የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

የተስፋው ቃል፡ የእግዚአብሔር ዘላለማዊ ኪዳን


2ኛ ሩብ ዓመት 2021

ከሚያዝያ 30 - ግንቦት 6

7ኛ ትምህርት

May 08 - May 14




ቃል ኪዳን በሲና ተራራ



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ዘዳ. 1:29–31፣ ሆሴ 11:1፣ ራእ. 5:9፣ ዘዳ. 29:10–13፣ ዘፀ. 19:5-6፣ ሮሜ 6:1-2፣ ራእ. 14:12፣ ሮሜ 10:3።


የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ“‘በግብፅ ላይ ያደረኩትን፤ በንስርም ክንፍ ተሸክሜ ወደ ራሴ እንዴት እንዳመጣኋችሁ እናንተ ራሳችሁ አይታችኋል’ ” (ዘፀ. 19:4)

ሰ ባት ልጆች ካሉት ቤተሰብ ትንሹና የመጨረሻው ልጅ አነስተኛ አደጋ ገጥሞት ወደ ሆስፒታል ተወሰደ። በቤታቸው እምብዛም በቂ ነገር ስላልነበር ከግማሽ ብርጭቆ ወተተት በላይ ተሰጥቶት አያውቅም። ብርጭቆው ሙሉ ከሆነ ሁለት ልጆች እንዲካፈሉት ይደረግ የነበረ ሲሆን፤ መጀመሪያ የሚጠጣው ልጅ ከሚፈቀድለት መጠን በላይ እንዳይጠጣ መጠንቀቅ ነበረበት። ታዲያ ይህ ትንሽ ልጅ በሆስፒታል ተገቢው ህክምና ከተደረገለት በኋላ ነርሷ አንድ ትልቅ ብርጭቆ ሙሉ ወተት አመጣችለት። ለጥቂት ጊዜ በጉጉት ወተቱን ከተመለከተ በኋላ በቤት ውስጥ የነበረው ችግር ትውስ አለውና ‘ምን ያህል ልጠጣ?’ ሲል ጠየቀ። የሚያበሩ ዐይኖች እና ሞላ ያለ ሰውነት ያላት ነርስ ‘ሁሉንም ጭልጥ አርገህ ጠጣ! የኔ ልጅ’ ብላ መለሰችለት። ”—H. M. S. Richards, “Free Grace,” Voice of Prophecy News, June 1950, p. 4.

የጥንት እስራኤላውያን ልክ እንደዚህ ልጅ እና እንደ እኛ ዘመን፤ ከደኅንነት የውሃ ጉድጓድ ጭልጥ አድርጎ የመጠጣት ልዩ መብትና ጥቅም ተሰጥቷቸው ነበር። እስራኤላውያን ከዘመናት ባርነት እና ጭቆና መዳናቸው አስደናቂ የመለኮታዊ ጸጋ ማሳያ ነበር። በተመሳሳይ፤ መለኮታዊው ጸጋ የገዛ ራሳችንን ከኃጢአት ነጻ መውጣት አስከትሏል።

ሣምንቱ በጨረፍታ፡ ጌታ ከእስራኤል ጋር ያለውን ግንኙነት ለመግለጽ ምን ዓይነት ምሣሌያዊ ትዕይንቶችን ተጠቅሟል? የዘፀአት እና የሲና ታሪኮች ከግል ደኅንነት ጋር በምን ዓይነት መንገድ ይመሳሰላሉ? በሲና ቃል ኪዳን፤ የሕጉ ሚና ምን ነበር?



ግንቦት 1
May 9

በንስር ክንፍ


እስራኤል እንደ ሕዝብ ከረጅምና አስቸጋሪ ምዕተ ዓመታት አንስቶ በግብፃውያን አረማዊ አምልኮ ተዘፍቀው መኖራቸው፤ በእግዚአብሔር፣ በእርሱ ፈቃድና መልካምነት ዙሪያ የነበራቸው ዕውቀትና ተሞክሮ እንዲደበዝዝ ማድረጉ ዕሙን ነው። ታዲያ ጌታ ወደ ራሱ አሸንፎ ሊወስዳቸው የሚችለው እንዴት ነው? ለጀማሪዎች፤ ለእስራኤል ያለውን ፍቅር እውነተኝነት ያሳየ ሲሆን፤ ይህን ያደረገው በታላላቅ የማዳን ሥራዎቹ ነበር። ሕዝቡን በፍቅር በማግባባትና ለቃል ኪዳናዊ ዕቅዱ የፍቅር ምላሽ በማቅረብ ይጀምራል። እግዚአብሔር በመጀመሪያ--በሲና ያደረገላቸውን በቸርነት የተሞሉ ድርጊቶች ሕዝቡን አስታውሷል። ጌታ እስራኤላውያንን ከግብፅ ወደ ሲና ያመጣበትን መንገዶች የሚገልጹ ሁለት ምሳሌዎች ምንድን ናቸው?

ዘፀ. 19፡4፣ ዘዳ. 32፡10-12 ___________________________________________

ዘዳ. 1፡29-31፣ ሆሴ 11፡1 ___________________________________________

ምሣሌዎቹ እግዚአብሔር ለሕዝቡ ስላለው አመለካከት፤ ለእስራኤል (ለእኛ ጭምር) ምን ያስተምራሉ? እግዚአብሔር አቅመቢስነታችንን በሚገባ የሚያውቅ አምላክ መሆኑን እነዚህ ምሣሌዎች ያመለክታሉ። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ መዝ. 103፡ 13-14። በንስር እና ለልጁ ጥንቃቄ በሚያደርግ ወላጅ በቀረበው ምሣሌ የደኅንነታችን ጉዳይ እግዚአብሔርን እንደሚያሳስበው እናስተውላለን። ርኅሩኅ፣ ደጋፊ፣ ጠባቂና አበረታች የሆነው አምላክ ምኞቱ እኛን ወደ ሙሉ ብስለት ማምጣት ነው።

“ንስር ለጫጩቶቿ ባላት ያልተለመደ ጥንቃቄ ትታወቃለች። የምትኖረውም በተራራ አናት ላይ ነው። ጫጩቶቿ እንዲበሩ ለማስተማር በጀርባዋ ላይ ተሸክማ የሲና መስኮች ጎልተው ወደሚታዩባቸው ከፍታዎች ሽቅብ ትበርና ትለቃቸዋለች። ጫጩቱ ገና ጨቅላና ለመብረር ግራ የሚጋባ ከሆነ አባት ንስር ከበታቹ አንዣቦ በጀርባው ላይ ያሳርፈውና መልሶ ወደ ላይ ይዞት ይበራል። መለኮታዊው ድምፅ እንዲህ ሲል ይናገራል ‘በንስርም ክንፍ ተሸክሜ ወደ ራሴ እንዴት እንዳመጣኋችሁ እናንተ ራሳችሁ አይታችኋል።’ ”—George A. F. Knight, Theology of Narration (Grand Rapids, MI: William B. Eerdmans Publishing Company, 1976), p. 128.

እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ፍላጎት አንዳችን ከሌላችን ጋር ካለን ፍላጎት አኳያ ያነጻጽሩ። እርሱ ለእኛ ያለው አሳቢነት ለሌሎች በሚኖረን አሳቢነት ዙሪያ እንዴት ተጽእኖ ያደርጋል? በግል ተሞክሮዎ ላይ በመመስረት እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ራስ ወዳድ ያልሆነ ፍላጎት ለመግለጽ ምን ዓይነት ሥዕላዊ መግለጫዎች ወደ አእምሮዎ ሊመጡ ይችላሉ? ከግል ተሞክሮዎ የራስዎ የሆኑ ጥቂት ሐሳቦችን ይፍጠሩ--ከሚኖሩበት ባህል ወዘተ። ለሰንበት ትምህርት ጥናት አባላት ያካፍሉ።



ግንቦት 2
May 10

የመዳን ምሣሌ


“ ‘ስለዚህ ለእስራኤላውያን እንዲህ በላቸው፤ “እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ከግብፃውያን ቀንበር አወጣችኋለሁ። ለእነርሱ ባሪያ ከመሆን ነጻ አወጣችኋለሁ፤ በተዘረጋች ክንድና በታላቅ ፍርድ እቤዣችኋለሁ። የራሴ ሕዝብ አደርጋችኋለሁ፤ እኔም አምላክ እሆናችኋለሁ ከግብፃውያን ቀንበር ያላቀቅኋችሁ እኔ እግዚአብሔር አምላክ መሆኔንም ታውቃላችሁ።” ’ ” (ዘፀ. 6፡6-7)።

ከላይ የቀረቡትን ጥቅሶች ይመልከቱ፡ እንደ ከዚህ በፊቱ ሁሉ፣ እግዚአብሔር ከሰዎች ጋር በገባው ኪዳናዊ ግንኙነት ባለው ሚና ምን ዓይነት መርኅዎችን እንመለከታለን? (በእነዚህ ቁጥሮች ውስጥ ቃሉ ስንት ጊዜ እንደተጠቀሰ ትኩረት ያድርጉ) የእስራኤል ከግብፅ ባርነት ነፃ መውጣት እና የኖኅ ከቤተሰቡ ጋር ከጥፋት ውሃ መዳን በሙሴ ጽሑፎች ሁለት ታዋቂ የመዳን ክስተቶች ናቸው። ሁለቱም ስለ ደኅንነት ሳይንስ ግንዛቤ ያስጨብጣሉ። ሆኖም መሠረታዊ የሆነውን ምሳሌ የሚሰጠን በተለይ፣ የዘፀአት ክስተት ነው። እግዚአብሔር (በሙሴ በኩል) “እቤዣችኋለሁ” (ዘፀ. 6፡6) ብሎ ሲናገር፤ እኔ ራሴ ቤዛ እሆናችኋለሁ እያለ ነበር።

“በቁ. 6 ላይ መቤዠት የሚለው ቃል፤ በተለይ አንድ የቤተሰብ አባል በዕዳ ወደ ባርነት እየገባ ከሆነ፤ እርሱን መልሶ መግዛትን ወይም ስለ እርሱ ቤዛ መሆንን ያመላክታል። እስራኤል ሊቤዣት የሚችል ምንም ዓይነት ምድራዊ ዘመድ አልነበራትም። ነገር ግን እግዚአብሔር አሁን ዘመዷና ቤዛዋ ሆነ።”—Bernard L. Ramm, His Way Out (Glendale, CA: Regal Books Division, G/L Publications, 1974), p. 50. አምላካዊውን “መቤዠት” ወይም ሕዝቡን ከባርነት መልሶ የመግዛት ጽንሰ ሀሳብ እንዴት ያስተውሉታል? መከፈል የነበረበት ዋጋ ምን ነበር? ያ ምን ያህል ዋጋ እንዳለን አስመልክቶ ምን ይነግረናል? (ማር. 10:45፣ 1ጢሞቴ. 2:6፣ ራእ. 5:9)

እግዚአብሔር በዘፀ. 3፡8 እስራኤልን ለማዳን “ወርጃለሁ” ይላል። ይህ እግዚአብሔር ከሰዎች ጋር ያለውን መስተጋብር የሚገልጽ የተለመደ የዕብራይስጥ ግሥ ነው። እግዚአብሔር በሰማይ፤ እኛ ደግሞ በምድር እንደመሆናችን፤ እርሱ እንደ አምላክ ወደ ምድር ሲወርድ ብቻ እኛን ሊቤዠ ይችላል። በጽንሰ ሀሳቡ እውነተኛ ፍቺ መሠረት የሱስ ወደ ምድር ሲወርድ፣ በመካከላችን ሲኖር፣ ሲሠቃይ፣ ሲሞት እና ስለ እኛ በትንሣኤ ሲነሣ ብቻ ልንዋጅ እንችላለን። “ቃልም ሥጋ ሆነ፤ በመካከላችንም አደረ” (ዮሐ. 1፡14) በሚል የቀረበው ጥቅስ፤ እግዚአብሔር እኛን ለማዳን ወረደ የተሰኘው አባባል ሌላው መግለጫ ነው።



ግንቦት 3
May 11

የሲናው ቃል ኪዳን


የዘፀአት መጽሐፍ የአንባቢውን ትኩረት ወደ ሶስት ዋና ዋና ክስተቶች ይስባል። ልክ እንደ ሦስት ተራሮች፣ ዘፀአት ራሱ፣ የቃል ኪዳኑ መመስረት እና የመገናኛ ድንኳኑ ቤተ መቅደስ ከኮረብቶች ግርጌ በላይ ከፍ ማለት ነው። ከዘፀ. 19 እስከ 24 ተመዝግቦ የሚገኘው የኪዳኑ መመስረት ከሦስቱ ተራሮች እጅግ የገዘፈው ነው። ከዘፀ. 19 እስከ 24 ያለው አጭር መግለጫ የክስተቶቹን ቅደም ተከተልና ግንኙነት ያሳያል። ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን ሁሉንም ጥቅሶች ለማውጣት ጊዜ ባይኖርዎትም እንኳ በክስተቶች ቅደም ተከተል ላይ ያተኩሩ፡

1.እስራኤላውያንን ጌታ ከታደጋቸው በኋላ በስፍራው መድረሳቸውና በሲና መስፈራቸው (ዘፀ. 19፡1-2)

2.እግዚአብሔር ከእስራኤል ጋር የቃል ኪዳን ውል መግባቱ (ዘፀ. 19፡7-8)

3.እስራኤል ቃል ኪዳኑን በመቀበል የሰጠው ምላሽ (ዘፀ. 19፡7-8)

4.ቃል ኪዳኑን በመደበኛ የመቀበል ዝግጅት (ዘፀ. 19፡9-25)

5.የዐሥርቱ ትእዛዛት መታወጅ (ዘፀ. 20፡1-17)

6.ሙሴ እንደ ቃል ኪዳኑ አማላጅ (ዘፀ. 20፡18-21)

7.የቃል ኪዳኑ መርኅዎች መቅረባቸው (ዘፀ. 20፡22-23፡22)

8.የቃል ኪዳኑ መጽናት (ዘፀ. 24፡1-18)

ይህ ቃል ኪዳን በደኅንነት እቅድ ወሳኝ ሚና ይጫወታል። በመጽሐፍ ቅዱስ በቅደም ተከተል ከተቀመጡት አንዱ የሆነው ይህ አራተኛው ኪዳን (ከአዳም፣ ኖኅ እና አብርሃም ቀጥሎ) ሲሆን፤ በዚህኛው ውስጥ እግዚአብሔር ከበፊቶቹ በበለጠ ራሱን ይገልጻል--በተለይ አጠቃላዩ የመገናኛ ድንኳን ሥርዓት ከመቋቋሙ አኳያ። በመሆኑም የመገናኛ ድንኳኑ እርሱ የደኅንነትን ዕቅድ ለሕዝቡ የሚያሳይበት፤ እነርሱ ደግሞ ይህንኑ እውነት ለዓለም የሚገልጡበት መንገድ ይሆናል።

ምንም እንኳ ጌታ እስራኤልላውያንን ከግብፅ ባርነት ነፃ ቢያወጣቸውም፣ መዋጀት ከአካላዊ ግዞተኝነት ነፃ ከመሆን የላቀ ግዙፍ አንደምታ እንዳለው እንዲገነዘቡ ፈልጎ ነበር። እነርሱን የመጨረሻ ባርነት ከሆነው ከኃጢአት ሊዋጃቸው ሻተ። ሆኖም ይህ እውን መሆን የሚችለው በመገናኛ ድንኳኑ ተምሳሌታዊ እና ሥርዓታዊ አገልግሎቶች በተማሩት መሠረት በመሲሕ መሥዋዕትነት ብቻ ነበር። ከባርነት ተዋጅተው ብዙም ሳይቆዩ ሕጉ በመሰጠቱ እስራኤላውያን የመገናኛ ድንኳኑን መሥራት መማራቸው ብዙም የሚደንቅ አይሆንም። እግዚአብሔር በዚያ ውስጥ የኪዳኑ እውነተኛ ትርጉም እና ዓላማ የሆነውን የደኅንነትን ዕቅድ ገልጦላቸው ነበር። ቃል ኪዳኑ ጌታ ለወደቀው ሰብዓዊ ዘር የሰጠው የመዳን ኪዳን መሆን ካልቻለ ምንም ነው። በኤደንም ሆነ በሲና የነበረው ይኸው ነው።

በእግዚአብሔር እና በእስራኤል ሕዝብ መሀል ቃል ኪዳን ለምን አስፈለገ? (ዘዳ. 29፡10-13። የኪዳኑን ዝምድናዊ ገጽታ በድጋሚ ያጢኑ።)

ግንቦት 4
May 12

እግዚአብሔር እና እስራኤል


“አሁንም በፍጹም ብትታዘዙኝና ቃል ኪዳኔን ብትጠብቁ እነሆ ከአሕዛብ ሁሉ እናንተ የተወደደ ርስቴ ትሆናላችሁ፤ ምንም እንኳ ምድር ሁሉ የእኔ ብትሆንም፣ እናንተ ለእኔ የመንግሥት ካህናት የተቀደሰ ሕዝብ ትሆናላችሁ፤ ለእስራኤላውያን የምትነግራቸው ቃሎች እነዚህ ናቸው” (ዘፀ. 19፡5-6)።

ጌታ በእነዚህ ቁጥሮች አማካይነት ለእስራኤል ልጆች የኪዳን ሀሳብ እያቀረበ እንደሆነ ይስተዋላል። ምንም እንኳ በአንድ በኩል ጌታ ጥሪ ቢያቀርብላቸውም፤ ነገር ግን ጥሪው ያለ እነርሱ ምርጫ ወዲያውኑ ተፈጻሚ የሚሆን አልነበረም። መተባበር ነበረባቸው። ከግብፅ መውጣታችን በራሱ የእነርሱን ትብብር ያካተተ ነበር። ጌታ የነገራቸውን ባይፈጽሙ ኖሮ (የበራቸውን መቃን ደም መቀባትና፣ የመሳሰሉት) አርነት ባልወጡ ነበር። ጉዳዩ ያን ያህል ቀላል ነበር። ጌታ “ብትወዱም ባትወዱም ለእኔ የተለያችሁ ርስቴ እና የመንግሥት ካህናት ትሆናላችሁ” አላላቸውም። ነገሩ በዚህ መልኩ የማይሠራ ሲሆን፤ ጥቅሶቹም እንዲያ አይሉም።

በመግቢያው የቀረቡትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ዘፀ. 19፡5-6። ጌታ እየተናገረ ያለውን ከጽድቅ በእምነት አውድ እንዴት ያስተውሉታል? ጌታን ስለ መታዘዝ የሚናገሩት እነዚህ ጥቅሶች የጽድቅ በእምነት ጽንሰ ሀሳብን ውድቅ ያደርጋሉ? የሚከተሉት ጥቅሶች መልሱን ማስተዋል እንዲችሉ እንዴት ይረዱዎታል? ሮሜ 3:19-24፣ ሮሜ 6:1-2፣ ሮሜ 7:7፣ ራእ. 14:12።



“በመታዘዛችን መዳን አናገኝም። መዳን በእምነት የምንቀበለው የእግዚአብሔር ነጻ ስጦታ ነው። ነገር ግን መታዘዝ የእምነት ፍሬ ነው።”—Ellen G. White, Steps to Christ, p. 61.

ጌታ ለእስራኤል ሕዝብ ምን ለማድረግ ፈቃደኛ እንደነበረ ያስቡ፡ በታምራዊ መንገድ ከግብፅ ባርነት ማዳን ብቻ ሳይሆን፣ ነገር ግን የራሱ ርስት እና የመንግሥት ካህናት ሊያደርጋቸው ፈለገ (ከግብፅ እንደ መውጣታቸው ጊዜያዊ እና ዘላለማዊ)። ከእርሱ ጋር ያላቸው ግንኙነት በእርሱ ማዳን ላይ የተመሠረተ እንዲሆን በማድረግ፤ ጌታ እነርሱን በጥንቱ ዓለም አስገራሚ ወደሚያደርጋቸው መንፈሳዊ፣ አእምሮአዊ እና ሥነ ምግባራዊ ከፍታ ሊያወጣቸው ተመኘ። እነርሱን የመጠቀም ዓላማ ወንጌልን ለሕዝቦች እንዲሰብኩ ሲሆን፤ በምላሹ ከእነርሱ የሚጠበቀው መታዘዝ ነበር። ከጌታ ጋር ያለን የግል፣ አንድ ለአንድ ተሞክሮ በዛሬው ጥናታችን የምንመለከተውን መርኅ በምን መንገድ በተመሳሳይ ሊያንጸባርቅ ይገባል?





ግንቦት 5
May 13

ቃል መግባት፣ ቃል መግባት… (ዘፀ. 19፡8)


ነገሩን ላይ ላዩን ሲያዩት መልካም ይመስላል። ጌታ ህዝቡን ያድናል፣ የቃል ኪዳኑን ተስፋዎች ይሰጣቸዋል፣ እነሱም ይስማማሉ፡ ጌታ የሚጠይቃቸውን ሁሉ ለማድረግ እሺታቸውን ይገልጻሉ። እንግዲህ ይህ “በሰማይ የተዘጋጀ” ውል ነው። አይደል? ጥቅሶቹን ያንብቡ። እስራኤላውያን ለቃል ኪዳኑ ስለ ሰጡት ምላሽ ምን ዓይነት ግንዛቤ ያስጨብጡናል?

ሮሜ 9:31-32_____________________________________________________

ሮሜ 10:3_________________________________________________________

ዕብ. 4:1-2________________________________________________________

እግዚአብሔር ለሚጠይቀን ለማንኛውም ነገር ከእርሱ ጋር ያለን ግንኙነት በእምነት ላይ የተመሠረተ መሆን አለበት። እምነት ሥራ የሚከተልበትን መሠረት ይሰጣል። ሥራ በራሱ የቱንም ያህል ንጹህ ተነሳሽነት፣ ቅንነትና ብዛት ቢኖረው እንኳ፤ ቅዱስ በሆነው አምላክ ፊት ተቀባይነት ሊያስገኝልን አይችልም። ይህ በእስራኤላውያን ዘመን እንዳልሆነ ሁሉ በእኛም ጊዜ ሊሆን አይችልም። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ በተደጋጋሚ ስለ ሥራ አጽንኦት ከመስጠቱ አኳያ ሥራ በእግዚአብሔር ፊት ተቀባይነት ሊያስገኝልን የማይችለው ለምንድን ነው? (ኢሳ. 53:6፣ ኢሳ 64:6፣ ሮሜ 3:23)

እንዳለመታደል ሆኖ ዕብራውያን ሕዝቦች መታዘዛቸውን የመዳናቸው ውጤት ሳይሆን የዳኑበት መንገድ አድርገው ያምኑ ነበር። በእምነት የሚገኘውን የእግዚአብሔር ጽድቅ ሳይሆን ለሕጉ በመታዘዛቸው የጽድቅ ባለቤት ለመሆን ፈለጉ። የሲና ቃል ኪዳን፤ ምንም እንኳ ብዛት ያላቸው ዝርዝር መመሪያዎችና ሕጎች ይዞ ቢመጣም፤ ልክ እንደ ቀዳሚዎቹ ኪዳኖች ሁሉ የጸጋ ቃል ኪዳን ሆኖ የተነደፈ ነበር። በነጻ የተሰጠው ይህ ጸጋ ወደ መታዘዝ የሚወስድ የልብ መለወጥ ያመጣል። በእርግጥ ችግሩ ለመታዘዝ መሞከራቸው አልነበረም (ቃል ኪዳኑ እንዲታዘዙ ይጠይቃል)። ይልቁንም ችግሩ የነበረው እነርሱ የሰጡት የ “መታዘዝ” ዓይነት ላይ ሲሆን--የሕዝቡ የኋላ ታሪክ እንደሚያሳየው ይህ በእርግጥ መታዘዝ አልነበረም።

ጥቅሱን ያንብቡ (በተለይ የመጨረሻውን ክፍል)፡ ሮሜ 10፡3። ጳውሎስ ምን እያመለከተ ነው? የራሳቸውን ጽድቅ ለመመስረት በሚፈልጉ ሰዎች ላይ ምን ይከሰታል? እንዲህ ያለው ሙከራ ወደ ኃጢአት፣ እርክስና እና አመጻ ማምራቱ አይቀሬ የሆነው ለምንድን ነው? እስቲ ወደ ራሳችን ሕይወት እንመልከት። ተመሳሳይ ነገር የማድረግ አደጋ ውስጥ አይደለንምን?

ግንቦት 6
May 14


ተጨማሪ ሀሳብ


የኃይማኖት አባቶች እና ነቢያት መጽሐፍ፡ “ከግብፅ መውጣት” ገጽ፡ 314-323፣ “ከቀይ ባሕር ወደ ሲና” ገጽ፡ 324-338 “ለእስራኤል የተሰጠው የእግዚአብሔር ሕግ” ገጽጽ 339-354 “የጭቆና መንፈስ በሕጋዊ ኃይማኖት መሠረት ለመኖር መፈለግንና የሕግን ጥያቄዎች በራሳችን ኃይል ለመፈጸም መጣርን ይወልዳል። ለእኛ ተስፋ የሚኖረው በክርስቶስ የሱስ በማመን የሚገኘው የጸጋ ቃል ኪዳን ወደ ሆነው አብርሃማዊ ቃል ኪዳን ስንመጣ ብቻ ነው። አብርሃም በተሰበከለት ወንጌል ላይ ተስፋ እንዳደረገ ሁሉ፤ እኛም በዚያው ተመሳሳይ ወንጌል ላይ ተስፋ እናደርጋለን። አብርሃም፤ የእኛም እምነት ደራሲና ፈጻሚ ወደ ሆነው የሱስ ተመለከተ።”—Ellen G. White Comments, The SDA Bible Commentary, vol. 6, p. 1077.

“እስራኤላውያኑ በምድረ ግብፅ የግዞት ዘመናቸው በከፍተኛ ሁኔታ የእግዚአብሔርን ሕግ ዕውቀት በመሳት አማኝ ካልሆኑ ሕዝቦች መርኅ፣ አስተምህሮ፣ ልምድና ባህል ጋር ተቆራኝተው ነበር። እግዚአብሔር እነዚህን ሕዝቦች ወደ ሲና በማምጣት በገዛ አንደበቱ ሕጉን አወጀላቸው።” የኃይማኖት አባቶች እና ነቢያት፡ ገጽ 377


የመወያያ ጥያቄዎች



፡ 1.ቃል ኪዳናዊው ግንኙነት የእስራኤልን አካላዊ እና መንፈሳዊ ነፃነቶች ለማቆየት በምን መልኩ ተቀይሶ ነበር (ያስተያዩ፡ ዘሌዋ. 26:3-13 እና ዘዳ. 28:1-15)።

2.ጥቅሶቹን በድጋሚ ያንብቡ፡ ዘፀ. 19፡5-6። ጌታ “ምድር ሁሉ የእኔ ብትሆንም” ብሎ መናገሩን ልብ ይበሉ። ለምን እንዲህ ይላል--በተለይ ከእነዚህ ሕዝቦች ጋር ቃል ኪዳን ለመመስረት በፈለገበት በዚህ ዐውደ ሀሳብ? ስለ ሰንበት ያለን ግንዛቤ እና ትርጉም ከዚህ ጋር እንዴት ይጣጣማል?

3.ኃጢአታችንን ይቅር የተባልነው በአምላካዊው ጸጋ አማካይነት ብቻ መሆኑን እንረዳለን። የእምነት እና የመታዘዝ ሕይወት እንድንኖር የሚያስችለንን የእግዚአብሔር ጸጋ ሚና እንዴት እናስተውለዋለን? ማጠቃለያ፡ እግዚአብሔር በሲና ከእስራኤል ጋር የገባው ቃል ኪዳን የጸጋ ቃል ኪዳን ነበር። ሕዝቡን ከግብፅ ባርነት ባልተለመደ መንገድ ለማውጣቱ፣ በቸርነት እና በፍቅር የተሞላ እንክብካቤው ከበቂ በላይ ማስረጃ ሊቀርብለት የሚችለው እግዚአብሔር አምላክ፤ ነጻነታቸው የተጠበቀና የጎለበተ እንዲሆን የሚያደርግ የቃል ኪዳን ግንኙነት ውስጥ ከእርሱ ጋር እንዲገቡ ግብዣ አቀረበላቸው። ምንም እንኳ እስራኤል አዎንታዊ ምላሽ ቢሰጥም፤ በፍቅር የተነሣሣ እውነተኛ እምነት ይጎድላቸው ነበር። የኋላ ታሪካቸው እንደሚያመለክተው--በአመዛኙ የቃል ኪዳኑን እውነተኛ ተፈጥሮ በትክክል መረዳት ባለመቻላቸው በጽድቅ በሥራ ሥርዓተ አምልኮ አበላሹት። ለኃጢአተኞች የተዘረጋውን አስደናቂ ጸጋ ገሸሽ በማድረግ የእስራኤልን ውድቀት መከተል የለብንም።




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA union SSL