የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ዘፍ. 1፣ ዘፀ. 20:8–11፣ ዘፀ. 16:14–31፣ ዘዳ. 5:12–15፣ መዝ. 92፣ ኢሳ. 58:13።
የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ “እግዚአብሔር ሰባተኛውን ቀን ባረከው፤ ቀደሰውም፤ ካከናወነው የመፍጠር ሥራው ሁሉ ያረፈው በሰባተኛው ቀን ነውና” (ዘፍ. 2፡3)።
በ
ጨለማ መሃል ብርሃን፣ ሕይወት የሞላባቸው ውቅያኖሶች፣ በድንገት
የሚበሩ ወፎች--ምን ይመስሉ እንደነበር ማን ሊገምት ይችላል?
ከተፈጥሮ በላይ የሆነው የአዳምና ሔዋን አፈጣጠርስ? እግዚአብሔር
ይህን እንዴት እንዳደረገው ፍጹም ማስዋል አንችልም።
ነገር ግን ከዚህ ሁሉ በንቁ ትዕይንት የተሞላ የመፍጠር ሥራ በኋላ
እግዚአብሔር ትኩረቱን ወደ ሌላ ነገር ያዞራል። በመጀመሪያ ሲታይ እንደ ዓሣ
ነባሪዎች ዝላይ ወይም በኅብረ ቀለማት እንዳጌጠ ላባ ልብን ወከክ የሚያደርግ
አልነበረም። ቀለል ባለ መልኩ እግዚአብሔር ቀን ፈጠረ--ሰባተኛውን ቀን።
ከዚያም ይህን ቀን ከሌሎቹ የሳምንት ቀናት ለየው። ሰብዓዊው ፍጡር
በጭንቀት የተሞላ ጥድፊያ ሕይወት ውስጥ ከመግባቱ አስቀድሞ እግዚአብሔር
ሕያው የመታሰቢያ መርጃ ምልክት አድርጎ ሰየመው። በዚህ ቀን ቆም ብለን፣
ሕይወትን በማስተዋል የምንደሰትበት ጊዜ እንዲሆንልን---በዕለቱ ከሥራችን
አርፈን፣ በሣሩ፣ በአየሩ፣ በዱር እንስሳት፣ በውሃው፣ በሰዎች--ከሁሉም በላይ
ግን የእያንዳንዱ መልካም ስጦታ ፈጣሪ በሆነው ሐሴት እንድናደርግ ፈልጎ
ነበር።
የመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት ከኤደን ከተባረሩ በኋላም ቢሆን ይህ ግብዣ
ቀጥሏል። እግዚአብሔር ግብዣው የጊዜን ፈተና መቋቋም መቻሉን ማረጋገጥ
ስለ ፈለገ ገና ከመጀመሪያ አንስቶ ከጊዜ ድርና ማግ ጋር አስተሳሰረው።
በዚህ ሳምንት በተደጋጋሚ ወደዚህ ሳምንታዊ ሰባተኛ ቀን ዕረፍት እንድንገባ
ስለ ቀረበልን አስደናቂ አምላካዊ ግብዣ እናጠናለን።
በመጀመሪያ እግዚአብሔር በዚያ ነበር። ጌታ እግዚአብሔር ተናገረ--ሆነ።
ብርሃን ቀኑን ከሌሊት ለየ። ጠፈር፣ ሰማይ እና ባሕር በሁለተኛው ቀን
ካለመኖር ወደ መኖር መጡ። የብስ እና ዕጸዋት በሦስተኛው ቀን ተከተሉ።
እግዚአብሔር መሠረታዊ የሆኑትን የጊዜ ቀመር እና መልክዓ ምድር ፈጠረ።
በቀጣዮቹ ሦስት ቀናት ደግሞ ይሞላቸዋል። ብርሃናት በቀን እና በማታ
በሰማዩ ላይ ይሰለጥናሉ። መጽሐፍ ቅዱሳዊው የፍጥረት ታሪክ ከአብዛኞቹ
ጥንታዊ ባህሎችና ትውፊቶች በተለየ መልኩ ፀሐይ፣ ጨረቃ ወይም ከዋክብት
አማልክት እንዳልሆኑ በግልጽ ያሳያል። ወደ ትዕይንቱ የሚገቡት አራተኛው
ቀን ላይ ሲሆን፣ ለፈጣሪ ቃል ተገዢ ናቸው።
ሙሴ ስለ አምስተኛው እና
ስድስተኛው ቀን የሰጠው መግለጫ (ዘፍ. 1፡20-31) በሕይወት እና በውበት
የተሞላ ነው። ዐዕዋፋት፣ ዓሦችና የየብስ እንስሳት--ሁሉም እግዚአብሔር
ያዘጋጀላቸውን ቦታ ይሞላሉ።
እግዚአብሔር የሰጠው የግምገማ ቃል ስለ ፍጥረት ምን ይጠቁማል-ዘፍ፣ 1፡1-31?
ይህ እንደው በእግዚአብሔር የተጠረ ብቻ ሳይሆን ፍጹም የፍጥረት ሥራ ነው። እነዚህ ፍጥረታት ምድርን ይሞላሉ። ቀልብ የሚስብ ውብ ዜማ-እግዚአብሔር ከእያንዳንዱ ቀን በኋላ “መልካም” ይል ነበር። የሰው ልጅ አፈጣጠር ከተቀሩት ፍጥረታት በምን ይለያል? ዘፍ. 1:26-27፣ ዘፍ. 2:7፣ 21–24።
እግዚአብሔር ጎንበስ ብሎ ከምድር አፈር ወስዶ በጭቃ ቅርጽ መሥራት
ጀመረ። ሰብዓዊው ፍጡር በእግዚአብሔር መልክ እና አምሳል መፈጠሩ
ተጨባጭ የመቀራረብና ወዳጅነት ትምህርት ነው። እግዚአብሔር ጎንበስ
ብሎ በአዳም አፍንጫ የሕይወት እስትንፋስ እፍ አለበት። እርሱም ሕያው
ነፍስ ሆነ። እግዚአብሔር ከአዳም ጎድን አጥንት ወስዶ ሔዋንን በተለየ መንገድ
የፈጠረበት ሁኔታ በፍጥረት ሳምንት ላይ አንድ ሌላ ወሳኝ አላባ ይጨምራል።
በወንድ እና በሴት መካከል የሚደረግ የተቀደሰ መታመን ጥምረት የሆነው
ትዳር--እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ያሰበው ዓላማ አካል ነው።
በዚህ ወቅት፤ ማለትም እግዚአብሔር በስድስተኛው ቀን ያደረገውን
ሁሉ ከተመለከተ በኋላ የተናገረው--ቀደም ሲል በየመደምደሚያው ይናገር
ከነበረው ለየት ይላል፡ “እግዚአብሔርም ያደረገውን ሁሉ አየ፤ እነሆም፣ እጅግ
መልካም ነበረ” (ዘፍ. 1፡31)።
የመጽሐፍ ቅዱስ የፍጥረት ታሪክ አስተምህሮ፤ ሰው ያለ
አምላካዊው ቃል ምሪት ከሚያስተምረው ምን ያህል በእጅጉ
የተለየ እንደሆነ ያስቡ። እውነትን ለመረዳት በእግዚአብሔር
ቃል ላይ ምን ያህል መታመን እንዳለብን አስመልክቶ ይህ ምን
ሊነግረን ይገባል?
አምላካዊው የፍጥረት ሥራ “እጅግ መልካም” የነበረ ቢሆንም ነገር ግን ገና
የተሟላ አልነበረም። የፍጥረት ሥራ የተደመደመው በእግዚአብሔር ዕረፍት
እና በሰባተኛው ቀን ሰንበት ልዩ በረከት ነበር። “እግዚአብሔር ሰባተኛውን
ቀን ባረከው፤ ቀደሰውም፣ ካከናወነው የመፍጠር ሥራው ሁሉ ያረፈው
በሰባተኛው ቀን ነውና” (ዘፍ. 2፡3)።
ሰንበት የእግዚአብሔር ፍጥረት ሥራ ክፍል እና ጥቅል ነው። እንዲያውም
የፍጥረት ሥራ መደምደሚያ ነው። እግዚአብሔር ከሥራው በማረፍ ሰብዓዊው
ፍጡር (በወቅቱ የአዳምና ሔዋን ቤተሰብ) የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴውን
አቁሞ ከፈጣሪው ጋር ጎን ለጎን የሚያርፍበትን የጊዜ ማዕቀፍ ፈጠረ።
የሚያሳዝነው፤ ኃጢአት ወደዚህ ዓለም ገብቶ ሁሉንም ነገር ቀየረ።
ከእግዚአብሔር ጋር ይደረግ የነበረ ቀጥተኛ ግንኙነት ከዚህ በኋላ አከተመ።
በዚህ የወደቀ ዓለም ሁላችንም በሚገባ የምናውቀው የወዮታ ምሳሌ ማለትም-በወሊድ ወቅት የምጥ መበርታት፣ ጥሮ ግሮ መኖር፣ በቀላሉ የሚበጠሱ
ወዳጅነቶች እና የከሸፉ ግንኙነቶች በየቀኑ የሚስተዋሉ ክስተቶች ሆኑ። በዚህ
ሁሉ መሃል የእግዚአብሔር ሰንበት የአምላካዊው ፍጥረት ሥራ ውጤት
መሆናችንን ሲዘክር የሚኖር ቋሚ ምልክት ከመሆኑ በተጨማሪ ዳግም
የፈጠራችን ተስፋ እና ኪዳን ነው። ከኃጢአት በፊት ዕረፍት ካስፈለጋቸው-ከዚያ በኋላ ምን ያህል ይበልጥ ያስፈልግ?
እግዚአብሔር ከብዙ ዓመታት በኋላ ልጆቹን ከግብፅ ባርነት አርነት ሲያወጣ፣
ይህን ልዩ ቀን በድጋሚ አስታውሷቸዋል።
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፀ. 20፡8-11። ሰንበት ከፍጥረት ጋር ካለው
ግንኙነት አኳያ ይህ ስለ አስፈላጊነቱ ምን ያስተምረናል?
በዚህ ትዕዛዝ መሠረት የእርሱ ፍጥረት ሥራ መሆናችንን እናስታውስ ዘንድ
እግዚአብሔር ጥሪ ያቀርብልናል። ብዙዎች ከሚያምኑት በተቃራኒ እኛ
የቀዝቃዛ፣ ደንታ ቢስና ጭፍን ኃይሎች አጋጣሚ ውጤት አይደለንም።
ይልቁንም በእግዚአብሔር መልክ የተፈጠርን የእጁ ሥራዎች ነን። ከአምላክ
ጋር ኅብረት ይኖረን ዘንድ ተፈጠርን። እስራኤላውያን የቱንም ያህል ዋጋ ቢስ
ባሪያዎች ተደርገው ቢቆጠሩም፤ በራሱ በእግዚአብሔር አምሳል የተፈጠረ
ትክክለኛ ማንነታቸውን በተለየ መንገድ በየሰንበቱ ያስታውሱ ዘንድ ተጠርተው
ነበር።
“ሰንበትም የፍጥረት ሥራ መታሰቢያ እንደመሆኑ፣ የክርስቶስ ፍቅርና ኃይል
ምልክት ነው።”—Ellen G. White, The Desire of Ages, p. 281.
የስድስቱ ቀናት የፍጥረት ሥራ ኃይማኖታዊ አስተምህሮ ምን ያህል
አስፈላጊ እንደሆነ ያስቡ። ለነገሩ ከሕይወታችን አንድ ሰባተኛውን
ያለ ግድፈት በየሳምንቱ እያስታወስን ለእርሱ እንድንሰጥ የሚያዘን
ሌላ አስፈላጊ አስተምህሮ ይኖር ይሆን? በዘፍጥረት መጽሐፍ
በተገለጠው መሠረት እውነተኛ አመጣጣችንን ማስታወሳችን
ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ አስመልክቶ ይህ እውነታ ብቻውን
ሊያስተምረን የሚገባው ነገር ምንድን ነው?
ከአርባ ዓመታት የበረሀ መቅበዝበዝ በኋላ ስለ ግብፅ ምንም ትውስታ
ያልነበረው አዲሱ ትውልድ ለአካለ መጠን ደረሰ። ይህ ትውልድ ከወላጆቹ
የተለየ የሕይወት ተሞክሮ ነበረው። አዲሱ ትውልድ የወላጆቹን ተደጋጋሚ
እምነት ማጣት ተመልክቷል። ይህን ተከትሎ የወላጆቻቸው ትውልድ
እስኪያልቅ በምድረ በዳ መንከራተት ነበረባቸው።
የመገናኛው ድንኳን በሰፈራቸው መሃል በመኖሩ የአምላካዊውን ሕልዎት
ከማደሪያው በላይ በሚሰፈው ደመና የማየት ልዩ መብት ነበራቸው።
ደመናው ከማደሪያው ላይ በተነሣ ጊዜ ዕቃቸውን ሸክፈው መከተል መጀመር
እንዳለባቸው ያውቁ ነበር። በቀን ጥላ፣ በምሽት ደግሞ ብርሃንና ሙቀት
ማግኘታቸው፣ እግዚአብሔር ዘወትር ለእነርሱ ያለውን ፍቅርና እንክብካቤ
የሚያስታውስ ነበር።
እነዚህ ሕዝቦች የሰንበት ዕረፍትን በግል ሊያስታውሳቸው የሚችል
ምን ዓይነት ነገር አገኙ? ዘፀ. 16፡14-31።
ከታዋቂው የሥነ መለኮት አስተምሮ በተቃራኒ--ሰባተኛው ቀን ሰንበት ከሲና
ተራራ በፊት መሰጠቱን እነዚህ ጥቅሶች ያረጋግጣሉ።
በዚህ ቦታ በትክክል የሆነው ምን ነበር?
እግዚአብሔር ለሕዝቡ የሰጠው በዓይነቱ ልዩ የሆነ ምግብ፤ እርሱ
ፍጥረታቱን በየዕለቱ የሚደግፍ አምላክ መሆኑን የሚያስታውስ ነበር።
እግዚአብሔር የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ በተጨባጭ ያሟላላቸው ነበር።
በየቀኑ ፀሐይ ስትወጣ ከሚሰበሰበውና ፀሐይ ስትጠልቅ አብሮ ያበቃለት
ከነበረው ከዚህ ምግብ ሁኔታ አኳያ፤ እያንዳንዱ ቀን በታምራት የተሞላ ነበር።
ሆኖም ከዕለቱ ምግብ ቀንሶ ለማሳደር የሞከረ፣ በማግሥቱ ተልቶ እና ሸትቶ
ያገኘው ነበር። በተቃራኒው በየሳምንቱ አርብ ለሁለት ቀን በቂ የሆነ እጥፍ መና
ይወርድ ነበር። ይህ ከአርብ ቀን ያደረ ምግብ በታምራዊ ሁኔታ ተስማሚና
ትኩስ እንደሆነ ይገኝ ነበር።
በዚህ ወቅት እስራኤላውያን የመገናኛ ድንኳኑ አገልግሎት፣ በዘሌዋውያን
እና ዘኍልቍ መጻሕፍት የሰፈሩ ሕግጋት እና ደንቦች ነበሯቸው። ዕድሜ
የተጫነው ሙሴ ሕዝቡ ያለፉ ታሪኮቹን ደግሞ ደጋግሞ እንዲያጤንና
እግዚአብሔር የሰጣቸውን ሕጎች በተደጋጋሚ እንዲመለከት ጥሪ ያቀርብ ነበር
(ዘዳ. 5፡6-22)።
ይህ አዲስ ትውልድ በመጨረሻ ወደ ተስፋይቱ ምድር ለመግባት ተዘጋጀ።
እስራኤል የአመራር ለውጥ ልታደርግ በነበረችበት ወቅት፤ በዕድሜ የገፋው
ሙሴ ይህ ትውልድ ማን እንደነበር እና ተልዕኮው ምን እንደ ሆነ የሚያስታውስ
ስለ መሆኑ ማረጋገጥ ፈለገ። አዲሱ ትውልድ የወላጆቹን ስህተት እንዲደግም
አልፈለገም። በዚህ የተነሣ የእግዚአብሔርን ሕግ በድጋሚ ነገራቸው። ይህ
በተረጋጋ መንፈስ የሚገኝና ከነዓንን ድል ለመንሳት በቋፍ የነበረ ትውልድ
አምላካዊውን ትእዛዝ እንዳይረሳ በማሰብ እነሆ ዐሥርቱ ትእዛዛት በድጋሚ
ተሰጡ።
ከግል ተሞክሮአችን አኳያ--የየሱስ ዳግም ምጽአት ከሞትን
በኋላ በጣም አጭር ከሚባል ጊዜ የዘለቀ ቆይታ አይኖረውም።
በመሆኑም የእርሱ መመለሻ ሁል ጊዜ በደጅ ነው፣ ምናልባትም
እኛ ከምንገምተው በላይ የቀረበ ነው። ሰንበትን መጠበቃችን
እግዚአብሔር ለእኛ ያደረገውን ብቻ ሳይሆን ነገር ግን ዳግም
ሲመለስ ምን እንደሚያደርግልን ጭምር እንዴት ያስታውሰናል?
እስራኤላውያን በዮርዳኖስ ምሥራቃዊ ክፍል ሰፈሩ። በዚህም የባሳንን ንጉሥ ምድር እና የሁለት አሞራውያን ነገሥታትን ግዛቶች ወረሱ። አሁንም በዚህ ወሳኝ ወቅት ሙሴ እስራኤላውያንን በአንድነት ጠርቶ በሲና የተደረገው ቃል ኪዳን ወላጆቻቸውን ብቻ ሳይሆን እነሱንም እንደሚያካትት አስታወሳቸው። ከዚያም ይጠቅማቸው ዘንድ ዐሥርቱን ትእዛዛት እንደገና አቀረበላቸው። ጥቅሶቹን ያስተያዩ፡ ዘፀ. 20፡8-11 እና ዘዳ. 5፡12-15። የሰንበት ትዕዛዝ ለእነርሱ የተገለጠው በምን ዓይነት የተለየ መንገድ ነበር?
በዘፀ. 20፡8 ትእዛዙ የሚጀምረው “አስብ” (1962 ትርጉም) በሚል ቃል ነው።
በዘዳ. 5፡12 ደግሞ “አክብረው” የሚል ቃል ጥቅም ላይ ውሏል። አስብ ወይም
አስታውስ የተሰኘው ቃል በራሱ በትእዛዙ የሚመጣው ከቀደመው ዘግየት ብሎ
ነው (ዘዳ. 5፡15)። በዚህ ቁጥር እነዚህ ሕዝቦች ባሮች እንደነበሩ ያስታውሱ
ዘንድ ተነግሯቸዋል። ምንም እንኳ ይኸኛው ትውልድ ከባርነት ቀንበር ነጻ
ሆኖ ቢያድግም፤ በታምራዊ መንገድ አርነት ባይወጣ ኖሮ ሁሉም በባርነት
በተወለዱ ነበር። በፍጥረት ታሪክ ንቁ የነበረው ያው አምላክ በነጻነታቸውም
ንቁ ስለ መሆኑ የሰንበት ትእዛዝ ማስታወስ ነበረበት፡ “አምላክህ አግዚአብሔር
በጸናች እጅና በተዘረጋ ክንድ እንዳወጣህ አስታውስ” (ዘዳ. 5፡15)።
ከአርባ ዓመታት በኋላ በተስፋይቱ ምድር ድንበር ላይ ለሁለተኛ ጊዜ
የቆሙት እስራኤላውያን የሚገኙበት ተጨባጭ ሁኔታ--ያ የመጀመሪያው
ትውልድ ከገጠመው አሳዛኝ ውድቀት ጋር ተመሳሳይ ነው። አባቶቻቸው
ከግብፅ አምልጠው ከወጡበት ሁናቴ በተመሳሳይ እነርሱም ይህን ምድር
ለመውረስ የሚያስችል አቅም አልነበራቸውም። “በጸናች እጅ” እና “በተዘረጋ
ክንድ” የሚሠራው ይህ አምላክ ያስፈልጋቸው ነበር።
ሰንበት አንድ ተጨማሪ ትኩረት ሊወስድ ነው። እግዚአብሔር የነፃነት
አምላክ እንደመሆኑ እስራኤላውያን የሰንበት ቀን ማክበር ነበረባቸው (ዘዳ.
5፡15)።
ምንም እንኳ በዘዳ. 5 የቀረበ የተለየ ምክንያት ቢኖርም፣ ፍጥረት ከሰንበት
ትእዛዝ ሩቅ አለመሆኑ እሙን ነው። በሌላ አነጋገር እስራኤላውያን ከግብፅ
ምድር ነፃ መውጣታቸው በዘፍጥረት መጽሐፍ ከተገለጸው የፍጥረት ታሪክ
ጋር የሚመሳሰል የአዲስ ፍጥረት መነሻ ነው። እስራኤል--ነፃ እንደ ወጣ ሕዝብ
የእግዚአብሔር አዲስ ፍጥረት ናት (ኢሳ. 43፡15)።
በከፍተኛ ቁጥር ነቅሎ መውጣት (ዘፀአት)--ከኃጢአት ነፃ የመሆን ምልክት
ተደርጎ በመታየቱ የተነሣ፤ በሰንበት ማግኘት የምንችለው አርነት የፍጥረትም
ሆነ የመዋጀት ተምሳሌት ነው። በመሆኑም ሰንበት ፈጣሪያችንና ቤዛችን ወደ
ሆነው የሱስ በተጨባጭ ያመላክተናል።
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዮሐ. 11-13። የሱስ ፈጣሪያችን እና ቤዛችን
ስለመሆኑ ምን ያስተምሩናል?
ሕዝቡ የሰንበትን ቀን ይጠብቅ ዘንድ እግዚአብሔር ያዛል። መጽሐፍ ቅዱስ ሰንበትን እንዴት በትክክል መጠበቅ እንዳለብን ልዩ መግለጫዎችን ባይሰጠንም እንኳ፤ አትግደል እና አትስረቅ ከሚለው ትእዛዝ በተጓዳኝ ተሰጥቷል። በሰንበት ልንፈጥርና ልናስተዋውቅ የሚገባው ድባብ ምን መሆን አለበት? መዝ. 92፣ ኢሳ. 58፡13።
ሰንበትን መጠበቅ በአምላካዊው የፍጥረት ሥራ እና መዋጀት ሐሴት ማድረግ
እንደመሆኑ፤ በዕለቱ በጌታ ደስ የመሰኘት እንጂ የትካዜ ድባብ መኖር
የለበትም።
የሰንበትን ቀን ማስታወስ በሰባተኛው ቀን ላይ አይጀምርም። የመጀመሪያው
ሰንበት ቀን የፍጥረት ሳምንት ማሳረጊያ እንደነበር ሁሉ፤ ሰንበት ሲመጣ
ከወትሮ ሥራችን ታቅበን ዕለቱን “ቅዱስ” አድርገን መጠበቅ እንችል ዘንድ
ሳምንቱን በሙሉ ስለ ሰንበት ቀን በማሰብ አስቀድመን ማቀድ ይኖርብናል።
በሳምንቱ ውስጥ ንቁ ዝግጅት ማድረግ አስፈላጊ እንደመሆኑ፣ በተለይ ደግሞ
የመዘጋጃ ቀን (ማር. 15፡42) ወይም አርብ--ዕለቱን በጉጉት ለመጠባበቅና
ይበልጥ አስደሳች ለማድረግ ቁልፍ ነው።
ዘሌዋ. 19፡3--የሰንበትን ቀን ከመጠበቅ ጋር በተያያዘ ስለ ምን
ዓይነት አስፈላጊ ጉዳይ አጽንኦት ይሰጣል?
ሰንበትን መጠበቅ ከቤተሰቦቻችንና ከጓደኞቻችን ጋር ያለንን ግንኙነት
ማጠናከር ማለት ነው። እግዚአብሔር ከመላው ቤተሰብ ጋር በትኩረት
ለሚያስተሳስር ህብረት ጊዜ የሚሰጥ ሲሆን፤ ይህ ደግሞ በቤት ውስጥ ያሉ
ሠራተኞችንና እንስሳትንም ይጨምራል (ዘፀ. 20፡8-11)። ሰንበት እና ቤተሰብ
ሳይነጣጠሉ አብረው ይጓዛሉ።
ዕረፍት እና የቤተሰብ ጊዜ አስፈላጊ መርኅዎች እንደሆኑ ሁሉ፤ ሰንበትን
መጠበቅ የቤተ ክርስቲያናዊውን ቤተሰብ ኅብረት ያማከለ አምልኮ ላይ
ተሳታፊ መሆን ነው። የሱስ በምድር በነበረበት ወቅት በመንፈሳዊ ጉባዔዎች
ላይ ይካፈል፣ አገልግሎቶችንም ይመራ ነበር (ዘሌዋ. 23፡3፣ ሉቃ. 4፡16፣ ዕብ.
10፡25)።
ምንም እንኳ ተደጋጋሚዎቹ ሳምንታዊ ተግባሮቻችን በጥድፊያ የተሞሉ
ቢሆኑም፤ ከፈጣሪያችን ጋር ግንኙነት የምንፈጥርበት እውነተኛ የሰንበት
ዕረፍት መናፈቅ በጥልቁ የልባችን ክፍል ውስጥ አለ። ከሥራዎቻችን እና
የሥራ ዕቅዶቻችን ታቅበን ጊዜአችንን ከእግዚአብሔር ጋር ማሳለፍና ከእርሱ
ጋር ያለንን ግንኙነት ማጎልበት እንዳለብን በማስታወስ ወደ ሰንበት ዕረፍት
መግባት እንችላለን።
ከሰንበት እና ሰንበትን በመጠበቅ ከሚገኙ በረከቶች አኳያ
የእርስዎ ተሞክሮ ምን ይመስላል? ዕለቱ እንደሚገባው የተቀደሰ
ይሆን ዘንድ ምን ተጨማሪ መንገዶች መቀየስ ይችላሉ?
“ሰዎች እግዚአብሔር እምላክን በእጁ ሥራዎች ለይተው
ይገነዘቡት ዘንድ እነሆ የፍጥረቱን ኃይል መታሰቢያ ሰጣቸው። ሰንበት በፈጣሪ
ሥራዎች ውስጥ የእርሱን ክብር እንድንመለከት ይጋብዘናል… በተቀደሰው
የዕረፍት ቀን--ከሁሉም በላይ እግዚአብሔር በተፈጥሮ አማካይነት የጻፈልንን
መልዕክቶች ማጥናት ይገባናል። ወደ ተፈጥሮ ልብ እየተቃረብን በመጣን
ቁጥር ክርስቶስ የእርሱን ህልዎት በተጨባጭ ይገልጥልናል፤ ሰላሙንና ፍቅሩን
በልባችን ይነግረናል።”—Ellen G. White, Christ’s Object Lessons, pp.
25, 26.
“ጌታ እስራኤልን ከግብፅ ባርነት ነፃ ካወጣበት ወሳኝ ምክንያቶች አንዱ
ቅዱስ ሰንበቱን እንዲጠብቁ ነበር… በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ሙሴ እና
አሮን ስለ ሰንበት ቅድስና በሚያስተምሩት ትምህርት ላይ ተሐድሶ አድርገዋል።
ምክንያቱም ፈርዖን “እንዳይሠሩ እያደረጋችኋቸው ነው” (ዘፀ. 5፡5) ብሎ
አማሯቸዋል። ይህ ደግሞ ሙሴና አሮን በግብፅ ስለ ሰንበት ቅድስና ተሐድሶ
መጀመራቸውን ያመለክታል።
“ሰንበትን ያከበሩት ከግብፅ ባርነት የመውጣታቸው መታሰቢያ እንዲሆን
አልነበረም። የፍጥረት ሳምንትን በማስታወስ የሚከበረው ሰንበት፤
በግብፅ ከነበረው ኃይማኖታዊ ጭቆና ነፃ ወጥቶ ዕለቱን በደስታ ማክበርን
የሚያካትት መሆኑ ጉዳዩን አስቸጋሪ አድርጎት ነበር። በተመሳሳይ--ከባርነት
ነፃ መውጣታቸው ለድኾች፣ ለተጨቆኑ፣ አባት ለሌላቸው እና ለመበለቶች
የርኅራኄ ስሜት በልባቸው እንዲቀጣጠል አድርጓል።”—Appendix note in
Ellen G. White, From Eternity Past, p. 549.
፡
1.አንዳንድ ክርስቲያኖች፣ ሰባተኛ ቀን የዳግም ምጽአቱን
ተጠባባቂዎች ጨምሮ--የዝግመተ ለውጥን ንድፈ ሐሳብ እንደ
አሳማኝ የፍጥረት ማብራሪያ አድርገው ይቆጥራሉ። የዝግመተ
ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ እና የሰባተኛው ቀን ዳግም ምጽአቱ
ተጠባባቂዎች አስተምህሮ እርስ በርስ የማይጣጣሙ መሆናቸውን
ሰንበት እንዴት ያሳያል?
2.በሳምንት አንድ የዕረፍት ቀን እስካለን ድረስ ዕለቱ ምንም
ይሁን ምን--ለውጥ የለውም ለሚለው መከራከሪያ እርስዎ ምን
ይላሉ? ወይም በሌላ በኩል--የሱስ የሰንበት ዕረፍታችን ስለ ሆነ
እንደ ዕረፍታችን የምንጠብቀው ቀን አያስፈልግም ለሚለው
አነጋገር ምላሽዎ ምንድን ነው?
3.ሰንበትን ቅዱስ አድርጎ ማክበር የነፃነት እና አርነት የመውጣት
ማስታወሻ ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው? እንደ ጥብቅ እና ደረቅ
ሕግ አድርጎ ከመመልከት መቆጠብ የምንችለው እንዴት ነው?
4. አንዳንዶች ሰባተኛውን ቀን ሰንበት መጠበቅ በሥራ ወደ
ሰማይ ለመሄድ እንደ መሞከር ነው ብለው ሲናገሩ ይደመጣሉ።
ይሁን እንጂ በሰባተኛው ቀን በማረፍ ወደ ሰማይ ለመሄድ ጥረት
እያደረግን ነው ብሎ የመናገር አመክንዮ ምንድን ነው?