የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

የተስፋው ቃል፡ የእግዚአብሔር ዘላለማዊ ኪዳን


2ኛ ሩብ ዓመት 2021

ከግንቦት 7 – 13

8ኛ ትምህርት

May 15 - May 21




ቃል ኪዳናዊው ሕግ



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ዘፀ. 19:6፣ ኢሳ. 56:7፣ ዕብ. 2:9፣ ዘዳ. 4:13፣ ዘዳ. 10:13፣ አሞጽ 3:3፣ ዘፍ. 18:19።


የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ “ስለዚህም አምላክህ እግዚአብሔር አምላክ መሆኑን ዕወቅ፤ እርሱ ለሚወዱትና ትእዛዞቹን ለሚጠብቁት የፍቅሩን ኪዳን እስከ ሺህ ትውልድ ድረስ የሚጠብቅ ታማኝ አምላክ ነው፡፡” (ዘዳ. 7፡9)፡፡

በ መዝ. 23 ከምናገኛቸው እጅግ አስፈላጊ ሐረጎች አንዱ እግዚአብሔር እኛን ለመምራት እንደሚመኝ ያመለክታል። “ስለ ስሙም በጽድቅ መንገድ ይመራኛል” ሲል ዳዊት በቁ. 3 ያውጃል። እግዚአብሔር ካለው የቀና ሥነ ምግባር የተነሣ ወደ ስህተት መንገድ አይመራንም። ይልቁንም ለመንፈሳዊው የሕይወት ጉዞአችን የሚበጁ አስተማማኝ መንገዶችን ይቀይስልናል። ለመሆኑ አስተማማኝና ደኅንነታቸው የተጠበቀ “የጽድቅ መንገዶች” የትኞቹ ናቸው? ባለ መዝሙሩ ይህን ጥያቄ እንዲህ በጸሎት ይመልሳል “ትእዛዛትህ ሁሉ የጽድቅ ትእዛዞች ናቸውና፣ አንደበቴ ስለ ቃልህ ይዘምር” (መዝ. 119፡172)። የእግዚአብሔር ሕግ ለማይታመነው ሰብዓዊ ፍጡር አስተማማኝና ጽኑ ጎዳና ነው።

የዚህ ሣምንት ትምህርታችን በእግዚአብሔር ሕግ እና በተሰጠበት የሲና ቃል ኪዳን ላይ ትኩረት ያደርጋል። ሣምንቱን በጨረፍታ፡ የእስራኤል ምርጫ ምን ማለት ነበር? የእስራኤል ምርጫ ከራሳችን ጋር እንዴት ይመሳሰላል? በቃል ኪዳኑ ውስጥ ሕጉ ምን ያህል አስፈላጊ ነበር? ቃል ኪዳኑ የመጣው ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ነበር? መታዘዝ የቃል ኪዳኑ ግንኙነት ወሳኝ አካል የሆነው ለምንድን ነው?



ግንቦት 8
May 16

የእስራኤል መመረጥ (ዘዳ. 7፡7)


እግዚአብሔር ከእስራኤል ጋር ቃል ኪዳን የገባው መጀመሪያ ላይ ሌሎች ሕዝቦች ይንሁኑ ጥሪ በመቃወማቸው ነው፣ ሲል የአይሁድ ወግ ያስተምራል። ምንም እንኳ ይህን አቋም የሚደግፍ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃ ባይገኝም፤ እርሱ ዕብራውያንን የመረጠበት የቱንም ዓይነት ምክንያት ቢኖረውም እንኳ--ልዩ መብትና ጥቅም የሚገባቸው ሕዝቦች አመሆናቸው ዋናውን ነጥብ ለማግኘት ይረዳል። የእግዚአብሔር ፍቅር እንዲገባቸውና ሕዝቡ አድርጎ እንዲመርጣቸው የሚያደርግ የራሳቸው አንዳች ብቃትም ሆነ መልካም ነገር ኖሯቸው አልነበረም። እነዚህ ሕዝቦች እጅግ አነስተኛ ቁጥር የነበራቸውና በባርነት ቀንበር ሥር የኖሩ ጎሳዎች ከመሆናቸው በተጨማሪ ፖለቲካዊም ሆነ የመከላከያ ሠራዊት ዝግጅታቸው ደካማ ነበር። እንዲሁም ከባህልና ኃይማኖት አንጻር የተደበላለቁ፣ ገራገርና ተጽእኖ መፍጠር የማይችሉ ነበሩ። በመሆኑም የእስራኤል መመረጥ መሰረታዊ ምክንያት በአምላካዊው ፍቅር እና ጸጋ ምስጢር ውስጥ ይቀራል።

በተመሳሳይ፤ ስለ እስራኤል መመረጥ ስንመለከት ጉዳዩ ሥነ መለኮታዊ አለመግባባት የመፍጠር አቅም ያለው እንደመሆኑ ጥንቃቄ ይፈልጋል። እግዚአብሔር እስራኤልን ለምን መረጠ? ሌሎቹ ተቀባይነት እንዲያጡና እንዲጠፉ እየተደረጉ እነርሱን ለመዋጀት ነው? ወይስ ለእነርሱ የተሰጣቸውን ለሌላው ሕዝብ እንዲያስተላልፉ የተመረጡ መሣሪያዎች ነበሩ? የሚከተሉት ቁጥሮች የጥያቄዎቹን መልሶች እንድናስተውል እንዴት ይረዱናል?

ዘፀ. 19:6_____________________________________________________

ኢሳ. 56:7____________________________________________________

ዕብ. 2:9_____________________________________________________

እንደ ሰባተኛ ቀን የዳግም ምጽአቱ ተጠባባቂነታችን--በጌታ መጠራታችን፣ በብቸኝነት የተዋጀን ሳንሆን ነገር ግን የመዋጀትን መልእክት ከሦስቱ መላእክት መልእክት ዐውድ ለዓለም እንድናውጅ በመጠራታችን--ራሳችንን እንደ ዘመናዊው እስራኤል መመልከት ይቀናናል። በአጭሩ ማንም ሊል የማይችለው--የምንናገረው ነገር እንዳለን እናምናለን። ይህ ከጥንት እስራኤል ጋር የሚያመሳስል ሁናቴ ነው።

የእስራኤል መመረጥ ዓላማ የደኅንነትን እቅድ እና መዋጀትን ብቸኛ ርስታቸው አድርጎ ለማስቀረት አልነበረም። በተቃራኒው፤ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ሁሉ መሞቱን የምናምን ከሆነ (ዕብ. 2፡9) ጌታ ለእስራኤል የከፈለው ቤዛነት ለተቀረውም ዓለም ተከፍሏል ማለት ነው። እስራኤል ይህ ቤዛነት የሚታወቅባት መሣሪያ መሆን ነበረባት። ቤተ ክርስቲያናችን ተመሳሳዩን እንድታደርግ ተጠርታለች። በቤተ ክርስቲያን በግል ያሎትን ሚና ይመልከቱ። እንድንሠራ የተጠራነውን ሥራ በማበረታታት ረገድ ምን ዓይነት እገዛ ሊሰጡ ይችላሉ? የሚችሉትን ያህል፣ በተወሰነ ደረጃ በንቃት እገዛ እያደረጉ ካልሆነ ራስዎን ይመርምሩ።



ግንቦት 9
May 17

የሚያስተሳስሩ ገመዶች


“እርሱ ኪዳኑን ይኸውም እንድትከተሏቸው ያዘዛችሁን ዐሠርቱን ትእዛዛት ዐወጀላችሁ፤ ከዚያም በሁለት የድንጋይ ጽላቶች ላይ ጻፋቸው” (ዘዳ. 4፡13)። ኪዳኑ ሁሌም የጸጋ ኪዳን ነው እያልን አበክረን ስንገልጽ ቆይተናል። በመሆኑም ጸጋ የሚያድነውን ኪዳን ከእርሱ ጋር ለገቡ የሚሰጥ--ሊቆጠር የማይችል የእግዚአብሔር ውለታ ውጤት ብቻ እንጂ ያለመታዘዝ ፈቃድ አይደለም። በተቃራኒው ኪዳን እና ሕግ አንድ ላይ ይውላሉ። እንደ እውነቱ ከሆነ ሁለቱ አይነጣጠሉም።

ከላይ በትምህርተ ጥቅስ የቀረበውን ጥቅስ ይመልከቱ። ቃል ኪዳኑ እና ሕጉ ምን ያህል በጥብቅ ተቆራኝተዋል? ሕጉ ለቃል ኪዳኑ ምን ያህል መሠረታዊ እንደሆነ እንዴት ያሳያል?



ስለ ኪዳን ምንነት ሲያስቡ፤ የሕጉ ጽንሰ ሀሳብ መሠረታዊ ክፍል ትርጉም የሚሰጥ ይሆናል። ኪዳኑን ከሌሎች ነገሮች እና ከግንኙነት በተጓዳኝ የምናስተውለው ከሆነ የተወሰኑ ሕግጋት እና ወሰኖች መቀመጥ ይኖርባቸዋል። ጋብቻ፣ ጓደኝነት ወይም የንግድ ሽርክና በገደቦች እና ሕግጋት በተለይ ካልተጠቀሱ ወይም በውስጠ ታዋቂ ካልተስተዋሉ ምን ያህል ሊዘልቁ ይችላሉ? ባል በሚስቱ ላይ ደርቦ ፍቅረኛ ለመያዝ ይወስናል ወይም ጓደኛ ራሱን ለመርዳት የባልንጀራውን የገንዘብ ቦርሣ ይወስዳል ወይም ደግሞ አንድ የንግድ ሸሪክ ያለ አጋሩ እውቅና ሌላው ሰው የጥምረታቸው አካል እንዲሆን ይጋብዛል። እንደነዚህ ዓይነቶቹ ድርጊቶች--ደንቦችን፣ ሕጎችን እና መርኅዎችን የጣሱ ይሆናሉ። እነዚህ ግንኙነቶች በእንደዚህ ዓይነት ሕገ-ወጥ ሁናቴዎች ለምን ያህል ጊዜ ይዘልቃሉ? በዚህ የተነሣ ድንበሮች፣ መስመሮች እና ሕጎች መቋቋማቸው የግድ ይሆናል። ግንኙነት ተጠብቆ መቆየት የሚችለው በእነዚህ አማካይነት ብቻ ነው።

በእርግጥ ቃል ኪዳን ለተሰኘው ቃል ተመሳሳይነት ያላቸው የተለያዩ መግለጫዎች አሉ፡ ሕግ (መዝ. 78፡10)፣ መብት (መዝ. 50፡16)፣ ኪዳን (25፡10)፣ ትእዛዛት (መዝ. 103፡ 18)፣ የጌታ ቃል (ዘዳ. 33፡9)። በግልጽ እንደሚታየው “የዚህ ኪዳን ቃል” (ኤር. 11፡3፣ 6፣8) የእግዚአብሔር ሕግ፣ ሥርዓቶች፣ መብት፣ ኪዳን እና ትእዛዛት ናቸው። እግዚአብሔር ከሕዝቡ እስራኤል ጋር የገባው ቃል ኪዳን፤ ከእነርሱ ጋር የፈለገውን ልዩ ግንኙነት ለማቆየት ወሳኝ የሆኑ ልዩ ልዩ መስፈርቶች ይዞአል። ዛሬ ከዚህ የተለየ ነገር አለ?

ከአንድ ወዳጅዎ ጋር ያለዎትን የጠበቀ ግንኙት ያስቡ። ለማናቸውም ዓይነት ደንቦች፣ ልማዶች ብሎም ሕጎች ተገዢ የመሆን ስሜት ሳይኖሮት፣ እንደው የፈለጉትን የማድረግ ሙሉ ነጻነት ቢሰማዎት ግንኙነታችሁ ላይ ምን ሊከሰት እንደሚችል ያስቡ። ምንም እንኳ ይህን ሰው እወደዋለሁ ቢሉና ያ ፍቅር ብቻውን ከእርሱ ጋር ያለዎትን ግንኙነት ይወስናል ቢሉ--አሁንም ሕጎች የሚያስፈልጉት ለምንድን ነው? ተወያዩበት።



ግንቦት 10
May 18

ሕጉ በኪዳኑ ውስጥ (ዘዳ. 10፡12-13)


ስለ ሕግ ሲያስቡ መጀመሪያ ወደ አእምሮዎ የሚመጡ ነገሮች ምንድን ናቸው? የፖሊስ ባልደረባ፣ ትራፊክ ፖሊስ፣ ዳኛ፣ ወህኒ ቤት? ወይስ ገደቦች፣ ደንቦች፣ ጥብቅ ወላጆች እና ቅጣት? ወይስ--ሥርዓት፣ ደንብ፣ መረጋጋት? ምናልባት… ፍቅር? በመጽሐፍ ቅዱሳችን “ሕግ” ተብሎ የተተረጎመው ቶራ የሚለው የዕብራይስጥ ቃል “ማስተማር” ወይም “መመሪያ” የሚል ፍቺ አለው። ሥነ ምግባራዊ፣ ብሔራዊ፣ ማኅበራዊ ወይም ኃይማኖታዊ--ቃሉ ሁሉንም አምላካዊ መመሪያዎች ለመግለጽ ጥቅም ላይ መዋል ይችላል። ሰዎች አካላዊም ሆነ መንፈሳዊ የተትረፈረፈ ሕይወት ይለማመዱ ዘንድ እግዚአብሔር በቸርነቱ ለሕዝቡ የሰጣቸውን ሁሉንም ዓይነት በጥበብ የተሞሉ ምክረ ሀሳቦች ለማመልከት ሊያገለግል ይችላል። ከዚህ አኳያ ባለ መዝሙሩ ሰው “ደስ የሚሰኘው በእግዚአብሔር ሕግ ነው፤ ሕጉንም በቀንና በሌሊት ያሰላስላል” (መዝ. 1፡2) ብሎ ቢናገር ብዙም ላያስገርም ይችላል።

በሙሴ መጽሐፍት ውስጥ የተመዘገቡ መመሪያዎች እና ትምህርቶች የእስራኤል ቃል ኪዳን አካል ሆነው በሕጉ ወይም ቶራ ስናነብባቸው፤ በእነዚያ መጠነ ሰፊ መመሪያዎች መደነቃችን አይቀርም። ሕጉ--ግብርና፣ የመንግሥት አስተዳደር፣ ማህበራዊ ግንኙነቶች፣ አምልኮ--እያንዳንዱን የእስራኤልን የአኗኗር ዘይቤ ይነካል። እግዚአብሔር ይህን ሁሉ መመሪያ የሰጠው ለምን ይመስሎታል? (ዘዳ. 10:13)። እነዚህ መመሪያዎች “ለበጎ” የሆኑላቸው በምን መልኩ ነበር?



በቃል ኪዳኑ ውስጥ ያለው “ሕግ” ሥራው ለሰብዓዊው የኪዳን አጋር አዳዲስ የሕይወት መመሪያዎችን መስጠት ነበር። በእምነት በመታዘዝ ትእዛዛቱን እና ሌሎች የፈቃዱን መገለጫዎች ሙሉ ለሙሉ ለማወቅ የሚመጣውን የቃል ኪዳን አባል የሆነውን ሰው፤ ሕጉ ከእግዚአብሔር ፈቃድ ጋር ያስተዋውቀዋል። እስራኤል የሌሎች ሕዝቦችን መንገድ መከተል የማትችል መሆኗን በቃል ኪዳኑ ግንኙነት ሕጉ በሚጫወተው ሚና አሳይቷል። በተፈጥሮ ሕግ፣ በሰዎች ፍላጎት፣ በምኞቶች ወይም አልፎ ተርፎ--በማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፍላጎቶች ላይ ብቻ ተመርኩዘው መኖር አይችሉም። የእግዚአብሔር የተቀደሰ ሕዝብ፣ የመንግሥት ካህናት እና የተወደደ ርስት ሆነው መቀጠል የሚችሉት በሁሉም የሕይወት ዘርፎች ለተገለጠው ቃል ኪዳን ሳያወላውሉ ለአምላካዊው ፈቃድ ሲታዘዙ ብቻ ነው።

እንደ ጥንቷ እስራኤል ሁሉ ሰባተኛ ቀን የዳግም ምጽአቱ ተከታዮችም ለዘመኑ በተገለጠው የትንቢት ስጦታ አማካይነት እያንዳንዱን የክርስቲያን አኗኗር የሚመለከቱ ሰፋ ያሉ ምክረ ሀሳቦች ተቀብለዋል። ምክሮቹ ነጻ አስተሳሰብንና ድርጊትን የሚጎዱ አድርጎ ከመመልከት ይልቅ ለምን እንደ እግዚአብሔር ስጦታ እንመለከታቸዋለን? በተመሳሳይ እስራኤላውያን እንዳደረጉት፤ እኛም ይህን ስጦታ የምንጠመዝዘው ከሆነ ምን ዓይነት አደጋ ሊገጥመን ይችላል? (ሮሜ 9:32)።



ግንቦት 11
May 19

የእግዚአብሔር ሕግ ጽኑነት


በቃል ኪዳን ግንኙነት ውስጥ የእግዚአብሔር ሕግ መኖሩ ስለ አምላካዊው አስፈላጊ እውነት ምን ያስተምረናል? ሚል. 3፡6 ፣ ያዕ. 1፡17 ።



የእግዚአብሔር ሕግ የአምላካዊው ፈቃድ የቃል ወይም የጽሑፍ መግለጫ ነው (መዝ. 40፡8)። ሕጉ የባሕሪው ግልባጭ መሆኑን ተከትሎ በቃል ኪዳኑ ውስጥ መገኘቱ፤ የእግዚአብሔርን ዘላለማዊነትና አስተማማኝነት ያረጋግጥልናል። ምንም እንኳ አምላካዊው በጎነት እንዴት እንደሚሠራ ለይተን ባናውቅም፤ እርሱ የሚታመን እንደሆነ ግን እናውቃለን። እርሱ የፈጠረው ዩኒቨርስ ባህሪያትም ሆነ ሕግጋት የማይለዋወጡ ናቸው። እውነተኛ ነፃነት እና ደህንነት የሚሰጠን ይህ እውነታ ነው።

“እግዚአብሔርን አስተማማኝ እና እምነት የሚጣልበት አምላክ ያደረገው፤ በሕግ ላይ ተመስርቶ የመሥራቱ እውነታ ነው። ፈቃዱና ሕጉ አንድ ናቸው። ትክክል የሆነው ትክክል ነው--ምክንያቱም ይህ ግንኙነትን ምርጥ በሆነ መንገድ እንደሚገልጽ እግዚአብሔር ይናገራል። ስለዚህ የእግዚአብሔር ሕግ በጭራሽ ከሥርዓት ውጪ ለሆነ ወይም ለድንገተኛ ሁናቴ ተገዢ አይደለም። ሕጉ በዩኒቨርስ እጅግ ተረጋግቶ ሰፍኗል።”—Walter R. Beach, Dimensions in Salvation (Washington, D.C.: Review and Herald Publishing Association, 1963), p. 143. የእግዚአብሔር ሕግ አንድን ሰው ከኃጢአት ማዳን ካልቻለ ለምን የቃል ኪዳኑ አካል አደረገው? (አሞጽ 3:3)



ግንኙነት--ስምምነት እና ውህደት ይፈልጋል። እግዚአብሔር የዓለም ፈጣሪ ብቻ ሳይሆን የመንፈስ ገዢዋ ጭምር እንደመሆኑ፤ ብልህ ፍጥረታቱ ከእርሱ ጋር በደስታና በውህደት ይኖሩ ዘንድ ሕግ እጅግ ወሳኝ ነው። የፈቃዱ መገለጫ የሆነው ሕግ የአምላካዊውን መንግሥት ሕገ-መንግሥት ይዟል። ይህ ሕግ በተፈጥሮው የቃል ኪዳኑ አደረጃጀት እና የግንኙነት ደንብ ወይም ግዴታ ነው። ዓላማው ማዳን ሳይሆን፤ ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ግዴታ (ትእዛዛት፡ 1-4) እና ከባልጀራችን ጋር ያለንን ግዴታ (ትእዛዛት፡ 5–10) ለመግለጽ ነው። በሌላ አነጋገር እግዚአብሔር የቃል ኪዳን ልጆቹ በደስታና ደኅንነታቸው በተጠበቀ አኳኋን እንዲኖሩ ያቀደውን የሕይወት ዘይቤ ያሳያል። እስራኤላውያን በሌላ የሕይወት ፍልስፍና መንገድ እንዳይተኩት ያግዳል። አማኙን በአምላካዊው ልብ የሚለውጥ ጸጋ ወደ ፈቃዱ እና ባህሪው ማምጣት የቃል ኪዳን ግንኙነቱ ዓላማ ነበር--ነውም።

ዙሪያዎን ይመልከቱ። ሕገ-ወጥነት እያስከተለ ያለውን አስከፊ ውጤት ማየት አይችሉም? በእራስዎ ሕይወት ውስጥ እንኳ፣ የእግዚአብሔርን ሕግ በመጣስ የደረሰ የተወሰነ ጉዳት ማየት አይችሉም? እነዚህ እውነታዎች የእግዚአብሔርን ሕግ መልካምነት ለማረጋገጥ እንዴት ይረዱናል? ሕግ--ከእርሱ ጋር ላለን ግንኙነት ወሳኝ ክፍል መሆን ያለበት ለምንድን ነው?



ግንቦት 12
May 20

ቢሆን…


የሚከተሉትን ጥቅሶች ይመልከቱ። የሚያመሳስላቸው አንድ ነጥብ ምንድን ነው? ስለ ኪዳኑም ባህሪ ምን ያስተምራሉ?

ዘፍ. 18:19_________________________________________________________

ዘፍ. 26:4-5________________________________________________________

አፀ. 19:5__________________________________________________________

ዘሌዋ. 26:3________________________________________________________

እግዚአብሔር ለአብርሃም ታማኝነትና ታዛዥነት ግልጽ ማረጋገጫ ይሰጣል፡ “ትዕዛዜን፣ ሥርዐቴንና ሕጌን በመጠበቁ” (ዘፍ. 26፡5)። እግዚአብሔር በቃል ኪዳኑ ውስጥ እንዲህ ዓይነቱን የአኗኗር ዘይቤ ከሰብዓዊው አጋር እንደሚጠብቅ በተዘዋዋሪ ቀርቦ እንመለከታለን። በሲና ስለሆነው የቀረበው የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ኪዳን ሙሉ መግለጫ የታዛዥነት ሁናቴዎች ከቃል ኪዳኑ መሠረታዊ ገጽታዎች አንዱ መሆናቸውን በግልጽ ያሳያል።

ዘፀ. 19፡5 “ብትታዘዙኝ…” ሲል ጉዳዩን በግልጽ ያስቀምጥልናል። የቃል ኪዳኑ በሁኔታዎች ላይ የተመረኮዘ ገጽታ ሊካድ አይችልም። ምንም እንኳ ኪዳናዊ የተስፋ ቃሎቹ የማይገቧቸውና በነፃ የተሰጧቸው የጸጋ ስጦታዎች ቢሆኑም--ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ የተሰጡ ግን አልነበሩም። ሕዝቡ አምላካዊውን ስጦታ ሊቃወም፣ ጸጋውን ሊክድ እና ከአምላካዊው የተስፋ ቃል ማፈገፍግ ይችላል። ኪዳኑ እንደ ደኅንነት ሁሉ የመምረጥ ነጻነትን አይጋፋም። ሰዎች የመዳን ግንኙነት ውስጥ ከእርሱ ጋር ይገቡ ዘንድ እግዚአብሔር አያስገድዳቸውም። ኪዳኑን በነጻ ያቀርብላቸዋል እንጂ አይጭንባቸውም። እነሆ እያንዳንዱ በግሉ ይቀበል ዘንድ ግብዣ ቀርቦለታል።

እርሱም ሆነ እርሷ ግብዣውን በግል ሲቀበሉ ግዴታዎች ይከተላሉ--ኪዳናዊ በረከቱን እንደ ማግኛ መንገድ ሳይሆን፤ ኪዳናዊ በረከቱን እንደ መቀበያ ውጫዊ መገለጫ። እስራኤል መታዘዝ ያለባት ተስፋዎቹን ለማግኘት ሳይሆን፣ የተስፋ ቃሎች በእርሷ ውስጥ መፈጸም ይችሉ ዘንድ ነው። መታዘዟ በጌታ መባረክ ምን እንደሚመስል የሚያሳይ ነበር። መታዘዝ እግዚአብሔር ተገድዶ በረከቶችን እንዲሰጥ አያደርግም። ይልቁንም መታዘዝ--የእምነት በረከት መገለጥ የሚችልበትን ከባቢያዊ ሁኔታ ይፈጥራል።

“በምትወርሷት ምድር በሕይወት ለመኖር እንድትችሉ፣ ለመልካም እንዲሆንላችሁና ዕድሜያችሁም እንዲረዝም፣ አምላካችሁ እግዚአብሔር ባዘዛችሁ መንገድ ሁሉ ሂዱ።” (ዘዳ. 5፡33)። ጌታ--የሚታዘዙኝ ከሆነ እነዚህን በረከቶች ያገኛሉ እያለ ነው? ወይስ--ብትታዘዙ እነዚህ በረከቶች ውጤት ሊያስገኙ ይችላሉ፤ ምክንያቱም መታዘዝ በረከቶችን በእናንተ ላይ ማፍሰስ የምችልበትን መንገድ ይከፍትልኛል--እያለ ነው? በሁለቱ ጽንሰ ሀሳቦች መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው?



ግንቦት 13
May 21


ተጨማሪ ሀሳብ


የሚከተሉትን ጽሑፎች ያንብቡ። የዘመናት ምኞት፡ “ክርክር” ገጽ 623-633 እንዲሁም የኃይማኖት አባቶች እና ነቢያት፡ “ሕጉና ኪዳኑ” ገጽ 410423። ማቴ. 22፡34-40 የሚከተሉትን ሁለት ነጥቦች በተሻለ እንድንረዳ እንዴት ይረዳናል?

(1) የእግዚአብሔር ሕግ በቃል ኪዳኑ ውስጥ ያለውን ቦታ እና ትርጉም፤

(2) ቃል ኪዳኑ ከግንኙነት ጋር ያለውን ተመሳሳይ ጽንሰ ሀሳብ፤

“አንድ ሰው በሚኖረው ጽናት እና በክርስቶስ ጸጋ የእግዚአብሔርን ሕግጋት ማክበር ከመጀመሩ አስቀድሞ በልቡ ውስጥ ፍቅር መኖር አለበት (ሮሜ 8፡3-4)። መታዘዝ ያለ ፍቅር ከንቱ ነው። ነገር ግን ፍቅር ሲኖር በትእዛዛቱ በተገለጸው መሰረት የግለሰቡ ህይወቱን ፈር አስይዞ ሳይውል ሳያድር ከአምላካዊው ፈቃድ ጋር ስምሙ ይሆናል።”—The SDA Bible Commentary, vol. 5, p. 484. “እግዚአብሔር በቅዱስ ሕጉ መርኅና አስተምህሮ መሠረት ለሕይወት የሚበጅ ፍጹም ደንብ ሰጥቶአል። ከዚህ ሕግ አንዲት ነቁጥ እንኳ ሳይነካና ሳይለወጥ፣ በሰው ልጆች ላይ ይገባኛል የሚለው ጥያቄ እስከ ጊዜው ማብቂያ ድረስ ይኖራል።

ክርስቶስ ሕጉን ሊያጎላ እና የተከበረ ሊያደርግ መጣ። እጅግ ሰፊ በሆነው--ፍቅር ለእግዚአብሔር እና ፍቅር ለሰው መሰረት ላይ የታነጸ መሆኑን አሳየ። ለመርኅዎቹ የሚደረግ መታዘዝ መላውን የሰው ልጅ ግዴታ አጠቃልሎ ይይዛል። እርሱ በገዛ ራሱ ሕይወት ለእግዚአብሔር ሕግ የመታዘዝ ምሳሌ ተወ። ሕጉ የሚጠይቃቸው ነገሮች ከውጪያዊ ድርጊቶች ባሻገር እንዴት እንደሚገዝፉ እና የልብን ሀሳቦች እና ዓላማዎች እንደሚገነዘቡ በተራራው ላይ ስብከቱ አሳየ።”—Ellen G. White, The Acts of the Apostles, p. 505.




የመወያያ ጥያቄዎች



፡ 1.ከፍርሃት ገመድ ይልቅ የፍቅር ክር የሰው ልጆችን ወደ እግዚአብሔር ለመሳብ ለምን የበለጠ ጉልበት ይኖረዋል?

2.“ ‘ “ጌታ አምላክህን በፍጹም ልብህ፣ በፍጹም ነፍስህ፣ በፍጹም ሐሳብህ ውደድ” ’ ” (ማቴ 22፡37) የሚለው ትእዛዝ የመጀመሪያውና ትልቁ ትእዛዝ የሆነው ለምንድን ነው?

3.ታዋቂዋ ፈረንሳዊት ፈላስፋ ሲሞን ዌይል “ ‘ከሁሉ በቀዳሚነት የሚያሻው ሥርዓትና ደንብ ነው’ ” ብላ ጽፋ ነበር። (Quoted in Russell Kirk, The Roots of American Order [Washington, D.C.: Regnery Gateway, 1992], p. 3) ይህን አባባሏን ከዚህ ሣምንት ጥናት ዐውድ አኳያ እንዴት ያስተውሉታል? በተለይ ከሕግ ጽንሰ ሀሳብ ጋር ከሚኖረው ዝምድና?

ማጠቃለያ፡ የእግዚአብሔር ሕግ የቃል ኪዳኑ ዋና አካል ነበር። እውነተኛ የጸጋ ኪዳንም እንዲሁ ነበር። ሆኖም ጸጋ የሕግን አስፈላጊነት ፈጽሞ አይሽርም። በተቃራኒው ሕጉ ጸጋን በሚቀበሉ ሰዎች ሕይወት ውስጥ የሚታይና ጸጋ የሚገለጥበት መንገድ ነው።




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA union SSL