የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

በክርስቶስ ማረፍ


3ኛ ሩብ ዓመት 2021

ከነሐሴ 1 – 7

7ኛ ትምህርት

Aug 7–Aug 13




ዕረፍት፣ ግንኙነት እና ፈውስ



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ዘፍ. 42:7–20፣ ማቴ. 25:41–46፣ ዘፍ. 42:21–24፣ ዘፍ. 45:1–15፣ ሉቃ. 23:34፣ ዘፍ. 50:15–21።


የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ “‘አሁንም በመሸጣችሁ አትቆጡ፣ በራሳችሁም አትዘኑ፣ ምክንያቱም እግዚአብሔር ሕይወት ለማዳን ሲል ከእናንተ አስቀድሞ እኔን ወደዚህ ልኮኛል” (ዘፍ. 45፡5)

አ ንድ ወንድ በአንዲት ሴት ላይ የወሲብ ጥቃት በመፈጸም ወንጀል ተከስሶ ነበር። ፖሊስ ካሰለፋቸው ተጠርጣሪዎች መካከል በእርግጠኝነት ለየችው። ምንም እንኳ በእርሱ ላይ የቀረቡ ማስረጃዎች በደለኛነቱን አጠያያቂ ቢያደርጉም፤ ሴትየዋ ግን “ጆኒ” ጥፋተኛ መሆኑን አጥብቃ ተናገረች። ይህን ተከትሎ ጆኒ ባልሠራው ወንጀል ለ14 ዓመታት በወኅኒ በሰበሰ። ሆኖም ከዚህ ሁሉ መከራ በኋላ የ ዲ.ኤን.ኤ ማስረጃ ወንጀለኛ አለመሆኑን በማመላከቱ “ጁአን” ዘግናኝ ስህተት መሥራቷን ተገነዘበች። ጆኒ ከእስር ከተፈታ በኋላ ልታገኘው ፈለገች። ለበርካታ ዓመታት ህይወቱን ካመሳቀለችው ከዚህች ሴት ጋር ፊት ለፊት ሲገናኝ ይህ በጣም ብዙ መከራ የደረሰበት ሰው ምን ያደርግ ይሆን?

በአንድ ክፍል ውስጥ ሆኖ እስኪመጣ መጠባበቅ ጀመረች። ጆኒ በክፍሉ ደርሶ ዐይን ለዐይን እንደ ተያዩ ጁአን ተንሰቅስቃ ማልቀስ ጀመረች። “ጆኒ ጎንበስ እንዳለ እጆቼን ያዝ ካደረገ በኋላ ወደ እኔ እየተመለከተ ‘ይቅር ብዬሻለሁ’ አለኝ። ማመን አልቻልኩም። በእጅጉ የጠላሁትና አጥብቄ እንዲሞት የተመኘሁት ፍጥረት ቢኖር ይህ ሰው ነበር። ሆኖም፣ አሁን በፊቴ የቆመው፣ ይህ አቻ የሌለው በደል ያደረስኩበት ሰው ይቅር አለኝ? የጸጋን ምንነት በትክክል መረዳት የጀመርኩት በዚያን ጊዜ ነበር። ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ፈውስ እና እውነተኛ ዕረፍት ማግኘት ጀመርኩ። በዚህ ሳምንት ስለ ይቅርታ ምንነትና ይቅርታ ለዕረፍት የለሹ ሰብዓዊ ልብ ማድረግ የሚችለውን እንመለከታለን።

ነሐሴ 2
Aug 8

ያለፈውን መጋፈጥ


በመጨረሻ ነገሮች ለዮሴፍ ትክክለኛውን አቅጣጫ ይዘው መጓዝ በመጀመራቸው የስኬት ማማ ላይ ወጣ። ከእስር ቤት መውጣት ብቻ ሳይሆን የፈርዖንን ህልም ከተረጎመ በኋላ የግብፅ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኖ ተሾመ (ዘፍ. 41)። ትዳር ይዞ የሁለት ልጆች አባት ሆነ (ዘፍ. 41፡50-52)። የግብፅ ጎተራዎች ከአፍ እስከ ገደባቸው ሞሉ። በትንቢት የተነገረው የረሃብ ዘመን ጀመረ። ከዚያም ከዕለታት በአንዱ ቀን የዮሴፍ ወንድሞች ወደ ግብፅ መጡ። ዮሴፍ ለመጀመሪያ ጊዜ ከወንድሞቹ ጋር ሲገናኝ የነበረውን ድባብ ምን ይመስል እንደ ነበር በዘፍ. 42፡7-20 ያንብቡ። ሴራው ለምን አስፈለገ? ዮሴፍ በዚህ የመጀመሪያ ግንኙነት ምን ለማድረግ እየሞከረ ነበር?



ዮሴፍ ከፍተኛ ሥልጣን ስለ ነበረው ለሚወስደው እርምጃ ማብራሪያ መስጠት ሳያስፈልገው በወንድሞቹ ላይ የበቀል እርምጃ መውሰድ ይችል ነበር። ይሁን እንጂ ዮሴፍ ከበቀል ይልቅ በቤት ውስጥ ያሉት የቤተሰቡ አባላት ጉዳይ አሳስቦት ነበር። የአባቱ ጉዳይ አስጨንቆታል። አሁንም በህይወት ይኖር ይሆን ወይስ የከሸፈው ቤተሰብ ያለ ወላጅ አባት ተበትኖ ቀረ? ወንድሙ ቢንያምስ? ለአባቱ ደስታና ተወዳጅ የሆነው ቢንያም አሁን የዮሴፍን ቦታ ወስዶ አጠገቡ አለ። ወንደሞቹ ያን አደገኛ ምቀኝነታቸውን ወደ እርሱም አዙረው ይሆን? አሁን ዮሴፍ በቤተሰቡ ውስጥ ያሉትን እነዚህን ለአደጋ ተጋላጭ ወገኖች ለመጠበቅ የሚያስችል ሁኔታ ላይ ይገኛል፤ ያደረገውም ይህንኑ ነበር።

የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ መርኅዎች በግንኙነታችን ውስጥ ተግባራዊ ማድረግ--በደልን መቀበል እንችላለን ወይም መቀበል አለብን ማለት አይደለም። እኛ እያንዳንዳችን በእግዚአብሔር ፊት የከበርን ነን። ስለዚህ የሱስ ለእያንዳንዳችን በመስቀል ላይ የመጨረሻውን ዋጋ ከፈለ። በሌሎች ላይ የሚደርስን ጉዳት ወይም ቸል መባል የሱስ በራሱ ላይ እንደ ደረሰ አድርጎ የሚቆጥረው ለምንድን ነው? ማቴ. 25:41–46።



እኛ ሁላችን በየሱስ ደም በመገዛታችን፣ በሕጋዊ መንገድ የእርሱ ነን። ማንኛውም በደል ፈጻሚ በየሱስ ንብረት ላይ ጥቃት ይሰነዝራል። ወሲባዊ ጥቃት መፈጸምም ሆነ ስሜትን መጉዳት ፈጽሞ የቤተሰብ አካል መሆን የለባቸውም። ይህ ውስጣዊ መፍትሔ ማግኘት ያለበት ግላዊ የቤተሰብ ጉዳይ አይደለም። ይልቁንም ውጪያዊ ዕርዳታና ጣልቃ ገብነት ይሻል። በእርስዎ ወይም ከቤተሰብ አባላትዎ በአንዱ ጥቃት ከደረሰ እባክዎ እምነት ወደሚጣልበት ባለሙያ በማምራት ዕርዳታ ያግኙ። አሁን እየገጠሞት ለሚገኝ የቱንም ዓይነት አስቸጋሪ ቤተሰባዊ ግንኙነት ከሚበጁ ጥቂት መጽሐፍ ቅዱሳዊ መርኅዎች መካከል አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው?

ነሐሴ 3
Aug 9

መድረኩን ማመቻቸት


ዮሴፍ ወንድሞቹን ይቅር ብሏል። መቼ ይቅር እንዳላቸው በትክክል ባናውቅም ነገር ግን በፊቱ ከመቅረባቸው ከረጅም ጊዜ በፊት መሆኑ ግልጽ ነው። ዮሴፍ ለደረሰበት በደል የይቅርታ ልብ ባይኖረው ኖሮ ምናልባት እንዲህ የበለጸገ ማንነት ባለቤት መሆን ይቅርና--ንዴቱ እና ምሬቱ ነፍሱን በልቶ ከጌታ ጋር የነበረውን ግንኙነት ሊያበላሽ በቻለ ነበር። በሌሎች ከደረሰባቸው አሰቃቂ ጥቃት በሕይወት የተረፉትን ማዕከል ያደረጉ በርካታ ጥናቶች በተጨባጭ እንደሚያመለክቱት፤ ሥቃይ የደረሰባቸው ተጎጂዎች ፈውስ አግኝተው ሕይወታቸውን ዳግመኛ ማጣጣም የሚያስችላቸው ቁልፍ ነገር--ይቅር ባይነት እንደሆነ አጽንኦት ሰጥተው ይናገራሉ።

ምንም እንኳ ዬሴፍ ወንድሞቹን ይቅር ቢላቸውም፤ ቤተሰባዊ ግንኙነቶቻቸው እርሱ ሲተዋቸው እንደ ነበረው፤ ማለትም በዶታይን ደረቅ ጉድጓድ ሁናቴ እንዲቀጥል ፈቃደኛ አልነበረም። አንዳች ለውጥ መኖሩን ማየት አለበት። ዮሴፍ ጆሮ ውስጥ ጥልቅ ያለው ምን ነበር? ዘፍ. 42፡21-24። ስለ ወንድሞቹ ምን ተረዳ?



ሁሉም ንግግሮች የተደረጉት በአስተርጓሚ እንደ መሆኑ፤ ዮሴፍ የሚናገሩትን መስማት እንደሚችል አልተረዱም። ዮሴፍ የወንድሞቹን የኑዛዜ ቃል ሰማ። ወንድማማቾቹ ዮሴፍን በማስወገድ ብላቴናው ለአባታቸው ያቀርብ ከነበረው ዘገባ ነጻ ሊሆኑ እንደሚችሉ አስበው ነበር። ሕልሞቹን መታገስ ወይም በአባታቸው የተወዳጅነት ሚና ሐሴት ሲያደርግ መመልከት እንደሌለባቸው ተገንዝበው ነበር። ይሁን እንጂ በድርጊታቸው ዕረፍት ከማግኘት ይልቅ እነዚህን ሁሉ ዓመታት በጥፋተኝነት ስሜት ሲሠቃዩ ኖሩ። ሥራቸው እንዲቅበዘበዙና በአምላካዊ የበቀል ቅጣት ፍርሐት እየተርበደበዱ እንዲኖሩ አድርጓቸዋል።

ስለ ደረሰባቸው ሥቃይ ሐዘን የተሰማው ዮሴፍ በእርግጥ አልቅሶላቸዋል። ረሀቡ አሁንም ለተጨማሪ ዓመታት እንደሚቆይ ዬሴፍ ያውቅ ስለነበር በሚቀጥለው ጊዜ እህል ለመግዛት ሲመጡ ብንያምን ይዘው እንዲመጡ አጥብቆ ነገራቸው (ዘፍ. 42፡20)። በተጨማሪ ስምዖንን በመያዣነት እርሱ ጋር እንዲቆይ አድርጎ ነበር (ዘፍ. 42፡24)። ብንያም በሕይወት መኖሩን ከተመለከተ በኋላ የቀድሞው የቅናት ስሜቶች ዛሬም አብረዋቸው እንዳሉ ለማየት ግብዣ አዘጋጀ (ዘፍ. 43፡34)።

ወንድሞቹ ምንም ዓይነት የቅናት ምልክት ሳያሳዩ ቢቀሩም፤ ዮሴፍ ግን ምን ያህል ተንኮለኞች ሊሆኑ እንደሚችሉ ይገነዘባል። ደግሞስ አንድ ከተማ ሙሉ ሕዝብ ያታለሉ አይደሉ (ዘፍ. 34፡13)? የእርሱን ዕጣ ፈንታ አስመልክቶም ቢሆን የገዛ አባታቸውን መዋሸታቸውን በእርግጠኝነት መገመት ይችላል (ዘፍ. 37፡3134)። ስለዚህ አንድ ተጨማሪ፣ ከፍ ያለ ፈተና ፈተናቸው (ዘፍ. 44)። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፍ. 45፡1-15። ይህ ሁኔታ ዮሴፍ ለወንድሞቹ ስላለው ስሜትና ስለ ሰጣቸው ይቅርታ ምን ይነግረናል? ከዚህ ታሪክ ምን ትምህርት ልናገኝ ይገባል?





ነሐሴ 4
Aug 10

ይቅርታ ማድረግ እና መርሳት?


ይቅር ማለት--በደል ባደረሰ ሰው ወይም አካል ላይ ቂም፣ ውግዘት እና በቀልን ለመተው ፈቃደኛ መሆን የሚል ፍቺ ተሰጥቶታል። ከናዚ ማሰቃያ ማለትም ሆሎኮስት እልቂት በሕይወት ለተረፉ ግፉአን የምክር አገልግሎት የሚሰጡት የሥነ ልቡናው ባለሙያ ዶ/ር ማርሊን አርሞር እንዲህ ብለዋል፡ “ይቅርታ የማድረግ ሐሳብ ሙሉ ለሙሉ የጥቃቱ ሰለባ የሆነ ሰው ሆነ ብሎ የሚፈጽመው ድርጊት እንጂ፣ ዝም ብሎ የሚከሰት ነገር አይደለም።”

ይቅር ማለት ምንም ዓይነት ውጤት አያስከትልም ማለት አይደለም። ይቅር ማለት ጥቃት አድራሹ ጎጂ ልማዶቹን እንዲከተል መፍቀድ ማለት አይደለም። ይልቁንም ይቅር ማለት ቂማችንን እና የበቀል ፍላጎታችንን ለፈጣሪ መተው ነው። ይህ ካልሆነ ግን ቁጣው፣ ምሬቱ፣ ቂሙና ጥላቻው--ጥቃት አድራሹ ካደረገው በላይ የከፋ ነገር ያስከትልብናል። ሌሎችን ይቅር ማለታችን ለእኛ ምን ፋይዳ አለው? ማቴ. 18:21–35



ይቅር ማለትን ለመማር ከሚረዱን ቁልፍ ነገሮች አንዱ በክርስቶስ ይቅር መባላችንን መረዳት መሆኑ አያጠያይቅም። ሁላችንም በድለናል። የበደልነው ደግሞ ሌሎችን ብቻ ሳይሆን እግዚአብሔር አምላክንም ጭምር ነው። እርግጥ ነው--እያንዳንዱ ኃጢአት የጌታችንና ፈጣሪያችንን ፈቃድ መጣስ እንደመሆኑ በእርሱ ላይ የሚፈጸም በደል ነው። ደግሞም በየሱስ አማካይነት ለኃጢአት ሁሉ ይቅርታ ማግኘት የቻልነው--የሚገባን ሆነን በመገኘታችን ሳይሆን፣ እግዚአብሔር ለእኛ በገለጠው ጸጋ ብቻ ነው። ይህን ቅዱስ እውነት አንዴ ከተረዳን፣ ይቅርታውን የራሳችን ማድረግ ከቻልን እና የእግዚአብሔርን ይቅርታ ምንነት በተጨባጭ ካስተዋልን--ያለፈውን ትተን ሌሎችን ይቅር ማለት መጀመር እንችላለን። ይቅር የምንለው የበደሉን ሰዎች ይቅርታችን ስለሚገባቸው ሳይሆን፤ ይቅርታ ከእግዚአብሔር የተቀበልነውና ለራሳችን የምንፈልገው በመሆኑ ነው። እኛስ ብንሆን ስንት ጊዜ ይቅር እንባል ዘንድ ይገባናል?

ቀደም ሲል ዮሴፍ ለቤተሰባዊው ግንኙነት ሁለተኛ ዕድል እንደሰጠ ተመልክተናል። እዚህ ላይ ቂም የለም። ባለፉት ጊዜያት የተፈጸሙ እንከኖችን እየመዘዙ መቆሳሰል አክትሟል። አንዳችን እንዴት ሌላውን ይበልጥ መጉዳት እንዳለብን አስመልክቶ በእጅጉ የተካንን እና የተጠበብን ከሆንን፤ የከሸፈው ቤተሰባዊው ግንኙነት ዳግም እንዲያንሰራራ ማድረግ የማይመስል ይሆናል። ይሁን እንጂ የዮሴፍ ምላሽ ከዚህ የተለየ ነበር። ያለፈውን ወደ ኋላ ትቶ በፍቅር እና በተቀባይ መንፈስ ወደፊት መግፋት የሚፈልግ ይመስላል። ዮሴፍ ከዚህ የተለየ አመለካከት ቢይዝ፣ የታሪኩ ፍጻሜ አሳዛኝ ሆኖ በተለወጠ ነበር።

“‘መተላለፋቸው ይቅር የተባለላቸው፣ ኃጢአታቸው የተሰረየላቸው፣ ብፁዓን ናቸው። ኃጢአቱን፣ ጌታ ከቶ የማይቆጥርበት ሰው ብፁዕ ነው’ ” (ሮሜ፡ 7-8)። ጳውሎስ በየሱስ ስለ ተሰጠን ነገር ምን እየነገረን ነው? ይህ አስደናቂ ተስፋ ከጎዱን ሰዎች ጋር በሚኖረን ግንኙነት ላይ ምን ተጽዕኖ ሊያሳድር ይገባል?

ነሐሴ 5
Aug 11

በተግባር መግለጥ


ይቅር ለማለት ጉዳት እንደ ደረሰብኝ አምኜ መቀበል አለብኝ። ብዙውን ጊዜ ስሜቶቻችን ላይ ለውጥ ለማምጣት ከመሥራት ይልቅ ወደ መቅበሩ አብልጠን ያዘነበልን እንደመሆናችን፣ ይህን ማድረግ ከባድ ሊሆንብን ይችላል። ክርስቲያናዊ ያልሆነ የቂም፣ ከዚያም አልፎ የቁጣ ስሜት መኖሩን በእግዚአብሔር ፊት አምኖ መቀበል መልካም ነው። ይህ በመጽሐፈ መዝሙር በተደጋጋሚ ተገልጾ እንመለከታለን። የሆነውን ነገር አለመውደዴን ወይም ሌሎች ለእኔ በጎ ምላሽ አለመስጠታቸውንና ጉዳዩ በእኔ ላይ ቅሬታ መፍጠሩን ለእግዚአብሔር ለመንገር ነፃነት ይሰማኛል።

በዮሴፍ ታሪክ፤ ወንድሞቹን ዳግመኛ ሲያያቸውና አንዳንድ ያለፉ ስሜቶች ዳግም ሲገለጡ ማልቀሱን እናያለን። የሱስ በመስቀል ላይ በይፋ የሰጠው መግለጫ የይቅርታ ጊዜን አስመልክቶ ምን ይነግረናል? ሉቃ. 23፡34



የሱስ እኛ በመጀመሪያ ይቅርታ እስክንጠይቅ አልጠበቀንም። እኛም የበደለን ሰው ይቅርታ እስኪጠይቀን መጠበቅ የለብንም። ሌሎች ይቅርታችንን እንዲቀበሉ ባናደርግም ይቅር ማለት ግን እንችላለን። ከሚበድሉን ጋር ምን ዓይነት ግንኙነት ሊኖረን እንደሚገባ አስመልክቶ የሚከተሉት ጥቅሶች ምን ያስተምራሉ? ሉቃ. 6፡ 28፣ ማቴ. 5፡44።



ይቅር ማለት እና ፍቅር መስጠት የመሳሰሉት ከስሜት ይልቅ በምርጫ ይጀምራሉ። ስሜታችን በዚህ ውሳኔ ላይስማማ ቢችልም እንኳ ይቅር ለማለት መምረጥ እንችላለን። ይህ ምርጫ በእኛ ብርታት ሊሆን እንደማይችል እግዚአብሔር ያውቃል። ነገር ግን “በእግዚአብሔር ዘንድ ሁሉ ይቻላል” (ማር. 10፡27)። ለሚጎዱን ሰዎች እንድንጸልይ የተነገረን ለዚህ ነው። በአንዳንድ ሁኔታ የበደለን ሰው በህይወት ላይኖር ቢችል እንኳ፤ ነገር ግን ግለሰቡን ይቅር ለማለት የሚያስችል ችሎታ እናገኝ ዘንድ አሁንም በዚህ ጉዳይ መጸለይ እችላለን።

ይቅርታ ማድረግ ሁሌም ቀላል አለመሆኑ አጠያያቂ አይደለም። የደረሰብን ሥቃይና ጉዳት አውዳሚ፣ የማይሽር ጠባሳ ጥሎ የሚያልፍ እና ሽባ የሚያደርግ ሊሆን ይችላል። የምንፈቅድ ከሆነ ፈውስ ይመጣል። ነገር ግን ምሬትን፣ ቁጣንና ቂምን የሙጥኝ ማለት የፈውስን መንገድ በእጅጉ አስቸጋሪ ያደርገዋል። መስቀሉ እግዚአብሔር እኛን ይቅር ለማለት እርሱን ራሱን ምን ያህል ዋጋ እንዳስከፈለው የሚያሳይ ምርጥ ምሳሌ ነው። ጌታ ብዙዎች እንደማይቀበሉት እያወቀ፣ ለእኛ ሲል በዚያ ውስጥ ማለፍ ከቻለ፤ እኛም ይቅር ማለትን በእርግጠኝነት መማር እንችላለን። ማንን ይቅር ማለት ይኖርቦታል--ስለዚያ ሰው ብለው ካልሆነ፣ ስለ ራስዎ ሲሉ?

ነሐሴ 6
Aug 12

ከይቅርታ በኋላ ዕረፍት ማግኘት


የዮሴፍ ቤተሰቦች በመጨረሻ ግብፅ ደረሱ። ከዚህ በኋላ በቤተሰቡ መሃል ምንም ዓይነት ድብቅ ምስጢር የለም። አባት ተገድሏል ብሎ እርሙን ያወጣለት ተወዳጅ ልጁ አሁን የግብፅ ጠቅላይ ሚንስትር ሆኖ መገኘቱን ለአባታቸው ሲነግሩ፣ ወንድሞቹ ያኔ ብላቴናውን መሸጣቸውን ሳያምኑ እንዳልቀረ ይታመናል።

ግንኙነቶችን ወደ ቀደመው ጤናማ ሁናቴ መመለስ ሁሌም የሚቻል ባይሆንም፣ ይቅር ማለት አንችልም ማለት አይደለም። ከበደለን ሰው ጋር መተቃቀፍና ማልቀስ ባንችልም ነገር ግን ይቅርታችንን በድምፅ ወይም በደብዳቤ ማሰማት እንፈልግ ይሆናል። ይህ ሥቃያችን በተቻለን መጠን ከእኛ እንዲርቅ የምናደርግበት መንገድ ነው። ምናልባት አንዳንድ የሥቃይ ስሜት ሁሌም ከእኛ ጋር ሊቀር ቢችልም፤ ነገር ግን ቢያንስ በፈውስ መንገድ ላይ መሆን እንችላለን።

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፍ. 50፡15-21። የዮሴፍን ወንድሞች ያስጨነቃቸው ምን ነበር? ይህ ፍርሃት ስለ ራሳቸው ምን ይናገራል?



የዮሴፍ ወንድሞች በግብፅ አሥራ ሰባት ዓመት ከኖሩ በኋላ (ዘፍ. 47፡ 28) ያዕቆብ ሲሞት ዮሴፍ ይበቀለናል የሚል ስጋት አደረባቸው። ዮሴፍን ምን ያህል እንደጎዱት እንደገና ተገነዘቡ። ዮሴፍ አባታቸው ከሞተ በኋላ ይቅር እንዳላቸው ዳግመኛ አረጋገጠላቸው። ይህ የማነቃቂያ ቃል ለዮሴፍም ሆነ ለወንድሞቹ ሳይጠቅም አልቀረም። የደረሰው ቁስለት ከባድ ከሆነ ብዙ ጊዜ ይቅር ማለት ይኖርብን ይሆናል። የጉዳት ትዝታዎች ወደ አእምሮአችን ሲመጡ ወዲያውኑ በጸሎት ወደ እግዚአብሔር በመቅረብ ዳግመኛ ይቅር ለማለት መምረጥ ይኖርብናል። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፍ. 50፡20። ይህ ጥቅስ ዮሴፍ ወንድሞቹ በእርሱ ላይ የፈጸሙትን በደል ይቅር ለማለት ፈቃደኛ መሆኑን ቢያንስ በከፊል ለማስረዳት እንዴት ይረዳል?



ዮሴፍ ህይወቱ በዚያን ጊዜ የነበረውን ዓለም ከረሀብ በመታደግ፣ ቤተሰቡ የእግዚአብሔር ታላቅ ሕዝብ የሚሆንበት አምላካዊ ኪዳን ቃል እንዲፈጸም ማድረግ ያስቻለ የጌታ ታላቅ እቅድ አካል መሆኑን አጥብቆ ያምን ነበር። እግዚአብሔር የወንድሞቹን ክፉ ዕቅድ ቀልብሶ ለመልካም ነገር እንዳዋለው ማወቁ ዮሴፍ ይቅር እንዲል ረድቶታል። የዮሴፍ ታሪክ ፍጻሜ አስደሳች ነበር። የአንድ ታሪክ መጨረሻ አስደሳች ሳይሆን ሲቀር ምላሻችን ምን ይሆናል? ወይም በኃጢአት ፍጻሜና በታላቁ ውዝግብ መጨረሻ--ሁሉም ጉዳዮች ሲፈቱ-አስደሳች ፍጻሜ ይሆናል ብሎ አንድ ሰው ሊሞግት ይችላል?

ነሐሴ 7
Aug 13


ተጨማሪ ሀሳብ


“ዮሴፍ በገዛ ወንድሞቹ ለባርነት የተሸጠው ኃይማኖት ለሌላቸው ሰዎች ሲሆን ክርስቶስም ከደቀ መዛሙርቱ በአንዱ አማካኝነት ለመራር ጠላቶቹ ተላልፎ ተሸጠ። ዮሴፍ ለመርኅ በመገዛቱ ምክንያት የሐሰት ውንጀላ ቀርቦበት ወደ እስር ቤት ተጥሎ ነበር። ክርስቶስ የተናቀውና ነቀፌታ የደረሰበት ጻድቅና እራስን የሚክድ ሕይወቱ ኃጢአትን በመገሰጹ ነበር። ምንም ዓይነት ስህተት ባይገኝበትም ነገር ግን በሐሰት ተመስክሮበት ጥፋተኛ ተባለ። ዮሴፍ በፍትህ ማጣትና ጭቆና ስር ሆኖ ያሳየው ታጋሽነት፣ ታዛዥነት፣ ይቅር ባይነትና በጨካኝ ወንድሞቹ ላይ ያሳየው ርኅራኄ --ክፉዎች አዳኙ ላይ ጭካኔና በደል ሲያደርሱበት ያሳየው ይቅርታ ለገዳዮቹ ብቻ ሳይሆን ነገር ግን ወደ እርሱ በመቅረብ ኃጢአታቸውን በመናዘዝ ይቅርታን ለሚለምኑት ሁሉ የሚሰጠውን ምህረት ያንጸባርቃል።”--የኃይማኖት አባቶች እና ነቢያት፡ ገጽ 269።

“ይቅር የማይል መንፈስን ፍትሐዊነት ምንም ነገር ሊያረጋግጥ አይችልም። ለሌሎች ምኅረት የማያደርግ እርሱ ራሱ የእግዚአብሔር ይቅርባይነት ጸጋ ተካፋይ አለመሆኑን ያሳያል። የጥፋተኛው ልብ በአምላካዊው ምኅረት ወሰን ወደሌለው አፍቃሪ ልብ ይሳባል። የመለኮታዊው ርኅራኄ ሞገድ ወደ ኃጢአተኛው ነፍስ ይፈሳል። ክርስቶስ በከበረው ሕይወቱ የገለጠው ርኅራኄ እና ምህረት የጸጋው ተካፋዮች በሚሆኑ ላይ ይታያል።”—Ellen G. White, Christ’s Object Lessons, p. 251.


የመወያያ ጥያቄዎች



፡ 1.አንድ ሰው እንዲህ ብሎ ነበር፡ “ይቅር አለማለት ሌላው ሰው ይሞታል ብሎ ተስፋ በማድረግ መርዝ እንደ መጠጣት ነው።” ይህ አባባል ምን ማለት ነው?

2.ዮሴፍ ማንነቱን ከመግለጹ በፊት በጥንቃቄ የሄደባቸው የእነዚያ ሁሉ እቅዶቹ ዓላማ ምን ነበር? ይህ ለእርሱም ሆነ ለወንድሞቹ ምን አስገኘ?

3.የዮሴፍ ቤት አዛዥ የዮሴፍን ወንድሞች አስመልክቶ በአንዳንድ ሴራዎች ውስጥ እጁ እንደነበረበት መገመት አይከብድም (ዘፍ. 44፡1-12)። የይቅር ባይነት ተሞክሮ በሰዎች ላይ ምን ዓይነት ተጽዕኖ ያሳድራል?

4.“እግዚአብሔር ይመራቸው ዘንድ የልጆቹ ፈቃድ ካልሆነ በቀር አያስገድዳቸውም። መጨረሻውን ከመጀመሪያው አንስቶ መመልከት ቢችሉና በሥራው ባልደረባነት የሚፈጽሙትን በክብር የተሞላ ዓላማ ለይተው ቢረዱ…”—Ellen G. White, The Desire of Ages, pp. 224, 225. መልእክቱን እያሰላሰሉ ስለ ራስዎ ሕይወት ያስቡ። ይህን መረዳታችን ሊያጋጥሙን የሚችሉ በርካታ ፈተናዎችንና ውጣ ውረዶችን ለመቋቋም እንዴት ይረዳናል?




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA union SSL