የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ወቅታዊ እውነት በኦሪት ዘዳግም


4ኛ ሩብ ዓመት 2021

ከህዳር 18 – 24

10ኛ ትምህርት

Nov 27-Dec 3




አስታውስ፤ ከቶም አትርሳ



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ዘፍ. 9:8–17 ዘዳ. 4:32–39፣ ራዕ. 14:12፣ ዘዳ. 4:9፣ 23፣ ዘዳ. 6:7፣ ዘዳ. 8:7–18፣ ኤፌ. 2:8–13።


የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ “‘አምላክህን እግዚአብሔርን በምድረ በዳ እንዴት እንዳስቆጣኸው አስታውስ፤ ከቶም አትርሳ። ከግብፅ ከወጣህበት ዕለት አንሥቶ እዚህ ቦታ እስከ ደረስህበት ጊዜ በእግዚአብሔር ላይ እንዳመፅህ ነህ።” (ዘዳ. 9፡7)።

በ መጽሐፍ ቅዱስ ሁለት ቃላት ተደጋግመው ተጠቅሰዋል፡ አስታውስ እና አትርሳ። ሁለቱም የሚያመለክቱት ከሰው ልጅ ባህሪ ጋር ስለ የተያያዘ፣ በአእምሮአችን ውስጥ ስለሚከናወን ነገር ነው። ሁለቱም ግሦች ሲሆኑ ተቃራኒ ፍቺ አላቸው፡ ማስታወስ አለመርሳት ሲሆን፤ አለመርሳት ደግሞ ማስታወስ ነው። እግዚአብሔር ለሕዝቦቹ ያደረጋቸውን ነገሮች--ለእነርሱ ያለውን ጸጋ እና ቸርነት እንዲያስታውሱ በተደጋጋሚ ይነግራቸዋል። ነቢያት ለሕዝቡ ያቀረቧቸውን መልእክቶች የያዘው አብዛኛው የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ክፍል የዕብራውያን ሕዝቦች እግዚአብሔር ያደረገላቸውን እዳይረሱ ይነግራል። በተጨማሪ በጣም አስፈላጊ የሆነው ነጥብ፤ በእርሱ የቀረበላቸውን ጥሪ እና ለጥሪው ምላሽ ለመስጠት ምን ዓይነት ሕዝቦች እንደ ነበሩ መርሳት አልነበረባቸውም። “የእግዚአብሔርን ሥራ አስታውሳለሁ፣ የጥንት ታምራትን በእርግጥ አስታውሳለሁ” (መዝ. 77፡11)።

በጋራም ሆነ በግለሰብ ደረጃ ከእኛ የዛሬው ሁኔታ የተለየ ነበር? እግዚአብሔር ለእኛ ያደረገውን ነገር መርሳት ምን ያህል ቀላል ነው? በዘዳግም መጽሐፍ እንደ ተገለጠው በዚህ ሳምንት እግዚአብሔር በሕይወታችን ያለውን መስጋብር ማስታወስና አለመርሳት በሚለው ወሳኝ መርኅ ዙሪያ ምልከታ እናደርጋለን።

ህዳር 1
Oct 31

ቀስተ ደመናን ማስታወስ


በመጽሐፍ ቅዱስ ለመጀመሪያ ጊዜ “አስታውስ” (አስብ) የሚለው ቃል የቀረበው የዘፍ. 9 ከዓለማቀፉ የጥፋት ውሃ በኋላ ነበር። በዚያን ወቅት ጌታ ምድርን ዳግመኛ በጥፋት ውሃ እንዳማያጠፋት ለማሳየት ቀስተ ደመናን የኪዳኑ ምልክት አድርጎ በሰማይ እንደሚገልጥ ለኖኅ ነገረው። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፍ. 9፡8-17። “አስታውስ” (አስብ) የሚለው ቃል በዚህ ስፍራ ጥቅም ላይ የዋለበት መንገድ ምን ይመስላል? እግዚአብሔር ለእኛ ያደረገልንን እንዴት ማስታወስ እንዳለብን አስመልክቶ ከቃሉ አጠቃቀም ምን እንማራለን?



እርግጥ ነው--እግዚአብሔር የሰጠውን የተስፋ ቃል እና የገባውን ኪዳን ለማስታወስ ቀስተ ደመና ማየት አያስፈልገውም። እዚህ ላይ ሰዎች ሊረዱት በሚችሉት ቋንቋ መናገሩን ልብ ይሏል። እንደ ሰው እግዚአብሔር ምድርን ዳግመኛ በጥፋት ውሃ እንደማያጠፋት የሰጠውን የተስፋ ቃል እና ኪዳን ለማስታወስ ቀስተ ደመናው አለልን። በሌላ አነጋገር ቀስተ ደመናው እግዚአብሔር የገባውን የተለየ ቃል ኪዳን ሕዝቡ እንዲያስታውስ የሚረዳ ነበር። ቀስተ ደመናው በታየ ቁጥር የእግዚአብሔር ሕዝቦች የሚያስታውሱት ዓለምን ስለ ኃጢአቷ የበየነባትን ፍርድ ብቻ ሳይሆን፤ ለዓለም ስላለው ፍቅርና ዳግመኛ በጥፋት ውሃ ውድመት እንደማያደርስባት የሰጠውን የተስፋ ቃል ጭምር ነው።

በመሆኑም የማስታወስ ጽንሰ ሀሳብን አስፈላጊነት እንደሚከተለው እንመለከታለን፡ የእግዚአብሔርን የተስፋ ቃሎች ማስታወስ፣ የእግዚአብሔርን ማስጠንቀቂያዎች ማስታወስ፣ እግዚአብሔር በምድር ላይ የሚወስደውን እርምጃ ማስታወስ። ብዙ ሳይንቲስቶች በዓለም ዙሪያ ተከስቶ እንደ ነበር የተገለጸውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ የጥፋት ውሃ እውነታ አይቀበሉም። ይህ ደግሞ በተፈጥሮ ሕግጋት ቀጣይነት ላይ የተመሠረተውን በሰማይ የሚወጣ ቀስተ ደመና ከመቼውም ይልቅ ዛሬ ይበልጥ አስፈላጊ ያደርገዋል።

የሚገርመው የጥፋት ውሃ ከመምጣቱ አስቀድሞ ብዙ ሰዎች ተመሳሳይ አስተሳሰብ ያራምዱ እንደ ነበርና--ከተፈጥሮ ሕግጋት ቀጣይነት አኳያ ምድር በጎርፍ ተጥለቅልቃ የመዋጧ ዕድል ፈጽሞ ሊሆን የማይችል ነው የሚል እሳቤ እንደ ነበራቸው ኤለን ኋይት በጽሑፏ ትጠቅሳለች። “ተፈጥሮ ከፈጣሪዋ በላይ በመሆኗ፤ ሕጎቿ እግዚአብሔር እራሱ ሊለውጣቸው በማይችለው መልኩ በጽኑ የቆሙ ናቸው” የኃይማኖት አባቶችና ነቢያት፡ ገጽ 98። ስለዚህ ከጥፋት ውሃ በፊት የነበሩ ሰዎች በምድር የተፈጥሮ ሕግጋት ላይ በመመሥረት ይህ ሊከሰት እንደማይችል ሲሞግቱ እንደ ነበር ሁሉ--ከጥፋት ውሃ በኋላም ሰዎች በተፈጥሮ ሕግጋት ላይ ተመሥርተው ተመሳሳይ ሀሳብ ሲያራምዱ ይታያሉ።

ይሁን እንጂ እግዚአብሔር በቃሉ አማካይነት ስለ ጥፋት ውሃ ነግሮን ሲያበቃ ለዓለም ምልክት ሰጥቶአል። ይኸውም ስለ ጥፋት ውሃ መከሰት ብቻ ሳይሆን፣ በድጋሚ እንደማያደርገው የሚገልጽ የተስፋ ቃል ጭምር ነው። ስለዚህ ቀስተ ደመና ምን ማለት እንደሆነ የምናስታውስ ከሆነ የአምላካዊውን ቃል ትክክለኛነት የሚገልጹ በሰማይ ላይ የተጻፉ ውብ ቀለማት ማረጋገጫ ይኖረናል። በዚህ የተስፋ ቃል ላይ የሰጠንን ቃል ማመን የምንችል ከሆነ፣ ታዲያ ቃሉ የሚነግረንን ነገር ሁሉ ለምን አናምነውም? በሚቀጥለው ጊዜ ቀስተ ደመና ሲያዩ ስለ አምላካዊው የተስፋ ቃል ያስቡ። በእነዚህ ሁሉ የተስፋ ቃሎች እምነት መጣል የምንችለው እንዴት ነው?





ህዳር 2
Nov 1

ያለፉትን ጊዜያቶች አስመልክቶ


ሕዝቡ እንደ አንድ በእግዚአብሔር የተመረጠ ወገን የተሰጠውን መብትና ጥቅም አስመልክቶ ጌታ በሙሴ አማካይነት የቸራቸውን አስደናቂ ምክርና ተግሳጽ በዘዳ. 4 አንብበናል። “ ‘አምላካችሁ እግዚአብሔር በዐይናችሁ እያያችሁ ለእናንተ በግብፅ እንዳደረገው ሁሉ በፈተና፣ በታምራዊ ምልክቶችና በድንቆች፣ በጦርነት፣ በጸናች እጅና በተዘረጋች ክንድ ወይም በታላቅና በአስፈሪ ሥራዎች’ ” ከምድረ ግብፅ በማውጣት ተቤዥቷቸዋል (ዘዳ. 4፡ 34)። በሌላ አነጋገር ጌታ ታላቅ ነገር ብቻ አላደረገላቸውም፤ ይልቁንም ለማስታወስ በማይቸገሩበትና ሊረሱ በማይችሉበት መንገድ እነሆ ታላላቅ ነገሮችን አደረገላቸው።

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘዳ. 4፡32፡39። ጌታ እንዲያስታውሱ እየነገራቸው የነበረው ነገር ምን ነበር? የእነርሱ እነዚህን ነገሮች ማስታወስ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምን ነበር?



ሙሴ ወደ ኋላ እስከ ፍጥረት ሳይቀር በመጓዝ በማናቸውም የቀደሙ ታሪኮች ለእነርሱ የተደረገውን ያህል የተደረገለት ማንም እንዳልነበር በሚያወሳ አሳማኝ ንግግር ሕዝቡን ይጠይቃል። እንዳውም ለራሳቸው በማጥናት፣ ከዚህ ቀደም እነርሱ ባለፉበት መንገድ የተስተዋለ አንድ እንኳ ክስተት መኖሩን እንዲጠይቁና እንዲመለከቱ ይጋብዛቸዋል። ሙሴ ጥቂት ጥያቄዎችን በመጠየቅ ጌታ ለእነሱ ያደረገላቸውን ለራሳቸው እንዲገነዘቡ ለማድረግ እየሞከረ ነበር። በዚህም እርሱ በኃያል ሥራዎቹ ምን ያህል ባለውለታቸው እና በሕይወታቸው ምስጋና ሊያቀርቡለት የሚገባ አምላክ እንደሆነ አመልክቷቸዋል። የእነዚህ ድርጊቶች አስኳል ከግብፅ መውጣታቸው እና ምናልባትም በአንዳንድ ሁኔታዎች ይበልጥ አስገራሚ የሆነው በሲና ተራራ “ከእሳት ውስጥ ቃሉን” መስማታቸው ነው።

ጥቅሱን ያንብቡ፡ ዘዳ. 4፡40። ሕዝቡ፡ እግዚአብሔር ስላደረገላቸው ነገሮች ከሚያወሱት ከእነዚህ ቃላት ተነስቶ ምን ዓይነት ድምዳሜ ላይ እንዲደርስ ነበር የሙሴ ፍላጎት?



ጌታ ከእነዚህ ነገሮች አንዱንም ያለ ዓላማ አላደረገም። ከእነርሱ ጋር የመሠረተውንና በእርሱ በኩል የገባውን ቃል ኪዳን በመጠበቅ የኔ ያለውን ሕዝብ ተቤዥቷል። አሁን ሕዝቡ ከግብፅ ነጻ ወጥቶ ወደ ተስፋይቱ ምድር የሚገባበት ሁኔታ ላይ ነበር። እግዚአብሔር የራሱን ድርሻ ተወጥቷል። እነርሱ ደግሞ በተራቸው የድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ የቀረበላቸው ሲሆን፤ ይኸውም መታዘዝ ነበር። ለመሆኑ ይህ ምሳሌ በአዲስ ኪዳን የተገለጠውን የመዳን ዕቅድ የሚወክለው እንዴት ነው? የሱስ ለእኛ ምን አደረገልን? ለዚህ ላደረገልን ነገር ምላሽ የምንሰጠው እንዴት ነው? (ራእ. 14፡ 12)።





ህዳር 2
Nov 1

ልብ በሉ… እንዳትረሱ


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘዳ. 4፡9፣23። ጌታ ምን እንዲያደርጉ እያዘዛቸው ነው? ይህ ምክር ለሕዝቡ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?



በሁለቱም ጥቅሶች መክፈቻ ላይ አበይት ሆነው የቀረቡት ግሶች፡ “ከልባችሁ እንዳይጠፉ” (ልብ በሉ) እና “እንዳትረሱ” የሚሉ ናቸው። ጌታ እያላቸው የነበረው፡ ልብ የምትሏቸው ከሆነ አትረሷቸውም--ነበር። ጌታ ለእናንተ ያደረገውን ወይም ከእናንተ ጋር የገባውን ቃል ኪዳን አትርሱ! “ከልባችሁ እንዳይጠፉ” (በዘዳ. 4፡9 ለየት ባለ ቅርጽ “ራሳችሁን ጠብቁ” በሚልም ጥቅም ላይ የሚውሉት) እነዚህ ቃላት በመላው የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት የሚገኙ ሲሆን ጠቅለል ብሎ ሲቀርብ፤ ራስን “መጠበቅ” የሚል ፍቺ አላቸው። የሚገርመው ቃሉ ለመጀመሪያ ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ የተጠቀሰው ኃጢአት ከመግባቱ አስቀድሞ እግዚአብሔር የኤደንን አትክልት ስፍራ “ጠብቅ” ብሎ ለአዳም በነገረው ጊዜ ነበር (ዘፍ. 2፡15)።

አሁን፣ ጌታ በተናጥል (ግሱ የቀረበው በነጠላ ነው) ቢያንስ ራሳቸውን መጠበቅ እንዳይረሱ ይነግራቸዋል። ይህ “መርሳት” ባብዛኛው የማስታወስ ችሎታን ከማጣት የሚመጣ ችግር ሳይሆን (ምንም እንኳ ከጊዜ በኋላ እና አዳዲስ ትውልዶች በመጡ ቁጥር ሊከሰት ቢችልም) በገቡት ኪዳን ላይ ልል ከመሆን የሚመነጭ ነው። የኸውም ምን ዓይነት ሕዝቦች እንደነበሩ እያስታወሱ--በእግዚአብሔር ፊት፣ በሌሎች ዕብራውያንና በመካከላቸው በሚኖሩ መጻተኞች ፊት እንዴት እንደሚመላለሱ መጠንቀቅ ነበረባቸው። እንደገና እነዚህን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ዘዳ. 4፡9 (በተጨማሪ፡ ዘዳ. 6፡7፣ ዘዳ. 11፡19 ይመልከቱ።) ሆኖም፤ በመጨረሻው ላይ ለልጆቻቸው እና የልጅ ልጆቻቸው ስለ ማስተማር በሚናገረው ክፍል ላይ ትኩረት ያድርጉ። እንዳይረሱ በመርዳት ረገድ ምን ፋይዳ ይኖረዋል?





ሙሴ “እንዳትረሱ” ብሎ ከነገራቸውና እነዚህ ነገሮች “ከልባችሁ እንዳይጠፉ” ብሎ ካሳሰባቸው በኋላ ቀጠል አድርጎ፣ ለልጆቻቸውና ለልጅ ልጆቻቸው እንዲያስተምሩ ማሳሰቡ አጋጣሚ አልነበረም። ምናልባትም ይበልጥ አስፈላጊ የሆነው ልጆቻቸው ስለ እነዚህ ነገሮች መስማታቸው ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔር ያደረገላቸውን ከትውልድ ወደ ትውልድ ማስተላለፋቸው ጭምር ነበር። ይህ ሲሆን የእነዚህን ነገሮች ምንነት ሕዝቡ አይዘነጋም። ታዲያ ጌታ ለተመረጡ ሕዝቦቹ ስላደረገላቸው ነገሮች ያለውን ዕውቀት ጠብቆ ማቆየት የሚያስችል ሌላ ምን የተሻለ መንገድ አለ? ከጌታ ጋር የነበርዎትን ተሞክሮ ለሌሎች መናገርዎ ሌሎችን ብቻ ሳይሆን ራስዎንም የጠቀመው እንዴት ነበር? የእግዚአብሔርን ምሪት ዘርዝረው ማውራትዎ አብሮነቱን እንዳይረሱ የረዳዎት እንዴት ነበር?





ህዳር 2
Nov 1

የበሉ እና የጠገቡ


በሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ጀነራል ኮንፈረንስ ለ34 ዓመታት የሠሩ አንድ የቀድሞ የቤተ ክርስቲያን መሪ ከብዙ ዓመታት በፊት እርሳቸውና ባለቤታቸው በአንድ አውሮፕላን ማረፊያ እንዴት ሻንጣቸው እንደጠፋባቸው ተናግረው ነበር። “እዚያው ሻንጣው የጠፋበትና ሰዎች የሚተላለፉበት ስፍራ ተንበረከክንና ሻንጣው እንዲመለስልን ጌታን በጸሎት ጠየቅን።” ይህ ከሆነ ከብዙ ዓመታት በኋላ ተመሳሳይ ሁኔታ ተከሰተ። አውሮፕላን ጣቢያው ቢደርሱም ነገር ግን አንድ ሻንጣ አብሯቸው የለም። ከዚያ በመቀጠል የሆነውን ሲናገሩ፡ ባለቤታቸውን “አታስቢ፣ ኢንሹራንስ ይሸፍነዋል” አሏቸው ይባላል።

ይህን ታሪክ በአእምሮዎ እንደያዙ ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘዳ. 8፡ 7-18። እዚህ ላይ ጌታ ለሕዝቡ እየሰጠ ያለው ማስጠንቀቂያ ምንድን ነው? ለእኛስ ምን ትርጉም ሊኖረው ይገባል?



ለጌታ ታማኝ መሆናቸው ምን ሊያመጣላቸው እንደሚችል ይመልከቱ። እነዚህ ሕዝቦች “ ‘ምንም ነገር የማይታጣባት፣ የዳቦም ዕጦት የሌለባት’ ” (ዘዳ. 8፡9) አስደናቂና የበለጸገ ምድር ባለቤት መሆን ብቻ ሳይሆን፤ በምድሪቷ ላይ ከመጠን በላይ የተባረኩ ይሆናሉ--የከብት መንጋዎች፣ ወርቅ፣ ብር እንዲሁም ውብ መኖሪያ ቤቶች ባለቤት ይሆናሉ። ማለትም፡ ይህ ሕይወት የሚሰጠው ማንኛውም ቁሳዊ ምቾት ይቸራቸዋል። ይህ ሲሆን ምን ሊከሰት ይችላል? ሁሌም ቢሆን ሀብት እና ቁሳዊ ብልጽግናን የሚጎበኘውን አደጋ የሚጋፈጡ ሲሆን፣ ይኸውም--ሀብት እንዲያፈሩ ችሎታ የሰጣቸውን (ዘዳ. 8፡18) ብቸኛውን ጌታ መርሳት ነው።

ምናልባት በመጀመሪያም ባይሆን ነገር ግን ዓመታት እያለፉ ሲሄዱና የሚያስፈልጓቸው ሁሉ ቁሳዊ ምቾቶች ሲሟሉላቸው ያለፈውን ይረሳሉ፣ ጌታ እንዴት “በዚያ ጭልጥ ባለና በሚያስፈራ ምድረ በዳ” (ዘዳ. 1፡19) እንደመራቸው ይዘነጋሉ። እናም አብልጠው ስኬታማ እንዲሆኑ የረዳቸው የገዛ ብልሀተኝነታቸው እና ልዩ ተሰጦአቸው እንደሆነ ያስባሉ። ይህ እንግዲህ ጌታ በትክክል እያስጠነቀቃቸው የነበረው ነገር ነው (ሆኖም በሚያሳዝን ሁኔታ፣ በተለይ ስለ ኋለኞቹ ነቢያት ስናነብ ይኸው በትክክል ደርሶ እንመለከታለን)።

በመሆኑም በብልጽግና ውስጥ ሆነው ይህን ያደረገላቸው ጌታ ብቻ መሆኑን እንዲያስታውሱና እርሱ በሰጣቸው ቁሳዊ በረከቶች እንዳይታለሉ ይነግራቸዋል። የሱስ ራሱ በመቶዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በኋላ ስለ ዘሪው ምሳሌ ሲናገር በጠቀሰው “የሀብት አጓጊነት” (ማር. 4፡19) አስጠንቅቋቸው ነበር።

የቱንም ያህል ገንዘብና ቁሳዊ ንብረት ቢኖረንም ሁላችንም ወደ ምድር ትቢያነት ለመቀየር የምንጠባበቅ ሥጋ እና ደም ነን። ይህ ሀብትን መሠረት አድርገው ሊመጡ ስለሚችሉ አደጋዎች ምን ሊነግረን ይገባል? ሀብት ከሞት ሊያድነን የሚችለው ብቸኛ አምላክ እንደሚያስፈልገን አድርጎ ሊያስረሳን የሚችለው እንዴት ነው?





ህዳር 2
Nov 1

ባሪያ እንደነበራችሁ አትርሱ


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘዳ. 5፡15፣ 6፡12፣ 15፡15፣ 16፡3፣12፣ 24፡18፣22። ጌታ በተለይ ፈጽሞ እንዳይረሱ የፈለገው ነገር ምን ነበር? ለምን?



ቀደም ሲል እንደተመለከትነው --ጌታ እንዴት አድርጎ በታምራዊ መንገድ ከግብፅ እንዳወጣቸው ሕዝቡ ወደ ኋላ መለስ እያለ ዘወትር እንዲያስብ ያለማቋረጥ ይነግራቸው ነበር። አይሁዶች በሺህ የሚቆጠሩ ዓመታት በኋላም እንኳ እነሆ ዛሬም ጌታ ያደረገላቸውን የሚያስታውሰውን የፋሲካ በአል ያከብራሉ። “እግዚአብሔር እሰጣችኋለሁ ብሎ በገባው ቃል መሠረት ወደ ምድሪቱ ስትገቡ ሥርዐት ጠብቁ። ልጆቻችሁ ስለ ሥርዐቱ ምንነት ሲጠይቋችሁ፣ ‘ግብፃውያንን በቀሰፈ ጊዜ፣ በግብፅ ምድር የእስራኤላውያንን ቤት አልፎ በመሄድ ቤታችንን ላተረፈ፣ ለእግዚአብሔር የፋሲካ መሥዋዕት ነው’ ብላችሁ ንገሯቸው። ” (ዘፀ. 12፡25-27)።

ለዛሬዋ ቤተ ክርስቲያን ፋሲካ በክርስቶስ የተሰጠን የመዳን ምልክት ነው፡ “የፋሲካ በጋችን የሆነው ክርስቶስ ተሠውቶአልና” (1ቆሮ. 5፡7)። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ኤፌ. 2፡8-13። እነዚህ የአሕዛብ አማኞች እንዲያስታውሱ የተነገራቸው ምንድን ነው? ይህ ሁኔታ በዘዳግም የተጠቀሱት ዕብራውያን እንዲያስታውሱ ከተነገራቸው ጋር እንዴት ይመሳሰላል?



እነዚህ ሕዝቦች እግዚአብሔር በክርስቶስ በኩል ያደረገላቸውን እንዲያስታውሱ፣ ከምን እንዳዳናቸውና ከተሰጣቸው አምላካዊ ጸጋ ብዛት አሁን ምን እንዳላቸው ያስታውሱ ዘንድ የጳውሎስ ፍላጎት ነበር። እንደ እስራኤል ልጆች ሁሉ አንዳችም በራሳቸው የሆነ ነገር አልነበረም:: ይልቁንም “ለኪዳኑ ተስፋ ባዕዳን” ሆነው ሳለ ለእነርሱ የተሰጠው የእግዚአብሔር ጸጋ ብቻ ነበር የክርስቶስ የሱስ ያደረጋቸው።

በምድረ በዳ ያሉ አይሁዶችም ሆኑ በኤፌሶን የሚገኙ ክርስቲያኖች ወይም ደግሞ በየትኛውም የዓለም ክፍል ያሉ ሰባተኛ ቀን የዳግም ምጽአቱ ተጠባባቂዎች--እግዚአብሔር በክርስቶስ ያደረገልንን ነገር ሁሌም ማስታወስ ወሳኝ ነው፡ “በየቀኑ ለተወሰነ ጊዜ ስለ ክርስቶስ ሕይወት ማሰላሰል ለእኛ ይበጀናል። የሕይወቱን ታሪክ በዘርፍ በዘርፉ አድርጎ እያንዳንዱን ትዕይንት፣ በተለይም የሕይወቱን መደምደሚያ ታሪክ በአእምሮ ዐይን ማየት ይገባናል። ለእኛ ያደረገልንን መሥዋዕት የዚህን ያህል በጥልቅ ያሰብንበት እንደሆነ በእርሱ ላይ ያለን አመኔታ አይዋልልም። ፍቅራችን ይጸናል፤ መንፈሱም ጠልቆ ይሰርጽብናል።” የዘመናት ምኞት፡ ገጽ 68።

ህዳር 2
Nov 1


ተጨማሪ ሀሳብ


“ርኅሩኁ አምላክ በኃጢአት ለወደቀው ሰብዓዊ ፍጡር ካለው አዘኔታና ፍቅር የተነሳ ክብሩን ወደጎን ትቶ ከሰው ጋር ቃል ኪዳን ገባ። ለቃል ኪዳኑ ማሰሪያ እንደ ምልክት አድርጎ ውብ የሆነውን ቀስተ ደመና አቆመ! ጌታ እንደተናገረው--ቀስተ ደመናውን በተመለከተ ጊዜ፤ ቃል ኪዳኑን ያስታውሳል። ይህ አባባል እግዚአብሔር የመርሳት ባህሪ አለው የሚል አንደምታ የለውም። ነገር ግን እርሱን በበለጠ እናስተውለው ዘንድ በሚገባን ቋንቋ መናገሩ ነው። አንዱ ትውልድ አልፎ ሌላው በተተካ ቁጥር ልጆች ሰማይን ያሰመረውን የውቡን ቀስተ ደመና ምንነት ወላጆቻቸውን ሲጠይቁ፤ ያን የቀደመ የጥፋት ውሃ ታሪክና የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ይተርኩላቸዋል። ይህም መለኮታዊውን ፍቅር ከአንዱ ትውልድ ወደ ሌላው የሚመሰክርና ሰዎች በእግዚአብሔር ላይ ያላቸውን እምነት የሚያጠነክር ይሆናል።” የኃይማኖት አባቶችና ነቢያት፡ ገጽ 111።

ክርስትና ከተመሠረተ ጊዜ አንስቶ ቤተ ክርስቲያን ዛሬ በአንዳንድ አገሮች የሚስተዋለው ዓይነት ሀብት እና የምዕመናን ምቾት ተካፋይ የሆነችበት ጊዜ የለም። እንዲህ ያለው ሀብት መንፈሳዊ ሕይወታችን ላይ ተጽእኖ ማሳደሩ ጥርጥር የለውም፤ በመሆኑም እንደ መልካም መታየት አይችልም። እንዴት? ሀብት እና ቁሳዊ ብልጽግና የክርስትና ምግባር የሆኑትን ራስን መካድ እና ራስን መሥዋእት አድርጎ የማቅረብ ባህሪያት የሚያጎለብቱት ከመቼ ጀምሮ ነው? በአብዛኛው የሚስተዋለው ከዚህ ተቃራኒ ነው። የሰዎች ሀብት ይበልጥ ባደገና በተመነደገ ቁጥር በእግዚአብሔር ላይ የሚኖራቸው መተማመን እየወረደ ይሄዳል። ሀብት እና ብልጽግና መልካም ቢሆኑም፣ አያሌ አደገኛ መንፈሳዊ ወጥመዶችን ይዘው ይመጣሉ።


የመወያያ ጥያቄዎች



1.ሀብት መንፈሳዊ ሕይወታችን ላይ እንዴት ተጽእኖ ያሳድራል በሚለው ሀሳብ ላይ ተወያዩ። ገንዘብ ያላቸው ሰዎች ሀብት ሊፈጥር ከሚችላቸው አንዳንድ መንፈሳዊ አደጋዎች ራሳቸውን የሚጠብቁባቸው መንገዶች የትኞቹ ናቸው?

2.በክርስቶስ ሕይወት መጨረሻ የነበሩት ትዕይንቶች ስለ እግዚአብሔር ፍቅር ምን ይነግሩናል? ያንን ተጨባጭ ፍቅር ፈጽሞ መርሳት የሌለብን ለምንድን ነው? ተወያዩበት። የእግዚአብሔርን ቸርነት የሚገልጹ ሌሎች ምን ዓይነት ነገሮችን ማሰብ ይችላሉ? ይህንን እውነታ ሁል ጊዜ በአእምሯችን መያዝ ያለብን ለምንድን ነው?

3.መጽሐፍ ቅዱስ የጥፋት ውሃ ተከስቶ ነበር ሲል (ቀስተ ደመናን በመጥቀስ) ቢናገርም አንዳንድ የሳይንስ ሊቃውንት ግን ይህን አይቀበሉም፤ መጽሐፍ ቅዱስ የፍጥረት ሥራ ስድስት ቀናት መውሰዱን (ሰባተኛው ቀን ሰንበት) ቢናገርም፣ አንዳንዶች ግን ስድስት ቀን የሚባል የለም ይላሉ። ባህል በእምነት ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ምን ያህል ኃይለኛና አሉታዊ ሊሆን እንደሚችል ይህ ምን ሊነግረን ይገባል?




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA union SSL