የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

የተስፋው ቃል፡ የእግዚአብሔር ዘላለማዊ ኪዳን


2ኛ ሩብ ዓመት 2021

ከመጋቢት18 - ሰኔ 18 (2013) ዓ.ም.

መደበኛ እትም

Dec 30 - Mar 26




አዘጋጅ: ገርሃርድ ኤፍ. ሀሰል

ዘላለም አስረስ እንደተረጎመው



ይህ የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ የሚዘጋጀው በሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተ ክርስቲያን ዋና መስሪያ ቤት በሆነው በጀነራል ኮንፍረንስ ውስጥ ሆኖ፤ የጎልማሶች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያን በሚያዘጋጀው ቢሮ ነው። መምሪያዎቹ የሚዘጋጁት የጀነራል ኮንፈረንስ አስተዳደር ኮሚቴ ንዑስ ኮሚቴ በሆነውና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያዎችን በሚያሳትመው የሰንበት ትምህርት ሕትመት ቦርድ ነው። የታተመው መምሪያ በውስጡ ዓለም አቀፋዊ የሆነ የምዘና ኮሚቴ ሀሳቦችንና የሰንበት ትምህርት ሕትመት ቦርድን ማረጋገጫ ስለሚያንጸባርቅ የአዘጋጁን (የአዘጋጆችን) ሀሳብ ብቻ የሚወክል አይደለም። በኢትዮጵያ አድቬንቲስት ማተሚያ ቤት ታተመ

ቃል ኪዳኑ

በ1588 አንዲት እንግሊዛዊት ወጣት (የሰባት ወር ነፍሰ ጡር) ወጣ ብላ ወደ ተንጣለለውን ባህር ስታማትር ያየችውን አስፈሪ ክስተት ዐይኖቿ ማመን አቃታቸው። የስፔን የጦር ጀልባዎችና ከባድ መሣሪያ የታጠቁ መርከቦች ደሴቲቱን ለመውረር በመገስገስ ላይ መሆናቸውን መመልከቷ ከፈጠረባት ብርቱ የፍርሐት ስሜት የተነሣ ያለ ጊዜዋ ምጥ ያዛት። አዋላጇም እንዲሁ ሁኔታው አስፈቷት ነበር።

ከአውሮፓ ታላላቅ የፖለቲካ ንድፈ ሀሳብ አመንጪዎች አንዱ የነበሩት ቶማስ ሆብስ እንደሚናገሩት፤ ፍርሐት ልጇ በራሱ የሰጠው ተገቢ ምላሽ ነበር። እንግሊዝ በእርስ በእርስ ጦርነትና ማለቂያ በሌለው ኃይማኖታዊ አመጸ በታመሰችበት ዘመን የኖሩት ሆብስ፤ የሰው ልጅ ጠንካራና ሁሉን አካታችት መንግሥት ከሌለው--ያለመረጋጋት ፍርሐት፣ እወረራለሁ ብሎ መፍራት፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ የሞት ዘላለማዊ ፍርሃት ነግሦበት ይኖራል። “ሁሉም በሁሉም ላይ የተነሣበት ጦርነት” ብለው እርሳቸው ለሰየሙት ዘመን--ሥር ነቀል ለውጥ ካልተደረገ በቀር የሰው ልጅ ሕይወት “ብቸኛ፣ ደኻ፣ አጸያፊ፣ አውሬ እና አጭር ይሆናል” ብለው አስጠንቅቀዋል።

መፍትሔው ምን ነበር? መፍትሔው አንድ ብቻ እንደነበር ሁብስ ይናገራሉ፡ የሕዝቡን መጠን የለሽ ፍላጎት ወደ አንድ ብቻ ፍላጎት የሚያመጣና በእነርሱ ላይ የተሟላ ሥልጣን ያለው ኃይል መመስረት። ይህ ኃይል፣ ይህ ሉአላዊ--አንድ ግለሰብ ወይም የግለሰቦች ስብስብ ሸንጎ ሊሆን ይችላል። ምንም እንኳ ይህ ኃይል በግዛቱ ላይ ፍጹም ፈላጭ ቆራጭ የሆነ አምባገነን ሥልጣን ሊኖረው ቢችልም፤ የሕዝቡን ሕይወት እጅግ አስፈሪና ያልተረጋጋ ያደረጉትን አስከፊ ሁኔታዎች ግን ያስቀራል። በሌላ አነጋገር ሕዝቡ መብቱን ለገዢዎቹ አሳልፎ ሲሰጥ፣ በልዋጩ ሰላምና ደህንነት ያገኛል። ይህ ሥልጣን ከሕዝብ ወደ አምባገነን፣ ፈላጭ ቆራጭ አካል የተሸጋገረበትን አካሄድ ሁብስ “ቃል ኪዳን” ብለው ጠርተውታል።

ሆኖም የቃል ኪዳን ጽንሰ ሀሳብ ጠንሳሽ--የፖለቲካ ንድፈ ሀሳብ አመንጪው ቶማስ ሆብስ አልነበሩም። በተቃራኒው በሺዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በፊት እግዚአብሔር ከእስራኤል ጋር ቃል ኪዳን ገብቷል። እንደ እውነቱ ከሆነ ቃል ኪዳን ከዚያም የቆየ ታሪክ አለው። ይህ ቃል ኪዳን ከሆብስ በተቃራኒ በእውነተኛው ሉአላዊ የሰማይና ምድር ፈጣሪ ተነሳሽነት ያገኘና የታወጀ ነው። ደግሞም ምንም እንኳ የሁብስ ቃል ኪዳን መነሾ ፍርሃት ብቻ ቢሆንም፤ የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን መነሾ ግን ለወደቀው ዘር ያለው ፍቅር፣ ወደ መስቀሉ የመራው ፍቅር ነበር።

በመሆኑም፤ ክርስቶስ ካደረገልን ነገር የተነሣ ለእግዚአብሔር የፍቅር ምላሽ እንሰጣለን። በሆብስ ቃል ኪዳን--ተገዢው ሕዝብ ለገዢው ሉአላዊ አካል ራሱን መስጠት እንዳለበት ሁሉ፤ እኛም ኃጢአተኛ መንገዳችንን፣ ፍርሐታችንን፣ ትክክል ከሆነውና ካልሆነው ጋር የተጠላለፉ አስተሳሰቦቻችንንና ምኞቶቻችንን አሳልፈን እናስረክባለን። ይህንን የምናደርገው በምላሹ አንድ ነገር ለማግኘት ሳይሆን፤ ነገር ግን እኛ ቀድሞውኑ ሉዓላዊው አካል ሊሰጠን የሚችለው ምርጥ ስጦታ ይኸውም የሱስ ክርስቶስን እና በእርሱ ብቻ የሚገኘውን ቤዛ ስለተሰጠን ነው።

ይህ ሁሉ እንዴት ይሠራል? ነገሩ የማለዋወጥ ያህል ቀላል ነው፡ ክርስቶስ ኃጢአታችን ወስዶ የእርሱን ጽድቅ ይሰጠናል። በዚህም በእርሱ አማካይነት--ልክ እንደ ራሱ እንደ እግዚአብሔር ጻድቅ ሆነን እንቆጠራለን። በዚህ መንገድ ኃጢአት የእኛ መገለጫ መሆኑ ስለሚያበቃ፤ ከእንግዲህ ከአምላካችን ነጥሎ ሊያኖረን አይችልም። ነፍሰ ገዳዮች፣ አመንዝራዎች፣ ትምክህተኞች፣ ሐሰተኞች፣ ሌቦች-እንደ ራሱ እግዚአብሔር ጻድቅ ሆነው ሊታዩ ይችላሉ። ይህ አስደናቂ ስጦታ፣ ይህ ጻድቅ ሆኖ መቆጠር የእነርሱ የሚሆነው በእምነት ነው ብቻ ነው። ይኸውም “ጽድቅ በእምነት” በሚባለው ሃረግ ይታወቃል።

ሆኖም ጉዳዩ በዚህ ብቻ አያበቃም። ነፍሰ ገዳዮች፣ አመንዝራዎች፣ ትምክህተኞች፣ ሐሰተኞች፣ ሌቦች--በክርስቶስ አማካይነት ከእግዚአብሔር ጋር ግንኙነት ወደ መመስረት መግባት ይችላሉ። ምክንያቱም የየሱስ ደም ይቅርታን ብቻ ሳይሆን ፈውስ እና ወደ ቀደመው ንጽህና መመለስንም ያቀዳጃል። እኛ በክርስቶስ አማካይነት ዳግም ተወልደናል፤ በዚህ ተሞክሮ አማካይነት እነሆ እግዚአብሔር በሥጋ የልቦቻችን ጽላት ላይ ሕጉን ይጽፋል። በዚህ የተነሣ ነፍሰ ገዳዮች፣ አመንዝራዎች፣ ትምክህተኞች፣ ሐሰተኞች፣ ሌቦች--ቀድሞ ያደርጓቸው የነበሩትን እነዚህን ነገሮች ከዚህ በኋላ አያደርጉም። ይህ በልብ ውስጥ የሚቀመጥ ሕግ የአማኞችን ሕይወት በትክክለኛው መንገድ ይቀርጻል። እግዚአብሔር በውስጣቸው ያስቀመጠውን ለመፈጸም ፍላጎት ስለሚያድርባቸው፤ ይኸው ፍላጎት ከመለኮታዊው ኃይል የተስፋ ቃል ጋር የተጣጣመ ይሆናል።

ከእግዚአብሔር ጋር በቃል ኪዳን ግንኙነት ውስጥ የመኖር መሠረታዊ ነጥብ ይኸው ነው።

በዚህ ሩብ ዓመት የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ምን እንደሆነ፣ ምን እንደሚሰጥ እንዲሁም ምን እንደሚጠይቅ በጥልቀት እንመለከታለን። ምንም እንኳ ትምህርቶቹ ብዛት ካላቸው ምንጮች የተውጣጡ ቢሆንም፤ በአብዛኛው በሟቹ ዶ/ር ገርሀርድ ሀሰል ሥራዎች ላይ የተመረኮዘ ነው። የቃል ኪዳኑ ተስፋዎች በተገለጡበት አምላካዊው ቃል ላይ የነበራቸው ግንዛቤ--ብርታት፣ ተስፋ እና ማስተዋል ይሰጣል። ምናልባት ቶማስ ሆብስ ፈጽሞ ያልተማሩት፣ ከዚህ የምናገኘው ትምህርት ይኖራል፡ “በፍቅር ፍርሀት የለም፤ ፍጹም ፍቅር ግን ፍርሀትን አውጥቶ ይጥላል” (1ዮሐ. 4፡ 18)።

ገርሀርድ ኤፍ. ሀሰል (ፒኤችዲ፡ ቫንደርቢልት ዩኒቨርሲቲ) በአንድሪውስ ዩኒቨርሲቲ የብሉይ ኪዳን እና የመጽሐፍ ቅዱስ ሥነ መለኮት ፕሮፌሰር ነበሩ። በጎርጎሮሳውያኑ ከ1981-88 የትህርት ቤቱ ዲን ሆነው ያገለገሉ ሲሆን ለ27 ዓመታት ደግሞ የ ቲኤችዲ/ ፒኤችዲ ፕሮግራም ዳይሬክቶር ሆነው አገልግለዋል።