ ሄደ፣ በዚህም በእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ህዝብ ታላቅ ታሪክ ውስጥ ሌላ ምዕራፍ ጀመረ።

ግንቦት 19
May 27


ተጨማሪ ሀሳብ


እግዚአብሔር ያዕቆብን የመረጠው እርሱ የሚገባው ዓይነት ሰው ስለነበር ሳይሆን ከጸጋው የተነሣ ነው። ያም ሆኖ፣ እርስ በርሱ ቢጋጭም፣ ያዕቆብ አምላካዊው ጸጋ እንደሚገባው ለማሳየት በርትቶ ሠርቷል። የሚገባው ቢሆን ኖሮ፣ በጸጋ ሳይሆን በሥራ በሆነ ነበር (ሮሜ 4፡1-5)። ይህ ደግሞ ከወንጌል ጋር ይቃረናል። ያዕቆብ የአምላካዊውን ጸጋ ትርጉም፣ በእግዚአብሔር መታመን፣ በእምነት መኖር፣ በጌታ ላይ ሙሉ በሙሉ መደገፍ ምን ማለት እንደሆነ መረዳት የጀመረው ከጊዜ በኋላ ነው። የያዕቆብ ተሞክሮ አንድን የተለየ ግብ ለማሳካት ለሥልጣን ጉጉ ለሆነ ሰው ትልቅ ትምህርት ይዟል--ለሌሎች ደንታ ሳይኖርህ ራስህን ለማደርጀት አትጣጣር!

“ያዕቆብ በማታለል የብኩርና መብት ለማግኘት ቢያስብም፣ ነገር ግን ራሱን ተስፋ አስቆራጭ ሁናቴ ውስጥ አገኘ። ከእግዚአብሔር ጋር የነበረውን ግንኙነት እንዲሁም ቤቱን እና ሁሉንም ነገር ያጣ መስሎት የነበረው ያዕቆብ፣ ተስፋ ቢስ ሆኖ ይታይ ነበር። ነገር ግን እግዚአብሔር ምን አደረገ? በተስፋ መቁረጥ ስሜት ላይ እያለ ተመለከተው፣ ቅር መሰኘቱንም አየ። ከዚያም ለእግዚአብሔር ክብር ሊሰጥ የሚችልበት ነገር እንዳለ ተመለከተ። እግዚአብሔር አምላክ የሱስ ክርስቶስን የሚወክለውን ምስጢራዊ መሰላል ሲያቀርብለት ምንም ያህል ጊዜ አልወሰደም ነበር። ከእግዚአብሔር ጋር የነበረውን ግንኙነት ሁሉ ያጣ ይህ ሰው ቢሆንም፣ ነገር ግን የሰማይ አምላክ ወደ እርሱ ተመለከተና ኃጢአት የሠራውን ገደል ክርስቶስ ድልድይ ሆኖ እንዲያገናኝ ፈቀደ። ወደ ሰማይ ቀና ብለን በመመልከት፡ ሰማይን ብናፍቅም ነገር ግን እዛ መድረስ የሚያስችል መንገድ አይታየኝም እንል ይሆናል። ያዕቆብ ያሰበው ይህንኑ ነበር። ስለዚህ እግዚአብሔር የመሰላሉን ራእይ አሳየው። መሰላሉ ምድርን ከሰማይ ጋር ያገናኛል። ግርጌው ምድር ላይ፣ አናቱ ደግሞ ሰማይ በደረሰው መሰላል ላይ፣ እነሆ ሰው መውጣት ይችላል።--—Ellen G. White Comments, The SDA Bible Commentary, vol. 1, p. 1095.


የመወያያ ጥያቄዎች



1.በአንዳንድ ቅዱስ ዘገባዎች የቀረቡትን የእነዚህን ሰዎች ታሪኮች ይመልከቱ (ይስሐቅ፣ ርብቃ፣ ያዕቆብ፣ ኤሳው፣ ላባ፣ ራሔል፣ ልያ)። በታሪካቸው የተካተቱ ሁሉንም ዓይነት ውሸቶች እና ማታለያዎች ይመልከቱ። ይህ በአጠቃላይ ስለ ሰው ተፈጥሮ እና ስለ እግዚአብሔር ጸጋ ምን ያስተምረናል?

2. የያዕቆብን ታሪክ ሲያነቡ በጊዜ ሂደት ባህሪው እየጎለበተና እያደገ መሆኑን የሚያሳይ ምን ማስረጃ ያገኛሉ?

3. እንደ ሰባተኛ ቀን የዳግም ምጽአቱ ተጠባባቂነታችን፣ ዔሳው ከበኩርነቱ ጋር በተያያዘ የነበረው ዓይነት የአመለካከት አደጋ በእኛም ሊኖር የሚችልባቸው መንገዶች የትኞቹ ናቸው?




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA union SSL