የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 1ኛ ሩብ ዓመት 2022

ከታህሳስ 23-29

2ኛ ትምህርት

Jan 1-Jan 7




ለዕብራውያኑ የተላከው መልዕክት



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሳምንት ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡- ዕብ.1፡5-14፣ሉቃ 1፡3033፣መዝ.132፡1-5፣ዕብ.2፡14-16፣ዕብ.5፡1-4፣1ጴጥ.2፡9፣ዕብ.8፡8-12።


የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ “ከተናገርነውም ዋና ነገሩ ይህ ነው፤በሰማያት በግርማው ዙፋን ቀኝ የተቀመጠ እንዲህ ያለ ሊቀ ካህናት አለን።” (ዕብ. 8፡1)

ከ ዕብራውያን መልዕክት ጥቂት አስርት ዓመታት በኋላ የተጻፈ የአይሁዳውያን ሰነድ እንዲህ የሚል ጸሎትን ይዟል። “ጌታ ሆይ ይህንን ነገር በፊትህ የምንናገረው ይህንን ዓለም የፈጠርኩት ለናንተ ነው ስላልከን ነው።…እናም አሁን ጌታ ሆይ እንደምናምንቴ የሆኑት እነዚህ ህዝቦች እየገዙንና እየበዘበዙን ናቸው። የበኩር ልጄ፣ ብቸኛ ልጄ፣ የወደድኳችሁና የምቀናላችሁ ያልከን እኛ ሕዝብህ ግን በነርሱ እጅ ተሰጥተናል።” James H. Charlesworth, ed., The Old Testament Pseudepigrapha, vol. 1, [New York: Hendrickson Publishers, 1983], p. 536 ምናልባትም የዕብራውያን መልዕክት አንባቢዎችም ተመሳሳይ ስሜት ተሰምቷቸው ይሆናል። የእግዚአብሔር ልጆች ከሆኑ በእንደዚህ አይነት መከራ ውስጥ እያለፉ ያሉት ለምን ይሆን?

ስለዚህ በመከራ ውስጥ እያለፉ ቢሆንም የአማኞቹን ልብ ለማጠናከር የዕብራውያን መልዕክትን ጻፈ። የእግዚአብሔር የተስፋ ቃላት ፍጻሜን የሚያገኙት በአብ ቀኝ በተቀመጠውና በቅርብ ወደቤቱ በሚወስደን በኢየሱስ በኩል መሆኑን እያስታወሳቸው(እያስታወሰን) ነበር። ይህ እስከሚሆን ግን ኢየሱስ መሃል ሆኖ የአብን በረከት ወደ እኛ ያፈሳል። ስለዚህ እስከመጨረሻው በዕምነታችን መጽናት ይኖርብናል። ለታህሳስ 30 ሰንበት ለመዘጋጀት የዚህን ሳምንት ትምህርት ያጥኑ።

ታህሳስ 24
Jan 2

ኢየሱስ ንጉሳችን ነው


የዕብራውያን መልዕክት ዋና ነጥብ በአብ ቀኝ የተቀመጠው ገዢ መሆኑ ነው(ዕብ. 8፡1)። አምላክ እንደመሆኑ ኢየሱስ ሁሌም የዓለማት ገዢ ነው። ነገር ግን አዳምና ሔዋን ኃጢአት ሲያደርጉ ሰይጣን የዚህ ዓለም ገዢ ሆነ(ዮሐ.12፡ 31፣ ዮሐ.14፡30፣ ዮሐ.16፡11)። ሆኖም ኢየሱስ መጣና ሰይጣንን በመስቀል ላይ አሸነፈው፤ እንደ አዳኛቸው በሚቀበሉት ላይ ገዢ የመሆንን ስልጣን አስመለሰ(ቆላ. 2፡13-15)። የዕብራውያን መልዕክት የመጀመሪያዎቹ ሁለት ምዕራፎች ኢየሱስ እንደ ንጉስ በመቀባቱ ላይ ያተኩራል። ዕብ.1፡5-14ን ያንብቡ። እዚህ ቦታ እየተፈጠረ ያለው ምንድነው?



እነዚህ ጥቅሶች ሶስት ክፍሎች አሏቸው። እያንዳንዱ ክፍል የወልድን(የንግስና) የሹመት በዓል አንድ ገጽ ያሳየናል። በመጀመሪያ እግዚአብሔር ኢየሱስን እንደ ንጉሳዊ ልጁ አድርጎ ይቀበለዋል(ዕብ.1፡5)። ሁለተኛ እግዚአብሔር ልጁን ለሚያመልኩት ለሰማይ ሰራዊት በማስተዋወቅ የወልድን ዘላለማዊ ገዢነት ያውጃል(ዕብ.1፡8-12)። በሶስተኛ ደረጃ እግዚአብሔር ለወልድ ሹመት ይሰጠዋል(ዕብ.1፡13-14)

። በአዲስ ኪዳን እጅግ ወሳኝ ከሆኑት እምነቶች መካከል እግዚአብሔር ለዳዊት የሰጠውን የተስፋ ቃል የፈጸመው በኢየሱስ በኩል ነው የሚለው ነው(2ሳሙ.7፡8-16፣ሉቃ.1፡30-33)። ኢየሱስ የተወለደው ከዳዊት ዘር በዳዊት ከተማ ነበር(ማቴ.1፡1-16፣ሉቃ.2፡10-11)። በአገልግሎቱ ወቅት ሰዎች ብዙ ጊዜ “የዳዊት ልጅ” ብለው ይጠሩት ነበር። የተሰቀለውም ራሱን የአይሁድ ንጉስ ብሏል በሚል ክስ ነበር(ማቴ.27፡37)።ጳውሎስና ጴጥሮስ ሲሰብኩ ኢየሱስ ከሞት መነሳቱ ለዳዊት የገባው ቃል ፍጻሜ ነው ብለዋል(ሐዋ.ሥራ 2፡22-36፣ሐዋ.13፡22-37)።ዩሐንስ ደግሞ ኢየሱስን “ከይሁዳ ነገድ የሆነው አንበሳ”(ዩሐ.ራዕይ 5፡5) ብሎ ጠርቶታል

። የዕብራውያን መልዕክትም በርግጥ ከዚህ ጋር ይስማማል። እግዚአብሔር ለዳዊት የገባውን ቃል በኢየሱስ ፈጽሞታል እግዚአብሔር ታላቅ ስም ሰጥቶታል (ዕብ.1፡4) ፣ እንደራሱ ልጅ ተቀብሎታል(ዕብ.1፡5)፤ዙፋኑን ለዘላለም አፅንቷል(ዕብ.1፡8-12) እንዲሁም በቀኙ አስቀምጦታል(ዕብ.1፡ 13-14)። በተጨማሪም እንደዕብራውያን 4 ገለጻ ኢየሱስ ሕዝቡን ወደ እግዚአብሔር እረፍት ይመራቸዋል፤እንዲሁም ኢየሱስ የእግዚአብሔር ቤት ሰሪ መሆኑን ያስታውሰናል(ዕብ.3፡3-4)

። ስለዚህ ኢየሱስ አታሎ ንግስናን ከያዘው ከሰይጣን ጋር ለመዋጋትና ለኛ ለመቆም የሚገባው ንጉስ ነው። በተለይ በችግሮች ውስጥ ስናልፍ ኢየሱስ የዓለም ሁሉ ንጉስ መሆኑን ማወቃችን ብርታትን የሚሰጠን እንዴት ነው?

ታህሳስ 25
Jan 3

ኢየሱስ አዳኛችን ነው


ከብሉይ ኪዳን የስነ-መለኮት አስተምሮ ፅንሰ ሀሳቦች መካከል አስደናቂው ከዳዊት የሆነው ንጉስ ህዝቡን በእግዚአብሔር ት ይወክላል የሚለው ነው። ዘፀ. 4፡22-23ን ከ2 ሳሙ.7፡12-14 ፤ዘዳ.12፡8-10ን ከ 2 ሳሙ. 7፡9-11 ጋር እና ዘዳ.12፡13-14ን ከመዝሙር 132፡1-5 ፤11-14 ጋር ያነፃፅሩ። ተስፋ በተገባው ከዳዊት ዘር በሆነው ንጉስ ውስጥ የሚፈፀሙት ለእስራኤል የተገቡ የተስፋ ቃላት የትኞቹ ነበሩ?



እስራኤል የእግዚአብሔር ልጅ የነበረ ሲሆን እግዚአብሔር ደግሞ ከጠላቶቻቸው የሚያርፉበት ቦታ ሊሰጣቸው ነበር። ስሙ የሚጠራበትን ቦታም የመረጠው እግዚአብሔር ነበር። እነዚህ ለእስራኤል የተገቡ ተስፋዎች ከአይሁድ ዘር ወደሆነው ንጉስ ተላልፈዋል። እርሱ የእግዚአብሔር ልጅ ይሆናል፤ እግዚአብሔር ከጠላቶቹ ያሳርፈዋል እናም እርሱ የእግዚአብሔር ስም የሚሰፍንበትን የእግዚአብሔር ቤተ-መቅደስ በፅዮን ይሰራል። ይህ ማለት እግዚአብሔር ለእሰራኤል የገባውን የተስፋ ቃል የፈፀመው ከዳዊት ዘር በሆነው ንጉስ በኩል ነው ማለት ነው። ይህ ንጉስ እስራኤልን በእግዚአብሔር ፊት ይወክላል

። በእግዚአብሔርና በእስራኤል መካከል የነበረውን ቃል-ኪዳናዊ ግንኙነት እውን ያደረገው በመካከላቸው ወኪል በመኖሩ ነው። በሙሴ ቃልኪዳን ሁሉም እስራኤል የእግዚአብሔርን ጥበቃና ባርኮት እንዲቀበሉ ታማኝ መሆን ይጠበቅባቸው ነበር።(ኢያሱ. 7፡1-13) ። ሆኖም ዳዊታዊው ቃልኪዳን በአንዱ ከዳዊት ዘር በሆነው ንጉስ ታማኝነት አማካኝነት በእስራኤል ላይ የእግዚአብሔርን ቃልኪዳናዊ በረከቶች እርግጠኛ አድርጓል። እንዳለመታደል የዳዊት ዘር የሆኑት አብዛኞቹ ነገስታት ታማኝ ባለመሆናቸው እግዚአብሔር እንደፈለገው ሊባርካቸው አልቻለም።የብሉይ ኪዳን መጽሐፍት አብዛኞቹ ነገስታት ምን ያክል ታማኝ እንዳልነበሩ በመዘርዘር የተሞሉ ናቸው

። መልካሙ ዜና ልጁ ከዳዊት የዘር ግንድ እንዲወለድ መላኩና ክርስቶስም ፍፁም ታማኝ መሆኑ ነው። ስለዚህ እግዚአብሔር ለህዝቡ የገባላቸውን ቃል ኪዳን በርሱ በኩል መፈፀም ይችላል። እግዚአብሔር ንጉስን ሲባርክ ህዝቡ ሁሉ የዚያ በረከት ተካፋይ ይሆናሉ። ለዚህ ነው እየሱስ የእግዚአብሔር በረከቶች አስተላላፊያችን የሆነው። መካከለኛ መሆኑ የእግዚአብሔር በረከቶች በእርሱ በኩል ስለሚፈሱ ነው። የመዳናችን እርግጠኛ ተስፋ በእየሱስና እርሱ ለኛ ባደረገው ላይ ብቻ የተመሰረተ ነው። በቃል-ኪዳኑ ውስጥ በእርሱ በኩል ታማኝ ስላልነበሩባቸው ጊዜያት ያስቡ ። ይህ ለመዳናችን ሙሉ በሙሉ በእየሱስ ላይ መደገፍ እንዳለብን የሚያስተምረን እንዴት ነው?

ታህሳስ 26
Jan 4

ኢየሱስ የእኛ አሸናፊ ነው።


ከ1ኛ ሳሙኤል 8:​19, 20 እና ከዕብራውያን 2:​14–16 ጋር አወዳድር። እስራኤላውያን ለንጉሥ ምን ይሹ ነበር? እነዚህ ምኞቶች በኢየሱስ ላይ ፍጻሜያቸውን ያገኘው እንዴት ነው?

እስራኤላውያን እግዚአብሔር ንጉሣቸው መሆኑን ስለዘነጉ በጦርነቱ ላይ ዳኛና መሪ እንዲሆንላቸው ፈለጉ። የእግዚአብሔር አገዛዝ በሕዝቡ ላይ ሙሉ በሙሉ እንደገና መቋቋሙ ከኢየሱስ ጋር ነው። ኢየሱስ እንደ ንጉሣችን ከጠላቶች ጋር በሚደረገው ውጊያ ይመራናል። ዕብራውያን 2፡14-16 ኢየሱስን የደካሞች የሰው ልጆች አሸናፊ መሆኑን ይገልፃል። ክርስቶስ ዲያብሎስን በብቸኝነት ተጋፍጦ አሸንፎ ከባርነት ነፃ ወጣን። ይህ መግለጫ በዳዊትና በጎልያድ መካከል የነበረውን ጦርነት ያስታውሰናል። ዳዊት ንጉሥ ሆኖ ከተቀባ በኋላ (1ሳሙ 16) ጎልያድን በማሸነፍ ወንድሞቹን ከባርነት አዳናቸው። የተሳትፎ ውሉ የሚወስነው የውጊያው አሸናፊ የሌላውን ወገን ህዝብ ባሪያ እንደሚያደርግ ነው (1ሳሙ. 17፡8–10)። ስለዚህ ዳዊት የእስራኤል አሸናፊ ሆኖ አገልግሏል። እሱ ወክሎባቸዋል። ኢሳያስ 42:13 እና ኢሳያስ 59:15–20ን አንብብ። በእነዚህ ምንባቦች ውስጥ ያህዌ ራሱን እንዴት ይገልፃል?

ዕብራውያን 2፡14–16 እግዚአብሔር እስራኤላውያንን በብቸኝነት በሚዋጋበት ጊዜ ያድናቸዋል የሚለውን አስተሳሰብ ይጠቅሳል። ይህን የኢሳያስን ክፍል አስተውል፡ “እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፡- የኃያላን ምርኮ ይማረካል የጨካኞችም ብዝበዛ ይድናል ከአንቺ ጋር የሚጣሉትን እጣላለሁና ልጆችሽንም አድናቸዋለሁ። ” ( ኢሳ. 49:25፣ ኢ.ኤስ.ቪ.)

ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ከሰይጣን ጋር በብቸኝነት እየተዋጋን እንዳለን እናስባለን። ኤፌሶን 6፡10–18 ን ስናነብ፣ አዎን፣ ከዲያብሎስ ጋር እንደምንዋጋ እናያለን። እግዚአብሔር ግን አሸናፊ ነውና በፊታችን ወደ ጦርነት ይሄዳል። እኛ የሠራዊቱ አካል ነን; ለዚህም ነው የጦር ትጥቁን መጠቀም ያለብን። በተጨማሪም ብቻችንን አንዋጋም። በኤፌሶን 6 ላይ ያለው “አንተ” ብዙ ነው። እኛ እንደ ቤተ ክርስቲያን ትጥቁን ይዘን ከኛ አሸናፊ ጀርባ አንድ ሆነን እንታገላለን እርሱም እግዚአብሔር ነው። (የመደበኛ እትም ገጽ 15)

የእግዚአብሔርን የጦር ዕቃ ልበስ ማለት ምን ማለት ነው? ማለትም፣ ከራስ፣ ከፈተና እና ከመሳሰሉት ጋር በየዕለቱ በምንታገለው ትግል፣ በእግዚአብሔር ኃይል ታማኝ እንድንሆን የሚያስችለንን ኃይል እንዴት ራሳችንን መጠቀም እንችላለን? 21

ታህሳስ 27
Jan 5

ኢየሱስ ሊቀካህናችን ነው


ዕብራውያን 5-7 የኢየሱስን ሁለተኛ ተግባር ያስታውቀናል። እርሱ ሊቀካህናች ነው። ጳውሎስ እንደሚገልጽልን ይህ ተግባር እግዚአብሔር ከዳዊት ዘር በሚሆነው ንጉስ በኩል እንደሚፈጸም የገባውን ተስፋ ማለትም እንደ መልከ ጼዴቅ ስርዓት ለዘላለም ካህን(መዝ.110፡4፣ዕብ.5፡5-6) እንደሚሆን የተናገረው ፍጻሜ ነው። ዘሌዋውያን1፡1-9፣ዘሌ.10፡8-11፣ሚል.2፡7፣ዘሁልቁ.6፡ 22-26ና ዕብ.5፡1-4ን ያንብቡ። ካህኑ ምን ምን ተግባሮችን ይፈጽማል?



ካህናቱ የሰው ልጆችን እንዲወክሉና ከእግዚአብሔር ጋር ባላቸው ግንኙነት መካከለኛ እንዲሆኑ የተሾሙ ናቸው። ካህኑ አማላጅ ነበረ። በየትኛውም የክህነት ስርዓት ማለትም በአይሁድ፣በግሪክ፣በሮም ወይም በሌላ ይህ ተመሳሳይ ሁኔታ ነበረ። ካህን ከእግዚአብሔር ጋር እንድንገናኝ ያስችለናል፤ካህኑ የሚያደርጋቸው ነገሮች በሙሉ ደግሞ በኛና በእግዚአብሄር መካከል ያለው ግንኙነት መፋጠንን አላማ አድርገው የተነሱ ናቸው። ካህኑ ሰዎችን ወክሎ መስዋዕቶችን ያቀርባል። ህዝቡ ራሱ እነዚህን መስዋዕቶች ማቅረብ አይችልም ነበር።ካህኑ ስጦታችን በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነትን እንዲያገኝ ወይም ኃጢአታችን ነጽቶ ይቅርታ እንድናገኝ ተቀባይነት ያለው ካህን እንዴት ማቅረብ እንደምንችል ያውቃል።

ካህናት የእግዚአብሔርን ሕግ ለህዝቡ ያስተምሩም ነበር። በእግዚአብሔር ትዕዛዝ የተካኑ ሲሆኑ መግለጽና መተግበርም ኃላፊነታቸው ነበር። በመጨረሻም ካህናቱ በያህዌ ስም የመባረክ ኃላፊነትም ነበራቸው። በነርሱ በኩል እግዚአብሔር ለህዝቡ ያለውን መልካም ኃሳብና መልካም አላማ ያስተላልፍ ነበር። ሆኖም በ1ጴጥ.2፡9 አንድ ሌላ ነገርን እንመለከታለን።እኛ በኢየሱስ የምናምን የንጉስ ካህናት ተብለን ተጠርተናል። ይህ ኃላፊነት አስደናቂ በረከቶችን የያዘ ነው። ካህናት በቤተመቅደሱ ውስጥ ወደ እግዚአብሔር ይቀርቡ ነበር። ዛሬ እኛ በጸሎት በድፍረት በእግዚአብሔር ፊት መቅረብ እንችላለን (ዕብ.4፡1416፣ዕብ.10፡19-23)። እንዲሁም ወሳኝ ኃላፊነቶችም አሉብን። በእግዚአብሔር ሰዎችን የማዳን ሥራ መተባበር ይኖርብናል። የእግዚአብሔርን ህጎችና መመሪያዎች ለሌሎች እንድናስተምርና እንድናብራራ ይፈልግብናል።

በተጨማሪም ለርሱ ደስ የሚያሰኘውን የምስጋና የመልካም ሥራ መስዋዕትን እንድናቀርብ ይፈልግብናል። እነሆ ድንቅ በረከትና ኃላፊነት! በርግጥም የንጉስ ካህናት መሆናችን በህይወታችን ምን አይነት ለውጦችን ሊያመጣ ይገባዋል? ይህ እውነት አኗኗራችን ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር የሚገባው እንዴት ነው?

ታህሳስ 28
Jan 6

ኢየሱስ የተሻለው ኪዳን መካከለኛ


ዕብራውያን 8-10 በኢየሱስ የአዲስ ኪዳን መካከለኛነት(አማላጅነት) ሥራ ላይ ያተኩራል። ብሉይ ኪዳን ወደፊት የሚመጡ መልካም ነገሮችን እንደጥላ ሆኖ የሚያሳይ ነበረ። ሥነስርዓቶቹ ኢየሱስ ወደፊት የሚሰራውን ሥራ በምሳሌ ለመግለጽ የታሰቡ ነበሩ። ስለዚህ ካህናቱ ኢሱስን የሚያመላክቱ ቢሆኑም ሓጢያተኞችና ሟቾች ነበሩ። እንደ ኢየሱስ ፍጹም አልነበሩም። ያገለግሉ የነበሩበት ቤተ መቅደስም የሰማዩ ቤተ መቅደስ ጥላና አምሳያ ነበር(ዕብ.8፡ 5)።

ኢየሱስ በእውነተኛው ቤተ መቅደስ እያገለገለ ያለ ሲሆን ወደ እግዚአብሔር እንድንቀርብ አስችሎናል። የእንስሳት መስዋዕቶቹ ኢየሱስ በኛ ፋንታ መሞቱን የሚያሳዩ ቢሆኑም ደማቸው ግን ሕሊናን ሊያነጻ አልቻለም። የኢየሱስ ሞት ግን ወደ እግዚአብሔር በድፍረት እንድንቀርብ ሕሊናችንን ያነጻል(ዕብ.10፡1922) ። ዕብ.8፡8-12ን ያንብቡ። በአዲሱ ኪዳን እግዚአብሔር ቃል የገባልን ምንድነው?



አብ ኢየሱስን ሊቀ ካህን አድርጎ ሲሾም ብሉይ ኪዳን ለመፈጸም ተስፋ ብቻ ሲያደርግ የነበረውን በአዲሱ ኪዳን ሊፈጽም ጀምሯል። አዲሱ ኪዳን ፍጹም፣ዘላለማዊና አምላክም ሰውም የሆነ ካህን ሊያደርጋቸው የሚችላቸውን ነገሮች የያዘ ነው። ሊቀ ካህናችን የእግዚአብሔርን ሕግ ማብራራት ብቻ ሳይሆን በልባችንም ይጽፈዋል። ይህ ካህን የሚያቀርበው መስዋዕት ይቅርታን ይሰጣል። ይህ ካህን ያነጻል፣ይለውጠንማል።ልባችንን ከድንጋይ ወደ ስጋ ልብ ይቀይርልናል (ሕዝ. 36፡26)። እኛን አዲስ አድርጎ ይሰራናል (2 ቆሮ.5፡ 17)።ይህ ካህን ወደራሱ እንድንቀርብ በማስቻል እጅግ አስደናቂ በሆነ መንገድ ይባርከናል።

እግዚአብሔር ብሉይ ኪዳንን ያሰበው ወደፊት ኢየሱስ ወደሚሠራው ሥራ እንዲያመላክት ነበር። በዕቅዱና በዓላማው ውብ ነበር። ሆኖም አንዳንዶች አላማውን በተሳሳተ መንገድ ተረዱ። ምክትና ጥላ የሆኑትን ለመተው ስላልፈለጉና ምልክቶቹ ያሳዩ የነበሩትን ለመቀበል ፈቃደኛ ስላልሆኑ የኢየሱስ አገልግሎት የሚሰጣቸውን ድንቅ በረከቶች አጡ።

ኢየሱስ የቤተመቅደሱ መሰረትና ህይወት ነበር። አገልሎቶቹም የእግዚአብሔርን ልጅ መስዋዕት የሚያሳዩ ነበሩ። የካህናቱ አገልግሎት የክርስቶስን የማማለድ ሥራና ባህሪ ለመወከል የተቋቋመ ነበር።የመስዋዕቱ አምልኮ ሙሉ ዕቅድ አለምን ለመዋጀት አዳኛችን የሚሞተውን ሞት የሚያመላክቱ ነበሩ። እነዚህ መስዋዕቶች ለዘመናት ሲያመላክቱ የነበሩት ታላቁ ክስተት ሳይፈጸም የተሟሉ አይሆኑም።” Ellen G. white, The Desire of ages, p.165

ታህሳስ 29
Jan 7


ተጨማሪ ሀሳብ


በዕብራውያን መልዕክት መልካምና ተስፋን የሚሞሉ እውነቶች ቢኖሩም ከምዕራፍ 10-12 ላይ ጡዘት ላይ የሚደርሱ ተከታታይ ማስጠንቀቂያዎችም አሉበት። እነዚህ ክፍሎች ቢያንስ ሁለት ክፍሎች ይኖራቸዋል። በመጀመሪያ ሁሉም የዕብራውያን መልዕክት አንባቢዎችን በበረሃ ከተጓዘው ትውልድ ጋር ያነጻጽራሉ። በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ እምነት እንዲኖረን ይመክሩናል። የምድረ በዳው ትውልድ የእግዚአብሔርን አስደናቂ ኃይል በድንቅና በተዓምራት ከግብጽ ሲያወጣቸው የተመለከተ ትውልድ ነው። ከሲና ተራራ እግዚአብሔር አስርቱን ትዕዛዛት ሲናገርም ሰምተዋል። በምሽቱ የእሳቱን አምድ በቀን የደመናውን አምድ ተመልክተዋል። ከሰማይ የሆነውን እንጀራ መናን በልተዋል። በሚያርፉበት ሁሉ ከዓለቶች የወጣውን ውሃም ጠጥተዋል።

ነገር ግን ወደ ተስፋይቱ ምድር ድንበር ሲደርሱ እግዚአብሔርን መተማመን አልቻሉም።(ዕብ.11፡6)። እግዚአብሔር በዋናነት የሚፈልገውን ዕምነት አጡ። ያለ ዕምነትም ማስደሰት አይቻልም።(ዕብ.11፡6) ጳውሎስ ሲናገር እኛም እንደ ምድረበዳው ትውልድ በተስፋይቱ ምድር ድንበር ላይ ያለን ነን(ዕብ.10፡37-39) ። ሆኖም በረከቶቻችንና ኃላፊነቶቻችን ከነርሱ የበለጡ ናቸው። እግዚአብሔር በሲና ሲናገር አልሰማንም ነገር ግን በቃሉ ውስጥ በጽዮን ተራራ እጅግ የበለጠውን የእግዚአብሔርን መገለጥ ማትም በአካል የተገለጠው ኢየሱስ ክርስቶስን ተመልክተናል(ዕብ.12፡1824) ። ጥያቄው፡- እምነት ይኖረን ይሆን? የሚለው ነው። ጸሐፊው ከኢየሱስ የሆኑትን ባህሪያት ዘርዝሮ ምሳሌውን እንድንከተል ያበረታታናል።


የመወያያ ጥያቄዎች



1. ኢየሱስ ከዲያብሎስ ጋር ባለብን ውጊያ ከፊታችን የሚሄድ መሪያችን መሆኑን ተምረናል። እንደ ቤተክርስትያን በህብረት ሆነን ከመሪያችን ጀርባ እንዴት መዋጋት እንችላለን? ይህ ህብረት እንዳይመጣ የሚከለክሉት ነገሮች ምንድናቸው? እንደ ቤተክርስትያን ሰይጣን ሊያዳክመን የሚችልባቸው መንገዶች የትኞቹ ናቸው? ሰይጣን እስራኤልን ያደከመው እንዴት ነበር?

2. አማኝ እንደመሆናችን በእግዚአብሔር ምሪት ውስጥ የምንኖር የካህናት ማህበር ነን። እርስዎ ያሉባት አጥቢያ ቤተክርስትያን የተሻለን የምስጋናንና የመልካም ስራዎችን መስዋዕቶች ልትሰዋ የምትችለው እንዴት ነው? እባክዎትን በዝርዝርና ተግባራዊ በሆነ መልኩ ይነጋገ?

3.እኛ ያለንበት ሁኔታ የምድረበዳው ትውልድ ወደ ተስፋይቱ ምድር ከመሻገሩ በፊት ከነበረበት ሁኔታ ጋር የሚመሳሰለው እንዴት ነው? ከመመሳሰሎቹ ምን ትምህርት እናገኛለን?




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA union SSL