የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

በክርስቶስ ማረፍ


3ኛ ሩብ ዓመት 2021

ከመስከረም 8-14

13ኛ ትምህርት

Sep 18–Sep 24




የመጨረሻው ዕረፍት



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ራእ. 1:9–19፣ ማቴ. 24:4–8፣ 23–31፣ ራእ. 14:6–12፣ ዕብ. 11:13–16፣ ፊልጵ. 4:4– 6።


የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ “ይሁን እንጂ፣ እንደ ተጻፈው፣ ‘ዐይን ያላየውን፣ ጆሮ ያልሰማውን፣ የሰውመም ልብ ያላሰበውን፣ እግዚአብሄር ለሚወዱት አዘጋጅቶአል’ እግዚአብሔር ግን ይህን በመንፈሱ አማካይነት ለእኛ ገልጦአል።” (1ቆሮ. 2፡9)።

በ መልካምና በክፉ መካከል እየተደረገ ባለ ታላቅ ፍልሚያ ውስጥ እንዳሉ ሆኖ ተሰምቶት ያውቃል? ብዙዎች፣ ዓለማዊ ሰዎችም እንኳ ሳይቀሩ ይህንን እውነታ ተገንዝበዋል። እንዲህ ያለው ስሜት የሚሰማን፣ ጉዳዩ ተጨባጭ እውነታ በመሆኑ ነው። በክርስቶስና በሰይጣን ማለትም በመልካም እና ክፉ መሃል እየተረደገ ባለው ፍልሚያ መሃል እንገኛለን። በመሆኑም ሕይወት በሁለት ደረጃ ሂደት ውስጥ ይገኛል። በክርስቶስ እና በሰይጣን መካከል ገቢራዊ እየሆነ ያለው ታላቁ ተጋድሎ በዓለማቀፋዊ ደረጃ እየተካሄደ ያለ ቢሆንም--ውጊያው የተጀመረው በሰማይ ከመሆኑ አኳያ አጽናፈ ሰማያትንም ያካትታል (ራእ. 12፡7)። ሆኖም ክስተቶች በሚፈጥሩት ግራ መጋባት መሃል እግዚአብሔር ከዚህ ዓለም እንደ ማምለጫ ዕቅድ አድርጎ ያዘጋጀውን ትልቁን ምስል በቀላሉ ልናጣ እንችላለን።

ጦርነቶች፣ የፖለቲካ አለመረጋጋትና የተፈጥሮ አደጋዎች ምንም ማድረግ በማንችልበት አጣብቂኝ ውስጥ ከትተው እንድንሸበር ሊያደርጉን ይችላሉ። ነገር ግን ላቅ ያለው የአምላካዊ የትንቢት ምሪት፤ ወዴት እንደምንሄድና እንዴት እዚያ እንደምንደርስ ከፍ ያለ ሥዕልና እገዛ በመስጠት በአእምሮአችን ጠብቀን እንድንይዝ ሊረዳን ይችላል። ከዚህም በላይ ታላቁ ተጋድሎ በእያንዳንዱ ግላዊ ሕይወት ከፍ ባለ መልኩ ገቢራዊ እየሆነ ይገኛል። እኛ ሁላችን በዕለት ተዕለት ሕይወታችን የእምነት ፈተናዎች የሚያጋጥሙን ሲሆን፣ የየሱስን ዳግም ምጽአት እንደሚጠባበቁ ሆነን ካልኖርን የመጥፋት አደጋ ሊገጥመን የሚችልበት ሁናቴ ሊከሰት ይችላል።

በዚህ ሳምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን አጭር ዕድሜ ባለው ዓለማቀፋዊ አለመረጋጋት መሃል በየሱስ እንዴት ማረፍ እንደምንችል እንመለከታለን። ረጅሙን ዘመን አስመልክቶ ግን ነገሮች በእርግጥም እጅግ ብሩህ እና ተስፋ ሰጭ ሆነው የሚታዩ ይመስላሉ!

መስከረም 9
Sep 19

ስለ መጨረሻው የተሰጠ ራእይ


በሕይወት የተረፈውና አሁን በዕድሜ አንጋፋ የሆነው ደቀ መዝሙር፣ በእርግጥ ከየሱስ ጋር የነበረ ቢሆንም ነገር ግን አጠገቡ ከነበረ ማንኛውም ነገር ርቆ እና ተገልሎ፣ ዙሪያ ገባውን በባሕር በተከበበና ቋጥኝ በወረሰው ደሴት ወህኒ ይገኝ ነበር። ዮሐንስ ራሱን በዚህ ከሰው በተገለለ ደሴት መሃል ሲያገኝ በአእምሮው ምን ተመላልሶ ይሆን? እንዴት መጨረሻው እዚህ ሆነ? ደግሞም የሱስ ወደ ሰማይ ሲያርግ ተመልክቶት ነበር። በወቅቱ ድንገት አጠገባቸው ቆመው የነበሩ ሁለት መላእክት እንዲህ ብለዋቸዋል፡ “ ‘እናንት የገሊላ ሰዎች ሆይ፤ ወደ ሰማይ እየተመለከታችሁ እዚህ የቆማችሁት ለምንድን ነው? ይህ ከእናንተ ዘንድ ወደ ሰማይ ሲያርግ ያያችሁት ኢየሱስ፣ ልክ ወደ ሰማይ ሲወጣ እንዳያችሁት በዚሁ ሁኔታ ይመለሳል’ ” (ሐዋ. 1፡11)።

ይህ ክስተት ገቢራዊ የሆነው ከብዙ ዓመታት በፊት ቢሆንም እስከዚያ ጊዜ ድረስ አልተመለሰም። ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ በዚያን ወቅት ሌሎቹ ሐዋርያት ሞተዋል። አብዛኞቹ ለየሱስ ምስክር በመሆን ተሠዉተዋል። ለጋዋ ቤተ ክርስቲያን ከትውልድ ወደ ትውልድ የመሸጋገር ለውጥ ላይ የነበረች ሲሆን፣ በወቅቱ ከውጭ አስከፊ ስደት ከውስጥ ደግሞ እንግዳ ከሆነ የሐሰት አስተምህሮ እንቅስቃሴ ጋር እየተፋለመች ነበር። በብቸኝነት ይንከላወስ የነበረው ዮሐንስ ድካም እና ዕረፍት ዐልባነት ሳያጠቃው አልቀረም። ታዲያ በዚህ መሃል፣ ድንገት ራእይ ተሰጠው። ዮሐንስ ከዚህ ራእይ ስላገኘው መጽናናት መገመት ይችላሉ--ራእ. 1:9–19?



“እኔም እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ” (ማቴ. 28፡ 20) በማለት የሱስ ለተከታዮቹ የነገራቸው ቃላት አስከፊውን ግዞት ብቻውን እየተጋፈጠ የነበረውን ዮሐንስ ሳያጽናናው እንዳልቀረ ይታመናል። በዚህ መገለጥ፣ በዚህ የየሱስ “ራእይ” አማካይነት “የመጀመሪያውም የመጨረሻውም” የሆነው እርሱ፣ በግዞት ለነበረው ሐዋርያ አሁን በተለየ ሁኔታ ራሱን እየገለጠለት መሆኑን ማወቁ ከፍ ያለ መጽናናት ሳያመጣለት አልቀረም። እነዚህን ቁጥሮች ተከትለው የቀረቡት--የወደፊቱን ዓለም ሁኔታ የሚገልጹ ራእዮች ናቸው። አስደናቂ የታሪክ ገጽታ የተላበሰ ትዕይንት በፊቱ ያልፋል። ይህ ለእኛ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ሲሆን ለእርሱ ደግሞ ትንቢት ነበር።

ዮሐንስ በራእይ የተገለጠለት ወደፊት የሚመጡት ፈተናዎች እና መከራዎች ብቻ ሳይሆኑ፣ ሁሉም እንደሚያከትሙ ጭምር ነበር፡ “ከዚህ በኋላ አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር አየሁ፤ የመጀመሪያው ሰማይና የጀመሪያይቱ ምድር ዐልፈዋልና፤ ባሕርም ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም። ቅድስቲቱ ከተማ፣ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ለባሏ እንደ ተዋበች ሙሽራ ተዘጋጅታ ከሰማይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ስትወርድ አየሁ።” (ራእ. 21፡1-2)።

ዮሐንስ በራእይ መጽሐፍ የጻፈው ታላቁ የዳግም ምጽአት መገለጥ፣ በአምላካዊው በጎነትና የተስፋ ቃል ላይ ልበ ሙሉ ሆኖ እንዲያርፍ ረድቶታል። ሕይወት በዚህ ዘመን ከባድ ሊሆን ቢችልም--አልፎ አልፎ ከዚህ በባሰ አስፈሪ ሆኖ ልናገኘው እንችላለን። ሆኖም እግዚአብሔር የወደፊቱን የሚያውቅ አምላክ መሆኑን መገንዘባችንና ማብቂያ የሌለው የወደፊቱ ዘመን መልካም መሆኑን ማወቃችን እንዴት ሊያጽናናን ይችላል?

መስከረም 10
Sep 20

ትንቢታዊ የጊዜ ሠሌዳ


በደብረ ዘይት ተራራ ሆነው፣ ደቀ መዛሙርቱ ለየሱስ ላቀረቡለት ጥያቄ መልስ ሲሰጣቸው፣ በግዙፉ ሸራ ቡሩሹን እየሞነጫጨረ ውስጡ ያለውን ምስል እንደሚያስቀምጥ ሠዓሊ የወደፊቱን የምድር ታሪክ ገጽታ ቁልጭ አድርጎ አቀረበላቸው፡ “ ‘እስቲ ንገረን፤ የምትለው ሁሉ መቼ ይሆናል? የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ ምልክትስ ምንድን ነው?’ ” (ማቴ. 24፡3)። በማቴ. 24 የምናገኘው ዝነኛው የየሱስ ስብከት ከዚያን ዘመን እስከ ዳግም ምጽአቱ፣ ብሎም ከዚያ ባሻገር ያለውን ዘመን ሳያቆራርጥ የዳሰሰ ነው። የሱስ በተለያዩ ዘመናት የሚኖሩ ሕዝቦቹ ስለ ምድር መጨረሻ ትንቢቶች መለኮታዊ ውጥን ከሞላ ጎደል የሚገልጽ ምስል ሊሰጣቸው ፈለገ። ለዚህ መንስዔው በተለይ በመጨረሻው ዘመን የሚኖሩ ሕዝቦቹ ለመጨረሻው ክስተት መዘጋጀት ይችሉ ዘንድ ነው። በዙሪያችን የሚገኝ ማንኛውም ነገር ሊፈራርስ ቢችል እንኳ በልበ ሙሉነት በፍቅሩ ላይ እንድናርፍ ፍላጎቱ ነው።

ሰባተኛ ቀን የዳግም ምጽአቱ ተጠባባቂዎች “መንግሥታት ከተመሠረቱበት ጊዜ ጀምሮ እስከዚያ ዘመን ድረስ ታይቶ የማይታወቅ ታላቅ የመከራ ጊዜ ይሆናል” (ዳን. 12፡1) በሚል በዳንኤል የቀረበውን መግለጫ ጠንቅቀው ያውቃሉ። የሱስ ከዳግም ምጽአቱ አስቀድሞ ላለው ለዚህ ክስተት እንድንዘጋጅ ይፈልጋል።

ዳግም ምጽአቱ ምን ይመስላል? እንዳንታለል ምን ማድረግ እንችላለን? ማቴ. 24፡4-8፣23-31።



የየሱስ ዳግም ምጽአት በጊዜው መጨረሻ ላይ በተጨባጭ ገቢራዊ የሚሆን ክስተት ነው። የሱስ በስብከቱ ሳይቀር በመጥቀስ ስለ ዳግም ምጽአቱ ትንቢት የሰጠውን ቦታ ከግምት በማስገባት ለዚህ ታላቅ ጉዳይ ከፍ ያለ አጽንኦት መስጠት ተገቢ ነው። ለመጨረሻ ጊዜ መላውን ዓለም ያካተተ የአየር ንብረት ለውጥ በተከሰተ ጊዜ ከዘመኑ የዓለም ሕዝቦች መሃል ከጥፋቱ ለመትረፍ ዝግጁ ሆነው የተገኙት ስምንት ሰዎች ብቻ ነበሩ። የሱስ በድንገት ገቢራዊ የሚሆነውን ዳግም ምጽአቱን ከዚህ ክስተት ማለትም ከጥፋት ውሃ ጋር በማነጻጸር አቅርቦታል (ማቴ. 24፡37-39)። ምንም እንኳ ዳግም የሚገለጥበትን ቀን ወይም ሰዓት ማንም ባያውቅም (ማቴ. 24፡36)፤ እግዚአብሔር በዙሪያችን ባለው ዓለም ውስጥ ሲከናወን ልንመለከት የምንችለውን ትንቢታዊ የጊዜ ሠሌዳ ሰጥቶናል። በዚህ ትንቢታዊ ተውኔት የምንሞላው ሚና ተሰጥቶናል።

የእኛ ድርሻ ምንድን ነው--ማቴ. 24 9–14?



በዚህ መላውን ምድር ያካተተ ተጋድሎ እኛ ከታዛቢዎች በላይ ነን። ወንጌልን እስከ ዓለም ዳርቻ በማሰራጨቱ ረገድ ንቁ ተሳታፊዎች መሆን አለብን። ይህ ደግሞ እኛም ስደት ይገጥመናል ማለት ነው። “እስከ መጨረሻው መጽናት” ፍቺው ምንድን ነው? ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? ብዙዎች እንዳደረጉትና እያደረጉ እንዳሉት ላለመውደቅ በየቀኑ ምን ዓይነት ምርጫዎች ማድረግ ያስፈልገናል?

መስከረም 11
Sep 21

ጊዜአቸውን ጠብቀው የሚገለጡት ክስተቶች


ፍጹም ልንቆጣጠር የማንችላቸው ክስተቶች በየተራ እየተገለጡ የሚስተዋሉበትን ከፍ ያለውን የታሪክ ትንቢታዊ ሥዕል ችላ ብለንና እጆቻችንን አጣጥፈን፣ ከኋለኛው ወንበር እንድንቀመጥ አይፈቀድልንም። ብዙዎች በዚህ ዙሪያ ያላቸው አመለካከት “ደህና፣ የመጨረሻዎቹ ክስተቶች በተተነበየው መሠረት ሊፈጸሙ ነው፣ እንግዲህ ዝም ብለን ከሁናቴዎቹ ጋር ከማዝገም ባለፈ ምን ማድረግ እንላለን? ደግሞስ እኔ ብቻዬን ምን ማድረግ እችላለሁ?” ይሁን እንጂ ክርስቲያኖች በዙሪያቸው ካለው ዓለም፣ በተለይም ከመጨረሻዎቹ ክስተቶች ጋር ራሳቸውን ማቆራኘት የሚኖርባቸው በዚህ መልኩ አይደለም።

ራእ. 14 እንደሚነግረን--በዚህ የታሪክ ክፍል የእኛ ዓላማ ስለ አምላካዊው ፍርድ ለሌሎች መንገር እና ለየሱስ ዳግም ምጽአት እንዲዘጋጁ መርዳት ነው። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 14፡6-12። በዚህ ክፍል የቀረበው አስተምህሮ ምን ይመስላል? ለዓለም የምናውጀው ምንድን ነው? ይህ መልእክት ለምን አጣዳፊ ሆነ?



እንደ ሰባተኛ ቀን የዳግም ምጽአቱ ተጠባባቂነታችን በተለይ “የሦስቱ መላእክት መልእክት” ብለን በምንጠራቸው ቁጥሮች ውስጥ ወቅታዊው እውነት (2ኛ ጴጥ፣ 1፡12) እንዳለ እናምናለን። በዚህ ስፍራ፣ በምንገኝበት የምድር ታሪክ የጥሪያችንን መሠረታዊ ነጥብ ምንነት እናገኛለን። የሚጀምረው--“ዘላለማዊ ወንጌል” በሆነው የክርስቶስ ሞት እና ትንሣኤ አስደናቂ ዜና መሆኑን እና ብቸኛው የመዳኛ ተስፋችን የሚያርፈው በዚህ ላይ እንደሆነ ልብ ይሏል። ደግሞም “የፍርዱ ሰዓት ደርሶአልና” (ራእ. 14፡7) የሚል መልእክት ያለ ሲሆን፣ ይህም የመጨረሻውን ጊዜ በብርቱ የሚያመላክት ነው።

በባቢሎን ቀርተው “ለአውሬውና ምስሉ” አምልኮ ለሚያቀርቡ ከተሰጠው አስፈሪ ማስጠንቀቂያ በተቃራኒ “ሰማይንና ምድር የፈጠረውን” አምላክ እንድናመልክ የቀረበ ጥሪ አለ። በመጨረሻ የእግዚአብሔርን የመጨረሻው ጊዜ ሕዝቦች ገላጭ መልእክት አለ፡ “የእግዚአብሔርን ትእዛዛት የሚጠብቁና ለኢየሱስም ታማኝ ሆነው በትዕግሥት የሚጸኑ ቅዱሳን የሚታወቁት በዚህ ነው።”

ጥቅሱን ያንብቡ፡ ራእ. 14፡11። ለአውሬውና ምስሉ የሚሰግዱ ሁሉ ዕረፍት የሌላቸው መሆኑን አስመልክቶ ጥቅሱ ምን ይላል?



ለአውሬውና ለምስሉ የሚሰግዱ ሁሉ ቀንና ሌሊት ዕረፍት የላቸውምን? ይህ ምን ማለት እንደሆነ አስመልክቶ የተለያዩ ሐሳቦች ሊኖሩ ቢችሉም ጌታ ለእርሱ ታማኝ ለሆኑ ሰዎች የሚያቀርብላቸው ዓይነት ዕረፍት እንደማያጋጥማቸው ሁሉም ይስማማሉ። የሦስቱ መላእክት የመጀመሪያው ክፍል መልእክት “የዘላለም ወንጌል” የሆነው ለምንድን ነው ብለው ያስባሉ? እነዚህን መልዕክቶች ለዓለም ስናውጅ ይህን አስደናቂ እውነት ሁሌም ከፊት ማስቀደም ያለብን ለምንድን ነው? ወንጌልን መረዳት የዕረፍት ጽንሰ ሀሳብ ማዕከላዊ አካል የሆነው እንዴት ነው?

መስከረም 12
Sep 22

በሰላም ማረፍ


ክርስቲያኖች የክርስቶስን ዳግም መገለጥ ለአያሌ መቶ ዓመታት ሲጠባበቁ ኖረዋል። ይህ በእውነቱ የሁሉም ተስፋዎቻችን ፍጻሜ ነው--የእኛ ብቻ ሳይሆን በዘመናት ታማኝ ሆነው ያለፉ የእግዚአብሔር ሕዝቦች ጭምር! ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዕብ. 11፡13-16። ለቀደሙት ሕዝቦች ብቻ ሳይሆን ነገር ግን ለእኛም የሚበጅ ምን ዓይነት ታላቅ ተስፋ ቀርቦአል?



በብዙዎች ዘንድ የተለመደው የሞት እሳቤ እውነት ቢሆን ኖሮ እነዚህ ጥቅሶች ትርጉም የለሽ በሆኑ ነበር። “የተስፋ ቃል ሳያገኙ” በሚል ጥቅሱ እየተናገረ ያለው ነገር ምንድን ነው? እነዚህ ሰዎች ሞተዋል። ቢሞቱም--አሁን በሰማይ ከየሱስ ጋር በታላቁ ሽልማታቸው ሐሴት እያደረጉ ነው--የሚል ዓይነት አነጋገር የተለመደ ነው። ይህ አባባል በተለይ ወንጌላዊው ቢሊ ግራሃም እንደሞቱ፣ በሰማይ ከየሱስ ጋር መሆናቸው በተደጋጋሚ ሲነገር ሰምተናል። ይህን አመለካከት ተከትሎ የሚስተዋል ሌላ አንድ ምጸታዊ አባባል ያለ ሲሆን ይኸውም ሰው ሲሞት “በሰላም ይረፍ” ሲባል መስማታችን ነው። ምን ለማለት ተፈልጎ ነው? እነዚህ ሰዎች በሰላም እያረፉ ነው ወይስ በሰማይ ማድረግ ያለባቸውን ሁሉ እያደረጉ ነው--(ለምሳሌ በምድር የሚደረጉትን “አዝናኝ” ትዕይንቶች መከታተል)?

የሱስ ሞትን እንዴት ነበር የገለጸው? ዮሐ. 11፡11



እንደ እውነቱ ከሆነ “በሰላም የማረፍ” ጽንሰ ሀሳብ በሞት ወቅት ገቢራዊ የሚሆን እውነታ ነው--አይደል? የሞተ ሰው በዕረፍት ላይ መሆኑ እሙን ነው። “ለሚያምን ሰው ሞት ከባድ ነገር አይደለም። ክርስቶስ ሞት የአጭር ጊዜ ጉዳይ መሆኑን ይናገራል። ‘ቃሌን የሚጠብቅ ከቶ አይሞትም።’ ‘ሕይወታችሁ የሆነው ክርስቶስ በሚገለጥበት ጊዜ እናንተም ከእርሱ ጋር ትገለጣላችሁ፤ የክብሩም ተካፋዮች ትሆናላችሁ’” ዮሐ. 10፡10፣ 4፡14፣ 6፡54። የዘመናት ምኞት ገጽ፡ 836።

በሞት እና በትንሣኤ ጠኋት መካከል የሚገኘውን ሰው ሁናቴ የሱስ አቅልን የሳተ እንቅልፍ አድርጎ ያቀርበዋል (ዮሐ. 11፡11፣14)። ሆኖም የዳኑትም ሆኑ የጠፉት ከትንሣኤ በኋላ የተዘጋጀላቸውን እንደሚቀበሉ አጽንኦት ሰጥቶ ይናገራል (ዮሐ. 5፡28-29)። ሞት በየትኛውም ጊዜ ቢመጣ ተዘጋጅቶ መገኘት በጣም አስፈላጊ መሆኑን አበክሮ ይናገራል። በሞት የተለዩዎ የሚወዷቸው ወገኖች በእርግጥ አሁን ዕረፍት ላይ መሆናቸውን ማወቅዎ ምን ያህል ያጽናናዎታል?

መስከረም 13
Sep 23

ምን ጊዜም በጌታ ደስ መሰኘት


በዘመናዊ ስልኮቻችን በእጅጉ ጥቅም ላይ ከዋሉ መተግበሪያዎች አንዱ የጉግል ካርታ መተግበሪያ ነው። ዓለማቀፍ የመሬት አቀማመጥ ሥርዓተ ማንበቢያ ወይም የጂፒኤስ ጠቋሚ ካርታዎች በስልኮቻችን ላይ ከመገጠማቸው አስቀድሞ እንዴት እንደ ነበርን ብዙዎቻችን ማስታወስ አንችልም። ከዚህ በፊት ሄደንባቸው ወደማናውቃቸው ስፍራዎች ለመሄድ የግርታና ፍርሐት ስሜት ሊንጸባረቅብን ቢችልም ነገር ግን የጉግል ካርታ (ጉግል ማፕስ) በስልኮቻችን ላይ መኖር በማንኛውም የማናወቀው አገር በልበ ሙሉነት ወዲህ ወዲያ መንቀሳቀስ አስችሎናል። ታዲያ ይህ መተማመን እግዚአብሔር በትንቢታዊ የጊዜ ሰሌዳው ሊሰጠን የፈለገው ዕረፍት ማሳያ ሊሆን ይችላልን? አልፎ አልፎ መተግበሪያችን ላይ የተሳሳተ አድራሻ ልንከት እንችላለን ወይም አቅጣጫውን እናውቀዋለን ብለን ስለምናስብ መመሪያዎቹን ላለመከተል እንወስን ይሆናል። ብቻ በዚህም ይሁን በዚያ፣ መጨረሻችን የማንፈልገው ሰፍራ ሊሆን ይችላል--ይህ በአብዛኛው የሚሆነው በዕረፍት ማዕቀፍ ውስጥ ባላደረ አዕምሮ ውስጥ ስንወድቅ ነው።

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ፊልጵ. 4፡4-6። በዚህ በጥድፊያ የተሞላና ህመም ያልተለየው ዓለም ውስጥ ሆነንም እንኳ--እውነተኛ ዕረፍት እና ሰላም ማግኘት ስለሚቻልበት መንገድ ጳውሎስ ምን እያለን ነው?



በጥቅሱ ጳውሎስ በሚገጥሟችሁ ፈተናዎች ሁሉ ምንጊዜም ደስ ይበላችሁ እያለ አይደለም። ይልቁንም “ምን ጊዜም በጌታ ደስ ይበላችሁ” ይለናል። አሁን ያለንበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን፣ የቱንም ዓይነት ፈተናዎች እያጋጥሙን ቢገኙም፣ በእግዚአብሔር ቸርነት፣ በፍቅሩ እና በመስቀል ላይ መሥዋዕትነቱ ብናተኩር--በእርሱ ደስ ይለናል፣ ለደከሙ ነፍሶቻችንም ሰላም እናገኛለን። የጥቅሱ ቃና ዕረፍትን፣ ሰላምንና ከዚህ ዓለም ባሻገር ሊገኝ የሚችል በሐሴት የተሞላ ተስፋን ያመለክታል።

በተጨማሪ እንደው “በከንቱ ተጨንቀን” ለነፍሳችን ምን ዓይነት ዕረፍት ልናመጣ እንደምንችል አሰብ ያደርጉ። ይህ በዚህ ዓለም ላለ ማንኛውም ሰው ትክክለኛ ቢመስልም (ጳውሎስ እንኳ ብዙ የሚያስጨንቁት ነገሮች ነበሩ)፤ ነገር ግን ውሎ አድሮ ሁሉም ነገር በአፍቃሪው አምላክ ቁጥጥር ስር መሆኑንና የመንግሥቱ ወራሾች አድርጎ እንደሚያድነን በድጋሚ መገንዘብ መቻላችን፣ የሚያስጨንቁንን ነገሮች በትክክለኛው መነጽር እንደንመለከት ይረዱናል። “ጌታ ቅርብ ነው”? አባባሉ እርሱ ሁሌም አጠገባችን መሆኑን ይገልጻል። ዐይኖቻችን ተጨፍነው በሞት እንቅልፍ ዕረፍት ውስጥ እንደገባን በቀጣይ የምናውቀው ነገር ቢኖር የክርስቶስን ዳግም ምጽአት ነው።

ሕይወት በውጥረት፣ በፈተና እና በትግል የተሞላ መሆኑ አጠያያቂ አይደለም። ሐዋርያውን ጳውሎስ ጨምሮ ማናችንም ብንሆን ከዚህ አናመልጥም (2ቆሮ. 11)። የሆነው ሆኖ፤ አሁን በብዙ ሁናቴዎች ውስጥ ብናልፍም በክርስቶስ በተሰጠን ነገር ሐሴት ማድረግ እንችላለን፣ አሁንም እንኳ ቢሆን ለነፍሳት ዕረፍት ማግኘት መቻላችን እውነት ነው--የሚል ጠቅለል ያለ ሀሳብ የጳውሎስ መልእክት ይዞአል። በድጋሚ ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ፊልጵ. 4፡4-6። የቱንም ዓይነት ፈተና እና መከራ ቢገጥሞትም እንኳ እነዚህን ድንቅ ቃላት ተግባራዊ ሊያደርጉ የሚችሉባቸው መንገዶች የትኞቹ ናቸው?

መስከረም 14
Sep 24


ተጨማሪ ሀሳብ


“ሁላችንም ለጸሎታችን ፈጣንና ቀጥተኛ መልስ ለማግኘት ስለምንመኝ፣ መልስ ሲዘገይ ወይም ባልታወቀ ቅርጽ ሲመጣ ተስፋ እንቆርጣለን። እግዚአብሔር ግን ሁሌም በተባለው ጊዜና በተመኘነው መንገድ ለጸሎታችን መልስ ለመስጠት እጅግ በጥበብ የተሞላና መልካም አምላክ ነው። ምኞቶቻችንን ሁሉ ከመፈጸም ባሻገር ለእኛ የላቀና የተሻለ ነገር ያደርግልናል። በጥበቡ እና በፍቅሩ ላይ መመካት ከመቻላችን አኳያ ለእኛ ፈቃድ እንዲገዛ መጠየቅ ሳይሆን--የዓላማው አካል ለመሆንና ያን ለመፈጸም መሻት ይኖርብናል። ምኞቶቻችንም ሆኑ ፍላጎቶቻችን በፈቃዱ ውስጥ ሊሰወሩ ይገባል።”—Ellen G. White, Gospel Workers, p. 219.

“የሱስ ልጆቹን ለማዳንና የማይሞተውን አካል ለመስጠት ሊገለጥ የቀረው ጊዜ ጥቂት ብቻ ነው… መቃብሮች ተከፍተው የሞቱ ወገኖች በድል አድራጊነት “ሞት ሆይ፤ ድል መንሣትህ የት አለ? መንደፊያህስ የት አለ?” እያሉ በታላቅ ድምፅ ይነሣሉ። በየሱስ ያንቀላፉ የምንወዳቸው ሁሉ እነሆ የማይሞተውን ለብሰው ይነሣሉ።”—Ellen G. White, Counsels on Stewardship, p. 350.


የመወያያ ጥያቄዎች



፡ 1.ስለ ታላቁ ተጋድሎ ተጨባጭ እውነታ አሰብ ያድርጉ። ይህን በዓለም ላይ እየተተወነ ያለ ትዕይንት እንዴት ይመለከቱታል? ከግል ሕይወትዎ አኳያ ሲመለከቱት--በገሃድ የሚስተዋል አይደል? አብዛኛው በለጸግን የሚለው ዓለም ዲያብሎስ የሚባል ነባራዊ ፍጡር የለም ብሎ ቢያስብም፣ ብዙዎች ከሚገምቱት በላይ ተጨባጭነት ያለው እውነታ ነው። የዓለማችንን ሁኔታ መረዳት እንችል ዘንድ የታላቁን ውዝግብ እውነታ ማስተዋላችን በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ደግሞም--ይህ ታላቅ ውዝግብ እንዴት እንደሚጠናቀቅ መረዳታችን ለምን ያጽናናል?

2.በግልጽ ከተገለጠው በላይ ለመሄድ የምንሞክር ከሆነ ትንቢት ጥፋት የሚያስከትል ሊሆን ይችላል። የማይፈጸሙ ትንቢቶች በመነገራቸው ወይም ባልሠመሩ ትንቢቶች በማመናቸው የተነሣ የቤተ ክርስቲያን አባላት ስንት ጊዜ ችግር ውስጥ ገብተዋል? እንዲህ ዓይነት ወጥመድ ውስጥ ከመውደቅ ራሳችንን መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው?

3.በሰንበት ትምህርት ጥናታችሁ ወደ ራእ. 14፡9-11 በማምራት ለአውሬውና ለምስሉ የሚሠግዱ ዕረፍት እንደሌላቸው የሚገልጸውን ክፍል ይመልከቱ። ይህ ምን ማለት ሊሆን ይችላል?

የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት መምሪያ የትንቢት መንፈስ መጻሕፍትን ተርጉሞና አሳትሞ ማሰራጨት ለሚፈልጉ የተደራጁ ቤተክርስቲያናት ሆነ ፈቃድ ያላቸው ደጋፊ የአገልግሎት ድርጅቶች የተሠጠ ማሳሰቢያ

የትንቢት መንፈስ ( Spirit of Prophecy - SOP) መጻሕፍት በሙሉ የሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት አለም አቀፍ ቤተክርስቲያን ንብረት ናቸው፡፡ እነዚህን ጽሁፎች በከፊልም ሆነ በሙሉ ወደ አማርኛም ሆነ ወደ ተለያዩ የአገሪቱ ቋንቋዎች በማስተርጎምና በማሳተም ለማዳረስ የሚፈልግ የተደራጀ ቤተክርስቲያንም ሆነ በዋናው መስሪያ ቤት ፈቃድ ያለው ደጋፊ የአገልግሎት ድርጅቶች ሥራውን ከመጀመሩ በፊት የኢትዮጵያ ዩኒየን ሚሽን በበላይነት በሚያስተዳድራቸው ሰበካዎችና ኮንፍራንስ የጽሁፍ ክፍል ጥያቄውን በጽሑፍ በማቅረብና በአካልም ቀርቦ በመወያየት ወደ ሰምምነት ከተደረሰ በኋላ እንዲያስተረጉም ፈቃድ ይሰጠዋል ትርጉሙም ሲጠናቀቅ የመጽሐፉን የመጀመሪያ ገጽ በታተመ ወረቀትና ሙሉውን መጽሐፍ በሲዲ ካስረከበ በኋላ ህትመቱና ስርጭቱ በድርጅቱ መተዳደሪያ ደንብ መሠረት ተከናውኖ ሥራውን መፈፀም ይቻላል፡፡

በዚሁ መሠረት የትንቢት መንፈስ ጽሁፎችን በማሳተም ወንጌልን ለማዳረስ የሚጥሩ የተደራጁ ቤተክርስቲያናት ሆነ ፈቃድ ያላቸው ደጋፊ የአገልግሎት ድርጅቶች በእጅጉ ይበረታታሉ፡፡ ሆኖም ግን ይህንን በመተላለፍ ያለ ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ዓለም አቀፍ ቤተ ክርስቲያን ፈቃድ በቤተክርስቲያኗ ስም የትንቢት መንፈስ ጽሁፎችን አሳትሞ ማስራጨት፣ በአገሪቱም ሆነ በዓለም ዓቀፍ የሥነ ጽሁፍ ህግ ያስጠይቃል፡፡ በተጨማሪም ድርጅቱ እያስተረጎመ ያለውን መጽሐፍ ሌላ አካል ተመሳሳዩን መጽሐፍ በመተርጎም ላልተፈለገ የጊዜ፣ የጉልበትና የገንዘብ ወጪም ይዳርጋል፡፡ ሰለሆነም የቤተክርስቲያኗ ህግና መተዳደሪያ ደንብ በሚፈቅደው መሠረት ሁላችንም ጽሁፎችን በማሳተምም ሆነ በማሰራጨት የሶስቱን መላዕክት መልዕክት ለማዳረስ እንድንችል ጌታ ይርዳን፡፡ ድርጅቱ




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA union SSL