የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

የተስፋው ቃል፡ የእግዚአብሔር ዘላለማዊ ኪዳን


2ኛ ሩብ ዓመት 2021

ከመጋቢት 18 – 24

1ኛ ትምህርት

Mar 27 - Apr 02




ከዚያስ ምን ተከሰተ?



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ መዝ. 100:3፣ ሐዋ. 17:26፣ ዘፍ. 2:7፣ 18–25፣ ዘፍ. 1:28-29፣ ዘፍ. 3:15።


የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ “እግዚአብሔር ‘ሰውን በመልካችን፣ በአምሳላችን እንሥራ’… አለ። ስለዚህ እግዚአብሔር ሰውን በራሱ መልክ ፈጠረው፤ በእግዚአብሔር መልክ ፈጠረው፤ ወንድና ሴት አድርጎ ፈጠራቸው።” (ዘፍ. 1፡26-27)።

የ ሰውን ልጅ ፍጥረት አስመልክቶ የቀረበው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ዘገባ በተስፋ፣ በደስታ እና በፍጽምና የተሞላ ነው። እያንዳንዱ የፍጥረት ቀን የተጠናቀቀው “መልካም” በሚል መለኮታዊ መግለጫ ነበር። አባባሉ ዐውሎ ነፋስን፣ ርዕደ መሬትን፣ ረሃብን እና በሽታን የሚያካትት እንዳልነበር እሙን ነው። ከዚያስ ምን ተከሰተ?

ስድስተኛው የፍጥረት ቀን የተጠናቀቀው “እጅግ መልካም” በሚል መለኮታዊ መግለጫ ነበር። ለዚህ ምክንያቱ ያን ቀን ጌታ ፍጡሮቹን፣ ማለትም ሰውን በገዛ አምሳሉ በመፍጠሩ ነበር። በየትኛውም የዘፍጥረት ዘገባ እርሱ ይህን ፈጽሞ አላደረገም። እነዚህ ፍጥረቶቹ በእርግጥ በሁሉም ረገድ ፍጹማን ነበሩ። መሆንም ነበረባቸው። ደግሞስ የተፈጠሩት በእግዚአብሔር አምሳል አልነበር? ነፍሰ ገዳዮች፣ ሌቦች፣ ሐሰተኞች፣ አጭበርባሪዎችና ክፉዎች ፈጽሞ የፍጥረቱ አካል አልነበሩም።

ፍጥረት ላይ ምልከታ የሚያደርገው የዚህ ሣምንት ትምህርት፣ በመጀመሪያ የእግዚአብሔርን የፍጥረት ሥራ፣ በመቀጠል ደግሞ ፍጹም በነበረው በዚያ የፍጥረት ሥራ መሃል የሆነውን ነገር ይቃኛል። በመጨረሻ እግዚአብሔር ነገሮችን ዳግመኛ ለማስተካከል ምን እያደረገ እንደሆነ አስመልክቶ የሩብ ዓመቱን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጭብጥ ይዳስሳል። ሣምንቱን በጨረፍታ፡ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ፍጥረት ጅማሮ ምን ያስተምራል? እግዚአብሔር ከሰብዓዊው ፍጡር ጋር ምን ዓይነት ግንኙነት እንዲኖረው ፈለገ? መልካምና ክፉ የሚያሳውቀው ዛፍ ዓላማ ምን ነበር? አዳምና ሔዋን እንደ ወደቁ የተሰጣቸው ተስፋ ምን ነበር?

መጋቢት 19
Mar 28

ቁልቁል የተደረደሩት ኤሊዎች…


“በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማያትንና ምድርን ፈጠረ” (ዘፍ. 1፡1) አንድ ሣይንቲስት በፀሐይ ምህዋር ዙሪያ ስለሚሽከረከሩ ፕላኔቶች እና በጋላክሲ አማካኝ ስፍራ ስለሚገኘው የፀሐይ ምህዋር ገለጻ እያደረገ እያለ፣ በዕድሜ ጠና ያሉና ጥቁር የቴኒስ ጫማ የተጫሙ አንዲት ሴት ብድግ ብለው፣ ምድር በኤሊ ጀርባ ላይ የተቀመጠች ጠፍጣፋ ዲስክ ናት አሉ። ሣይንቲስቱ እንደ መቀለድ ብሎ ኤሊዋ ምን ላይ እንደተቀመጠች ጠየቃቸው። ሴትየዋም--ሌላ ኤሊ ላይ መቀመጧን ተናገሩ። ሣይንቲስቱ መቀለዱን በመቀጠል “ሌላዋ ኤሊ ምን ላይ ተቀመጠች?” ሲል በድጋሚ ሴትየዋን ቢጠይቃቸው--“አሁንም ሌላ ኤሊ ላይ” ብለው መለሱ። እንደገና ሌላዋ ኤሊ ምን ላይ እንደተቀመጠች ሣይንቲስቱ ከመጠየቁ አስቀደሞ፤ ሴትየዋ ሌባ ጣታቸውን--አይደለም በሚል ስሜት እየነቀነቁ “ምን አለፋህ ልጄ፣ ኤሊዎቹ እንደሆኑ ቁልቁል ተደርድረዋል” አሉት ይባላል።

ታሪኩ የቱንም ያህል መሳጭ ሊሆን ቢችልም የራሱን የአጥናፈ ሰማይ ተፈጥሮን ጨምሮ በጣም አንገብጋቢ ስለ ሆነው የሰው ልጅ አመጣጥ ጉዳይ ለማውሳት ይሞክራል። የገዛ ምርጫችንን ሳናደርግ ራሳችንን ያገኘንበት ይህ ዓለም ምንድን ነው? እዚህ ለምንና እንዴት ልንገኝ ቻልን? በመጨረሻስ እኛ ሁላችን ወዴት እንሄዳለን? እነዚህ እንግዲህ፣ ሰዎች ሊጠይቁ የሚችሏቸው በጣም መሠረታዊና አንገብጋቢ ጥያቄዎች ናቸው። ምክንያቱም ስለ ማንነታችን እና እዚህ እንዴት እንደተገኘን የሚኖረን ግንዛቤ፣ በምድር እስካለን በምንኖረው እና በምንሠራው ነገር ላይ ተጽእኖ ይኖረዋል።

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፍ. 1:1፣ መዝ. 100:3፣ ኢሳ. 40:28፣ ሐዋ. 17:26፣ ኤፌ. 3:9፣ ዕብ. 1:2፣ 10። እያንዳንዱ ጥቅስ ከላይ ለቀረቡት ጥያቄዎች እንዴት በራሱ መንገድ መልስ ይሰጣል? ሁሉንም የሚያመሳስል አንድ ነጥብ ምንድን ነው?



ዘፍ. 1፡1 (ወይም ሌሎቹን ጥቅሶች) አስመልክቶ ልብ ከሚመስጡ ነጥቦች አንዱ ጌታ ፈጣሪ መሆኑን ለማረጋገጥ አለመሞከሩ ነው። የእርሱን ፈጣሪነት አጉልተው ለማሳየት የቀረቡ አንዳችም ዓይነት የሙግት ሀሳቦች የሉም። እንደውም-ለማብራራት፣ ለማስረዳት ወይም ለማረጋገጥ አንዳችም ሙከራ ሳይደረግ፣ የሆነውን ሁሉ እንደው በቀላሉ ሊስተዋል በሚችልና ግልጽ በሆነ ቋንቋ ሲጠቅስ ይስተዋላል። እኛ ደግሞ--በእምነት እንቀበለዋለን ወይም እንቀበለውም። አንድ ቀላል ምክንያት ለማቅረብ ያህል--ልንቀበል የምንችልበት ብቸኛው መንገድ እምነት መሆኑ እሙን ነው። ከመካከላችን አንዳችንም ብንሆን የፍጥረትን ሥራ ሂደት ለመታዘብ በዚህ አልነበርንም። እርግጥ ነው፣ በገዛ አፈጣጠራችን ላይ መገኘት የማይሆን አመክንዮ ሊሆን ይችል ነበር። ራሳቸው ዓለማውያን፤ አጀማመርን አስመልክቶ የቱንም ዓይነት አመለካከት ቢጋሩ እንኳ፣ እኛ በፍጥረት ሥራ ከምናምነው በተመሳሳይ እነርሱም በአመለካከታቸው ላይ እምነት ሊኖራቸው የግድ ይሆናል። ያን ክስተት ለመታዘብ አንዳችንም በዚያ አልነበርንም።

የሆነው ሆኖ፣ እግዚአብሔር በፈጣሪነቱ እንድናምን የሚጠይቀን ቢሆንም እንኳ፣ እርሱን እንድናምን የሚያደርጉ ጥሩ ምክንያቶች ሳይሰጠን፣ እንደው በደፈናው እንድናምነው አይጠይቀንም። በማንኛውም በምናምነው ነገር፣ የተወሰነ መጠን ያለው እምነት እንደሚፈለግብን በመገንዘብ፤ ጅማሮአችን በሌላ ሳይሆን ሙሉ ለሙሉ በዕድል ላይ የተመሰረተ ነው ከሚለው እሳቤ በተቃራኒ--እኛ እዚህ ለመኖራችን ምክንያት ፈጣሪ ዓላማ እንዳለው ማመናችን ትርጉም ሊሰጠን የቻሉባቸውን ምክንያቶች ይጻፉ።

መጋቢት 20
Mar 29

በፈጣሪ አምሳል (ዘፍ. 1፡27)


እግዚአብሔር ሰውን ወንድና ሴት አድርጎ “በራሱ መልክ” (ዘፍ. 1፡27) እንደፈጠረ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። ከዚህ ጽንሰ ሀሳብ በመነሣት የሚከተሉትን ጥያቄዎች ይመልሱ፡ 1.እግዚአብሔር በራሱ መልክ ፈጠረን ማለት ምን ማለት ነው? “በራሱ መልክ” የሆንነው በምን መልኩ ነው

? 2.በዘፍጥረት ዘገባ መሠረት ጌታ ከሰው ልጆች ሌላ “በራሱ መልክ” የፈጠረው ነገር አለ? ካልሆነ፣ ከተቀሩት የምድር ፍጥረታት በተቃራኒ ስለተላበስነው ልዩ ማንነት ምን ይነግረናል? ከዚህ ንጽጽር ምን ዓይነት ትምህርት እናገኛለን

? 3.ስለ ሰው ልጅ አፈጣጠር በቀረበው ዘገባ መሠረት ይህን ዘር ከማንኛውም ጌታ ከፈጠረው ፍጥረት በተለይ ነጥሎ የሚያስቀምጥ ሌላ ምን ነገር ይገኛል? ዘፍ. 2፡7፣ 18-25።

ምንም እንኳ በሰዋዊው አነጋገር ስለ እግዚአብሔር መናገር ቢኖርብንም፤ እርሱ መለኮታዊ ባህሪያትን የተላበሰ መንፈሳዊ ማንነት (ዮሐ. 4፡24) ያለው አምላክ መሆኑን መዘንጋት የለብንም። እኛ በአካላዊ፣ አእምሮአዊ እና መንፈሳዊ ተፈጥሮአችን በተወሰነ መንገድ መለኮታዊ ፈጣሪያችንን የምናንጸባርቅ ቢሆንም፤ ነገር ግን አሁንም ቢያንስ ለእኛ ከመጋረጃ ጀርባ እንደ ተሸሸገ የሚቆይ ብዙ ምስጢር አለ። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ በመንፈሳዊና አእምሮአዊ ገጽታዎቻችን ላይ አጽንኦት ይሰጣል። እነዚህን ገጽታዎች ማጎልበት እና ማሻሻል እንችላለን። የተቀረው የእግዚአብሔር ምድራዊ ፍጥረት ሊያደርግ የማይችለውን ከእግዚአብሔር ጋር ገንቢ የሆነ ግንኙነት እንዲኖር የሚያደርግ፣ ይኸው በዓይነቱ ልዩ የሆነ የሰው አእምሮ ነው።

እግዚአብሔር በዓይነቱ ልዩ በሆነ መንገድ እንዴት ሴትን እንደፈጠረ ልብ ማለቱም እንዲሁ ተገቢ ነው። እነዚህ ወንድ እና ሴት--ሁለቱም በእግዚአብሔር አምሳል የመፈጠር፣ ለማመን የሚያዳግት ልዩ መብትና ጥቅም ይጋራሉ። አፈጣጠራቸውን አስመልክቶ አንዳቸው ከሌላቸው ማነሳቸውን የሚያሳይ ምንም ዓይነት ፍንጭ አልታየም ነበር። እግዚአብሔር ራሱ ሁለቱንም ከተመሳሳይ ነገር አበጃቸው። እርሱ ገና ከመጀመሪያው ሁለቱንም እኩል አድርጎ ፈጥሮ ሲያበቃ፣ ከእርሱ ጋር የተለየ ግንኙነት እንዲኖራቸው አድርጎ በአንድ ላይ አኖራቸው። ሁለቱም እግዚአብሔር የሰጣቸውን ባህሪያት ለእርሱ ክብር እንደሚያመጣ አድርገው ማጎልበት የሚችሉባቸው ተመሳሳይ ዕድሎች ነበሯቸው።

“እግዚአብሔር ራሱ ለአዳም አጋር ፈጠረለት። ረዳትና ድጋፍ የምትሆነውን፣ በፍቅርና በእርዳታ ከእርሱ ጋር አንድ ልትሆን የምትችለውን አጋሩን ፈጠረለት። ሔዋን ከአዳም እራስ በላይ ሆና እንዳትሰለጥንበት ከእግሮቹ በታችም ሆና እንዳይረግጣት ነገር ግን ከአዳም እኩል ሆና ከጎኑ እንድትሆን፤ አዳምም እንዲወዳትና እንዲጠብቃት በማለት እግዚአብሔር ሔዋንን ከአዳም ከጎኑ አጥንት ወስዶ ፈጠራት።” (የኃይማኖት አባቶች እና ነቢያት፡ ገጽ 37-38)

መጋቢት 21
Mar 30

የእግዚአብሔር እና የሰው አብሮነት (ዘፍ. 1፡28-29)


እግዚአብሔር ለመጀመሪያ ጊዜ ለሰብዓዊው ፍጡር የተናገራቸውን ቃላት ልብ ይበሉ። አምሳያ ልጆቻቸውን የመውለድ ብሎም አብልጠው የመራባት ችሎታ እንዳላቸው ይጠቁማል። በተጨማሪ ወደ ራሷ ወደዚህች ምድር እንዲሁም ወደ ፍጥረታት እያመላከተ እንዲሞሏት፣ እንዲቆጣጠሯትና የበላይዋ ሆነው እንዲገዟት ሲነግራቸው ይታያል። ሊመገቡ ወደሚችሏቸው ተክሎችም ያመላክታቸዋል። በአጭሩ፣ መጽሐፍ ቅዱስ በሚናገረው መሠረት እግዚአብሔር ለወንድ እና ለሴት የተናገራቸው የመጀመሪያዎቹ ቃላት በተለይ ከአካላዊው ዓለም ጋር ያላቸውን መስተጋብር እና ግንኙነት ይመለከታሉ።

እግዚአብሔር በቁሳዊው ዓለም ላይ ስላለው አመለካከት ዘፍ. 1፡28-29 ምን ይነግረናል? በቁሳዊው ዓለም እና በዚያ ደስ በመሰኘታችን ውስጥ የሆነ አጉል ነገር መኖሩን ያመላክታሉ? ከራሱ ከፍጥረት ጋር እንዴት መዛመድ እንደሚኖርብን አስመልክቶ ከእነዚህ የመጀመሪያዎቹ የሰው ልጅ ታሪካዊ ትዕይንቶች ምን ዓይነት ትምህርቶች ማግኘት እንችላለን?



እግዚአብሔር በእነዚህ ቃላት አማካይነት ከሰብዓዊው ፍጡር ጋር ለመሰረተው ግንኙነት የመጀመሪያውን እርምጃ ይወስዳል። ያናግራቸዋል፣ ትእዛዝ ይሰጣቸዋል፣ ምን ማድረግ እንዳለባቸውም ይነግራቸዋል። በቃላት ያልተገለጹ ኃላፊነቶችም እንዲሁ አሉ። እግዚአብሔር አምላክ ራሱ በሠራው በዚህ አስደናቂ ፍጥረት ላይ ጌቶች ይሆኑ ዘንድ ጠየቃቸው። ዘፍ. 1፡28 እግዚአብሔር አዳምንና ሔዋንን እንደባረካቸው ይናገራል። ለመሆኑ ይህ ምን ማለት ነው? በእነርሱ እና በፈጣሪያቸው መካከል ምን ዓይነት ግንኙነት መኖሩን ያመለክታል

? አዳምና ሔዋን ለአምላካዊው በጎነት ምላሽ መስጠት እና ከእርሱ ጋር ህብረት መፍጠር እንደሚችሉ ብልህ ሰዎች አነጋገራቸው። ደግሞም አዳምና ሔዋን እንደ ፍጥረት ልጅነታቸው በፈጣሪ አባታቸው በረከት እና እንክብካቤ ጥላ ስር ነበሩ። የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ ሰጣቸው። የሰጣቸው ነገር ይገባቸው ዘንድ አንዳችም ያደረጉት ነገር አልነበረም። ያልደከሙበት ነገር ንጹህ ተቀባዮች ነበሩ። ስለ ወንድ እና ሴት መፈጠር ስናነብ ኃጢአት ከመግባቱ አስቀድሞ የነበሩትን መሰረታዊ ባህሪያት እና አሁን ከኃጢአት በኋላ ከእግዚአብሔር ጋር እንድንመሰርት የሚፈልገውን የግንኙነት ዓይነት መመልከት እንችላለን። የዕለቱን ጥናት በመገምገም በዚህ በወደቅንበት ሁኔታ ውስጥ ሆነንም እንኳ፣ ከእርሱ ጋር ዝምድና መፍጠር የምንችልበትን መንገድ እንድናስተውል የሚረዱንን ትይዩ ነጥቦች ይመልከቱ።

መጋቢት 22
Mar 31

ከ…ዛፉ


“እግዚአብሔር አምላክ ሰውን እንዲህ በማለት አዘዘው፤ ‘በአትክልት ስፍራው ውስጥ ከሚገኝ ከማንኛውም ዛፍ ፍሬ ትበላለህ። ነገር ግን መልካምና ክፉን ከሚያሳውቀው ዛፍ አትብላ፤ ምክንያቱም ከእርሱ በበላህ ቀን በእርግጥ ትሞታለህ’” (ዘፍ. 2፡16-17)። ይህ ፈተና አዳምና ሔዋን ነፃ የመምረጥ ችሎታቸውን የሚለማመዱበት ዕድል አስገኘላቸው። እንዲሁም ከፈጣሪ ጋር ባላቸው ግንኙነት አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ምላሽ እንዲሰጡ ፈተናቸው። በተጨማሪ እግዚአብሔር ነፃ የሆነ ሥነ ምግባር ባለቤት አድርጎ ፈጥሮአቸው እንደነበር ያሳያል። ለነገሩ እንዳይታዘዙ ያደረጋቸውን ዕድል ባያገኙ ኖሮ እግዚአብሔር እነርሱን ለማስጠንቀቅ ባልተጨነቀ ነበር

። “በምዕራፉ በቀዳሚነት የቀረበ ማንኛውም ነገር ወደዚህ ጡዘት የሚያደርሰውን መንገድ ጠርጓል (ዘፍ.2፡16-17)። የወደፊቱ ፍልሚያ እምብርት ይህ ብቸኛ ክልከላ ይሆናል። ሰው በብዙ ጉዳዮች ግራ መጋባት የለበትም። አንድ መለኮታዊ ሥርዓት ብቻ በአእምሮ ውስጥ እንደ ተጠበቀ ሊኖር ይገባል። በመሆኑም፣ የትእዛዞች ቁጥር በአንድ መገደባቸው የያሕዌን ምህረት ምልክቶች ይሰጣል። በተጨማሪም፣ ይህ አንድ ትእዛዝ ከባድ አለመሆኑን ለመግለጽ ጌታ ‘‘በአትክልት ስፍራው ውስጥ ከሚገኝ ከማንኛውም ዛፍ ፍሬ ትበላለህ’ ከሚል ሰፊ ፈቃድ አኳያ አስቀምጦታል።”—H. C. Leupold, Exposition of Genesis (Columbus, OH: Wartburg Press, 1942), vol. 1, p. 127.

እግዚአብሔር--አዳምና ሔዋን ፈቃዱን እንዲታዘዙ ጥሪ ሲያቀርብላቸው፡ እኔ ፈጣሪያችሁ ነኝ፣ በአምሳሌ ፈጥሬአችኋለሁ እያላቸው ነበር። ሕይወታችሁ በእኔ የተደገፈ ነው፣ በእኔ ትኖራላችሁ፣ ትንቀሳቀሳላችሁ፣ ህልውናም አላችሁ። ምቾታችሁና ደስታችሁ የተሟላ ይሆን ዘንድ ሁሉንም ነገር (የተሟላ አቅርቦት፣ መኖሪያ፣ የሰው አብሮነት) በመስጠት በስሬ የዚህ ዓለም ገዢ አድርጌ ሾሜያችኋለሁ። እኔን ከመውደዳችሁ የተነሣ ይህን ግንኙነት ለማጽናት ፈቃደኞች ከሆናችሁ፣ እነሆ እኔ አምላካችሁ እሆናለሁ እናንተም ልጆቼ ትሆናላችሁ። እናም፣ ይህን ግልጽ ሆኖ የቀረበ ልዩ ትዕዛዝ በመታዘዝና በመታመን ግንኙነቱ ጸንቶ እንዲኖር ማድረግ ትችላላችሁ።

በመጨረሻም፣ ከእግዚአብሔር ጋር ያለን ግንኙነት ውጤታማ እና ዘላቂ ሊሆን የሚችለው በነፃነት ፈቃዱን ለመቀበል ከመረጥን ብቻ ነው። አምላካዊውን ፈቃድ መቃወም፣ ከእርሱ ነፃ ነኝ እንደማለት ነው። እርሱ አያስፈልገንም ብለን ማመናችንን ያመለክታል። ምርጫ ክፉን የማወቅ ውጤት ሊያስከትል የሚችል ኃይል ያለው ሲሆን፣ ክፉ ደግሞ ማግለል፣ ብቸኛ ማድረግ፣ ተስፋ ማስቆረጥ ብሎም ሞት ያስከትላል።

እግዚአብሔር ለአዳምና ሔዋን የሰጠው ፈተና አንዱ የታማኝነት እና የእምነት አካል ነበር። የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ ለሰጣቸው ፈጣሪያቸው ታማኝ እንደሆኑ ይጸናሉ፤ በዚህም ምድር የደስታ ስፍራ ትሆንላቸዋለች--ወይስ ከእርሱ ፈቃድ ነፃ ሆነው በራሳቸው መንገድ ይጓዛሉ? ቃሉን ተቀብለው ለመተግበር በእርሱ ላይ በቂ እምነት ይኖራቸው ይሆን? ታማኝነታቸው እና እምነታቸው መልካም እና ክፉ በሚያሳውቀው ዛፍ ተፈተነ። እኛ በየቀኑ ተመሳሳይ ፈተናዎች የምንጋፈጥባቸው መንገዶች የትኞቹ ናቸው? የእግዚአብሔር ሕግ በዘፍ. 2:16-17 ከተጠቀሰው ትእዛዝ ጋር ትይዩ ሆኖ የሚሠራው እንዴት ነው?

መጋቢት 23
Apr 1

ግንኙነትን ማፍረስ


እኛ የምናውቃቸውን ሰዎች የማመን አዝማሚያ ያለን ሲሆን፤ የማናውቃቸውን ግን በደመ ነፍስ አናምናቸውም። ሔዋን እንደው በተፈጥሮ በሰይጣን ላይ እምነት እንድትጥል የሚያደርጋት አንዳች ነገር አልነበረም። ከዚህ አልፎ በእግዚአብሔር ላይ ሊሰነዘር ለሚችል ማንኛውም ዓይነት ቀጥተኛ ጥቃት ተከላካዩ ትሆናለች ተብሎ ነው የሚታሰበው። ታዲያ ሰይጣን የሔዋንን ተፈጥሯዊ መከላከያዎች ለማለፍ ምን ዓይነት ቅደም ተከተሎችን ሥራ ላይ አዋለ--(ዘፍ. 3:1–6)

? “የሔዋን መተላለፍ ከአስከፊነቱ ባሻገር በሰብዓዊው ቤተሰብ ላይ ወዮታ ማስከተል የሚችል አቅም የነበረው ቢሆንም፤ የእርሷ ምርጫ ሰብዓዊውን ዘር በመተላለፍ ቅጣት ውስጥ የግድ የሚያካትት አልነበረም። ኃጢአትንና ሞትን አይቀሬ የሰው ዘር ፍርጃ ያደረገው ከእርሷ ይልቅ የእግዚአብሔርን ግልጽ ትእዛዝ በሚገባ ያውቅ የነበረው አዳም ሆነ ብሎ የመረጠው ምርጫ ነበር። ሔዋን ተታላለች፤ አዳም ግን አልተታለለም ነበር”–The SDA Bible Commentary, vol. 1, p. 231.

ይህን ግልጽ መተላለፍ እና አምላካዊውን ትእዛዝ አለማክበር ተከትሎ በእግዚአብሔር እና በሰው ልጆች መካከል ያለው ግንኙነት ተቆረጠ። ከእግዚአብሔር ጋር ግልጽ ህብረት መፍጠር--ከእርሱ መገኛ በፍርሃት ወደ መኮብለል ተቀየረ (ዘፍ. 3፡8-10)። ሕብረት እና እጅግ የቀረበው መንፈሳዊ ግንኙነት በመነጠል እና መለያየት ተተካ። ኃጢአት በመከሰቱ ሁሉም ዓይነት አስቀያሚ ውጤቶች ተከትለውት መጡ። አንድ ነገር ካልተደረገ በቀር የሰው ልጅ ወደ ዘላለማዊ ጥፋት እያመራ ነበር። በዚህ አሳዛኝ ሁኔታ መሃል እግዚአብሔር ምን የሚሉ የተስፋ ቃላት ተናገረ? (ዘፍ. 3:15)



የእግዚአብሔር አስገራሚ የትንቢታዊ ተስፋ ቃል በእባቡና በሴቲቱ፣ በዘሯ እና በዘሩ መካከል ስላለው የጠላትነት መለኮታዊ ድንጋጌ ይናገራል። የሴቲቱ ዘር ተወካይ የሆነው ፍሬ በሰይጣን ራስ ላይ የሚያደርሰውን ለሞት የሚዳርግ ቅጥቀጣ የመጨረሻ የድል አድራጊነት ገጽታ የሚያስቃኝ ሲሆን፤ ሰይጣን ግን የመሲሁን ተረከዝ ብቻ ይቀጠቅጣል። ይህ ተስፋ በእግዚአብሔር የተሰጠና በእግዚአብሔር የተደገፈ እንደ መሆኑ፤ ፍጹም ረዳት አልባ ሁናቴ ውስጥ የነበሩት አዳምና ሔዋን ህልውናቸውን ሊቀይር በሚችለው በዚህ መሲሐዊ ኪዳን ተስፋ ማግኘት ነበረባቸው። ይህ የመሲሑ ተስፋ እና የመጨረሻ ድል በዚያን ወቅት በማያሻማ ሁኔታ ቢነገርም፤ ኃጢአት የጽልመት ጥላ አጠላበት።

እግዚአብሔር አምላክ አዳምን “‘የት ነህ?’” ሲል የጠየቀበትን ጥቅስ ያንብቡ፡ ዘፍ. 3፡9። በእርግጥ እግዚአብሔር የት እንደ ነበሩ ያውቅ ነበር። የተናገራቸው ቃላት ከመኮነን ይልቅ በጥፋተኝነት ስሜት የተሞላውን ሰብዓዊ ዘር ወደ እርሱ የሚመልሱ ነበሩ። በአጭሩ እግዚአብሔር ለወደቀው የሰው ዘር የተናገራቸው የመጀመሪያዎቹ ቃላት በእርሱ ጸጋ እና ምህረት ተስፋ የቀረቡ ነበሩ። ዛሬም ቢሆን እግዚአብሔር ወደ ምህረቱ እና ጸጋው እየጠራን መሆኑን የምናይባቸው መንገዶች የትኞቹ ናቸው?

መጋቢት 24
Apr 2


ተጨማሪ ሀሳብ


መጽሐፍ ቅዱስ ለኃጢአተኞች እና ኮብላዮች በቀረቡ ጥሪዎች የተሞላ ነው። ጥቅሶቹን ያስተየዩ፡ መዝ. 95:7-8፣ ኢሳ. 55:1-2፣ 6-7፣ ሉቃ. 15:3–7፣ ሉቃ. 19:10። ሌሎች ተመሳሳይ ጥቅሶች ማግኘት ይችላሉ? የኃይማኖት አባቶች እና ነቢያት በሚል ርዕስ ከተተረጎመው የኤለን ኋይት መጽሐፍ፡ “ፍጥረት” ከገጽ 35-44፣ “ፈተናና ውድቀት” ከገጽ፡ 45-58፣ “የደኅንነት እቅድ” ከገጽ 59-69 ያንብቡ። “በልምላሜ የተሞላውን የአትክልት ስፍራ አልፈው ‘የት ነህ?’ በሚል ወደ ተቅበዝባዦቹ ጆሮዎች በደረሱ በእነዚያ ሁለት መለኮታዊ ቃላት ውስጥ የወንጌል ስብከት ይደመጥ ነበር። አምላክህ አንተን ለማጣት ፈቃደኛ አይደለም። ውሎ አድሮ በልጁ አካል ሆኖ ሊፈልግህ እንደሚመጣ እየነገረህ ነው። ይኸውም ለመፈለግ ብቻ ሳይሆን የጠፋውን ለማዳን ጭምር ነው።” —Charles Haddon Spurgeon, The Treasury of the Bible (Grand Rapids, MI: Zondervan Publishing House, 1962) Old Testament, vol. 1, p. 11.


የመወያያ ጥያቄዎች



፡ 1.ደግ እና አሳቢ የሆነው እግዚአብሔር አምላክ የሰው ልጆችን የሚፈልግ እንደመሆኑ፤ ለዚህ በአብ እና በየሱስ ክርስቶስ የተገለጠ ፍቅር ምላሻችንን መስጠት የምንችለው እንዴት ነው? ጌታ ምላሻችንን እንድንሰጥ የሚጠባበቅበት መንገድ ምን ይመስላል

? 2.ሰብዓዊው ፍጡር ከነበረበት የእግዚአብሔር ፍጥረት ከፍታ መውደቁን የሚያሳየውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ገጽታ፤ ከዝግመተ ለውጥ የሰው አመጣጥ ንድፈ ሀሳብጋር ያነጻጽሩ። የትኛው የበለጠ ተስፋ ይሰጣል? ለምን

? 3.በፍቅር የተሞሉ ግንኙነቶች ለሰው ልጅ ደስታ ምን ያህል አስፈላጊ ናቸው? ከእግዚአብሔር ጋር የሚኖር እየበለጸገ የሚሄድ ግንኙነት ለእንዲህ ዓይነቱ ግንኙነት አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? እንዲህ ዓይነቶቹ ግንኙነቶች (በልጆችና በወላጆች፣ በባልና በሚስት፣ በተቀጣሪ እና በቀጣሪ ወዘተ) መሃል በሚኖራቸው ተጽእኖዎች ዙሪያ ተወያዩ።

ማጠቃለያ፡ እግዚአብሔር በእኛ እና በእርሱ መሀል በፍቅር የተሞላ ኅብረት እንዲኖር ስለፈለገ እነሆ በአምሳሉ ፈጠረን። ምንም እንኳ የኃጢአት መግባት የቀደመውን ግንኙነት ቢያፈርስም፤ እግዚአብሔር በደኅንነት እቅድ አማካይነት ለማደስ ይፈልጋል። ህልውናችን በእርሱ ላይ የተመሰረተ እንደመሆኑ፤ ከፈጣሪያችን ጋር ወደ አንድ ኅብረት ስንገባ ብቻ ህይወት እውነተኛ ትርጉም ያለውና የከበረ ይሆናል።




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA union SSL