የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

በክርስቶስ ማረፍ


3ኛ ሩብ ዓመት 2021

ከነሐሴ 8– 14

8ኛ ትምህርት

Aug 14–Aug 20




ለማረፍ ነጻ መሆን



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ማር. 2:1–12፣ 1ነገሥ. 18፣ 1ነገሥ. 19:1–8፣ ማቴ. 5:1–3፣ ኢሳ. 53:4–6፣ 2ነገሥ. 2:11።


የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ “እግዚአብሔር ብርሃኔና መድኅኔ ነው፤ የሚያስፈራኝ ማን ነው? እግዚአብሔር ለሕይወቴ ዐምባዋ ነው፤ ማንን እፈራለሁ? (መዝ. 27፡1)

የ ሱስ በምድራዊ አገልግሎቱ ከተገናኛቸው ሰዎች መሀል አብዛኞቹ የታመሙ፤ አልፎ አልፎም የሞቱ ነበሩ። ፈውስ ለማግኘትና ከሥቃያቸው ለማረፍ ያጨናንቁት ነበር። በዚህም ሕዝቡ ሁሌም የሚሻውን ያገኝ ነበር። አንዳንዴ አንድ ቃል ብቻ መናገሩን ተከትሎ ሙሉ ፈውስ ያገኙ ነበር። ሌላ ጊዜ ደግሞ የታመሙትን ሲነካ፣ ታምራዊ ፈውስ ያገኙ ነበር። በሌላ አጋጣሚ ደግሞ ካሰናበታቸው በኋላ በመንገድ እያሉ ፈውስ ያገኙ ነበር። የሱስ ወንዶችን፣ ሴቶችን፣ ህፃናትን፣ አይሁዶችን፣ አይሁድ ያልሆኑትን፣ ሐብታሞችን፣ ደኻዎችንና ምስኪኖችን ፈውሷል። በወቅቱ የከፉ ተደርገው ይታዩ የነበሩት ቁምጥና እና ዐይነ ሥውርነት ከእርሱ አቅም በላይ አልነበሩም። ከዚህ በላይ--ከህመም ሁሉ የገዘፈውን ሞት ሳይቀር ፈውሷል።

በዚህ ሳምንት ሁለት በጣም የተለያዩ የፈወስ ምሳሌዎችን እንመለከታለን። በአንደኛው--በሽተኛው በጣም ከመታመሙ የተነሳ ራሱን ችሎ ወደ የሱስ መምጣት እንኳ ተስኖት ነበር። የበሽታው ምልክቶች ሁሉም ሰው በግልጽ የሚያያቸው ነበሩ። በሌላኛው ላይ ግን--አንዳችም የሚታዩ የበሽታ ምልክቶች አልነበሩም። ሆኖም በእግዚአብሔር ጊዜና መንገድ ሁለቱም ፈውስ አገኙ። የዕረፍትን ርዕሰ ጉዳይ ከህመምና ሥቃይ ዐውድ ስንመረምር፣ ሁላችንም በአንድ ወይም በሌላ ወቅት በክርስትና ጉዟችን ያጋጠመንን ጥያቄ እናሰላስላለን። በፈውስ ዙሪያ ያቀረብነው ጸሎት መልስ ሳያገኝ ሲቀር ምን ይከሰታል?

ነሐሴ 9
Aug 15

በዕረፍት መፈወስ


ዕረፍት በእጅጉ የሚያስፈልገን ህመም ሲሰማን ነው። ሰውነታችን በሽታ የመከላከል አቅሙን ያጠናክር ዘንድ አካላዊ ዕረፍት ያስፈልገናል። ደግሞም፣ ብዙውን ጊዜ የአእምሮ ዕረፍት ያስፈልገናል። አንዳንዴ እንደ ጉንፋንና ራስ ምታት ዓይነት ለሕይወት አስጊ ያልሆኑ የህመም ስሜቶች ይገጥሙናል። ጋደም ብለን ማድረግ ስላለብን ነገሮች ላለማሰብ ብንሞክርም አይሆንልንም።

አልፎ አልፎ ለሕይወት አስጊ ህመም ሲገጥመን፤ የህክምና ውጤታችን ምን ሊሆን እንደሚችል ስለሚያሳስበን፣ ለወጉ ብንተኛም ዕንቅልፍ ባይናችን አይዞርም። ብዙውን ጊዜ ይህ ስለ ምን ሆነ ብለን ማሰላሰል እንጀምራለን። ጤነኛ ያልሆነው የአኗኗር ዘይቤ በመጨረሻ ጠልፎ ጣለን? ከ20 ዓመት በፊት የወሰድናቸው ጎጂ ዕጾች ይሆኑ? ባለፉት ጥቂት ዓመታት የመጣው ውፍረት፣ ተጨማሪ ክብደት ምክንያት ይሆን? እግዚአብሔር አምላክ ማንም በማያውቀው በዚያ የተሰወረ ኃጢአት መዘዝ እየቀጣን ይሆን? ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ማር. 2፡1-4። በታሪኩ የተከሰተው ምንድን ነው?



በዚህ ታሪክ የቀረበው ሽባ ሰው ሁናቴ ተጨባጭ ክስተት ነበር። በዘመናት ምኞት፡ ከገጽ 271–377 የታሪኩን የኋለኛ ክፍል እናገኛለን። ሽባው ሰው አንዳንድ የማይኮራባቸውን ነገሮች አድርጓል። ኃጢአተኛ ሕይወቱ ለዚህ በሽታ እንደ መንስዔ ተደርጎ ተቆጥሯል። በመሆኑም የኃይማኖት አስተምህሮ ጠበብት፣ መንስኤ እና ውጤትን ያማከለ ቀጥተኛ መስመር በማስመር--ይህን በሽታ በራሱ ላይ ያመጣው በገዛ ኃጢአቱ ስለሆነ ፈውስ የለውም--ብለው ደምድመዋል።

ይህ ዓይነቱ አመለካከት በጣም የተለመደ ሊሆን ይችላል። ብዙውን ጊዜ ይህን ያደረገው ማን ነው እያልን እንብሰለሰላለን። ወንጀል ከተሠራ አንድ ሰው የዚያን ዋጋ መክፈሉ የግድ ይሆናል። የሆነ ቦታ አደጋ ቢከሰት በጉዳዩ ክስ የሚመሰረትበት የሆነ ሰው መኖር አለበት። ይሁን እንጂ ሰበብ መደርደር ለታመመው ፈውስ አያመጣም። የእግዚአብሔር የመጀመሪያ ሰብዓዊ ንድፍ ህመም፣ በሽታና መከራ ያካተተ አልነበረም። በሽታ ወደዚህች ምድር የመጣው የኃጢአትን መግባት ተከትሎ ነበር። ዛሬ ምርጥ በሆነ የህይወት ዘይቤ ሐሴት እናደርግ ዘንድ እነሆ እግዚአብሔር የጤና መመሪያዎችን ሰጠን። ይሁን እንጂ በኃጢአት በታወከው በዚህ ዓለም እስከ ኖርን ድረስ፣ የቱንም ያህል ጤናማ የሆኑ መርኅዎችን በትጋት ብንከተልም፣ የጤና ዋስትና ሊሆኑን አይችሉም።

ጥሩው ዜና ቢያመን ወይም ጤናማ ብንሆን እግዚአብሔር ዕፍት ሊሰጠን መቻሉ ነው። ህመማችን የራሳችን ሥራ ውጤት ይሁን ወይም የሌላው ቸልተኝነት፣ ሰብዓዊው ዘረመል ወይም በኃጢአተኛው ዓለም የመኖራችን መንስዔ--እግዚአብሔር ግን እንዴት ዕረፍት ሊሰጠን እንደሚችል ያውቃል። አንድ ሰው ሲታመም በዚህ ምክንያት ነው እያሉ ሰበብ መደርደርና ማላከክ መጀመር ጥሩ አይደለም። በሌላ በኩል የህመሙን መንስዔ መረዳት አንዳንዴ ለፈውስም ሆነ ለማገገም ወሳኝ እርምጃ ሊሆን የሚችለው ለምንድን ነው?

ነሐሴ 10
Aug 16

ከሥረ መሥረቱ ማከም


ሽባው የተኛበትን አልጋ የሱስ ባለበት በኩል ቁልቁል ሲያወርዱ፣ የሁሉም ዐይኖች በየሱስ ላይ ተተክለው ነበር። በእርግጥ ኃጢአተኛ የሆነውን ይህን ሰው መፈወስ ይመርጥ ይሆን? አንድ ቃል ተናግሮ በሽታውን ይገስጽ ይሆን? የሱስ ሽባውን የፈወሰበት መንገድ ምን ይመስላል? በመጀመሪያ ያደረገለት ነገር ምንድን ነው? ማር. 2፡5–12



ብዙውን ጊዜ የአንድን በሽታ ምልክቶች ከማስተዋላችን በፊት ስለ በሽታው ምንም ማለት አንችልም። ስለዚህ በሽታውን እንደ ምልክት እንቆጥረዋለን። ከበሽታዎቹ ምልክቶች ነጻ መሆንን፤ ፈውስ እንደ ማግኘት እንቆጥረዋለን። የሱስ በሽታን የሚመለከትበት መንገድ ግን ከዚህ የተለየ ነው። እርሱ የእያንዳንዱን ሥቃይና ደዌ ሥረ መሠረት ጠንቅቆ ስለሚያውቅ ይህን አስቀድሞ ማከም እንዳለበት ያውቃል።

ሽባውን ሰው አስመልክቶ በሽታው ያስከተላቸውን ይፋዊ ውጤቶች ወዲያውኑ ከማከም ይልቅ፤ ሰውየውን አብልጦ ወደ ሚያስጨንቀው ነገር መነሾ በቀጥታ ያመራል። ሽባው ሰው በሽታው ካስከተለበት ሥቃይ ይልቅ የጥፋተኝነት እና ከእግዚአብሔር የመለየት ስሜት ደቁሶት ነበር። በእግዚአብሔር የሚያርፍ ሰው በኃጢአት በታመመው በዚህ ዓለም ውስጥ የሚደርስበትን ማንኛውንም ዓይነት አካላዊ ሥቃይ በጽናት መቋቋም ይችላል። በመሆኑም የሱስ በቀጥታ ወደ ችግሩ ሥረ መሠረት በማምራት በቅድሚያ ይቅርታ ይሰጣል። የሱስ ኃጢአቱ ይቅር መባሉን ሲያውጅ የሰሙት የኃይማኖት መሪዎች ተደናገጡ። በልባቸው ያሰላስሉ ለነበረው ክስ መልስ ለመስጠት አንድ ጥያቄ አቀረበ።

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ማር. 2፡8-9። የሱስ በስፍራው ለነበሩ ጸሐፍት ያቀረበው ፈታኝ ሁኔታ ምን ነበር? እርሱ በትክክል እያቀረበ የነበረው ርዕሰ ጉዳይ ምን ይመስላል?



ከአንደበት የሚወጡ ቃላት በአጠቃላይ ሲታዩ ርካሽ ቢሆኑም፤ እግዚአብሔር ሲናገር ግን ነገሩ ከዚህ ፍጹም የተለየ ነው። በእግዚአብሔር በኃይል የተሞላ ቃል እነሆ ሁሉም ነገር ተፈጠረ (ዘፍ. 1)። ምንም እንኳ ይቅር ማለትን በዐይናችን ልናየው የምንችለው ነገር ባይሆንም ከፍተኛ ዋጋ የሚያስከፍል ነው። ይቅር ማለት በመስቀል ላይ የተቸነከረውን የእግዚአብሔር ልጅ ሕይወት ጠይቋል። የተቀረው ሁሉ በሁለተኛ ደረጃ የሚቀመጥ ነው። የሱስ የይቅርታን ኃይል እና እውነታ ለማሳየት ሲል ሽባውን ለመፈወስ መረጠ።

እግዚአብሔር በመጀመሪያ ውስጣችንን መፈወስ ይፈልጋል። እናም አንዳንዴ እንደ ሽባው አፋጣኝ አካላዊ ፈውስ ሊያመጣልን የሚመርጥ ሲሆን፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ አካላዊ ፈውስን እንለማመድ ዘንድ የትንሣኤ ጠዋትን መጠበቅ ሊኖርብን ይችላል። ያም ሆነ ይህ፤ አሁን በመከራችን ወቅትም እንኳን ቢሆን አዳኛችን በፍቅሩ፣ በጸጋውና በይቅርታው ማረጋገጫ ውስጥ ማረፍ እንድንችል ይፈልጋል። ፈውስ እናገኝ ዘንድ የምንጸልየው ጸሎት ባይመለስም እንኳ ዕረፍት እና ሰላም ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው?

ነሐሴ 11
Aug 17

ሽሽት


ከዓለም ጤና ድርጅት (WHO) በተገኘ መረጃ መሠረት በየዓመቱ ከሦስት መቶ ሚሊዮን በላይ ሰዎችን እየጎዳ ያለ በሽታ በአብዛኛው በግልጽ የሚታዩ ምልክቶች የሉትም። ድባቴ ወይም የመንፈስ ጭንቀት በዓለም ዙሪያ ዋንኛው የአቅመ ውሱንነት መንስዔ ሲሆን ለዓለም አቀፉ የበሽታ ጫና የአንበሳውን ድርሻ ይይዛል። የሚያሳዝነው ድባቴ በክርስትና እምነት ውስጥ እምብዛም አይነገርም። ለዚህ ምክንያቱ የእምነት ማነስ ምልክት ተደርጎ መወሰድ መቻሉ ነው። ለነገሩ ክርስቲያኖች ሁሌም በደስታና ሐሴት የተሞሉ ተደርገው ከመታሰባቸው አኳያ--ድባቴ ከእግዚአብሔር ጋር ባለን ግንኙነት መሀል የሆነ እንከን ለመኖሩ ጠቋሚ አይሆንም?

ብዙ ሰዎች ይህ እውነት እንዳልሆነ ያውቃሉ። ታማኝ ክርስቲያኖችም እንኳ በተለይ፣ ከሆነ አሰቃቂ ክስተት በኋላ አልፎ አልፎ ከድባቴ ጋር ሊታገሉ ይችላሉ። ስለዚህ ጉዳዩ የእምነት ጉድለት ወይም በእግዚአብሔር የመታመን ችግር ምልክት ሊሆን አይችልም። አሁንም ቢሆን የመዝሙር መጽሐፍን በማንበብ የአምላክ ታማኝ ሕዝቦች ያለፉበትን ሥቃይ፣ መከራና እንግልት መመልከት ይቻላል። አንዳንድ ጊዜ ድባቴ በዝግታ እና ቀስ በቀስ መዳፉ ያስገባንና፤ ችግሩ መኖሩን የምንረዳው መፈናፈኛ ሲያሳጣን ብቻ ይሆናል። ሌላ ጊዜ ደግሞ በተለይ አስቸጋሪ የሆነ ስሜታዊ ወይም አካላዊ ክስተት ከገጠመን በኋላ በፍጥነት ሊያውከን ይችላል። ለምሳሌ የእግዚአብሔር ታማኝ ነቢይ የነበረው ኤልያስ ከቀርሜሎስ ተራራ ተሞክሮ በኋላ በስሜትም ሆነ በአካል ሙሉ በሙሉ ዝሎ ነበር።

ኤልያስ በ1ነገሥ. 18 እሳት በታምራት ከሰማይ ሲወርድ ተመልክቶ ነበር። ጸሎቱ መልስ ማግኘቱን ተከትሎ--ዝናብ ዘንቦ ለሦስት ዓመት የዘለቀው የድርቅ ዘመን ሲያበቃ ተመልክቷል። ኤልያስ ለኤልዛቤል ዛቻ ምላሽ ሽሽትን የመረጠው ለምንድን ነው? 1ነገሥ. 19፡1-5።



ኤልያስ ያሳለፋቸው እነዚያ ሃያ አራት ሰዓታት እጅግ አስጨናቂ ነበሩ። ይህ ተሞክሮ፣ ከተላከበት የሞት ዛቻና ማስፈራሪያ ጋር ተደማምሮ ኤልያስን ድባቴ ውስጥ እንዲገባ አደረገው። ቁጥራቸው 850 የሚደርስ የበአል ነቢያት በታረዱበት ወቅት ኤልያስ በዚያ የነበረ ሲሆን፤ ምናልባት አንዳንዶቹ በእርሱ እጅ ሳይገደሉ እንዳልቀረ ይታመናል (1ነገሥ. 18፡40)። እንዲህ ያለው ክስተት፣ ጻድቅ ዓላማ ያነገተም እንኳ ቢሆን፤ ትዕይንቱን የሚመለከቱትንም ሆነ--ይባስ ብሎ ደግሞ አድራጊዎቹን አሰቃቂ ድባቴ ውስጥ ሊከት ይችላል።

ስለዚህ ኤልያስ መሸሽና ከስፍራው ርቆ መሄድ ጀመረ። አንዳንዴ ፈጥነን ወደ ምግብ ማቀዝቀዣው አምርተን እንደገና ደስ ብሎን ራሳችንን ለመመገብ እንሞክራለን። አልፎ አልፎ ጋደም ብለን የስሜታችንን መዛል ለማሳረፍ እንሞክራለን። አንዳንድ ጊዜ ለመሄድ ባለን ፍላጎት አዲስ ግንኙነት፣ ሥራ ወይም አካባቢን እናስሳለን። ሌላ ጊዜ ደግሞ ደስታችንን እና ዕረፍታችንን ከሚያሳጣን ይህ ነው ተብሎ ከማይገለጽ ነገር ለመራቅ ብለን ራሳችንን በተጨማሪ ሥራ እና ሥራ ነክ የጊዜ ገደቦችና ቀጠሮዎች እንቀብራለን። ብዙ ሰዎች የድባቴ ህመማቸው እንዲቀንስ ለማድረግ “መድኃኒት” ለመጠቀም መሞከራቸው እሙን ነው። ሆኖም በመጨረሻ እነዚህ ነገሮች የበሽታውን ምልክቶች ከመሸፋፈን ውጪ ችግሩን አይፈቱም። እንደውም በተደጋጋሚ እንደሚስተዋለው ችግሩን ከማባባስ የዘለለ ፋይዳ አይኖራቸውም።

ነሐሴ 12
Aug 18

መሸሽ የማይቻልበት ከባድ ድካም


ኤልያስ በጣም ስለደከመው ከዚህ በላይ መሸሽ የማይችልበት ሁኔታ ላይ ደርሷል። ስለዚህ በድጋሚ ሲጸልይ ይታያል። ይህ ጸሎት ኤልያስ በበአል ካህናትና ነቢያት፣ በሸንጎ አባላት እና በተራው ሕዝብ ፊት ከጸለየውና እግዚአብሔር በቀርሜሎስ ተራራ (1ነገሥ. 18፡36-37) ከመለሰው በእምነት የተሞላ ጸሎት በእጅጉ የተለየ ነው። በመሆኑም ይህ ተስፋ መቁረጥ የሚታይበት ተራና አጭር ጸሎት ነው። ኤልያስ በ1ነገሥ. 19፡4 ከቀደሙት አባቶቹ እንደማይበልጥ ገልጾአል። ስለ ምን እየተናገረ ነበር?



በመጨረሻ ኤልያስ በጸጥተኛ ሁኔታ ላይ ሲገኝ የጥፋተኝነት ስሜት እየደቆሰው እንደነበር እንመለከታለን። የእርሱ ፈጥኖ መውጣት ለእስራኤል ተሐድሶ ታላቅ ዕድል ሊያስገኝ ይችል የነበረውን ነገር ጠልፎ እንዳስቀረ ተንዝቧል። እርሱን የፈለጉትን እንዳሳዘነ ተገንዝቧል። ስለዚህ በዚህ ዙሪያ ምንም የማድረግ አቅም አልነበረውም። ስለ ግል ባሕሪና ድርጊቱ በጥልቀት ባሰበበት እና የገዛ ሕዝቡን ታሪክ ጠንቅቆ ባወቀበት በዚያ የሥቃይ ወቅት እውነተኛ ማንነቱን ተመለከተ። እውነተኛውን ማንነታችንን ማየት--ይህ ለማናችንም ቢሆን ህመም ያለው ትዕይንት ሊሆን አይችልም? ህይወታችን በኃጢአት የተሞላ ቢሆንም እግዚአብሔር የሱስን በሚያይበት ዐይን እኛንም እንደሚያይ ለተሰጠን ተስፋ ምንኛ አመስጋኞች ልንሆን ይገባል! የክርስቶስን ጽድቅ በእምነት የራሳችን የማድረግ ባለ መብት ከመሆን የላቀ ምን ተስፋ ሊኖረን ይችላል? (ፊል. 3፡9)።

የሆነ ሆኖ ድባቴ ራስን የመጥላት ጨለማ አዙሪት ውስጥ ስቦ የማስጠም አቅም አለው። እናም አንዳንዴ ሞትን እንደ ብቸኛ መውጫ መንገድ አድርገን ማሰብ እንጀምራለን። የኤልያስም ጉዳይ ከዚህ የራቀ አይመስልም። ሁሉም ነገር ከአቅሙ በላይ የሆነበት ይመስላል፡ “ ‘እግዚአብሔር ሆይ በቅቶኛል! እኔ ከቀደሙት አባቶቼ አልበልጥምና ነፍሴን ውሰዳት!’ ” (1ነገሥ. 19፡4)። ደስ የሚለው ነገር ታላቁ ፈዋሽ ኤልያስን አያወግዘውም። ከድባቴ ጋር ስንፋለም ከምንገኝበት ሁናቴ አኳያ ከእኛ ይልቅ እግዚአብሔር በተሻለ ይገነዘበናል።

“የቤዛችን ፊት በርኅራኄና በፍቅር ወደ እኛ ማዘንበሉን በተጨባጭ የምንገነዘብበት አስገራሚ ማስረጃ ባይኖረንም፤ ነገሩ ግን እንዲያ ነው። ምንም እንኳ ሲዳስሰን ባይሰማንም፣ የፍቅርና ርኅራኄ እጁ ግን እነሆ በእኛ ላይ ናት”—Ellen G. White, Steps to Christ, p. 97. የምናደርገው የ “ሩቅ መንገድ” ሽሽት ለእኛ እጅግ ረጅም መሆኑን እግዚአብሔር ስለሚያውቅና ስለሚገነዘብ (1ነገሥ. 19፡1) አንዳንዴ ቆም እስክንል መጠበቅ ይኖርበታል። ያኔ ጣልቃ ሊገባ ይችላል።

አንዳንድ ጊዜ ውኃ ውስጥ እየሰጠሙ ያሉ ሰዎች ግራ ከመጋባታቸው የተነሣ ከሕይወት አድን ዋናተኛው ጋር ይተናነቃሉ። በዚህ ጊዜ የሕይወት አድን ዋናተኛው የማዳን ሥራውን መሥራት ይችል ዘንድ እየሰጠመ ያለው ሰው ራሱን መሳት እስኪጀምር ወደ ኋላ ማፈግፈግ ይኖርበታል። ከሚከተሉት ጥቅሶች ምን ዓይነት የተስፋና ማጽናኛ ቃላት ማግኘት ይችላሉ፡ መዝ. 34:18፣ ማቴ. 5፡1-3፣ መዝ. 73:26፣ ኢሳ. 53፡4-6?

ነሐሴ 13
Aug 19

ዕረፍት እና ተጨማሪ ነገር


ኤልያስ ያደረጋቸው ሽሽቶች በሙሉ ድካም ውስጥ እንደከተቱት እግዚአብሔር ያውቃል። ኤልያስ ከደረሰበት አካላዊ ድካም በላቀ ስሜቱ እንደዛለና መጠነ ሰፊ የጥፋተኝነት ስሜት እንደተሸከመ እግዚአብሔር ያውቅ ነበር። ከብዙ ዓመታት በኋላ የሱስ ለሽባው ሰው ከሚያደርገው በተመሳሳይ፤ እግዚአብሔር ኤልያስን አጸዳድቶ ዕረፍት ሰጠው። በመጨረሻ በትክክል መተኛት የሚችልና የሚታደስ ሆነ።

ይህ የታሪኩ መጨረሻ ይሆናል ብለን ልንጠብቅ ብንችልም፤ ነገር ግን አይደለም። የእግዚአብሔር ዕረፍት የአንድ ጊዜ ክስተት አይደለም። ወደ አምላካዊው ዕረፍት መግባት ከፈውስ ጋር የተጎዳኘ እንደመሆኑ--አሉታዊ አስተሳሰቦችንና ጎጂ ልምዶችን ቀስ በቀስ እየሰበርን የምንሄድበት ሂደት ነው። እግዚአብሔር ለፈውስ አይቸኩልም። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ 1ነገሥ. 19፡5-8። ኤልያስ ወዴት እየሄደ ነው? ለምን?



ኤልያስ ዕረፍት ካደረገ በኋላ እንደገና ጉዞውን ቀጠለ። ሆኖም በዚህ ጊዜ እግዚአብሔር የጉዞውን አቅጣጫ ይለውጠዋል። በዚህ ኃጢአተኛ ዓለም ውስጥ መኖር የመንፈስ ጭንቀት ሊያስከትል እንደሚችልና እንደሚያመጣ እግዚአብሔር ጠንቅቆ ያውቃል። ለመሮጥ ያለንን ምኞት የሚያስተውል ቢሆንም፤ የሩጫችንን አቅጣጫ ለመቀየር ይፈልጋል። በራሳችን ላይ ውድመት ለማድረስ ከምንሞክራቸው አስቸጋሪ ትግበራዎች በተቃራኒ ወደ እርሱ እንድንሮጥ ይፈልጋል። እናም አንዴ ወደ እርሱ መሮጥ ከጀመርን ዕረፍት የሚሰጠንን “ለስለስ ያለ ድምፅ” (1ነገሥ. 19፡12) መስማት ሊያስተምረን ይፈልጋል።

ኤልያስ አንገቱን ቀና አድርጎ ከአምላክ ጋር መገናኘት የሚያስችለውን ጉዞ የማድረግ ኃይል አልነበረውም። እግዚአብሔር እርሱን ለመገናኘት የሚያስችለንን ጉልበት ይሰጠናል፣ የተሻለ ነገ ባለቤት እንደምንሆንም ተስፋ ይሰጠናል። ኤልያስ በክትክታው ዛፍ ስር ተቀምጦ ለመሞት ሲመኝ፤ የእርሱ የተሻሉ ቀኖች እንዳከተሙ አምኖ ነበር። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ 1ነገሥ. 19፡15-16፣ 2ነገሥ. 2፡11። አሁንም ለኤልያስ ተዘጋጅቶ ይጠብቀው የነበረ በጎ ነገር ምንድን ነው?



ኤልያስ የተሻሉ ቀናት እንደሚጠብቁት እግዚአብሔር ያውቅ ነበር። ነቢዩ ሕይወቱን በአምላካዊው ዜማ ድምጸት ምት ሲቃኝ እና ዕረፍቱን ሲቀበል፣ ፈውስ ወደ እርሱ ይመጣል። ከዚህ በኋላ ገና በእርሱ የሚቀቡ እና የሚመረጡ ተተኪ ነገሥታት ነበሩ። እግዚአብሔር ለኤልያስ የልጁ ያህል ስለሚቀርበው ስለ ኤልሳዕ አስቀድሞውኑ ያውቅ ነበር። ኤልያስ በእምነት እንደ ገና እሳት ከሰማይ እንደሚያወርድ እግዚአብሔር ያውቅ ነበር (2ነገሥ. 1፡10)። ከእንግዲህ ኤልያስ በእሳት ሠረገላ ወደ ሰማያዊው ዕረፍት ከመውጣት በቀር ክትክታ ዛፍ ስር ተቀምጦ የሚያውጠነጥነው ተስፋ አስቆራጭ ሞት አይኖርም። የቱንም ያህል አጉል ዓይነት ድባቴ ቢሰማንም በእግዚአብሔር ብርታት ተስፋ ላለመቁረጥ መጣር እንዳለብን አስመልክቶ ከኤልያስ ታሪክ ምን መማር እንችላለን?

ነሐሴ 14
Aug 20


ተጨማሪ ሀሳብ


“በሁናቴዎች የማያቋርጥ ለውጥ የተነሣ፤ ለውጦች የተሞክሮአችን አካል ሆነው ብቅ ይላሉ። ተዲያ እነዚህ ለውጦች ደስታ ያመጡልናል ወይም ጭንቀት ያስከትሉብናል። ሆኖም የሁናቴዎች መለዋወጥ እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ያለውን ግንኙነት ለመለወጥ የሚያስችል አቅም የለውም። ትናንት፣ ዛሬ እና ለዘላለም ያው የሆነው አምላክ በፍቅሩ ላይ የማያጠያይቅ ትምክህት እንዲኖረን ይጠይቀናል።”—Ellen G. White, In Heavenly Places, p. 120.

“በግልጽ የሚታይ ስሜት ቢኖሮትም፣ ባይኖሮትም ጸሎትዎን በእምነት እያቀረቡና ብርታቱን አጥብቀው እየያዙ ወደ የሱስ ይመልከቱ። እያንዳንዱ ጸሎትዎ በእግዚአብሔር ዙፋን እንደቀረበና የተስፋ ቃሎቹ በማይታጠፉት አምላክ ምላሽ እንዳገኘ ሆኖ ይሰማዎ። በብርቱ ጫና እና የሐዘን ስሜት በሚዋጡ ጊዜም እንኳ በልብዎ ለእግዚአብሔር ከመዘመር ወደ ኋላ አይበሉ። ብርሃን ይፈነጥቃል፣ ደስታ የእኛ ይሆናል፣ ጭጋጉ እና ደመናውም ይገፈፋል። በዚህም ከሚጨቁነው የጥላ እና የጽልመት ኃይል--የብርሃን ጸዳል ወደ ፈነጠቀበት ወለል ያለ አምላካዊ መገኛ እንሸጋገራለን።”—Ellen G. White, Selected Messages, book 2, pp. 242, 243.


የመወያያ ጥያቄዎች



፡ 1.ብዙውን ጊዜ በአእምሮ ሕመም ወይም በድባቴ የሚሠቃይ ሰውን መርዳት በጣም አስቸጋሪ ነው። ቤተ ክርስቲያንዎ በድባቴ የተጠቁ ምዕመናንን ይበልጥ ውጤታማ በሆነ መንገድ ማገልገል መማር የምትችልበት ጥሩ ዘዴ ምንድን ነው?

2.ብዙውን ጊዜ በእግዚአብሔር ፊት ግልጽና ሐቀኛ ለመሆን እንታገላለን። አንዳንድ የመጽሐፈ መዝሙር ገጾችን በማገላበጥ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች በአምላክ ፊት ምን ያህል ግልጽና ሐቀኛ እንደነበሩ ይመልከቱ። በአጥቢያ ጉባኤያችን ግልጽነትና ሐቀኝነት እንዲሰፍን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

3.ብዙውን ጊዜ ድባቴ ስሜት ውስጥ ስንሆን መጸለይ አስቸጋሪ ይሆንብናል። ለራሳቸው መጸለይ ለማይችሉ ሰዎች በምልጃ ጸሎት ኃይል ዙሪያ ተወያዩ።

4.እምነት ስሜት አለመሆኑን ማስታወስ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ድባቴ፣ ተስፋ መቁረጥ፣ ፍርሃትና ጭንቀት ስለያዘን ብቻ በእግዚአብሔር ላይ እምነት ወይም መታመን ይጎድለናል ማለት አይደለም። ሁላችንም በአንድ ወይም በሌላ ወቅት በጊዜያዊ ድባቴ፣ ተስፋ መቁረጥ፣ ፍርሀት እና ጭንቀት ውስጥ ወድቀን እናውቃለን። ጉዳዩ የቱንም ያህል ከባድ ቢመስልም እንደዚህ ባሉ ጊዜያቶች በእምነት መድረስ በጣም አስፈላጊ መሆኑን እንዴት መማር እንችላለን?

5.ከሽባው ሰው ታሪክ ምን ዓይነት ታላቅ ተስፋ ማግኘት ይችላሉ-በተለይ ኃጢአት መር የአኗኗር ዘይቤ በሽታና ህመም አምጥቶ ከሆነ?




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA union SSL