የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

፡ ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ዘፍ. 9:15፣ ኢሳ. 54:9፣ ዘፍ. 12:1–3፣ ገላ. 3:6–9፣ 29፣ ዘፀ. 6:1–8፣ ኤር. 31:33-34።
የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ “አሁንም በፍጹም ብትታዘዙና ቃል ኪዳኔን ብትጠብቁ እነሆ ለአሕዛብ ሁሉ እናንተ የተወደደ ርስቴ ትሆናላችሁ፤ ምንም እንኳ ምድር ሁሉ የእኔ ብትሆንም” (ዘፀ. 19፡ 5)፡፡
ያ
ለፈውን ሣምንት ጥናታችንን ያቆምነው የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን
ኃጢአት በሰው ልጅ ላይ ያስከተለውን ውድቀት በማንሣት ነበር። የዚህ
ሣምንት ጥናታችን--እነዚያን በገዛ ራሳቸው መንገድ፣ በአንድነት ሆነው
የእውነተኛውን ኪዳን እውነት የሚገልጡትን የቀደሙ ኪዳኖች፣ በየሱስ ደም
በቀራኒዮ የጸናውን እና እኛ እንደ ክርስቲያን ከጌታችን ጋር የምንገባበትን-- እያስቃኘ
አጠቃላዩን ሩብ ዓመት በአጭሩ ያስዳስሰናል።
እግዚአብሔር ኖህ እና ቤተሰቡን ከጥፋት ለመታደግ ሲል ከእርሱ ጋር በገባው ኪዳን
እንጀምራለን። በመቀጠል ለሁላችንም የተትረፈረፈና የተሟላ የሆነውን ከአብርሃም
ጋር የገባውን ኪዳን እንመረምራለን። ከዚያም በሲና የተገባውን ኪዳን እና የዚህን
ኪዳን መታወጅ አስፈላጊነት የምንመለከት ሲሆን፣ በመጨረሻ ሁሉም ኪዳኖች
በአንድነት ወደሚያመላክቱት አዲሱ ኪዳን እናቀናለን። እነዚህ ሁሉ በሚቀጥሉት
ጥቂት ሣምንታት ጥልቅ ጥናት ይደረግባቸዋል። የዚህ ሣምንት ጥናት--ከጨረፍታ
የዘለለ ምልከታ አያደርግም።
ሣምንቱን በጨረፍታ፡ ለመሆኑ ኪዳን የተሰኘው ቃል ፍቺ ምንድን ነው? ኪዳንን
የሚያዋቅሩ አላባዎች ምንድን ናቸው? እግዚአብሔር ከኖህ ጋር የገባው ኪዳን ምን
ነበር? ከአብርሃም ጋር በገባው ኪዳን ውስጥ ምን ተስፋ ተገኘ? በሰው በኩል ባለው
የኪዳን ድርሻ፣ እምነት እና ሥራ ምን ሚና ይኖራቸዋል? ኪዳን ውል ብቻ ነው ወይስ
ተያያዥ የግንኙነት ገጽታዎች አሉት? የ “አዲስ ኪዳን” መሰረታዊ ነጥብ ምንድን
ነው?
“በእኔና በአንተ መካከል የተመሰረተውን ኪዳን አጸናለሁ፤ ዘርህንም እጅግ
አበዛለሁ።” (ዘፍ. 17፡2)
“‘ኪዳን’ ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል (በብሉይ ኪዳን 287 ጊዜ
መጠቀሱን ልብ ይሏል) ግዝረት ነው። እንዲሁም “ኑዛዜ” ወይም “የመጨረሻ ኑዛዜ”
ተብሎ ሊተረጎም ይችላል። የቃሉ አመጣጥ ግልጽ ባይሆንም “ሁለት አካላትን
በአንድነት የሚያስር” የሚል አንደምታ አለው። ቃሉ በሰው እና በሰው--እንዲሁም
በሰው እና በእግዚአብሔር መሃል ሊኖሩ በሚችሉ የተለያዩ ዓይነት ‘ትስስሮች’ ጥቅም
ላይ ውሏል። በግራም ሆነ በቀኝ ያሉት አካላት ሰዎች ሲሆኑ የጋራ ጥቅም ያለው
ሲሆን፤ ኪዳኑ በሰው እና በእግዚአብሔር መካከል ሲሆን ግን ከተለመደው በለተለየ
ለኃይማኖት ነክ ጉዳይ ጥቅም ላይ ይውላል።
ለኃይማኖታዊ ጉዳይ የሚውልበት
መንገድ ለጋራ ጥቅም የተመሰረተ ዘይቤያዊ ባህሪ ቢኖረውም፤ ነገር ግን ጥልቅ
ትርጉም አለው።”—J. Arthur Thompson, “Covenant (OT),” The International Standard Bible Encyclopedia, revised edition (Grand Rapids, MI:
William B. Eerdmans Publishing Company, 1979), vol. 1, p. 790.
ልክ እንደ ጋብቻ ቃል ኪዳን ሁሉ መጽሐፍ ቅዱሳዊው ኪዳን--ግንኙነትን እና
ድርድርን ይገልጻል። የመጽሐፍ ቅዱሳዊው ኪዳን አደረጃጀት የሚከተሉትን
መሰረታዊ አላባዎች ያካትታል፡
1.እግዚአብሔር የኪዳኑን ተስፋዎች በመሃላ አረጋግጧል (ገላ. 3፡16፣ ዕብ. 6፡
13፣17)።
2.የኪዳኑ ግዴታ በአሥሩ ትእዛዛት እንደተገለጸው አምላካዊውን ፈቃድ
መታዘዝ ነበር (ዘዳ. 4፡13)።
3.የአምላካዊው ኪዳን ግዴታ በመጨረሻ ላይ ፍጻሜ የሚያገኘው በክርስቶስ
እና በዘላለማዊው የደኅንነት ዕቅድ አማካይነት ይሆናል (ኢሳ. 42፡1፣6)።
ከላይ የቀረቡትን ሦስት ነጥቦች ይመልከቱ (የእግዚአብሔር ተስፋ፣ መታዘዛችን እና
የደኅንነት እቅድ)። ከጌታ ጋር በሚያደርጉት ጉዞ እነዚህ ነገሮች ሲሠሩ መመልከት
የሚችሉት እንዴት ነው? አሁን በህይወትዎ እንዴት እንደሚታዩ የሚገልጽ አጠር
ያለ አንቀጽ ይጻፉ።
በብሉይ ኪዳን ዘመን ይቀርቡ የነበሩ የመሥዋእት ሥርዓት ዓይነቶች መላውን
ሕዝብ ስለ ደኅንነት እቅድ ያስተማሩ ነበሩ። የኃይማኖት አባቶች እና እስራኤል
በእነዚያ በቀረቡላቸው ተምሳሌታዊ ሥርዓቶች አማካይነት ወደፊት በሚመጣው
ቤዛ ላይ እምነት ማድረግ መለማመድ ተማሩ። ተነሳሂው በደለኛ በሚፈጽመው
ሥርዓተ አምልኮ የኃጢአት ይቅርታ ያገኛል፣ ከጥፋተኝነት ስሜት ነጻ መሆንም
ይችላል። የኪዳኑ በረከቶች በዚህ መንገድ ተጠብቀው ሲቆዩ--ሰብዓዊው ፍጡር
የተስማማበትን ሥርዓቶች በበቂ ሁኔታ ማክበር ሲሳነው እንኳ፣ አምላካዊውን
አምሳል በሕይወት ውስጥ ጠብቆ ሊያኖር የሚችለው መንፈሳዊ ዕድገት ክንውን
ማግኘቱን ሊቀጥል ይችላል።
ምንም እንኳ በሰዎች መካከል ቃል ኪዳኖች ቢኖሩም፤ በዕብራይስጡ
ብሉይ ኪዳን የቀረበው ግርዘት--በዋነኝነት ጥቅም ላይ የዋለው
በእግዚአብሔር እና በሰው ልጆች መካከል ያለውን ግንኙነት ለማመላከት
ነው። እግዚአብሔር ማን እንደሆነ እና እኛ ከእርሱ አኳያ ስንነጻጸር
ምን እንደሆንን ከግምት ውስጥ በማስገባት--እንዲህ ያለው ኪዳን ምን
ዓይነት ግንኙነትን ያሳያል?
“ከአንተ ጋር ቃል ኪዳን እመሠርታለሁ። አንተና ወንዶች ልጆችህ፣ ሚስትህና
የልጆችህ ሚስቶች ከአንተ ጋር ወደ መርከቧ ትገባላችሁ።”
ቃል ኪዳን የተሰኘው ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ የተገለጠው ከላይ
በቀረው ጥቅስ ነው። ኃጢአት በከፍተኛ መጠን በምድር በመስፋፋቱ የተነሣ
እግዚአብሔር ምድርን ሊያጠፋ መወሰኑን ለኖኅ እንደ ነገረው በዚህ ዐውደ ጽሑፍ
እንመለከታለን። ምንም እንኳ ይህ የጥፋት ውሃ በመላው ምድር ላይ ውድመት
የሚያደርስ ቢሆንም፤ እግዚአብሔር የፈጠረውን ዓለም እየተወ አልነበረም።
ከውድቀት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በሥራ ላይ የዋለውን የቃል ኪዳን ግንኙነት
ማቅረብ ቀጠለ። ኪዳኑን ያቀረበው ያ መለኮታዊ “እኔ” ራሱ፣ የኖኅ ደኅንነት መሠረት
ነው። ለገባው ኪዳን ተገዢ የሆነው አምላክ፤ በቁርጠኛ ኪዳናዊ ግንኙነት እርሱን
እየታዘዙ አብረውት ለመኖር ፈቃደኞች የነበሩትን የቤተሰብ አባላት ለመጠበቅ ቃል
ገባ።
ከኖኅ ጋር የተገባው ኪዳን የአንድ ወገን ብቻ ነበር? የኪዳኑ ጽንሰ ሀሳብ ከአንድ አካል
በላይ ማካተቱን ማስታወስ ተገቢ ነው። ኖኅ በእርሱ በኩል ለገባው ስምምነት ተገዢ
መሆን ነበረበት? በእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ውስጥ ምን ዓይነት ትምህርት እናገኛለን?
የጥፋት ውሃ እንደሚመጣና በዚሁ ምክንያት ምድር እንደምትጠፋ እግዚአብሔር
ለኖኀ ነግሮታል። ይህን ተከትሎ ኖኅንና ቤተሰቡን ለማዳን የገባውን ኪዳን ከእርሱ
ጋር አደረገ። በሁለቱም አካላት በኩል የነበረው ድርሻ ከፍተኛ ነበር። ምክንያቱም
እግዚአብሔር በእርሱ በኩል የነበረውን ቃል ኪዳን ባይጠብቅ፤ ኖኅ ምንም ያድርግ
ምን--ከተቀረው ዓለም ጋር ተደምስሶ ሊጠፋ ይችል ነበር።
እግዚአብሔር ከኖኅ ጋር “ቃል ኪዳን” እመሠርታለሁ ሲል ተናገረ። እርሱ
አደርገዋለሁ ያለውን ለማክበር ያለመ መሆኑን ቃሉ በራሱ አመላካች ነው። ከዚህ
ውጪ መግለጫው የሚዋልል ዓይነት ይዘት የለውም። የቃሉ አመጣጥ በራሱ
በቁርጠኝነት ላይ የታመቀ ነው። ምናልባት ጌታ ለኖኅ እንዲህ አለው እንበል፡
“እነሆ፣ የዓለም ነገር በአስፈሪ የጥፋት ውሃ የሚጠናቀቅበት ጊዜ ተቃርቧል። ከዚህ
መአት ላድንህም፣ ላላድንህም እችላለሁ። እስከዚያው ግን ይህን፣ ይህን አድርግ
እና የሚሆነውን እናያለን። ምንም ዓይነት ዋስትና ልሰጥህ ግን አልችልም።” እንዲህ
ዓይነቶቹ መግለጫዎች በራሱ በኪዳኑ ውስጥ የሚገኙትን የተስፋ ቃሎች እና ቃል
ኪዳኖች የቱንም ያህል አያካትቱም።
በኖህ ዘመን የተከሰተው የጥፋት ውሃ መላውን ዓለም ሳይሆን የተወሰነ
አካባቢን ብቻ ያካተተ ነበር ሲሉ አንዳንዶች ይከራከራሉ። እንደነሱ
አስተሳሰብ ከሆነ በዘፍ. 9፡15 (እንዲሁም ኢሳ. 54፡9) መሰረት
በየጊዜው ሌላ አካባቢያዊ ጎርፍ በተከሰተ ቁጥር እግዚአብሔር የገባውን
ኪዳን ይጥሳል ማለት ነው። በአንጻሩ ሌላ ዓለማቀፋዊ ይዘት ያለው
የጥፋት ውሃ አለመኖሩ የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ትክክለኛነት
ያረጋግጣል። በአምላካዊው ተስፋዎች ላይ እንዴት መተማመን
እንደምንችል ይህ ምን ይነግረናል?
“የሚባርኩህን እባርካለሁ፤ የሚረግሙህን እረግማለሁ፤ በምድር የሚኖሩ ሕዝቦች፣ በአንተ አማካይነት ይባረካሉ።” (ዘፍ. 12፡3)። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፍ. 12፡1-3። እግዚአብሔር ለአብራም የገባቸውን በዓይነታቸው ልዩ የሆኑ ኪዳኖች ይጻፉ።
ከእነዚህ ተስፋዎች መካከል “በምድር የሚኖሩ ሕዝቦች፣ በአንተ አማካይነት
ይባረካሉ” በማለት እግዚአብሔር የተናገረውን ልብ ይበሉ (ዘፍ. 12፡3)። ምን ማለት
ነው? ሁሉም የምድር ቤተሰቦች በአብርሃም የተባረኩት እንዴት ነበር (ገላ. 3፡6-9)?
የመሲሁን የሱስ ተስፋ፣ በዚህ የቀደመ የተስፋ ቃል እንዴት መመልከት ይችላሉ--ገላ.
3፡29?
በዚህ መለኮት ለመጀመሪያ ጊዜ ለአብራም እንደተገለጠለት በሚጠቁም ዘገባ፤
እግዚአብሔር ስለ ቃል ኪዳኑ የሚናገረውን የትኛውንም ዓይነት ቋንቋ ከመጠቀሙ
አስቀድሞም እንኳ ከእርሱ ጋር ቅርበት ያለውና እስከ መጨረሻው የሚዘልቅ ግንኙነት
ለመመስረት ቃል መግባቱ ተመልክቷል። ኋላ ላይ ፈጣሪ አምላክ እንደሚመጣ
የሚያመለክት ቀጥተኛ የኪዳን ማመሳከሪያም ቀርቦአል (ዘፍ. 15፡4-21፣ ዘፍ. 17፡
1-14)። ለጊዜው ግን፣ እግዚአብሔር ለመለኮታዊ--ሰብዓዊ ግንኙነት ታላቅ አጽንኦት
ሲሰጥ ይስተዋላል።
በተጨማሪ አብራም አንድ ትእዛዝ ቢቀበልም፤ ነገር ግን “ውጣ” የሚለው ይህ
ትእዛዝ ፈታኝ ነበር። እርሱ በእምነት ታዘዘ (ዕብ. 11፡8) ነገር ግን መታዘዙ ቃል
የተገቡትን ኪዳኖች እውን በማድረግ ጉዳዩን በዚያው የሚቋጭ አልነበረም።
ይልቁንም መታዘዙ እግዚአብሔር እንዲቋቋም ለፈለገው የፍቅር ግንኙነት የእምነቱ
ምላሽ ነበር። በሌላ አነጋገር አብራም ቀድሞውኑ በእግዚአብሔር እና በአምላካዊ
ቃል አምኗል፣ በእርሱም ታምኗል። ይህ ባይሆን፣ ቤተሰቦቹን ብሎም የአያት ቅድመ
አያቶቹን ምድር ትቶ--ሀ ብሎ ወደ ማያውቀው አገር ለመጓዝ ፍጹም ባልደፈረ ነበር።
መታዘዙ እምነቱን ለሰውም ሆነ ለመላእክት የገለጠ ነበር።
አብራም በዚያን ጊዜ እንኳ በእምነት እና በሥራ መካከል ያለውን ቁልፍ ግንኙነት
ገልጦ አሳይቷል። የዳንነው በእምነት ነው--ወደ መታዘዝ በሚመራና በሥራ በሚገለጥ
እምነት። የመዳን ተስፋ አስቀድሞ የሚመጣ ሲሆን፤ ሥራ ደግሞ ይከተላል።
ምንም እንኳ መታዘዝ ዐልባ ኪዳናዊ ኅብረትም ሆነ በረከት ባይኖርም፤ መታዘዝ
እግዚአብሔር አስቀድሞ ላደረገው ነገር የሚሰጥ የእምነት ምላሽ ነው። እንዲህ
ያለው እምነት በዮሐ. 4፡19 የቀረበውን መርኅ በጉልህ ያንጸባርቃል “እርሱ አስቀድሞ
ወዶናልና እኛ እንወደዋለን።”
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፍ. 15፡6። መልእክቱ የሁሉንም ቃል ኪዳናዊ
ተስፋ መሰረቶች በብዙ መንገድ ገልጦ የሚያሳየው እንዴት ነው? ይህ
በረከት ከሁሉ ይልቅ የከበረ የሆነው ለምንድን ነው?
ጥቅሶቹን ያንብቡና ጥያቄዎቹን ይመልሱ፡ ዘፀ. 6፡1-8፡
1.ስለ ምን ዓይነት ኪዳን ነበር የሚናገረው--ዘፍ. 12፡1-3?
2.በነዚህ ኪዳናዊ ተስፋዎች ክፍል፣ የዕብራውያን ከግብፅ መውጣት
ፍጻሜ የሚያገኘው እንዴት ነበር?
3.እግዚአብሔር በዚህ ስፍራ ለሕዝቡ በሰጠው ተስፋ እና ከጥፋት ውሃ
በፊት ለኖኅ በሰጠው ተስፋ መካከል ምን ዓይነት መመሳሰል ማግኘት
ይችላሉ?
የእስራኤል ልጆች የግብፅን ምድር ከለቀቁ በኋላ--ከባርነት መውጣታቸው ዐውድ
(ዘፀ. 20፡2) በሲና ኪዳኑን የተቀበሉ ሲሆን፤ ይኸው ኪዳን አምላካዊውን የሥርየት
መሥዋዕት ድንጋጌዎች እና የኃጢአት ይቅርታ የያዘ ነበር። ስለዚህ፣ እንደ ሌሎቹ
ሁሉ ይህም የጸጋ ኪዳን ነበር--ለሕዝቡ የተዘረጋ አምላካዊ ኪዳን።
እግዚአብሔር ከአብራም ጋር የገባቸው ዋና ዋናዎቹ ኪዳኖች፣ በብዙ መንገድ በዚህ
ኪዳን ተደጋግሞ ቀርቧል፡
1.እግዚአብሔር ከሕዝቡ ጋር ያለው የተለየ ግንኙነት (ጥቅሶቹን ያስተያዩ፡ ዘፍ. 17:78 እና 19:5-6)።
2.ታላቅ ሕዝብ እንደሚሆኑ መነገሩ (ዘፍ. 12፡2፣ ዘፍ. 19፡6)
3.እንዲታዘዙ መጠየቃቸው (ዘፍ. 17:9–14፣ ዘፍ. 22:16–18፣ ዘፀ. 19:5)
“ይህን ቅደም ተከተል ልብ ይበሉ፡ ጌታ በመጀመሪያ እስራኤልን አዳነ፤ ከዚያም
ይጠብቁት ዘንድ የእርሱ የሆነውን ሕግ ሰጣቸው። በተመሳሳይ ያው ትእዛዝ በወንጌል
ይሠራል። ክርስቶስ በመጀመሪያ እኛን ከኃጢአት ያድነናል (ዮሐ. 1፡29፣ 1ቆሮ. 15:3፣
ገላ 1፡4) ከዚያ የእርሱ ሕግ በውስጣችን ይሠራል (ገላ. 2፡20፣ ሮሜ 4:25፣ 8:1–3፣
1ጴጥ. 2:24)። ” –The SDA Bible Commentary, vol. 1, p. 602.
ጥቅሱን ያንብቡ፡ ዘፀ. 6፡7። እነርሱ ሕዝቦቹ፣ እርሱም አምላካቸው ይሆናል በሚለው
በመጀመሪያው ክፍል የሚመጣው አንድ ነገር ምንድን ነው? እግዚአብሔር ለእነርሱ-እነርሱም ለእግዚአብሔር ምን ትርጉም እንዳላቸው አስመልክቶ የቀረበውን
ተመጋጋቢ ሁኔታ ልብ ይበሉ። እግዚአብሔር በልዩ መንገድ ከእነርሱ ጋር መዛመድ
ብቻ አይፈልግም፤ ነገር ግን እነርሱም ቢሆኑ በልዩ ሁኔታ ከእርሱ ጋር ዝምድና
እንዲፈጥሩ ይፈልጋል። ጌታ ዛሬ ከዚህ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ግንኙነት ከእኛ ጋር
እንዲኖረው አይፈልግም? በዘፀ. 6፡7 የቀረበው የመጀመሪያ ክፍል ከጌታ ጋር ያሎትን
ግንኙነት ያንጸባርቃል ወይስ ስሙ በቤተ ክርስቲያን መዝገብ የሰፈረ ዓይነት ሰው
ብቻ ነዎት?
“አዲስ ኪዳን” በሚል በብሉይ ኪዳን ሲጠቀስ እነዚህ ምንባቦች የመጀመሪያ ናቸው።
ከእስራኤላውያን የግዞት መልስ ዐውድ የቀረበው ይህ ሃረግ፤ እነዚህ ሕዝቦች
ከእግዚእሔር ስለሚቀበሏቸው በረከቶች ይናገራል።
እንደ ቀደሙት ሁሉ፤ የቃል ኪዳኑ አፍላቂም ሆነ አነሳሽ አሁንም እግዚአብሔር
ነው። በጸጋው አማካይነት እንዲሳካ የሚያደርገውም እርሱ ነው።
በተጨማሪ ቋንቋው የቀረበበትን ዐውድ ልብ ይበሉ። እግዚአብሔር ራሱን እንደ
ባል በማቅረብ ሕጉን በልባቸው እንደሚጽፍ ይናገራል። ለአብርሃም ቃል ኪዳን
የገባበትን ቋንቋ ተጠቅሞ፤ እርሱ አምላካቸው እነርሱም ሕዝቦቹ እንደሚሆኑ
ይናገራል። ስለዚህ እንደ ቀደመው ሁሉ፣ ኪዳኑ እንደ ዛሬው የፍትሕ አካላት ሕግ-ሕጋዊ ማዕቀፍ ያለው ስምምነት ብቻ ሳይሆን ከዚያ የላቀ አንደምታ አለው።
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ኤር. 31፡33። ከእስራኤል ጋር የተገባውን የቃል ኪዳን ክፍል
ከሚዘረዝረው ከዘፀ. 6፡7 ጋር ያነጻጽሩ። አሁንም፣ በዚህ ስፍራ የቀረበው ቁልፍ
ባሕርይ ምንድን ነው? እግዚአብሔር ከሕዝቡ የሚፈልገው ምንድን ነው?
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ኤር. 31፡34። በዚህ ስፍራ የተነገረውን ከዮሐ. 17፡3 ጋር ያነጻጽሩ። ለዚህ ግንኙነት መገንባት ጌታ የሚጫወተው ቁልፍ ሚና ምንድን ነው?
እንደ ቀደሙት ቃል ኪዳኖች ሁሉ በኤር. 31፡31-34 የጸጋ እና መታዘዝ አላባዎችን
ማየት ይቻላል። እግዚአብሔር ኃጢአታቸውን ይቅር ይላል፣ ከእነርሱ ጋር ግንኙነት
ይመሰርታል፣ እንዲሁም ጸጋውን በሕይወታቸው ወስጥ ያኖራል። ይህን ተከትሎ
ሰዎች በቀላሉ ይታዘዙታል። ሆኖም መታዘዛቸው ልማዳዊ ወይም ግብታዊ በሆነ
መንገድ ሳይሆን ነገር ግን እርሱን በትክክል ከማወቅ፣ ከመውደድ እና ለማገልገል
ከመፈለግ አኳያ ይሆናል።
ይህ፤ ጌታ ከሕዝቡ ጋር እንዲኖረው የሚፈልገውን መሠረታዊ ነጥብ ይይዛል።
ሕጉ በልባችን ስለ መጻፉ የሚያወሳውን ይህን ጽንሰ ሀሳብ እንዴት
ይረዱታል? ሕጉ እንደየ ግለሰቡ የልቡና አወቃቀር የሚተረጎም እና
ጥቅም ላይ የሚውል፣ ከግላዊ ሕሊና ጋር የተቆራኘ ነው የሚል አንደምታ
በውስጡ ይዟል? ወይስ ከዚህ ይለያል? ከተለየ ምንድን ነው?
የኃይማኖት አባቶች እና ነቢያት “አብርሃም በከነዓን” (ገጽ 142159)፣ “The Prophets of God Helping Them,” pp. 569–571, in Prophets
and Kings.
ከአገልግሎት ጋር የሚያስተሳስረው ቀንበር የእግአብሔር ሕግ ነው። ሰብአዊ
ሠራተኛውን ከእግዚአብሔር ፈቃድ ጋር የሚያስተሳስረው በተድላ ገነት የተገለጸው
በሲና ተራራ ላይ በይፋ የታወጀውና በአዲሱ ቃል ኪዳን በሠረት በሰዎች ልብ ላይ
የተጻፈው ሕግ ነው። የራሳችንን ዝንባሌ እንድንከተልና ፍላጎታችን ወደሚመራን
አቅጣጫ ሁሉ እንድንሔድ ቢደረግ ኖሮ የሰይጣን ጭፍራዎችና የእርሱ ባሕርይ
አንጸባራቂዎች በሆንን ነበር። ስለዚህ እግዚአብሔር ከፍ ባለው፤ በተከበረውና
ወደ ላይ በሚስበው ፈቃዱ ክልል ውስጥ እንድንወሰን አደረገን። የአገልግሎት
ተግባራችንን በትዕግሥትና በአስተዋይነት እንድንቀበል ፍላጎቱ ነው።
ክርስቶስ
እራሱ የአገልግሎትን ቀንበር ሰው ሆኖ ተሸክሞታል። እርሱ “አምላኬ ሆይ! ፈቃድህን
ማድረግ በጣም እወዳለሁ፣ ሕግህንም በልቤ አኖራለሁ” አለ (መዝ. 40፡8)። “እኔ
ከሰማይ የወረድሁት የላከኝን ፈቃድ ለማድረግ እንጂ የራሴን ፈቃድ ለማድረግ
አይደለም” (ዮሐ. 6፡38)። ክርስቶስ ለእግዚአብሔር የነበረው ፍቅር፤ ለእርሱ
ክብር የነበረው ቅንአትና ለወደቀው ሰብአዊ ዘር የነበረው ፍቅር ወደ ዓለም መጥቶ
እንዲሰቃይና እንዲሞት አደረገው። ይህ ነበር የሕይወቱ መሪ ኃይል። ይህን መርሖ
እንድንቀበል ያዘናል።” የዘመናት ምኞት ገጽ 332።
፡
1.እግዚአብሔር ከኖኅ፣ ከአብርሃም፣ ከሙሴ እና ከእኛ ጋር የገባው
ኪዳን--ከአዳም ጋር የገባው ቀጣይ ወይስ አዲስ ነበር? ከሚከተሉት
ጥቅሶች ጋር ያስተያዩ፡ ዘፍ. 3:15፣ ዘፍ. 22:18፣ ገላ. 3:8፣ 16።
2.ኪዳናዊው ግላዊ የግንኙነት ገጽታ በእጅጉ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን
ነው? በሌላ አነጋገር እርስዎ ከሆነ ግለሰብ ጋር ምንም ዓይነት ግላዊ
መስተጋብር ሳይኖሮት ሕጋዊ ውል ሊዋዋሉና “ቃል ኪዳን” ሊገቡ
ይችላሉ። ሆኖም እግዚአብሔር ከሕዝቡ ጋር ባለው ኪዳናዊ ግንኙነት
ይህ ዓይነት መስተጋብር አንዲኖር አይፈልግም። ለምን? ተወያዩበት።
3.ጋብቻ ለዚህ ኪዳን ጥሩ ማሳያ የሆነው እንዴት ነው? የጋብቻ ትስስር
ይህን ኪዳናዊ ግንኙነት ከመግለጽ የሚስተጓጎለው እንዴት ነው?
ማጠቃለያ፡ የኃጢአት መግባት ፈጣሪ የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን
ከሆኑት ሰብዓዊ ቤተሰብ ጋር የመሠረተውን ግንኙነት አፈረሰ። አሁን
ያንኑ በፍቅር የተሞላ ግንኙነት በቃል ኪዳን አማካይነት መልሶ ማቋቋም
እነሆ የእርሱ ፍላጎት ነው። ይህ ኪዳን በሁለታችንም--ማለትም በእኛ
እና በእግዚአብሔር መካከል ላለው ቁርጠኛ (የጋብቻ ዓይነት) ግንኙነት
አጽንኦት የሚሰጥ፣ የመዳናችን እና ከፈጣሪያችን ጋር ወደ ስምምነት
የመምጣታችን ውል ነው። ለእኛ ባለው ታላቅ ፍቅር የተነሣሣው እርሱ
ራሱ የኪዳናዊው ግንኙነት ጀማሪ ነው። በቸርነት በተሞሉ ተስፋዎቹ እና
በርኅሩኅ ተግባራቱ ከእርሱ ጋር ወደ አንድነት እንድንመጣ ያግባባናል።