የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ዘፍ. 32:22–31፣ ሆሴ 12:3-4፣ ኤር. 30:5–7፣ ዘፍ. 33፣ ዘፍ. 34:30–35:29።
የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ “ሰውየውም ፣ ‘ከእግዚአብሔርም፣ ከሰዎችም ጋር ታግለህ አሸንፈሃልና ከእንግዲህ ስምህ እስራኤል እንጂ፣ ያዕቆብ አይባልም’ አለው (ዘፍ. 32፡28)።
የ
ያዕቆብ ቤተሰብ ታሪክ መልካሙንም ሆነ መጥፎውን ይዞ ቀጥሏል።
ሆኖም፣ በዚህ ሁሉ፣ አምላካዊው እጅና ለቃል ኪዳኑ ተስፋዎች ያለው
ታማኝነት ተገልጦ መታየት ችሏል።
የዚህ ሳምንት ጥናት በአብዛኛው ያዕቆብን የሚከተል ሲሆን፣ አሁን ያዕቆብ
ከላባ ወጥቶ ወደ ቤቱ ሲመለስ የክህደት ሰለባው የሆነውን ዔሳው መጋፈጡ
የግድ ይሆናል። ከባድ በደል የተፈጸመበት ወንድሙ አሁን ምን ያደርገው
ይሆን?
ደግነቱ ምን ሊከሰት እንደሚችል ፈርቶ በነበረበት ወቅት፣ ኋላ ላይ “የያዕቆብ
የመከራ ጊዜ” ተብሎ ለሚጠራው ክስተት መነሻ በሆነ ድንገተኛ ሁናቴ
የአባቶቹ አምላክ እንደ ገና ተገለጠለት (ኤር. 30፡5–7)። በዚያ ሌሊት አታላዩ
ያዕቆብ “እስራኤል” ተብሎ ተጠራ። ይህ ለአዲስ ጅማሮ የተሰጠ አዲስ ስም
ሲሆን፣ ጅማሮው ውሎ አድሮ በዚህ በራሱ ስም የሚጠራ ህዝብ ወደ መፍጠር
የሚያመራ ይሆናል።
በሌላ አነጋገር ይህ ሁሉ ቢከሰትም፣ እግዚአብሔር ቃል የገባውን ለመፈጸም
የታመነ መሆኑንና አንዳንዴ የገዛ ሕዝቦቹ የተስፋ ቃሉ ፍጻሜ እንዳያገኝ
ለማስቆም የማይመስል መፍጨርጨር ከማድረግ ወደ ኋላ አለማለታቸውን፣
በቅዱሳት መጻሕፍት የሰፈሩ የኃይማኖት አባቶችና ቤተሰቦቻቸው ታሪክ
ያሳየናል።
ከላባ ወጥቶ የሄደው ያዕቆብ ብዙም ሳይቆይ ከእግዚአብሔር ጋር ሌላ
ተሞክሮ ገጠመው። ዔሳው “ ‘አራት መቶ ሰዎች’ ” (ዘፍ. 32፡6) ይዞ ወደ
እርሱ በመምጣት ላይ እንደሆነ ተገነዘበ። ምንም እንኳ “ ‘እኔ ባሪያህ እስካሁን
ላደረግህልኝ ቸርነትና ታማኝነት ብቁ አይደለሁም’ ” (ዘፍ. 32፡10) ብሎ
በመጸለይ ዋጋን ሁሉ ለእግዚአብሔር ቢሰጥም፣ ያዕቆብ ወደ ጌታ ጽኑ ጸሎት
አቀረበ። ያዕቆብ፣ በእውነት፣ ስለ ጸጋ ምንነት በተሻለ አስተውሎ ነበር።
ጌታ ምን ምላሽ ሰጠው?
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፍ. 32፡22-31 እና ሆሴ 12፡3-4። የዚህ
አስደናቂ ታሪክ መንፈሳዊ ትርጉም ምንድን ነው?
ያዕቆብ እየሆነ ባለው ነገር ተጨንቆ ነበር። ቤተሰቡን ለመጠበቅ የተቻለውን
ሁሉ ካደረገ በኋላ ምሽት ላይ አዳሩን በአንድ ቦታ ላይ አደረገ። በዚህ መሃል
“አንድ ሰው” (ዘፍ. 32፡24) ጥቃት ሰነዘረበት። ይህ መለኮታዊውን መገኘት
ወደ አእምሮ የሚያመጣ ልዩ ፍቺ ሊኖረው የሚችል ቃል ነው (ኢሳ. 53፡3)።
ዳንኤል ሰማያዊውን ካህን ሚካኤል ለማመልከት ተጠቅሞታል (ዳን. 10፡5)።
በተጨማሪም ኢያሱ ራሱ ጌታ ያሕዌ የነበረውን “የእግዚአብሔር ሰራዊት
አለቃ” ለማመልከት የተጠቀመበት ቃል ነበር (ኢያሱ 5፡13-15)።
ያዕቆብ በትግሉ መሃል “ ‘ካልባረክኸኝ አልለቅህም’ ” (ዘፍ. 32፡26) ሲል
በተናገረው ቃል፣ ከራሱ ከእግዚአብሔር ጋር እየታገለ እንደሆነ ሳይገለጥለት
አልቀረም። ሆኖም አምላክን የሙጥኝ ማለቱና እርሱን ለመልቀቅ ፈቃደኛ
አለመሆኑ፣ ምህረት ለማግኘትና ከጌታው ጋር ቀና ግንኙነት ለመፍጠር ያለውን
ከፍተኛ ፍላጎትና ምኞት ያሳያል።
“ያዕቆብ ብኩርናውን በሐሰተኛ መንገድ እንዲያገኝ ያስቻለው ስህተት አሁን ከፊት
ለፊቱ ጥርት ብሎ ታየው። የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ባለማመን እግዚአብሔር
በራሱ ሰዓት እና መንገድ ሊፈጽመው የሚችለውን ተግባር በራሱ ጥረት ለማሳካት
ሞከረ።”--የኃይማኖት አባቶችና ነቢያት፡ ገጽ፡ 220-221።
ይቅር የመባሉ ማስረጃ ኃጢአቱን ከሚያስታውሰው፣ አሸናፊነቱን
እስከሚያበስረው ያለው የስሙ መለወጥ ነበር። “ ‘ከእግዚአብሔርም ከሰዎችም
ጋር ታግለህ አሸንፈሃልና ከእንግዲህ ስምህ እስራኤል እንጂ ያዕቆብ [አታላይ]
አይባልም’ ” (ዘፍ. 32፡28)።
ከእግዚአብሔር ጋር ያደረጉትን ትግል አስመልክቶ የግል ተሞክሮዎ
ምን ይመስላል? ይህን ማድረግ ሲባል ምን ለማለት ነው? አንዳንዴ
በእንዲህ ያለው ተሞክሮ ማለፋችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
ያዕቆብ ከእግዚአብሔር ጋር አስገራሚውን ተሞክሮ ካገኘበት ጵንኤል
“የእግዚአብሔር ፊት” (ዘፍ. 32፡30) ተነስቶ ወንድሙን ለመገናኘት መንቀሳቀስ
ጀመረ። ከ20 ዓመታት መለያየት በኋላ፣ ያዕቆብ ከ400 ሰዎች ጋር ሲመጣ
ተመለከተው (ዘፍ. 33፡1)። በጭንቀት ውስጥ የወደቀው ያዕቆብ፣ ሊመጣ
ለሚችል ማንኛውም ነገር ራሱንና ቤተሰቡን አዘጋጀ።
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፍ. 33። ያዕቆብ የእግዚአብሔርን ፊት በጵንኤል
በማየቱ እና የወንድሙን ፊት በማየቱ መካከል ምን ዝምድና አለ?
ከአምላክ ጋር ያለን ዝምድና እና የቱንም ዓይነት ሰዎች ቢሆኑ እንኳ
“ከወንድሞቻችን” ጋር ያለን ግንኙነት አንድምታ ምንድን ነው?
ያዕቆብ ወንድሙ ጋ እስኪደርስ “ ‘ጌታዬ’ ” (ዘፍ. 33:8፣ 13፣ 15) ብሎ በመጥራት
ሰባት ጊዜ ለጥ እያለ እጅ የነሳው (ዘፍ. 33፡3) ሲሆን፣ ራሱን “ ‘አገልጋይህ’ ”
(ዘፍ. 33፡5 ያስተያዩ ዘፍ. 32፡4፣18፣20) ብሎ ሲጠራም ይታያል። ያዕቆብ ሰባት
ጊዜ እጅ መንሳቱ የአባቱን ሰባት ምርቃቶች በጉልህ ያስተጋባል (ዘፍ. 27፡27- 102 -
29)። ከዚህ በተጨማሪ፣ ጎንበስ ብሎ እጅ መንሳቱ በተለይ አባቱ “ ‘ሕዝቦችም
ተደፍተው እጅ ይንሡህ’ ” (ዘፍ. 27፡29) ሲል የመረቀውን ገልብጦ እያሳየ ነበር።
የያዕቆብ ሀሳብ የወንድሙን ዕዳ መክፈልና ከእርሱ የሰረቀውን በረከት ለመመለስ
ይመስላል (ዘፍ. 33፡11)። ዔሳው ወንድሙን ባየ ጊዜ፣ ይጠበቅ ከነበረው በተቃራኒ
ወደ ያዕቆብ ሮጦ አቀፈው። እርሱን በመግደል ፋንታ “በአንገቱ ላይ ተጠምጥሞ
ሳመው፤ ሁለቱም ተላቀሱ” (ዘፍ. 33፡4)።
ከዚያም ያዕቆብ ስለ ዔሳው በሰጠው አስተያየት “ ‘ፊትህን ማየት መቻሌ ራሱ፣
የእግዚአብሔርን ፊት የማየት ያህል እቆጥረዋለሁ” (ዘፍ. 33፡10) ሲል ነገረው።
ያዕቆብ ይህን ያልተለመደ ዓይነት አነጋገር የተናገረበት ምክንያት ዔሳው ይቅር
እንዳለው በመገንዘቡ ነው። ደስ መሰኘት ወይም ራትሻ የሚለው የዕብራይስጥ
ቃል፣ “ደስ ለሚያሰኝ” ወይም “በእግዚአብሔር ፊት ተቀባይነት ያለውን”
መሥዋዕት ለማመልከት ጥቅም ላይ የሚውል ሥነ መለኮታዊ ቃል ነው፤ ይህም
መለኮታዊውን ቅርታ ያሳያል (ዘሌዋ. 22፡27፣ አሞጽ 5፡22)።
ያዕቆብ የእግዚአብሔርን ፊት ባየበት በጵንኤል አምላካዊውን ይቅርታ እንደ
ተለማመደ ሁሉ፣ አሁንም የእግዚአብሔርን ፊት እንዳየ በቆጠረበት በወንድሙ
ይቅርታ ይኸው ተሞክሮ ተደገመ። ያዕቆብ አሁን ከእግዚአብሔር እና ከገዛ
ወንድሙ ይቅርታ አግኝቷል። በዚህ ወቅት፣ በእርግጠኝነት የጸጋን ትርጉም
ከበፊቱ በበለጠ ሳይረዳ እንዳልቀረ ይታመናል።
ሌሎች እንዴት ይቅር እንዳሎት (ከጌታ በተጨማሪ) መገንዘብዎ ስለ
ጸጋ ምን አስተማሮት?
አሁን ያዕቆብ ከወንድሙ ጋር ስለታረቀ በከነዓን ምድር በሰላም መኖር ይፈልጋል።
ሻሎም “ሰላም” ከሚለው የዕብራይስጥ ቃል የመጣው ሻለም “በደኅና” (ዘፍ. 33፡
18) ለመጀመሪያ ጊዜ የእርሱን ጉዞ ይገልጻል።
ከነዋሪዎቹ መሬት ከገዛ በኋላ (ዘፍ. 33፡19) በስፍራው መሠዊያ ያቆመ ሲሆን፣
ይህም እምነቱን እና ምን ያህል በእርግጠኝነት በጌታ ላይ እንደሚመካ የሚያሳይ
ነበር። ይቀርብ ለነበረው እያንዳንዱ መሥዋዕት አምልኮአዊ ተግባር ይፈጸም
ነበር።
ሆኖም ያዕቆብ-እስራኤል በሕይወቱ ለመጀመሪያ ጊዜ በምድሪቱ ሲኖር ለችግር
ተጋለጠ። ይስሐቅ በጌራራ በሚኖረው አቢሜሌክ እንዳደረገው (ዘፍ. 26፡1-33)
ያዕቆብም በከከነዓናውያን ማረፊያ ለማግኘት ሞከረ።
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፍ. ምዕ. 34። ሰላማዊ የመኖር እቅዱን
ያሳዘነ ምን ነገር ተከሰተ?
ይህ አስነዋሪ ክስተት የባለታሪኮቹን አሻሚ ባህሪና ድርጊት በጉልህ ያሳየ
ነበር። ስሜቱን መቆጣጠር ተስኖት በዲና ላይ ነውር የፈጸመውና እንደ ቅን
ብሎም ከልቡ እንደሚወዳት ሆኖ የቀረበው ሴኬም፣ ለፈጸመው ወራዳ ተግባር
ካሳ ለመክፈል እሺታውን አሳይቷል። ከዚህም አልፎ የግርዘት ቃል ኪዳን ሥነ
ሥርዓት ለመፈጸም ፈቃደኛ ሆኗል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ከከነዓናውያን ጋር ጋብቻ መፈጸም የለበትም ብለው
በመቃወም (ዘሌዋ. 19፡29)፣ ራሳቸውን እንደ እግዚአብሔር ጠበቃና የትእዛዛቱ
ጠባቂ አድርገው የሚቆጥሩት ስምዖን እና ሌዊ፣ በምላሳቸው ሸንግለው--ነገር ግን
ውሸት እና ማታለል በልባቸው ሰንቀው ሊገድሏቸውና ሊዘርፏቸው ተዘጋጁ (ዘፍ.
34፡13)። እርምጃቸው አስከፊ ብቻ ሳይሆን (ጥፋቱን የፈጸመው ሰው ብቻ ለምን
እንዲቀጣ አልተደረገም?) ከዚያ በላይ ብዙ ችግሮች የመፍጠር አቅም ነበረው።
ያዕቆብን የሚያሳስበው የሰላም ጉዳይ ብቻ ነው። ያዕቆብ የሴት ልጁ መደፈር
ሲነገረው በወቅቱ ምንም ያለው ነገር አልነበረም (ዘፍ. 34፡5)። ይሁን እንጂ ልጆቹ
ያደረጉትን ነገር ከሰማ በኋላ እንዲህ ሲል በግልጽ ተናገራቸው፡ “በዚህ አገር
በሚኖሩት በከነዓናውያንና በፌሩዛውያን ዘንድ እንደ ጥምብ አስቆጠራችሁኝ፣
ጭንቀትም እንዲደርስብኝ አድርጋችኋል። እኛ በቁጥር አነስተኞች ነን፤ ተባብረው
ቢነሡብኝና ቢያጠቁኝ እኔና ቤተሰቤ መጥፋታችን አይደለምን?” (ዘፍ. 34፡30)።
በእነዚህ ዘገባዎች ውስጥ ተንኮል እና ማታለል እንዲሁም የደግነት
እና የጸጋ ድርጊቶች በተደጋጋሚ ቀርበው እናያለን። ይህ ስለ ሰው
ተፈጥሮ ምን ይነግረናል?
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፍ. 34፡30-35፡15። እዚህ ላይ ከሆነው ነገር ስለ እውነተኛ አምልኮ ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን?
ያዕቆብ ከከነዓናውያን ጋር የነበረው ሰላም እንዳይሆን ከሆነ በኋላ (ዘፍ. 34፡
30) እና ሁለቱን ወንዶች ልጆቹን ከገሰጸ በኋላ (ዘፍ. 34፡30) ቃል ኪዳኑን ያድስ
ዘንድ ሴኬምን ትቶ ወደ ቤቴል እንዲመለስ እግዚአብሔር አዘዘው። እርግጥ ነው፣
በዚያ እንደ ደረሰ መሠዊያ እንዲያቆም ጌታ ነግሮታል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ እግዚአብሔር ካዘዘው በኋላ የተመዘገበው ቀዳሚ
ነገር፣ ከሴኬም ከተማ የተዘረፉ የከነዓናውያን ጣዖታት እና ራሔል ከአባቷ ቤት
የሰረቀችውን የጣዖት ምስል (ዘፍ. 31፡19፣32) እንዲወገዱ ያዕቆብ ለሕዝቡ
መንገሩ ነው። ይህ ሁሉ፣ ከእግዚአብሔር ጋር ለሚገባው ኪዳናዊ ጽንሰ ሀሳብ
በእጅጉ ወሳኝ ነው።
ያዕቆብ እግዚአብሔርን በቁርጠኝነት የሚያመልክ ቢሆንም፣ ምናልባት እነዚህ
ጣዖታት ሳይመለኩ እንዳልቀረ ይገመታል። ያዕቆብ ከከነዓናውያን ተጽዕኖ
ለማምለጥ ሴኬምን ለቅቆ መውጣቱ በቂ አልነበረም። ይልቁንም በእርሱ ሰፈር
ውስጥ እና በሕዝቡ ልብ ውስጥ ያሉትን ጣዖታት ማስወገድ ነበረበት።
የንስሐ ሂደት ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ወይም ከአንዱ ቤተ ክርስቲያን ወደ ሌላ
ከሚደረግ አካላዊ ዝውውር የላቀ ነገርን ያካትታል። ከሁሉም በላይ የምንኖርበት
ቦታ የትም ይሁን የት፣ የጣዖት አምልኮን በእግዚአብሔር ጸጋ ከልባችን ለማጽዳት
ፍላጎት ማሳየታችን በጣም አስፈላጊው ነጥብ ነው። ምክንያቱም ከማንኛውም
ነገር ጣዖታትን መሥራት እንችላለንና።
ያዕቆብ እግዚአብሔርን በመታዘዝ በአምላካዊው ፈቃድ መሠረት ጉዞውን
ሲቀጥል፣ በመጨረሻ እግዚአብሔር ጣልቃ ገብቶ በመንገዳቸው ባሉ ሁሉ ላይ
“ፍርሀትና ድንጋጤ” (ዘፍ. 35፡5) ስለለቀቀባቸው በያዕቆብ ላይ ጥቃት ለመሰንዘር
አልደፈሩም። ከዚያም ያዕቆብ “አብረውት ከነበሩት ሰዎች ሁሉ” (ዘፍ. 35፡
6) ጋር አምልኮ ለማድረግ መዘጋጀቱ፣ ቤተሰባዊው አንድነት ወደ ቀድሞው
መመለሱን ይጠቁማል። ያዕቆብ ለተወሰነ ጊዜ ተቋርጦ የነበረውንና አሁን ግን
የጸናውን፣ በሰማይና በምድር መካከል ያለውን ግንኙነት የሚያሳይ ምልክት
የሆነውን የመሰላሉን ሕልም ያየበትን ይህን ስፍራ ለማስታወስ ኤል ቤቴል ብሎ
ይሰይመዋል።
በዚህ ወቅት ትኩረት የተሰጠው ለራሱ ለቦታው ሳይሆን ለቤቴል አምላክ ነው።
ያዕቆብ “እስራኤል” (ዘፍ. 35፡10) በሚል የተሰጠውን ስም እግዚአብሔር እንደገና
የሚያስታውሰው ሲሆን፣ ይህ በረከት ድርብ የተስፋ ቃል ይዟል። የያዕቆብ
በረከት፣ በቅድሚያ--ፍሬያማነት፣ የመሲሕ ዘር መተላለፊያ መስመር እና የብዙ
ሕዝቦች ትውልድ መሆን የሚል ፍቺ ያለው ሲሆን (ዘፍ. 35፡11)፣ በሁለተኛ
ደረጃ፡ የተስፋይቱን ምድር ያመለክታል (ዘፍ. 35፡12)።
ጣዖት አምልኮ በልባችን ውስጥ ሊገባ የሚችልባቸው ስውር መንገዶች
የትኞቹ ናቸው? በዚህ ጉዳይ ምን ማድረግ እንችላለን?
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፍ. 35፡15-29። ያዕቆብ ክሽፈት በገጠመው ቤተሰቡ መሃል ምን ሌሎች ችግሮች ደርሰውበት ነበር?
ያዕቆብ ከቤቴል ወጥቶ ወደ ተስፋይቱ ምድር ባደረገው የመጨረሻ ጉዞ
ሦስት ተያያዥነት ያላቸው ክስተቶች ገቢራዊ ሆኑ፡- የያዕቆብ የመጨረሻ
ልጅ ተወለደ፤ ራሔል ሞተች፤ እንዲሁም ከልያ የወለደው የመጀመሪያ ልጁ
ሮቤል ከአባቱ ዕቁባት ጋር ተኛ። ምንም እንኳ ጥቅሱ ወጣቱ ለምን እንዲህ
ያለውን ክፉ ነገር እንዳደረገ ባይነግረንም፣ ምናልባት የያዕቆብን የመጨረሻ
ልጅ መወለድ በሆነ መንገድ ለማርከስና የራሔልን ትውስታ ለማዋረድ ፈልጎ
ሊሆን ይችላል። ብቻ አናውቅም።
የያዕቆብ የመጨረሻ ልጅ መወለድ የተስፋይቱ ምድር አካል ከሆነችው
ቤተልሔም (ዘፍ. 35፡19) ጋር ተያያዥነት አለው። የህጻኑ መወለድ
እግዚአብሔር ለወደፊቷ እስራኤል የሰጠው የተስፋ ቃል የመጀመሪያ ፍጻሜ
ነው። አዋላጇ “ ‘አትፍሪ’ ” ስትል ራሔልን ለማበረታታት የተጠቀመችው
ቃል፣ እግዚአብሔር ለአብርሃም ከተናገረው ትንቢታዊ ቃል ጋር ተመሳሳይነት
አለው (ዘፍ. 35፡17 ያስተያዩ፡ ዘፍ. 15፡1)።
በሞት አፋፍ የነበረችው ራሔል ህመሟን ለማመልከት፣ ወንድ ልጇን፣
ቤንኦኒ “የመከራዬ ልጅ” ስትል ያወጣችለትን ስም ያዕቆብ ግን ቀይሮ ብንያም
“የቀኜ ልጅ” ብሎ ጠራው። ለዚህ መንስኤው ምናልባት ስለ ተስፋይቱ ምድር
ያለውን ተስፋና ሕዝቡ በዚያ ከሰፈረ በኋላ እግዚአብሔር እንደሚያደርግ
የተናገረውን የሚፈጽምበትን የደቡብ አቅጣጫ ለማመልከት ሊሆን ይችላል።
ሆኖም በዚህ ጊዜ ሮቤል ከአባቱ ቁባትና የራሔል አገልጋይ ከሆነችው ባላ
ጋር ተኛ (ዘፍ. 35፡25፣ ዘፍ. 30፡3)። ይህ ድርጊት ለሰው ልጅ ወራዳነት
ሌላ ምሳሌ ከመሆን ባለፈ፣ ልጁ ለምን ይህን ዘግናኝ ድርጊት እንደፈጸመ
አናውቅም።
የሚገርመው፣ ምንም እንኳ ያዕቆብ ስለዚህ አሰቃቂ ድርጊት ቢነገረውም
ምንም ምላሽ አልሰጠም (ዘፍ. 35፡22)። ምናልባት በዚህ በነበረበት ሁኔታ፣
በዙሪያው አልፎ አልፎ ኃጢአትና ክፋት ቢፈጸምም፣ ነገር ግን እግዚአብሔር
ቃሉን ይፈጽም ዘንድ በእርሱ ላይ እምነት ጥሎ ነበር።
የእስራኤል ዘር ግንድ በሆኑት በያዕቆብ ዐሥራ ሁለት ልጆች ዝርዝር ውስጥ
የተመለከተው ይህ ትክክለኛ የእምነት ትምህርት ነው (ዘፍ. 35፡22–26)።
እንደምንመለከተው እነዚህ ሰዎች ቅመሞች ወይም እጅግ ደግ ሰዎች
አልነበሩም። ሆኖም እነዚህ ሁሉ ችግሮች፣ ክሽፈቶች፣ አልፎ ተርፎም ሮቤል
ከባላ ጋር የፈጸመው ዓይነት ፍጹም እርኩሰት በመሃላቸው ቢስተዋልም፣
አምላካዊው ፈቃድ በዚህ ቤተሰብ አማካይነት ይፈጸም ነበር።
ምንም እንኳ የሰዎች ስህተት ቢኖርም፣ የእግዚአብሔር የመጨረሻ
ዓላማዎች ግን ፍጻሜ ያገኛሉ። ሰዎች በአንድ ልብ ለአምላካዊው
ፈቃድ ቢገዙ ምን ሊከሰት እንደሚችል አሰብ ያድርጉ። በአነስኛ
ሰብዓዊ ሥቃይ፣ ጭንቀትና መዘግየት የእግዚአብሔር ፈቃድ ፍጻሜ
ማግኘት ይችል ይሆን?
የሚከተለውን የኤለን ጂ. ኋይት መልእክት ያንብቡ፡
“የትግል ምሽት” ገጽ፡ 217-235--የኃይማኖት አባቶችና ነቢያት።
“ያዕቆብ በዚያ የትንቅንቅ እና የጭንቀት ምሽት ወቅት ያሳለፈው ሁኔታ
የእግዚአብሔር ሰዎች ከክርስቶስ ዳግም ምጽአት በፊት ሊያልፉበት
የሚገባውን ፈተና የሚያሳይ ነው።... የእግዚአብሔር ህዝቦች ከክፉ ኃይላት
ጋር በመጨረሻ በሚያደርጉት ትግል የሚያጋጥማቸው ተሞክሮ ይኸው ነው።
እግዚአብሔር እነርሱን ለማዳን ባለው ኃይል ላይ የያዙትን እምነት፣ ጥንካሬ
እና መንፈስ ይፈትናል። ሰይጣን ደግሞ የእነርሱ ጉዳይ ያለቀለት፣ ተስፋ ቢስ
እና የፈጸሙት ኃጢአት ከይቅርታም እጅግ
ያለፈ እንደሆነ በመግለጽ ሽብር ሊነዛባቸው ይሞክራል። ስለ ድክመቶቻቸው
ጥልቅ የሆነ ሀሳብ ይገባቸዋል። እንዲሁም ሕይወታቸውን መለስ ብለው
ሲቃኙ ተስፋቸው ይሟጠጣል። ነገር ግን የእግዚአብሔርን ምኅረት ታላቅነት
እና የራሳቸውን ልባዊ ንስሐ በማስታወስ ለረዳት የለሾች እና ንስሐ ለገቡ
ኃጢአተኞች በክርስቶስ የተገባው ቃል እንዲፈጸምላቸው ይለምናሉ።
ፀሎታቸው ወዲያውኑ ምላሽ ስላላገኘ ብቻ እምነታቸው አይወድቅም።
ልክ ያዕቆብ መልአኩን አጥብቆ እንደያዘ ሁሉ እነርሱም የእግዚአብሔርን
ጥንካሬ አጥብቀው ይይዛሉ። ነፍሳቸው የምትናገረው ቋንቋም “ካልባረክኸኝ
አልለቅህም” የሚል ይሆናል…
“የያዕቆብ ታሪክ በኃጢአት ውስጥ ተዘፍቀው በእውነተኛ ንስሐ ወደ እርሱ
የሚመለሱትን እግዚአብሔር እንደማይተዋቸው ማረጋገጫ ይሰጠናል።
ያዕቆብ በራሱ ጥንካሬ ታግሎ ሊያገኝ ያልቻለውን ነገር ያገኘው እራሱን
በመስጠትና ጥፋቱን በመናዘዝ ነው። ስለዚህም መለኮታዊ ኃይል እና ፀጋ
ብቻውን እርሱ የፈለገውን በረከት እንደሚሰጠው እግዚአብሔር ለአገልጋዩ
ትምህርት ሰጥቶአል። ይህ ደግሞ በመጨረሻው ዘመን በሚኖሩ ሰዎች ላይ
እውን ይሆናል። እነዚህ ወገኖች በአደጋ ሲከበቡና ተስፋ መቁረጥ በነፍሳቸው
ላይ ሲያንዣብብ በአዳኙ የሥርየት ሥራ ላይ ብቻ መተማመን አለባቸው።
ስለራሳችን ምንም ልናደርግ አንችልም።” ኤለን ጂ. ኋይት፡ የኃይማኖት
አባቶችና ነቢያት፡ ገጽ፡ 222-225።
1.የያዕቆብ ድካም የአምላካዊው ጸጋ መገለጥ ምክንያት የሆነው
ለምንድን ነው? የያዕቆብ ተሞክሮ ጳውሎስ “ስደክም ያን ጊዜ
ብርቱ ነኝና” (2ቆሮ. 12፡10) ብሎ ከተናገረው ጋር እንዴት
ይዛመዳል?
2.መጽሐፍ ቅዱስ የብዙዎቹ የቅዱሳት መጻሕፍት ተዋናዮችን
ወራዳ የህይወት ዝርዝሮች የገለጠው ለምን ይመስሎታል? ማሳየት
የተፈለገው ነጥብ ምንድን ነው? ከዚህ ምን ዓይነት መልእክት
ማግኘት እንችላለን?
3.በጣዖት አምልኮ ጥያቄዎች ዙሪያ በቂ ትኩረት ያድርጉ።
የባህላችን፣ የሥልጣኔአችን ጣዖታት ምንድን ናቸው? ከጌታ
በቀር ለማንም ሆነ ለምንም ላለመስገዳችን እንዴት እርግጠኞች
መሆን እንችላለን?