የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

በክርስቶስ ማረፍ


3ኛ ሩብ ዓመት 2021

ከነሐሴ 22- 28

10ኛ ትምህርት

Aug 28–Sep 3




የሰንበት ዕረፍት



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ዘፍ. 1:26-27፣ ዘፍ. 9:6፣ 2ጴጥ. 2:19፣ ሮሜ 6:1–7፣ ዘፀ. 19:6፣ ዮሐ. 5:7–16።


የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ “ሥራ የምትሠሩበት ስድስት ቀን አላችሁ፤ ሰባተኛው ቀን ግን የዕረፍት ሰንበት፣ የተቀደሰ ጉባኤ ዕለት ነው። የእግዚአብሔር ሰንበት ስለ ሆነ፣ በምትኖሩበት ስፍራ ሁሉ ምንም ዐይነት ሥራ አትሥሩበት” ዘሌዋ. 23፡3)።

ሰ ባተኛው ቀን ሰንበት እንዳይከበር የሚከላከሉ የተለያዩ ዓይነት ክርክሮችን እንሰማለን--አይደል? የሱስ የሰንበትን ቀን ወደ እሁድ ቀይሯል ከሚለው ጀምሮ ሰንበትን አስወግዷል፣ ጳውሎስ ወይም ሐዋርያት ስለ ትንሣኤው ክብር የሰንበትን ቀን በእሁድ ተክተዋል የሚሉና የመሳሰሉ ሀሳቦችን እንሰማለን። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የሚቀርቡ አንዳንድ የመከራከሪያ ነጥቦች ይበልጥ የረቀቁ ሆነዋል። ለምሳሌ፡ የሱስ የሰንበት ዕረፍታችን በመሆኑ ቀኑን ወይም ማንኛውንም ቀን ቅዱስ አድርገን መጠበቅ አያስፈልገንም--የሚሉ ሀሳቦች ይደመጣሉ። እናም በሰባተኛው ቀን በማረፍ በሆነ መንገድ ወደ ሰማይ ለመሄድ እደምንጥር ተደርጎ የሚቀርብ ዕንግዳ ሙግት ሁሌም ይኖራል።

በሌላ በኩል አንዳንድ ክርስቲያኖች በዕረፍት ጽንሰ ሀሳብ ይበልጥ ፍላጎት እያደረባቸው ይገኛል። ዕለቱ እሁድ ወይም የትኛውም ቀን ቢሆን ችግር የለውም ብለው ቢከራከሩም፤ መጽሐፍ ቅዱሳዊውን የዕረፍት ሀሳብ አስፈላጊነት ተቀብለዋል። እርግጥ ነው፤ እንደ ሰባተኛ ቀን የዳግም ምጽአቱ ተጠባባቂነታችን የእግዚአብሔርን ሕግ ዘለቄታዊነት ማስተዋላችንና በተጻፈው መሠረት አራተኛውን ሕግ መታዘዛችን--ሌሎቹንም ሕጎች ማለትም አምስተኛውን፣ ስድስተኛውን፣ የመጀመሪያውን ወዘተ ካላካተተ ብቻውን ለሰማያዊው መንገዳችን ፋይዳ አይኖረውም። በዚህ ሳምንት እግዚአብሔር በሰንበት ትዕዛዝ ስለ ሰጠን ዕረፍት እና በአስፈላጊነቱ ዙሪያ ጠለቅ ብለን እንመለከታለን።

ነሐሴ 23
Aug 29

ሰንበት እና ፍጥረት


ከአሥርቱ ትእዛዛት ውስጥ “አስብ” ወይም አስታውስ (እንግሊዝኛው ትርጉም Remember ማለቱን ልብ ይሏል) በሚል ግስ የሚጀምረው አራተኛው ብቻ ነው። “መስረቅ እንደሌለብህ አስታውስ” ወይም “መመኘት እንደሌለብህ አስታውስ” አይልም። ይልቁንም “የሰንበትን ቀን አስብ…” በሚል የቀረበው አራተኛው ትእዛዝ ብቻ ነው። የማሰብ ወይም የማስታወስ ጽንሰ ሀሳብ ቀደም ያለ ታሪክ መኖሩን ያመለክታል። ልናስታውሰው የሚገባ ቀደም ሲል የተከናወነ አንድ ነገር መኖሩን ያስገነዝባል። ስናስታውስ፣ ካለፉ ክስተቶች ጋር ግንኙነት እንፈጥራለን፣ እናም “የሰንበትን ቀን ትቀድሰው ዘንድ አስብ” (1962 ትርጉም) ሲል ከራሱ የፍጥረት ሳምንት ጋር ቀጥተኛ ትይዩ መስመር ያሰምራል።

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፍ. 1፡26-27፣ ዘፍ. 9፡6። እኛ የሰው ልጆች ምን ያህል ልዩ እንደሆን እና ከሌሎቹ የእግዚአብሔር ምድራዊ ፍጡራን ምን ያህል የተለየ እንደሆን አስመልክቶ ምን ያስተምሩናል? በተጨማሪ ይህን ልዩነት መረዳታችን በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?



ፍጥረትን ስናስብ ከሌሎቹ አፈጣጠር በተለየ በእግዚአብሔር መልክ መፈጠራችንን እናስታውሳለን። ከአንዳንድ እንስሳት ጋር የቱንም ያህል በራሂ (ዲ.ኤን.ኤ.) ልንጋራ ብንችልም--እንደ ሰው፣ በዚህች ፕላኔት ከማንኛውም ሌላ ፍጡር እጅግ የተለየን መሆናችን ግልጽ ነው። እንዲሁም በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት ካገኙ አፈ ታሪኮች ወይም ንድፈ ሀሳቦች በተቃራኒ እኛ የላቁ ዝንጀሮዎች ወይም በዝግመተ ለውጥ የበለጸጉ ስሪቶች አይደለንም።

በእግዚአብሔር አምሳል የተሠራን ሰዎች እንደመሆናችን መጠን፣ እኛ በዚህ ዓለም እግዚአብሔር ከፈጠራቸው ሁሉ ልዩ ነን። የፍጥረት ታሪክ ከፍጥረት ጋር ያስታውሰናል? ዘፍ. 2:15፣19 ያለንን ግንኙነት እንዴት



እግዚአብሔር ዓለማችንንም እንደፈጠረ መገንዘባችን ለፍጥረት ያለንን ሃላፊነት ያስታውሰናል። በፍጥረት ላይ “ሥልጣን እንዲኖረን” ተጠርተናል። ሥልጣን ተሰጠን ማለት ኃላፊነታችንን ያለ አግባብ ጥቅም ላይ ማዋል ማለት አይደለም። ይልቁንም እንደ እግዚአብሔር ወኪልነታችን በኃላፊነት መግዛት ይጠበቅብናል። እግዚአብሔር ከፍጥረታዊው ዓለም ጋር የሚያደርገው ዓይነት መስተጋብር መፍጠር አለብን።

ኃጢአት ሁሉንም ነገር ማመሳቀሉ የማይታበል ሃቅ ቢሆንም፤ ነገር ግን ይህች ምድር ዛሬም የእግዚአብሔር ፍጥረት በመሆኗ እንድንበዘብዛት መብት የሚሰጠን አንዳችም ኃይል የለም--በተለይ አዘውትሮ የሚስተዋለውን፣ ሰብዓዊ ፍጡራንን የመጉዳት ነገር። ሰንበት የእግዚአብሔር ፈጣሪነት መታሰቢያ ከመሆኑ ባሻገር፤ መልካም የአካባቢአችን አስተዳሪዎች የመሆን ፍላጎታችንን የበለጠ እንድንገነዘብ፤ ዕለቱን ማክበር በምን መንገዶች ሊረዳን ይችላል?

ነሐሴ 24
Aug 30

ነጻነትን ማክበር


ቀደም ብለን እንደተመለከትነው የሰንበት አንደምታ ከፍጥረት ቀናት ባሻገር ነው። ስለ ዐሥርቱ ትእዛዛት ለሁለተኛ ጊዜ የምንሰማው ሙሴ የእስራኤልን የ40 ዓመታት የምድረ በዳ ጉዞ በሚገመግምበት ወቅት ነው። በዚህ ወቅት ሰንበትን ቅዱስ አድርጎ መጠበቅ ተገቢ የሆነበትን ምክንያት የሚያስተዋውቀው ዓረፍተ ነገር--ፍጥረትን ሳይሆን ከግብፅ ባርነትና ግዞት ነፃ መውጣታቸውን አስመልክቶ ነው (ዘዳ. 5፡12-15)። ምንም እንኳ ዛሬ በግብፅ ባርነት ስር እየኖርን ባይሆንም፤ ነገር ግን ሁላችንም በተለያዩ መንገዶች ሌላኛውን ዓይነት ጨቋኝ ባርነት ልንጋፈጥ እንችላለን። ዛሬ እያጋጠሙን ያሉ ለየት ያለ ገጽታ ያላቸው የባርነት ዓይነቶች የትኞቹ ናቸው--ዘፍ. 4:7፣ ዕብ. 12:1፣ 2ጴጥ. 2:19?



ሰንበት በግዞት ከሚያቆዩን ነገሮች ሁሉ ባሻገር በነፃነታችን ሐሴት የምናደርግበት ዕለት ነው። በሰንበት--በገዛ ብርታታችን ሳይሆን ነገር ግን በእምነት በተሰጠን በእግዚአብሔር ኃይል ከኃጢአት ነፃነት እንዳለ እንገነዘባለን። እንዲሁም ይህ በራሳችን ያገኘነው ነፃነት አለመሆኑን እንረዳለን። የእስራኤላውያን የበኩር ልጆች የዳኑት ከግብፅ ከመውጣታቸው በፊት ምሽት ላይ በበራቸው ጉበን እና መቃን በቀቡት የበግ ጠቦት ደም ነበር (ዘፀ. 12)። እኛ በበጉ ደም የዳንን-በተመሳሳይ በክርስቶስ የሱስ ባገኘነው ነጻነት እንድንመላለስ ተጠርተናል። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ሮሜ 6፡1-7። ጳውሎስ በሰንበት ከተሰጠን ጋር ተዛምዶ ሊኖረው ስለሚችል ምን ነገር እየተናገረ ነው?



“በግብፅ ሳለህ አንተም ባሪያ እንደ ነበርህ፣ ከዚያም አምላክህ እግዚአብሔር በጸናች እጅና በተዘረጋ ክንድ እንዳወጣህ አስታውስ፤ ስለዚህ አምላክህ እግዚአብሔር የሰንበትን ቀን ታከብረው ዘንድ አዘዘህ።” (ዘዳ. 5፡15)። በጥቅሱ እንደተመለከተው እነዚህ ሕዝቦች የዳኑት እግዚአብሔር ስለ እነርሱ በሠራው ሥራና በገለጠው ኃይሉ እንደሆነ ተደጋጋሚ ማሳሰቢያ ተሰጥቷቸዋል። እንደ ክርስቲያን--ከኃጢአት የዳንነው ክርስቶስ ለእኛ በሠራው ሥራና በእርሱ በተገለጠው ኃይል ብቻ መሆኑን ምን ያህል መገንዘብ ይኖርብን ይሆን? ይህ ትዕዛዝ እግዚአብሔር በብርቱ ክንዱ ለእኛ ባስገኘልን መዳን ማረፍ እንዳለብን ይነግረናል።

የእግዚአብሔርን ፈጣሪነት በማስታወስ በእኛ ውስጥ እንዲሠራ የምንታመንና የምንፈቅድለት ከሆነ፤ አሁን ዳግመኛ ሊፈጥረንና ከኃጢአት እሥራት ነጻ ሊያወጣን ይችላል። ከኃጢአት ባርነት ጋር በተያያዘ ያሎት ተሞክሮ ምን ይመስላል? ከዚያ ባርነት አርነት ስለ መውጣታችን በየሱስ ላገኘነው ተስፋ ዋጋ መስጠትን መማር የምንችለው እንዴት ነው?

ነሐሴ 25
Aug 31

በደጅዎ ያለ እንግዳ


ጥቅሱን ያንብቡ፡ ዘፀ. 19፡6። የጥንቷ እስራኤል ትገኝበት ስለነበረው ሁናቴ ምን ይነግረናል? (1ጴጥ. 2:9)



እስራኤላውያን የእግዚአብሔር የቃል ኪዳኑ ህዝቦች ይሆኑ ዘንድ ከግብጽ ተጠርተው ነበር። ሕዝቡ ለእግዚአብሔር ታማኝ እንደሆነ ቢጸና፤ ወንጌል ለዓለም በተሰራጨ ነበር። የእግዚአብሔር ልዩ ጥንቃቄና አሳቢነት ያልተለያቸው፣ ልዩ መብትና ጥቅም የተቸራቸው እና የዚያኑ ያህል በዓይነታቸው የተለዩ ኃላፊነቶች የተሰጣቸው ሕዝቦች መሆናቸው አያጠያይቅም። ጥቅሱን ያንብቡ፡ ዘፀ. 23፡12። እየተካሄደ የነበረው ሌላው ነገር ምንድን ነው? መልእክቱ ከራሳቸው ከእስራኤላውያን በተጨማሪ እግዚአብሔር ሌሎችን እንዴት ይመለከት እንደነበር አስመልክቶ ጥቅሱ ምን ያስተምረናል?



ብዙዎች የሰንበትን ሁሉን አካታች ባህሪ ይስታሉ። በጣም የተለመደው ስህተት በዘፍጥረት መጽሐፍ የመጀመሪያዎቹ ሁለት ምዕራፎች ላይ የሚፈጸመው ሲሆን፤ ይኸውም ለአይሁዳውያን ብቻ ተደርጎ የመታሰቡ ጉዳይ ነው። የሁሉም ሰው ፈጣሪ እግዚአብሔር አምላክ እንደመሆኑ፤ ሁሉም የሰንበትን ቀን ማስታወስ ይኖርበታል። ምንም እንኳ ሰንበት ለእኛ ስለሚወክለው ነገር ዘወትር ማሰብ ቢኖርብንም፣ ስለ ሌሎችም ምን ሊነግረን እንደሚገባ በተጨማሪ ማስታወስ ይኖርብናል።

ከፈጣሪያችንና ከቤዛችን ጋር የምናደርገው ዕረፍትና ተዛምዶ--ሌሎችን በአዲስ ዓይን እንድንመለከት፣ እኛን በፈጠረው አምላክ የተፈጠሩ፣ እኛን በሚወደንና በሞተልን ያው አምላክ የተወደዱና የሞተላቸው ፍጥረታት አድርገን እንድንመለከታቸው አጥብቆ ይገፋፋናል። ቀደም ብለን እንደተመለከትነው (ዘፀ. 20፡10፣ ዘዳ. 5፡14) አገልጋዮች፣ እንግዶች፣ እንስሶችም እንኳ ሳይቀሩ የሰንበት ዕረፍት ሊሰጣቸው የተገባ ነው።

ለእስራኤል የተሰጡት ቃል ኪዳኖች ተካፋይ ያልሆነ በደጃፋቸው ያለ እንግዳ እንኳም ቢሆን በሰንበት ዕረፍት ሐሴት ሊያደርግ እንደሚገባ አስመልክቶ ብዙ ይላል። የሰው ልጆች--ሌላው ቀርቶ እንስሳት እንኳ ሳይቀሩ ፈጽሞ ሊበዘበዙ፣ ሊበደሉና ባልተገባ መንገድ መጠቀሚያ ሊሆኑ አይገባም። ዕብራውያን ሕዝቦች (እኛን ጨምሮ) ከሌሎች ሕዝቦች ጋር ምን ያህል የጋራ ስብዕና እንዳላቸው አስመልክቶ በየሳምንቱ ብርቱ በሆነ መንገድ መገንዘብ ነበረባቸው። ምንም እንኳ ሌሎች የማያገኙትን በረከትና መብት ብንጎናጸፍም፣ አሁንም የአንድ ሰብዓዊ ቤተሰብ አባል መሆናችንን በማስታወስ ለሌሎች ተገቢውን አክብሮት ልንሰጥ ይገባል።

የእርስዎ ሰንበትን መጠበቅ--ሰንበትን ለማያከብሩ እንዴት በረከት መሆን ይችላል? ይኸውም ሰንበትን ለሌሎች እንደ መመስከሪያ መሣሪያ ሊጠቀሙ የሚችሉት እንዴት ነው?

ነሐሴ 26
Sep 1

ሌሎችን ማገልገል ለአምላካዊው ሰንበት ክብር ያመጣል


በአዲስ ኪዳን ዓለም የኃይማኖት መሪዎች ሰንበትን ከመጠበቅ ጋር በተጎዳኘ አያሌ ሕግጋት ነበሯቸው። ሰንበትን ቅዱስ አድርጎ ለመጠበቅ የሚረዱ በደርዘን የሚቆጠሩ ክልከላና ደንቦች ነበሯቸው። በዚህም ማንኛውንም ነገር ለማሰር ወይም ላለማሰር የሚደረግ ሙከራ፣ ሁለት ክሮችን መለያየት፣ እሳት ማጥፋት፣ በግል ግዛትና በሕዝብ ክልል መሃል ዕቃ ማጓጓዝ ወይም በሕዝብ ክልል ውስጥ ዕቃን ከተወሰነ ርቀት በላይ ማጓጓዝ የተከለከለ ነበር። በጥቅሱ እንደ ተመለከተው በየሱስ ላይ ምን የሚል ክስ ነበር የቀረበበት--በዮሐ. 5፡7-16?



የአይሁድ መሪዎች የሱስ ያደረገውን ድንቅ ታምራት እና በደዌ ላይ ያጎናጸፈውን ነፃነት ከምንም ሳይቆጥሩ--ነገር ግን የተፈወሰው ሰው በሰንበት ቀን አልጋውን በአደባባይ ተሸክሞ መሄዱ አስጨነቃቸው። መሪዎቹ “የሰንበት ጌታ” (ማር. 2፡ 28) ይህን ልዩ ቀን እንዴት ጥቅም ላይ እንዳዋለው ከማየት ይልቅ የራሳቸውን ደንብና ሥርዓት ጠብቀው የመኖር ዓላማ ነበራቸው። እኛም በራሳችን መንገድና ዐውድ ተመሳሳይ ስህተቶች እንዳንሠራ መጠንቀቅ ይኖርብናል። ኢሳ. 58፡2-3 እግዚአብሔር በሰንበት አጠባበቅ ዙሪያ ስላለው እቅድ ምን ይለናል?



እግዚአብሔር የምዕመኑን ባዶ አምልኮ ወይም ዝምታ አይፈልግም። ሕዝቦቹ ከሌሎች ጋር--በተለይ ከተገፉ፣ ከተገለሉና ከተጨቆኑ ጋር ሲተባበሩ ማየት ይፈልጋል። ኢሳይያስ ይህን ግልጽ አድርጎ ያስቀምጣል፡ “ ‘እግሮችህ ሰንበትን እንዳይሽሩ ብታሳርፍ፣ በተቀደሰው ቀኔ የልብህን ባታደርግ፣ ሰንበትን ደስታ፣ የእግዚአብሔርን ቅዱስ ቀን የተከበረ ብለህ ብትጠራው፣ የገዛ መንገድህን ከመሄድ፣ እንደ ፈቃድህ ከማድረግና ከከንቱ ንግግር ብትቆጠብ፣ በዚያን ጊዜ በእግዚአብሔር ደስ ይልሃል፣ በምድር ከፍታዎች ላይ እንድትጋልብና የአባትህን የያዕቆብን ርስት ጠግበህ እንድትበላ አደርግሃለሁ።’ ” (ኢሳ. 58፡ 13-14)።

በዕለቱ የገዛ ልባችንን ፍላጎትን ማድረግ ሰንበትን ከመሻር ጋር እኩል ነው። ሰብዓዊ አጀንዳዎች የአምላካዊው ሰንበት ዓላማ ተስማሚ ክፍል አይደሉም። ይልቁንም የሚታገሉ፣ በምርኮ የወደቁ፣ የተራቡ፣ የተራቆቱ፣ በጨለማ ውስጥ የሚጓዙና ስማቸውን እንኳ ማንም የማያስታውሰውን ሰብዓዊ ወገኖች እንድንመለከት ተጋብዘናል። ሰንበት ከማንኛውም የሳምንቱ ቀን በላይ ከገዛ ፍላጎታችንና ራስ ወዳድነታችን አውጥቶ ሌሎች ስለሚያሹአቸው መሠረታዊ ዕጦቶች እንድናስብ ሊያደርገን ይገባል።

ነሐሴ 27
Sep 2

የእግዚአብሔር የመሆናችን ምልክት


በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት እንግሊዝ የጀርመን ጦር በቅርቡ እንደሚወራት ትጠብቅ ነበር። ይህችን ዙሪያ ገባዋን በባሕር የተከበበች አገር በተቻለ መጠን ለመከላከል ዝግጅት ተደርጓል። በባህር ዳርቻዎች ተጨማሪ ምሽጎች ተቆፍረዋል። መንገዶች የጠላትን ዓላማ በፍጥነት ለማሳካት የሚያስችሉ እንደመሆናቸው ወሳኝ የሚባሉ መውጫና መግቢያዎች ተዘጉ። ከዚያም የእንግሊዝ ባለ ሥልጣናት አንድ እንግዳ ነገር አደረጉ። የጠላትን ፍጥነት ለማጓተትና ግራ ለማጋባት ሲባል የባቡር ሐዲድ ምልክቶች ተወገዱ፤ የመንገድ ምልክቶችም ተነሡ።

ሰንበት የምን ምልክት ነው? ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፀ. 31፡13፣ 16-17። እኛ በእግዚአብሔር ሕግ ዘላለማዊነት የምናምን በዚህ ስፍራ የተነገረውን ለራሳችን ተግባራዊ ማድረግ የምንችለው በየትኞቹ መንገዶች ነው?



ምንም እንኳ እነዚህ ቃላት በተለይ ለጥንታዊቷ እስራኤል የተነገሩ ቢሆንም የክርስቶስ የሆንን እኛ “የአብርሃም ዘር… እንደ ተስፋውም ቃል ወራሾች” (ገላ. 3፡29) በመሆናችን ዛሬም ሰንበት በእግዚአብሔርና በሕዝቡ መካከል ምልክት ሆኖ ቀርቷል። ሰንበት የእግዚአብሔር ዘላለማዊ ቃል ኪዳን ምልክት መሆኑን ዘፀ. 31 ያመላክተናል (ዘፀ. 31፡16-17)። ይህ ምልክት ፈጣሪያችንን፣ ቤዛችንንና የሚቀድሰንን አምላክ “እንድናወቅ” ይረዳናል። የመዘንጋት አዝማሚያ ስላለን ይህ ዕለት በየሰባት ቀን ብቅ ብሎ እንደ ባንዲራ እየተውለበለበ እንድናስታውስ ይረዳናል።

የእግዚአብሔር ሰንበት--የቀደመ አመጣጣችንን፣ ነፃነታችንን፣ መዳረሻችንን ብሎም ለተጣሉና ለተገፉ ያለንን ኃላፊነት ሰርክ የሚያሳስበን ነው። ሰንበት በጣም አስፈላጊ ከመሆኑ የተነሣ እኛ ወደዚህ ዕለት በመሄድ ፋንታ ያለ ልዩነት በየሳምንቱ ወደ አኛ በመምጣት፣ እኛ ማን እንደሆንን፣ ማን እንደፈጠረን፣ የፈጠረን አምላክ ምን እያደረገልን እንደሆነ፣ እንዲሁም አዲስ ሰማያትና ምድር ካዘጋጀ በኋላ በስተመጨረሻ ምን እንደሚያደርግልን የሚዘክር ዘላለማዊ አስተዋሽ ነው።

ፈጣሪ እና ቤዛ በሆነው አምላክና በአፈንጋጩ ሰው መሃል ለተቀመጠው የማዳን ግንኙነት--የአምላካዊው ኪዳን ሸሪክ የሆኑት የሰው ልጆች አጽንኦት ይሰጡ ዘንድ ቅዱስ የሆነው እግዚአብሔር ግብዣ ያቀርባል። በየሳምንቱ ከእግዚአብሔር በሚመጣ ኃይልና ሥልጣን በክርስቶስ የሱስ በነጻ ወደተሰጠን ዕረፍት እንድንገባ ታዝዘናል፡ “የእምነታችን ጀማሪና ፍጹም አድራጊ የሆነው ኢየሱስ.. በፊቱ ስላለው ደስታ መስቀሉን ታገሠ” (ዕብ. 12፡2)።

ነሐሴ 28
Sep 3


ተጨማሪ ሀሳብ


“ሳምንቱን ሙሉ ሰንበትን በልባችን እንደ ያዝን በትእዛዙ መሠረት ለመጠበቅ ዝግጅት ማድረግ ይኖርብናል። ሆኖም ሰንበትን የምናከብረው ከሕጋዊ ጉዳይ ጋር አቆራኝተን አይደለም።”—Ellen G. White, Testimonies for the Church, vol. 6, p. 353. “መላው ሰማይ ሰንበትን የሚጠብቅ ሲሆን ይኸውም ታካች ባልሆነና ምንም በማይደረግበት ሁኔታ ነው። ዕለቱ ከእግዚአብሔር አምላካችንና ከክርስቶስ አዳኛች ጋር የምንገናኝበት እንደ መሆኑ እያንዳንዱ ጉልበት ንቁ መሆን የለበትም? በእምነት ልናየው የምንችለው እርሱ፤ እያንዳንዱን ነፍስ ለማደስና ለመባረክ ይናፍቃል።”—Page 362.

“እግዚአብሔር ከሌላ ቀን ይልቅ በሰንበት ቀን ብዙ ነገር እንዲደረግ ይጠይቃል። የእርሱ ወገኖች የሆኑ ሁሉ በሰንበት ዕለት የዘወትር ሥራቸውን ትተው ሲጸልዩና ስለ መንፈሳዊ ነገር ሲያሰላስሉ ይውላሉ። ከሌሎች ቀኖች ይልቅ በሰንበት ቀን አምላካቸው የበለጠ በረከት እንዲሰጣቸው ይለምኑታል። ልዩ አስተያየት እንዲያደርግላቸውም ይማጸናሉ። ልዩ በረከት ይሻሉ። እግዚአብሔርም እነዚህን በረከቶች ለመለገስ ሰንበት እስኪያልፍ አይጠብቅም። ሰማያዊ ሥራ ምን ጊዜም አይቋረጥም፤ ሰዎችም ደግ ሥራ መሥራትና ማቋረጥ የለባቸውም። ሰንበት የቦዘኔነት ቀን እንዲሆን አልታቀደም። በአምላክ የዕረፍት ቀን ዓለማዊ ሥራ እንዳይሠራ ሕጉ ይከለክላል። ለየዕለት ኑሮ የሚካሔድ ሥራ ሁሉ መቆም አለበት። በዚያ ቀን አርፎ እንደባረከው ሁሉ እንዲሁም ሰው የየዕለት ተግባሩን አቋርጦ የተቀደሱትን የሰንበት ሰዓቶች ለጤናማ ዕረፍት፤ ለስግደትና ለተቀደሰ ሥራ ሊያውላቸው ይገባል። ክርስቶስ በሽተኛውን በመፈወስ ያከናወነው ሥራ ሕግን አይቃረንም። ይልቅስ ሰንበትን አከበረ።” የዘመናት ምኞት ገጽ 196።


የመወያያ ጥያቄዎች



፡ 1.የአካባቢ ጥበቃ ጉዳይ በብዙ አገሮች ከፍተኛ የፖለቲካ ክርክር የሚነሣበት ርዕስ ሆኗል። እኛ እንደ ሰባተኛ ቀን የዳግም ምጽአቱ ተጠባባቂነታችን ከፖለቲካ አጀንዳ ውጪ ጥሩ የተፈጥሮ መጋቢዎች መሆን የምንችለው እንዴት ነው?

2.አገልግሎት የሚጀምረው በአእምሮ ውስጥ ነው። በዙሪያችን ያሉትን (ቤተሰቦቻችንን፣ ቤተ ክርስቲያናችንንና ማኅበረሰባችንን) ከልባችን የማገልገል አስተሳሰብ እንዴት ማጎልበት እንችላለን? ሰንበት ይህን ለማድረግ የበለጠ ዕድል የሚሰጠን እንዴት ነው?

3.በእያንዳንዱ ሰንበት የሰው ልጅ ሁሉ በእግዚአብሔር የተፈጠረ መሆኑን እናስታውሳለን። ዕለቱ ሰዎችን በእግዚአብሔር ዓይን እንድንመለከት ይረዳናል። ሰንበት በእግዚአብሔር አምሳል መፈጠር እና የፍቅሩ አካል መሆንን አስመልክቶ--የዘር፣ የጎሣ፣ የማኅበራዊና ኤኮኖሚያዊ ደረጃ፣ የፆታ ልዩነቶች ፋይዳ ቢስ መሆናቸውን እንድናስታውስ እንዴት ሊረዳን ይገባል?




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA union SSL