የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

በክርስቶስ ማረፍ


3ኛ ሩብ ዓመት 2021

ከመስከረም 1–7

12ኛ ትምህርት

Sep 11–Sep 17




ዕረፍት ዐልባው ነቢይ



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ዮናስ 1–4፣ ኤር. 25:5፣ ሕዝ. 14:6፣ ራእ. 2:5፣ ሉቃ. 9:51–56፣ ይሁዳ 1–25።


የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ “ ‘ታዲያ፣ እኔ ቀኝና ግራቸውን ለይተው መናገር የማይችሉ፣ ከአንድ መቶ ሃያ ሺህ በላይ ሰዎችና አያሌ እንስሶች ለሚኖሩባት ለታላቂቷ ከተማ ለነነዌ ማዘን አይገባኝምን?’ ” (ዮናስ 4፡11)።

ከ ቅዱሳት መጻሕፍት እጅግ መሳጭ ታሪኮች አንዱ የዮናስ ታሪክ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም። እርሱ በእግዚአብሔር የተጠራ ነቢይ የነበረ ቢሆንም--ከዚያስ ምን ተከሰተ? የእግዚአብሔርን ጥሪ ወደ ጎን ብሎ ኮበለለ። ከዚያም ሀሳቡን ለውጦ ጌታን ይታዘዝ ዘንድ በሚገርም መንገድ እንዲያምን ከሆነ በኋላ የተባለውን ቢያደርግም--ግን እስከምን ሄደ? እንዲመሰክርላቸው የተጠራባቸው ሕዝቦች በእውነት ንስሐ በመግባታቸው እና ሊመጣባቸው ከነበረው ቁጣ በመትረፋቸው ተቆጣ! በልቅሶው እንኳ--በዕረፍት ውስጥ ያልሆነና ሰላም የማያውቀው ሰው ዓይነተኛ ምሳሌ ሆኖ ቀርቧል፡ “አሁንም እግዚአብሔር ሆይ ነፍሴን ውሰድ፤ ከምኖር መሞት ይሻለኛልና” (ዮናስ 4፡3)።

የሱስ ራሱ የዮናስን ታሪክ በመጥቀስ እንዲህ ብሏል፡ “ ‘የነነዌ ሰዎች በፍርድ ዕለት ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥተው ይፈርዱበታል፤ እነርሱ በዮናስ ስብከት ንስሐ ገብተዋልና’ ” (ማቴ. 12፡41)። እርሱ በእርግጥ ከዮናስ ይበልጣል! ያ ባይሆንማ ኖሮ አዳኛችን መሆን ባልቻለ ነበር። በዚህ ሳምንት ወደ ዮናስ ታሪክ በመመልከት ከእርሱ የዕረፍትና ሰላም እጦት መማር የምንችለውን እንመለከታለን።

መስከረም 2
Sep 12

ኩብለላ


ዮናስ አስገራሚና የተዋጣለት ሚሲዮናዊ ነበር። የዚያኑ ያህል ደግሞ ቢያንስ በመጀመሪያ ላይ እንደተስተዋለው እንቢተኛና ዳተኛ ነበር። ዮናስ ያደርግ የነበረው ነገር ምንም ይሁን ምን--አምላካዊው ጥሪ ሕይወቱን በከፍተኛ ደረጃ አስተጓጉሏል። የእግዚአብሔርን ቀንበር በጫንቃው ተሸክሞ፣ ቀንበሩ ልዝብ ሸክሙም ቀላል መሆኑን በመፈተሽ ፋንታ (ማቴ. 11፡30) ዮናስ የራሱን ዕረፍት ለማግኘት ወሰነ። ይህንንም ያደረገው እግዚአብሔር እንዲሄድ ከጠራው በተቃራኒ አቅጣጫ በመኮብለል ነበር። ዮናስ ከአምላክ ጥሪ ሰላምና ዕረፍት ለማግኘት ተስፋ ያደረገው የት ነበር? ምን ያህል በትክክል ሠራለት? ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዮና. ምዕ. 1።



ዮናስ እግዚአብሔር ከጠራው በተቃራኒ አቅጣጫ ኮበለለ። ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ነቢያት የእግዚአብሔር መልእክተኞች እንዲሆኑ በተጠሩ ጊዜ ያደርጉ እንደነበረው ቆም ብሎ እንዲህ ነው፣ እንዲያ ነው እንኳ አልተባባለም (ዘፀ. 4፡ 13)።

የሚገርመው ነገር፤ በ2ነገሥ፣ 14፡25 እንደተገለጸው ዮናስ ስለ እግዚአብሔር እንዲናገር ጥሪ ሲቀርብለት ይህ የመጀመሪያው አልነበረም። ሆኖም በዚህ ጊዜ ዮናስ የተጠየቀውን ያደረገ ይመስላል። ታዲያ አሁን ምን ነካው? ዮናስ በእስራኤል አገልግሎት ይሰጥ በነበረበት ከክርስቶስ ልደት በፊት ስምንተኛው ምዕተ ዓመት ላይ በቅርብ ምሥራቅ አካባቢ ከፍተኛ ተጽእኖ የነበራቸው አዳዲሶቹ የአሦር ጌቶች የጭካኔ ተግባር ይፈጽሙ እንደ ነበር የታሪክ እና ሥነ ቅርስ መዛግብት ያሳያሉ። ከ75 ዓመታት ገደማ በኋላ የአሦር ንጉሥ ሰናክሬም በይሁዳ ላይ ጥቃት ሰነዘረ። እስራኤልና ሰማርያ ቀደም ሲል ማለትም ከሃያ ዓመታት ገደማ በፊት በዚሁ ኃይል ስር ወድቀው የነበረ ሲሆን፤ ንጉሥ ሕዝቅያስ የጸረ-አሦር ጥምረትን በይፋ ተቀላቅሎ ነበር።

አሁን አሦራውያን ሂሳብ የሚያወራርዱበት ጊዜ ደረሰ። መጽሐፍ ቅዱስ (2ነገሥ. 18፣ ኢሳ. 36)፣ የአሦራውያን የታሪክ መዛግብት እንዲሁም በነነዌ ይገኝ የነበረው የሰናክሬም ቤተ መንግሥት ግድግዳ ላይ ታትመው የተገኙ ማስረጃዎች ስለ ጨካኙ ለኪሶ ውድቀት ይነግሩናል። በአንደኛው ጽሑፍ ሰናክሬም ደመሰስኳቸው ከሚላቸው 46 የተመሸጉ ከተሞች ውስጥ ከሁለት መቶ ሺህ በላይ እሥረኞች መውሰዱን ይናገራል። የአሦር ንጉሥ ለኪሶን በያዘበት ወቅት በመቶዎች ወይም በሺዎች የሚቆጠሩ እስረኞች በሥቅላት የተገደሉ ሲሆን፣ የንጉሥ ሕዝቅያስ ጠንካራ ደጋፊዎች በሕይወት እያሉ ቆዳቸው ተገፏል። የተቀሩት ደግሞ በርካሽ የባሪያ ጉልበት እንዲያገለግሉ ወደ አሦር ተልከዋል።

በዘመኑ ይታይ ከነበረው ጭካኔ የተሞላው የዓለም ተግባር አኳያ፣ የአሦራውያኑ ወደር የማይገኝት ሊሆን ይችላል። እግዚአብሔር ደ’ሞ ዮናስን ወደዚያ ግዛት እምብርት እየላከው ነበር? ታዲያ ዮናስ ለመሄድ አለመፈለጉ ሊያስገርም ይችል ይሆን? ከእግዚአብሔር መሸሽ? ከዚህ በፊት እንዲህ አድርገው ያውቃሉ? ከሆነ፣ ምን ያህል ጥሩ ውጤት አስገኘልዎ? ከዚህ ስህተት ምን ዓይነት ትምህርት መማር ይገባዎታል?

መስከረም 3
Sep 13

የሦስት ቀናት ዕረፍት


የዮናስ ከእግዚአብሔር መኮብለል--ችግር ሳያስከትልበት የቀረ አልነበረም። ያ ለአጭር ጊዜ ብቻ የዘለቀው የእርሱ “ዕረፍት” በእግዚአብሔር ታምራዊ ማዕበል ጣልቃ ገብነት ተናጋ። እግዚአብሔር ዓሣው ዮናስን እንዲያድን በማዘዙ እነሆ ከውሃው መቃብር ዳነ። ይሁን እንጂ ዮናስ በዚያ ትልቅ ዓሣ ሆድ ውስጥ ለሦስት ቀናት በግድ እንዲያርፍ በተደረገ ጊዜ ብቻ ነበር በእግዚአብሔር ላይ ምን ያህል ጥገኛ እንደሆነ መገንዘብ የቻለው። እኛ በትክክል የሚያሻን የሱስ መሆኑን መገንዘብ እንችል ዘንድ፣ አንዳንዴ ይህ ዓለም እንድንደገፍበት የሚያቀርብልን ምንም ነገር አለመኖሩን ወደሚያሳይ ሁናቴ መምጣት ሊኖርብን ይችላል። ዮናስ በዓሳው ሆድ ውስጥ ሆኖ የጸለየውን ጸሎት ያንብቡ (ዮናስ. 2፡1-9)። ስለምን ነበር የጸለየው?



ዮናስ እጅግ አስፈሪ በሆነ መልኩ በጥልቅ ባህር ስር የወደቀ ቢሆንም፣ በጸሎቱ ስለ መቅደሱ ያነሣል። “ወደ ቅዱስ መቅደስህ እመለከታለሁ”--በማለት። እየሆነ ያለው ነገር ምንድን ነው? መቅደሱ የዚህ ጸሎት ዋንኛ ክፍል ከመሆኑ አኳያ፤ በአጠቃላይ የጸሎት ማዕከላዊ አካል መሆን እንዳለበት ይታመናል። በብሉይ ኪዳን እግዚአብሔር ሊገኝ ይችል የነበረበት ስፍራ አንድ ብቻ ሲሆን፤ ይኸውም መቅደሱ ነበር (ዘፀ. 15፡17፣ 25፡8)። ቤተ መቅደሱ ለእግዚአብሔር ጸሎትና የኅብረት አምልኮ የሚቀርብበት ዓይነተኛ ማዕከላዊ ክፍል ነበር። ሆኖም ዮናስ በየሩሳሌም ይገኝ የነበረውን ቤተ መቅደስ እየጠቀሰ አልነበረም። ይልቁንም ስለ ሰማያዊው መቅደስ እየተናገረ መሆኑን ልብ ይሏል (ዮና. 2፡7)። እነሆ የአምላካዊው ተስፋ መገኛ እዚያ ነው፤ ምክንያቱም እግዚአብሔር እና የእርሱ ማዳን በእርግጠኝነት ከዚያ ይመጣልና።

ዮናስ በመጨረሻ ይህን ወሳኝ እውነት መረዳት ቻለ። የእግዚአብሔርን ጸጋ መለማመድ ቻለ። መዳን ቻለ። ትልቁ ዓሣ ወደ ደረቁ ምድር በተፋው ጊዜ፤ ኮብላዩ ነቢይ እግዚአብሔር ለእርሱ ያለውን ፍቅር በተጨባጭ አስተዋለ። ለማንኛውም አማኝ አስተማማኝ የሆነው አካሄድ በእግዚአብሔር ፈቃድ ስር መመላለስን አጥብቆ መፈለግ መሆኑን በእርግጠኝነት መማር ቻለ። የዚህች ከመጠን በላይ በእርክስና የተሞላች ከተማ ሕዝቦች ምን ያህል መጥፎ እንደሆኑ ይህ ባዕድ ነቢይ ይነግራቸው ዘንድ ደስተኞች ላይሆኑ ቢችሉም እንኳ፣ ግዴታውን ለመፈጸምና የእግዚአብሔርን ትእዛዛት ለመከተል የወሰነው ዮናስ፣ በእምነቱ ላይ የነበረውን ጥርጣሬ አስወግዶ በመጨረሻ ወደ ነነዌ አመራ።

አንዳንድ ጊዜ በነገሮች ላይ አዲስ አመለካከት ለማግኘት ከማንኛውም ሁናቴ ገሸሽ ማለት ያስፈልገን ይሆናል። ምንም እንኳ በዓሳው ሆድ ውስጥ በታምር በሕይወት የተረፈው የዮናስ ታሪክ ከተለመደው በእጅጉ የወጣ ቢሆንም፣ ከተለመደው ሁናቴ ዞር ማለትዎ ክስተቱን በአዲስ ምናልባትም ወሳኝ በሆነ ዕይታ መመልከት እንዲችሉ እንዴት ይረዳዎታል?

መስከረም 4
Sep 14

ተልዕኮው ተፈጸመ


ነነዌ በእስራኤል ውስጥ ከነበሩ ከማናቸውም ከተሞች ጋር ስትነጻጸር ግዙፍ ከተማ ነች። “እርሷን ከዳር እስከ ዳር ለመጎብኘት ሦስት ቀን ያስፈልግ ነበር” (ዮናስ 3፡3)። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዮናስ 3፡1-10። የዚህ በእርክስና የተሞላ ስፍራ ምላሸ ምን ነበር? ለሌሎች ለመመስከር በምንሞክርበት ወቅት ከዚህ ታሪክ ምን ትምህርት መውሰድ እንችላለን?



ዮናስ በከተማዋ እየተዘዋወረ የእግዚአብሔርን መልእክት እንዲህ ሲል አወጀ፡ “ነነዌ በአርባ ቀን ውስጥ ትገለበጣለች” (ዮናስ 3፡4)። ምንም ሳያድበሰብስ እቅጩን ነበር ያስቀመጠው። ምንም እንኳ ዝርዝር መረጃ ባይሰጥም መልእክቱ በአድማጭ ጆሮ ውስጥ መግባቱ ግልጽ ሆነ፤ በዚህም የነነዌ ሕዝቦች (በአጠቃላይ!) በዮናስ የማስጠንቀቂያ ቃላት አመኑ። በቅርብ ምሥራቅ የዓለም ክፍል የተለመደ በነበረው አካሄድ፣ የልብ መለወጥን ለማሳየት በነነዌ ንጉሥ አዋጅ ታወጀ። እንስሳትን ጨምሮ ሰው ሁሉ መጾምና ስለ በደላቸው ማዘን ነበረባቸው። ንጉሡ ከዙፋኑ ወርዶ፣ ማቅ ለብሶ ዐመድ ላይ ተቀመጠ። ይህ በእጅጉ ወሳኝ የሆነ ምሳሌያዊ ተግባር ነበር። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዮናስ 3፡6-9። ከሚከተሉት ጥቅሶች ጋር ያስተያዩ፡ ኤር. 25፡5፣ ሕዝ. 14፡6፣ ራእ. 2፡5። ንጉሡ እውነተኛውን ንስሐ መረዳቱን የሚያሳዩ በንግግሩ ውስጥ የተካተቱ አበይነት ነጥቦች ምን ነበሩ?



የዮናስ ስብከት አጭርና እቅጩን የሚናገር ቢሆንም፤ እውነተኛ ንስሐን አስመልክቶ ትክክለኛ በሆነ ኃይማኖታዊ አስተምህሮ የተሞላ ነበር። ዮናስ ይሰብክ በነበረበት ወቅት መንፈስ ቅዱስ በነነዌ ሕዝቦች ልብ ውስጥ ተግቶ ሳይሠራ እንዳልቀረ ይታመናል። የነነዌ ሕዝቦች እስራኤላውያን የነበራቸው ዓይነት የእግዚአብሔር በርኅራኄ የተሞላ ምሪት ታሪክ አልነበራቸውም። ይህም ሆኖ አዎንታዊ ምለሽ ሰጥተውታል። እነዚህ ሕዝቦች “በገዛ ስኬቶቻችን መታመናችንን ትተን ራሳችንን በእግዚአብሔር ምህረት ሥር እንጣል!” ብለው በተጨባጭ እየተናገሩ ነበር። በአምላካዊው መልካምነትና በጸጋው ሙሉ ለሙሉ እንመካ።

የሚገርመው ነገር--የእግዚአብሔርን ጸጋ በግል የተለማመደው ዮናስ፤ ይህ ጸጋ የተወሰኑ ብቻ በዚያው ውስጥ የማረፍ ዕድል የሚያገኙበትና ለእነርሱ ብቻ የተወሰነ አድርጎ የሚያስብ ይመስላል። ንስሐ የክርስቲያኖች ተሞክሮ ወሳኝ ክፍል የሆነው ለምንድን ነው? ከኃጢአታችን በተለይ ደጋግመን ከሠራናቸው ኃጢአቶች ንስሐ መግባት ሲባል ምን ማለት ነው?

መስከረም 5
Sep 15

ቁጡና ዕረፍት የለሹ መልእክተኛ


አንዳንዶች የዮናስ ታሪክ በምዕራፍ 3 ቢያልቅ ይበጅ ነበር ቢሉም ታሪኩ ግን ይቀጥላል። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዮና. 4፡1-11። የዮናስ ችግር ምን ነበር? ከእርሱ አጉል ባሕሪ ምን እንማራለን?



የዮናስ ተልዕኮ እጅግ ስኬታማ መሆኑን ተከትሎ ዮና. ምዕ. 4 ይህ ነቢይ በእግዚአብሔር መቆጣቱን በመግለጽ ይጀምራል። ዮናስ የተጃጃለ መምሰሉ ያሳሰበው ይመስላል። ንዴቱ ብልጭ እንደሚልበት እልኸኛ ህጻን የሚመስለውን ነቢይ እግዚአብሔር ጊዜ ወስዶ ሲያናግረውና እውነታውን በተጨባጭ ሲያስረዳው ይታያል። ነቢያትን ጨምሮ እውነተኛ የእግዚአብሔር ተከታዮች በውስጣቸው ገና እያደጉና እየበለጸጉ የሚሄዱ ባህሪያት እንዳሉ የሚያመለክቱ ማስረጃዎች እንደሚከተለው ቀርበዋል።

“ምንም እንኳ ከተማዋ በእርክስና ብትሞላም ነገር ግን ማቅ ለብሳ እና ዐመድ ነስንሳ ንስሐ መግባቷን ተከትሎ እግዚአብሔር እንደ ማራት ዮናስ ተገነዘበ። በዚህ አስደናቂ አምላካዊ ጸጋ በቅድሚያ ሊደሰት ይገባ የነበረው እርሱ ቢሆንም፤ ነገር ግን እንደ ሐሰተኛ ነቢይ የሚታይበት ሁኔታ በአእምሮው እንዲያድር ፈቀደ። በተቀዳጀው ዝና ላይ ባደረበት ምቀኝነት ኃያሉ አምላክ ለዚያች ምስኪን ከተማ ነፍሳት የሚሰጠውን የከበረ ዋጋ ከማየት ታወረ።”— Ellen G. White, Prophets and Kings, p. 271. እግዚአብሔር በዚህ ነቢይ ላይ የነበረው ትዕግሥት በጣም አስደናቂ ነው። ዮናስን ለመጠቀም ቢፈልግም እርሱ ግን ከፊቱ ኮበለለ። ስለዚህ እርሱን ለመመለስ ማዕበል እና ትልቅ ዓሣ ላከ። አሁንም፣ ዮናስ ተቃራኒ ሲሆን የተመለከተው እግዚአብሔር ተጨባጩን እውነታ ሊያሳየው እየጣረ “ ‘በውኑ ልትቆጣ ይገባሃልን?’ ” (ዮሐ. 4፡4) ሲለው ይስተዋላል።

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ሉቃ. 9፡51-56። ይህ ዘገባ በዮናስ ታሪክ ውስጥ ከተፈጸመው ጋር በተወሰነ መልኩ የሚመሳሰለው እንዴት ነው?



“ ‘በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስከ መስጠት ድረስ ዓለምን እንዲሁ ወዶአልና’ ” (ዮሐ. 3፡16) ወይም እግዚአብሔር በዮናስ 4፡11 እንዳስቀመጠው፡ “‘ታዲያ፣ እኔ ቀኝና ግራቸውን ለይተው መናገር የማይችሉ፣ ከአንድ መቶ ሃያ ሺህ በላይ ሰዎችና አያሌ እንስሶች ለሚኖሩባት ለታላቋ ከተማ ለነነዌ ማዘን አይገባኝምን?’” በመጨረሻም--የልባችን፣ የአእምሮ እና የተነሳሽነታችን የመጨረሻው ዳኛ እግዚአብሔር እንጂ እኛ አለመሆናችን ምን ያህል አመስጋኝ ሊያደርገን ይገባል። እንደ እግዚአብሔር ያለ ርኅራኄና ትዕግሥት ለሌሎች እንዲኖረን መማር የምንችለው እንዴት ነው--ወይም ቢያንስ ያንን ርኅራኄና ትዕግሥት ማንጸባረቅ መማር የምንችለው እንዴት ነው?

መስከረም 6
Sep 16

መንታው መንገድ


ዮናስ ከሚገባው በላይ ችግር ያለበት ይመስላል። ነነዌ አደገኛ የነበረች ቢሆንም ነገር ግን በዮናስ ታሪክ የነነዌ ሰዎች የችግር አካል አይመስሉም። መልእክቱን ተረድተው በፍጥነት ንስሐ ገቡ። መልእክተኛው ዮናስ ግን በዚህ ታሪክ ደካማ ሰንሰለት ይመስላል። በዚህ ዘገባ እግዚአብሔር ዳተኛውን ነቢይ ሲከታተለው ይስተዋላል። ለዚህ ምክንያቱ ዮናስ ወደ ነነዌ የሚያደርገው የመልእክተኝነት ጉዞ--የነነዌ ሕዝቦች የዚህን መልእክተኛ መልእክት የመስማታቸውን ያህል አስፈላጊና ወሳኝ እንደሆነ ያውቅ ነበር። “በእግዚአብሔር ፍቅር ራሳችሁን ጠብቁ” (ይሁዳ 21)። የጥቅሱ ፍቺ ምንድን ነው?



በአዲስ ኪዳን በሚገኘውና አንድ ምዕራፍ ብቻ በያዘው በዚህ የይሁዳ መጽሐፍ ቁ. 21 ላይ፡ “ወደ ዘላለም ሕይወት የሚያደርሳችሁን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ምሕረት ስትጠባበቁ ሳለ፣ በእግዚአብሔር ፍቅር ራሳችሁን ጠብቁ” በማለት ይሁዳ ይነግረናል። የእግዚአብሔርን ፍቅርና ጸጋ በግል መለማመድ የአንድ ጊዜ ብቻ ክስተት አይደለም። ራሳችንን በእግዚአብሔር ፍቅር መጠበቅ ማለት ወደ ሌሎች መድረስ ነው። በቀጣዮቹ ቁጥሮች ለሌሎች “እንድንራራ”፣ “አንዳዶችን ከእሳት ነጥቀን እንድናድን” ይሁዳ ይነግረናል። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ይሁዳ 20-23። ከዮናስ ታሪክ ጋር ተዛምዶ ባለው መልኩ በዚህ ስፍራ ምን እያለ ነው--ለእኛስ ምን እየተናገረን ነው?



ዮናስ ወደ ነነዌ እንዲሄድ እግዚአብሔር ጥሪ ያቀረበለት ምክንያት ምናልባት ዮናስ ከዚህ በዓይነቱ የተለየ ጥሪ አስቀድሞ እርሱ ከአሦራውያን ጋር ስላለው ግንኙነት ብዙ ጊዜ ወስዶ ስላላሰበ ሊሆን ይችላል። ምናልባት ዮናስ እነዚህን ሕዝቦች እንደማይወዳቸው ቢያውቅም--ምን ያህል እንደሚጠላቸው ወይም እነርሱን ከፊቱ ዞር ለማድረግ የቱን ያህል ርቀት መጓዝ እንደነበረበት ጥሪው ከደረሰው በኋላም እንኳ እርግጠኛ አልነበረም። ዮናስ በሰማይ የነነዌ ተወላጅ ጎረቤት ይኖረው ዘንድ ዝግጁ አልነበረም። ዮናስ እግዚአብሔር ሰዎችን እንደሚወድ ሁሉ እርሱም መውደድ እንዳለበት አልተማረም ነበር። እግዚአብሔር የነነዌን ሕዝቦች ስለሚወድና የመንግሥቱ ወራሾች እንዲሆኑ ስለሚፈልግ ዮናስ ወደ ነነዌ እንዲሄድ ጥሪ አቀረበለት።

ደግሞም እግዚአብሔር ዮናስንም ስለሚወደው ለእርሱም ጥሪ አቀረበለት። በአብሮነት ሥራቸው ዮናስ እንዲያድግና አብልጦ እርሱን እንዲመስል ይፈልጋል። ዮናስ ከአምላካዊው የሚያድን ማንነት ጋር ግንኙነት በመፍጠር እና ፈቃዱን በማድረግ ብቻ የሚገኘው እውነተኛ ዕረፍት ባለቤት እንዲሆን እግዚአብሔር ይፈልጋል። ይህ ደግሞ ወደ ሌሎች መድረስ እና እኛ ባለቤት ወደሆንበት እምነት እና ተስፋ ማመላከትን ያካትታል። ስለ ሌሎች መዳን ለመሥራት ያዋሉት ጊዜ ምን ያህል ነው? ከመንፈሳዊው ነገር አኳያ--እንዲህ ዓይነቱ ሥራ በየሱስ እውነተኛ ዕረፍት እንድናገኝ እንዴት ይመራናል?

መስከረም 7
Sep 17


ተጨማሪ ሀሳብ


“የዮናስን ተልዕክ በተመለከተ ይህ ነቢይ ከባድ ኃላፊነት ተሰጥቶት ነበር። ሆኖም እንዲሄድ የላከው አገልጋዩን ሊደግፈውና ስኬት ሊያስጨብጠው ይችላል። ነቢዩ ያለ ምንም ጥያቄ ቢታዘዝ ኖሮ ከአያሌ መራራ ተሞክሮዎች መትረፍ በቻለና የተትረፈረፉ በረከቶችን በተቀበለ ነበር። ሆኖም ዮናስ ተስፋ አስቆራጭ ጊዜያቶች በገጠሙት ጊዜ ጌታ አልተወውም። በተከታታይ ፈተናዎችና እንግዳ ሁኔታዎች አማካይነት ነቢዩ በእግዚአብሔር እና ማብቂያ በሌለው የማዳን ኃይሉ የነበረው መተማመን ተነቃቃ።”—Ellen G. White, Prophets and Kings, p. 266.

“ውስብስብ ያልሆነና ትህትና የተላበሰ መንገድ ተጠቅሞ በሺዎች ለሚቆጠሩ ወገኖች መድረስ ይቻላል። በዓለማቀፍ ደረጃ ምሑር የሚባሉና ከፍተኛ ተሰጥኦ እንዳላቸው ተደርገው የሚታዩ ወንዶችና ሴቶች፤ ብዙውን ጊዜ እግዚአብሔርን የሚወድ ሰው በሚሰነዝራቸው ቀላል ቃላት መነቃቃትና መታደስ ሊያገኙ ይችላሉ። እነርሱ በለመዱት የዘወትር ቋንቋ ስለዚያ ፍቅር ሲናገሩ፣ በሌላው ላይ ጥልቅ ፍላጎት ያጭራሉ።”—Ellen G. White, Christ’s Object Lessons, p. 232.


የመወያያ ጥያቄዎች



፡ 1.“የእግዚአብሔር ነቢይ” የተቆጣው ደኅንነት ያገኙ ዘንድ በምስክርነት ወደ ሕዝቡ ስለላከው ነው? ይህን በዮናስ በኩል የተስተዋለ አመለካከት እንዴት እናስተውለዋለን? ሕዝቡ ከእውነት ብርሃን በተቃራኒ በሚጓዝበት ወቅት እግዚአብሔር ለእነርሱ ያለውን ትዕግሥት ማሳየት የሚችል እንዴት ያለ ብርቱ ምሳሌ ነው!

2.የዮናስ ታሪክ እግዚአብሔር አመጸኛ ሰዎችን የማዳን ሥራ ብቻ ሳይሆን ተከታዮቹን የመለወጥ ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለው የሚጠቁም ይመስላል። ጌታን እና ለዚህ ዘመን የተሰጠውን እውነት የምናውቅ ቢሆንም እንኳ “አዲስ ልብ” እና “አዲስ መንፈስ” ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው? እውነትን በማወቅና በእውነት በመለወጥ መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው?

3.የይሁዳን መጽሐፍ በድጋሚ ያንብቡ። መሠረታዊው የመጽሐፉ መልእክት ምንድን ነው? እንደ ቤተ ክርስቲያን መልእክቱ ለእኛ ወሳኝ የሆነው ለምንድን ነው?

4.ለሌሎች መዳን የመሥራት ተሞክሮ ከፍ ያለ መንፈሳዊ ጥቅም የሚያስገኝልን እንዴት ነው?

5.ዮናስ ወደ ነነዌ ለመሄድ ያልፈለገበት ምክንያት ምንም ይሁን ምን፣ እግዚአብሔር ምን ያህል ስህተት እንደሠራ በገሃድ አሳይቶታል። ዮናስ ያሳየው ዓይነት የተሳሳተ አመለካከት ሊያንጸባርቁ ለሚችሉ ሌሎች ወገኖች እንዴት ያለ አመለካከት ሊኖረን ይችላል?




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA union SSL