የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

በክርስቶስ ማረፍ


3ኛ ሩብ ዓመት 2021

ከነሐሴ 29 - ጳግሜ 5

11ኛ ትምህርት

Sep 4–Sep 10




ከፍ ያለውን መናፈቅ



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ 1ቆሮ. 10:1–11፣ ዘሌዋ. 4:32–35፣ ዮሐ. 1:29፣ ዕብ. 4:1–11፣ መዝ. 95:8–11።


የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ “እነርሱ ክፉ እንደ ተመኙ እኛም ደግሞ እንዳንመኝ እነዚህ ነገሮች ምሳሌ ሆነውልናል” (1ቆሮ. 10፡6)::

በ ኒው ዮርክ፣ ዩናይትድ ስቴትስ የሚገኘው የኩዊንስ የሥነ ጥበብ ሙዚየም፣ የኒው ዮርክን ሕንፃዎች በሙሉ የሚያሳይ የዓለማችን ትልቁ የሥነ ሕንፃ ሞዴል ነው። ይህ ወደ 870 ካሬ ሜትር የሚጠጋ ስፋት ላይ ያረፈ የሥነ ሕንፃ ሞዴል በመጀመሪያ የተጠናቀቀው በ1964 ሲሆን ፕሮጀክቱን ለማጠናቀቅ ከሦስት ዓመት በላይ ወስዷል፤ 100 ባለሙያዎችም ተሳትፈዋል። እስከ 1990ዎቹ ድረስ እየተሻሻለ የተሠራ ቢሆንም፤ የጎርጎሮሳውያኑን 2021 የከተማ ገጽታ ግን አይያንጸባርቅም።

በመጨረሻ፣ ይህ የሥነ ሕንፃ ሞዴል የዚያ የረቀቀውና የተወሳሰበው አካል-ቅጂ፣ ምሳሌና ማሳያ ከመሆን አያልፍም። እንደ እውነቱ ከሆነ ሁሉም ሞዴሎች በዚህ መልኩ ይቀርባሉ። ሞዴሎች ዋናው አካል አይደሉም። ሆኖም የዋናው አካል ምሳሌ ሆነው ያገለግላሉ። አንድ ሞዴል የመጀመሪያውን ሥራ ፍሬ ነገር እንድናስተውል ቢረዳንም ሊተካው ግን ፈጽሞ አይችልም። ይልቁንም የመጀመሪያው ሥራ ምን እንደ ሆነ ሰዎች በተሻለ እንዲገነዘቡ ለመርዳት የተዘጋጀ ነው። ቅዱሳት መጻሕፍት በራሳቸው ወደ ትላልቅና ሰማያዊ እውነታዎች የሚያመላክቱ ትናንሽ ማስተማሪያ ምሳሌዎች ናቸው። ዕብ. 4 ከመጽሐፍ ቅዱስ የዕረፍት ጥያቄ ጋር ባለው ተዛምዶ ከእነዚህ እውነታዎች መሃል አንዱን እንድናውቅ ይረዳናል።

ነሐሴ 30
Sep 5

ከግብጽ ባርነት እንዲያመልጡ ያስቻለው የሙሴ ጥምቀት


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ 1ቆሮ. 10፡1-11። ጳውሎስ “ምሳሌዎችን” ሲጠቅስ በቆሮንቶስ ለነበሩ አንባቢዎቹ ማስተላለፍ የፈለገው መልእክት ምን ነበር?



በ 1ቆሮ.10፡6--“ምሳሌ” በሚል የቀረበው ቃል መጀመሪያ የተጻፈበት ግሪክኛ ታይፖስ ነው። ለእንግሊዝኛው “ታይፕ” መሠረቱ ይኸው የግሪክ ቃል ነው። ዓይነት ወይም ምሳሌ--በፍጹም ዋናውን አካል ሊሆን ወይም ሊወክል አይችልም። ይልቁንም የሌላ ነገር ምሳሌ ነው። ዕብ. 8፡5 ለእንዲህ ዓይነቱ ግንኙነት ጥሩ ምሳሌ ይሰጠናል፡ “እነርሱ (የብሉይ ኪዳን ቤተ መቅደስ አገልጋይ ካህናት) ያገለገሉት በሰማይ ላለችው መቅደስ ምሳሌና ጥላ በሆነችው ውስጥ ነው፤ ሙሴ ድንኳኒቱን ለመሥራት በተነሣ ጊዜ፣ ‘በተራራው ላይ በተገለጠልህ ምሳሌ መሠረት ሁሉን ነገር እንድታደርግ ተጠንቀቅ’ የሚል ትእዛዝ የተሰጠው በዚህ ምክንያት ነበር።”

በዕብራውያን መጽሐፍ ውስጥ የሚገኘው ይህ ጥቅስ በሰማያዊና ምድራዊ እውነታዎች መካከል ያለውን ቀጥተኛ ግንኙነት ካጎላ በኋላ፣ በመቀጠል ሙሴ በተራራው ላይ ባየው ምሳሌ መሠረት፤ በምድረ በዳ እግዚአብሔር መቅደስ እንዲሠራ የነገረውን ከዘፀ. 25፡9 በመጥቀስ ያስቀምጣል። ዋናው ነጥብ ምድራዊው መቅደስ ከሁሉም ዓይነት ኃይማኖታዊ ሥርዓቶችና አሠራሮቹ ጋር--በሊቀ ካህናችን የሱስ በሰማይ እየተከናወነ ላለው “ምሳሌ” መሆኑ ነው። ይህን በአእምሮአችን ስንይዝ፣ ጳውሎስ በ 1ቆሮ. 10 ስለ ምን እየተናገረ እንዳለ በተሻለ መንገድ መረዳት እንችላለን። በእነዚህ ቁጥሮች፣ የእግዚአብሔር ሕዝቦች ወደ ተስፋይቱ ምድር ያደርጉ በነበረው ጉዞ አንዳንድ ቁልፍ ተሞክሮዎችን ዳግመኛ ይቃኛል። “አባቶቻችን” የሚለው ቃል የሚያመለክተው--ግብፅን ለቅቀው የወጡትን፣ ከደመናው በታች የነበሩትን፣ በባህር ውስጥ ያለፉትን እና ከባርነት ነጻ በሆነ አዲስ ሕይወት የተጠመቁትን አይሁድ ወላጆቻቸውን ነው።

ጳውሎስ እነዚህን የምድረ በዳ ጉዞ አስፈላጊ ምድብ ስፍራዎች እንደ ግለሰብ ጥምቀት ምሳሌ ይመለከታቸዋል። በጳውሎስ አመክንዮአዊ ዱካ ለ “መንፈሳዊ ምግብ” ተሰጠው ማጣቀሻ መናን ያመላክታል ተብሎ ይታሰባል (ዘፀ. 16፡ 31-35)። እስራኤላውያን ከዐለት ከፈለቀ ውሃ፣ ይኸውም ጳውሎስ ክርስቶስ ብሎ ከጠቀሰው ጠጡ (1ቆሮ. 10፡4)። ለምሳሌ የሱስን “የሕይወት እንጀራ” (ዮሐ. 6፡48)፣ “የሕይወት ውሃ” (ዮሐ. 4፡10) አድርገው ሲያስቡት፣ ሁሉም ፍጹም ትርጉም የሚሰጥ ሆኖ ያገኙታል። በመሆኑም ጳውሎስ የብሉይ ኪዳንን ታሪክ፣ በዚህ ዘመን ባሉ ክርስቲያን ወገኖች ላይ ሊተገበሩ የሚችሉ መንፈሳዊ እውነቶችን ለመግለጥ የተጠቀመበትን ምሳሌ በዚህ ስፍራ እንመለከታለን። በዘፀአት የቀረበውን የእስራኤላውያን ተሞክሮ መለስ ብለው ያስቡ። እነርሱ ትተውልን ከሄዱት መልካምም ሆነ መጥፎ “ምሳሌ” ምን ዓይነት መንፈሳዊ ትምህርቶችን እንማራለን?

ጳግሜ 1
Sep 6

ኃይማኖታዊ ሥርዓቶች እና መሥዋእቶች


በኦሪት ዘሌዋውያን የሚገኘው ዓይነት የብሉይ ኪዳን ኃይማኖታዊ ሥርዓትና መሥዋዕት በትናንቱ ጥናታችን ላየነው ተጨማሪ ምሳሌዎች ያቀርባል--ወደ አዲስ ኪዳን እውነቶች የሚጠቁሙ የብሉይ ኪዳን ምልክቶች። ምንም እንኳ ዘመናዊ የመጽሐፍ ቅዱስ አንባቢዎች እነዚህን ሥርዓቶች ዘለው ቢያልፏቸውም፤ ለሚያጠኗቸው ታላቅ ዋጋ ያላቸው አያሌ አስፈላጊ መንፈሳዊ እውነቶችን ይዘዋል።

አንድ እስራኤላዊ የኃጢአት መሥዋዕት ይዞ ሲቀርብ የሚካሄደውን ሥርዓት በሌዋ. 4፡32-35 ያንብቡ። ምንም እንኳ ለኃጢአታችን መሥዋዕት ማቅረብ የምንችልበት መሠዊያ ያለው ቤተ መቅደስ ባይኖረንም ከዚህ ሥርዓት ምን እንማራለን? ይህን ሥርዓተ አምልኮ ከዮሐ. 1፡29 እና 1ጴጥ. 1፡18-21 ጋር ያገናኙ።



ኃይማኖታዊ ሥርዓት በጣም አስፈላጊ የሆኑ እሴቶችን እና መረጃዎችን የሚያስተላልፍ እንደመሆኑ መልእክቱ የተጻፈበት ዐውደ ሀሳብ በቅጡ ሊስተዋል ይገባል። ውጤታማ ለመሆን ባብዛኛው--የተወሰነ ጊዜ፣ ቦታ እና አስቀድሞ የተወሰነ የድርጊት ቅደም ተከተል ይጠየቃል። እርግጥ ነው-በብሉይ ኪዳን፣ መሥዋዕትን አስመልክቶ የተሰጡ የመጽሐፍ ቅዱስ ትዕዛዞችን ስናነብ ስለ መሥዋዕቱ ምንነት፣ መቼ እና የት መሥዋዕት ሆኖ እንደሚቀርብና ሊከተሉት ስለሚገባ ኃይማኖታዊ ሥርዓትና ደንብ እግዚአብሔር ዝርዝር መግለጫ እንደ ሰጠ እንመለከታለን።

እርግጥ ነው--የብዙዎቹ አምልኮ ሥርዓቶች ዋነኛው ነጥብ ደም እና ደም መፍሰስ፣ እንዲሁም መርጨት ነበር። ይህ የሚያስደስት ነገር አይደለም፣ እንዲህ እንዲሆንም አልነበረም--ነገር ግን ጉዳዩ በዩኒቨርስ እጅግ አጸያፊ የሆነውን ኃጢአት ማስወገድ የሚቻልበት ብቸኛ መፍትሔ በመሆኑ እንጂ! ደሙ ምን ዓይነት ትክክለኛ ሚና ነበረው? የመሠዊያውን ቀንዶች መቀባት ያስፈለገው ለምን ነበር? ከመቅደሱ ጋር ተያያዥነት የነበራቸው አብዛኞቹ የአምልኮ ሥርዓቶች ትዕዛዛዊ ቅርጽ ይዘው ቢታዩም (ማለትም፣ እንዴት መደረግ እንዳለባቸው መመሪያ ይሰጣሉ) ሁሌም፣ ሁሉንም ማብራሪያዎች አያካትቱም። ይህ ሊሆን የቻለው ምናልባት ምን ማለት እንደሆነ ሕዝቡ አስቀድሞ ስለተገነዘበ ሊሆን ይችላል። ለነገሩ የእስራኤል ሕዝቦች የደምን ትርጉም ተረድተው ነበር (ዘሌዋ. 17፡11)።

ከዘሌዋ. 4፡32–35 የተወሰደው ምሳሌ አንድ ጠቃሚ ማብራሪያ ይዟል፡ “በዚህ መሠረት ሰውየው የሠራውን ኃጢአት ካህኑ ያስተሰርይለታል፤ ሰውየውም ይቅር ይባላል” (ዘሌዋ. 4፡35)። እኛ ኃጢአተኞች ቅዱስ በሆነው አምላክ ፊት ጻድቅ ሆነን እንታይ ዘንድ ደም ለመላው የሥርየት ሂደት ቁልፍ ነበር። በእነዚህ መሥዋእቶች የምንመለከተው ስለ እኛ የተከፈለውን የክርስቶስን ሞት እና አገልግሎት ምሳሌ ነው። የሥላሴ አንዱ አካል የሆነው የሱስ ሥርየት ለማምጣት ራሱን መሥዋእት አድርጎ እንዲሰጥ ያደረገው ኃጢአት፣ ምን ያህል አሰቃቂ እንደሆነ ያስቡ። ይህ--በሥራችን ሳይሆን ነገር ግን በጸጋ ላይ ብቻ መተማመን እንደሚኖርብን ምን ሊያስተምረን ይገባል? ለነገሩ ክርስቶስ ለእኛ በሠራው ሥራ ላይ ምን ልናክል እንችላለን?

ጳግሜ 2
Sep 7

የዕረፍት “ምሳሌ”


ቀደም ሲል ከተመለከትናቸው ምሳሌዎች በተጨማሪ ይህ የምሳሌዎችና የምልክቶች ጽንሰ ሀሳብ፣ በመጽሐፍ ቅዱሳዊው የዕረፍት ጽንሰ ሃሳብ ላይም እንዲሁ ሊተገበር ይችላል። ይህን ለማየት ወደ አዲስ ኪዳን በማምራት የዕብራውያን መጽሐፍን እንመለከታለን። ጥቅሱን ያንብቡ፡ ዕብ. 4፡11። ወደ ዕረፍቱ ለመግባት የቀረው የተስፋ ቃል ምን ያመለክታል? እስራኤላውያን በኃይል ከግብፅ የመውጣታቸው እና በምድረ በዳ የመቅበዝበዛቸው ተሞክሮ ወደ አምላካዊው ዕረፍት የመግባት ጽንሰ ሀሳብ ላይ ተጨማሪ ግንዛቤ የሚሰጠው እንዴት ነው?



የጽናትና የታማኝነት ጉዳይ እዚህ ላይ በጣም አስፈላጊ ነው። ምንም እንኳ ስለ ሰባተኛው ቀን ሰንበት ቢናገርም፣ የእነዚህ ቁጥሮች ዋንኛ ትኩረት (ቀደም ብሎ የቀረበውን--ዕብ. 3:7–19 ይመልከቱ) የእግዚአብሔር ሕዝቦች እምነታቸውን እንዲጠብቁ የቀረበ ጥሪ መሆኑ እሙን ነው። ይኸውም ለጌታ እና ለወንጌል ታማኝ እንደሆኑ መጽናት ነው። “ማንም የእነዚያን አለመታዘዝ ምሳሌ ተከትሎ እንዳይወድቅ” (ዕብ. 4፡11) በሚል የቀረቡት ቃላት አንባቢው ቀደም ሲል ከነበረው አምላካዊ አመራር የተማራቸውን ትምህርቶች በቁም ነገር እንዲመለከት ያስታውሱታል። ልብ ይበሉ፣ ይህ ታላቅ መታደል ነው!

እስራኤላውያን ወንጌል ሰምተዋል፤ ነገር ግን ቃሉ አልጠቀማቸውም። እየታመኑና እየታዘዙ እምነታቸውን በማጠናከር ፋንታ ዐመጻን መረጡ (ዕብ. 3፡7፡7-15)፤ በዚህም እግዚአብሔር እንዲያገኙ የፈለገውን ዕረፍት ፈጽሞ ሳይለማመዱ ቀሩ። ዕብራውያን 4፡3--በእምነት እና በዕረፍት መካከል ያለውን የጠበቀ ግንኙነት ያመለክታል። ወደ ዕረፍቱ መግባት የምንችለው ዕረፍት ለመስጠት ቃል የገባውንና ይህን ቃል መፈጸም የሚችለውን ይኸውም የሱስ ክርስቶስን ስናምን ብቻ ነው። ጥቅሱን በድጋሚ ያንብቡ፡ ዕብ. 4፡3። የእነዚህ ሕዝቦች ዋንኛ ችግር ምን ነበር? እኛ “የምሥራቹ ቃል የተሰበከልን” (ዕብ. 4፡2) ለራሳችን የሚሆን ምን ትምህርት ከዚህ እናገኛለን?



የጥንቱ ክርስቲያናዊ ማኅበረሰብ የቀደመውን አምላካዊ መገለጥ (እኛ “ብሉይ ኪዳን” ብለን የምንጠራውን) ተቀብሎ እና የኃጢአታችን መሥዋእት የሆነው የሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር በግ መሆኑን አምኖ ነበር። በመሥዋእቱ ላይ በሚኖራቸው እምነት በየሱስ የሚገኘውን ደኅንነት እና በእርሱ የተሰጠንን ዕረፍት ይለማመዱ ነበር። በየሱስ ደም መዳን ምን ማለት እንደሆነ መረዳታችን በየሱስ ልናገኝ ወደ ምንችለው ዕረፍት ለመግባት የሚረዳን እንዴት ነው-በሥራ ሳይሆን በጸጋ መዳናችንን ከማወቃችን አኳያ?

ጳግሜ 3
Sep 8

ልባችሁን አታደንድኑ


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዕብ. 4፡4-7፣ መዝ. 95፡8-11። በመዝሙርም ሆነ በዕብራውያን መጽሐፍ የተሰጠው ማስጠንቀቂያ ምንድን ነው? ዛሬ እኛን ምን ይለናል?



ዕብ. 4፡4-7 የፍጥረትን ነባራዊ ሁኔታ በማከል የሚያቀርብ ሲሆን--መዝ. 95፡ 11 ደግሞ ከእስራኤላውያን ታማኝ አለመሆን እና ያን ተከትሎ እግዚአብሔር እንዲገቡ ወደ ፈለገው ዕረፍት ሳይገቡ ስለ መቅረታቸው ያወሳል። እርግጥ ነው--መዝ. 95፡ 8–11 የእስራኤልን የምድረ በዳ ተሞክሮ ከአምላካዊው ዕረፍት ጋር በማስተሳሰር ያቀርብና፣ እምነተ-ቢሱ እስራኤል ወደ ዕረፍቱ አይገቡም የሚለው መለኮታዊ መሐላ ከተስፋይቱ ምድር ጋር የተዛመደ ነው። እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር መግባታቸው እሙን ነው። አዲሱ ትውልድ ድንበሩን ተሻግሮ፣ በአምላክ እርዳታ የምድሪቱን ጠንካራ ምሽጎች ተቆጣጥሮ በዚያ መኖር ጀመረ።

ይሁን እንጂ ወደ አምላካዊው ዕረፍት አልገቡም፤ ብዙዎች በየሱስ የሚገኘውን የመዳን ሐቅ ጽንሰ ሀሳብ ያልተለማመዱት አለማመናቸው ጉልህ በሆነ አለመታዘዝ በመገለጡ ነበር። ምንም እንኳ ዕረፍት ከምድሪቱ ጋር የተቆራኘ ቢሆንም፣ ሰዎች ከሚኖሩበት ቦታ የላቀ አንደምታ አለው። የመለኮታዊውን እውነተኛ ዕረፍት ተስፋ የሰሙ ባለመታዘዛቸው ጠንቅ እንዳልገቡ ዕብ. 4፡6 ይጠቁማል። ባለመታዘዝ እና ወደ እግዚአብሔር ዕረፍት ባለመግባት መካከል ያለው ግንኙነት ምንድን ነው?



“ዛሬ” የተሰኘው ቃል አስቸኳይ ሁኔታን ያመላክታል። “ዛሬ” ማለት የሚባክን ጊዜ የለም እንደ ማለት ነው። “ዛሬ” ፈጣን ምላሽ እና ውሳኔ ይጠይቃል። ጳውሎስ ሴምሮን ወይም “ዛሬ” የሚለውን ቃል በመውሰድ ቃሉ ከዕረፍት ዐውድ አኳያ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ አጽንዖት ይሰጣል። ይህ በዚህ እንዳለ፤ የእግዚአብሔር ሕዝቦች የአባቶቻቸውን ስህተት እንዳይደግሙና እግዚአብሔር ብቻ በሚሰጠን ደኅንነት ወደ ተገኘ እውነተኛ ዕረፍት ከመግባት እንዳይሰናከሉ መዝ. 95፡7-8 ማስጠንቀቂያ እና ተማጽኖ ያቀርባል።

“ዛሬ ድምፁን ብትስሙ ልባችሁን አታደንድኑ” የሚለው መልእክት ለእኛ ምን ዓይነት ትርጉም ሊኖረው ይገባል? “ዛሬ” ከሚለው ቃል ጀርባ ያለው በጣም አስፈላጊ ነገር ምንድን ነው? ለነገሩ ቃሉ በመዝሙር መጽሐፍ ጥቅም ላይ የዋለው ከብዙ ሺህ ዓመታት በፊት ነው። የሆነው ሆኖ፤ በሺዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት እንደ ሰሙት ሁሉ ለእኛ “ዛሬ” አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?





ጳግሜ 4
Sep 9

ሰማያዊዋን ከተማ መውረስ


በዕብ. 4 የቀረቡት ቁልፍ ጽንሰ ሀሳቦች አመክንዮአዊ እድገት በተለይ ዕብ. 4፡8-11 ላይ በግልጽ ይታያል። ኢያሱ ለእስራኤላውያን ዕረፍት አልሰጠም። እንግዲህ፣ እግዚአብሔር ሐሰት የማያውቅ አምላክ እንደ መሆኑ ለእግዚአብሔር ሕዝብ የቀረ ሌላ “ዕረፍት” መኖር አለበት። ይህ ቡድን በአይሁድ አማኞች ብቻ የተዋቀረ አይደለም። ይልቁንም የሱስን የግል አዳኛቸው አድርገው የተቀበሉትን ሁሉ ያጠቃልላል።

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ገላ. 3፡26-29። ከመስቀሉ በኋላ ያሉትን የእግዚአብሔር ኪዳን ሕዝቦች ባህሪ ልብ ይበሉ። ጳውሎስ በጻፈበት አግባብ በአይሁድና በግሪክ፣ በባሪያና በነጻ ሰው፣ በወንድና በሴት መካከል ልዩነት የለም ሲል ምን ማለቱ ነው?



አልፎ አልፎ ዕብ. 4 ስለ ሰባተኛውን ቀን ሰንበት አጽንኦት ለመስጠት ጥቅም ላይ ሲውል፤ ሌሎች ደግሞ ሌላ (የመጨረሻ ጊዜ) ዕረፍት በተጨባጭ ከመኖሩ አኳያ፣ የዚህን ሰንበት ዕረፍት ትክክለኛነት ለመሞገት ተጠቅመውበታል። ከእነዚህ ከሁለቱም አቋሞች አንዳቸውም መጽሐፍ ቅዱሳዊውን ጥቅስ በጥሩ ሁኔታ አያንጸባርቁም። ይልቁንም በእግዚአብሔር ልዩ ዕረፍት ላይ ያለው የፍጻሜ ጊዜ ትኩረት ከፍጥረት አንስቶ እንደነበረና የሰንበትን ዕረፍት ማክበር ያንን የመጨረሻ ጊዜ ዕረፍት በሳምንታዊው ዕለት በጥቂቱ ማጣጣም እንደሆነ ጥቅሱ ይጠቁማል። እርግጥ ነው--ሰንበት በአይሁዳውያን ዘንድ “ኦላም ሃባ” (የሚመጣውን ዓለም) በትንሹ የሚያበስር ተደርጎ ይስተዋላል።

ከእግዚአብሔር ሕዝቦች ጋር እንዲዘልቅ የተሰጣቸው የሰንበት ዕረፍት-በምድር ታሪክ በመጀመሪያው ሰንበት ገቢራዊ የሆነውን አምላካዊ ዕረፍት ያስተጋባል። ይህ ማለት ከሥራችን ሁሉ አርፈን ለእኛ የገባውን የመዳን ተስፋ ቃል እንደሚፈጽምልን ልንተማመንበት እንችላለን ማለት ነው። ክርስቲያኖች የሰንበትን ሕግ መታዘዛቸው አስፈላጊ እንዳልሆነ አድርገው ከሚያቀርቡ አንዳንድ ተርጓሚዎች የሙግት ሀሳብ በተቃራኒ--የሰንበት ሕግ ክርስቶስ ባስገኘው ደኅንነት ተፈጽሟል የተሰኘውን አባባል የመልእክቱ ዐውደ ሐሳብ አይደግፈውም። ክርስቶስ ለእኛ የከፈለልንን ዋጋ ተከትሎ የተሰጠን የመጨረሻው ዕረፍት የተስፋ ቃል--የመጽሐፍ ቅዱስን ሰባተኛ ቀን ሰንበትን አይተካውም፤ እንዲያውም ያጸናዋል።

በጥረታቸው ስኬታማ ለሆኑ ጠንካራ ሠራተኞችና ታታሪዎች ከፍተኛ ዋጋ በሚሰጥበት ዓለም፣ በየሱስ ማረፍ እና ጸጋው እኛን ለማዳንና ለመለወጥ በቂ እንደሆነ መተማመን በእርግጥም ከተለመደው ባህል ውጪ ነው። ኃጢአታቸው በጣም ከባድ፣ ልባቸው ሊለወጥ እንደማይችልና ሁኔታቸው ተስፋ አስቆራጭ እንደሆነ አድርገው ለሚያስቡ ወገኖች፣ በየሱስ ዕረፍት ያገኙ ዘንድ እንዴት ሊረዷቸው ይችላሉ? የትኛውን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ያካፍሏቸዋል?

ጳግሜ 5
Sep 10


ተጨማሪ ሀሳብ


“እኛ ከነፈተናዎቻችን እና ከነችግሮቻችን ወደ የሱስ ለመቅረብ ሁሌም ፈቃደኞች አይደለንም። የሐዘንን መንገድ ወደ ደስታ እና ሰላም ሊለውጥ በሚችለው የሱስ ከመታመን ይልቅ፣ እርሱን ችላ ብለን ችግሮቻችንን ወደ ሰዎች ጆሮዎች እናፈሳለን፣ መከራዎቻችንን ሊቀርፉ ለማይችሉት እንነግራቸዋለን። ራስን መካድ ለመስቀሉ ክብርና ድል ይሰጣል። አምላካዊው የተስፋ ቃሎች እጅግ የከበሩ ናቸው። ፈቃዱን ማወቅ ከፈለግን ቃሉን ማጥናት ይኖርብናል። አምላካዊውን ቃል በጥንቃቄ የምናጠና እና መታዘዛችንን በተግባር የምንገልጥ ከሆነ፣ (ቃሉ) እግሮቻችን ሳይሰናከሉ መራመድ በሚያስችላቸው በቀናው መንገድ ይመራናል። አገልጋዮችም ሆኑ ሕዝቡ ሸክሞቻቸውንና ግራ መጋባታቸውን ተቀብሎ ሰላምና ዕረፍት ለመስጠት ወደሚጠባበቃቸው የሱስ ይውሰዱ! በእርሱ የሚታመኑትን ፈጽሞ አይተዋቸውም።”—Ellen G. White, The Signs of the Times, March 17, 1887, p. 161.

“የተወደዳችሁ ወጣቶች፣ ጻድቅ ፈራጃችሁ ጌታ በአባቱ እና በቅዱሳን መላእክት ፊት ስማችሁን ጠርቶ ስለ እናንተ ሲመሰክር ለመመልከት በደስታና በጉጉት እየተጠባበቃችሁ ትገኛላችሁ? እርስዎ ለክርስቶስ ዳግም መገለጥ ሊያደርጉ የሚችሉት ምርጥ ዝግጅት በመጀመሪያ ምጽአቱ ባስገኘልን ታላቅ ደኅንነት ላይ በጽኑ እምነት ማረፍ ነው። ክርስቶስን እንደ ግል አዳኝዎ ሊያምኑበት የግድ ነው።”—Ellen G. White, Our High Calling, p. 368.


የመወያያ ጥያቄዎች



፡ 1.የእግዚአብሔርን ሰማያዊ ዕረፍት ለሕዝቦቹ ስለሚያመላክተው ሰባተኛው ቀን ሰንበት በተለየ የቀረበው ነገር ምንድን ነው? ይኸውም የሰንበት ዕረፍት የዘላለማዊውን ነገር ቅምሻ የሚሰጠን እንዴት ነው?

2.ሥርየት እርቅ የሚል ፍቺ ያለው ሲሆን፣ ወደ እግዚአብሔር የምንመለስበትን መንገድ ያመለክታል። እንደሚከተለው ስለቀረበው አስፈላጊ መግለጫ አሰብ ያድርጉ፡ “ይህ ብቻ አይደለም። ነገር ግን አሁን እርቅን ባገኘንበት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በእግዚአብሔር ደግሞ ሐሤት እናደርጋለን” (ሮሜ 5፡11)። አንድ ሰው “ከእግዚአብሔር ጋር መታረቅ ማለት ምን ማለት ነው? ይህ እርቅ በሕይወትዎ ውስጥ ምን ለውጥ አምጥቷል?” ብሎ ቢጠይቅዎ ምን ይመልሳሉ?

3.በክርስትና ሕይወታችን አላስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ለአካለ መጠን ካልደረሱ ልጆች ማስወገድ የምንችለው እንዴት ነው? በአምላካዊው ቃል በቀረበው ትልቁ ሥዕል ላይ እንድናተኩር የሚያደርገን ምንድን ነው?

4.የእስራኤል ልጆች በምድረ በዳ ስለታዩባቸው ስህቶች እና የእምነት መጉደሎች በድጋሚ ያስቡ። ምንም እንኳ የእነርሱ ተግዳሮት ዝርዝሮች ከእኛ የተለዩ ቢሆኑም (በተንጣለለው ምድረ በዳ ውስጥ እየተንከራተትን ባለመሆናችን) በአንድ ላይ የምንጋራቸው መርኅዎች የትኞቹ ናቸው? ይኸውም በክርስትና ጉዞአችን፣ እነርሱ ከገጠሟቸው ተመሳሳይ ፈታኝ ሁናቴዎች ጋር መጋፈጥ የምንችለውና ከእነርሱ ስህተት የምንማረው እንዴት ነው?




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA union SSL