የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ኢሳ. 7:14– 16፣ ኢሳ. 7:17–25፣ ኢሳ. 8:1–10፣ ኢሳ. 8:11–15፣ ኢሳ. 8:16–22።
የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ፡- “ፊቱን ከያዕቆብ ቤት የሸሸገውን እግዚአብሔርን እጠብቃለሁ፤ እርሱንም ተስፋ አደርጋለሁ”(ኢሳ. 8:17)
በ
ኒው ዮርክ ከተማ ሃርለም የመኖሪያ ሰፈር በአንድ መኖሪያ ሕንፃ ላይ እሳት
ተነስቶ ነበር። ዙሪያውን በሚፋጅ የእሳት ወላፈን መሃል አንዲት ዓይነ ስውር
ልጃገረድ አራተኛ ፎቅ መስኮት ጥጋት ትታያለች። በስፍራው የተገኙት የእሳት አደጋ
ተከላካይ ሠራተኞች ባለ መሰላሉን የጭነት መኪና ከሕንጻው አስጠግተው ማቆምም
ሆነ ይህች ማየት የማትችል ልጃገረድ በተዘረጋው መረብ ላይ እንድትዘል ማድረግ
ባለመቻላቸው ተስፋ ቆርጠዋል።
“በመጨረሻ አባቷ በስፍራው ደረሰና ከታች ለእርሷ ደኅንነት የተወጠረ መረብ
መኖሩን በመንገር ቁልቁል እንድትዘል በድምጽ ማጉያ ነገራት። ይህች ልጅ የአባቷን
ትእዛዝ ተቀብላ ከአራተኛ ፎቅ ቁልቀል ተምዘግዝጋ ስትወርድ--የአጥንት ስብራትም
ሆነ ወለምታ አልገጠማትም ነበር። አባቷን ሙሉ በሙሉ ታምን የነበረችው ይህች
ልጅ፤ ድምፁን በሰማች ጊዜ እርሱ ምርጥ አማራጭ ብሎ ያመነበትን አድርጊ ሲላት
አደረገች።”—Edited by Michael P. Green, 1500 Illustrations for Biblical
Preaching, p. 135.
በተመሳሳይ እግዚአብሔር ለልጆቹ የተሻለውን እንደሚመኝ የሚያሳዩ ጠንካራ
መረጃዎችን፤ ገና በመጀመሪያ ኮለል ብሎ በሚወርድ ድምፀት ሲሰጣቸው
አልተቀበሉም። ስለዚህ በሚያገሳ አንበሳና ነጎድጓዳማ ድምፀት መናገሩ የግድ
ይሆናል!
እኛ ዛሬ ከእነርሱ ስህተት ምን እንማራለን?
ከአካዝ የምርጫ አጣብቂኝ ጋር ተያይዞ ህፃኑ አማኑኤል እንደ ምልክት መቅረቡ በኢሳ. ምዕ. 7 ቁ.14-16--ተመልክቷል። ህፃኑ ክፉውንና መልካሙን መምረጥ ከመቻሉ አስቀድሞ “የፈራሃቸው የሁለቱ ነገሥታት ምድር ባድማ ይሆናል” (ኢሳ. 7፡16)። የሶርያንና ሰሜን እስራኤልን ምድር እና ነገሥታት የሚመለከተው (ኢሳ. 7፡ 1፣2፣4-9) ይህ ትንቢት ኃይላቸውን በቅርቡ እንደሚያጠፋ እግዚአብሔር የገባውን ቃል ይደግማል። ሕፃኑ “ ‘ቅቤና ማር’ ” መብላት እንደሚኖርበት ኢሳይያያስ የጠቀሰው ለምንድን ነው--ኢሳ. 7:15?
የይሁዳ ሰብሎች እና እርሻዎች በአሦራውያን ይጠፋሉ (ኢሳ. 7፡23-25)። ስለዚህ
የብሉይ ኪዳኑን አማኑኤል (ማንም ሊሆን ቢችልም፡ ኢሳ. 7፡14-15) እርሱን ጨምሮ
ወደ ተለመደው ዓይነት የአርብቶ አደር አመጋገብ ይመለሳሉ (ኢሳ. 7፡21-22)።
ቢደኸዩም፤ በሕይወት ለመኖር የሚያስችል በቂ ነገር ይኖራቸዋል።
ስለ ሶርያና ሰሜናዊ እስራኤል የተነገረው ትንቢት የተፈጸመው መቼ
ነው? 2ነገሥ. 15:29-30፣ 2ነገሥ. 16:7–9፣ 1ዜና 5:6፣ 26።
ይህ የኢሳይያስ ትንቢት የተሰጠው ከክርስቶስ ልደት በፊት 734 ላይ ነበር።
ቴልጌልቴል-ፌልሶር 3ኛ--አካዝ ላቀረበው ጉቦ ምላሽ በመስጠት ማድረግ የነበረበትን
አደረገ። ሰሜናዊውን ጥምረት አፍርሶ ገሊላን እና የሰሜናዊውን እስራኤል ዮርዳኖስ
አካላይ ግዛቶችን ድል ካደረገ በኋላ፤ የተወሰነውን ሕዝብ ከግዛቱ አባሮ ግዛቶቹን
የአሦራውያን አውራጃዎች አካል አደረገ (734-733)። ቀሪው የእስራኤል ክፍል
መትረፍ የቻለው ሆሴዕ ንጉሥ ፔካን ከገደለ በኋላ እጅ ሰጥቶ ግብር በከፈለ ጊዜ
ነበር። በ733 እና 732 ቴልጌልቴል-ፌልሶር የሶርያን መዲና ደማስቆ ድል አድርጎ
ተቆጣጠረ። ከዚያም ሶርያን የአሦራውያን አውራጃ አደረገ። የኢሳይያስ ትንቢት
በተነገረ በሁለት ዓመት ውስጥ፤ በ732 በአካዝ ላይ ዛቻና ማስፈራሪያ ሲያደርሱ
የነበሩ ሁለቱ ነገሥታት--ሶርያ እና እስራኤል በዚህ ሁኔታ ሙሉ በሙሉ ድል ሆኑ።
ከክርስቶስ ልደት በፊት 727 ላይ ቴልጌልቴል-ፌልሶር 3ኛ በ ሰልምናሶር 5ኛ ተተክቶ
ብዙም ሳይቆይ፤ የእስራኤሉ ንጉሥ ሆሴዕ በአሦር ላይ በማመጽ በራሱ ላይ ፖለቲካዊ
ሞት አስከተለ። አሦራውያን ዋና ከተማዋን ሰማሪያን በ722 ተቆጣጠሩ። በሺህ
የሚቆጠሩ እስራኤላውያንን ወደ ሜሶፖታሚያ እና ሜዶን ያባረሩ ሲሆን፤ እነዚህ
ሕዝቦች ውሎ አድሮ በአካባቢው ሕዝብ ተውጠው ማንነታውን እንዳጡ ይታመናል
(ኢሳ. 7፡8--በ65 ዓመት ውስጥ የኤፍሬም ሕዝብ ይበታተናል፤ ሕዝብ መሆኑም
ይቀራል።) በይሁዳ ጠላቶች ላይ የሚደርሰውን ጥፋት እግዚአብሔር አስቀድሞ
ተንብዮ ነበር።
ይህ መሆኑ ስለማይቀር በአሦር ላይ ምንም ዓይነት መመካት
እንደማያስፈልግ እግዚአብሔር ለአካዝ ሊነግረው የፈለገው ነጥብ ነበር።
እርስዎ ይህ ሁሉ ክስተት በተፈጸመበት ሰሜናዊው መንግሥት ውስጥ
ቢኖሩ ኖሮ፤ እምነት ማጣት ምን ያህል ቀላል ሊሆን እንደሚችል ያስቡ።
የነገዎቹ ጥፋቶች ሲደርሱ ጠንካሮች ሆነን ለመቀጠል፤ እምነታችንን
ጠብቀን ለመቆየት ዛሬ ምን ማድረግ አለብን? 1ጴጥ. 1፡13-25
ከላይ የቀረቡትን ጥቅሶች ያንብቡ። ጌታ በምድሪቱ ላይ ስለሚሆነው ነገር ምን አለ? ይህ መዘዝ ሊያስደንቀን የማይገባው ለምንድን ነው?
“በስህተት ጎዳና ላይ የነበረችው እስራኤል በታማኝነት ወደ እግዚአብሔር ትመለስ
ዘንድ ተደጋጋሚ ጥሪ ቀርቦላታል። በነቢያት ያላሰለሱ ልመናዎች ቀርበዋል። ሕዝቡ
በንስሐና ተሐድሶ እንዲመለስ ያቀረቧቸው ጽኑ ቃላት ለእግዚአብሔር ክብር ፍሬ
አፍርተው ነበር””—Ellen G. White, Prophets and Kings, p. 325.
የሶርያ እና እስራኤል መጥፋት የእምነት ሳይሆን የፍርሃት ሰው ለነበረው አካዝ
መልካም ዜና ነበር።
መጥፎው ዜና ደግሞ እርሱን ለመርዳት የመረጠው አጋር እና
“ጓደኛ” የነበረው አሦር፤ ከሶርያ እና ከእስራኤላውያኑ እጅግ በጣም የከፋ ጠላት
ሆኖ ብቅ ማለቱ ነበር። እግዚአብሔር እንደሚታደገው በነፃ ያቀረበለትን ስጦታ
የተቃወመው አካዝ፤ በቂ የሽንፈት ዋስትና አገኘ። አካዝ የቆመባት ምድር እንደ
ከዳችው አሁን የሚሰማው ከሆነ፤ ነገሮች እየባሱ ከመሄድ ውጪ ሌላ አማራጭ
የለም!
“በገዦች ተስፋ ከማድረግ ይልቅ፣ በእግዚአብሔር መታመን ይሻላል” (መዝ. 118፡
9)። ቴልጌልቴል-ፌልሶር 3ኛ በሰሜን የነበሩት አገራት በቁጥጥሩ ስር በማዋሉ
ረክቶና ይሁዳን አክብሮ ይቀመጣል ብሎ አካዝ እንዴት ተማመነ? የአሦር ንጉሥ ዜና
መዋዕልን ጨምሮ ሌሎች ዘገባዎች እንደሚያመላክቱት የአሦራውያኑ ኃያልነት ጥም
የማይረካ ነበር።
ጥቅሶቹን ያንበብቡ፡ 2ነገሥ. 16:10–18፣ 2ዜና 28:20–25። በአካዝ
ላይ ምን እየደረሰ ነበር? በዚህ ስፍራ የተገለጠው መንፈሳዊ መርኅ ምንድን
ነው? በዚህ ድርጊት መደነቅ የሌለብን ለምንድን ነው?
አካዝ በጌታ ላይ ከመታመን ይልቅ የአሦርን እርዳታ መጠየቁ ያስከተለው መዘዝ
ድምር ውጤት በ2ዜና 28፡20-23 ቀርቦአል።
ተፈጥሮአችን በምናየው፣ በሚሰማን፣ በምንቀምሰውና በምንዳስሰው
ዓለማዊ ነገር ላይ ለመታመን ያዘነብላል። ሆኖም እንደምናውቀው የዓለም
ነገሮች ጠፊ ናቸው። 2ቆሮ. 4፡18 ይመልከቱ። ጥቅሱ ምን እያለን ነው?
መልእክቱን በሕይወታችን ውስጥ እንዴት ተግባራዊ ማድረግ እንችላለን?
ካደረግን ምን ለውጥ ያመጣልናል?
ከኢሳይያስ ሁለተኛ ልጅ ጋር አብሮ ኳስ ስለ መጫወት ማሰብ ይችላሉ? “ማኸርሻላል-ሃሽ-ባዝ፤ እስቲ ኳሷን አቀብለኝ!” ማለት ቢችሉም በጣም የዘገየ ይሆናል። ነገር
ግን ከስሙም የረዘመው ደግሞ ፍቺው ነው፡ “ምርኮ በቶሎ ይሆናል፣ ብዝበዛው
ይፈጥናል” ወይም “ጉዳቱን አፍጥን፣ ብርበራውን አቻኩል”
የስሙ መልእክት በፍጥነት ከመቆጣጠር ጋር ግልጽ ተያያዥነት ቢኖረውም፤
ነገር ግን ማን-ማንን ነው ድል የሚያደርገው? (ኢሳ. 8፡4)።
በኢሳ. 8፡1-10 የቀረበው መልእክት ለምዕ. 7 ማጠናከሪያ ይሆናል። አንድ ህፃን
የተወሰነ የዕድገት ደረጃ ላይ ከመድረሱ አስቀድሞ የሶርያ እና ሰሜን እስራኤል ርዕሰ
ከተሞች በጦር ምርኮና ብዝበዛ ስር ይወድቃሉ። በተጨማሪ ይሁዳ በእግዚአብሔር
የቀረበላትን የማረጋገጫ መልእክት በመቃወሟ ከታላቁ የኤፍራጥስ ወንዝ በከፍተኛ
ጉልበት በሚወጣውና በየሩሳሌም ኮለል ብሎ በሚፈሰው፣ የሲሎ ወንዝ በተመሰለው
የአሦርያውያን ብርቱ ኃይል ስር ትወድቃለች።
አካዝ ወደ አሦር በመመለሱ ምክንያት ስለ ይሁዳ እንዲሁም ሰሜናዊ እስራኤል
የሚያወሱት የኢሳይያስ ልጆች ስም፡ “ምርኮ በቶሎ ይሆናል፣ ብዝበዛው ይፈጥናል”
ነገር ግን “ትሩፋን ይመለሳሉ” የሚል ነበር። አሁንም ቢሆን ተስፋ የነበረው ለምን
ነበር? ምንም እንኳን የአማኑኤል ምድር በአሦራውያን ቢጥለቀለቅም (ኢሳ. 8፡8)
አሁንም “እግዚአብሔር ከእኛ ጋር” የተሰኘው የተስፋ ቃል ነበራቸው (ኢሳ. 8፡
4)። እንደ እውነቱ ከሆነ አጠቃላዩን የኢሳይያስ መጽሐፍ ጭብጥ በዚህ ስፍራ
እንመለከታለን። በይሁዳ እና በሌሎች የእግዚአብሔር ጠላት ግዛቶች ላይ ፍርድ
ቢኖርም--እነርሱን ከወታደራዊ መአት፣ ሥቃይና ግዞት ውስጥ በማዳን ጌታ አብልጦ
ከታማኝ ትሩፋን ሕዝቦቹ ጋር ይሆናል፣ ወደ ምድራቸውም ይመልሳቸዋል።
ኢሳይያስ ሕጋዊውን የልጁን ስም እና ከሚስቱ (ነቢዪቱ) ጋር የነበረውን
የጋብቻ ግንኙነት ለምን ይነግረናል? (ኢሳ. 8፡1-3)።
ይህ ልጅ የሚገኝበት የዕድሜ ሁናቴ እንደ ምልክት አስፈላጊና ትርጉም ያለው ነበር።
አሦር ሶርያን እና እስራኤልን ድል የሚያደርገው በምልክትነት የቀረበው ሕፃኑ
አማኑኤል ተጸንሶ፣ ተወልዶና እማማ እና አባባ ብሎ መጥራት ከመቻሉ በፊት
በሚኖረው የዕድገት ደረጃ ነው (ኢሳ. 8፡4)። ኢሳይያስ የሕጻኑን ስም ከመጸነሱ
አስቀድሞ በመመዝገብ፤ ህፃኑን እና ስሙን በቀጣይ ክስተቶች ሊፈትን የሚችል
ትንቢት ይፋ አደረገ።
ምንም እንኳን እግዚአብሔር ሕዝቤ ብሎ የጠራቸው ወገኖች ተደጋጋሚ
ስህተቶች ቢሠሩም፤ ጌታ አሁንም እነርሱን ለማዳን ፈቃደኛ ነበር። በተለይ
በመንፈሳዊ ህይወታችን ላይ ውድቀት ሲደርስ፤ ይህን መርኅ ለየግላችን
መተግበር የምንችለው እንዴት ነው?
ፍራንክሊን ሩዝቬልት የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ሆነው በተመረጡበት በዓለ ሲመታቸው
ሥነ ስርዓት ላይ ባደረጉት የመጀመሪያ ንግግር፤ የአገሪቱ ምጣኔ ሐብት ላይ ከፍተኛ
ቀውስ ፈጥሮ በነበረው ታላቁ የኤኮኖሚ መቀዛቀዝ ተስፋ ቆርጦ የነበረውን ሕዝብ
እንዲህ ብለው ነበር፡ “ልንፈራ የሚገባው ብቸኛ ነገር ራሱን ፍርሀትን ነው” —U.S.
Capitol, Washington, D.C. (March 4, 1933) ኢሳይያስ ተስፋ ቆርጠው ለነበሩ
ሰዎች የሰጠው መልእክት “እግዚአብሔርን ራሱን የምንፈራው ከሆነ፤ በሌላ ነገር
መሸበር የለብንም”
ሕዝቡ በፈራው ነገር እርሱም መሸበር እንደሌለበት እግዚአብሔር ኢሳይያስን
አስጠንቅቆት ነበር (ኢሳ. 8፡12-13)። ይህ በእጅጉ ወሳኝ የመጽሐፍ ቅዱስ ጭብጥ
ነው። ለምሳሌ በራእ. 14፡6-12 ሦስት መላእክት ዓለማቀፋዊ መልእክት ያውጃሉ፡
በምዕራፍ 13 የተጠቀሰውን ምድራዊውን አውሬ ከመፍራትና ለእርሱ ክብር
ከመስጠት ይልቅ--እግዚአብሔርን ፍሩ፣ ክብርም ስጡት፤ እያሉ።
እግዚአብሔርን “መፍራት” የሚለውን ጽንሰ ሀሳብ እንዴት ይረዱታል?
በተለይ እግዚአብሔርን እንድንወድ ከተሰጠን ትእዛዝ ብርሃን አኳያ ይህ
ምን ማለት ነው (ማቴ. 22፡37)?
ቅዱስ የሆነውን እግዚአብሔር አምላክ መፍራት ማለት እርሱ በዩኒቨርስ
የመጨረሻው ኃይል መሆኑን አምኖ መቀበል ነው። እርሱን ቢወዱት ፤ እንዲህ ያለው
ፍርሀት ማንኛውንም ፍርሀት ማሸነፍ ይችላል። እርሱ ከለላዎ እስከሆነ ድረስ ማንም
ያለ ፈቃዱ ሊነካዎ አይችልም። እርሱን ባይወዱት ጀርባዎን ቢሰጡት፣ በእርሱ ላይ
ቢያምጹና ቢኮበልሉ እንኳ ከእርሱ መደበቅ አይችሉም!
እግዚአብሔርን መፍራት እንዳለብን የሚነግረን ጽንሰ ሀሳብ ከ1 ዮሐ. 4፡
18 ጋር አይጋጭም? “በፍቅር ፍርሀት የለም፤ ፍጹም ፍቅር ግን ፍርሀትን
አውጥቶ ይጥላል፤ ፍርሀት ከቅጣት ጋር የተያያዘ ነውና። የሚፈራውም ሰው
ፍቅሩ ፍጹም አይደለም”
የተለያዩ ዓይነት ፍርሀቶች አሉ። አንድ ከፍ ያለ ሥልጣን ያለው ሰው ጓደኛዎ ቢሆንና
ብትዋደዱ፤ ግለሰቡ ሊጎዳኝ ይችላል በሚል አስተሳሰብ ሊፈሩት አይችሉም። ነገር
ግን ለዚያ ሰው ሥልጣን ተገቢውን እውቅና የመስጠት፣ የማክበርና የግንኙነታችሁን
ገደብ የመጠበቅ ዓይነት ፍርሀት ይኖሮታል።
እንደ ክርስቲያን የዓለምን ነገሮችም ሆነ ራሳቸው ዓለማዊ ሰዎች የሚወዷቸውን
ነገሮች መውደድ የለብንም (1ዮሐ. 2፡15)። ታዲያ ዓለም የሚፈራቸው
እኛ ግን እንደ ክርስቲያን ልንፈራቸው የማይገቡ ነገሮች ይኖሩ ይሆን? ካሉ
ምንድን ናቸው? ለምን አንፈራቸውም? በተቃራኒው ዓለም የማይፈራው እኛ
ክርስቲያኖች ግን መፍራት የሚገባን ነገሮችስ ምንድን ናቸው? (ለምሳሌ፡
ማቴ.10፡28፣ ኤር. 10፡2፣3)።
ከላይ የቀረቡትን ጥቅሶች ያንብቡ። ይህ ከንጉሥ አካዝ ጋር ምን ያገናኘዋል? ሀሳቦቹን ጠቅለል አድርገው ያቅርቡ።
አካዝ የአረማውያን ባዕድ አምልኮ ሥርዓት ውስጥ ጠልቆ ገባ (2ነገሥ. 16:3-4፣
10–15፣ 2ዜና 28:2–4፣ 23–25)፤ ይህ ሥርዓተ አምልኮ ከጥንቆላና መተት ጋር ሰፊ
ቁርኝት ነበረው (ያስተያዩ፡ ዘዳ. 32፡17 “አምላክ ላልሆኑ አጋንንት… ሠዉ”፣ 1ቆሮ. 10፡
20)። ከመጽሐፍ ቅዱስ ውጭ ያሉ ጥንታዊ ጽሑፎች እንደመሰከሩት፤ የዘመናዊው
ጥንቆላ የተለያዩ ገጽታዎች ከጥንቱ የቅርብ ምሥራቅ አምልኮ ሥርዓቶች ጋር
አስገራሚ ተመሳሳይነት አላቸው። እንደ እውነቱ ከሆነ ብዙዎቹ የዘመናችን አዳዲስ
ልምምዶችም እንዲሁ የእነዚህ ጥንታዊ አስማታዊ የአምልኮ ሥርዓት ዘመናዊ
መገለጫዎች ናቸው።
ከጌታ ይልቅ በባዕድ መናፍስ ላይ መተማመን (ኢሳ. 8፡21-22) የሚያስከትለውን
ተስፋ መቁረጥ ያመለከተው የኢሳይያስ መግለጫ፤ ከአካዝ ጋር ይገጥማል (ያስተያዩ፡
2ዜና 28፡22-23)። ኢሳይያስ በቁጣ ተሞልተው ንጉሣቸውን የሚራገሙ ሰዎችን
ይጠቅሳል (ኢሳ. 8፡21)። አካዝ ሕዝቡን ወደ ጥንቆላ መምራቱን ተከትሎ እርግማን
እንደሚያወርዱበት የሚገልጽ ለእርሱ የተሰጠ ማስጠንቀቂያ ነው። እርግጥ ነው፤
ከሞተ በኋላ የቀብር ሥነ ስርዓት አፈጻጸሙ ላይ የአክብሮት ክፍተት ነበር፡
“የተቀበረው ግን በእስራኤል ነገሥታት መካነ መቃብር አልነበረም” (2ዜና 28፡27)።
መተትና ጥንቆላን አስመልክቶ ጥቅሶቹ ምን ይነግሩናል? ዘሌዋ.
20:27፣ ዘዳ. 18:9–14።
ከመተት እና ጥንቆላ መለየት ለእግዚአብሔር ያለንን ታማኝነት የምንገልጽበት መንገድ
ነው። 1ዜና 10፡13-14 ይህን መርኅ ከንጉሥ ሳኦል ሁኔታ ጋር በማያያዝ ያቀርባል፡
“ሳኦል እግዚአብሔርን ስላልታዘዘ ሞተ፤ የእግዚአብሔርን ቃል አልጠበቀም፤
ይልቁንም ከሙታን ጠሪ ምክርን ጠየቀ፤ ይህን ከእግዚአብሔር አልጠየቀም፤ ስለዚህ
እግዚአብሔር ገደለው፤ መንግሥቱንም ወደ እሴይ ልጅ ወደ ዳዊት እንዲተላለፍ
አደረገ”
እስቲ ወደ ራስዎ ሕይወት ማለትም በዙሪያዎ ወዳሉ ተጽዕኖዎች ይመልከቱ።
በስተ ጀርባ በተሸሸጉ አስማታዊና ጥንቆላ ነክ መናፍስታዊ መገለጫ
መርኅዎች እንዴት በረቀቀ መንገድ ተጋላጭ መሆን ይችላሉ? ሙሉ ለሙሉ
ሊያስወግዷቸው ባይችሉ እንኳን በእርስዎ ወይም በቤተሰብዎ ላይ ሊኖራቸው
የሚችለውን ተጽእኖ እንዴት መቀነስ ይችላሉ?
Read in The Great Controversy, “Can Our Dead Speak
to Us?” pp. 551–562.
“ዛሬ የሙታን መንፈስ እንጠራለን ከሚሉ ጋር የሚመሳሰሉ መናፍስት ጠሪዎች
ጥንት በዕብራውያን ዘመንም ነበሩ። ሆኖም ከሌላ ዓለማት የመጡ ‘ቤተኛ መናፍስት’
ብለው ቢጠሯቸውም፤ መጽሐፍ ቅዱስ ግን ‘የአጋንንት መንፈሶች’ ይላቸዋል (
ዘኁ. 25:1–3፣ መዝ. 106:28፣ 1ቆሮ. 10:20፣ ራእ. 16:14.)። ከእነዚህ መናፍስት ጋር
ግንኙነት ለመፍጠር የሚሠራ ሥራ በጌታ ፊት እርኩሰት በመሆኑ ጽኑ የሞት ቅጣት
ያስቀጣል (ዘሌዋ. 19፡31፣ 20፡27)። ጥንቆላ የሚለው ቃል ዛሬ በንቀት ይታያል።
ሰዎች ከአጋንንት መናፍስት ጋር ወሲባዊ ግንኙን መፈጸም ይችላሉ የተሰኘው አባባል
የጨለማው ዘመን ተረት ተደርጎ ይወሰዳል። ነገር ግን አባላቱ በመቶ ሺህዎች ብሎም
በሚሊዮኖች እያደጉለት የሚገኘው ከሙታን መንፈስ ጋር ግንኙነት እንፈጥራለን
የሚለውና አካሄዱ ሣይንሳዊ ገጽታ እንዲላበስ በማድረግ አብያተ ክርስቲያናትን
በመውረር ላይ የሚገኘው ይህ ተቋም፤ ማታለያው በሕግ አውጪ አካላት ብሎም
በነገሥታት ፊት ተቀባይነት እያገኘ መምጣቱ፤ ጥንት የተወገዘውና የተከለከለው
የቀደመው የጥንቆላ ማታለያ በአዲስ መልክ ማንሰራራቱን ያሳያል።”—Ellen G.
White, The Great Controversy, p. 556.
1.የሙታንን መንፈስ መጥራት በተሰኘው ርዕሰ ጉዳይ ዙሪያ በሚቀርቡ
ፊልሞች፣ መጽሐፎች፣ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች እና ታዋቂ ባህሎች ዙሪያ
ተወያዩ። ይህን ለማስቆም ምንም መደረግ የማይችል እስከ ከሆነ ድረስ፤
እንዲህ ያለውን ለብዙዎች ጉዳት የማያስከትል የሚመስል፤ ነገር ግን አውዳሚ
ውጤት ከሚያመጣ አደጋ መጠበቅ እንዲችሉ ሌሎችን የምናስጠነቅቀው
እንዴት ነው? ከእነዚህ ማታለያዎች ለመጠበቅ፤ የሞቱ ሰዎች ስለሚገኙበት
ሁኔታ ትክክለኛ መረዳት ማግኘት አስፈላጊ የሆነው ለምንድነ ነው?
2.የሚከተለውን ጥቅስ ያንብቡና በራስዎ ቃላት ደግመው ይጻፉት፡ ኢሳ. 8፡
20። የሰንበት ትምህርት ጥናት አባላት በራሳችሁ መንገድ የጻፋችሁትን ሀሳብ
ድምጻችሁን ከፍ አድርጋችሁ አቅርቡ። ጌታ በዚህ ስፍራ ምን እያለን ነው?
3.እግዚአብሔርን በተመሳሳይ ዐውድ ስለ መውደድ እና ስለ መፍራት
የቀረበውን ጽንሰ ሀሳብ በጥልቀት ለመመልከት ይሞክሩ። ፍቅራችን ከዚህ
ፍርሀት የሚገታባቸው መንገዶች ምንድን ናቸው? ወይስ ፍርሀታችን
ከፍቅራችን ይገታናል?
ማጠቃለያ፡ እግዚአብሔር በኢሳይያስ ድርጊቶች፣ ቤተሰባዊ ሁናቴዎች ብሎም
ሥራዎች አማካይነት የማስጠንቀቂያ እና የተስፋ መልእክቱን አጠናክሮ አቅርቦአል፡
እርሱ በሚያደርገው ነገር ላይ እምነት መጣል፤ ብቸኛውና አስተማማኙ መንገድ
ነው። ጌታ የሚፈቅዱትን የሚመራ፣ የሚጠብቅና የሚያስፈልጋቸውን የሚያሟላ
ፍቅርም ሆነ ኃይል አለው። ፊታቸውን ወደ ሌሎች ኃይላት የሚያዞሩ--ከጽልመት
የዘለለ ተስፋ የላቸውም።