የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

የተስፋው ቃል፡ የእግዚአብሔር ዘላለማዊ ኪዳን


2ኛ ሩብ ዓመት 2021

ከሚያዝያ 16 - 22

5ኛ ትምህርት

Apr 24 - Apr 30




የቃል ኪዳኑ ልጆች



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ዘፍ. 15:1–3፣ ኢሳ. 25:8፣ 1ቆሮ. 2:9፣ ራእ. 22:1–5፣ 1ጴጥ. 2:9፣ ዘፍ. 11:4፣ ዘፍ. 12:2።


የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ “እኔም እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁል ጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ” (ማቴ. 28፡20)

ወ ላጅ አባት እና የአሥር ዓመት ሴት ልጃቸው የእረፍት ጊዜያቸውን በባህር ዳርቻ እያሳለፉ ነበር። ሁለቱም ጥሩ ዋናተኞች ቢሆኑም ከባሕሩ ዳርቻ የተወሰነ ርቀት ከሄዱ በኋላ ተለያዩ። በባሕሩ ሞገድ እየተገፉ ርቀው እየሄዱ መሆኑን የተገነዘቡት አባት፡ ‘ሜሪ ዕርዳታ ፍለጋ ወደ ባሕሩ ዳርቻ እየተመለስኩ ነው። ድካም ከተሰማሽ በጀርባሽ ተንጋለዪ። በዚያ ሁኔታ ቀኑን ሙሉ መቆየት ትችያለሽ። ተመልሼ እመጣልሻለሁ’ አሏት ድምፃቸውን ከፍ አድርገው።

“ብዙም ሳይቆይ ብዛት ያላቸው አሳሾች እና ጀልባዎች ትንሽዬዋን ልጅ ፍለጋ በባሕሩ ላይ መቅዘፍ ጀመሩ። ዜናውን የሰሙ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የሚሆነውን በጉጉት ይጠባበቁ ጀመር። ከአራት ሰዓት ፍለጋ በኋላ ከባሕሩ ዳርቻ በብዙ ርቀት ሜሪ ስትገኝ--ተረጋግታ በጀርባዋ ተንጋላ እየተንሳፈፈች ነበር። ያገኟት አሳሾች ያቺን የከበረች ብላቴና በታላቅ እፎይታ ወደ ባሕሩ ዳርቻ ይዘው ሲመለሱ፤ በታላቅ ጉጉት ይጠባበቅ የነበረው ሕዝብ በደስታ እና በእንባ የታጀበ የእፎይታ ሰላምታ አቀረበ። ልጅቷ ግን ብዙም መገረም የሌለበት የተረጋጋ ሁናቴ ይታይባት ነበር።

እንደውም የሰዉ ምላሽ እንግዳ የሆነባት ይህች ብላቴና ‘በውሃው ላይ በጀርባዬ ተንጋልዬ ቀኑን ሙሉ መቆየት እንደምችልና ተመልሶ እንደሚመጣልኝ አባቴ ነግሮኝ ነበር። ስለዚህ እየዋኘሁና በጀርባዬ እየተንሳፈፍኩ ጠበቅኩት።’ ”—H. M. S. Richards, “When Jesus Comes Back,” Voice of Prophecy News, March 1949, p. 5. ሣምንቱን በጨረፍታ፡ ጌታ ራሱን እንደ አብርሃም ጋሻ አድርጎ የጠራው ለምን ነበር? “የምድር ሕዝቦች ሁሉ” በአብርሃም አማካይነት እንዴት ሊባረኩ ቻሉ? ከቃል ኪዳኑ ተስፋዎች ሁሉ የሚበልጠው የትኛው ነው?



ሚያዝያ 17
Apr 25

ጋሻህ


“ከዚህም በኋላ፤ የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል በራእይ ወደ አብራም መጣ፤ ‘አብራም ሆይ፤ አትፍራ፤ እኔ ለአንተ ጋሻህ ነኝ፤ ታላቅ ዋጋህም እኔው ነኝ።’ ” ጥቅሱን ያንብቡ--ዘፍ. 15፡3። መልእክቱ ስለ ተሰጠበት ዐውደ ሀሳብ ያስቡ። ጌታ “አትፍራ” ሲል በመጀመሪያ አብርሃምን የተናገረው ለምንድን ነው? አብርሃም መፍራት የነበረበት ነገር ምንድን ነው?



እዚህ ላይ በተለይ በጣም ደስ የሚያሰኘው ነገር ቢኖር ጌታ አብራምን “እኔ ለአንተ ጋሻህ ነኝ” ማለቱ ነው። ግላዊ ተውላጠ ስም መጠቀሙ የግንኙነቱን ግላዊ ተፈጥሮ ያሳያል። እግዚአብሔር ከሁላችንም ጋር በሚሆንበት መንገድ በተመሳሳይ--አንድ ለአንድ የሆነ ዝምድና ከእርሱ ጋር ይፈጥራል።

እግዚአብሔር “ጋሻ” ተብሎ የተጠራበት ስያሜ በዚህ ስፍራ ለመጀመሪያ ጊዜ ቀርቧል። ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ስለ እግዚአብሔር ለመናገር ይህን ቃል ቢጠቀሙም (ዘዳ. 33:29፣ መዝ. 18:30፣ መዝ. 84:11፣ መዝ. 144:2) ጌታ ራሱን ለመግለጽ ይህን ስያሜ ሲጠቀም ይህ ብቸኛው ጊዜ ነው።

እግዚአብሔር የሆነ ሰው ጋሻ ነኝ ብሎ ራሱን ሲጠራ ምን ማለቱ ነው? እርሱ ለአብርሃም የተናገረው ቃል ዛሬ ለእኛ አይሠራ ይሆን? ያንን ተስፋ የራሳችን አድርገን መቀበል እንችላለን? አካላዊ ጉዳት አይደርስብንም ማለት ነው? እግዚአብሔር ጋሻ የሚሆንባቸው መንገዶች የትኞቹ ናቸው? ይህን ገጽታ እንዴት ይረዱታል?



“ክርስቶስ ስለ እኛ ያለው ፍላጎት ተራ ዓይነት ሳይሆን እናት ለልጇ ካላት ፍላጎት የበለጠ ነው… አዳኛችን እኛን የገዛን--ሰው ሆኖ በተቀበለው ሥቃይ፣ ሐዘን፣ ስድብ፣ ዘለፋ፣ ጥቃት፣ ፌዝ፣ ነቀፋ እንዲሁም በሞቱ ነው። ጸንተው ለመቆም እየተውተረተሩ ላሉት--የእግዚአብሔር ልጅ ለሆኑት ለእርሶ ጥበቃ እያደረገ ይገኛል። ደኅንነትዎን በጥበቃው ሥር አስተማማኝ ያደርጋል… ደካማ ሰብዓዊ ተፈጥሮአችን ወደ ሰማያዊው አባት እንዳንደርስ አያግደንም፤ እነሆ ክርስቶስ እኛን ሊያማልድ ሞቷልና።”—Ellen G. White, Sons and Daughters of God, p. 77.

ሮናልዶ በማንኛውም ውጪያዊ ማንነቱ ሲታይ ታማኝ የጌታ ተከታይ ነበር። ሆኖም ሳይታሰብ በድንገት ሞተ። የዚህ ግለሰብ ጋሻ የነበረው አምላክ ምን ነካው? ወይስ እግዚአብሔር ጋሻችን የመሆኑን ጽንሰ ሀሳብ በሌላ መንገድ ልንረዳ ይገባ ይሆን? ያብራሩ። እግዚአብሔር ሁሌም ቢሆን ከምን ጋሻ እንደሚሆንልን ነው ቃል የገባልን? 1ቆሮ. 10፡13።





ሚያዝያ 18
Apr 26

የመሲሁ ቃል ኪዳን፡ ክፍል 1


“የምድርም ሕዝቦች ሁሉ በአንተና በዘርህ አማካይነት ይባረካሉ” (ዘፍ. 28፡14) “የክርስቶስ ከሆናችሁ፣ እናንተ የአብርሃም ዘር ናችሁ፤ እንደ ተስፋውም ቃል ወራሾች ናችሁ።” (ገላ. 3፡29)። በአብርሃም ዘር እና በእርሱ ትውልድ አማካይነት በምድር የሚኖሩ ሕዝቦች ሁሉ እንደሚባረኩ እግዚአብሔር ከአንድ ጊዜ በላይ ተናግሯል (ዘፍ. 12:3፣ ዘፍ. 18:18፣ ዘፍ. 22:18)። ይህ ሌሎቹ ሁሉ ዋጋ እንዲያገኙ የሚያደርግ እና ተደጋግሞ የተነገረ አስደናቂ ቃል ኪዳናዊ የተስፋ ቃል ከተሰጡት የተስፋ ቃሎች ሁሉ በጣም አስፈላጊውና ዘላቂው ክፍል ነው። በአንድ በኩል ይህ ስለ አይሁድ እንደ አገረ መንግሥት መነሣት እና ጌታ ስለ እውነተኛው አምላክ እና የደኅንነት እቅድ በእነርሱ አማካይነት ለ “ምድር ሕዝቦች ሁሉ” ለማስተማር የሰጠው የተስፋ ቃል ነው። ሆኖም የተስፋ ቃሉ ሙሉ ለሙሉ ፍጻሜ የሚያገኘው ከአብርሃም ትውልድ በሚወጣውና ለ“ምድር ሕዝቦች ሁሉ” ኃጢአት በመስቀል ላይ ዋጋ በሚከፍለው በየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው።

ከጥፋት ውሃ በኋላ ስለ ተሰጠው ቃል ኪዳናዊ የተስፋ ቃል (ጌታ ምድርን ዳግመኛ በውሃ እንደማያጠፋት ቃል ከዳን የገባበትን) ያስቡ። በየሱስ ከሚገኘው የመቤዠት ተስፋ ውጪ ይህ ምን ዓይነት መልካም ነገር ሊኖረው ይችል ነበር? በክርስቶስ የሚገኝ የዘላለም ሕይወት ተስፋ ባይኖር ማናቸውም አምላካዊ የተስፋ ቃሎች መጨረሻቸው ምን ያህል መልካም ሊሆን ይችል ነበር? በአብርሃም፤ ይኸውም በየሱስ ክርስቶስ አማካይነት “የምድር ሕዝቦች ሁሉ” እንደሚባረኩ የሚናገረውን ጽንሰ ሀሳብ እንዴት ይረዱታል? ምን ማለትነው? የዓለም አዳኝ የሆነው ቃል ኪዳናዊ የተስፋ ቃል ከሁሉም አምላካዊ ተስፋዎች ሁሉ የላቀ መሆኑ አጠያያቂ አይደለም። ቤዛ የሚሆነው ጌታ ራሱ የቃል ኪዳኑ ግዴታዎች የሚሟሉበት እና ሌሎቹ ሁሉ ተስፋዎች የሚፈጸሙበት መንገድ ይሆናል።

ከእርሱ ጋር አንድነት ውስጥ የገቡ ሁሉም አይሁድ ወይም አሕዛብ የአብርሃም እውነተኛ ቤተሰብ እና የተስፋው ወራሾች ተደርገው ይቆጠራሉ (ገላ. 3:8-9፣ 27–29)። ይኸውም--ክፋት፣ ህመም እና ሥቃይ ዳግመኛ የማይነሣበት ኃጢአት ዐልባ ሁናቴ ማለትም የዘላለማዊ ሕይወት የተስፋ ቃል ነው። ከዚህ የተሻለ የተስፋ ቃል ማሰብ ይችላሉ?

ኃጢአት እና ሥቃይ የሌለበት ዓለም ውስጥ የመኖርን--ልብ የሚያማልል የተስፋ ቃል እንዴት ይመለከቱታል? እንዲህ ያለውን ዓለም የምንናፍቀው፣ ገና በመጀመሪያ የዚያ ባለቤት እንድንሆን በመፈጠራችን የተነሣ እና ያን መሠረታዊ ተፈጥሮአችንን እየናፈቅን ይሆን?

ሚያዝያ 19
Apr 27

የመሲሁ ቃል ኪዳን፡ ክፍል 2


“በእውነተኛ ደስታ ሐሴት ለማድረግ ከራሳችን ውስጥ ሳይቀር ወጥተን ወደ ሩቅ አገር መጓዝ ይኖርብናል”—ቶማስ ብሮውን። ይህን በ1600ዎቹ የተጻፈ ጥቅስ ልብ ብለው ይመልከቱ። በሀሳቡ ይስማማሉ ወይስ አይስማሙሙ? እስቲ በሚከተሉት ዐውደ ሐሳቦች ያንብቡት፡ 1ተሰ. 4፡16-18፣ ራእ. 3፡12።



አውጉስቲን ስለ ሰው ሁኔታ ሲጽፍ እንዲህ ብሏል፡ “በከፍተኛ ህመም የታወከው ይህ የእኛ ሕይወት--በትክክል ሕይወት ተብሎ የሚጠራ ከሆነ፤ ገና ከመጀመሪያ አንስቶ ሟች የሆነው የሰው ዘር የተኮነነ ዘር ለመሆኑ ምስክር መሆን ይችላል። በመጀመሪያ ሁሉም ስህተቶች ስለሚፈጠሩበት አስፈሪ የአለማወቅ የጥፋት ገደል ያስቡ። ከአዳም ልጆች አንዳቸውም ሊያመልጡ የማይችሉበት ይህ የጨለማ አረንቋ--ከመከራ ፍዳ፣ ፍርሃትና እንባ በቀር ሌላ የለበትም።

በመቀጠል የልብ መሰበር፣ ችግር፣ ሐዘንና ፍርሃት ለሚያስከትሉ እጅግ ከንቱና መርዛማ ነገሮች ያለንን ብርቱ ፍቅር ይመልከቱ። በጸብ፣ ብጥብጥ፣ ሁከትና ጦርነት ውስጥ የሚገኙ እብደት የተጸናወታቸው ደስታዎች--በማጭበርበር፣ ስርቆትና ዝርፊያ የሚገኙ ፈንጠዝያዎች-ሸፍጥ፣ መታበይ፣ ምቀኝነት፣ ከንቱ ክብር መሻት፣ ሰው መግደል፣ ጨካኝነት፣ አረመኔነት፣ ሕገ-ወጥነት፣ ርኩስ የሆኑ የብልግና ምኞቶች ሁሉ--ዝሙት፣ ምንዝርና ተፈጥሮአዊ ያልሆኑ ኃጢአቶች፣ አስገድዶ መድፈር እና ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሌሎች ርኩሰቶችን ለመጥቀስ እንኳ የሚያስጸይፉ ናቸው።

በኃይማኖት ላይ የሚፈጸሙ የእርክስና እና መናፍቅነት ኃጢአቶች ማለትም እግዚአብሔርን መሣደብ እና ሐሰተኛ መሐላ፤ በባልንጀራችን ላይ ከምንፈጽማቸው እርክስናዎች--ሐሜት፣ ማጭበርበር፣ መዋሸት፣ በሐሰት መመስከር፣ በሰዎችና ንብረታቸው ላይ የሚፈጸሙ የአመጽ ተግባራት፣ የፍትሕ አካላት ኢፍትሐዊነትና ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሌሎች ችግሮች እና በሽታዎች ከትኩረት እንዳመለጡ ይገኛሉ።”—Augustine of Hippo, City of God, Gerald G. Walsh, S. J. trans. (New York: Doubleday & Co., 1958), book 22, chap. 22, p. 519. ይህ በትምህርተ ጥቅስ የቀረበ የአውጉስቲን ጽሑፍ ከአንድ ሺ አምስት መቶ ዓመታት በፊት ቢጻፍም፤ ለብዙዎቹ የዛሬ ዘመናዊ ከተሞች ገጣሚ መሆን ይችላል። ሰውን አስመልክቶ አነስተኛ ለውጥ በመኖሩ ብዙዎች ማምለጫ መንገድ ሲፈልጉ ይስተዋላሉ።

አሁን ያለንበት ሁናቴ የቱንም ያህል ከባድ ቢሆንም፤ እንደ መታደል ሆኖ የወደፊቱ ዘመን ብሩህ ነው። ይህ የሆነው እግዚአብሔር በየሱስ ክርስቶስ ህይወት፣ ሞት፣ ትንሣኤና የሊቀ ካህንነት አገልግሎት ለእኛ ባደረገልን ነገር ብቻ ነው። ለአብርሃም በተሰጠው የቃል ኪዳኑ የመጨረሻ ፍጻሜ መሠረት፣ በዘሩ የምድር ቤተሰቦች ሁሉ ይባረካሉ።

አውጉስቲን ያሰፈረውን መልእክት ደግመው ይመልከቱ። በአሁኑ ጊዜ በዓለም ላይ ያለውን አሳዛኝ ሁኔታ ለመግለጽ በራስዎ ቃላት አንድ ነገር ይጻፉ። በተመሳሳይ እግዚአብሔር በየሱስ ክርስቶስ ስለ ሰጠን የተስፋ ቃል የሚናገሩ ማናቸውንም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ይፈልጉ (ለምሳሌ፡ ኢሳ. 25፡8፣ 1ቆሮ. 2፡9፣ ራእ. 22፡ 2-5)።



ሚያዝያ 20
Apr 28

ታላቅ እና ብርቱ ሕዝብ…


በምድር ያሉ ሕዝቦች በአብርሃም አማካይነት ይባረካሉ ሲል ብቻ እግዚአብሔር ቃል አልገባለትም። ነገር ግን ጌታ “ታላቅና ብርቱ ሕዝብ” (ዘፍ. 18፡18፣ 12፡12፣ 46፡ 3) እንደሚያደርገው ጭምር ነግሮታል። ልጅ መውለድ ከምትችልበት ዕድሜ በላይ ያለች ሴት ጋር በትዳር ለሚኖር ሰው ይህ ታላቅ የተስፋ ቃል ነው። በመሆኑም፤ አብርሃም የአብራኩ ክፋይ ወንድ ልጅ በሌለው ሁናቴ ውስጥ እያለ እግዚአብሔር ሁለቱንም ተስፋ ሰጠው።

ሆኖም ይህ የተስፋ ቃል አብርሃም በሕይወት እያለ ሙሉ በሙሉ አልተፈጸመም። ይስሐቅም ሆነ ያዕቆብ ሲፈጸም አላዩም። የተስፋ ቃሉ በግብፅ ፍጻሜ እንደሚያገኝ (ዘፍ. 46፡3) ተጨማሪ መረጃዎችን በማከል እግዚአብሔር በድጋሚ ለያዕቆብ ነግሮት ነበር። ያዕቆብ የሆነውን ባያይም በመጨረሻ ግን ያ ተስፋ ተፈጽሟል። ጌታ ከአብርሃም ዘር ልዩ ሕዝብ ማዘጋጀት ለምን ፈለገ? ጌታ የተወሰነ የዘር ምንጭ ያለው ሌላ አገር ፈልጎ ነበር? ይህ ህዝብ ምን ዓይነት ዓላማዎችን ማከናወን ነበረበት? ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፀ. 19:5-6 ኢሳ. 60:1–3፣ ዘዳ. 4:6–8። ከታች በቀረቡት መስመሮች መልስዎን ይጻፉ፡



በቅዱሳት መጻሕፍት እንደምንመለከተው እግዚአብሔር በአምላካዊው ባርኮት፣ ደስታ፣ ጤና እና ቅድስና ስር በነበረው በእስራኤል ምስክርነት የዓለምን ሕዝቦች ወደ ራሱ ለመሳብ ያቀደ ይመስላል። እንዲህ ያለው ሕዝብ ለፈጣሪ ፈቃድ በመታዘዙ የጎበኘውን አምላካዊ በረከት ለሌሎች የሚያሳይ ይሆናል። ስፍር ቁጥር የሌላቸው የምድር ሕዝቦች እውነተኛውን አምላክ ለማምለክ ይሳባሉ (ኢሳ. 56፡7)። ስለዚህ የሰዎች ትኩረት ወደ እስራኤል፣ ወደ አምላካቸው እና በመካከላቸው ወደ ሚገለጠው የዓለም አዳኝ የሆነው መሲህ የሚሳብ ይሆናል።

“የእስራኤል ልጆች በእግዚአብሔር የተወሰነላቸውን ግዛት ሁሉ ይወርሱ ነበር። የእውነተኛውን አምላክ አምልኮና አገልግሎት የተቃወሙ ሕዝቦች ግዛት እንዲወረስ ተደርጓል። ነገር ግን በእስራኤል በኩል በተገለጠው አምላካዊ ባህሪ ሰዎች ወደ እርሱ ይሳቡ ዘንድ የእግዚአብሔር ዓላማ ነበር። የወንጌል ግብዣ ለዓለም ሁሉ መቅረብ ነበረበት። በመሥዋዕት ሥርዓቱ አገልግሎት አስተምህሮ አማካይነት ክርስቶስ በሕዝቦች ፊት ከፍ ማለት ነበረበት። ወደ እርሱ የሚመለከቱ ሁሉ በሕይወት ሊኖሩ የተገባ ነውና።”—Ellen G. White, Christ’s Object Lessons, p. 290. ጌታ በእስራኤል እና በቤተክርስቲያናችን ውስጥ ማድረግ በሚፈልጋቸው ነገሮች ወስጥ ምን ዓይነት ተመሳሳይ ነገሮችን ማየት ይችላሉ? ካሉ ምንድናቸው? 1ጴጥ. 2:9።





ሚያዝያ 21
Apr 29

“ስምህን ገናና አደርገዋለሁ”


“ታላቅ ሕዝብ አደርግሃለሁ፤ ደግሞም እባርክሃለሁ፤ ስምህን ገናና አደርገዋለሁ፤ ለሌሎች በረከት ትሆናለህ” (ዘፍ. 12፡2)። በዘፍ. 12፡2 እግዚአብሔር የአብርሃምን ስም ገናና ወይም ዝነኛ እንደሚያደርው ቃል ገብቷል። ሰው የቱንም ያህል ታዛዥና ታማኝ ቢሆን--ጌታ እንዲህ ያለውን ነገር ለኃጢአተኛ ለማድረግ ለምን ፈለገ? “ገናና” የሚገባው ማን ነው? (ጥቅሶቹን ይመልክቱ፡ ሮሜ 4፡ 1-5፣ ያዕ. 2፡21-24)። እግዚአብሔር ለአብርሃም ግላዊ ጥቅም ሲል ታላቅነትን ሰጠው ወይስ ጉዳዩ ከዚያ የላቀ አንደምታ ይወክላል? ይግለጹ።



ጥቅቹን ያስተያዩ፡ ዘፍ. 11፡4 እና ዘፍ. 12፡2)። በሁለቱ መካከል ያለው ትልቅ ልዩነት ምንድን ነው? አንዱ “ጽድቅ በሥራ” ሌላኛውን ደግሞ “ጽድቅ በእምነት” የሚወክለው እንዴት ነው?



የሆነው ሆኖ አብዛኛው የደኅንነት እቅድ ክርስቶስ ስለ እኛ በከወነው የጽድቅ ሥራ ላይ የሚያርፍ ቢሆንም--እኛ እንደ እግዚአብሔር ጸጋ ተቀባይነታችን በተመሳሳይ የዚሁ ተግባር ተሳታፊዎች ነን። እኛ የመምረጥ ነጻነት እንዳለን ሁሉ የምንጫወተውም ሚና አለን። ዘመናት ያስቆጠረው በክርስቶስ እና በሰይጣን መካከል እየተደረገ ያለው የፍልሚያ ትርኢት ዛሬም በእኛ ውስጥ እየተካሄደ ይገኛል። በውዝግቡ በእኛ ውስጥ እየሆነ ያለውን ሰዎች እና መላእክት እየተመለከቱ ይገኛሉ (1ቆሮ. 4፡9)።

ስለዚህ ማንነታችን፣ የምንናገረውና የምናደርገው ነገር ከገዛ ራሳችን ምህዋር ባሻገር ዩኒቨርስን አልፎ ማስተጋባት የሚችል አንደምታ አለው። ከአንደበታችን በሚወጡት ቃላት፣ በድርጊቶቻችን እንዲሁም በአመለካከታችን እጅግ ብዙ ላደረገልን ጌታ ክብር ማምጣት ወይም በእርሱና በስሙ ላይ ሐፍረት ማምጣት እንችላለን። በመሆኑም ጌታ ስምህን ገናና አደርገዋለሁ ብሎ ለአብርሃም ሲነግረው፤ ዓለም ገናና ብሎ ስለ ሚጠራው ዓይነት ስም እየተናገረ አልነበረም። በእግዚአብሔር ዐይን ስምን ገናና የሚያደርገው ባህሪ ማለትም እምነት፣ መታዘዝ፣ ራስን ዝቅ ማድረግና ሌሎችን መውደድ--ብዙውን ጊዜ በዓለም ፊት ክብር ሊያቀዳጁ ቢችሉም፤ በአብዛኛው እንደሚስተዋለው ዓለም ለአንድ ሰው ስም ታላቅነት የሚያስባቸው ምክኒያቶች ግን አይደሉም።

ዛሬ በዓለም ዙሪያ “ገናና” ስም ያላቸውን የፊልም ተዋናዮች፣ ፖለቲከኞች፣ አርቲስቶች፣ ሐብታሞች ወዘተ ይመልከቱ። እነዚህን ሰዎች እንዲህ ገናና ያደረጋቸው ነገር ምንድን ነው? ይህን--ከአብርሃም ገናናነት ጋር ያነጻጽሩ። የዓለም የታላቅነት ጽንሰ ሀሳብ ምን ያህል የተዛባ እንደሆነ ይህ ምን ይነግረናል? ዓለማዊው አመለካከት ለታላቅነት ባለን እሳቤ ላይ ምን ያህል ተጽእኖ ያደርጋል?





ሚያዝያ 22
Apr 30


ተጨማሪ ሀሳብ


የኃይማኖት አባቶች እና ነቢያት መጽሐፍ፡ “አብርሃም በከነዓን” ገጽ፡ 142-159፣ “የእምነት መፈተን” ገጽ፡ 160-171። ለአብርሃም የተሰጠው ፈተና ቀላል አልነበረም፤ እንዲያቀርብ የተጠየቀው መሥዋዕትም እንዲሁ የዋዛ አልነበረም።… ነገር ግን ጥሪውን ለመቀበል አላመነታም። ስለ ተስፋይቱ ምድር… ጥያቄ አላቀረበም። እግዚአብሔር ከተናገረ አገልጋዩ መታዘዝ አለበት። ለእርሱ በምድር ላይ እጅግ የሚያስደስተው ቦታ እግዚአብሔር እንዲገኝ የሚጠይቀው ስፍራ ነው።” የኃይማኖት አባቶች እና ነቢያት ገጽ 135።

አብርሃም ወደ ከነዓን ሲገባ ጌታ ተገልጦ የሚቀመጥባትን ምድር ለዘሩ እንደሚሰጥ ግልጽ አድርጎለታል (ዘፍ. 12፡7)። እግዚአብሔር ይህን የተስፋ ቃል ደጋግሞ ነግሮታል (ዘፍ. 13:14-15፣ 17፣ ዘፍ. 15:13፣ 16፣ 18፣ ዘፍ. 17:8፣ ዘፍ. 28:13፣ 15፣ ዘፍ. 35:12)። ከአራት መቶ ዓመታት በኋላ ገቢራዊ በሆነው የተስፋ ቃሉ ፍጻሜ (ዘፍ. 15፡13፣16) ጌታ እስራኤልን ከግብፅ አውጥቶ ማርና ወተት ወደ ምታፈሰው ምድር እንደሚያመጣ ለሙሴ አስታወቀው (ዘፀ. 3፡8፣ 17፣ ዘፀ. 6፡8)። እግዚአብሔር ይህንኑ የተስፋ ቃል በድጋሚ ለኢያሱ የነገረው ሲሆን (ኢያሱ 1፡3)፤ በዳዊት ዘመን ሙሉ ለሙሉም ባይሆን በአብዛኛው ፍጻሜ አግኝቶ ነበር (ዘፍ. 15፡18-21፣ 2ሳሙ. 8:1–14፣ 1ነገሥ. 4:21፣ 1ዜና. 19:1–19)።

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዕብ. 11፡9-10፣ 13-16። አብርሃም እና ሌሎች ታማኝ የኃይማኖት አባቶች ከነዓንን የተቤዡ የእግዚአብሔር ሕዝቦች የመጨረሻው ቋሚ መኖሪያ ተምሳሌት አድርገው ይመለከቱ ነበር። ኃጢአት ባለበት ሁኔታ ቋሚ መኖሪያ ጉዳይ የማይሆን ነው። ህይወት “ለጥቂት ጊዜ ታይቶ ኋላ እንደሚጠፋ እንፋሎት” (ያዕ. 4፡14) ናት። አበክረን ልንገነዘብ የሚገባው ነገር ቢኖር--በመንፈስ የአብርሃም ዘር የሆንነው እኛም “በዚህ ቋሚ ከተማ የለንም፤ ነገር ግን ወደፊት የምትመጣውን ከተማ እንጠብቃለን” (ዕብ. 13፡14)። ከክርስቶስ ጋር የሚኖረን የወደፊት ሕይወት እርግጠኝነት፤ በዚህ በአሁኑ የለውጥ እና መበስበስ ዓለም ጸንተን እንድንቆም ይረዳናል።




የመወያያ ጥያቄዎች



፡ 1.እግዚአብሔር ስለ አዲሲቱ ምድር የሰጠው የተስፋ ቃል በግል ክርስቲያናዊ ልምዳችን ላይ ምን ተጽዕኖ ሊኖረው ይገባል? (ጥቅሶቹን ያነጻጽሩ፡ ማቴ. 5:5፣ 2ቆሮ. 4:17-18፣ ራእ. 21:9-10፣ ራእ. 22:17)።

2.“እውነተኛ ታላቅነት የእግዚአብሔርን ትእዛዛት የመጠበቅና ከመለኮታዊ ዓላማው ጋር የመተባበር ውጤት ነው።”—SDA Bible Commentary, vol. 1, p. 293. በሀሳቡ ላይ ተወያዩ። ማጠቃለያ፡ የተስፋ ቃል! እነዚህ ቃላት ለአማኙ ምን ያህል የከበሩ ናቸው! ፍጻሜ ያገኛሉ? አዎ--ሲል እምነት ይመልሳል።




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA union SSL