የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ኢሳ. 9:1–5፣ ኢሳ. 9:6-7፣ ኢሳ. 9:8–10:34፣ ኢሳ. 11፣ ኢሳ. 12:1–6።
የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ፡- “ሕፃን ተወልዶልናልና፤ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናል፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል። ስሙም፣ ድንቅ መካር፣ ኀያል አምላክ፣ የዘላለም አባት፣ የሰላም ልዑል ይባላል።” (ኢሳ. 9፡6)።
የ
መጀመሪያው አቶሚክ ቦንብ ሲፈጠር ሥራውን በበላይነት ይቆጣጠሩ የነበሩት
ዶክተር ሮበርት ኦፕንሄይመር በዩናይትድ ስቴትስ ኮንግረስ ኮሚቴ ፊት ቀርበው
ነበር። ለጦር መሣሪያው ደህንነት የሚያስፈልግ አንዳች ነገር እንዳለ ሲጠየቁ፡ ታላቁ
የፊዚክስ ሊቅ ‘በእርግጥ አለ’
“ይኸውም-“ዶክተሩ የሚሉትን ለመስማት በጸጥታ እየተጠባበቀ ወዳለው ታዳሚ ከተመለከቱ
በኋላ፣ ለስለስ ባለ ድምፅ፡ ‘ሰላም ነው’ ሲሉ መለሱ”—Compiled by Paul Lee
Tan, Encyclopedia of 7,700 Illustrations: Signs of the Times (Rockville,
Md.: Assurance Publishers, 1985), p. 989.
ሰላም ለሰብዓዊው ዘር የማይጨበጥ ሕልም ነው። የዓለም ታሪክ መጻፍ ከጀመረበት
ጊዜ አንስቶ ዓለም ሙሉ በሙሉ ሰላም የሆነችበት ዘመን 8 ከመቶ ብቻ ነው።
በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ቢያንስ ስምንት ሺህ ስምምነቶች ፈርሰዋል (Paul Lee
Tan, p. 987, adapted)። የጦርነቶች ሁሉ ማክተሚያ ይሆናል ተብሎ የታሰበው
የመጀመሪያው ዓለም ጦርነት ካበቃ በኋላ በነበረው ግማሽ ምዕተ ዓመት ውስጥ
ለእያንዳንዱ የጦርነት ዓመት ለሁለት ደቂቃ ብቻ የዘለቀ ሰላም ነበር።
የድማሚት ፈጣሪ የሆነው አልፍሬድ ኖቤል ለሰላም ከፍተኛ አስተዋፅኦ ላበረከቱ
ግለሰቦች ሽልማት የሚሰጥ ድርጅት በጎርጎሮሳውያኑ 1895 ላይ አቋቋመ (Paul
Lee Tan, p. 988, adapted)። ሆኖም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እንደሚስተዋለው
አንዳንድ የኖቤል ሰላም ሽልማት አሸናፊዎች በኃይል ግጭት ውስጥ ተሳታፊ የነበሩም
ናቸው።
በዚህ ሣምንት እውነተኛ እና ዘላለማዊ ሰላም ሊያመጣ ስለሚችለው ብቸኛው አካል
እናጠናለን።
ኢሳ. 9፡1 የሚጀምርበትን (ነገር ግን) ቃል፤ ተከትሎት ከሚመጣው ሀሳብ ጋር ልዩነት መኖሩን አመላካች የሆነው ለምንድን ነው?
ፊታቸውን ከእውነተኛው አምላክ ሰውረው ጥንቆላና አስማት ላይ የሚያደርጉ
ሰዎች ምን ዓይነት ተስፋ አስቆራጭ ሁናቴ ውስጥ ሊወድቁ እንደሚችሉ ኢሳ. 8፡
21-22 ይገልጻል። የሚያዩት ሁሉ “ጭንቀት፣ ጨለማና የሚያስፈራም ጭጋግ ብቻ
ነው፤ ወደ ድቅድቅ ጨለማም ይጣላሉ” (ኢሳ. 8፡22)። በተቃራኒው ጊዜው ሲደርስ
“ተጨንቀው የነበሩ ከእንግዲህ ተስፋ ቢስ አይሆኑም” (ኢሳ. 9፡1)። የገሊላ ሕዝብ
በዓይነቱ ልዩ በረከት የሆነውን “ታላቅ ብርሃን” (ኢሳ. 9፡2) በተለይ እንደሚቀበል
ሆኖ ተጠቅሷል። እግዚአብሔር “የተጨቆኑበትን ዘንግ” (ኢሳ. 9፡1) ስለሚሰብር
ሕዝቡ ሐሴት ያደርጋል።
የገሊላ ሐይቅ አካባቢ በጥቅሱ የቀረበበት ምክንያት ስፍራው የእስራኤል እርስት
አካል ሆነው ከተያዙ ቀደምት ግዛቶች አንዱ በመሆኑ ነው። አካዝ ለ ቴልጌልቴልፌልሶር 3ኛ ያቀረበውን የድረስልኝ ልመና ተከትሎ ገሊላን እና ሰሜናዊ እስራኤል፣
ዮርዳኖስ አካባቢን በቁጥጥሩ ስር በማዋል ሕዝቡን ማርኮ ወሰደ። ግዛቶቹንም የአሦር
አውራጃ አካል አደረገ (2ነገሥ. 15፡29)። ስለዚህ በመጀመሪያ ድል ሆኖ የሚያዘው፤
ቀድሞ ነጻነቱን እንደሚያገኝ የኢሳይያስ መልእክት ያመለክታል።
እግዚአብሔር ሕዝቡን ለማዳን ማንን ይጠቀማል? ኢሳ. 9: 6-7
የኢሳይያስ 9፡1-5 ትንቢት መቼ እና እንዴት ተፈጸመ? ማቴ. 4፡12-25
የሱስ የእግዚአብሔርን መንግሥት የምሥራች ቃል እያወጀ፣ ሕዝቡን እየፈወሰና
ከአጋንንት ባዕድ አምልኮ እስራት እየፈታ አገልግሎቱን በገሊላ አውራጃ የጀመረው
በአጋጣሚ አይደለም (ማቴ. 4፡24)።
መጽሐፍ ቅዱስ በብሉይ ኪዳን ዘመን የተከናወኑ ክስተቶችን ወስዶ፤ ወደፊት በአዲስ
ኪዳን ገቢራዊ በሚሆኑ ሁነቶች ላይ እንዴት እንደሚጠቀም የሚያሳይ ፍጹም የሆነ
ምሳሌ በዚህ ስፍራ እንመለከታለን። የሱስ በማቴ. 24 መልእክቱ በ70 ዓ.ም. ላይ
የሚደርሰውን የየሩሳሌም ጥፋት ከዓለም ፍጻሜ ጋር አዋህዶ እንዳቀረበው ሁሉ፤
ጌታ የአንድ ዘመን ክስተት ገጽታ ከሌላው ጋር ሕብር እንዲፈጥር ያደርጋል።
አንድ ሰው--የሱስ ከምን እንዳዳኖት ቢጠይቆት መልስዎ ምን ይሆናል?
ክርስቶስ በሕይወትዎ ስላለው ኃይል ምን ዓይነት የግል ምስክርነት
መስጠት ይችላሉ?
ከአማኑኤል እና ማኸር-ሻላል-ሃሽ- ባዝ ቀጥሎ በኢሳይያስ መጽሐፍ የተመለከተው የሦስተኛው ህፃን መወለድ በዚህ ስፍራ ተመልክቷል። ሕፃኑን አስመልክቶ በእነዚህ ቁጥሮች ምን የተለየ ነገር ቀርቧል? ኢሳ. 9:6-7
ይህ አዳኝ--እርሱን በተለያዩ መንገዶች የሚገልጹ ብዙ ስሞች/ ቅጽል ስሞች
እንዳሉት ልብ ይሏል። በጥንታዊው ቅርብ ምሥራቅ የነበሩ ነገሥታት እና አማልክት
ታላቅነታቸውን በሚያሳዩ የተለያዩ ስሞች መጠራታቸው የተለመደ ነበር።
መለኮታዊው የጌታ መልአክ “ድንቅ” (መሳ. 13፡18) ብሎ ስሙን ለሳምሶን አባት
እንደ ገለጸለት ሁሉ--“ድንቅ” የሆነው እርሱ ከማኑሄ መሠዊያ ወደ ሰማይ በወጣው
የእሳት ነበልባል ውስጥ ዐረገ (መሳ. 13፡20/ ስሙ ተመሳሳይ የዕብራይስጥ ስርወቃል
ይዟል/) በዚህም ከአንድ ሺ ዓመታት በላይ ከሆኑ ዘመናት በኋላ ወደዚያ ለራሱ
ወደቀረበ መሥዋዕት ሲያመላክት ይታያል።
መለኮታዊ (“ኃያል አምላክ”) በሚል የተጠራው እርሱ ዘላለማዊ ፈጣሪ (“የዘላለም
አባት” ነው--ሉቃ. 3፡37፡ “…የአዳም ልጅ፤ የእግዚአብሔር ልጅ”)።
እርሱ የዳዊት ሥርወ መንግሥት ንጉሥ ነው። የሰላም መንግሥቱ ዘላለማዊ ይሆናል።
ከእነዚህ ከቀረቡት ባህሪያት አኳያ ይህ ልጅ ማን ሊሆን ይችላል?
(ሉቃ. 2፡8-14)
አንዳንዶች ከንጉሥ ሕዝቅያስ ጋር ሊያገናኙት ቢሞክሩም፤ ነገር ግን ይህ እርሱን
አስመልክቶ የተሰጠ መግለጫ ማንኛውም ሰብዓዊ ፍጡር ሊኖረው ከሚችል ስብዕና
የላቀ ነው። አንድ ሰው ብቻ ለዚህ ገጣሚ ሲሆን፤ እርሱም እኛን ሊያድነንና ሰላም
ሊሰጠን የተወለደልን የመለኮታዊው ፈጣሪ እግዚአብሔር አምላክ ልጅ የሱስ
ክርስቶስ ነው (ዮሐ. 1፡1-3፣ 14፣ ቆለ. 1:5–17፣ ቆለ. 2:9፣ ዕብ. 1:2)። ሥልጣን
ሁሉ በሰማይና ምድር የተሰጠው እርሱ ሁል ጊዜ ከእኛ ጋር ነው (ማቴ. 28፡1820)። መለኮታዊ ባህሪውን ትቶ እንደ እኛ የተፈተነ በድካማችን የሚራራልን “ህፃን
ተወልዶልናልና” (ዕብ. 4፡15)።
“ክርስቶስ ወደ ዓለማችን ሲመጣ--ከተወለደበት ግርግም እስከ ቀራኒዮ የነበረውን
ግስጋሴ ለመግታት ሰይጣን ያልሸረበው ሴራ፣ ያልፈነቀለው ድንጋይ አልነበረም።
ምን ማለት እንደሆነ እርሱ ራሱ ፈጽሞ የማይገባውንና ስለ ሌሎች መሥዋዕትነት
ከፍሎ የማያውቀው ሰይጣን፤ መላእክት ራስን የመካድ ህይወት እንዲመሩ ተደርገዋል
ሲል በእግዚአብሔር ላይ ክስ ያቀርብ ነበር።
ሰይጣን በሰማይ በእግዚአብሔር
ላይ ይሰነዝር የነበረው ክስ ይህ ነበር። ክፉው ከሰማይ ከተባረረም በኋላ እርሱ
ራሱ የማይሰጠውን--ጥንቃቄ የሚፈልግ አገልግሎት አላቀረበም እያለ በጌታ ላይ
ጣቱን መቀሰሩንም ሆነ ክስ ማቅረቡን አጥብቆ ገፋበት። ክርስቶስ የእነዚህን ክሶች
ሐሰተኝነት ለማሳየትና አብን ለመግለጥ ወደ ዓለም መጣ።”—Ellen G. White,
Selected Messages, bk. 1, pp. 406, 407.
መልእክቱ ስለ እግዚአብሔር ባሕርይ ምን ይነግረናል?
በጨለማ ይኖሩ ለነበሩ ሰዎች ደኅንነት እንደሚመጣ የሚተነብየው ይህ--በኢሳ.
9፡1-5 የቀረበ ክፍል፤ በጥንቆላ ስር የወደቁትንና የወታደራዊ ምርኮ ጭቆና ገፈት
ቀማሾችንና በጭንቀት የሚገኙ ሰዎችን ሁኔታ ጥሩ አድርጎ ያብራራል፡ “ምድያም
ድል በተመታ ጊዜ እንደሆነው… የተጨቆኑበትንም ዘንግ ሰብረህላቸዋል”
ከዚህ በላይ በቀረቡት ጽሑፎች የተመለከተውን የእግዚአብሔር ህዝብ ሥቃይ
ያንብቡ። በዘሌዋ. 26፡14-9 የቀረቡትን እርግማኖች ያስተያዩ። እግዚአብሔር
በአንዴ ሳይሆን ደረጃ በደረጃ የቀጣቸው ለምን ነበር? ይህ ስለ እርሱ ባህሪ እና ግብ
ምን ይጠቁማል?
እግዚአብሔር ህዝቡን ሊያጠፋ ቢፈልግ ኖሮ ወዲያውኑ ለአሦራውያን አሳልፎ
ይሰጣቸው ነበር። “ነገር ግን ማንም እንዳይጠፋ ፈልጎ፣ ሁሉ ለንስሐ እንዲበቃ”
ስለ እነርሱ ታገሰ (2ጴጥ. 3፡9)። በ “መሳፍንት” ዘመን እንደሆነው ሁሉ የይሁዳ
እና የእስራኤል ሕዝብ ምን እያደረጉ እንደነበር እንዲገነዘቡና የተሻለ ምርጫ
የማድረግ ዕድል እንዲኖራቸው ለማስቻል፤ በጅልነት ያደረጓቸውን ከንቱ ውጤቶች
ይመለከቱ ዘንድ እግዚአብሔር ፈቀደ። በክፉ ድርጊቶቻቸው ጸንተው፤ ልቦቻቸውን
እግዚአብሔር በላከላቸው መልእክተኞቹና በእርሱ ላይ ሲያደነድኑ ጥበቃውን እያነሳ
መጣ። እነርሱም በዐመጻቸው ገፉበት። ይህ አዙሪት እግዚአብሔር ምንም ማድረግ
የማይችልበት ደረጃ ላይ እንኪደርስ ተደጋግሞ ቀጠለ።
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ኢሳ. 9፡8 እስከ 10፡2። ሕዝቡ በደለኛ የሆነው
በየትኞቹ ኃጢአቶች ነበር? በማን ላይ ፈጸሟቸው? ከመካከላቸው
ጥፋተኛው ማን ነበር?
በዚህ ስፍራ የምንመለከተው ሀሳብ፤ እንደ ቀሪው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ሁሉ
የመምረጥ ነፃነትን ተጨባጭ እውነታ ያሳያል። እግዚአብሔር ሰውን ነጻ የመምረጥ
መብት አጎናጽፎ የፈጠረ ሲሆን (ይህን ማድረግ ነበረበት፤ ያለ በለዚያ በእውነት
ሊወዱት አይችሉም ነበር)፤ ነፃነት ስህተት የመሥራት ምርጫንም ያካትታል። ምንም
እንኳን እግዚአብሔር ፍቅሩንና ባህሪውን እየገለጸ ወደ እርሱ ሊስበን በተደጋጋሚ
ቢሻም፤ ከእርሱ ማፈግፈግ ወዴት ሊያመራን እንደሚችል ግንዛቤ እንድናገኝ ሊረዳን
በማሰብ--ህመም፣ ሥቃይ፣ ፍርሐት፣ በጥብጥና የመሳሰሉት የተሳሳቱ ውሳኔዎቻችንን
ፍሬ እንድንጋፈጥ ይፈቅዳል። ይህም ሆኖ፤ እነዚህ ነገሮች ሰዎች የታሰበውን ያህል
ኃጢአትን ትተው ወደ ጌታ እንዲመጡ አያደርጓቸውም። የመምረጥ ነፃነት አስገራሚ
መብት ነው። ይህ ባይኖረን ሰው መሆን ባልቻልን ነበር። ይህን በተሳሳተ መንገድ
ለሚጠቀሙ ወዮላቸው!
እግዚአብሔር እርስዎን ከተሳሳተ መንገድ ለመመለስ ሲል ምን ዓይነት
መከራ በህይወትዎ እንዲደርስ ፈቀደ?
“ከእሴይ ግንድ” የሚወጣው “ቅርንጫፍ” (ኢሳ. 11፡1) ማን ነው? (ዘካ. 3፡ 8፣ 6፡12)። በኢሳ. 10፡33-34 የተመለከተው ምናባዊ የሚገነደስ ዛፍ በኢሳ. 11፡1 ቀርቦ እንመለከታለን። ይህ ደግሞ--የ “እሴይ ግንድ” የሆነው የዳዊት ሥርዎ መንግሥት (የእሴይ ልጅ) ኃይሉን ያጣል (ዳን. 4፡10-17፣ 20-26) የሚለውን ጽንሰ ሀሳብ ይወክላል። ነገር ግን ከዚያ ያበቃለት ከሚመስል ግንድ ላይ “ቅርንጫፍ” ይወጣል። ይኸውም ከዳዊት ዘር የሆነ ገዢ ነው። አዲሱ ዳዊታዊ ገዥ “የእሴይ ሥር” ተብሎ የተጠራው ለምንድነው (ኢሳ. 11፡10)? ይህ ምን ዓይነት ስሜት ይሰጣል? ራእ. 22 16። መግለጫው የሚገጥመው “የዳዊት ሥርና ዘር” (ራእ. 22፡16) ለሆነው ለየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው። ክርስቶስ “የእግዚአብሔር ልጅ” (ሉቃ. 3፡38) ከሆነው የአዳም ዘር፣ ይኸውም ከዳዊት የትውልድ ሀረግ (ሉቃ. 3፡23-31) መምጣቱ፤ ክርስቶስ እርሱን እንደ ፈጠረው ያሳያል (ዮሐ. 1፡1-3፣14)። ስለዚህ ክርስቶስ የዳዊት አያቶችም ሆነ የልጅ ልጆች ዝርያ ነበር! አዲሱ ዳዊታዊ ገዥ ኃጢአት እና ክህደት ያስከተላቸውን መጥፎ ውጤቶች በምን ዓይነት መንገዶች ይለውጣል? (ኢሳ. 11)
በጥልቅ የሚያስበውና ከጌታ ጋር ተስማምቶ የሚሠራው እርሱ--ቅን ፍርድ ይሰጣል፣
ክፉዎችን ይቀጣል፣ ሰላምንም ያመጣል። ሥልጣኑን ሲይዝ ታማኞቹን የእስራኤልና
ይሁዳ ትሩፋን ወደ ቀደመው በመመለስ እንደፊቱ በአንድ ያዋህዳቸዋል (አሳ. 10፡
20-22)። ፍልስጥኤሞችንና ሌሎች ሕዝቦችን ድል እንዳደረገው እንደ ዳዊት ዘመን
ጠንካራና አንድነት ያለው ንግሥና ይኖራል። ነገር ግን አዲሱ ገዥ ሰላምን ወደ
ቀደመ ንጽሕናው የሚመልሰው ከራሱ ከፍጥረት መሰረታዊ ሁኔታ አኳያ እንደ
መሆኑ ከዳዊትም የበረታ ይሆናል። አድነው የሚኖሩ አውሬዎች ከእንግዲህ ሥጋ
በል ስለማይሆኑ ከቀድሞ ታዳኞች ጋር በሰላምና በጸጥታ ይኖራሉ (ኢሳ. 11፡6-9)።
ኢሳያስ 11 እየተናገረ ያለው ስለ ክርስቶስ የመጀመሪያ ምጽአት፣ ስለ
ሁለተኛው ወይስ ስለ ሁለቱም ነው? ትንቢቶቹን በመመርመር የትኞቹ
ጥቅሶች ስለ የትኛው ምጽአት እንደሚናገሩ ምልክት ያድርጉ።
በኢሳ. 11 ሁለቱም የየሱስ ምጽአቶች በአንድ ምስል ቀርበዋል። እነዚህ ሁለት ክፍሎች
እንደ አውሮፕላን ሁለት ጎኖች በአንድ ላይ የተሳሰሩ ናቸው። የደኅንነት እቅድ ፍጻሜ
ያገኝ ዘንድ ሁለቱም ምጽአቶች ገቢራዊ መሆን ይኖርባቸዋል። ፍጻሜ ያገኘው
የመጀመረያው እና የክርስቲያኖች ተስፋ ፍጻሜ የሆነው፣ እየተጠባበቅን የምንገኘው
ዳግም ምጽአት።
ስለ ዳግም ምጽአቱ እንዲህ ያለ ዋስትና የሚሰጠን ክርስቶስ በመጀመሪያ
ምጽአቱ ምን አከናወነ? የመጀመሪያው ምጽአት ለሁለተኛው መንስኤ
መሆን ካልቻለ ፋይዳው ምንድን ነው?
ኢሳ. 12 ስለ እግዚአብሔር ምኅረት እና ብርቱ አጽናኝነት የቀረበ አጭር የውዳሴ መዝሙር ነው። ይህ ድነት ካገኙ ትሩፋን ከአንዱ አፍ የወጣ መዝሙር፤ ከግብፅ ለወጡ ዕብራውያን የተሰጠውን የደኅንነት ተስፋ በንጽጽር ያቀርባል (ኢሳ. 11፡16)። መዝሙሩ እስራኤላውያን በቀይ ባሕር ከፈርዖን ሰራዊት በዳኑ ጊዜ ከተዜመው የሙሴ እና እስራኤላውያን መዝሙር ጋር ተመሳሳይ ነው (ዘፀ. 15)። ይህን በኢሳ. 12 የቀረበ መዝሙር ከራእ. 15፡2-4 የሙሴ እና የበጉ መዝሙር ጋር ያነጻጽሩ። ሁለቱም ዝማሬዎች እግዚአብሔርን የሚያወድሱበት ምክንያት ምንድን ነው?
ኢሳ. 12፡2 የሚመጣውን አዳኝ የሱስ ለይቶ ወደ ማሳየት የተቃረበ ይመስላል። “እነሆ
እግዚአብሔር ድነቴ ነው” እና “ድነቴም ሆኖአል” ይላል። የሱስ የተሰኘው ስያሜ
“ጌታ ድነት ነው” (ማቴ. 1፡21) የሚል ፍቺ አለው።
በየሱስ ስም ውስጥ የሚገኘው ጌታ ድነት ነው--ትርጉሙ ምንድን ነው?
ጌታ የሚያድን ብቻ ሳይሆን (ኢሳ. 12፡2) እርሱ ራሱ ድነት ነው። የእስራኤል ቅዱስ
በመካከላችን መገኘት (ኢሳ. 12፡6) ለእኛ ሁሉም ነገር ነው። እግዚአብሔር ከእኛ
ጋር! የሆነው የሱስ ታምራት ብቻ አላደረገም፤ ነገር ግን “ሥጋ ሆነ፤ በመካከላችንም
አደረ” (ዮሐ. 1፡14)። ኃጢአታችንን በመስቀል ላይ መሸከም ብቻ ሳይሆን፤ ስለ እኛ
ኃጢአት ሆነ (2ቆሮ. 5፡21)። ሰላም የሚያመጣ ብቻ ሳይሆን እርሱ ሰላማችን ነው
(ኤፌ. 5፡14)
“የእሴይ ሥር ለሕዝቦች ምልክት ሆኖ ይቆማል” (ኢሳ. 11፡10) የሚለው አባባል ብዙም
ሊያስገርም አይችልም። እርሱ ከፍ ብሎ መስቀል ላይ በተሰቀለ ጊዜ እነሆ ሰውን ሁሉ
ወደ ራሱ ሳበ! (ዮሐ. 12፡32-33) የተረፉት--ለእኛ የተወለደው ሕፃን “የሰላም ልዑል”
(ኢሳ. 9፡6) ወደ ሆነው “ወደ ኃያሉ አምላክ ይመለሳሉ” (ኢሳ. 10፡21)።
የሱስ ድነታችን ነው በሚለው ጽንሰ ሀሳብ ዙሪያ በቂ ምልከታ
ያድርጉ። ጥቅሱን ያንብቡ፡ ሮሜ 3፡24። ጥቅሱ መቤዠት የሚገኘው
በየሱስ መሆኑን ይናገራል።
ቤዛነት በእርሱ የሆነ ነገር ከመሆኑ የተነሳ-በእግዚአብሔር ጸጋና ምህረት በኩል፤ በቤዛነቱ የእርሱ ዘላለማዊ
ተካፋዮች መሆን እንድንችል ጭምር ነው። በሌላ አነጋገር በእርሱ
ውስጥ የነበረው ድነት በሥራችን ሳይሆን በእምነት የእኛ መሆን
ይችላል። ምክንያቱም ማንኛውም በጎ ሥራችን እኛን ለመቤዠት በቂ
አይደለም። ክርስቶስ የሠራው--ለእኛ በእምነት የሚቆጠርልን ሥራ
ብቻ ድነት ሊያመጣልን ይችላል። በተለይ የገዛ ማንነትዎ ደካማነትና
የሥጋ ከንቱነት ሲያስጨንቅዎ፤ ይህ እውነት ተስፋና የድነት ዋስትና
የሚሰጥዎ እንዴት ነው?
“ሰብዓዊ ፍጡር የሆነ አባት ለልጁ ይራራል። የልጁን ፊት
ተመልክቶ በሕይወቱ ሊደርስ የሚችለውን አደጋ ሲያስታውስ ይሰቀጥጠዋል።
ውድ ልጁን ከሰይጣን ኃይል ለመከላከል፣ ከፈተናና ከአደጋ ሊጠብቀው ይወዳል።
ለልጆቻችን የሕይወት ጎዳና እንዲሰምርላቸው እግዚአብሔር አንድ ልጁን ከአስከፊ
ግጭትና አስፈሪ አደጋ ሁሉ ጋር እንዲጋፈጥ ላከው። ፍቅር ማለት ይህ ነውና፤ ሰማይ
ግሩም ይበል መሬትም ትደነቅ!” የዘመናት ምኞት፡ ገጽ 35።
“ለሰው ልጅ ድነት አስፈላጊ የሆኑትን መስፈርቶች ሁሉ ለማሟላት ፈቃደኛ የሆነው
ክርስቶስ ነበር። ታላቁን ሥራ እውን ለማድረግ አንድም መልአክ ወይም ሰው ብቁ
አልነበረም። በመሆኑም በዚህ ረገድ የሰው ልጅ ብቻውን ከፍ ማለት ነበረበት።
በመቤዠት ሂደት ማለፍ የሚችል ውሱን ያልሆነ ተፈጥሮ ባለቤት ብቻ ነበር።
ክርስቶስ የሰውን ተፈጥሮ በመውሰድ ታማኝ ካልሆነውና ከኃጢአተኛው ጋር ራሱን
በማስተሳሰር፣ የገዛ ራሱን ደም ለመስጠትና ነፍሱን ለኃጢአት መሥዋዕት ለማድረግ
ፈቀደ። በሰማያዊው ጉባዔ የሰው በደል ተለካ፣ የኃጢአት ቁጣ ተገመተ፤ ሆኖም
ለወደቀው ዘር ተስፋ ለማምጣት የሚያስችለውን ቅድመ ሁናቴ ራሱ ለማሟላት
ኃላፊነቱን እንደሚወስድ ውሳኔውን አስታወቀ።”—Ellen G. White, The Signs
of the Times, March 5, 1896.
1.ጌታ ሁለቱንም የክርስቶስ ምጽአቶች በአንድ ሥዕል ማቅረቡን
በኢሳ. 11 ተመልክተናል። አንዳንድ አይሁዶች በክርስቶስ ዳግም
ምጽአት ወቅት ገቢራዊ የሚሆኑትን ክስተቶች በመጀመሪያ ምጽአቱ
እንደሚፈጽም አድርገው መጠባበቃቸው፤ እርሱን ለምን በመጀመሪያ
ምጽአቱ እንዳልተቀበሉት በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ለማስረዳት ሊረዳ
ይችላል። በቅርቡ ገቢራዊ የሚሆነውን የክርስቶስ መገለጥ ትክክለኛ
ባህሪ መረዳታችን ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ይህ ምን ይነግረናል?
ለምሳሌ በዳግም ምጽአቱ ዙሪያ የሚቀርቡ የተሳሳቱ አመለካከቶች
ሰዎችን ለታላቁ የመጨረሻው ጊዜ ማታለያ እንዴት ይዳርጋሉ? (See
Ellen G. White, The Great Controversy, chapter 39.)
ማጠቃለያ፡ እግዚአብሔር “የጌታ ድነት” የተሰኘ ፍቺ ያለውን ስያሜ
(በኢሳይያስ ዘመን) በመስጠት--ሕዝቡ በፈጸመው ብሔራዊ ክህደት
ምክንያት ከሚደርስባቸው ጭቆና ጠብቆ ድነት እንደሚሰጣቸው ቃል ገባ።